አድባራተ ጥበብ

ኢትዮጵያዊው ቨርጂል ማጅስተር ዮሐንስ (ዮን) ላቲኖ (1518-1608)

ዮን ላቲኖ (Juan Latino) በ16ኛው መጀመሪያ እስከ 17ኛው ምዕት ዓመት መባቻ በስፓኝ (ስፔይን) ከአውሮፓ በአንጋፋዎች አንዱ በሆነው በግራናዳ ካቴድራል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተመራማሪነትና በመምህርነት ዝናን ያተረፈ፣ ክብርን የተጎናፀፈ ጥልቅና ምጡቅ ዕውቅ ባለ ቅኔ፡- ገጣሚ፣ ሰዓሊና ሙዚቀኛ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር እንደነበር በዘመነ-ሬኔሳንስ “ወርቃማው የስነ-ጽሑፍ ታሪክ” ላይ በተለያዩ ቋንቋዎች የተካሂያዱ አያሌ የምርምር ሥራዎች ያመላክታሉ፡፡ ጌትስና ወልፍ (1998፡15-51) ዮን ላቲኖ የሚለውን ስም የሬኔሳንስ ሂዩማኒዝም ሌላው ወይም ተለዋጭ መጠሪያ ስም ሆኖ የስፔይንን ወርቃማ ስነ-ጽሑፍ ዘመን መመስረት የቻለ፣ አስገራሚ የቅኔና የቋንቋ ተሰጥዖና ችሎታ የታደለ ኢትዮጵያዊ ነበር በማለት ይናገራሉ፡፡ በዘመኑም ከየአቅጣጫው በሚሰነዘር የአድናቆት ማዕበል ተጥለቅልቆ እንደሞተ በሰፊው ያትታሉ፡፡ ታሪኩም ሆነ ሥራዎቹ ለአራት መቶ ዓመታት ያህል ተዘንግተው ሳይወሱ የመቆየታቸው ሁኔታም ፀሐፍቱ በፀፀት ይገልፃሉ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋና ትኩረትም ዮን ላቲኖ ከሀገሩ በምን ምክንያት ወጣ? ታሪኩስ ምን ይመስላል? እሱ ስለ ራሱ ማንት የተናገረው፣ በዘመኑ የነበሩ ምሁራንም ስለሱ ያሰፈሯቸው አስተያየቶች እንዲሁም ያበረከታቸው ‹‘ኢትዮጵያዊ ቨርጂል’ ያሰኙት ዋና ዋና ሥራዎች ምን ነበሩ? የፈጠው ተፅዕኖስ ምን ይመስላል? የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሳት አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦችን በመሰንዘር ኢትዮጵያዊውን ምጡቅ ባለ ቅኔ (ምን አልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ) ለኢትዮጵያውያን ማስተዋወቅ ነው፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ ስሙን በማስተዋወቅ በታሪኩ ላይ አተኩራለሁ፡፡

ከፀሐፍቱ መካከል ከላይ እንደተጠቀሰው “ዮን ላቲኖ” (Juan Latino) በሚል ስያሜ፣ ብዙዎቹ ደግሞ፣ “ዮአንስ (ዮሐንስ) ላቲኖ” (Joannes Latno) በሚል ስም ይጠሩታል፡፡ በልጅነቱ “ዮኒስ የሴዛው” በሚል ባርነቱን በሚገልፅ መጠሪያ ነበር፡፡ ይሁንና እሱ በአንደበቱ በመጀመሪያው ማለትም “ዮን ላቲኖ” (Juan Latino) ብሎ ራሱን ይጠራል፡፡ በዚህ ስም ራሱን ሲጠራም ማንነቱ “ኢትዮጵያዊ” መሆኑን በመግለፅ ነበር፡፡ እኔም ከኢትዮጵያዊ ስያሜ ብሂልና እሱም ራሱ ኢትዮጵያዊነቱን ካረጋገጠበት ማንነት ጋር በእጅጉ የተሰናኜ በመሆኑ በዚህ ፅሑፍ ለአንባብያን “ዮን” የሚለውን በመግደፍ ከዚህ በኋላ “ዮሐንስ” የሚለውን ስም በመጠቀም አቅርቤዋለሁ፡፡

ጌትስና ወልፍ (1998) ገና በጥናቱ መግቢያ መነሻ ሀተታቸውን የጀመሩት በአሜሪካ ታሪክ ከጥቁሮች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ፊሊስ ዊትሊ የተባለች በጌታዋ በጆን ዊትሊ በባርነት ያደገች ጥቁር ባለ ቅኔ አስደናቂ የግጥም መድበል አዘጋጅታ፣ ከጌታዋም ፈቃድ አግኝታ፣ ለማሳተም ወደ ማተሚያ ቤት ስትሄድ የገጠማትን ውጣውረድ እንደ ማነፃፀሪያ በማውሳት ነበር፡፡ ይኸውም፡- ጥቁሯ ገጣሚ ፊሊስ ዊትሲ በጥንታዊ የግሪኮ-ሮማን ሚቶሎጂ፣ ፍልስፍና እና ሥነ-ምግባር ላይ የተመረኮዘ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ፣ የግጥም መጽሐፍ ለማሳተም ወደ ማተሚያ ቤት በሄደች ጊዜ “ዕውን አንድ ጥቁር እንዲህ ያለ የመጠቀና የረቀቀ ቅኔ ከአእምሮው አፍልቆ ማቅረብ ይችላል ለማለት አያስደፍርምን?” ተብላ በእርግጥ ሥራው ከእርሷ አዕምሮ የመነጨ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ለምርመራ እንዲቀርብ ተደረገ፡፡ ዊትሊም በተጠየቀችው መሠረት መፅሐፉን ለምርመራ አቀረበች፡፡ ይሁን እንጂ ሊታተምላት አልቻለም፡፡ በመጨረሻም ከሌላ ነጭ ገጣሚ የተሰረቀ ካልሆነ መፅሐፉ ፈፅሞ ያንች ሊሆን አይችልም ተባለች፡፡ እሷም የራሴ አእምሮ ውጤት ነው በሚል ተከራከረች፡፡ ጌታዋ ጆን ዊትሊም በነገሩ አዝኖ ከጎኗ ሆኖ ብዙ ጥረት አደረገ፡፡ በኋላም በማተሚያ ቤቶች በኩል “በታሪክ ይህን የመሰለ የመጠቀ የጥበብ ሥራ ማሳተም የቻለ አንድ ጥቁር ለአብነት ከተገኘ ምን አልባትም ሊታተምልሽ ይችል ይሆናል” የሚል መልስ ተሰጣት፡፡ ዊትሊም በአውሮፓ ውስጥ የእርሷን የመሰለ መፅሐፍ ማሳተም የቻለ አንድ ጥቁር ባለቅኔ እንደ ዋቢ በምሳሌነት ለመጥቀስ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን እና በስፔን ሳይቀር ብዙ ተንከራተተች፡፡ እውነቱን ለመናገር ዊትሊ ቂልነት ነበረባት! በስፔን ቆይታዋ ልብ ያላለችውና ሊያመልጣት የማይገባ ምን አልባትም ለችግሯ መፍትሔ የሚሰጥ ዕድል ከራሷ ድከመት የተነሳ አምልጧታልና! በግራናዳ ቆይታዋ በስፔን ውስጥ የግጥም መፅሐፍ ለማሳተም የበቃ ዕውቅ ጥቁር ባለ ቅኔ አለ ወይ ብላ ሁነኛ ሰዎችን መጠየቅ ወይም ወደ አብያተ-መፃሕፍት ሄዳ ሳትታክት ካታሎጎችን ብትመለከት ኖሮ የባለ ቅኔውን የኢትዮጵያዊውን ዮሐንስ ላቲኖን ዘመን አይሽሬ ሥራዎች በማግኘት  በማስረጃነት ማቅረብ በቻለች ነበር፡፡ ይህን አለማድረጓ በእጅጉ አስጠቅቷታል፡፡

በፊሊስ ዊትሊን ያጋጠመው ይህን የመሰለው ከዘረኝነት የመነጨ መጉላላትና እገዳ በዘመኑ በነበሩ ነጭ ጸሐፍት ላይ የተጣለ እገዳ አልነበረም፡፡ እሷም የተሳሳተ ግምት ነበራት፡፡ ምክንያም ገና መጽሐፏን ወደ ማተሚያ ቤት ይዛ በሄደች ጊዜ “በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ጥቁሮች የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደምና ፈር ቀዳጅ ጥቁር ገጣሚ ተብየ ስጠቀስ እኖራለሁ” በሚል የተሳሳተ እምነት የነበራት በመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም በጥቁሮች ላይ በተጣለው እገዳ ምክንያት ምኞቷ አልተሳከላትም፡፡ ደግነቱ ተስፋ ቆርጣ መጽሐፏን ከማሳተም አለመገታቷ በእርግጥ ብርቱ ሰው አሰኝቷታል፡፡ ከዚህ ሁሉ ውጣውረድና ድካም በኋላም ቢሆን መጽሐፏን እንድያትሙላት መወትወቷን ባለማቆሟ ማተሚያ ቤቶች ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ ብዛት ያለው የነጭ ህዝብ የድጋፍ ፊርማ አሰባስባ እንድታመጣ መልስ ሰጧት፡፡ በዚህ ጊዜ “እንዲህ የመጠቀ ድንቅ ቅኔ የጥቁር ጭንቅላት ሊያፈልቅ አይችልም” በሚል ከንቱ አመለካከት ማተሚያ ቤቶች በር እንደዘጉባት ዊትሊ የነበራት ምርጫ ወደ አውሮፓ ሳይቀር ከሀገር ወደ ሀገር እየተዘዋወረች ዝናቸው የተናኘ የታላላቅ ባለ ቅኔዎችንና መሪዎችን ጭምር ‹ግጥሙ የራሷ የዊትሊ የአእምሮ ውጤት ነው› ብለው በፊርማቸው ድጋፍ እንዲሰጧት መማፀኗን ቀጠለች፡፡ በዚህ ጊዜ ግጥሞቿን በቅድሚያ አንብቦ የአድናቆት አዋጅ ያስነገረላት አንዱ ቮልቴር ሲሆን፤ ሌላው አቤ ግሪጎይር ነበር፡፡ ካስፈረመቻቸው አሥራ ስምንት ዝነኛና ዕውቅ ባለ ቅኔዎች፣ ደራሲያንና መሪዎች መካከልም ጆርጅ ዋሽንግተንና ቶማስ ጀፈርሰን ይገኙበታል፡፡ በመጨረሻም ተስፋ ሳትቆርጥ ባደረገችው ጥረት (እኤአ) በ1773 ዓ.ም የግጥም መጽሐፏን ለማሳተም በቃች፡፡

ፊሊስ ዊትሊ ‹የጥቁር አእምሮ ምጡቅና ጥልቅ የቅኔ ጥበብ ከቶ ሊያመነጭ አይችልም› በሚል የዘረኝነት ፍልስፍና በፈጠረው እምነት ከደረሰባት እንግልት፣ የሞራል ድቀትና ብስጭት ይልቅ በየሀገሩ እየዞረች ከእርሷ በፊት ለማሳተም የበቃ ጥቁር ለመፈለግም፣ ከዚያም የነጮችን የድጋፍ ፊርማ ለማሰባሰብ በደከመችው ድካም የፈጀችው ጊዜና ያፈሰሰችው ገንዘብ በቀላሉ የሚገመት አልነበረም፡፡ ከዚህ ይልቅ ደግሞ የዮሐንስ ላቲኖን ዕፁብ ድንቅ ሥራዎች በማስረጃነት ለማቅረብ ያላስቻላት የራሷ ዝና ፈላጊነት የጋረደው ግብዝነት ያስከተለባት ችግር በእጅጉ ጎድቷታል፡፡ ዊትሊ ልበኛ ብትሆን ኖሮ አንድ ጥቁር የምዕራቡን ዓለም ጥንታዊ እምነት፣ ፍልስፍና፣ ሥነ-ምግባርና ታሪክ በምዕራብያኑ ቋንቋ በረቀቀ የቅኔ ጥበብ ተወዳዳሪ በማይገኝለት ሁኔታ ማቅረብ እንደሚችል የግራናዳውን ጥቁር ፕሮፌሰር የዮሐንስ ላቲኖን ሥራዎች በምሳሌነት ለማተሚያ ቤቶቹም ሆነ በንቀት ዓይን ይመለከቷት ከነበሩ ነጮች በጊዜው በማቅረብ ያን ያህል ከተራዘመ እንግልትና ብክነት ማምለጥ ትችል እንደነበር ተመራማሪዎቹ በመግለፅ የኢትዮጵያዊውን “ቨርጂል” ታሪክ በሚከተለው ሁኔታ ይተርካሉ፡፡

ቨርጅል እንደገና፡- ከቨርጅል በኋላ እንደገና ቨርጂል የተባለው ባለ ቅኔ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ በላቲን ቋንቋ አስተሪያድ የተሰኘውን መጽሐፍ ያሳተመው ፈሊስ ዊትሊ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከማሳተሟ ከ200 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ የሚያስደንቀው ነገር ቢኖር ደግሞ ስርባንቴስ በ1605 ባሳተመው ዶንኪዮቴ በተሰኘው መጽሐፉ የኢትዮጵያዊውን ሥርወ-አመጣጥ ታሪክ፣ የነበረበትን ሁኔታና ሥራዎቹን ያነሳሳበትን ጥራዝ ዊትሊ በፊርማ ለማሰባሰብ እንግሊዝ አገር በሄደች ጊዜ ወዳጆቿ በስጦታ ሸልመዋት በእጇ ይገኝ ነበር፡፡ ዊትሊ በተለያዩ መስኮች አንዳንድ ጥረት ያደረጉ ከዘመኗ በፊት እና በዘመኗ የነበሩትን ጥቁሮች በመጽሐፏ መግቢያ ስትጠቅስ የፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖን አስትሪያድ ለምን የጥቁር አእምሮ የረቀቀና የጠለቀ ቅኔ ሊያፈልቅ እንደሚችል ለምስክርነት እንዳልጠቀሰችውና እንደተወችው እነ ጌትስ ትዝብታቸውን በዚሁ ገልፀው ወደ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ ታሪክ ያመራሉ፡፡

የእነ ጌትስ ጥናት እንደሚያትተው የዮሐንስ ላቲኖን በአውሮፓ መገኘት አስመልክቶ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ አንደኛው በበርበራ ወደብ በኩል ከኢትዮጵያ ወደ ፖርቱጋል እንደሄደና ከዚያም ወደ ስፓኝ የመጣ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ሌላው ግምት ደግሞ ትምህርት ፍለጋ ከትውልድ አገሩ ከኢትዮጵያ ወደ ፖርቱጋል እንደሄደና በኋላም ወደ ስፔይን እንዳመራ የሚጠቁም ነው፡፡ በእነዚህ የአስተያየት አቅጣጫዎች መካከል ደግሞ በሃያኛው ክፍለ-ዘመን ማብቂያ ገደማ የነበሩ ሁለት ጸሐፍት በደፈናው በባርነት የተፈነገለ አፍሪካዊ በማለት የትውልድ አገሩን ሳይጠቅሱ አልፈውታል፡፡ ታሪኩን ከመጀመሪያው አቅጣጫ አንፃር የሚያቀርቡት ጸሐፍት እጅግ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ጸሐፍቱ እንደሚሉት ዮሐንስ ላቲኖ በልጅነቱ “ዮኒስ

ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ – ኢትዮጵያዊው ቨርጂል

የሴዛው” እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ ይህ ስምም በዘመኑ ለባሪያ መጠሪያ የሚሰጥ ነበር፡፡ ዮኒስ በአስራ አራት ዓመቱ የሴዛው መሥፍን የፍራንሲስ ፈርዲናንድ የቦክር ልጅ የዮን ጎንዛሎ አገልጋይ ሆኖ ሲመደብ “ዮኒስ የሴዛው” የሚለውን የጌታውን ስም ወሰደ፡፡ በዕድሜም ወጣቱን መስፍን ዶን ጎንዛሎን በስምንት ዓመት ያህል ይበልጠው ነበር፡፡ (Schild and Norman: 1972: 189-190)::

እሱ በዚህ ሁኔታ ሲኖር እናቱ ደግሞ የጎንዛሎ ፈርናንዴዝ ልጅ የኮርዶቫይቱ የዶና እልቪራ ባሪያ ሆና ተቀመጠች፡፡ አንዳንዶች “ዮኒስ የሴዛው” የተወለደው (እኤአ) በ1518 ዓ. ም. ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ በ1495 ዓ.ም ነበር ይላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ የዮኒስ የሴዛው ዋነኛ ተግባር የጌታው ወጣቱ መስፍን ዶን ጎንዛሎ ትምህርት ቤት ሲሄድ መጽሐፍቱን፣ የጽሕፈት መሣሪያዎቹንና ካፖርቱን ተሸክሞ መከተል፣ ዶን ጎንዛሎ በሚማርበት ሰዓት ደግሞ ፈቅ ብሎ በመቀመጥ ጌታውን በመጠበቅና ከትምህርት ገበታው ሲነሳ መጽሐፍቱንና የጽሕፈት መሣሪያዎቹን እንደዚያው ተሸክሞ ወደ ሠፈር ተከትሎ መሄድ ነበር፡፡

በዚህ የልጅነት የአሽከርነት የዕለት ተዕለት ሕይወቱ ነበር ኢትዮጵያዊው ዮኒስ የሴዛው የብርሀን ዓለም በውስጡ የፈነጠቀው እና የዕድሉን አቅጣጫ ያሰመረው፡፡ በርካታ ጸሐፍትን ዋቢ አድርገው እነ ጌትስ (1998) እንደሚሉት፤ ዮኒስ የሴዛው ብሩህ አእምሮ ነበረው፡፡ በመሆኑም ጌታው ወጣቱ መሥፍን በትምህርት ገበታ ላይ ይቀስመው የነበረውን ትምህርት ፈቅ ብሎ ተቀምጦ በጉጉትና በተመስጦ በማዳመጥ እንደተጠማ መሬት ምጥጥ አድርጎ ቀለም ሊጠጣ ችሏል፡፡

ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ የሞተው በ1608 (እኤአ) ነበር፡፡ እንደሞተም ቤርሙዴ ይ ፔድራዛ ጥቁሮችን በሚል የሀዘን እንጉርጉሮ በግጥም በማቅረብ ስለ ሕይወት ታሪኩ በላቲን ቋንቋ ካሠፈረው ትርጉም የተገኘ ጽሑፍ ዮሐንስ ላቲኖን የአገረ ኢትዮጵያ ክብር (“The Honor of The Ethiopian Nation”) ብሎታል፡፡ የሴዛው ብላቴና የጎንዛሎ አሽከር ሆኖ ያገለግል የነበረበትን የሕይወት ዘመኑንም “በማስተዋል ብቻ ከጌታው በላቀ ሁኔታ መማር የቻለ አስደናቂ፣ ልዩ የሆነ፣ ኢትዮጵያዊ ፍጡር!” ብሎ ማድነቁም እንደዚሁ ተጠቅሷል፡፡

ቤርሙዴ ይ ፔድራዛ ከፕሮፌሰር ሁዋን ላቲኖ ጋር በግሬናዳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያስተምር የነበረ የቅርብ ጓደኛው ነበር፡፡ እሱም የልጅነት ታሪኩን ሲገልፅ፣ “ይህ ለባርነት ተወስኖ የነበረው ኢትዮጵያዊ አስደናቂ ፍጡር ልዩ የሆነ የተሰጥኦውን ስለት ያሳረፈው በጌታው በመሥፍን ጎንዛሎ አእምሮና ሥነልቦና ላይ ነበር” ማለቱም ሠፍሮ ይገኛል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም ዶን ጎንዛሎ እንደ አገልጋይ ሳይሆን እንደ ዕውቀት ጓደኛው አድርጎ በመቀበል የላቀ ችሎታ እንዳለው ይናገርለትና ያከብረው ከመጀመሩም በላይ “እንደ ፊኒክስ በምድር ላይ ብርቅ የሆነ ጥቁር” ሲል አድናቆቱን በማስተጋባት እየቆዬ የባርነት ቀንበሩን ሊያወርድለት ችሏል፡፡ ምንም እንኳን በስሙ ዮኒስ የሴዛው ተብሎ መጠራቱ እና መታወቁ ለተወሰነ ጊዜ አብሮት ቢቀጥልም ነፃ ሆኖ ቆይቶ በአንድ የትምህርት ገበታ አብሮት እንዲማር አድርጓል፡፡

እናም ትንሳኤው እውን ሆኖ ዮኒስ የሴዛው ከዶን ጎንዛሎ ጋር ትምህርቱን በመቀጠል በ1546 ዓ.ም በግሬናዳ ዩኒቨርሲቲ በላቲን ሥነ-ጽሑፍ ቋንቋ የባችለር ዲግሪ አገኘ፡፡ ቀጥሎም በ1548 የክብር ማስትሬት ዲግሪውን በላቲን ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ለማግኝት በቃ፡፡ በልጅነቱ ሕክምና ለመማር የነበረው ፍላጎት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ሆኖም አንድ ጓደኛው የህክምናውን ፍላጎት ትቶ በላቲን ቋንቋና ሥነጽሑፍ እንዲቀጥል ይገፋፋውና ‹ዮኒስ የሴዛው› በሚል ይጣራበት የነበረውን የባርነት ስም በመቀየር ‹ዮሐንስ ላቲኖ› በሚል ስም ይጠራው እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ ዮሐንስ ላቲኖ በዚያው በግሬናዳ ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪውን በከፍተኛ መዐርግ ባገኘ ማግስት የሆሬስን ሥራዎችን ተረጎመ፡፡ በ1556 በግሬናዳ ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ፣ በተለይም በላቲን ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ የፕሮፌሰርነት መዐርግ ተሰጠው፡፡ ስሙም በይፋ ዮሐንስ ላቲኖ እንዲሆን ተደረገ፡፡ በአጠቃላይ በርካታ የሆኑ የዘመኑ ጸሐፍት ዮሐንስ ላቲኖ ከኢትዮጵያ በባርነት ተሽጦ ወደ እስፓኝ የመጣና ዕድሉን በራሱ የውስጥ ጥንካሬ መለወጥ የቻለ ብቻ ሳይሆን በሬኔሳንስ ሂዩማኒዝም የለውጥ ዘመን የላቀ ሚና የተጫወተ የስፓኝን ወርቃማ የሥነ-ጽሑፍ ዘመን መመሥረት እና መገንባት የቻለ፣ እንዲሁም የአፍሪካዊያንን ዕውቀትና ችሎታ ያስመሰከረ ኢትዮጵያዊ ነው ብለውት እናገኛለን፡፡

የባለቅኔው ፕሮፌሰር የዮሐንስ ላቲኖን ታሪክ ከላይ ከቀረበው ለየት ባለ መንገድ አስፍረውት እንደሚገኙ የተጠቀሱት ጸሐፍት ደግሞ ባዮግራፊ ዩኒቨርዛሌ ክላሲክቷ (1829) እና ባዮግራፊ የኒቨርዛሌ ዴስ ሆሚስ ኪ. ሲ. ሶንት ፌት ኡንኖም (1860 ) የተባሉትን ኢንሳይክሎፔዲያዎች ያዘጋጁት ጎሲሊንና ፌለር ናቸው፡፡ እነዚህ ጸሐፍት የሳላማንካንና የግሬናዳ ዩኒቨርሲቲዎችን የታሪክ መዘክሮች ዋቢ በማድረግ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ባሠፈሩት ጽሑፍ ዮሐንስ ላቲኖ የዝነኛው ክሌናርድ ዝነኛ ኢትዮጵያዊ ደቀ መዝሙር እንደነበረ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡ ጸሐፍቱ አሠፈሩት የተባለው የኢንግሊዝኛው ትርጉም እንደሚገልፀው ዮሐንስ ላቲኖ ከአገሩ ከኢትዮጵያ የወጣበት መሠረታዊ ምክኒያት በባርነት ሳይሆን ለትምህርት ፍለጋ ነበር፡፡ ለዚሁ ዓላማ በመጀመሪያ ወደ ፖርቱጋል በመሄድ ከዝነኛው ክሌናርድ ለመገናኘት ከዚያም እንደተመኘው ሁሉ ትምህርት ለማግኜት ችሏል፡፡

እንደምንረዳው ዮሐንስ ላቲኖ ትምህርቱን ደህና አድርጎ ለመቀጠል ከቻለ በኋላ እዚያው ፖርቱጋል ውስጥ በሚገኘው በሳላማንካ ዩኒቨርሲቲ ለጥቂት ጊዜ አስተምሯል፡፡ ከዚያም በ1535 ዓ.ም ወደ ስፓኝ አምርቷል፡፡ ከፖርቱጋል ወደ ስፓኝ ለመሄድ ያነሳሳው ምክኒያትም ዓረብኛ ቋንቋን በጥልቀት ሊያስተምረው የሚችል መምህር በመፈለግ ነበር፡፡ ይህን ፍላጎቱ ማሟላት መቻል አለመቻሉ ባይገለፅም እንኳን ዮሐንስ ላቲኖ በቀጥታ ግሬናዳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለማስተማር መግባቱን ግን ጸሐፍቱ አመልክተዋል፡፡ ጎሲሊንና ፌለር ያሠፈሩት ይህ ታሪክ ተቀባይነት ያለው ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ከ15ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ አንስቶ ፖርቱጋሎች የንግድ እንቅስቃሴያቸውን አጠንክረው ይገኙ ስለነበር የውጪውን ዓለም ትምህርት ለመቅሰም ፍላጎት የነበረው ዮሐንስ ላቲኖ በፖርቱጋል ነጋዴዎች ወይም ተወላጆች እርዳታ አውሮፓ ለመድረስ ዕድል አግኝቷል ማለት የሚያስችል በመሆኑ ነው፡፡

ከላይ ከተገለፁት የዮሐንስ ላቲኖ የአውሮፓ ጉዞ ታሪኮች ውጭ በ20ኛው ክ/ዘመን ጉዳዩን ያነሱ አንዳንድ ጸሐፍት ዮሐንስ ላቲኖ በጥቅሉ አፍሪካዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ ነው ብሎ ሙሉ በሙሉ ለመናገር የማያስደፍር መሆኑን የገለፁበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህ ሁኔታም በመላው ዓለም የሚገኝ ጥቁር ሁሉ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ማለቱ የተለመደ ክስተት ሆኖ ከመገኘቱ ዕውነታ ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ሺልድ እና ኞርድማን (1672) “በጊኒ በኩል ተሽጦ የወጣ አፍሪካዊ ሳይሆን አይቀርም” ሲሉት ማሪን ኦቺቴ (1925) ወደ ኢትዮጵያ ራስን የማስጠጋት የተለመደ አዝማሚያ ስላለ ዮሐንስ ላቲኖ በጥቅሉ አፍሪካዊ ነው ማለቱ ከጥርጣሬ ነፃ ያደርጋል ማለቱ ተጠቅሷል፡፡

ይህ ዓይነቱ አስተያየት የዮሐንስ ላቲኖ ማንነት አድበስብሶ ለማለፍ መፈለግ ብቻ ሳይሆን ከታሪክ መሸሽም ይሆናል፡፡ በእርግጥ የዓለም ጥቁሮች በኢትዮጵያ ይመካሉ፡፡ ይሁን እንጂ በጥቁሮች ዘንድ ኢትዮጵያን እንደ ዐርማ የማየቱ ስሜት ሥርዓትና ጥንካሬ ግን ከ1896 ዓ.ም ከዓድዋው ጦርነት ወዲህ በይበልጥ የዳበረ እንጂ ዮሐንስ ላቲኖ አውሮፓ በነበረበት በዚያን ዘመን መንፈሱ እንዲህ የተንሰራራ ነበር ለማለት የማያስደፍር በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክን መመርመርና እና እሱ ማንነቱን የገለፀበት አውደ ሁኔታና ዕውነታ ማጤንን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ ስለ ራሱ ኢትዮጵያዊነት ኤል ኤስኮሪያል በተባለው የግጥም መጽሐፉ ሌሎቹም በዘመኑ የነበሩ ጸሐፍትና ሃያሲያን ስለሱ ማንነት ያሠፈሯቸውን ገሸሽ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ነበር ማለቱ ስለሚከብድ በደፈናው አፍሪካዊ ሙሉ ደም ያለው ቢባል ከጥርጣሬ ነፃ ያደርገዋል ማለት ሊገጣጠም በሚያዳግት ከዘመናት በኋላ በታዬ ክስተት ይበልጥ ሀሳብ መወሰንን የሚያመለክት አስተያየት እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡

እንግዲህ የተለያዩ ጸሐፍት ስለ ዮሐንስ ላቲኖ ያቀረቡትን የማንነትን ታሪክ ለግንዛቤ ያህል ከላይ እንደተመለከትን ሁሉ እሱም ስለ ራሱ በተናገራቸው በጻፋቸው መረጃዎች ላይ ትኩረት መስጠት ተገቢ ይሆናል፡፡ ጌትስና ወልፍ (1998፡41) ባቀረቡት መሠረት ባለ ቅኔው ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ በ1576 በላቲን ቋንቋ ባሳተመው ኤል ኤስኮሪያል በተባለው የግጥም መጽሐፍ ውስጥ የኦስትሪያን ያሸበረቁ ገድሎች በቅኔ ለመዘመር “ከኢትዮጵያ ምድር መጣሁ እንጂ ከዚህ አከባቢ (አውሮፓ ውስጥ) አልተፈጠርኩም” ማለቱን በሚከተለው አገላለፅ እንረዳለን፡፡ ይህም፡-

“The Writer was not engendered in [this] region. He Comes, Latino from the Land of the Ethiopian to sing the marvelous deeds of Austria with the art of song”.

የሚል ነው፡፡ በዘመኑ የስፓኝ ንጉሥ ለነበረው ዳግማዊ ፍሊፕ ንጉሥ ሆይ! “ጥቁረታችን ሚኒስትሮችዎን እያስጠላቸው ቢሆንም ነጭነትም እንደዚሁ ለኢትዮጵያዊያን አስደሳች አይደለም” ሲል ፊት ለፊት እንደተናገረው ተጠቅሷል፡፡ ይኸውም፡-

For if our black face, Oh king, is displeasing to your ministers, the white face is not pleasing to the men of Ethiopia. There, he Who, being white, visits the East is held in little esteem. The leaders are black, and The king there is black (Gates  and wolf 1998:28)

የሚል ሆኖ ይገኛል፡፡ እንደዚህ ማንነቱን የገለፀባቸው ቃሎችም በ1608 ዮሐንስ ላቲኖ እንደሞተ በሳንታ አና ቤተክርስቲያን ባረፈው አፅሙ ላይ በተሠራው ሐውልት ተቀርጸው እንደነበር ጨምረን እንገነዘባለን፡፡ በታሪኩ ላይ እንደተገለፀው ዮሐንስ ላቲኖ በግሬናዳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ 60 ዓመት አስተምሯል፡፡ ከሬኔሳንስ ሂውማኒዝም ዕድገት እና ለውጥ ጋር በማጣጣምም በላቲን ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ይዞታ ላይ ጉልህ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በዚህ ረገድ ለከፍተኛ ትምህርት ተስማሚ የሆኑ የዘመኑን የሂዩማኒዝም የአስተሳሰብ አቅጣጫ የተከተሉ መጽሐፍትን ማበርከቱ ብቻ ሳይሆን ብቃት ያላቸውን ምሁራን አፍርቷል፡፡ ይህ አስተዋጽኦውም ማንነቱን ጨምሮ በሚገልጽበት ሁኔታ ከሀውልቱ ላይ በግጥም ተቀርጾ እንደነበር እነ ጌትስ (1998፡14) ጠቅሰው ትርጉሙን እንደሚከተለው አስፍረውታል፡፡

Scholar of Famous Granada and teacher of brilliant young students, Orator pious in speech, Outstanding in doctrine and morals, Offspring And son deep black with Ethiopian forebears, He learnt as an innocent Child the precepts that lead to salvation. He sang in the fair latin tongue the illustrious Austrian’s glories, under this pillar he lies; he will rise with his Wife well-beloved.

በመሆኑም እሱ በዚያ ዘመን ስለ ራሱ ማንነት ተናግሮት ጽፎት ያለፈውም ሆነ ሌሎች የፃፏቸው እንዲሁም በቀብሩ ሐውልት ላይ የሠፈረው ግጥም የሚያንፀባርቀው ኢትዮጵያዊነቱን ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡

የስፓኙ ንጉሥ ዳግማዊ ፍሊፕ በመካከለኛው ዘመን (Middle Ages) የተቋቋሙ ሕግጋትን በዘመኑ የለውጥ መንፈስ አስገዳጅነት ለማሻሻል ሙከራ ያደርግ ነበር፡፡ የሃይማኖት መሪዎችም እንደዚሁ አንዳንድ የቆዩ ደንቦችንና ሕጎችን አሻሽለው ለመታየት ፍላጎቱ ነበራቸው፡፡ ይህን ለማከናወን ደግሞ የሬናይሳንስን የለውጥ መንፈስ መረዳትና መተርጎም ያሻ ስለነበር ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ ለከፍተኛ ትምህርት ማስተማሪያ እንዲሆኑ ያዘጋጃቸውን መጻሕፍት ቤተ-መንግሥቱና ቤተ-ክርስትያኗ እንደ መርህ ምንጭ ተገልግለውባታል፡፡ የእርሱ ምክርና አስተያየትም በሰፊው ተጠቅመውበታል፡፡ በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያዊውን የዮሐንስ ላቲኖን ዕውቀት እንደ መቅረዝ ብርሃን የተጠቀሙበት የእስፓኝ መሪዎች ብቻ አልነበሩም፡፡ እነ ጌትስ ያቀረቡት ጥናት (1998) እንደሚያመለክተው እንደ ዶን ዮን  ያለ የአውሮፓ ጀግና (The Hero of the whole Europe) ተብሎ በታሪክ የሚጠቀሰው መሥፍን በፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ ምክር ተጠቅሟል፡፡ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖም ያገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም አይበገሬ “The invincible” ተብሎ በቅፅል ስም የሚጠቀሰውን የስፓኙን ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕን ከኢትዮጵያውያን ነገሥታት ጋር መልካም ግንኙነት እንዲፈጥር እና ቀሪውን የአፍሪካ ክፍል በክርስትና ሃይማኖት እንዲያጠምቀው ይገፋፋው እንደነበር ጸሐፍቱ ጠቁመዋል፡፡ ይልቁንም የአይበገሬው የዳግማዊ ፊልፕና የእርሱ ግንኙነትም አጋጣሚ የፈጠረው ሳይሆን በክርስቶስ ፈቃድ የመጣ መሆኑን ማመን እንዳለበት እንዲህ ሲል በቅኔ መግለፁን እነ ጌትስ ጨምረው አሥፍረታል (1998፡28)፡፡

“Philip meeting the Ethiopian teaches him Christ by the word of mouth, Christ sent the disciple to the Ethiopian by Heaven accidentally, Great Philip, Do not deny these just thing to the Ethiopian.”

ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው የዛሬ አራት መቶ ዓመት ገደማ በአውሮፓ (ስፓኝ) በግሬናዳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለ60 ዓመታት ያስተማረው ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ ታሪኩ ይህን ሲመስል፤ የቅኔ ሥራዎቹ እና ስለ ሥራዎቹ በዘመኑም ሆነ በዘመን ርቀት የቀረቡ አስተያየቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን እንደሚከተለው በአጭሩ በማመልከት እናጠቃልላለን፡፡

ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ ሦስት የግጥም መጻሕፍትን አሳትሟል፡፡ ከእነዚህ ሦስት የግጥም ሥራዎቹ መካከል አድናቆትን ያተረፈው በ1573 በላቲን ቋንቋ የታተመው ኦስትሪያድ የተባለው መጽሐፉ እንደሆነ ጸሐፍቱ ያትታሉ፡፡ ኦስትሪያድ በሁለት ተከታታይ ቅጾች የተዘጋጀ ሲሆን እያንዳንዳቸው 763 ገጾችን ይዘዋል፡፡ በአንድ ላይ 1526 ገጾችን በማጠቃለል አስትሪያድ 1538 ሎፔዝ ዴ ቶር “የኦስትሪያድ ጥናት” በሚል ርዕስ ያቀረበውን በመጥቀስ እነ ጌትስ (1998፡30) እንዳሠፈሩት፣

“Austrian… of the black Juan Latino, a professor of humanities in Granada is a rare and famous book, because it is, as it seems, the oldest printed literary work of an individual of the dark race and of Ethiopian descent. From this, principally, comes its celebrity… The black poet is patriarch of Africa.”

ሲል አድንቋል፡፡ ከላይ እንደምንረዳው ኦስትሪያድን ብርቅና ዝነኛ ካደረጉት ክብርንም ካጎናፀፉት ዓይነተኛ ምክንያቶች አንዱ እና ዋነኛው ጉዳይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ እና ከጥቁር ዘር አእምሮ የፈለቀ ጥንታዊ ሥራ የመሆኑ ገጽታ ነው፡፡ ሌላው አስትሪያድን “ምርጥ፣ ፈፅሞ ሊገኝ የማይችል ውድ የሙዚየም ዕቃ፣ እውናዊ የሥነ-ውበት እና የምናብ ብርሃን” በማለት በ1938 ዓ.ም አድናቆቱን የገለፀው ደግሞ ባላውሬዝ ቢሰፕራትሊን ነው፡፡ ማሪን ኦቼቴም ቢሆን “ተመጥኖና፣ ተለክቶ፣ ከማይዝግ፣ ከማይማርት፣ ብረት የተሠራ ጥበብ ነው” ማለቱ ሲጠቅስ፣ በ1908 ዓ.ም የታተመው ኢንሳይክሎፔዲያ ኤስፖዛም እንዲሁ “የሥነ-ጽሑፍ ኅያው ሐውልት ነው” በማለት የገለፀው ሠፍሮ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፔሬ ላሮስ በ1873 ባሳተመው ግራንድ ዲክሽኒያሬ ዩኒቨርሳል፡፡

‘Latino’s poetry is not only one of the rarest books in the world but also one of the most remarkable illustrations of the intellectual faculties and possible accomplishment of the African race.’

በማለት ማድነቁን እነ ጌትስ (1998፡43) ጠቅሰዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ ኤል ኤል ኢስኮሪያል (El Escorial) የተባለውንና ሁለተኛው የግጥም (ቅጽ) መድብል ያሳተመው በ1576 ዓ.ም ሲሆን በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊነቱን በሰፊው ማንጸባረቁን እንረዳለን፡፡ በቀብር ሐውልቱ ላይ የተቀረጹት ስንኞችም ከዚሁ መጽሐፍ የተጠቀሱ መሆናቸውን አጥኚዎቹ ጨምረው ያስገነዝባሉ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ በ1585 ‹የሴዛው መሥፍን› በሚል ርዕስ የሃዘን እንጉርጉሮ የሚደረድር የግጥም መጽሐፍ ማሳተሙ ተመልክቷል፡፡

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የሴዛው መሥፍን የልጅነት ጌታው ነው፡፡ የሴዛው መሥፍን ከሁሉ አስቀድሞ ተሰጥኦ እና ችሎታ ያለው መሆኑን ተረዳለት፣ የቤተሰቡንና የአከባቢውን አመለካከት የለወጠለት ዋነኛ አጋዢው ነበር፡፡ ይህ በአስደናቂዋ የምናብ ዓለም ጥቁር አሞራ በ‹ፊኒክስ› የመሰለው ጓደኛው እንደሞተ ዮሐንስ ላቲኖ እጅግ በጣም ይወዳት እና ትወደው የነበረች ዶና አና ቀጥላ ሞተችበት፡፡ ዶና አና የሴዛው መሥፍን አገር ገዢ የጌታ ካርሎባል ልጅ ስትሆን በውበት የታደለች እንደነበረችም ይነገርላታል፡፡ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ ይደነቅ የነበረው በቅኔና በቋንቋ ችሎታ ብቻ ሳይሆን የሙዚቃ ጥበብም ጨምሮ ስለነበር ውቢቱ ዶና አና በፍቅሩ ልትጠመድ መቻሏ ይነገራል፡፡ ዶና አና በጥቁር ፍቅር የመጠመዷ ሁኔታ ግን አባቷን ጌታ ካርሎባልን በእጅጉ ስላስከፋቸው በድርጊቱ ትቀጣ ዘንድ ፍርድ ቤት ከስሰው አቅርበዋት እንደነበር ጨምሮ ሥፍሮ ይገኛል፡፡ እንደሠፈረውም ለዶና አና ዮሐንስ ላቲኖ የነጮች ነጭ ነበር፡፡ በመሆኑም ሁዋን ለእርሷ ብርሃን እንጂ ጨላማ እንዳልሆነ ለፍርድቤት ከገለፀች በኋላ እንዲያውም ከእርሱ ጋር እንዳትገናኝ ከተከለከለች ሕይወቷን እንደተነጠቀች ተደርጎ መታየት እንዳለበት ማስረዳት በመቻሏ በመጨረሻ ልታገባውና አራት ልጆች ለመውለድ በቁ፡፡ ሆኖም አባቷ ጌታ ካርሎባል በዚህ ምክንያት በብስጭት ሰልስለው እንደሞቱ እንገነዘባለን፡፡ ጸሐፍቱ እንደሚሉት ዮሐንስ ላቲኖና ዶና አና በታሪክ ታላቅ የፍቅር ምሳሌዎች ሆነው ይጠቀሳሉ (ጌትስ እና ወልፍ፣ 1998፡18)፡፡ ዳሩ ግን ይወደው የነበረውን የሴዛው መሥፍንን ተከትላ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየች ሌላ ተጨማሪ ሀዘን ገጠመው፡፡ ይኸው ብርቱ ወዳጁ የአውሮፓ ጀግና ተብሎ በታሪክ የሚጠቀሰው የኦስትሪያው ዶን ዮን በዚያው ዓመት የሞተበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አንዱን ሃዘን ተወጥቶ ራሱን ለማጽናናት በማይችልበት ሁኔታ ሌላ ሃዘን እየተተካ በመምጣቱ ዮሐንስ ላቲኖ መራራውን ስሜት ተክዞ ሊገፋው አልቻለም፡፡ ስለዚህ የሃዘኑን ክብደት የሴዛው መሥፍን በሚል ሚሾ እና የእንጉርጉሮ ግጥም ደርድሮ እንዳሳተመ ዓይኑ ታወረ፡፡ ቢሆንም ማስተማሩን ቀጥሎ እንደነበር እንረዳለን፡፡

እነ ጌትስ ብዙዎቹን ጠቅሰው እንዳሠፈሩት ባለ ቅኔው ፕሮፌሰር ራሱን ለሰዎች ያስተዋውቅ የነበረው “ማጅስተር ዮን ላቲኖ” በማለት ነበር፡፡ ፌርማውንም ማጁስተር ላቲኖ በሚል ያስቀምጥ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የቅኔ ሥራዎቹን በሚመለከት የተለያዩ ሃያሲያን ከቅርፆቻቸው እና ከቋንቋ አጠቃቀማቸው አኳያ በመመርመር “ቨርጂላዊ ባለ ቅኔ” በማለት አድናቆታቸውን እንደገለፁ እንገነዘባለን፡፡ ከሃያሲያን መካከልም ስፕራትሊን አንዱ አድናቂው ነበር፡፡ በእነ ጌትስ (1998፡25) እንደጠተጠቀሰውም፤

“Latino seems to have attempted to achieve an application of linguistics elements in every way similar to that of the ancient.”

ማለቱ ተመልክቷል፡፡ ግጥሞቹም ሆኑ የምርምር ሥራዎቹ ሁሉ የሬኔሳንስ ሂዩማኒዝም የለውጥ አስተሳሰብ ያስገኛቸው እና አዳዲስ ፅንስ ሃሳቦች አንድምታ ትርጓሜ እና ትንታኔ በመስጠት ጥልቀት እና ስፋት ያላቸው ሆነው በጥንታዊ ትውፊቶች፣ በፍልስፍና እና በታሪክ፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በግሪኮ-ሮማን ሚቶሎጂ ደንብ እና ሥርዓት ላይ ተመርኩዞ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር በመዋሀድ መቅረባቸውን እንረዳለን፡፡

ባለ ቅኔው ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ በሥራዎቹ ውስጥ ኢትዮጵያንና ማንነቱን በመግለጽ የእትብቱን መቀበሪያ ብቻ ሳይሆን የእምነቱንም ትስስር ጨምሮ መዘከሩ ሠፍሮ እናገኛለን፡፡ ኢትዮጵያዊው ባለ ቅኔ ዮሐንስ ላቲኖ የዘመናት አድማስ ጥሶ የሰውን ልጅ ዕውቀት እና ታሪክ አጣቅሶ በማዋሀድ በቅኔ ጥበብ ለሰው ልጅ በማበርከት እንዲሁም የምዕራቡ ዓለም ባህል በምዕራቡ ዓለም ጥንታዊ ቋንቋ የምዕራቡን ዓለም ሰዎች በማስተማር እና ይልቁንም የላቲን ቋንቋ ሥርዓት እና ሕግጋት በመተንተን ከዘመኑ የለውጥ መንፈስ እና ግስጋሴ አኳያ ውስብስብነት የነበራቸውን አዳዲስ መርሆዎች በመንደፍ ብቻ አልነበረም አስተዋጽኦው የተወሰነው፡፡ ባሕርይው፣ ስብዕናው፣ ሥነ-ምግባሩ፣ ችሎታው እና ተሰጥኦው ሁሉ የብዙዎችን ገጣሚዎችና ጸሐፌ-ተውኔት ቀልብና ትኩረት ስቧል፡፡

ዮሐንስ ላቲኖ ቀለሙ ጥቁር አስተሳሰቡ ግን ነጭ ወይም ጥቁር የሚባል አልነበረም- ሁለንተናዊ ሰው እንጂ! በዕውቀት ደረጃው “ማጅስተር ዮን ላቲኖ” ብሎ እንደሚኮራበት ሁሉ በኢትዮጵያዊነቱ እና በቀለሙ ይኮራበት እንደነበረና ራሱን ዝቅ አድርጎ አይቶ እንደማያውቅ ተደጋግሞ ተነግሮለታል፡፡ ይህ ሊፈረካከስ ያልቻለ ባሕርይው እና ስብዕናው፣ ዕምነቱ እና አስተሳሰቡ ይልቁንም የነበረበት ዓለም በጥቁሮች ላይ ይዞት የቆየውን አመለካከት እና አስተያየት አዙሮ ራሱን እንዲጠይቅ ፈትኖት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ዮሐንስ ላቲኖ ከንቀት አመለካከት የመነጩ እንቅፋቶችን በንቀት መወጣት ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ንቀት በአክብሮት እንዲተካ አድርጓል፡፡ አስገድዷልም፡፡ ሂደቱ አሳዛኝም አስገራሚም ሊሆን እንደመቻሉ መጠን በዘመኑ የነበሩ ተውኔት ጸሐፊዎችን ምናብ በማነሳሳት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዮሐንስ ላቲኖ በሚሉ ርዕሶች ሦስት ተውኔቶች ካቀረቡ ጸሐፍት መካከልም ኤክዚሜኔዝ ዴ ኢንሶዞ፣ ሎፔዝ ዴ ኢንሲዞ፣ እንዲሁም ሰርባይል ይገኝበታል (ጌትስ እና ወልፍ፣ 1998፡40-50)፡፡

በአጠቃላይ ባለ ቅኔው ፕሮፌሰር ታሪኩ ያልተቃኘ፤ በኢትዮጵያዊያን ዘንድም ከአራት መቶ ዓመታት በላይ ሳይታወቅ የኖረ በላቲን ቋንቋ ሦስት አስደናቂ የግጥም መጻሕፍትን በማሳተም በአውሮፓ፣ በሬኔሳንስ ዘመን፣ ግንባር ቀደም ወይም ፋና ወጊ የሆነ አፍሪካዊ ኢትዮጵያዊ ነው ማጅስተር ዮሐንስ ላቲኖ፡፡ ጌትስና ወልፍ (1998፡32) “በሬኔሳንስ ሂዩማኒዝም እና በአውሮፓ አፍሪካዊያን ታሪክ ውስጥ በተመራማሪነቱ የታወቀ፣ ተሰጥኦ የታደለው፣ የሥነ-ጽሑፍ እና የአካዳሚያ ሊቅ የነበረ ነው” ሲሉት ሰርባንቴስም በ1605 ዓ.ም “ሁዋን ላቲኖ የሚለው ስም የሬኔሳንስ ሂዩማኒዝም ባህል ሌላ ተለዋጭ ስም፣  “Juan Latino a metaphor for traditional Renaissance Humanism.”

ብሎ እንደገለጸው አሥፍረውታል (ገጽ 33)፡፡ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ በ1608 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየም ቤርሙድስ ይ ፔድራዛ “የሴዛው መሥፍን ሞገስ፣ የበጎ ሰዎች መምህር፣ የኢትዮጵያ ክብር” በማለት ሲያወሳው አንቶኒዮ ጎንሳሌስ ጋርቢስ ደግሞ በ1886 ዓ.ም “ኤል ኔግሮ ዮሐንስ ላቲኖ” በሚል ሥራው ውስጥ “የእኛው ገጣሚ ዮሐንስ ላቲኖ ዝነኛው አፍሪካዊ ፍፁም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ኢትዮጵያዊ (incomparable Ethiopian)” ማለቱን እንረዳለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በ1908 የታተመው ኢንሳይክሎፔዲያ ኤስፓዛ “ለ60 ዓመታት ያህል በግሬናዳ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምር የግሬናዳ ጸሐፍትን አጥብቆ ከተጠናወታቸው ከትርጉምና ከቅጅ ሥራ አላቆ ወርቃማውን የስፓኝ የሥነ-ጽሑፍ ዘመን ያመጣ፣ የመሠረተ፣ ኅያው የጥበብ ኃውልት” በማለት ሲገልፀው፣ በ1860 በታተመውና ባዮግራፊ ሁኒቨርዛል ዴ ዜም ሆሜስ ኪ. ሲ. ሶንት ፌት ኧንኖም በተባለው ኢንሳይክሎፔዲያ ውስጥ በምናባዊ የፈጠራ ዓለም ውስጥ የአፍሪካን ችሎታና ዕውቀት ያስመሰከረ ዝነኛ ኢትዮጵያዊ ነው ካለ በኋላ፣

“His reputation was extraordinary and all the curious people flocked to see a Black. Shine in his knowledge of the finest minds of Europeans, and teach them to the European themselves.”

ማለቱ እነሆ ተብራርቶ ተገልጾ ይገኛል (ጌትስና ወልፍ 1998፡41)፡፡ በመጨረሻም በ1908 ዓ.ም የታተመው ኢንሳይክሎፔዲያ ኡኒቨርዛሎ ኡሉስትራዳ ኤሮፒዮ አሜሪካኖ ያሠፈረውን መሠረት አድርገው እነ ጌትስ (1998) እንደፃፉት ኢትዮጵያዊው ባለ ቅኔ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖ በአውሮፓ ከዛሬ አራት መቶ ዓመት በፊት በአድናቆት ማዕበል ተጥለቅልቆ ቢሞትም እንኳን ሥራዎቹና ታሪኩ ግን እስከ ዛሬ ተረስተው፣ ተዘንግተው አሊያም ተደብቀው ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም፤ በተለይም የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የሥነ-ጽሑፍና የቋንቋ ምሁራንን ሰፊ ትጋት፣ ጥናትና ምርምር ይጋብዛል፡፡ በተዛማጅም በተጓዳኝም እሱንም ፕሮፌሰር ዮሐንስ ላቲኖን እና የመሳሰሉትን በየዘመኑ ድንቅ ሥራ ያበረከቱ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አጠቃላይ ቅኝት ማድረግ አስፈላጊ እንደሚሆን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top