አጭር ልብወለድ

የህዳሴ ግድብ ድርመሳ ሴራ

1963 ዓ.ም. ከካይሮ አንስቶ አስከ አስዋን ያለዉ 853 ኪሎሜትር መንገድ ከየአቅጣጫዉ በመኪና፣ በባቡር፣ በእግረኛ ተጨናቋል። የምድረ ምስር ሰማይ በሶቪየት የመጓጓዣ አይሮፕላኖች ይታረሳል። በአስዋን ግድብ ምረቃ ስነስርአት ላይ ለመታደም አንድም የግብጥ ሰዉ በቤቱ አልቀረም። ህጻን ሽማግሌዉ፣ ወንዱ ሴቱ ከዳር ዳር ነቅሎ ወደዚያ ይጎርፋል። አካባቢዉ ከበረሀ ነዲድነቱ በላቀ፣ በድልና በስኬት ፈንጠዚያ ግሏል። አየሩ በሳቅ፣ በጩኸት፣ በዘፈን ታፍኗል። በግድቡ ላይ የተፈጠረዉ የናስር ሀይቅ ከጣና ገዝፎ ስራ ብዙ ሆኗል። ትናንሽና ትላልቅ ጀልባዎች እያጓሩ ይከንፋሉ። የረቡ አሳዎች ከሀይቁ ወደ አየር እየተመነጠቁ መልሰዉ ይጠልቃሉ። የአረብና የብዙ አገራት ዲፕሎማቶች ትርኢቱን በተመስጦ ይመለከታሉ። ከፊት ረድፍ የተቀመጡት የግብጡ ፕሬዚዳንት ጋማል አብዱል ናስርና የሶቪየት ኅብረት ፕሬዚዳን ኪሩታ ኪሩቼቭ በተለየ የደስታ ስሜት ይፍለቀለቃሉ።

ኢንጂነር ኡስማን በኩራት አካሄድ ከመድረክ ወጣ። ድምጽ ማጉያዉን መታ መታ አድርጎ ሞከረ።

“ዋሂድ! ኢትኒን! ተላታ!”

ዲስኩሩን ቀጠለ። አንዳንድ ንግግሮችን ሲያሰማ በክፍተኛ ድምጽና፣ ሲቃ በተሞላበት የሀያል አገላለጽ ነበር። በተለይም የሚከተሉትን ሲል፡–

“የአስዋን ግድብ ዛሬ ለኢጅብት ኃያልነት የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል። ከእንግዲህ ለሀበሻ ነገስታት ማስፈራርያ ወርቅ የምንገብር አንሆንም።”

የህዝብ ጩኸት አካባቢዉን አናወጠ። አጀብ ይባልለት የነበረዉ፣ ያን እለት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “ፋኖ ተሰማራ!” እያሉ ከጮሁት ጋር ሲወዳደር ልዩነቱ የመድፍና የሽጉጥ ጥይት ድምጽ ያክል ይራራቃል።

“የዛሬ 77 ዓመት በሀበሻ ምድር በኢትዮጵያዊያኖች የተገደለዉ ቅድመ አያቴ በዚህች ቅጽበት ከመቃብሩ ፈንቅሎ ተነስቶ በፈገግታ ዕያየኝ መሆኑ ሲሰማኝ ግላዊ ደስታዬ ከመጠን በላይ መሆኑን እንድገልጽ ይፈቀድልኝ” እንባዉን አበሰ። ሰረቅ አድርጎ ፕሬዚዳንት ናስርን ዐየ። ስለግል ታሪኩ ለመስማት እንዳልፈለጉ ጠርጥሮ ወደ ዋና ማጣቀሻዎች አፈገፈገ።

“እድሜ ለፕሬዚዳንት ጋማል አብዱል ናስር! የአያት ቅድመ አያቶቻችን ህልም፣ በተለይ የንጉሳችን የኢስማኤል ፓሻ ህልም፣ በሌላ አማራጭ እዉን ሆነ። የአባይን ዉሃ ለግብጣዉያን እስተንፋስ ለማዋል ሲሉ በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በጉራዕ እና በጉንደት በረሃ ህወታቸዉን ያጡትን የጦር አዛዦች እነ ራሺድ ፓሻ፣ ኡስማን ቤ-ነጊብ፣ ዶክተር ሞሀመድ አሊ ፓሻ፣ እንዲሁም ከእነሱ ጋር መስዋእት የሆኑ 20 ሺህ ግብጻዊያን በዚህች በዛሬዋ የድል ቀን በክብር ይታወሳሉ። የቆሰሉትን እነ ዶክተር በድሪ…”

ሲቃ ይዞት አረፍተ ነገሩን አቋረጠ። እንባ ተናነቀዉ። ንግግሩን ሊቀጥል ሲል ድምጹ ተዘጋ።ከመድረክ ፈጥኖ ወረደ።

ኢንጂነር ኡስማን የተናገረዉ ታሪካዊ እዉነታነት አያጣዉም።

ከ1886 ዓ.ም. እስከ 1888 ዓ.ም. ድረስ ግብጥ በቱርክ እየታገዘች ኢትዮጵያን ለመዉረር በርካታ ጦርነቶችን አካሂዳለች። ወረራዉ ተራ የግዛት ማስፋፋት ሳይሆን የአባይን ምንጭ ከነተፋሰሱ ለመቆጣጠር እና የቀጠናዉ ፈርጣማ ኃያል ለመሆን ነበር። የኢትዮጵያ ነገሥታት በተተነኮሱ ቁጥር እየተነሱ “ዋ! አባይን ገድቤ ልክ እንዳላስገባችሁ!.” የሚሉትን ፉከራ ለአንዴ እና ለመጨረሻዉ ለማክሰም ነበር።

ይህን ለማሳካት የግብጡ ንጉስ ኸዲፍ እስማኤል የምስራቁን እና የሰሜኑን የኢትዮጵያ ግዛት ቀስ በቀስ እየተቆጣጠረ አባይን ሊያፍን ጠንካራ ጦር አደራጀ። መጀመርያ ቦገስን (ከረንን) በመያዝ የቀይ ባህር ግዛቷን ቆረጠባት። ምርጥ የአሜሪካና የአዉሮፓ የጦር መሪዎችን ቀጠረ። በሰሜኑ በኩል 3ሺህ የግብጥ ጦር በዴንማርካዊዉ ኮሎኔል አረን ድሩፕ እና በአርመናዊዉ አራኬል ባየ መሪነት ከምጥዋ ተነስቶ ህዳር 8 ቀን 1886 ዓ.ም. ጉንደት- ጉንዳጉዲን ያዘ። አጤ ዮሀንስ ከወደላይ፣ ሻቃ አሉላ ከወደታች እና ከጎን ቀስፈዉ ይዘዋቸዉ፣ በአንዲት ዠምበር አንድም የወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ የኢትዮጵያን አፈር አለበሷቸዉ። ከኛም ወገን፤ መድፍ እየጓራበት፣ ጥይት እየዘነበበት፣ ጎራዴ እያብረቀረቀ፣… ወደምሽግ ከሚሮጠዉ አርበኛ 550 ለአገሩ ክብር ተሰዉቷል። 400 ያህል ቆስሏል። ከቆሰሉት ዉስጥ አንዱ የጀግናዉ  የጦር አዛዥ አሉላ አባነፍሶ ወንድም ባሻ ተሰማ ነበር።

ኢንጅነር ኡስማንን ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያንገበግበዉና የበቀል ሲቃ የሚያስተናንቀዉም ይህ ከታሪክ የሚያነበዉ የግብጦች ዉርደትና የኢትዮጵያ ጀግንነት ነዉ።

ይበልጥ የሚያብከነክነዉ ደግሞ በ1868 ዓ.ም. የተካሄደዉ የጉራዕ ጦርነት ዉጤት ነው። ኸዲፍ እስማኤል ሽንፈቱን ሊያካክስ ሲል፣ ወደ ጀርመን ልኮ፣ ጦር አዛዥነትን አስተምሮ በሻለቃነት ያስመረቀዉን የገዛ ልጁን ሙለይ ሀሰን ፓሻን የ15 ሺህ ሰራዊቱ መሪ አደረገ። አሜሪካዊዉን ጀኔራል ሎሪንግን ቀጥሮ ኤታማዦር እና ሁለተኛ የጦር አዛዥ አድርጎ ሾመ። አሜሪካዊዉን ኮሎኔል በይን ምክትል አዛዥ መደበለት።

የመድፉና የጠመንጃዉ ብዛት የትየለሌ ነበር።

በኛ ወገን ደግሞ አጤ ዮሀንስ የክተት ጥሪ አድርገዉ፣ ትግሬዉ ተመመ። በተጨማሪ የጎንደር፣ የወሎ፣ የጎጃምና የሸዋ ነፍጠኛ ያለመሪዎቹ ተቀላቅሎ፣ በስድሳ ሺህ ሰራዊት አዛዥ በሻቃ አሉላ መሪነት የግብጡን ጦር መጋቢት 2፣ 3 እና 4 ለሦስት ቀናት  ቀስፎ  ተገተገዉ። የግብጡን ጦር ሙጥጥ አደረገዉ። አጤ ዮሐንስን ከድተዉ ለግብጥ ይዋጉ የነበሩት ደጃች ወልደሚካኤል ሰሎሞን፣ አለቃ ብሩና ባሻ ገብረ ሥላሴ ንጉሴም መግለጽ በሚከብድ ሁኔታ እዚያዉ አብረዉ ተፈጠሙ።

  ኢንጅነር ኡስማን፣ በነ ኮሎኔል ባይ የዐይን ምስክርነት ስለጉራዕ የተዘገበዉን ታሪክ ባነበበ ቁጥር እፍረት ይሰቀጥጠዋል። ታሪኮቹን የት ይደብቃቸዉ? ምንስ ያድርጋቸዉ?

“…በወራሪዉ ጦር ደም የተበከለዉ የአበሻ ሠራዊት እጅ፣ ማረኝ እያለ ለሚያለቅሰዉ የግብጥ ቁስለኛ ይቅርታ ሳይዘረጋ አሻፈረኝ ማለቱ፤ ሰዉነቱ በጦር ከመሬት ጋር ተጣብቆ የሚያጣጥረዉ፣ እጁ ከትከሻዉ የተቀነጠሰ፣ አንገቱ ባንዲት የደም ስር የተንጠለጠለ፣ አናቱ በጎራዴ የተገመሰ፣ እዚያም እዚህ በጉራዕ መሬት የተበታተነ ያ ሁሉ የተረፈረፈ የግብጥና የቱርክ ጀሌ፣ የአዉሮፓ-አሜሪካ ጦር መኮንኖች የስቃይ ጩኸት ሰቆቃ፤ ከጥይት ሲሸሽ-በጦር፣ ከጦር ሲያመልጥ በጎራዴ– አቤት የግብጥ ጦር ፍርጃ! አቤት የኢትዮጵያውያን ድፍረትና ጀግንነት!“ ሲል የተጻፈዉን እንዴትስ አቃጥሎ ያዉድመዉ! አዝማሪም፡-

ዐጨደዉ ከመረዉ ያን የግብጥ ገብስ

ወቃዉ ደበደበዉ ሰጠዉ ለንፋስ

ዐሊሙ ነፍጠኛ ዐጼ ዮሐንስ

እያለ ዘምሮ በአበሻ ሰማይ የናኘዉንስ እንዴት ያጥፋዉ።

በዚህም ወቅት፣ ግብጣዊ ዝርያ ኖሮት በአባቱ ሱዳናዊ፣ በእናቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነዉ  መሀመድ ራኡፍ ፓሻ በዋና ጦር አዛዥነት ተሹሞ፣ ከሶማሌ ተነስቶ ጥቅምት 2 ቀን 1868 ዓ.ም. ሀረርን በግብጥ ቅኝ ግዛት ስር አስጥሏታል።

መነሻዉን ጅቡቲ አድርጎ ሸዋን ሰንጥቆ ወደሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ የገሰገሰዉ 1 ሸህ 2 መቶ የግብጥ ሰራዊት፣ በሱዊስ ተወላጁ በወርኔር ሙንዚንጀር ፓሻ ጠቅላይ አዛዥነት ነበር የተመራዉ። ይሄ ሰዉዬ በአጤ ቴዎድሮስ ዘመን እንግሊዞችን ወደ መቅደላ መርቶ ያስመታን ከይሲ ነበር። የሱ ሠራዊት የአፋርን ምድር እንደረገጠ፣ የአፋር ህዝብ በመሪዉ በመሀመድ ሀንፈሬ ስልት ነዳፊነት የግብጡን ጦር እንደነፈረ ግብጦ ደፈጠጠዉ። አንድም ሳያስቀር ሁሉንም አጨደዉ። ሙንዚንጀርም ከነሚሰቱ ተገደለ።

ኢንጅነር ኡስማን፣ በንግግሩ ላይ ዶክተር በድሪን ጠቅሶ እምባ የተናነቀዉም፣ በነዚህ ዉግያዎች ላይ ቆስሎ በርህሩኋ ሰገነይቲ ድጋፍ ህይወቱ የተረፈዉን ቅድመ አያትነቱን አስታዉሶ ነዉ። በዘመን ተዋረድ በወላጆቹ ሲተረክለት የሰማዉን በምናቡ ዐይቶ ነዉ። ምን መሰላችሁ የታየዉ!

 ጀግናዉ አሉላ አባነጋ የጉራዕን ምሽግ እንደሰበረ፣ ዶክተር በድሪ ሽጉጥ ሊመዝበት ሲል ያየዋል። ጎራዴዉን በንፋስ ፍጥነት መዝዞ የበድሪን ክንድ ያሳጥርና በወደቀበት ተረማምዶት ወደ ዋናዉ አዛዡ ይወረወራል። ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ዐይን ያዝ ሲያደርግ ዶክተር በድሪ ከዘመዶቹ ሬሳ ስር ወጥቶት ወደመንደር ያለከልካል።

ዘመዶቿ ሁሉ ጉራዕ ላይ ያለቁባት ሰገነይቲ ከጎጆ ስር ሆና ታነባለች። ጠመንጃ አንጠልጥሎ ወደ እሷ የሚያመራ አረብ እንዳየች ከቤት ዘልላ ገብታ ዱላ ይዛ ትወጣለች። ወዲያዉ ዶክተር በድሪ ጠመንጃዉን ከእግሯ ስር ከመሬት ይጥላል። ሮጣ ታነሳዋለች። ትደግንበታለች። በደም የተጨማለቀዉን ጉራጅ ሰዉነቱን ያሳያታል። በምልክት ዉሀ እንድትሰጠዉ ይለምናታል። የጠመንጃዉን ቃታ ታቀባብላለች። ከመሬት ተንበርክኮ ባልተቆረጠዉ እጁ ይማጠናታል። በዝምታ አፍጣ ካየችዉ በኋላ ሀዘን ይሰማታል።

“አነ ከማኻ ጨካን አይኮንኩን።” (እኔ እንዳንተ ጨካኝ አይደለሁም)

ዉሀ በቅል ሞልታ ስትሰጠዉ በአንድ ትንፋሽ ይጨልጣል። የፍየል ሞራ አሙቃ ቁስሉን ጠራረገችዉ። ምኑ ቅጡ እንዲያ… እንዲያ እንዲያ እያለ ሳምንት እያለፈ፣ ያ ፍቅር የሚሉት ምትሀት ይቀስፋቸዋል። “ሀቢብቲ” ሲላት “ሀቢቢ” ማለት መጣ። በጠፍ ጨረቃ ወጥተዉ፣ ካይሮ ገብተዉ፣እስማኤልን ወለዱ።

እስማኤልን ጉንደት ላይ ከተገደለዉ የግብጥ ጦር አዛዥ ሸጋ ልጃገረድ ጋር ያጋቡታል። በሞስኮ የግብጥ ዲፕሎማት ሆኖ ሲኖር ኡስማንን ይወልዳል። እዚያዉ በዉሀ ምህንድስና ትምህርት ያስመርቀዉና ኢንጂነር ኡስማን ያሰኘዋል። ይህ እንጂነር ነዉ እንግዲህ ከግብጥ ወጣት መኮንኖች፣ በተለይም ከመሪያቸዉ ጋማል አብዱልናስር ጋር እየመሰጠረ መፈንቅለ መንግሥቱን ያሳካዉ

ኢንጂነር ኡስማንና ናስርን ያስተሳሰረዉና፣ ለመንግሥት ግልበጣ ዋና መቀስቀሻ የሆነዉ የአባይ ግድብ ጉዳይ ነበር። የንጉስ ፋሩቅ አማካሪ እንግሊዛዊዉ መሀንዲስ ሀርሰት፣ አባይ በግብጥ በረሃ ዉስጥ ተገድቦ ዉሃዉ እየተነነ ከሚበክን፣ ሱዳን ዉስጥ ወይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተገድቦ ወዲህ ቢፈስ ይሻላል የሚል ምክር ለግሶ ንጉሱም በዚያዉ ተስማምተዉ ነበር። ኢንጂነር ኡስማንና ናስር ደግሞ በተቃራኒ ቆመዉ ሠራዊቱን ለአመጽ መቀስቀሻ ተጠቀሙበት። መንግሥት ፈንቅለዉ ናስር የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በሆነ ማግስት ኢንጂነር ኡስማንን የታላቁ አስዋን ግድብ ግንባታ ብሄራዊ ባለሥልጣን አድርጎ ሾመዉ። ኢንጂነር ኡስማንም በአያት ቅደመ አያቶቹ የበቀል መናፍስት እየተበረታታ አጣድፎ አጠናቀቀዉ።

በግድቡ መመረቂያ እለት ፕሬዚዳንት ጋማል አብዱል ናስር እና የሶቭየት ኅብረት ፕሬዚዳንት ክሩታ ክሩቼቭ ከመድረክ ወጥተዉ ሪበኑን ቆረጡና ተቃቀፉ።

“የለገስኩጽ 1.12 ቢሊዮን ዶላር ሳይባክን ለዚህ ድል በመብቃታችን ደስተኛ ነኝ።” አለ ክሩቼቭ እንዳቀፈዉ።

“ኢምፔሪያሊዝም ይዉደም! ሶሻሊዝም ይለምልም!” አለ ናስር አንዳቀፈዉ።

“ሌላ ምን እንድተባበርህ ትፈልጋለህ? የተወሰነ የብድር እርዳታ…”

“የጦር አየሮፕላን በብድር እንዲሰጡኝ በማክበር እለምናለሁ።”

“ስንት የጦር አይሮፕላን”

“መቶ።”

“መቶ?” ምነዉ ዓለምን ለመዉረር ታስባለህ እንዴ!?”

የአባይ ዉሀን ልጠብቅበት ብዬ ነዉ።” አፍሮ ረጅም አፍንጫዉን በመዳፉ ሸፈነ።

ክሩቼቭ ትከሻዉን መታ መታ አድርጎ ከመድረክ ሲወርድ፣ አብዱል ናስር በቆመበት ኢንጂነሩን በምልክት ጠራዉ። ወደ ራሱ ደረት ዐየና ትልቁን ንሻን ነቀለ። ከኢንጂነሩ ደረት ላይ እየሰካ አንሾካሾከ..

“ግድቡንስ ሞላህ። ኢትዮጵያ ፍሰቱን ብታቋርጥብንስ?” አለ በፈገግታ ተሞልቶ።

ለኢንጅነር ኡስማን ዱብዳ ቀልድ ሲለሆነበት መልስ አጥቶ ሳቅ አለ።

“አንተ ጀግና! ምንጩን ካልተቆጣጠርክ ግድብህ ይደርቃል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ትሄዳለህ። ካንድ ወር በኋላ ከሞስኮ ዩኒቨርሲቲ የምትመረቀዉን አበሻ መሀንዲስ በአፋጣኝ ዉሰዳት። ግንኙነትህ ከኔ ጋር ብቻ ይሆናል።” ከመድረክ ወረደ።

ሶስት ወር ባልሞላዉ ጊዜ ዉስጥ፣ በተአምራዊ ቅንብር የየመን ፓስፖርት ተዘጋጅቶለት፣   ሞሰኮ ሄዶ፣ ከኢንጂነር ሳራ ጋር ኒካ አስሮ፣ አዲስ አበባ ቦሌ ላይ ረጅሙ ህንጻ ዉስጥ “ኡቴክ ኢንተርናሽናል የብረታብረት እና የግንባታ እቃዎች አስመጪ ድርጅት” ከፍቶ ተደላደለ። በዓመቱ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ አስደረገ። ስሙንም ጃፋር አለዉ።

ጃፋር በ1964 ዓ.ም. ተወልዶ በዲታ ልጅ አስተዳደግ በቁመቱም፣ በእዉቀቱም እተመዘዘ ማትሪክን በከፍተኛ ነጥብ አለፈ፤ ራሺያ በስኮላርሺፕ ሄዶ ለሁለተኛ ዲግሪ የዉሀ እና ግድብ ቴክኖሎጂ አጠና፤ በከፍተኛ ማእረግ ተመረቀ። እግረ-መንገዱን የአባቱን አገር ግብጥን የአስዋን ግድብን ጎብኝቶ (ጉብኝት ብቻ እንዳይደለ በቅርቡ የጠቆመ ፌስቡክም ተነቧል) ወደ እናቱ አገር ኢትዮጵያ ተመለሰ። አዲስ አበባ አልመደብም ብሎ እናቱን አስጨንቆ በዚያም በዚህም ብሎ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪግ መምህር ሆኖ ተቀጠረ።

ጃፋር በተማሪዎችና በመምህራን የስራ ባልደረባዎቹ ዘንድ እንደተግባቢና ታታሪ ለመቆጠር ጊዜ አልፈጀበትም። ብስል ቀይዳማነቱ፣ ደልዳላ መዘዞ ሰዉነቱ፣ ፈጣን እና አንደበተ ርቱእነቱ በተለይ ከብዙ ሴት መምህራን እና ተማሪዎች ግብቡ እንዲሆን ረድቶታል። ለጋስነቱ እና ጋባዥነቱ ከተራ ሰዉ ጋር ብቻ ሳይሆን ከፌደራልና ክልላዊ ባለሥልጣናት ዘንድም ተወዳጅነትን አትርፎለታል። ይበልጥ ዝነኛ መምህር ያደረገዉ ግን እምብዛም ሳይተኮርበት የቀረዉን የመስክ ጥናት በአዲስ መልክ አደራጅቶ፣ ተማሪዎች በየወሩ በአባይ ወንዝና በጣና ላይ ጉብኝት እንዲካሄዱ ማድረጉ ነበር። ይህ ችሎታዉ የሹማምነቱን አድናቆት አትርፎለት፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ለመገንባት ገና ሀሳብ ሲፈነጥቅ፣ ያለምንም ተቃዋሚ የተሾመዉ ጃፋር ብቻ ነበር። ጃፋር፣ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የቴክኒክ አማካሪ ቦርድ አባል ብቻ ሳይሆን፣ መደበኛ ስራዉ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስለሆነ ወደ ግድቡ ስፍራ እየተመላለሰ ግንባታዉን ከቴክኒክ አኳያ እንዲያግዝ የተለየ ሀላፊነትም ተጥሎበታል።

በዚያ ሰበብ ሩጫዉ ወደ ህዳሲዉ ግድብ ሆነ። መኪናዉን አስነስቶ ፈትለክ ነዉ። ከባህርዳር እንደተመለሰም ከምርጥ ባለሥልጣናት ጋር ጣና ሆቴል ሲመካከር ማምሸት ነዉ። ይህ ሁኔታዉ፣ አንድ ሰሞን ከነፍኩልሽ ብሎ ስጦታ በስጦታ ሲደርጋት የነበረችዉን የድርጅቱን የግዢዎች የጥራት እና ቁጥጥር ዲሬክተር ከስጋት ላይ ጥሏታል። ፉንጊት እያለ የሚቀልድባት አንድ ቀን ወደ ቆንጂት ሊመራዉ ይችላል። ለሷ ጊዜ አልኖረዉም። ለግንኙነታቸዉ የተወሰነ ሰዓት እንዲሰጥ በምክር የጀመረችዉ ወደ መነታረክ- ከዚያም ወደ መኮራረፍ ሰፍቷል። ወራቶች እየነጎዱ ነዉ።

አንዴ ሳያስበዉ ከጉባ ከንፋ ቁና ቁና እየተነፈሰች ከዩኒቨርሲቲ ቢሮው ገባች። ደነገጠ። ያዉ እንደተለመደዉ “አግብቼ ልጅ እንድወልድ ወላጆቼ እየወተወቱኝ ነዉ። እድሜ ቆሞ አይጠብቅም። አንተ ስለዚህ የረሳህ ትመስላለህ።” እንደምትለዉ ሲጠብቅ፣ ሞባይሏን ከፍታ ፎቶ ያነሳችዉን ጽሁፍ እንዲያነብ ሰጠችዉ።

“ምንድነዉ እሱ?”

“ሰራተኛዉ ፒቲሽን ተፈራርሞብናል። በተለይ አንተ ላይ”

በችኮላ አልፎ አልፎ ማንበብ ጀመረ።…

“8ኛ/ በዚህ ሦስት ወራት እየተዘረገፈ ያለዉ የግንባታ ብረት ጥራት ደረጃዉን ያልተጠበቀ ብቻ ሳይሆን፣ በጠባዩ በፍጥነት ከብረትነት ወደ አፈርነት የመለወጡ ባህርይ የዉሃ ሙሌቱን ከሁለት ወራት በላይ የማይሸከመዉና ግድቡ የሚደረመስ መሆኑ ተረጋግጧል።”

“11/ የብረትና የህንጻ ግንባታ መሳርያዎች በተጭበረበረ ጨረታ “ኡቴክ” ለሚባለዉ፣ የቦርድ አባሉ ኢንጂነር ጃፋር አባት ድርጅት ተሰጥቶ በብዙ ሚሊዮን ብሮች አልባሌና ጎጂ መሳርዎች ገብተዋል”

“12/ የኢንጂነር ጃፋር የሴት ጓደኛ የድርጅቱን የግዢዎች የጥራትና ቁጥጥር ዲሬክተር ሆና መሾም ለተቀነባበረ ሴራ ለመሆኑ መረጃዎች አሉ።”

“14/ ይህም አካሄድ የህዳሴዉ ግድብ እንዳይጠናቀቅ ከዉጭ ጠላት አገር ጋር የተሸረበ ደባ ስለመሆኑ ፍንጭ አለ። በተለይም የኢንጂነር ጃፋር የሚያዘወትረዉ ቱታ ቀለም ቀይ፣ ነጭና ጥቁር መሆኑ፣ የግብጥን ሰንደቅ አላማን መልበሱ እንደሆነ ያመለክታል…”

ኢንጂነር ከልቡ ሳቀ። “አይ አበሻ! ወሬና ተረት ማቀነባበር ሲያዉቅበት! የሰንደቅ አላማዉ ቀለም ቀይ፣ ነጭና ጥቁር የሆነ የኢትዮጵያ ክልል የለም እንዴ? እንኳን ለስራ ለበአል አሰፍቼ ብለብሰዉ ምን ያሳፍራል!”

“ግጥምጥሞሹ ከግብጥ ጋር የተያያዘ መነሻ አለዉ እያለ ነዉ ነፍጠኛዉ። በተለይም ሁለቱ ኢንጂነሮች ሞተዉ ከተገኙ በኋላ ነገሩን ከዚህ ጋር እያያዙት ሰልፍ ሊወጡ ነዉ።”

“ማነዉ መሪያቸዉ?”

“መች አጣኸዉ!”

የሞባይሉን ቁጥሮች መታ። “ሀይ ጀኔራል! የግድቡ ግንባታ ሊቆም ነዉ። ያ ሰዉዬ አድማ እያስነሳ ነዉ። አንድ ነገር አድርግ”

“ዛሬዉኑ!” አለ ጎርናና ድምጽ ከወዲያኛዉ ጫፍ።

አሁኑኑ በርሬ እመጣለሁ። ትልቁ ሆቴል እንገናኝ።

ቦሌ ከጠበቀዉ ጥቁር መርሰዲስ የኋላ መቀመጫ እንዳረፈ መኪናዋ በከፍተኛ ፍጥነት ከነፈች። ትራፊክ ያፈናጠጠ ሞተረኛ ከኋላዉ ቀድሞት ጥግ እንዲይዝ አመላከተዉ።

“መንጃ ፈቃድ።” አለ የተፈናጠጠዉ ትራፊክ ዱብ እንዳለ ሰላምታ ሰጥቶ።

ሹፌሩ መንጃ ፈቃድ አሳየ።

“አስቲ የሁለታችሁን መታወቂያ።”

ጃፋር እየኮራ መታወቂያዉን ሰጠ።

ትራፊኩ የመኪናዉን የኋላ በር ከፍቶ ገባና ዘጋ። ሽጉጡን አመቻቸ።

“መሳርያዎን ይስጡኝ።”

“ለምንድነዉ የምሰጥህ.. መንግሥት ያስታጠቀኝን..”

“ጊዜ አናባክን። ሹፌር፣ ዝምብለህ በፍጥነት ቀጥታ ንዳ።”

”ምንድነዉ ጥፋቱ?” የት ነዉ የምንሄደዉ?”

 የትራፊኩን ሽጉጥ እንዳየ እያመነታ አስረከበ።

”ስልክ ልደዉል ጀኔራል ጋ” አለ ጃፋር ሞባይሉን እንደማዉጣት እያለ።

”አርፈዉ ይቀመጡ። እሳቸዉ ጋ እኮ ነዉ የምወስዶት። ሹፌር በፍጥነት ንዳ” አለ በፈገግታ ነጭ መለዮዉን እያስተካከለ።

ሞተረኛዉ ከመርሴዲሱ ቀድሞ የአደጋ ጊዜ ዋይታ እያሰማ ሲበር ተከተሉት።

የመስቀለኛዉን መንገድ ቀይ መብራት ጥሰዉ ሲበሩ አንዲት የመከላከያ ታርጋ የለጠፈች ፒካፕ ከሞተረኛዉና ከመርሰዲሱ መሀል ዘዉ ብላ ገባች። በማይታመን ቅልጥፍና ጃፋር በሩን በርግዶ ወደ ማርሰዲሱ ሲሮጥ፣ የኡቴክ ባለቤት ሸማግሌዉ አባቱ ከጋቢና የአቶማቲክ ተኩስ ሽፋን ሰጠዉ።

አጸፋ የተኩስ ዉርጅብኝ ከጎን በርሮ ከች ካለዉ ላንድክሩዘር ዘነበ። አካባቢዉ በጥይት እሩምታ ሲናጥ ጥቂት ቆይቶ፣ የመርሰዲሱ ተኩስ ቆመ። በመጨረሻ አንዲት ጥይት ተሰማች። እንጂነር ጃፋር የአባቱን ጭንቅላት ያፈረሰባት የመጨረሻ ጥይታቸዉ ነበረች።

ጃፈር እጁን ሰቅሎ ከመኪናዉ ወጣ። ከእጁ ሰንሰለት ሲገባለት የወርቅ አምባር የገባለት ይመስል ከትከት ብሎ ሳቀ።

“አልረፈደባችሁም?” አለ በግዴለሽነት።

የሀገር ጉዳይ ከሚመለከተዉ ዋና መስሪያ ቤት ሰፊዉ ቢሮ እንደገቡ ከፍተኛ ሹሙ ተነስተዉ እንደተራ ወዳጅ ጨበጡትና ከማዶዉ ሶፋ እንዲቀመጥ ጋበዙት።

“ሰንሰለቱን ፍቱለት።” አሉ እንደቀላል ነገር።

“እዉነትም እኒህ ሹም ርህራሄ ስለሚያበዙ ለስራዉ አይመቹም” ሲል በልቡ እያማ የሰንሰለቱን መክፈቻ ጎረጎረ ትራፊኩ።

“እንዴ ለካ በስላችኋል! ይልቅስ እንደደንባችሁ ደስጣ ወረቀት ስጡኝኛ ሁሉን ልጻፍላችሁ።” አለ ጃፋር እጁን እያስፈታ።

 “ትንሽ በቃል አጫዉተን። አንደበተ ርቱእ ስለሆንክ እዉነቱን እያሳመርክ።” አሉ ሹሙ እንደጫወታ።

“ከየት ልጀምርላችሁ፤ የአባይን ግድብ እንደ ተበላ አከርካሪ ከወገቡ ማሳሳት- በ65.7 ሚሊዮን ባጀት። በ92 ሚሊዮን የብሄር ብሄረሰብ አመጽና ክፍፍል አፋፍሞ ኢትዮጵያን መበተን። ያለ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የለምና…”

“ጃፈር፣ የምናዉቀዉን አትንገረን። ከከፍተኛ ሹማምንት እና ነጋዴዎች፣ ከፖለቲከኛ ልሂቃን ዉስጥ አብራችሁ ከምትሰሩት አስራ ሁለቱን ብቻ ንገረኝ።” ፈገግ እያሉ።

ጀኔራል እየተጣደፈ ገብቶ አፍጦ ጃፈርን ዐየዉ።

“ከከፍተኛ ሹማምንት አንደኛዉ ከፊትዎ የቆመዉ ጀኔራል ነዉ። ጀኔራል፣ እንዴት ብትሰለጥን ነዉ እባክህ አብረኸኝ በልተህ፣ ጠጥተህ፣ ሰርተህ፣ ከብረህ ያጋለጥከኝ።” እንደቀልድ።

“ያጋለጡህ እናትህ ጊፍቲ ሳራ ናቸዉ።”

“አታደርገዉም ማማ! ማዉጣጣትህ እንዳይሆን። ለአባይ ግድብ ቅዠት ብላ እናት ልጇን ለሞት አሳልፋ አትሰጥም።” ብልጣብልጥ ዐይኑን ቀሰረበት።

“የኢትዮጵያ እናት እንኳን ልጇን ራስዋንም አሳልፋ ትሰጣለች። ዲስኩርህን ተዉና ከእነማን ጋር ትሰራ እንደነበረ ዘርዝር።” ቆጣ አሉ ሹሙ።

“አያት ቅድመ አያቶቻችን በደረሰባቸው…”

”ጃፈር! ልትተባበር አልፈለክም ማለት ነዉ። በተረት መቶ ሀምሳ ዓመት  ወደ ኋላ አትጎትተን። ወደ ፊት ካላራመድከን ስራዉ ምን እንደሚጠይቅ ታዉቃለህ…” አለ ጀነራሉ ተኮሳትሮ።

“ደክሞኛል እባካችሁ። መናገር አልችልም። ወረቀት ስጡኝ። ሌላዉን ካረፍኩ በኋላ እዘረዝርላችኋለሁ።” በእርጋታ ልመና።

ጀኔራሉ ተነሳና ወረቀት ከሹም ተቀብሎ እስኪሰጠዉ ድረስ ጃፈር የሸሚዙን ኮሌታ ጫፍ በፍጥነት እያኘከ እንደ ከበሜላ ደጋግሞ መጠጠ።

ጄኔራሌ እንደ ነብር ጉብ ብሎበት ሊያስጥለዉ ቢል በድን ሆነበት።

ሹሙ በድንጋጤ ከወንበራቸዉ ተስፈንጥረዉ ጮኹ …”ጃፈር!” ”ጃፈር!” ”ጃፈር!” ”ጃፈር!”…

የድምጹ ገደል ማሚቶ ከፈርኦን ፒራሚድ ላይ ነጥሮ፣ የአስዋኑን የናስር ሀይቅ አናዉጦ፣ከትንታኔ ጋር የአሜሪካን እና የአዉሮፓን ቴሌቪዥኖች አጦዘ። የአባይ ተፋሰስ አገሮች ጆሮዎች ተቀሰሩ። ትላንት ማለዳ።

እኩለ ሌት ላይ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቻናሎች በአንዱ፣ መልከ መልካም ቄንጠኛ አንባቢ  እንዲህ ሲል አበሰረ፡-

“ሰበር ዜና። ከታላቁ ህዳሴ ጋር በተያያዘ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ። ምርመራዉ ሲጠናቀቅ ዝርዝር ሁኔታዉን ወደፊት ይገለጻል። ዜናዉ የቢቢሲ ነዉ።”

ብዥዥዥ..ድርግም…ቦግ፣ የመሳሪያ ለስላሳ ሙዚቃ፤ ከዛፍ ዛፍ የሚዘል ዝንጀሮ ምስል እየታጀበ። የቋንጣ እሽግ ሊያሳኝክ ከሚችል ጊዜ በኋላ የአንባቢዉ ምስል ብቅ አለ።

 “ስላአጋጠመዉ የቴክኒክ ችግር ይቅርታ። እንደገና አነበዋለሁ። ከታላቁ የህዳሴ ግድብ…”

ድርግም!           

ቂ! ቂ! ቂ!ቂ! ቂ! ቂ!

መች ስራ ይወዳል። ከትላንት ወዲያ ስለተራገፈዉ ብረት ደስ የማይል ወሬ እየነፈሰ ነዉ። “ባል የቦርድ አባል ሆኖ፣ እንዴት ሚስት የጥራትና ቁጥጥር ኃላፊ ትሆናለች” ብሎ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መጽሔት ጽፏል እያሉ ያወራሉ።“

የጉራ ሽንፈታቸዉ ቀጥታ ወረራ እንዳያደርጉ ይሄዉ እስከ ዛሬ ትምህርት ሰጥቷቸዉ አደብ ገዝተዋል። ኢትዮጵያን ወግተዉ ድል ሊያደርጉ እንደማችሉ የሚያስደሰኩራቸዉም ይሄ ትምህርት ነዉ።

መድሀኒቱ አንድና አንድ ነዉ። በጦርነት የማይቻለዉን አንድም በአስዋን ላይ አባይን ገድቦ፣ አናቱንም ተቆጣጠሮ፣ ተሸናፊን ባለ ድል- ባለድሉን ተሸናፊ ማድረግ- ለዘልዓለሙ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top