ማዕደ ስንኝ

ትናንትና እና እኛ

ትናንትና እና እኛ

ለካስ ትናንትም ይሻክራል!…

አሽክላ እንደበላው ማድጋ

አፈር እንደላሰው ምሳር

ለካስ የድሮ ድሮ ይጓጉጣል!…

ሲሶው ቢጥም፤ ቀሪው ያማል፡፡

ጨው እንደበላው ቆርቆሮ

ለካስ የትናንት ዛሬ ያስጠላል!…

ጠባሳው ውርዴ ሁኖ

ትዝታም እንደቁስል ያዣል…

ላይሰሙት፣ ላይዳስሱት፣ ላይጨብጡት

እንደ ሳማ ያቃጥላል፤ ይለበልባል

ለካስ ትናንትም ይሻክራል!…

መጅ አውጥቶ፤ ቡሃ ቆርቆሮ ሁኖ

የሃቻምናው ልጅነት

በዛሬው ሰውነት ሲወሳ…

ለካስ ትናንትም ይቆረቁራል!…

ባዛሬ እኔነት ላይ ተኝቶ

በዛሬው ትናንት ተድጦ

ያ ዘመን፤ያ ማሙሽነት ቀረንቶ፣

ለካስ ትናንትም ይሻክራል!…

ለካስ ትናንትም ይመራል!…

ትዝታ እንቆቆ ሁኖ ያቋቁታል

ትናንት ጥላውን ሲያጠላ

ልጅነት የዛሬ ቅስምን ሲበላ

ለካስ አዳሜ ይታመማል…

ትዝታም ሳንጃ ሁኖ ያመግላል

ለካስ ትናንትም ያማል!…

ጅል ከትናንት ራሱ ይጣላል

በዛሬ ሰውነቱ ይማልላል

አንጀት ምሶ ቆሽት አድብኖ

ከልጅነት ጥላ አብንኖ

ለካስ ትናንት እንዲህ ያማል!…

ለካስ ትናንት እንዲህ ያዣል!…

ወለላው ፈሶ፤ ገፈት አምቡላው ይጠላል፣

አበራ ለማ (አውጫጭኝ)

እየሄዱ መጠበቅ

ሆድ ከሀገር ይሰፋል ሲባል ሰምቻለሁ

ይህንን አምናለሁ በዚህ እታመናለሁ

እውነትም እንዳሉት ሆድ ከሀገር ሰፋ

ስንቱ ሀገሩን ትቶ ሆዱን ብሎ ጠፋ

በላይ በቀለ ወያ (እየሄዱ መጠበቅ)

ሀገር ማለት

ጭቁን፣ ምስኪን ህዝቦች የያዘች በሆዷ

እልፍ ብልህ ህዝቦች ያኖረች በከርሷ

ጥቂት ብልጣብልጦች በገመድ አስረዋት

በሁሉም አቅጣጫ ደርሰው የሚስቧት

ወዴትም የማትሄድ

      ይ‘ቺው ኢትዮጵያ ናት፡፡

አንዷለም ኪዳኔ (በፀሐይ ቅጠሪኝ)

ልሒቃን

ተወልደው፣ ጡት ጠብተው፣ ወራት እንዳለፉ

ወጉ ሳይደርሳቸው፣ ሳይኮላተፉ

ዳዴ ወፌ ቆመች፣ ድክ ድክ ቀርቶ

እግራቸውን ቀድሞ – አፋቸው ተፈትቶ

በተቀመጡበት – ወሬ ሲያላዝኑ

ምዕተ ዓመት አልፎ – ዳግም ቢመዘኑ

እግራቸው አልፈታ – ቁመት አልጨመሩ

ሽበታም ሕፃናት – አገር ምድር ሞሉ፡፡

በአካል ንጉሴ (ፍላሎት)

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top