ጥበብ በታሪክ ገፅ

ትዝታ ዘመንግሥቱ ለማ በሀገረ እንግልጣር (ሪቻርድ ፓንክረስት እንደፃፈው)

ትዝታ ዘመንግሥቱ ለማ በሀገረ እንግልጣር

(ሪቻርድ ፓንክረስት እንደፃፈው)

ታላቁ ባለቅኔ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ተመራማሪ፣ መምህር፣ የተባ አንደበት እና የሰላ አዕምሮን የታደለው መንግሥቱ ለማ ኢትዮጵያ ከፋሽስት ጣሊያን አገዛዝ ነፃ ከወጣች ከ1941 ዓ.ም. (እኤአ) ወዲህ ባሉት ዓመታት፤ ለትምህርት ወደ ውጪ ሐገር ከተጓዙት በርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በ1940ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ለንደን የደረሰው መንግስቱ፤ ለ40 ዓመታት የዘለቀ ጓደኝነት ከመሰርትንበት ‹‹ለንደን ስኩል ኦቭ ኢኮኖሚክስ›› (LSE) ገብቶ ለመማር መሰናዶ ከሚያደርግበት ‹‹ሪጀንት ስትሪት ፖሊቴክኒክ›› ተመዘገበ፡፡

መንግስቱ ለማ በለንደን ቆይታው የግድ ሊያነባቸው የሚገቡ የትምህርት መጻሕፍትን ብቻ ሳይሆን፤ በፖለቲካ ሳይንስ እና በሥነ ጽሑፍ ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን በሰፊው ያነብ ነበር፡፡ የታወቁ ማርክሳዊ መጻሕፍትን ጠልቆ ማንበብ ያዘ፡፡ ትዝ እንደሚለኝ፤ የአስተያየት ሐተታዎችን እየጻፈ፤ የሌኒንን ‹‹መንግሥት እና አብዮት›› (State and Revolution) እንዲሁም ‹‹ኢምፔሪያሊዝም፡ የካፒታሊዝም ከፍተኛ ደረጃ›› (Imperialism the Highest Stage of Capitalism) ያጠና ነበር፡፡

በተጨማሪም መንግሥቱ፤  እንደ ጎጎል፣ ደስቶየቭስኪ፣ ቶልስቶይ፣ ቼሆቭ፣ ጎርኪ እና ሌሎች  ታዋቂ የሩሲያ የልቦለድ እና የተውኔት ጸሐፊዎችን ሥራ በጋለ ፍቅር ያነብ ነበር፡፡ እነዚህ ደራሲዎች በሥራዎቻቸው በሚገልፁት ጥንታዊ የሩሲያ ማኅበረሰብ እና በእርሱ ዘመን በነበረው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ መካከል ሰፊ ተመሳሳይነት መኖሩን ተገንዝቦ ነበር፡፡ በኋላም ሶቪዬት ኅብረትን ጎብኝቷል፡፡ አዘውትሮ የ19ኛው እና የ20ኛው ክፍለ ዘመን የሩሲያ ሥነ ጽሑፎች ወደ አገርኛ ቋንቋ መተርጎም አስፈላጊ መሆኑን ይናገርም ነበር፡፡

እንዲሁም ይሰነዝሩት በነበረው ማኅበራዊ ሂስ ከፍተኛ ግምት ይሰጣቸው የነበሩትን ሁሉንም የጆርጅ በርናርድ ሾው ተውኔቶችን እና ጄ.ቢ.ፕሪስትሌይ የተውኔቶችን በጉጉት ያነብ ነበር፡፡ ቆይቶም ከፕሪስትሌይ ሥራዎች አንዱን ወደ አማርኛ ተርጉሟል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው የብሪትሽ ካውንስልም፤ እንደ ‹‹የበጋ ሌሊት ህልም›› (Midsummer Nights Dream) ያሉ የሼክስፔር ሥራዎችን የሚተውኑ ተዋንያንን በመጋበዝ ድራማ ለህዝብ እንዲያቀርቡ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት በተጨማሪ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከ19ኛው እና ከ20ኛው ክፍለ ዘመን የእንግሊዝ ድራማ ጋር እንዲተዋወቅ ማድረግ አለበት የሚል አስተያየትም ዘወትር ያቀርብ ነበር፡፡

ተማሪ በነበርንበት ወቅት መንግሥቱ የኢትዮጵያን ባህል ፋይዳ በጥልቅ በመገንዘብ ረገድ ባለው ግንዛቤ ሁላችንንም ያስደንቀን ነበር፡፡ እንግሊዝ በቆየባቸው ጊዜያት ከእናቴ ከሲልቪያ ፓንክረስት ጋር ወዳጅነት ፈጥሮ፤ በወቅቱ የምዕራቡ ዓለም በደንብ የማያውቀን የኢትዮጵያ የቤተክርስቲያን ትውፊታዊ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴን ለእናቴ ይነግራት ነበር፡፡ በተለይም እርሱ እራሱ ቅኔን (ግዕዝን) ስለተማረባቸው ትምህርት ቤቶች ልዩ መረጃ እና የረቀቀ ዕውቀት ነበረው፡፡ እናቴም  ከሚነግራት ነገር ሰፊ ማስታወሻ በመያዝ፤ ‹‹የኢትዮጵያን ባህላዊ ታሪክ›› (Ethiopian Cultural History) በሚል ርዕስ ባሳተመችው መጽሐፍ ስለእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚገልጽ አንድ ምዕራፍ አካታላች፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ምዕራፍ የመንግሥቱ ለማ የመጀመሪያ የታተመ ሥራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው፤ በተጠቀሰው የእናቴ መጽሐፍ ውስጥ ከበርካታ የመንግሥቱ ለማ የስዕል ሥራዎች አንዱ ቅጂ ታትሞ ወጥቷል፡፡ መንግሥቱ ለማ በወጣትነት ዘመኑ የሰዓሊነት እና የገጣሚነት ክህሎትን ያሳይ እንደነበር መዘንጋት አይገባም፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንግሥቱ ለማ የኢትዮጵያን ባህል የመጠበቅ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ትልቅ ስሜት ያንፀባርቅ ነበር፡፡ ከአዛውንቱ ካህን ከአባቱ ካለቃ ለማ ኃይሉ ጋር ለበርካታ ወራት ያደረገውን ቃለ ምልልስ በቴፕ ሲመዘግብ እና በመጽሐፍ መልክ ለማተም የአርትኦት ሲሰራ ቆይቶ የተወሰነውን የትዝታቸውን ክፍል አሳትሞታል፡፡ እንዲሁም ቅኔዎችን መዝግቦ፤ ባህላዊውን የኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ አንድምታ የተመለከተ ሐሳብም አካቶበታል፡፡ ለመንግሥቱ ራዕይ እና ተነሳሽነት ምስጋና ይግባውና፤ እኔ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር በነበርኩ ጊዜ፤ በተቋሙ እየተባዛ በሚቀርብ እና ‹‹የቅኔ ስብስቦች›› የሚል ርዕስ በሰጠነው ‹‹መጽሔት›› በርካታ ግጥሞችን አሳትመናል፡፡ ይህ ሥራ መነሻ ሆኖ መንግሥቱ ከአብዮቱ በኋላ በኢትዮጵያ የባህል ሚኒስቴር እገዛ እጅግ በርካታ የቅኔ ስብስቦች የተካተቱበት ሥራ ሰርቷል፡፡

መንግሥቱ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ከማውቃቸው ሰዎች የላቀ የተባ ህሊና እና ርቱዕ አንደበት ያለው ማለፊያ ተራኪ ነው፡፡ መንግሥቱ ይህን ክህሎቱን ያገኘው፤ (ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ 1888 እስከ 1893 ዓ.ም. በተከሰተው ታላቁ የኢትዮጵያ ረሀብን በተመለከተ ላደረግኩት ጥናት ቃለ ምልልስ ከሰጡኝ) ከአባቱ ከአለቃ ለማ ነው፡፡ አለቃ ለማ ከነገሩኝ ታሪኮች አንዳንዶቹን፤ የ30 ዓመታት ዕድሜ በነበረው የጓደኝነት ዘመናችን ደጋግሞ ሲተርክልኝ የነበሩ ናቸው፡፡ ታሪኮችን ደጋግሞ ቢናገራቸውም፤ ሁል ጊዜም የአዲስነት ለዛ የማያጡ ናቸው፡፡ ደግሞ ሲነግረኝ፤ ቀድሞ ከተናገራቸው ለየት ባሉ ቃላት፤ ትንሽ ለየት ባለ ፈገግታ፤ ለየት ባለ የተኮሳተረ ገጽታ፤ ለየት ባለ የዐይን አገላለጽ እያጀበ ትኩስነት ለዛ እንዲያገኙ ያደርግ ነበር፡፡

ከእነዚህ ታሪኮች አንደኛው ጥርሱን ለመታከም ለንደን ከሚገኝ አንድ ሐኪም ዘንድ በሄደ ጊዜ የገጠመው ነው፡፡ መንግሥቱ ሐኪሙ ዘንድ የሄደው፤ የሮማ ጳጳስ ስለድንግል ማሪያም ዕርገት አዲስ ዶግማ ይፋ ያደረጉበት ወቅት ነበር፡፡ መንግሥቱ የሄደበት ሐኪም ደግሞ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበር፡፡ መንግሥቱ ከካቶሊኩ የጥርስ ሐኪም ወንበር ተቀምጧል፡፡ ሐኪሙ ጥርስ መንቀያውን ከመንግሥቱ አፍ እንደከተተ በዚያ የጭንቅ ሰዓት እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ ‹‹የማርያምን ዕርገት ታምናለህ ወይስ?›› መንግሥቱ ጥርስ መንቀያውን ከአፉ እንደከተተ ጥያቄ ያቀረበለትን ሐኪም ላለማስደንገጥ እና ላለማበሳጨት እጀግ ተጠንቅቆ፤ አፍታ ሳይወስድ ጥያቄውን በአወንታ መለሰለት፡፡

ከዚህ ሌላ መንግሥቱ እዛው ለንደን ‹‹ኤፕሶም›› በተባለ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ለበርካታ ወራት ህክምና ሲከታተል በነበረ ወቅት የገጠመው ነገር ነበር፡፡ መንግሥቱ ስለኢትዮጵያ አንዳች ዕውቀት የሌላቸው እና አዘውትረው ‹‹የሐገርህ ልጆች እንደ ዝንጀሮ በዛፍ ላይ ነው የሚኖሩት?›› የሚል የጅል ጥያቄ ይጠይቁት የነበሩትን ነርሶች በጣም ያዝናናቸው ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ሊያላግጥባቸው ፈልጎ እንዲሁ የፈጠራ ወሬ እየቀመረ ያጫውታቸዋል፡፡ መንግሥቱ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ነው፡፡ በወቅቱም ሚስት አላገባም ነበር፡፡ ሆኖም ከዕለታት አንድ ቀን ለገራገሮቹ አድማጮቹ (ነርሶች) ከአራት የማያንሱ ሚስቶች እንዳሉት ነገራቸው፡፡ ይህን ታሪክ ነግሯቸው ብዙም ሳይቆይ፤ እንዳጋጣሚ በእንግሊዝ ይማሩ የነበሩ አራት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሊጠይቁት ይመጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከነርሶቹ አንዷ መንግሥቱ ወደ ተኛበት ዋርድ ስትጣደፍ ሄዳ በአድናቆት ስሜት እንደ ተዋጠች ‹‹አቶ መንግሥቱ… አቶ መንግሥቱ›! ሚስቶችህ መጡ! ቅድሚያ እንድታይህ የምትፈልገው የትኛዋን ነው?›› አለችው፡፡ አራቱ ጠያቂዎቹ እነማን እንደሆኑ የማያውቀው መንግሥቱ ምንም ሳይደናገር በቅጽበት ‹‹ቁጥር አንድን ግቢ በያት›› ሲል መለሰላት፡፡

ከብዙ ጉዳዮች አንጻር መንግሥቱ በለንደን የነበረው ቆይታ በህይወቱ ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ እንደሚታወቀው፤ በእንግሊዝ ይማሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዓመት ውስጥ በተደጋጋሚ (በተለይም በገና እና በፋሲካ የዕረፍት ወቅት) ትምህርት ቤት ሲዘጋ ስብሰባ ያካሄዱ ነበር፡፡ እኔም ከእነሱ ጋር እቀላቀላለሁ፡፡ ከእነዚህ ስብሰባዎች በአንዱ መንግሥቱ አጭር ቲያትር እንዲያዘጋጅ ጥያቄ ቀረበለት፡፡ እኔ የመንግሥቱ ታላቅ የቲያትር ጥበብ ክህሎት ሊዳብር የቻለው ከዚያች የመጀመሪያ የፈጠራ ጽሑፍ ዝግጅት መሆኑን አምናለሁ፡፡  

መንግሥቱ ሁልጊዜም እንከን አልባ ሆኖ መታየት የሚፈልግ ሰው በመሆኑ፤ ሥራዎቹ የህትመት ብርሃን ከማየታቸው አስቀድሞ ደግሞ ደጋግሞ ለማሻሻል ይሞክራል፡፡ ወደ በኋላ አንዳንድ የድርሰት ሥራዎቹን ረቂቅ ያሳየኝ ነበር፡፡ እናም የድርሰት ሥራውን ለእኔ ካሳየኝ በኋላ ደጋግሞ ያሻሽለዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የተውኔቱን ገቢር ቁጥር ይቀንሰዋል ወይም ይጨምረዋል፡፡ መንግሥቱ ሥራዎቹን ደጋግሞ እንደሚያሻሽል እና እንደሚያስተካክል በቀላሉ መረዳት የምችለው በገፁ ላይ በሚታየው የእስክሪቢቶ ቀለማት ነው፡፡ መንግሥቱ ሥራውን ዳግም ሲያሻሽል ቀድሞ ከተጠቀመበት ብዕር የተለየ ቀለም ያለው ብዕር ስለሚጠቀም ሥራው በምን ዓይነት የአርትኦት ሂደት እንዳለፈ በግልጽ ለመረዳት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ በአጽንዖት ሊነገር የሚገባው፤ መንግሥቱ የቲያትር ሙያን በተመለከተ አንዳችም አማተራዊ የነገር አያያዝ ያልነበረው መሆኑ ነው፡፡ እኔ ከኢትዮጵያ ወደ እንግሊዝ በሄድኩ ቁጥር ለንደን ከሚገኙት የመጻሕፍት መሸጫ መደብሮች ጎራ ብዬ በድራማ አዘገጃጀት ላይ ያተኮሩ አዳዲስ ሥራዎች መውጣታቸውን፤ እንዲሁም ለህትመት የበቁ አዳዲስ የአውሮፓ የተውኔት ድርሰቶች መኖራቸውን እንዳይለት ይጠይቀኝ ነበር፡፡ መንግስቱ በቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት (በአጠቃላይ በቢቢሲ) ይቀርቡ የነበሩ የራዲዮ ተውኔቶችን በከፍተኛ ጉጉት ይከታተል ነበር፡፡ ሆኖም በቢቢሲ የሚተላለፉት የራዲዮ ተውኔቶች ከፖለቲካ ዝንባሌ የተጠበቁ እንዳልሆኑ አሳምሮ ያውቅ ነበር፡፡ እናም የቀዝቃዛውን ጦርነት ዘመን በማስታወስ፤ በዓይኑ ጠቀስ እያደረገኝ ሌላው ቀርቶ በቢቢሲ የአየር ትንበያ ዝግጅት ጭምር ‹‹ከምሥራቅ አውሮፓ ይነፍስ የነበረው ቀዝቃዛ ንፋስ…›› የሚል አገላለጽ ይሰማ እንደነበር ደጋግሞ አጫውቶኛል፡፡

በሌላ በኩል መንግስቱ በለንደን ያሳለፈው ጊዜ፤ ለፈጠራ ሥራ የሚያነሳሳ የባህል ግጭትን በመፍጠር በኩል እገዛ ያደረገለት ይመስለኛል፡፡ እነዚህም የባህል ግጭቶች፤ በበለጠ ከግል ህይወቱ ጋር በተዛመዱት፤ የህይወት ታሪኩን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በሚያጣቅሱት እና አውሮፓ ደርሰው በሚመጡ ኢትዮጵያውያን ላይ ትኩረት በሚያደርጉት የመጀመሪያ የድርሰት ሥራዎች የተንፀባረቀ ጉዳይ ነው፡፡  ከአንዳንድ ጉዳዮች አንጻር፤ (በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የእርሱ ተማሪዎች ተዋናይነት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ እየታየ ባለው) ‹‹አላቻ ጋብቻ›› በተሰኘው ድርሰቱ ውስጥ የሚገኘው ባህሩ የተሰኘ ገፀ-ባህርይ መንግስቱ አምሳያ ነው፡፡

በለንደን ያሳለፈው እና ከሀገር ቤቱ ጋር ተቃርኖ ያለው ህይወቱ መንግስቱ በርካታ ልምዶችን ለማግኘት ያስቻለው ህይወት ነው፡፡ ለምሣሌ የንጉስ ጆርጅ አራተኛን ዜና ዕረፍት የሰማነው በ‹‹ለንደን ስኩል ኦቭ ኢኮኖሚክስ›› በነበርንበት ወቅት ነው፡፡ መንግስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ልምድ መሠረት አድርጎ፤ በንጉሡ ሞት ምክንያት፤ ምናልባት ለአንድ ሣምንት ያህል ሁሉም ነገር ዝግ ይሆናል የሚል ግምት ነበረው፡፡ ሆኖም ከእኔ ጋር ወደ መማሪያ ህንፃችን ከሚያስገባው በር እንደቆምን፤ መደበኛው ትምህርታችን አለመቋረጡን እና ዩኒቨርስቲአችን ‹‹ለንደን ስኩል ኦቭ ኢኮኖሚክስ›› ምንም እንዳልተፈጠረ ዘወትራዊ ተግባሩን ሲቀጥል በመመልከቱ በእጅጉ ተገረመ፡፡

አንድ ጊዜ ታዋቂው ፈላስፋ በርትራንድ ረስል፤ በእኛ ትምህርት ቤት በ‹‹ለንደን ስኩል ኦቭ ኢኮኖሚክስ›› ተገኝቶ፤ በባላንጣነት በሚተያዩት በምዕራቡ እና በምሥራቁ ዓለም መካከል ተደጋግፎ የመኖርን ጥቅም እና የሰላምን አስፈላጊነት የሚያስረዳ ሐሳብ ማቅረቡን አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ ዕለት አብዛኞቹ የት/ቤት ጓደኞቻችን በረስል ሐሳብ ተስማምተው ነበር፡፡ መንግስቱም፤ ሲቆይ ዘንግቸው ካልሆነ፤ በግቢያችን ባለው ‹‹የረስል አደባባይ›› አጠገብ፤ በሁዳዱ ላይ በተዘጋጀ አንድ ታላቅ የሙዚቃ ድግስ በመገኘት ተመሳሳይ ጥሪ ካስተላለፈው ከዝነኛው ጥቁር አሜሪካዊ ዘፋኝ ከፖል ሮብሰን ሐሳብ ጋር የተጣጣመ አቋም ነበረው፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለፀው፤ በ‹‹ለንደን ስኩል ኦቭ ኢኮኖሚክስ›› በተዘጋጀው መድረክ ተገኝቶ ንግግር ያደረው ታዋቂው ፈላስፋ በርትራንድ ረስል የጠቀሰው ‹‹የአብሮ መኖር›› ሐሳብ እንዲሳካ፤ ሁለቱ ኃያላን ሐገራት አንዱ በሌላኛው የተጽዕኖ ክበብ ውስጥ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ እንዳለባቸው ገልፆ ነበር፡፡ ሶቪየት ህብረት በምሥራቅ፤ እንዲሁም የምዕራብ ኃያላን በአፍሪካ እና በሰፊው እስያ ያለ ተቀናቃኝ መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል የሚል ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህ የረስል ገለፃ እንደ ተጠናቀቀ ከሁሉ ቀድሞ ከመቀመጫው የተነሳው ወጣቱ መንግስቱ ለማ ነበር፡፡ እናም በአዳራሹ ወደ ኋላ አካባቢ የተቀመጠው መንግስቱ፤ በፍፁም አፍሪካዊ መንፈስ፤ የአፍሪካ ህዝቦች ነፃነታቸውን እንደሚፈልጉ አስታወቀ፡፡ (መንግስቱ ይህን የተናገረው፤ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ቀንብር ነፃ መውጣት ከመጀመራቸው ከብዙ ዓመታት በፊት መሆኑ ልብ መባል አለበት፡፡) ታላቁ ፈላስፋ ሓሳቡን ይውደደው ይጥላው ሳያስጨንቀው፤ መንግስቱ ንግግሩን በመቀጠል አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ከዚያ በላይ ለመቆየት ዝግጁ አለመሆናቸውን ተናገረ፡፡

ዛሬ ከኢትዮጵያ ጎምቱ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች አንዱ አድርገን በታላቅ አክብት የምንመለከተው መንግስቱ በወጣትነት ዘመኑ ሥር ነቀል ለውጥ ፈላጊ ከሆኑ ተማሪዎች ግንባር ቀደሙ ነበር፡፡ በለንደን ቆይታውም በኢትዮጵያ የተማሪዎች ማህበር ወሳኝ ሚና ሲጫወት የነበረና ወግ አጥባቂ – መሳፍንታዊ ባህርይ ጎልቶ የሚታይባቸውን እና ማህበራዊ ንቃታቸው ደካማ የሆኑ ወጣት የሐገሩ ልጆችን የትምክህት እና የግብዝነት ባህርይ ይገዳደር የነበረ ሰው ነው፡፡ በእንግሊዝ ይማሩ የነበሩት የሃገሩ ልጆች ከሁሉ የላቀ ፋይዳ ላለው የሃገራቸው የማህበራዊ ልማት ጥያቄ ትልቅ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ ያቀርብ ነበር፡፡

የሃገሩን ልጆች ለዚህ ዓላማ ለማነሳሳትም ‹‹ኢትዮጲስ›› በሚል የብዕር ሥም ጽሁፎችን ያቀርብ እንደ ነበር ዛሬ በይፋ መግለጽ ይቻላል፡፡ ምናልባት ሁለት ወይም ሦስት ከሚሆኑ የቅርብ ጓደኞቹ በቀር ለብዙዎች ምስጢር ሆኖ የቆየውን ይህን የብዕር ሥሙን በመጠቀም፤ በእንግሊዝ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ያሳትሙት ለነበረው ‹‹ላየን ከብ›› (የአንበሳ ደቦል) ለተሰኘ ጆርናል ‹‹ምርጡ የሐሳብ ሥርዓት›› (The Best system of Ideas) በሚል ርዕስ አንድ አስደናቂ መጣጥፍ ጽፎ ነበር፡፡ ይህ በ1952 ዓ.ም (እኤአ) የፀደይ ወራት የታተመው መጣጥፍ ዘመን አይሽሬ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ከሞላ ጎደል ዛሬም [ከ37] ዓመታት በፊት የነበረው ድምቀት ሳይደበዝዝ ዘልቋል፡፡ ኢትዮጲስ (ማለትም መንግስቱ) ለመጣጥፉ በሰጠው ርዕስ ሊገልጽ የፈለገውን ሐሳብ ለአንባቢያን ሲያብራራ፤ ‹‹አብዛኞቹ ሰዎች፤ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ አንድ ዓይነት ‹የሐሳብ ስርዓት› አላቸው፡፡ በቃላት ሊገልፁት፣ ሥነ አመክንዮን በተከተለ አግባብ ሊያብራሩት የሚችሉት ሆነ -አልሆነ፤ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ‹የሐሳብ ሥርዓት አላቸው›› በማለት ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም፤ ‹‹ሐሳቦች የሚቀመሩት በልምድ እና ያ ልምድ በሚተረጎምበት ይትብሃል እንዲሁም በልምዱ ላይ ሌሎች በሚደርስበት ተጽእኖ ነው›› በማለት ያክላል፡፡

ከዚህ አያይዞም አንድ ጥያቄ ያነሳል፡፡ ‹‹ታዲያ እነዚያ ምርጥ ሐሳቦች፤ ምርጥ ሐሳብ የሚሆኑት ለማን ነው?›› የሚል ጥያቄ በማንሳት፤ ‹‹በአንድ ቦታ እና በአንድ ዘመን ምርጥ የነበሩ ሐሳቦች፤ በሌላ ዘመን እና በሌላ ቦታ ምርጥ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ወይም በአንድ ዘመን ምርጥ የሆኑ ሐሳቦች፤ የወደፊቱ ጊዜ በሚያመጣው አዲስ የዕውቀት ብርሃን እና በአዳዲስ ሁኔታዎች ውስጥ ሲታዩ በዚያው ምርጥ በተባሉበት ቦታ ምርጥ ሆነው ላይታዩ ይችላሉ›› በማለት ክርክር ያቀርባል፡፡

መንግስቱ ያነሳውን ጭብጥ በአጽንዖት ሲገልጽ፤ ‹‹ምርጥ የሐሳብ ስርዓት››ን በተመለከተ ያነሳውን ጥያቄ ለመመለስ ያደረገው ጥረት፤ መጀመሪያ ካነሳው ጥያቄ ጋር የቅርብ ዝምድና ወዳለው ሌላ ሁለተኛ ጥያቄ፤ ‹‹የተልዕኳችን ባህርይ ምንድነው?›› ማለትም በእንግሊዝ የሚገኙ ተማሪዎች ተልዕኮ ምንድነው ከሚል ጥያቄ  እንዳደረሰው ይገልጻል፡፡

እናም ስለ ተማሪዎቹ ሚና ሲያትት፤  

‹‹እኛ ሁላችን እዚህ የተገኘነው አንድ ተልዕኮን ለማሳካት ነው፡፡ ያን ተልዕኮም ሁላችንም አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ ወደ ሐገር ቤት ስንመለስም ‹ሐዋርያት እንደምንሆን› (በሐይማኖታዊ ትርጉም አይደለም) እናውቃለን፡፡ አንድ ነገር ይዛችሁ ኑ ተብለን ወደ እዚህ ሐገር ስንመጣ፤ የላኩን ሰዎች የሚፈልጉትን እና እነሱ ባይሉትም በጣም አስፈላጊ የሆነን አንድ ነገር ይዘን ወደ ሐገር ቤት ለመመለስ ነው፡፡ ግን ያ አንድ ነገር ምንድነው? ለመሆኑ ‹ነገር› ተብሎ ሊጠራ የሚችልስ ነው ወይ? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ፤ ይህ መጣጥፍ ለሚያነሳው ጥያቄ መፍቻ ቁልፍ ሊሆን ይገባል፡፡

‹‹በርግጠኝት ሁላችንም ‹ያ ነገር› ምን እንደሆነ እናውቀዋለን ብለን እናስባለን፡፡ አንዳንዶቻችን የህክምና ሳይንስን፣ ሌሎቻችን የምጣኔ ሐብት ሳይንስን፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ የምህንድስና ሳይንስን እና ህግን ይዘናል፡፡ አንዳንዶች የነርስነት ሙያን፤ አንዳንዶች ማህበራዊ ሳይንስን ወዘተ እያጠናን ነው፡፡ ሁላችን ይህን ስናደርግ ሐገራችን የሰለጠኑ ዶክተሮችን፣ መሃንዲሶችን፣ የምጣኔ ሐብት አዋቂዎችን፣ ነርሶችን የህግ ባለሙያዎችን ወዘተ ትፈልጋለች በሚል እምነት እና የጋለ ቁርጠኝነት ነው፡፡ ይህም አንዳች ስህተት የሌለበት ትክክለኛ እምነት እና እውነት ነው፡፡ እናም ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ስሜት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በውጭ ሐገርም ሆነ በሐገር ቤት እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ፡፡

‹‹እውነት ነው፤ እኛ በየዘርፉ የሰለጠኑ እና በርካታ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የኪነ ጥበብ መስኮች ልዩ ጥበብን የታጠቁ ብቁ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡ ነገር ግን ሐገራችን የሚያስፈልጓት የመማሪያ መጻሕፍታቸውን እንደ ወንጌል የሚይዙ፣ ከሰለጠኑበት የሙያ መስክ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ካልተማሩት ሰዎች ያልተሻሉ (ምናልባት ከእነሱም በታች ካልሆኑ)፤ የማህበራዊ ሳይንስ እና ይህ የሳይንስ ዘፈር መልስ ለማግኘት ትግል ለሚያደርግባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ደንታ የሌላቸውን ሰዎች አይደለም፡፡ የስፔሻላይዜሽን እና የምዕራቡ ዓለም ኢንዱስትሪያላዊ ሥልጣኔ መገለጫ የሆነው የሙያ ግርዶሽ ሰለባ (ጠቅላላ ስዕልን በሚያጠፋ መጠን በዝርዝር የመዋጥ እና መዳረሻን በሚያስረሳ አኳኋን በመንገድ ባሉ ነገሮች ላይ የማትኮር ችግር ሰለባ) የሆኑ ሰዎችን አይደለም፡፡

‹‹ስለመንገድ አሰራር፣ ስለ ቤት ግንባታ ስለ ድልድይ አሰራር ዘመኑ የደረሰበትን የመጨረሻ ዕውቀት ጨብጦ ሲያበቃ (ጨብጣ ስታበቃ)፤ የሚሰራው ሥራ (የምትሰራው ሥራ) ምን ዓይነት ማህበራዊ ዓላማ እንዳለው የማያውቅ (የማታውቅ)፤ እንዲሁም የህዝቡ (የህዝቧ) ማህበራዊ ዓላማ ግድ የማይሰጠው (የማይሰጣት) መሐንዲስ ለእንደኛ ያለች ሐገር  የሚኖራቸው ፋይዳ ምንድነው? ስለ የምጣኔ ሐብት ባለሙያው፣ ስለ ህግ አዋቂው፣ ስለ ኪነጥበብ ባለሙያው ወዘተ ተመሳሳይ ነገር ለማለት ይቻላል፡፡ እንዲህ ካሰብን፤ ከእኛ የሚፈለገው፤ ከኛ የሚጠበቀው እና በትምህርት ቤት ውሏችን ይዘን መመለስ ያለብን ነገር፤ በአንድ የትምህርት ወይም የሙያ፣ የእደ ጥበብ እና የቴክኒክ መስክ የመጨረሻውን የረቀቀ ሐሳብ ይዞ መገኘት ብቻ አለመሆኑን ማየት እንጀምራለን፡፡ የተልዕኳችን ባህርይ እንዲህ ያለ በመሆኑ፤ ሙያዊ ዕውቀትን በመያዝ ብቻ መርካት የሌለብን እና መርካት የማይገባን መሆናችንን መረዳት እንጀምራለን፡፡ ከዛ በተጨማሪ፤ ከእኛ ልዩ የጥናት መስክ አድማስ ውጪ ያሉ በሚመስሉን ርዕሰ ነገሮች እና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ ሊኖረን ይገባል፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ሲባል አንድ ሰው በሁሉም መስክ የተለየ ብቃት ያለው ባለሙያ ሊሆን ይገባል ለማለት አይደለም፡፡ ይህ ቢፈለግም ሊሳካ የሚችል ፍላጎት አይደለም፡፡ ነገሩን በአጭሩ ለመግለጽ፤ እኛን እዚህ የላኩን ሰዎች ያሸከሙን አደራ እንዲሁ በአንድ ሙያ የሰለጠነ ሰው ሆነን ብቻ ወደ ሐገር ቤት እንድንመለስ አይደለም፡፡ እንዲያ ሆኖ ከመመለስ ከፍ ያለ ነገር ይጠይቀናል፡፡ በሙያ የሰለጠነ ሰው ከመሆን አልፈን ምርጥ የሐሳብ ስርዓትን ታጥቀን -ምርጥ ሐሳብ በዘመናችን ለምትገኘው ኢትዮጵያ ይዘን የተመለስን መሆናችንን ማረጋገጥን ይጠይቀናል፡፡

‹‹በእርግጥ እስካሁን በተናገርኩት ነገር፤ ለኢትዮጵያ ምርጥ ሆኖ የቆየውና ዛሬ ምርጥ ሆኖ የሚታሰበው ነገር፤ በአውቶማቲክ ለሌላ ሃገር ምንም ጥቅም የለውም ወይም ለሌላ ሃገር ጠቃሚ የሆነው ወይም ሆኖ የቆየው ነገር ለኢትዮጵያ አንዳችም ፋይዳ የለውም ለማለት አይደለም፡፡ ሃገራት አንዳቸው ከሌላቸው ሊለያዩ እና ሊመሳሰሉም ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ መንገድ ልዩ ነች፡፡ እናም ይህች ልዩ ሐገር ከውጭው ዓለም ልምድ ምንም ጥቅም አታገኝም ለማለት አይደለም…..›› እያለ ያትታል፡፡

እናም ‹‹ምርጥ የሐሳብ ስርዓት የቱ ነው›› ወደሚለው ጥንታዊ ጥያቄው በመመለስ፤ ኢትዮጲስ (መንግስቱ ለማ)፤ እንዲህ ይላል፤

‹‹ለኢትዮጵያ ህዝብ ምርጥ የሆነው ነገር ለኢትዮጵያም ምርጥ ይሆናል፡፡ …. ይህን ግብ ለማሳካት የሚያግዝ ‹የሐሳብ ስርዓት›፤ ዞሮ ዞሮ ለኢትዮጵያ ምርጥ የሐሳብ ስርዓት መሆኑ አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ባህርይ፤ የሐገሪቱ አንገብጋቢ ፍላጎት፣ እንዲሁም ያሉት ማህበራዊ እውነታዎች፤ የቱ ነው ምርጥ የሚለውን ጉዳይ ይወስናሉ፡፡ ስለዚህ፤ ዓይን ገላጭ ግንዛቤ ለማግኘት፤ እና ለጥያቄአችን መልስም ለማግኘት ስንል ልንመረምር ይገባል፡፡

‹‹የሃገራችን ህዝብ የኑሮ፣ የጤና እንዲሁም የትምህርት ደረጃ እና የሃገራችን ባህል ከፍ ከፍ እያለ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በዕድገት ከገሰገሱት ሃገራት ተርታ መሰለፍ ችያለሁ ብላ አፏን ሞልታ መናገር እስክትችል ድረስ ይህ መሻሻል ይበልጥ መጎልበት እና መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ፤ ‹በጣም ምርጡ የሐሳብ ስርዓት›፤ ከዚህ ግብ በፍጥነት እና በማያዳግም አኳኋን ለመድረስ የሚያስችለን የሐሳብ ስርዓት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን የሐሳብ ስርዓት ፈልጎ የማግኘት ሥራ፤ ከተሰጠን ተልዕኮ ጋር አንድ እና ያው ነው፡፡››

መንግስቱ ከፍ ብሎ ከተጠቀሰው ሐቲቱ ጋር አጎዳኝቶ፤ ዘወትር ከእርሱ አንደበት የማይጠፋ አንድ የማስጠንቀቂያ ቃልን ያክላል፡፡ እናም እንዲህ ሲል ይጽፋል፤

‹‹ከሁሉም ነገር በላይ፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሌላን ነገር ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ማንነት መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡ ከምዕራባውያን ምሁራን ጋር የሚያጃምል ‹የእኛነት ስሜት› ከማዳበር፣ በአሉታዊ ስሜት (pessimisim) ከመጥለቅለቅ እና ከዝቅጠት አስተሳሰብ (decadence) ራሳቸውን ነቅተው መጠበቅ አለባቸው፡፡ እናም፤ በዘመናችን ዋና ዋና አጀንዳ ተደርገው በሚታዩ ወሳኝ እና አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ከተዛባ ስሜት የተጠበቀ እና በነባራዊ ሀቅ ላይ የተመሰረተ ዳኝነትን ማሳለፍ የሚያስችል ምሁራዊ ነፃነትን ያካተተ እውነተኛ የነፃነት ስሜት ማዳበር ይገባናል፡፡ በዚህ ተቃራኒ ሐሳቦች በነገሡበት፤ እርስ በእርስ የሚራኮቱ ሥልጣኖች እና ፍልስፍናዎች በሚገኙበት እና አንዱ ከአንዱ ጋር ውጊያ የሚያደርጉ ‹የህይወት ዘይቤዎች› በሚታዩበት ግራ አጋቢ ዓለም የሚሰሩት ጋዜጦች እና ራዲዮዎች ከሚያረቡት ስንክሳራዊ አጀንዳ ተሻግረን ለማየት እንችል ዘንድ የዓይነ ህሊናችንን መነጽር በደንብ መወልወል ይኖርብናል፡፡

እንግዲህ መንግስቱ ውሎ አድሮ አውራ ሆኖ የሚታይበት የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፤ ‹‹በቅርጽ ሐገርኛ – በይዘት ተራማጅ መሆን ይገባዋል›› የሚል ጥልቅ መሠረት የያዘ አመለካከቱን የቀመረው በዚህ ለንደን በቆየበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ የአመለካከቱ ይትብሃል ተቀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው፤ New Times and Ethiopia News በሚል ስያሜ እናቴ ታሳትመው በነበረው ሣምንታዊ ጋዜጣ ለታተመ አንድ የአማርኛ ግጥሙ አጃቢ ርዕስነት ባሰፈረው ሐረግ ነው፡፡

ወደ ኋላ ከሚገለጠው ሥነ ጽሑፋዊ እና ምሁራዊ የህይወት ጉዞው አንጻር፤ መንግስቱ ለማ በእንግሊዝ ሐገር ያሳለፈው የተማሪነት ህይወት፤ አብዝቶ በማጥናት፣ በማሰላሰል እና በመማር የትልቁ መንግስቱ መሠረት የተጣለበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አዎ፤ በኋለኛው ዘመን የሚመጡት የበርካታ የኪነ ጥበባዊ ሥራዎቹ መሠረት የተነጠፈበት ዘመን ነው፡፡

እናም የእርሱ ሞት፤ አንድ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው የማጣትን ብቻ ሳይሆን (ለኔ በግል በጣም የምወደውን ጓደኛዬን፤ በጋብቻዬ ሚዜ ከሆኑኝ ከሁለት ሰዎች አንዱን፤ እንዲሁም ሩብ ምዕተ ዓመት ለሚሆን ጊዜ ከሞላ ጎደል በየዕለቱ ሳናግረው የቆየሁትን ሰው ማጣቴ እንደ ተጠበቀ ሆኖ) ጥንታዊቱን ኢትዮጵያ ከዘመናዊቷ ጋር የሚያይዝ አንድ ሁነኛ ገመድ መቆረጡን የሚያረዳ ክስተት ነው፡፡ ይህን ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ መንግስቱ፤ በጥንታዊት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከተደራጁት ት/ቤቶች በአንዱ የተማረ፤ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቋንቋ ለሆነው ለግዕዝ ራሱን አሳልፎ የሰጠ እና በዚህ ላይ ደርቦ ለማህበራዊ ዕድገት ዓላማ የቆመ ዘመናዊ ምሁር በመሆኑ ጭምር ነው፡፡

እናም ጥንታዊቷን እና አዲሲቷን ኢትዮጵያ የሚያስተሳስር ጎልቶ የሚታይ ገመድ ሊባል የሚችለውን መንግስቱ ለማን ማጣታችን፤ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እና በሌሎች ተቋማት ውስጥ የምንገኝ ሰዎች፤ በግዕዝ ቋንቋ እና ከግዕዝ ጋር ተያያዥ በሆነ ባህል ዙሪያ የሚካሄዱ ጥናቶችን የማጠናከርን ጉዳይ እንድናስብበት የሚገፋፋ የማንቂያ ደወል ነው፡፡ ሐሳብ አነቃቂ መምህር፤ እንዲሁም ባለቅኔ፣ ፀሐፌ ተውኔት እና ከበሬታን ያተረፈ ምሁር የነበረው መንግስቱ፤ ይኸው ልባም የሆኑ በርካታ ተማሪዎችን አፍርቶ ከዚህ ዓለም ተሰናብቷል፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                             

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top