የታዛ ድምፆች

የሕዝብ ተሳትፎ ሲባል

በዚህ ጽሑፍ ስለ ህዝብ ተሳትፎ ምንነት አንዳንድ መሰረታዊ የጽንሰ ሃሳብ ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ። እጅግ ጠቦ የነበረው የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ሰፋ እያለ በመምጣቱ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በስፋት መወያየት ጀምረዋል። በአንፃራዊ መልኩም ቢሆን የሚዲያው መብዛት፣ በተለይም የማህበራዊ ሚዲያው መምጣት የውይይቱን አድማስ ከማስፋቱ በተጨማሪ ቅጥ ያጣና የከረረ አድርጐታል። በእርግጥ በሁሉም የሚዲያ አማራጮች ጠቃሚ ሃሳቦች መቅረባቸው አልቀረም። ነገር ግን ደስ የማያሰኘው የብዙዎቹ ሃሳቦች ቀጫጫነትና ተንኳሽነት ነው።

በእርግጥ ለውጥ የሚካሄድበት ዘመን ለዜጎች ዙሪያ-መለስ ተሳትፎ የተመቸ ድባብ ይፈጥራል። ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው ሁኔታ በንቃት መወያየታቸውና ለተግባር መነሳሳታቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ከቅርቡ ዘመን ታሪካችን እንኳ የልጅ እያሱ ስልጣን ተሽሮ ወጣቱ ተፈሪ መኮንን የለውጥ ሃዋርያ በነበሩበት በ1920ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ በዘመኑ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው እጣፋንታ በንቃትና በስሜት ተወያይተዋል፤ ተከራክረዋል። በዋናነት የመከራከሪያ መድረካቸው የተፈሪ ንብረት የነበረው የብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ነበር። አልዘለቀም እንጂ 1966ንና 1983ን ተከትለው በመጡት ዓመታትም በኢትዮጵያውያን መካከል ሰፊ የሃሳብ ተራክቦ ተስተውሏል። አሁን በምንገኝበት የለውጥ ዘመንም ተመሳሳይ ሁኔታ እየተስተዋለ ነው። ከሃሳብ ልውውጥ አልፎ ተግባራዊ ተሳትፎ በልዩ ልዩ መልክ ይታያል። ስለዚህ የህዝብ ተሳትፎ ምንድን ነው? ምክንያቱና ፋይዳውስ? ተሳትፎን የሚያበረታቱና የሚያቅቡ ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚሉና ተዛማጅ ጥያቄዎችን በማንሳት አንኳር ሃሳቦችን ለማጋራት እሞክራለሁ። በጐደለው ላይ ሌሎች ጸሐፍት ይሙሉበት።

አጠቃላይ ነጥቦች

ለህብረተሰብ ልማት የህዝብ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው። በጋራ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የህዝብ ተሳትፎ ከግሪኩ ፈላስፋ ከፕሌቶ ዘመን የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ጋር ይያያዛል። ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተግባር እውን የሚሆኑት በሌላ ሳይሆን በህዝብ ተሳትፎ ነው። ስለዚህ የህዝብ ተሳትፎ የዴሞክራሲም መሰረት ነው ለማለት ይቻላል። ሽፒግል (1968) የተባለ ጸሐፊ እንደጠቀሰው የልማት ትልሞችን ከህዝብ ጋር የማስተሳሰሪያው ሂደት ራሱ የህዝብ ተሳትፎ ነው።

የህዝብ ተሳትፎን ተንከባክበው የሚያጐለብቱት የሙያ ማህበራትና የማህበረሰብ ተቋማት መሪዎች ናቸው። የእንደነዚህ ዓይነት የተለያዩ የአደረጃጀት አመራሮች ለህዝብ ተሳትፎ መነሻ የሚሆኑ የረዥም ጊዜ ራዕይ በመቅረጽ ሁኔታውን ትርጉም ባለው መንገድ ሊያግዙ ይችላሉ። ዜጎች ለተለያዩ የማህበረሰብ ተቋማት የየበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ መፍቀድና ሁኔታዎችን ማመቻቸት የህዝብን የመሳተፍ አቅምና የተሳትፎ መጠን ማጐልበት ነው።

የህዝብ ተሳትፎ አንድ ዜጋ ፖለቲካዊና በሌላ ማናቸውም ህዝባዊ ጉዳይ ላይ በንቃት መሳተፍ የሚችልበትን ሁኔታ ያመለክታል። ዜጎች በፖለቲካና በሌሎች ህዝባዊ ጉዳዮች ዙሪያ ንቁ ተሳታፊ በሚሆኑበት ሁኔታ ውስጥ የሲቪክ ማህበራት ህያው የመሆን ስልጣንና የህግ ከለላ አላቸው፤ ተጠያቂነትም ይኖርባቸዋል። ተቋማዊና ሙያዊ ነፃነታቸው በመንግስት ተጽዕኖ ስር የማይወድቅ የተለያዩ ሚዲያዎች ይኖራሉ። ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብትና መረጃን የማግኘት መብት ለሁሉም እኩል ተግባራዊ ይደረጋል። የፖለቲካ ፖርቲዎች በነፃነት ይደራጃሉ፤ ጥበቃም ይደረግላቸዋል። የሲቪክ ማህበራት፣ ሚዲያና የፖለቲካ ፖርቲዎች ህጋዊ መድረኮችንና ሌሎች የምክክር ዘዴዎችን በመፍጠር የሃይልና የግጭት/የነውጥ አጋጣሚዎችን ያረግባሉ። በእነዚህ ዘዴዎች ህዝቡ በፖለቲካ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የመሳተፍ፣ የመንግስት አሰራርን የመቆጣጠርና በፖሊሲዎቹ ላይ የራሱን ተጽዕኖ የማሳረፍ እድል ያገኛል። ዜጎች ማህበረሰባዊ በሆኑ ጉዳዮች የመሳተፍ እድል ሳያገኙ ሲቀሩ ድምፃቸው እንዲሰማና ፍላጐታቸው እንዲሟላ የአመጽ መንገድ ለመከተል ይገፋፋሉ። የህዝብ ተሳትፎ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ያረግባል። ሆኖም የህዝብ ተሳትፎ የአናሳ ቡድኖችን የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች መከበርን የግድ ይላል።

ጠንከር ያለ የህዝብ ተሳትፎን ለመፍጠር አንዱ ዘዴ በተለያዩ የሲቪክ ማህበራት የዜጎችን ተሳትፎ ማጠናከር ነው። ሪቻርድ ፑትናም (2000) እንደሚለው ዘመናዊ አኗኗር የሚፈጥረውን የግለኝነት ስሜት፣ ማህበራዊ መገለል እንዲሁም በግለሰብና በማህበረሰብ መካከል ያለውን ልል ግንኙነት ለመስበር አንዱና ሁነኛው ዘዴ ማህበረሰቡን ጠንካራ ማድረግ ነው። ማህበረሰቡን ለማጠናከር ደግሞ ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ የሚጋብዙ የልማት ተግባራትን በማቀድ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖር መስራት ነው።

የሲቪክ ማህበራት ስፍራ በግለሰብና በመንግስት መካከል ነው የሚባል አባባል አለ። ስፍራው ዜጎችና የበጎ ፈቃድ ማህበራት ከመንግስት፣ ከቤተሰብና ከግሉ ሴክተር ተጽዕኖ ነፃ ሆነው በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ነው። የሲቪክ ማህበራት የያዟቸው ተቋማት ዓይነታቸው ብዙና የተለያየ ነው። ማህበራቱ የአባላቱን ባህላዊ፣ ሞራላዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች ዕሴቶችን ምክንያት በማድረግ የተቋቋሙ የንቁ ዜጎች ስብስቦች ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ መንግስትና ህዝብን ለማገናኘት እንደ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ። የመንግስት ውሳኔዎችን ለማስተካከልና ለመከታተል፣ ህብረተሰቡን ለማነሳሳት (ሞቢላይዝ ለማድረግ) እና መብቶቻቸውን እንዲያውቁና ግዴታዎቻቸውንም እንዲገነዘቡ ለማድረግ፣ ለውጥና የተሻሻሉ ህዝባዊ አገልግሎቶች እንዲቀርቡ ጥያቄዎቻቸውን ለማቅረብ፣ በተለያዩ ቡድኖች መካከል ሰላማዊና ጤናማ ውይይት እንዲካሄድ፣ በዚህም ግጭቶች ያለደም መፋሰስ በሰላም እንዲፈቱ የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ።

የህዝብ ተሳትፍ ጽንሰ ሃሳብ

የህዝብ ተሳትፎ ጽንሰ ሃሳብ የመንግስትን፣ የህብረተሰብንና የዜጎችን መስተጋብር የሚመለከት አስተሳሰብ ነው። በምሁራን አስተያየት የህዝብ ተሳትፎ ለህብረተሰብ ጥቅም ያለሙ በጎ አስተሳሰቦችን፣ ስሜትና ተግባራትን ያመለክታል። ሊንድሃል (2011) እንደሚለው የህዝብ ተሳትፎ አግባቦችን በተግባር ማጠናከር ደግሞ የዜጎችን የሲቪክ ክህሎት፣ የምርጫ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን እንደማጎልበት ተደርጐ ይወሰዳል። ይሁን እንጂ በህዝብ ተሳትፎ ጽንሰ ሃሳብ አተረጓጎም ላይ በተለያዩ ምሁራን ዘንድ ተመሳሳይ አስተሳሰብ የለም። ለምሳሌ አድለርና ጎጊን (2005) የተባሉ ጸሐፊዎች በህዝብ ተሳትፎ ላይ የቀረቡትን የተለያዩ ትርጓሜዎች ከመረመሩ በኋላ ብዘዎቹ የሚስማሙበት አንድ አጠቃላይ ወይንም ሰፊ የሆነና ሁሉን አቀፍ የሆነ ትርጓሜ እንደሌለ አረጋግጠዋል። ይልቁንም በተለያዩ ምሁራን የሚሰነዘሩት ትርጓሜዎች በውስን ሁኔታዎች (ለምሳሌ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በቡድን ስራ አሊያም በፖለቲካ ተሳትፎ) ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ። 

የህዝብን ተሳትፎ ከማህበረሰብ አገልግሎት ጋር የሚያቆራኘው አተረጓጎም ተሳትፎውን ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጋር በማያያዝ ሁኔታውን የዜጎች ግዴታ ወይንም ሃላፊነት ያደርገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የማህበረሰብን ህይወት ለማሻሻል በሚደረግ ጥረት ውስጥ ዜጎች የሚያሳዩት ትብብርና የጋራ ተግባር ከቡድን ስራ ጋር የተያያዘው የህዝብ ተሳትፎ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። ከፖለቲካ ተሳትፎ ጋር የሚያያዘው የህዝብ ተሳትፎ አተያይ ደግሞ የወል ባህርይ ቢኖረውም በተለይ ግን ከመንግስት አገልግሎቶች ወይንም ተግባራትና እርምጃዎች ጋር የተሳሰረ ነው (አድለርና ጎጊን፣ 2005)።

ኤህርሊክ (2000) የተባለ ጸሐፊ ደግሞ የህዝብ ተሳትፎ የሚባለው ህዝባዊ የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ ምላሽ ለመስጠት በግልም ሆነ በህብረት የሚደረግ ጥረት ነው በማለት ይገልጸዋል። ጥረቱ ከግል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስከ የድርጅት ማህበርተኝነትና የፖለቲካ ምርጫ ተሳትፎ ድረስ የተለያዩ መገለጫዎች ሊኖሩት ይችላል። አንዴ የሆነ ጉዳይን በሚመለከት በቀጥታ መሳተፍና ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ጥረት ማድረግ፣ ወይንም ለመፍትሄው ከሌሎች ጋር መስራት ወይንም አግባብነት ካላቸው የውክልና ተቋማት ጋር በመሆን መንቀሳቀስ ከህዝብ ተሳትፎ አንፃር ሊታይ የሚችል ተግባር ነው። በተሳትፎ የሚከናወኑት ተግባራትም እንዲሁ የተለያዩ ናቸው። አግባብነት ላላቸው የአካባቢ ተወካዮች፣ ተመራጮችና ሃላፊዎች የተቃውሞ ወይንም የማሳሰቢያ ደብዳቤ ከመጻፍ እስከ ተለያዩ የአካባቢ የልማት ተግባራት ተሳትፎ ድረስ የሚከናወኑት ተግባራት የህዝብ ተሳትፎ አካላት ናቸው። ህዝባዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በዚህ አግባብ በንቃት የሚሳተፍ ዜጋ ችሎታ፣ ተሳትፎውን እውን የሚያደርግበት መንገድ ወይንም ድርጅት ወይንም ማህበርና መልካም አጋጣሚዎች ያሉት ነው። በተለያዩ የተሳትፎ አግባቦች ውስጥ ራሱን እያስገባ ምንም ዓይነት የፍርሃትና የሃፍረት ስሜት ሳይሰማው የፍላጎቱን ማበርከት ይችላል (ኤህርሊክ 2000)። 

በሌላ አገላለጽ የህዝብ ተሳትፎ የማህበረሰብን አጠቃላይ ህይወት ለመለወጥ ህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን እውቀት፣ ክህሎት፣ መልካም እሴትና መነሳሳት አዋህዶና አጎልብቶ ለውጡን እውን ለማድረግ መስራትን ያመለክታል። ይህም ፖለቲካዊና ፖለቲካዊ ባልሆኑ እርምጃዎች የህብረተሰቡ የኑሮ የጥራት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ እንዲሄድ ማበረታታትና መደገፍ ማለት ነው (ኤህርሊክ 2000)። 

ይሁን እንጂ በተለይ በ1960ዎቹ አሰርት ውስጥ የህዝብ ተሳትፎ ትርጉም ትኩረቱ የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች ምርጫና ፖሊሲዎቻቸውን ማጽደቅ ላይ ያተኮረ ሆኖ ነበር (ቬርባ፣ ናይ 1972፣ ኢስተን 1953)። ተደጋግሞ ከሚጠቀሰው የህዝብ ተሳትፎ ትርጉም ውስጥ አንዱ ሚሌብሬይዝ እና ጎል (1977) የተባሉ ጸሐፍት የሰነዘሩት ነው። በእነርሱ አስተያየት የህዝብ ተሳትፎ ‹‹እያንዳንዱ ዜጋ የመንግስትንና የፖለቲካውን ተጽዕኖ ወይንም ድጋፍ ለማግኘት የሚወስዱት እርምጃ ወይንም የሚያከናውኑት ተግባር ነው።›› ካሴ እና ማርሽ (1979) ባቀረቡት ሃሳብ ደግሞ የህዝብ ተሳትፎ የሚያመለክተው ‹‹በአንድ ሀገር የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ አማራጮች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጫና ለማሳረፍ ታልመው በዜጎች ውዴታና ፈቃድ የሚከናወኑ ተግባራትን›› ነው። በእነ ቬርባ፣ ናይ እና ኪም (1978) አገላለጽ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ ማለት ‹‹ዜጎች በፖለቲካ ተመራጮች ምርጫና ኋላም የተመረጡት ባለስልጣናት ስልጣን ይዘው በሚፈጽሙት ተግባር ላይ አነሰም-በዛ በቀጥታ ጫና ለማሳረፍ የሚወስዱት ህጋዊ እርምጃ ነው።››

በሞራልም በዜግነትም ሃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ራሱን የሰፊው ማህበረሰብ አባል አድርጐ ስለሚመለከት ማህበራዊ ችግሮችን በተወሰነ መልኩ የራሱም ችግሮች እንደሆኑ ይቀበላል። እንደ ኤህርሊክ አስተያየት እንዲህ ዓይነቱ ዜጋ ሁኔታዎች ከሞራልና ከሲቪክ አንፃር ያላቸውን አንድምታ ለመረዳት፣ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ሞራላዊና የዜግነት ሃላፊነት የተመላበት ውሳኔ ለመወሰን፣ ውሳኔውንም በምክንያት ለማስደገፍ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም እርምጃ ለመውሰድ ፍላጐትና ተነሳሽነት ይኖረዋል።

የሆነው ሆኖ በማናቸውም ህብረተሰብ ውስጥ ማህበራዊ ዕሴቶችን የሚወስኑት የፖለቲካ ልሂቃኑ ብቻ አይደሉም። ተርታው ዜጋና ልዩ ልዩ የሲቪክ ማህበራትም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። በተለይም የዜጎች ተሳትፎ በምርጫ ጊዜ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በየምርጫ ዘመኑ መካከልም የሚከናወን በመሆኑ ከተለያዩ የድጋፍ ተግባራት ጀምሮ እንደ ሰላማዊ ሰልፍ፣ የስራ ማቆም አድማና ሌሎች ልዩ ልዩ የተቃውሞ አግባቦችን የሚያካትት ይሆናል (ባርነስ፣ ካሴና ሌሎች 1979)። ስለዚህ በማናቸውም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተቋማትና አንቀሳቃሾች ላይ ያነጣጠረ ተቃውሞ ሁሉ የዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል (ቲኦሬልና ሌሎች 2007፣ ኖሪስ 2002)።

በአጠቃላይ በምዕራብ ሀገሮች ከፖለቲካ አንፃር የህዝብ ተሳትፎ ተብሎ የሚወሰደው በዋናነት የዜጎች የፖለቲካ ምርጫ ተሳትፎ ነው። ስለዚህ በምርጫ ወቅት የመራጮች ቁጥር መብዛትና ማነስ እንደ ዋና የተሳትፎ መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል (ብራዲ 1999፤ ቫን ዴት 2001)።

የህዝብ ተሳትፎን በተመለከተ የቅርብ ጊዜያት ትርጓሜዎች ሰፋ ያሉ ናቸው። ለምሳሌ ብራዲ (1999) በፖለቲካ ተሳትፎ ምንነት ላይ ሦስት ባህርያትን ያስቀምጣል። የመጀመሪያው ሰዎች ወደውና ፈቅደው በተግባር የሚሳተፉበት፣ ግልጽና የሚታይ ድርጊት ነው ይላል። ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ሰዎች›› የሚለው ቃል የሚያመለክተው የፖለቲካ ልሂቃንን ወይንም የመንግስት ተቀጣሪ ሰራተኞችን ሳይሆን ተርታ ዜጎችን እንደሆነ ይጠቅሳል። ሦስተኛው ባህርይ እንደ ጽንሰ ሃሳብ የህዝብ ተሳትፎ የፖለቲካ ሃላፊዎች ላይ ጫና ለማሳደርና ለውጥ ለማምጣት ሆን ተብሎ የሚከናወን ተግባር ነው ይላል። 

ከፍ ሲል በጠቀስናቸው በቬርባ እና በናይ (1972) አስተሳሰብ የህዝብ ተሳትፎ አራት መገለጫ ባህርያት አሉት። እነርሱም፡- 

 1. ድምፅ መስጠት (ወይንም በፖለቲካ ምርጫ ለመምረጥና ለመመረጥ የሚደረግ ተሳትፎ)፣ 
 2. የዘመቻ ተግባራት ተሳትፎ (በፖለቲካ ፓርቲ ወይንም በሌላ ድርጅት አባልነት የሚደረግ ተሳትፎ፣ የአባልነት መዋጮ፣ ወዘተ)
 3. ሃላፊዎችን ወይንም የህዝብ ተመራጮችን ፈልጎ የማግኘት፣ የማነጋገርና የማግባባት ተግባርና፣ 
 4. የአካባቢ የትብብር ስራዎች ወይንም ማህበራዊ የልማት ተሳትፎ ናቸው። 

ቲኦሬል እና ባልደረቦቹ ደግሞ በ2007 ባሳተሙት ጽሑፍ ከፍ ሲል በተጠቀሰው የቬርባ እና የናይ ጽሑፍ ላይ በመመርኮዝ የህዝብ ተሳትፎ ትርጓሜን ትንሽ ሰፋ በማድረግ አምስት ዓይነት ባህርያትን ለማመላከት ሞክረዋል። እንደነቲኦሬል አስተያየት የህዝብ ተሳትፎ የሚከተሉት አምስት መገለጫ ባህርያት አሉት። 

 • በቅድሚያ የሚጠቀሰው የምርጫ ተሳትፎ ነው። 
 • ሁለተኛው ዜጎች በሸማችነታቸው የሚያደርጉት ተሳትፎ ነው። ይህም ሸማቾች በፍጆታ ተጠቃሚነታቸው ተደራጅተው የሚሰጡትን ድጋፍ ወይንም የበጎ ፈቃድ እርዳታ፣ የአንሸምትም ተቃውሞ፣ ቅሬታን ወይንም አቤቱታን ተፈራርሞ የማቅረብ እርምጃ (ፓቲሺን)፣ ወዘተ ያጠቃልላል። 
 • ሦስተኛው የህዝብ ተሳትፎ መገለጫ የፓርቲ አባልነት ነው። 
 • አራተኛው ባህርይ የተቃውሞ ተሳትፎ ነው። ይህ በማናቸውም ዓይነት አመጽ (ሰላማዊ ሰልፍ፣ አድማ፣ የስራ ማቆም አድማና ሌሎች ተቃውሞዎች) የመሳተፍ ተግባርን ያመለክታል። 
 • አምስተኛው መገለጫ የማግባባት ወይንም የአድቮኬሲ ተሳትፎ ነው። ይህ ለአንድ ግብ ድርጅቶችን፣ የፖለቲካ ሰዎችን፣ የተቋም ሃላፊዎችን ወይንም ሰራተኞችን ቀርቦ የማነጋገር፣ የማግባባትና አሳምኖ ከጎን የማሰለፍ ጥረትን የሚያመለክት ነው።     

እንደ ፑትናም (2000) አስተያየት በህዝባዊ የተሳትፎ አግባቦች ውስጥ ዜጎች በሦስት ዓይነት ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ። እነኚህም በስፍራ፣ በሃሳብና በሁኔታዎች የሚገለጹ ናቸው። ስለዚህ አካባቢያዊ ጉዳዮች ለህዝብ ተሳትፎ ዋነኛ መንስዔዎች ናቸው። ዜጎች በየሚኖሩበት አካባቢ በሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደየስሜትና ፍላጎታቸው ይሳተፋሉ። በሁለተኛ ደረጃ ዜጎች ማህበረሰባቸውን በሚመለከቱ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት፣ በመከራከርና ሃሳብን በጽሑፍ በማቅረብና በማሰራጨት ይሳተፋሉ። ጉዳዩ አካባቢያዊ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ክርክሩና የሃሳብ ፍጭቱ ወደ አንድ የተግባር እርምጃ ያመራል። ሦስተኛውና በሁኔታዎች ላይ ያነጣጠረው የህዝብ የተሳትፎ አግባብ ደግሞ አንድ የሆነ ማህበራዊ ችግርን ለማስወገድ በታለመ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፍ ሊሆን ይችላል።

ሊንድሃል (2011) የተባለ ጸሐፊ ለህብረተሰብ እድገት ቁልፍ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ትምህርት አበክሮ ይገልጻል። ሀገር ተረካቢው ትውልድ ምንጊዜም ቢሆን ስለ ህዝብ ተሳትፎ ፋይዳ ማወቅ አለበት። ይህን የማድረግ ሃላፊነት የቀደመው ትውልድ ነው። ጠንካራ ህብረተሰብን የመገንቢያው አንዱ ዘዴም ይህ ነው። አንድ ሰው በማህበረሰብ ውስጥ ለማህበረሰብ መልካም ህይወት ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ችሎታውን በተግባር የሚያውለው በተለያዩ የህዝብ ተሳትፎ አግባቦች ነው። ሆኖም ትልቁ ፈተና ለተሳትፎ የሚጋብዙ ሃሳቦችን ማመንጨቱና ለተግባር ማመቻቸቱ ነው።   

የህዝብ ተሳትፎ ምክንያትና ፋይዳው

የዜጎች ተሳትፍ መገለጫው ብዙ ነው። በፖለቲካ ምርጫ ድምፅ መስጠት፣ ለበጎ አድራጎት ተግባር ገንዘብ መለገስ፤ የስፖርት ክለብ አባል መሆን፣ የፖለቲካ ጉባዔዎችንና ዘመቻዎችን መሳተፍ፣ ወዘተ በተለያዩ መስኮች የዜጎች ተሳትፎ እውን የሚሆኑባቸው አብነቶች ናቸው (በርገር፣ 2009)። በምዕራቡ የፖለቲካ ስነ ጽሑፍ፣ በተለይም የዩኤስ አሜሪካን ነባራዊ ሁኔታ እንደ አውድ በመውሰድ፣ የህዝብ ተሳትፎ ጽንሰ ሃሳብን ያኸዘበው (በስፋት እንዲታወቅ ያደረገው) ፑትናም የተባለው ጸሐፊ እንደሆነ ይጠቀሳል። ፑትናም የተለያዩ የፖለቲካ ሳይንስ ጽሑፍችን ያዘጋጀ ተመራማሪ ቢሆንም ‹‹ቦውሊንግ አሎን…›› በሚል ርዕስ ያቀረበው ጥናት የህዝብ ተሳትፎ ጽንሰ ሃሳብን በተመለከተ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ይስተዋላል። እንደ ፑትናም አስተሳሰብ የህዝብ ተሳትፎ፣ ፋይዳ ላለው ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ የማህበራዊ እሴትን (ወይንም የሶሺያል ካፒታልን) ጠቀሜታ አጉልቶ የማሳየት ጉዳይ ነው። የፑትናም ትኩረት በይበልጥ ተሳትፎው ላይ እንጂ ተሳታፊዎቹ ላይ ወይንም ፖለቲካዊ በሆነው ጉዳይ ላይ አይደለም። የዜጎችንም የተሳትፎ ደረጃ ሲተነትን ከሞላ ጎደል ሁሉንም ነገር ለማካተት ይሞክራል፤ የተለያዩ ጋዜጦችን ማንበብን፣ በፖለቲካ ጉዳዮች መሳተፍን፣ የተለያዩ ማህበራት አባል መሆንንና ከዚያ የሚመነጨውን የአባላቱን የእርስ በርስ መተማመን ሁሉ በተሳትፎነት ይጠቀልላል። ፑትናም እንደሚለው እንዲህ ያለው ተሳትፎ በተግባር እየተተረጎመ ላለ ዴሞክራሲና ለገበያ ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ አለው (ፑትናም፣ 1993፣ 2000)። 

የህዝብ ተሳትፎ መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? ወይንም ዜጎች ህዝባዊ በሆኑ ጉዳዮች ለምን ይሳተፋሉ? ኬህን እና ኬምፏር (1968) የሚከተሉትን ሦስት ምክንያቶች ያስቀምጣሉ።

 1. በቅድሚያ ህዝባዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመምከርና ለመሳተፍ መቻልን ማወቅ በራሱ በግለሰቡ ላይ የራስ ክብርን፣ የብቁነትንና የነፃነትን ስሜት ይፈጥራል።
 2. ተሳትፎ የየግለሰቡን ጉልበትና ሃብት ለማህበረሰብ ጥቅም እንዲውል ለማድረግ ያስችላል።
 3. ማህበራዊ በሆኑ ችግሮች ላይ ሁነኛ መፍትሄዎችን ለማስቀመጥ ጥልቅ አስተያየቶችን፣ በቂ መረጃዎችን፣ እውቀትና ተሞክሮን ለማግኘት ይረዳል። 

የዜጎች ተሳትፎ ከተሳትፎው ከሚገኝ ጥቅም ወይንም ለተሳትፎው ከሚከፈል ዋጋ ጋር ተገናዝቦ ሊታይ ይችላል። አንዳንድ ጸሐፊዎች እንደሚሉት በተሳትፎ ውስጥ አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ያለው ግንኙነትና በሌሎች ጉዳይ የራስ ድርሻን በማበርከት የሚገኝ የራስ ክብር፣ እርካታና ማንነት ሁሉ ተካትተው ይገኛሉ። በተለይ ዜጎች በሆነ ተግባር በጋራ ለመሳተፍ እንዲያመቻቸው የሚመሰርቷቸው የበጎ ፈቃድ ቡድኖች ወይንም ማህበራት ግለሰቦችን ከማህበረሰብ እንደሚያገናኙ ድልድዮች (ወይንም እንደሚያያይዙ ሰንሰለቶች) ተደርገው ይወሰዳሉ (ዴሬስባኽ 1992፣ ፒሴዊትዜ 1991፣ ቤሊህና ባልደረቦቹ 1985፣ ኮርንሆውሰር 1959)። 

‹‹ተሳትፎ ለተርታው ዜጋ ምን ፋይዳ አለው?›› የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል። ብሪጅስ (1974) የተባለ ጸሐፊ ይህን ጥያቄ ሲመልስ አምስት ጠቀሜታዎችን ይሰነዝራል። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡-

 1. ህዝባዊ በሆኑ ጉዳዮች በመሳተፍ አንድ ዜጋ የራሱን ፍላጐት በራሱ በኩል ወይንም በማህበረሰቡ በኩል በማቅረብ የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ አስተዋጽዖ ማድረግ ይችላል፤
 2. ተሳታፊው ግለሰብ እንዲመጣ የሚፈልገው ለውጥ በምን ዓይነት መንገድ እውን እንደሚሆን ትምህርት ያገኝበታል፤
 3. በተሳትፎ ወቅት ተሳታፊው በግለሰብ ስሜትና በማህበረሰብ አባላት ፍላጎት መካከል ያሉትን ሁኔታዎች ያስተውላል፣ ይረዳል፣ ይገነዘባል፣ ያደንቃልም፤
 4. በተሳትፎ ወቅት አንድ ዜጋ እርስ በርስ የሚጋጩ ፍላጎቶች ለአጠቃላዩ ማህበረሰብ ጥቅምና ደህንነት ሲባል በምን አግባብ ሊፈቱ እንደሚችሉና እንደሚፈቱ ይማራል፤
 5. በተሳትፎ ተሳታፊው በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ያሉት ተለዋዋጭ ሁኔታዎች (ዳይናሚክስ) ምን እንደሚመስሉ ይገነዘባል፤

ህዝብን ማማከርና ማሳተፍ የተብላሉና በጣም ጥሩ የሆኑ ውሳኔዎችን ለመወሰን ይረዳል። መክረው ዘክረው የወሰኑት ውሳኔ ደግሞ በአብዛኛው ሰው ዘንድ ተቀባይነትን የማግኘት ዕድል አለው። አብዛኛው ሰው የተቀበለው ውሳኔ ደግሞ ለተርታው ዜጋ ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይታመናል (ኸበርለን 1976)። 

የዜጎች ተሳትፎ ሌላው ፋይዳ የፖለቲካ ተግባራትን ትክክለኝነትና ሚዛን ለመጠበቅ የሚያስችል መሆኑ ነው። ፖለቲካዊ አድልዖ፣ በዘመድ አዝማድ መጠቃቀም፣ ለግል ጥቅም የህዝብ ሃብትን መጠቀም ሚዛን የሳቱና በመሰረቱ የተሳሳቱ ተግባራት ናቸው። በየደረጃው ባሉ የውሳኔ አሰጣጥ እርከኖች ዘርፈ-ብዙ የዜጎች ተሳትፎ መኖር መሪዎች ለግል ጥቅም አመቺ የሆኑ ውሳኔዎችን እንዳያሳልፉና እንዳይፈጽሙ ለመከታተልና ለመቆጣጠር ያግዛል። ከተሳትፎ ውጭ ሆኖ እነኚህን ሁኔታዎች መታገልና መቆጣጠር አይቻልም። በሌላ አነጋገር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ከዳር ሆኖ የጥቅም ተቋዳሽ መሆን አይቻልም። ተጠቃሚነት ተሳትፎን ይጠይቃል። የህብረተሰብ መሻሻልም የዜጎች ተሳትፎ ውጤት ነው (ዌዴ 1989)። 

የልማት ፕሮግራሞች፣ እቅዶች፣ ተግባራቱና አመራራቸው ተቀባይነት የሚያገኙት ህዝባዊ ተሳትፎ ሲኖር ነው። ውድቀትንም ስኬትንም የሚወስነው ተቀባይነት ነው። ህዝባዊ ተቀባይነትን ያገኙ መሪዎች ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ ስራዎችን ለመፈጸም ቢታትሩም አይሳካላቸውም። የልማት ተግባራት በህብረተሰብ ውዴታና ፍቃድ ሲከናወኑ ወጪ ይቀንሳል፤ ሃብትም ይቆጠባል። ህዝብ ያልተቀበለው፣ ተቀብሎም ድጋፉን ያልሰጠው እቅድ፣ ማህበራዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ቢሆንም በሚፈለገው መልኩ የተሳካ አይሆንም (ኩክ 1975)።  

የህዝብ ተሳትፎን የሚያበረታቱ ሁኔታዎች

በህዝብ ተሳትፎ ጽንሰ ሃሳብ የህዝብ ተሳታፊነትን ሊያበረታቱ ይችላሉ ተብለው የሚታመኑ አምስት ሁኔታዎች አሉ። 

 1. የአደረጃጀቶች መኖር

ዜጎች ከተሳትፎ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት በአደረጃጀት ሲታቀፉ ነው። ነገር ግን ይህ ሁሌ ተሟልቶ አይገኝም። የማህበረሰብ አባላት ያለምንም አደረጃጀት በተለያዩ ህዝባዊ ተግባራትና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ ሊሳተፉ ይችላሉ። አግባብነት ያለው አደረጃጀት መኖሩና ዜጎችም በዚያ ስር ተጠልለው ተሳትፎ ማድረጋቸው አስተዋጽዖአቸውን ለማሳለጥና ተጠቃሚነታቸውን የጎላ ለማድረግ ይረዳል (ሲልስ 1966)። የተደራጀን አካል በቀላሉ ለመድረስ፣ ለማማከርና ለማገዝ ይቻላል። ያልተደራጀ ሃይል የተበተነ ነው፤ ለመድረስም፣ ለማማከርም፣ ለማገዝም ያስቸግራል።

ይሁን እንጂ አደረጃጀቶች ቢኖሩም ለማህበረሰብ አባላት ምቹና ሳቢ ካልሆኑ ተሳትፎው በሙሉ ፍላጎትና በሙሉ ልብ ሊሆን አይችልም። የህዝብ ተሳትፎን የሚጠይቁ አንዳንድ ተግባራት ቀድሞ ከነበሩት የተለያዩና ገለልተኛ የሆኑ አዳዲስ አደረጃጀቶችን ሊጠይቁ ይችሉ ይሆናል። ሆኖም ቀደም ሲል የተፈጠሩት ድርጅቶች ወይንም ማህበራት ተገቢ ሆነው የሚገኙበት ሁኔታም አለ። ልምድና እውቀት ያላቸው ሰዎች ሁኔታውን መዝነው በተሻለው አማራጭ ላይ መወሰን ይጠበቅባቸዋል። በማህበረሰብ አባላት አስተያየት ያሉት አደረጃጀቶች በጣም የተለጠጡ፣ ጊዜን የሚገድሉ፣ ዴሞክራሲያዊ አመራር የጎደላቸውና የተዝረከረኩ ከሆኑ ዜጎች ከጅምሩ አባል ሆነው ለመሳተፍ ፍላጎት አይኖራቸውም። በተለያዩ ሁኔታዎች ግፊት አባል ቢሆኑ እንኳ ውለው አድረው ለቀው መውጣታቸው አይቀርም፤ አሊያም ተሳትፏቸውን በማስተጓጎል (አከታትለው በመቅረት) አለመፈለጋቸውን ይገልጻሉ። ድጋፍና ትብብር በሚጠየቁ ጊዜም ጭራሽ እምቢ ሊሉ ይችላሉ። 

ከአደረጃጀት ጋር በጽኑ የሚያያዘው የተአማኒነት ጉዳይ ነው። እምነት የማይጣልባቸው ሰዎች ያሉባቸውና የሚመሯቸው ድርጅቶች የህዝብ ተሳትፎን እውን ሊያደርጉ ይቸግራቸዋል። በሌላ  አነጋገር፣ የማህበረሰብ አባላት የጎደፈ ስም ያላቸው ሰዎች ያሉበትንና የሚመሩትን ድርጅት ለመቀላቀል ወይንም ለማገዝ ፍቃደኞች አይሆኑም።

 1. ከመሳተፍ የሚገኝ ጥቅም ሲኖር

ዜጎች በተለያዩ ህዝባዊ ተግባራት የሚሳተፉት የሚያገኙት አንዳች በጎ ነገር መኖሩን ሲያዩ ወይንም ሲያምኑ ነው። በህዝባዊ ተግባራት በመሳተፍ የሚገኝ ጥቅምን መሻትና ለማግኘት መሞከር በጭፍኑ ጥቅም ፈላጊነት ነው ለማለት አይቻልም። ተሳታፊዎች ከመሳተፍ የሚያገኙትም ጥቅም በገንዘብ ወይንም በማቴሪያል ብቻ የሚገለጽ አይደለም። የግል መንፈሳዊ ፍላጎትን ከማርካት ጀምሮ የማህበረሰብን ሞራል ከፍ ለማድረግ የህብረተሰብ አባላት በልዩ ልዩ ተግባራት መሳተፍን ሊመርጡ ይችላሉ። ዋናው ነጥብ የማህበረሰብ አባላት የህዝብ ተሳትፎን የሚጠይቅ አንድ ጉዳይ መኖሩን መረዳታቸው፣ ሁኔታውም ሊለወጥ እንደሚገባ ማመናቸውና ከተሳትፎው የሚገኘውን በጎ ነገር ማጤናቸው ነው። ሰፊና ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎን እውን ለማድረግ በተጨባጭ ይገኛል ተብሎ በእርግጠኝነት የታመነበትና ይገኛል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ጥቅም በግልጽ ተለይተው መታወቅ ይኖርባቸዋል (ብሎው 1964፣ ሆማንስ 1974፣ ኮሰር እና ሮዘንበርግ 1970)።

ሆኖም ጥቅም ለማግኘት አንዳንድ ጊዜ የሚከፈል ዋጋ ሊኖር ይችላል። የዜጎች ተሳትፎም ወጪውን ከሚገኘው ጥቅም ጋር በማነጻጸር ይሆናል። የሚከፈለው ዋጋ በግል አሊያም በቡድን ሊሆን ይችላል። የሚከፈለው ዋጋም ዓይነቱ የተለያየ ነው። በገንዘብ፣ በጊዜ፣ በጉልበት ሊሆን ይችላል። ተሳትፎው ከሌሎች ጋር መቀያየምን አስከትሎ ተሳታፊው ወዳጆቼ የሚሏቸውን ሰዎች ሊያጡ ይችላሉ፤ ወይንም መገለልን የሚያስከትሉና ክብርን የሚነኩ ሊሆኑ ይችላሉ። ዋናው ነጥብ በህዝባዊ ጉዳዮች ሊይ በንቃት መሳተፉም ሆነ ጨርሶ አለመሳተፌ የየራሱ የሚያስከፍለው ዋጋ መኖሩ ነው። ዜጎችም ለመሳተፍ ወይንም ላለመሳተፍ ከመወሰናቸው በፊት ጥቅምና ጉዳቱን በራሳቸው መንገድ ያመዛዝናሉ። መቼ፣ ለምን፣ እንዴትና እስከምን ድረስ እንደሚሳተፉ ያወጣሉ ያወርዳሉ፤ በመጨረሻም ይወስናሉ (ብሎው 1964፣ ቫንደርዊስት 1975፣ ሆማንስ 1974፣ ኤመርሰን 1976፣ ኩሌበርግ 1977፣ ተርነር 1975)። 

 1. ኑሮን የሚያናጋ ሁኔታ ሲፈጠር

ሰዎች ኑሯቸውን የሚፈታተን ነገር ሲያጋጥማቸው ሆ! ብለው መነሳታቸው የተለመደ ነው። ለምሳሌ ትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራዎች፣ የትምህርት ቤት ማስፋፊያ፣ የአካባቢ ድንበር ከለላ፣ ወዘተ የማህበረሰብን ህይወት በጋራ የሚነኩ፣ መሰባሰብንና እርምጃ መውሰድን የሚጠይቁ ናቸው። አሳሳቢው ጉዳይ በባህርይው የተለያየ ሊሆን ይችላል። በህብረተሰቡ አስተያየት ህዝቡን በአንድ ያሰባሰበው ጉዳይ ከሞራል፣ ከባህል፣ ከኢኮኖሚ ወይንም ከሃይማኖት አንፃር ተቀባይነት የሌለው ሆኖ ይገኛል። የሰዎች ዓላማም ትክክል ወይንም የተሳሳተ ሊሆን ይችላል። ዋናው ነጥብ በፈቃዳቸው ተሰባስበውና እርምጃ ወስደው ሁኔታውን ለመለወጥ መነሳሳታቸው ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ ነው በህዝብ ተሳትፎ አግባብ የሚታየው። የተሳትፎው አነሳስ ግብታዊ፣ ደረጃውም ሰፊ ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ዜጎች ህይወታቸውን የሚነካ ነገር ሲያጋጥማቸው በህብረትና በፈቃደኝነት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸው ነው። 

 1. የዜግነት ግዴታ 

ዜጎች ህዝባዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት ሌላው ምክንያት ሁኔታውን እንደ የዜግነት ግዴታ አድርገው የተመለከቱት ሲሆን ነው። አንዳንድ ጸሐፊዎች መሆን ወይንም ሌሎችን የመርዳት ፍላጎት ብቻውን የተትፎ መነሻ ምክንያት ላይሆን ይችላል የሚል አመለካከት አላቸው። በማህበራዊ ጉዳዮች ለመሳተፍ ዋናው ምክንያት የተሳታፊው ሞራላዊ እምነት ወይንም የውስጥ ፍላጎት ነው። ካላመኑበት በስተቀር ሰዎችን ለማህበራዊ ተግባራት የየበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉና እንዲሳተፉ ማግባባት አዳጋች ነው (ሲልስ 1966)። በሀገራችን ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ ለቤተክርስቲያን ወይንም ለመስጊድ ግንባታ፤ አሁን አሁን ደግሞ ለትምህርት ቤቶች ምስረታና ማስፋፊያ እንዲሁም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የዜጎች መጠነ ሰፊ ተሳትፎ ምንጩ በጉዳዩ ላይ ያላቸው እምነት፣ ብሎም ከእምነቱ የሚቀዳ የዜግነት ግዴታ ነው ለማለት ይቻላል።

 1. በቂ መረጃ/እውቀት

ሰዎች በማያውቁት ነገር ውስጥ መሳተፍን አይፈልጉም። ስለዚህ አሳታፊው አካል የማህበረሰብ አባላትን ተሳትፎ በሚፈልግ ጊዜ ስለ ጉዳዩ በቂ መረጃ ማቅረብና ማሰራጨት ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ ዜጎች ሃላፊነት በተመላበት መንገድ በጉዳዩ ላይ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ያግዛቸዋል፤ ውጤቱንም የላቀ ያደርገዋል። አለበለዚያ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ይገባቸዋል። በዚህ የተነሳ ተሳትፏቸውን በቂ መረጃ እስከሚያገኙ ድረስ ሊያዘገዩት ይችላሉ፣ አሊያም እስከነ አካቴው ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ። የተሳትፎ ጥያቄው ግዳጅ የተቀላቀለበት ከሆነ የዜጎች ምላሽ በተቃራኒው ይሆናል። በውስን መረጃ ላይ የተመሰረተ ተሳትፎም ውሎ አድሮ ተቃውሞን ማስከተሉ አይቀርም። 

የሆነው ሆኖ ህዝባዊ ተሳትፎ በቀረበው ጉዳይ ላይ ጥሩ ግንዛቤን ለመያዝ መረጃ ብቻውን በቂ አይሆንም። ዜጎች በተጠየቁት ጉዳይ ላይ ከመሳተፋቸው በፊት የቀረበላቸውን መረጃ መመዘን፣ ቀድሞ ከነበራቸው እውቀትና ተሞክሮ ጋር ማነጻጸርና ሁኔታውን በራሳቸው መንገድ መረዳትን ይመርጣሉ። ስለዚህ አሳታፊው አካል ከዜጎች ሊያገኝ የፈለገውን ግብዓት የሚያገኝበትን መንገድ አስቀድሞ በተደራጀ አግባብ ማዘጋጀትና ሁኔታውንም ምቹ ማድረግ ይኖርበታል። 

ተሳትፎን ሊገድቡ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች

በአንዳንድ ምሁራን አስተያየት አደረጃጀቶች ወይንም የማህበር አባልነት ከሰዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ጋር የተያያዙ ናቸው። አነስተኛ ገቢ፣ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ፣ አነስተኛ ስራና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በበጎ ፈቃድ ማህበራት ውስጥ ለመሳተፍ ብዙም ተነሳሽነቱ የላቸውም። በዚህ አስተያየት ከፍ ያለ ገቢ፣ የትምህርት ደረጃ፣ ጥሩ የሚባል ስራና ደህና ኑሮ ያላቸው ሰዎች በህዝባዊ ጉዳዮች የተሻለ ተሳትፎ አላቸው። ልዩነታቸው የማህበረሰቡ አባላት ባላቸው የኑሮ ዘይቤ፣ አስተሳሰብ ፍላጎትና ዕሴት ላይ ይንጸባረቃል። እነኚህ ልዩነቶች ተሳታፊዎችን ምቾት ሊነሷቸው ይችላሉ። በእነዚህ ምሁራን አስተሳሰብ ዜጎች ማህበረሰባዊ በሆኑ ጉዳዮች ፈታ ዘና ብለው በደስታ የሚሳተፉት በሚመስሏቸው ሰዎች መሃል ነው (ሌን 1959፣ ሜልብራዝ 1965፣ ዴፉ እና ሌሎች 1974፣ ሃሪ እና ሌሎች 1969፣ ስተርን እና ኖ 1973፣ ፓስዊትዝ 1991፣ ድሬስባሽ 1992)። 

ሃብታምና ድሃው ተመሳቅሎ በሚኖርበት በእኛ ሃገር ይህን አስተያየት መቀበል ይከብድ ይሆናል። ነገር ግን አስተያየቱን ሙሉ ለሙሉ ማጣጣል አይቻልም። የተጠቀሱት ማህበረ – ኢኮኖሚያዊ ባህርያት ተሳትፎን ሊገድቡ ወይንም ለያውኩ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ አይቀርም። ስለዚህ የማህበረሰብ አባላትን ለተሳትፎ የሚጋብዘው አካል እነኚህ ባህርያት ተጽእኖ የሚያሳርፉ መሆን አለመሆናቸውን መገንዘብና አስቀድሞ መላ ማበጀት ይኖርበታል።

ሙራይና ባልደረቦቹ ‹‹በማህበረሰብ ህይወት የቡድን ስራ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ የህዝብ ተሳትፎን በሚጠይቁ ተግባራት የዜጎችን አስተዋጽዖ ከሚገድቡት ነገሮች ዋነኛው ፍርሃት ነው የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። ፍርሃቱንም በሦስት ይከፍሉታል። የመጀመሪያው ከእውቀት ማነስ ወይንም አልተማርኩም ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ ፍርሃትና የበታችነት ስሜት ነው። ይህ እውነት ወይንም ግምት ሊሆን ይችላል። ለመደበኛ ትምህርት ከፍ ያለ ቦታ በሚሰጥ ህብረተሰብ ውስጥ ይህ አስተሳሰብ ፍርሃትን መፍጠሩ አይቀርም። ሁለተኛው ባይተዋር ከመሆን የሚመነጭ ፍርሃት ነው። ብዙ ጊዜ በአዲስ መልክ የተቋቋሙ አደረጃጀቶች የተለያየ ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች ያሰባስባሉ። ይህ የተሞክሮ ብዝሃነት የሚፈለግ ቢሆንም ተሳታፊዎችን ባልለመዱት የስራ ድርሻና ሃላፊነት ላይ ሊጥላቸው ይችላል። ሰው በሚያውቀውና በለመደው ተግባር አስተዋጽዖ ቢያደርግ ይቀለዋል፤ ይፈልጋልም። ስለዚህ የሚመጣው በማይታወቅበት ሁኔታ ‹‹የእኔ ድርሻ ምን ይሆን? ምንስ ይመጣ ይሆን?›› የሚል ስጋትና የፍርሃት ስሜት መፍጠሩና ተሳትፎን መገደቡ አይቀርም። በእነሙራይ አስተሳሰብ ሦስተኛው የፍርሃት ስሜት ከኑሮ ደረጃ መለያየት ጋር የተያየዘው ነው። ይህም ከአለባበስና ከአነጋገር ጋር ይያያዛል። ልዩነቱ ሰፊ ከሆነ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳይኖር ሊያደርግ ሁሉ ይችላል። 

ከፍ ሲል የተዘረዘሩት ነጥቦች የህዝብ ተሳትፎን ሊገድቡ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ሁኔታዎችን ሁሉ አጠናቀው የሚያሳዩ አይደሉም። ይልቁንም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርና አዋኪ ሁኔታዎችን በማስወገድ የህዝብ ተሳትፎን የላቀ ማድረግ እንደሚቻል የሚያስገነዝቡ ናቸው። ለማህበረሰብ መሻሻል አስፈላጊ የሆነው የህዝቡ የራሱ ተሳትፎ በማህበረሰብ አባላት ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መርሆዎችን በመከተልና በመተግበር እንጂ በአጋጣሚ እንደ እድል የሚከሰት ነገር አይደለም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top