ከቀንዱም ከሸሆናውም

የወል ምልልስ

በቅርቡ በህይወት ያጣናቸው ጋዜጠኛ ካህሳይ ገ/ህይወት ሥራዎች በዛሬው ከቀንዱም ከሸኾናውም አምዳችን ላይ ቀርበዋል፡፡ በመጽሐፎቻቸው ውስጥ ከተካተቱት ሥራዎች መካከል የመረጥናቸው ስናቀርብ መታሰቢያነቱን ለመስጠት በማሰብ ነው፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ለቤተ-ሰቦቻቸው እና ለአድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡

እሱ፡- በቁንዳላሽ አምላክ- በአንዲቱ ዘለላ

     እሾህ ወጋኝ ብለሽ- ቅሪ ወደኋላ

እሷ፡- እሾኽ ወጋኝ ብዬ- ብቀር ወደኋላ

     የዛሬ ዘመን ሰው- ያደርገዋል ሌላ፤

     አፍንጫህ ጎማዳ- ሆድህ ዘረከቦ

     እንዴት አርጎ ሰራህ- እንደድንጋይ ክቦ

እሱ፡- አፍንጫ ጎማዳ- ብለሽ የላክሽብኝ

    እግዜር ሰራኝ እንጂ- የዘረን አለብኝ፤

    መረሬ አፈር- ያበቅላል እንግጫ

    ቢዞሩ ቢፈርጡ- አይገኝ አፍንጫ

እሷ፡- አፍንጫ ጎራዳ- ትለኛለህ ምነው

    ሌላ የክት አለኝ- ይሄ የሰርኬ ነው

እሱ፡- እንዴት ነሽ በሉልኝ አንድ እጇን ይዟችሁ

     መቼም የኮራች ነች- አታናግራችሁ

እሷ፡- እንዴት ነሽ እንዴት ነሽ- ብሎ የላከው

    እሱን ባለጤና- ማን አደረገው

እሱ፡- ሲሰራሽ ዋለና- እግዜር ቢታክተው

     ከወደእግርሽ ሲደርስ- አለሽ እንደመተው

እሷ፡- እንሳደብ ካልክስ- ስድብ ባንተ ይብሳል

     እግርህ እንደማጭድ- ሳር ያግበሰብሳል

እሱ፡- ዋለል ጨግለል ብለሽ- እዚያ ላይ ደርሰሽ

     የነፋሱ ወሬ- ምን ይዘሽ መጣሽ፤

     እንደአህያ ፈሳም- እንደጅብ ደንደሳም

     አንቺን ለወፍጮ እንጂ- ማን አለሽ ለመሳም፤

አሁንማ ተጋፍቶ ይግባ

አንዲት ሴት ድንገት ባሏ ሞቶባት ገና ሃዘኗን ሳትወጣ፤ የንስሃ አባቷ “በይ እስቲ፤ ለሠልስቱ አንድ ነገር አድርጊ” ብለው አዘዟት። በዚህ ሳያበቁ በነጋታው መጡና በሰባተኛው ቀን ለፍትሃት የሚሆን ጠላ እና ምሳ ማምጣት እንዳለባት ነገሯት፤ በ20ኛው እና በ40ኛው ቀን ደግሞ በእርድ የታጀበ ሞቅ ያለ ድግስ መደገስ እንዳለባት አስረግጠው ነገሯት። በዚህ የተነሳ የነበራትን ጥሪት እያለቀ፣ እየተሟጠጠ ስለመጣ በጣም አሳሰባት። በዛው ላይ መሬቷን የሚያርስላት ስላልነበረ ከነልጆቿ ለረሃብ እንደምትጋለጥ ስታስበው ጨነቃት። የንስሃ አባቷ ግን ችግሯን ከግምት ሳያስገቡ ለፍትሃት እያሉ ድግስ እንድትደግስ  ማዘዛቸውን አላቆሙም። በመሆኑም አሁንም ለ80ኛው ቀን እንድትደግስ፤ በተለይ ደግሞ ለሙት ዓመቱ ካሁኑ እንድታስብበት አደራ ጭምር የታከለበት ማሳሰቢያ ሰጧት።

በዚህ ሁሉ የተማረረችው ሴት ታዲያ

“ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ድግስ ለሟች ባሌ ምንድነው የሚጠቅመው?” ስትል ያልታሰበ ጥያቄ አቀረበችላቸው።

ቄሱም እንደመደንገጥ ብለው “ካህናቱ እየፀለዩ የባልሽ ነፍስ መንግሥተ-ሰማያት ገነት እንድትገባ ነው”  አሏት።

እሷም በመቀጠል “ድግስ በተደገሰ ቁጥር ለባሌ ነፍስ የሚፀልዩ ከሆነ፣ እንዴት እስካሁን ነፍሱ መንግሥተ-ሰማያት አልገባችም?” በማለት ሌላ ጥያቄ አከለች።

በሁኔታው ግራ የተጋቡት ቄስ “አሁን እንኳ የባልሽ ነፍስ ከመንግሥተ-ሰማያት በር ደርሳለች። ከአሁን በኋላ አንድ ሁለቴ ብትደግሺ ልትገባ ትችላለች” አሉ።

እሷም “እንኳን በሩ ጋር ደረሰ እንጂ፤ ከአሁን በኋላ ተጋፍቶም ቢሆን ይግባ እንጂ እኔ አልደግስም” አለች ይባላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top