ስርሆተ ገፅ

ኤልያስ መልካ ከተለያዩ ሚዲያዎች ጋር ያደረጋቸውን ቆይታዎች ጥቂቶቹን…..


ይዛችሁ የመጣችሁትን እንግዳ የአዘፋፈን ስልቶችን . . . አንዳንዶች ለኢትዮጵያ ሙዚቃ አንድ የዕድገት እርምጃ ሲሉት ሌሎች ደግሞ ሙዚቃችንን መላ አሳጡት ብለው ይፈርጁታል። አንተ ምን ትላለህ?


ለውጥ ያለው፤ ግን አዲስ ሊባል የማይችል ለውጥ ነው፤ በሙዚቃው ላይ ለውጥ መኖሩን ነው። ነገር ግን አዲስ የሚባል ፈጠራ የለም። የሬጌ፣ እና ቴክኖ ስልቶ በሙዚቃዎቻችን ውስጥ ሲገቡ እናያለን። እኛ ሙዚቀኞችና አቀናባሪዎችም በነዚሁ ስልቶች እንጠቀማለን። . . . ይህን ግን ለኢትዮጵያዊው ሙዚቃ እድገት ሊባል የሚችል አይደለም። ሙዚቃ ቅንብሩን ስንሰራው የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማሳደግ አይደለም። የተለየ አዲስ ነገር ሰርቶ እኔ ካለፍኩም በኋላ ስሜ እንዲጠራበት በማለትም አይደለም። . . . በ1970ዎቹ ዓመታት ኢትዮጵያዊው የቅንብር ስልት እንዳለ ሆኖ የራሱን የተለየ ስልት ይዞ ብቅ በማለት ለሀገሪቱ ሙዚቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ የሚገለፀው ሮሃ ባንድ ነው። ከኛ ይልቅ ሮሃ ባንዶች ናቸው ትልቅ ነገር የሰሩት። የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቅንብር በስራቸው ውስጥ እንዳለ ሆኖ ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል። ሙዚቃው ጠንካራና ጆሮ ገብ እንዲሆን አድርገዋል፤ አዲስ ስልትን አስተዋውቀዋል። እኛ ስንሰራ የጆቫኒ ሪኮን ስልት ተከትለን ነው። ጆቫኒ አዲስ ስልት ፈጥሯል ማለት ነው። እነሱ ናቸው ትልቅ ነገር የሰሩት። /ፈርጥ መፅሔት፣ መስከረም/ጥቅምት፣ 1994/

ኤልያስ በፕሮግራም አይመራም ይባላል እውነት ነው?

ጥሩ ፕሮግራም አክባሪ አይደለሁ። ስራዎችን የምሰራው ዘና ብዬ ነው። . . .  እስካሁን ድረስ እኔ ጋር መጥተው በጣም ከሚገባው ጊዜ በላይ የቆዩ ዘፋኞች የሉም። የቆዩትም ስራው ጥሩ እንዲሆን ነው ያደረጋቸው እንጂ አልተጎዱም። እንዴት ለሚለው ስቱዲዮ ውስጥ በቆየህ ቁጥር ስራውን የበለጠ እያሻሻልክና እያስተካከልክ ነው የምትሄደው። አስፈላጊ ከሆነም የዘፈንከውን ዘፈን እንደ አዲስ ትጫወተዋለህ። ይሄ ደግሞ የሚጠቅመው ራሳቸውን ድምፃዊያኑን ነው። ስለዚህ በእኔ ምክንያት በፕሮግራማቸው መሰረት ያልጨረሱ ድምፃዊያን ቢኖሩም በመቆየታቸው ግን አልተጎዱም።


በአማካይ አንድ ድምፃዊ ስቱዲዮ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

እንደ ሁኔታው . . . የሚቆዩት ግን ሁልጊዜ በፕሮግራም መፋለስ ሳይሆን በራሳቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል . . . ለምሳሌ ሊታመሙ ይችላሉ፣ ውጪ ሀገር ሊሄዱ ይችላሉ፣ ዜማ ለመለወጥ ይጠፋሉ። በዚህ የተነሳ ስራው ሊቆይ ይችላል። ከዚህ ውጪ ፕሮግራም ከተፋለሰ እኔም የማሳብበው በእኔ ነው፤ እነሱም የሚያሳብቡት በእኔ ነው/ሳቅ/።


ወደዚህ ሙያ ስትገባ አርአያ የሆነህ አበጋዝ እንደሆነ ተናግረሃል። አሁን የተሸለምከው ከአበጋዝ ጋር በእጩነት ቀርበህ በመሆኑ ምን ይሰማሃል?

የአበጋዝን ሥራዎች በፊት ቤተክርስቲያን እያለሁ ሁሉ ነበር የምከታተላቸው። ወደ ካሴት ቅንብሩ ስገባም በብዙ ነገር ምክር የምጠይቀውና ብዙ ነገሮችን ያሳየኝ ሰው ነው። በቸገረኝ ቁጥር ስጠራው እዚህ ሀገር ካለ መጥቶ ሚክስ አደራረግ ላይ ያሉትን ችግሮች የሚያሳየኝ ነው። በስራዎቹም የማከብረው ሰው ነው። አሁን በዚህ ሽልማት ላይ አብረን በእጩነት መቅረባችን ደስ ነው ያለኝ። በመጀመሪያ በመሸለሜ በግሌ ደስ ነው ያለኝ። ነገር ግን የተሸለምኩ ከእከሌ ስለምበልጥ ነው የሚል አስተሳሰብ የለኝም። በአንድ ወቅት አንድ ሰው በርከት ያሉ ስራዎችን ሊሰራ ይችላል። ሌላው ደግሞ ብዙ ላይሰራ ይችላል። ሽልማቱም ይህንን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው የሚመስለኝ እንጂ በችሎታ ከአበጋዝ በላይ ነው ኤልያስ ብለው አይመስለኝም የሸለሙት። በአጠቃላይ የሙዚቃ ህይወትን ከተመለከትክ አበጋዝ በርካታ ምርጥ ምርጥ ስራዎችን የሰራ አሁንም እየሰራ ያለ ባለሙያ ነው። ስለዚህ በዚህ ሁሉ አልፎ ሁላችንንም በሙያው እየረዳ ያለ ሰው ነው። ስለዚህ በዚህ ወቅት በመሸለሜ በመጀመሪያ እግዚአብሔርን ነው የማመሰግነው። ሽልማቱ ሞራልን ይገነባል። በመሸለምህ ደስ ብሎሃል ወይ ላልከኝ አዎ እልሃለሁ፤ አበጋዝ ቢሸለም ኖሮ ደስ ይልሃል ወይ ብትለኝ አዎ እልሃለሁ።/ሳቅ/


በቅርቡ ከሰራኸው ካሴት የዘሪቱ ካሴት ለየት ያለ ነው፤ ዜማዎቹ እንደውም የውጪ ዜማዎች ናቸው የሚል ነገር አለ?

ካሴቱ እንዳልከው ለየት ያለ ቢሆንም ከውጪ የተወሰደ ዜማ እንደሌለ ነው የማውቀው። ደስ የሚለው ግን እንዲህ አይነት አስተያየት ከተሰጠ የውጪ ዘፈን አስመስለን መስራት ደረጃ ላይ ደርሰናል ማለት ነው። እንዲህ አይነት አስተያየት ያስደስታል። የውጪ ዘፈን የሚመስል ዘፈን በራሳችን መስራት መቻላችንን ነው የሚያሳየው/ሳቅ/።


ኤልያስ አለባበስ አያውቅም ይባላል?

ይህን የሚሉ ሰዎች በደንብ አያዩኝም ማለት ነው። እንደውም በደንብ እንደ እኔ የሚለብስ የለም። ስለዚህ በደንብ እዩኝ ነው የምለው /ሳቅ/


ኤልያስ ሙዚቀኛ ባይሆን ምን ይሆን ነበር?


እኔንጃ ምን ልሆን እንደምችል አስቤ አላውቅም። ምናልባት ኳስ ተጫዋች እሆን ይሆን ኳስ ልጅ ሆኜ እጫወት ነበር። ግን አሁን ልጫወት ብል አያስገቡኝ ይሆናል። ስለዚህ ሙዚቀኛ መሆን ነበረብኝ ሆኛለሁ። ሙዚቀኛ የማልሆን ቢሆን ኖሮ አልወለድም ነበር ብዬ ነው የማስበው።


12ኛ ክፍል ገብተህ ማትሪክ ሳትፈተን ያቋረጥከው ለምንድነው?


በልጅነቴ ትምህርት አልወድም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ደስ እያለኝ የተማርኩት የሙዚቃ ትምህርት ነው። 12ኛ ክፍል እንደገባሁ ስድስት ወር ተምሬ ማትሪክ መፈተን ነበረብኝ። ነገር ግን ልክ ወደ 12ኛ ክፍል እንዳለፍኩ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አለፍኩና ትምህርቱን ሳልጨርስ ገባሁ። የሙዚቃ ፍቅር ስለነበረኝ ያሬድ ለመግባት አላመነታሁም። ትምህርቱን ማታ ማታ ተምሬ እፈተናለሁ ብዬ ነበር የገባሁት። ግን ያሬድ ከገባሁ በኋላ ሁሉን ነገር አስረሳኝ። አሁን እንደውም ሳስበው በዚያ ወቅት ያንን ውሳኔ ወስኜ ወደ ያሬድ መግባቴ ትክክል ነበር ብዬ አስባለሁ። የዚያን ጊዜ ባልገባ ኖሮ እኮ ዛሬ ይህንን ሽልማት አላገኝም ነበር/ሳቅ/።


የተማርከው የሙዚቃ መሳሪያ ምንድነው?


ሜጀሬ ቼሎ ማይነሬ ፒያኖ


የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ ትሰራለህ?


ያው ፊልሙን በማየት ነው የምሰራው፤ ፊልም ማየት እወዳለሁ። የፊልሙን ታሪክ እየተመለከትኩ ነው ኢፌክቶችን የምሰራው። ሌሎች ፊልሞችን ስለምመለከት በዚያ አይነት እሰራለሁ። በነገራችን ላይ የፊልም ሙዚቃ አውቄ አይደለም፤ ስሰራ እንደመሰለኝ እንደ ፊልሙ ታሪክ ነው የምሰራው። ምን ያህል ትክክል እንደሆንኩ አላውቅም።


ዲቪ ሞልተሃል?


ዲቪ ልጅ ሆኜ በየጊዜው ነበር የምሞላው። እንደ እኔ አሜሪካ ለመሄድ የሚፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም። አንድ ጊዜ አሜሪካ ከሄድኩ በኋላ ግን ቶሎ ወደ ሀገሬ መመለስ ነው ያሰኘኝ። ከዚያ በኋላ ሞልቼ አላውቅም። /ዛሚ 90.7 ኤፍ.ኤም፣ ጥር 1998ዓ.ም/

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top