ቀዳሚ ቃል

የሰከነ የፖለቲካ ባህል ያስፈልገናል!

የምንገኘው ታላቅ የታሪክ መታጠፊያ ላይ ነው፡፡ የሐገሪቱን የሩብ ክፍለዘመን ኑሮ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት የመራው ኢሕአዴግ ነባሩን በማጥበቅ እና አዲሱን በመናፈቅ መካከል ላይ ወድቋል፡፡ የኢትዮጵያ የብልጽግና ፓርቲ (ብልጽግና)ን በማዋለድ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)ን በማዘመን ወይም ግብአተ መሬት በማፋጠን ውርክብ ውስጥ ይገኛል፡፡ ከኢሕአዴግ ውጭ ያሉ ፓርቲዎችም ጭምር የትላንትናውን መስመር በመደገፍ በጋራ ቆመዋል፡፡ የአዲሱን ሕብረት እና አደረጃጀት ተቀብለው ለእውናዊነቱ ሙሉ ድጋፋቸውን የሰጡ ኢሕአዴጋዊ ያልሆኑም አሉ፡፡

የሁለቱም ወገን ባለሐሳቦች የታሪክ ተወቃሽነት አና ተወዳሽነት እድላቸው በእጃቸው ላይ ትገኛለች፡፡ በፖለቲካዊ ልዩነት መገዳደል የሚያበቃበትን ኢትዮጵያዊ ባህል ለመገንባት የሚችሉበት የታሪክ አጋጣሚ ላይ ናቸው፡፡ ሐሳቦች የሚሸናነፉበት፣ ተሸናፊዎች ሽንፈትን በጸጋ የሚቀበሉበት ፖለቲካዊ ባህል ያስፈልገናል፡፡ አሁን የምንገኝበት ፖለቲካዊ ሂደት ከነበረው መጥፎ ጠባሳ የሚማረውን ማስታወስ የታዛ መጽሔት ዘወትራዊ ትጋት ነው፡፡ በሐሳባቸው ግጭት በሚፈጠር ብልጭታ ነገን አሻግረው መመልከት የሚችሉ ዜጎች እንዲኖሩ እንተጋለን፡፡ ፍላጎታቸው ከሐሳባችን የሰመረ ጸሐፊዎች ስራዎቻቸውን ቢያቀብሉን መጽሔታችን የርዕሰ ጉዳይ ምርጫ ሳይኖራት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን በዚህ አጋጣሚ እናሳውቃለን፡፡

በዛሬዋ የታዛ መጽሔት ቁጥር 26 እትማችን በወቅታዊው የፖለቲካ ሂደት ሁለቱም ወገን በይፋዊ መግለጫዎቻቸው እና ቃለ መጠይቆቻቸው የተናገሩትን የየራሳቸውን እምነት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ሞክራለች፡፡ “በቀና ሐሳቦች የተሞላ፣ የሰከነ የፖለቲካ ባሕል ማዳበር የምንችልበት መላ እንደምን ያለ ነው?” ስትል ትጠይቃለች፡፡ በተለይም የፖለቲካ ባህላችንን ከጥይት እና ከደም፣ ከሴራ እና መጠላለፍ፣ በትላንት ስህተቶች ከመቆዘም፣… እንድንወጣ የሚያመላክቱ ሐሳቦችን ማቅረባችንን እንደትላንት እንደዛሬው ነገም እንቀጥልበታለን፡፡ የተመቻቸ የአየር ንብረት ያለው ሜዳ የመፍጠር ባህላችንን ለማሳደግ፣ ወገንተኝነት የሌለበት ሚድያ ለመፍጠር እንተጋለን፡፡  

በተጨማሪም ትኩረታቸውን በኪነጥበብ፣ በታሪክ እና በፍልስፍና ላይ ያደረጉ ጽሑፎች አካተናል፡፡ የመጽሐፍ ዳሰሳ፣ አጭር ልብ ወለድ፣ አጫጭር እና አዝናኝ ጽሑፎችም የህትመቱ አንድ አካል ሆነዋል፡፡ በንባባችሁ ጊዜ ከማሳለፊያ በላይ ቁምነገር እንደምታገኙ እናምናለን፡፡ ከአጭር ጊዜ ንባብ በላይ የሆኑ ሐሳቦች የሚያቀብላችሁ ውጤታማ ንባብ እንዲሆንላችሁ እንመኛለን፡፡

መልካም ንባብ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top