መጽሐፍ ዳሰሳ

ታክዮን

የመጽሐፉ ርዕስ ታክዮን

የገጽ ብዛት፡- 324

ደራሲ፡- ዳንኤል ለገሰ (ፒ.ኤች.ዲ)

በ1988 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ተቋም (አይ.ኤል.ኤስ) የድኅረ-ምረቃ ትምህርት ቤት ስለ አማርኛ ግጥም አመጣጥ እና ዕድገት አንድ ኮርስ እሰጥ ነበር፡፡ ከተሳታፊዎቹ መካከል አንዱ ዳንኤል ለገሰ ነበር፡፡ የግዕዝ ጉባኤ ቃና መርጠው እንዲተረጉሙና እንዲመሰጥሩ የቤት ሥራ ሰጥቼ ዳንኤል የሚቀጥለውን አቅርቦ ነበር፡፡

  “ድህረ ተሰብረ አጽንኦ ሰብእናነ ልህኩት

   ልባዊ ክርስቶስ በማዬ አዲስ ጥምቀት”

ሲተረጉመው፡- የስብእናችን ገንቦ ከተሰበረ በኋላ ልባዊ ክርስቶስ በአዲስ ጥምቀት አነጸው፡፡ ከሀያ ሦስት ዓመት በኋላ “ታክዮን” የተሰኘ ልብወለድ አሳትሞ እንድመርቅለት ሲልክብኝ የአሁኑ ደ/ር ዳንኤል ለገሠ ማነው? ብዬ ትውስታየን እፈትሽ ጀመርኩ፡፡ ከዚያም ካስቀመጥኳቸው የጥናት ጽሑፎች መሀል ላይ የጠቀስኩትን ወረቀት እንደ አጋጣሚ አገኘሁት፡፡

ዘግይቶ ስለደረሰኝ መጽሐፉን ያነበብሁት ከምረቃው በኋላ ነው፡፡ “ታክዮን” ደግሞ የኔኑ የኡመር ኻያም ልቦለዳዊ የህይወት ታሪክ አዛማጅ ትርጓሜን አስታወሰኝ፡፡ በታክዮን ውስጥ የማቲ እና የሳባ በረሄን ፍቅር ከዑመር ኻያም እና ከጃሃን ፍቅር ጋር እንዳነፃፅረው ጠቆመኝ፡፡ እንደዚሁም በሀዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ” ከበዛብህ እና ሰብለወንጌል ፍቅር ጋር፣ ወይ ፍቅር! አሰኘኝ፡፡ ለሥነ-ጽሑፍ እና ሙዚቃ ተዝቆ የማያልቅ ጭብጥ፡፡

ዶ/ር ዳንኤል ግሩም ዘእምገግሩም ሥራ አቅርቦልናል፡፡

በአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ዐቢይ ሥራዎች (ማስተር ፒስስ) ከሚባሉት መካከል ሊመደብ የሚችል መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

ከፍቅር እስከ መቃብር፣ አንጉዝ፣ ከኦሮማይ፣ ከዴርቶ ጋዳ እና ከሌሎችም በጣም ጥቂቶች ጋር፡፡

  ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ዕድገት ቀናኢ ስለሆንኩ የሚሰማኝን እንድገልጽ ይፈቀድልኝ፡፡ በዓለም ውስጥ ወደር የለሽ ነው ተብሎ የሚነገርለት ልቦለድ የቶልስቶይ war and Peace (ሠላምና ጦርነት) ነው፡፡ በታሪክነቱ፣ በፍልስፍናው፣ በወቅታዊነቱ፣ በዘመን ዘለልነቱ፣ በኹለንተናዊነቱ:: መቼስ ጥበብ ቃላት (የአስፋው ዳምጤን ስያሜ ለመጠቀም) ሁሉን አቀፍ ነው፡፡ ፖለቲካውን፣ ውዳሴውን ውግዘቱን፣ ሂሱን ሽሙጡን የማይዳስሰው የህይወት መስተጋብር የለም፡፡ ጥያቄው የሚያጋድለው ወዴት ነው? ሚዛኑ በየት በኩል ነው የሚደፋው? ነው፡፡

የዳንኤል ርዕስ “ታክዮን” ምን ማለት ነው? “ከምናውቀው ብርሃን የሚፈጥን ጨረሮች ያሉት ኃይል ነው” ይለናል፡፡ ይኸውም ፍቅር፡፡

ከዚሁ ጀምሬ ልሞግተው፡፡ በዓለም ላይ ከብርሃን የሚልቅ ፍጥነት ያለው ኃይል የለም፡፡ እሱንም ቢሆን ግን ጠጣር ..ቁስ አካል (matter) ያግደዋል፡፡ አይንስታይን E=MC2 ብሎ ቀምሮታል፡፡ በሴኮንድ 67 ሺ ማይል (18,000 ኪ.ሜ) የሚጓዘውን ኃይል ጠጣር አካል ያግደዋል፡፡ ግን ይህ ኃይል (E) ራሱን በራሱ ፍጥነት ሲያባዛ (C2) ይጠጥራል፡፡ ስለዚህ ኢ ማለት ኤም ነው፡፡ ብርሃን ከሌለ ግን ኤም አይታይም፡፡ ስላልታየ ግን የለም ማለት አይደለም፡፡ አንፃራዊ ነው፡፡ ያላዩት አገር አይናፍቅም እንደማለት ነው፡፡

ሳይንሱን ልተወውና ወደ ጥበበ ቃላቱ ልዛወር፡፡ ታዲያ “የለም” ማለት “አለ” ሊሆን ነው፡፡ እንዲሁም በግልባጩ “አለ” ማለት “የለም”፡፡

በልቦለዱ (ታኪዮን) ውስጥ ናቲ “ነቲንግ” ብሎ ያነሳዋል፡፡ “‘ነቲንግን’ ማንሳት ብንችል እንዴት ታላቅ ነገር ነው” ይላል፡፡ ግን አይገፋበትም፡፡ “ነቲንግ” በኢንግሊዝኛ ነው “ምንም” በአማርኛ፡፡ በዚህ መሠረታዊ ተቃርኖ ውስጥ ዳንኤል ይዘፍቀናል፡፡ ግን እንዴት አሪፍ አድርጎ ነው የሚዘፍቀን? የጀርመናዊውን ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒትሼን አባባል “የመጨረሻው ክርስቶስ መስቀል ላይ ተሰቅሏልን” አፈር ያስግጠዋል፡፡ ግን ሁሉ ሲሞት ልብ ይሞታል መቼ?

አዎ እናት ዓለም ብትሞትም ፍቅር አይሞትም፡፡ (በአንፃሩ ደግሞ እንኳን ያንቺንና የእናት ሞት ይረሳል ይሏል፡፡

ሳባ “ብሀቂ! ብሀቂ!” እያለች ብትንጰረጰርም መሞቷ አልቀረላትም፡፡ ሀቁ እውነታው ይህ ነው፡፡ ሶመርሴት ሞም “የህይወት ትራዠዲ ሞት አይደለም፤ የፍቅር መሞት እንጂ” ብሏል፡፡

ዳንኤል ግን እንደ ሎንግፌሎው “ፍቅር እንደ ሕይወት እውን እንደሆነ ይቀራል፡፡ መቃብሩም ግቡ አይደለም፡፡” ይለናል፡፡

እኔ ተስፋዬ ገሠሠ “አሌ” ስለው በጥፊ ያጨሰኛል፡፡ በታክዮን ጥሬ

 “አውች!” ሲል

“አየህ አንተም እኔም አለን” ይለኛል፡፡

ያጮለኝ ጥፊ ግን እውን ነው፡፡ ግን ሌላ ጉንጬን አላዞርለትም፡፡ በሀቅ! እኔም መልሼ አቾለዋለሁኝ እንጂ

ምራቁን ይውጥ እና “ዐየህ አንተም እኔም አለን” ይለኛል፡፡

“አዎን እኔም በመጀመሪያ ጥሬህ አንተም በአጠፋዬ ጥሬህ ካልተጥፋፋን አለን እንኖራለን”

“አንተም እንደ ምርጫህ የለሁም በለኝ፡፡ እኔ ዳንኤል ሁሌም እኔ ነኝ፡፡ በአምላክ አምሳያ እንደተፈጠረ ማንነት እንደሆንሁ አትርሳ፡፡ ከእኔነቴ ውጪ ሊገልፀኝ የሚችል ትንግርታዊ ትንተና የለኝም፡፡ በሀሳብ ላይ ተመርኩዞ መደመርም መቀነስም እንጂ ሌላው ትክክል አይደለም፡፡”

“ወይ አንተ ወይ እኔ ኢድየት ነን” አልኩት፡፡

“ከአንተ ኢድዮሲ ኒሂሊዝም ፍልስፍናህ በተቀናሽ መዝግበኝ፡፡ አራት ነጥብ” ብሎ ዘጋኝ፡፡

“እኔ ተስፋዬ ገሠሠ መች ፍንክች! ያንተኑ ገጸ-ባህርይ ማርቲን በኋላ በመኪና አደጋ የምትገድላትን እጠቅስልሃለሁ፡፡ “አሁን ሥልጣን ያለው ሰው… ሰው ነው! ሲሞ! ሲሞ! ይልቅ የጠገቡትን ዝንቦች ከቁስሉ ላይ አታባርራቸው፡፡ አዳዲሶች ዝንቦች እስኪጠግቡ ድረስ ሌላ አሠርታት መፍጀቱ አይቀርም!”

“አድርባይ!”

“እኔ ወይስ አንተ?”

“ዳንኤል አድሏዊነትን የማይቀበል ሌባ የሚቀጣ ሕዝብ ነው፡፡ ባለሥልጣን አይደለም፡፡”

“አጃኢብ!”

በዚሁ ቴአትራዊነቴን ላቆም፡፡ ዳንኤል ከዊሊያም ፎክነር ኖቤል ፕራይዝ ሲወስድ የተናገረው ቃል ጋር ይዳመራል፡፡ Ibelieve that man will not merely endure, he will prevail.

“I… (ሰው መቻል ብቻ ሳይሆን (ሞትን ጥቃት ገሽታን) ሰው ህላዊነቱን ይጠብቃል፡፡ ህልው ነው፡፡ ሰው የሚለውን ቃል ኢትዮጵያ በሚለው ተኩት፡፡ የደራሲው መልዕክት ሲያጠሉት ይኸው ነው፡፡ ኤርትራ ብትገነጠልም ብትገነጣጠልም ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች፡፡

በጽሑፌ መጀመሪያ የጠቀስኩት ጉባኤ ቃና እንደሚመሰጥረው ሰብእነት (ኢትዮጲያዊነት) እንደ ገንቦ ቢፈረካከስም ልባዊ መሪ በአዲስ ጥምቀት ያንፀዋል፡፡

ሕይወት ሁለት ጽንፎች አሏት፡፡ ጥፋት፣ ልማት፣ እኩይ፣ ሠናይ፣ ክፋት፣ ደግነት፡፡ ከበደ ሚካኤል ጨርሰውታል፡፡

“ጽድቅ እና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም

ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም፡፡”

ዳንኤል ልድገመውና፤ ግሩም ዘእምግሩም ሥራ አከናውኗል፡፡ መጽሐፉን እንድመርቅለት ሲመርጠኝ የቴአትር ሰው በመሆኔ ይሆናል፡፡ በቴአትራዊ ሂስ ልደምድመው፡፡ መጨረሻው (ሪዞሊሽኑ)፣ ልቀቱ ሜሎድራማዊ ነው፡፡ በውንነት የተሳለው ገፀ-ባህርይ ተክሎም አስገዶም ከምፅዋ አፈትልኮ መጥቶ አስመራ ፓላስ ሆቴል ሳራ በረሔን ሁለት ጥይት ሲያጠጣት የመጨረሻ ቃልዋ “አነ ይፈትወካ” ባሏም ሲመልስ “እኔም እወድሻለሁ” ሜሎድራማቲክ ነው፡፡ ዳንኤል ከተንታኝነት ወደ ስሜታዊነት አዘነበለ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top