የጉዞ ማስታወሻ

በ‘ኦሮማይ’ መንገድ

በዓሉ ግርማ በኦሮማይ መጽሐፉ “መንገዶች ሁሉ ወደ አስመራ ያመራሉ” እንዳለው እኔም ዕድሉ ደርሶኛል። በታሪክ የማውቀውን፣ ህልም የሚመስለኝን ዳሰስኩት። ለአንድ ኦሮማይን ላነበበ ኢትዮጵያዊ አስመራን መጎብኘት ናይሮቢን ወይም ካይሮን ከመጎብኝት ይልቃል። ምክንያቱ ደግሞ በዓሉ ግርማ ነው።  ኦሮማይ በተሰኘ መጽሐፉ ለከተማዋ ኣንባቢዎች ልብ ውስጥ ሀውልት  አቁሞላታል። በተለይ የመጽሐፉ ዋና ገፀ-ባህሪ የሆነችውን ፊያሜታ ጊላይን  በአእምሮአችን ሸራ ላይ በደማቅ ብሩሽ  ስሏታል።

“ክቡራትና ክቡራን መንገደኞቻችን ወደ መዳረሻችን ኤርትራ፣ አስመራ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ደረሠናል። ቆይታችሁ መልካም እንደነበር ተስፋ እናደርጋለን። መልካም ጊዜ!”

የሚለውን የኢትዮጵያ አየርመንገድ የበረራ አሰተናጋጆች መልዕክት ተከትሎ ቪዛ ወደሚመታበት ክፍል ተወሠድን። የቪዛ ሰራተኛው የፓስፖርቱን ፎቶ ከገጻችን ጋር እያመሳሰለ ጥያቄ ይጠይቃል። ከአዲስ አበባ መምጣታችንን እና ኢትዮጵያዊያን መሆናችንን ሲያውቅ ደስታ ጎብኝቶታል። በተኮላተፈ አማርኛው                        

“እንኳን ደህና መጥአችሁ!” አለን
“እንኳን ደህና ጠበቅኸን” 

ወደ መውጫው እየሸኘን አንድ ውለታ ጠየቀን። የገንዘብ ኖት እያስጠጋልን ቢራ እንድንገዛለት ጠየቀን። ሦስት ሳጥን ቢራውን ገዝተን አየር መንገዱን ስንለቅ

ሦስት ደርዘን ቢራ እንድንገዛለት ጠይቀን። አያይዞም ብሩን ሠቶን በዛውም የገዛንለትን ቢራ ለመቀበል ውጪ እንደሚጠብቀን ነገረን። ደልዳላ ሠውነት ያላት ሴት በፈገግታ ተቀበለችን። ወደ ቤት የሚያደርሰንን መኪና ጠቆመችን።

በጉዟችን ሳንገፋ የላከን ወጣት በቅርብ ርቀት ሲከተለን ተመለከትነው።  

ቢራውን ተቀባብለን “የቐንየለይ” ብሎ ተሠናበተን።

በከተማዋ ቢራ ውድ ነው። ዋጋው አይቀመስም። ይህን የታዘቡ ዕድሉ ያላቸው ሰዎች ከአየር መንገድ ያወጡትን አትርፈው ለነጋዴዎች ይሸጡታል። የኤርትራን አየር መተንፈስ ከጀመርን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ያስተዋልነውን አዲስ ነገር እየታዘብን ጉዞ ወደፊት ቀጠለ።

የዘንባባ ዝንጣፊ እያለፍን በከተማዋ ትልቁ ሆቴል በአስመራ ፖላስ በኩል ‘ገጀረት’ በመባል የሚታወቅ ሠፈር ደረሰን።

ተቀባያችን ራሄል ወደ ቤቷ ተጣድፋ ገባች። ድክ ድክ ከምትለው ኤልሣ እስከ በሃያዎቹ መጀመሪያ እስከምትገመተው ሠሚራ ድረስ እንግድነት እንዳይሠማን ጣሩ። ሁሉም ነገር ምቹ እንዲሆንልን የሚቻላቸውን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ተጉ።  

እጃችንን አስታጥበው እንጀራ አቀረቡልን። የቀረበልን እንጀራ የምናውቀውን ዓይነት ነው። አቆራረጡ ግን ይለያል። በአስመራ እንጀራ  በፒዛ ቅርፅ የመቁረጥ ልማድ አለ። ፒዛ በእንጀራውን በቆንጆ ቀይ ወጥ ካጣጣምን በኋላ ቡና ተጠጣ።

አሁን ሁለቱም ወገን ስለመጣበት እና ስላለበት ከተማ ማውጋት ጀምሯል። እኛ ስለ አዲስ አበባ እነርሱ ስለ አስመራ የምናውቀውን፣ ቢነገር ጥሩ ነው የምንለውን እየተጨዋወትን ነው።

በወዲ ተካቦ፣ በአብርሃም አፈርቂ፣ በሄለን መለስ ዜማዎች የምናውቃትን ኤርትራ በበአሉ ግርማ ብዕር የተዋወቅናትን ኤርትራ በአካል ለማየት እየጓጓን በነገ ቀጠሮ ወደ አልጋችን አመራን።

የንጋት አብሳሪ ወፎችን ድምጽ ተከትለን ከአልጋችን ተነሳን። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎቿ የሚርመሰመሱባትን ከተማ የማለዳ አየር እየሳብን ታክሲ ተሳፈርን። ከገጀረት ወደ ካቴድራል የሚወስደውን ታክሲ ያዝን። በርካታ ብስክሌት ተጠቃሚዎች አሉ። ከመኪናው የሚበልጥ ቁጥር አላቸው።  

የከተማዋ  ሞገስ ካቴድራል ነው። ስሜትን የሚቆነጥጥ የስነ ህንፃ ውበት የፈሰሰባት አስመራ ካቴድራል  የሙሽርነትዋ ዘመን ማብሰሪያ ይመስላል። ማእከሉን ከጎበኘን በኋላ ቁርስ ለመመገብ ከካቴድራሉ ጀርባ ወደሚገኙት ቁርሲገዛ (ቁርስ ቤት) አዘገምን። የካፌዋ ባለቤት መሆንዋ የተነገረን እንስት የትግርኛችንን መንቀራፈፍ ተመልክታ በአማርኛ ታወራን ጀመረች። የፊቷ ፀዳል የሚረጨውን ፈገግታ አስቀድማ

“ስለመጣችሁ ደስ ብሎናል” አለችን። ምን ላምጣላችሁ ለሚል ጥያቄዋ ምን አላችሁ የሚል ጥያቄያዊ መልስ አስከተልን። የጣሊያን ተጽዕኖ ያረፈባቸው የምግብ ዓይነቶች ጠራችልን። ፍሬታታ፣ካፕሬቶና ስፔሻል፣ ፋታ፣… የሚባሉ ምግቦች ለምርጫ ቀርበዋል።

ወደ አማርኛ ተረጕመን ተመገብን። ጣፋጭ ነበር። ፍሪታታ እንቁላል ፍርፍር ካፕሬቶ መረቅ የበዛበት ጥብስ ነው። እነዚህ የምግብ ዝርዝሮች በአስመራ ከሻይ ቤት እስከ ባለ ትልልቅ ስታር ሆቴሎች ይቀርቡልሃል።

በሰፊው ልንመለከታት ፅብቐቲን ልናያት ቀጣይ እቅዳችንን መጀመሪያ ወደ በዓሉዋ ካራቭል ሆቴል አመራን። ካራቬል በኦሮማይ መጽሐፍ ፀጋዬ የተባለው ገፀ ባህሪይ ከእጮኛው ፊያሜታ ጋር ያዘወትርበት የነበረበት “ለጥሩ መጠጥና የፈረንጅ ምግብ ካራቬል” ያለላት ሬስቶራንት ነበረች። ከናቅፋ ሀውስ ወደ ቀኝ የሚታጠፈውን መንገድ ይዘን እንደተጓዝን የታክሲዋ ሹፌር “ይኸው ካራቬል” አለን። ወደ ውስጥ ዘለቅን  ከ50 ዓመት በፊት እንደተሰራ ቤት አልነበረም። ታድሷል ወንበር ስቤ ተቀመጥኩ። ቀይ ሰደርያ በነጭ ሸሚዝ፣ ከጥቁር ቀሚስ፣.. ጋር የለበሰች ሴት በትግርኛ ምን እንደምፈልግ ጠየቀችኝ። ከማዘዜ በፊት ባለቤቱ ካለ ማናገር እንደምችል ጠየኳት።  ትችላለህ ብላኝ ወደ ሚገኝበት ክፍል ወሠደችኝ። በሩን ከፍታ አስገባችኝ። ቆብ ያጠለቀ፣  ዕድሜው በ50ዎቹ መጀመሪያ የሚገመት ደልደል ያለ ሠውነት ያለው ጎልማሣ ቆሞ በፈገግታ ተቀበለኝ። ከአዲስ አበባ መምጣቴን ስነግረው ደግሞ ይበልጥ ተንከባከበኝ። ስለ ሬስቶተራንቱ ያወቅኩት “ኦሮማይ” በተባለው የበዓሉ ግርማ መጽሐፍ መሆኑን ነገርኩት።

“መፅሀፉን አንብቤያለሁ። በዓሉንም በልጅነቴ አየው ነበር” ብሎኛል። ሆቴሉን አስጎበኘኝ። ፍያሜታ ጊላይ ታዘወትረው የነበረውን አስመራ ቢራ በሰፕራይት አዘዝኩ። ጉዞ ኦሮማይ ቀጥሏል። ፓራዲዞን ወደሚያውቅ ሠው ደወልኩ። ፖራዲዞ ቡና ቤት ከላይ የደርግ ባለስልጣናት የሚሠበሰቡበት  ከስር (underground) የሻዕቢያ አመራሮች ይመክሩበት የነበረ መሆኑን አውቃለሁ። የማየት ጉጉቴ ግን አልተሳካም። የደወልኩለት ሰው ቦታው እንደፈረሰ አረዳኝ። ከአስመራ ዕቅዶቼ ውስጥ አንዱ ራሱን ሰረዘ። መፍረሱን በአካል ተገኝቼ ማረጋገጥ አሰኘኝ። በወዳጆቼ እርዳታ አደረኩት። ቀጣይ ማረፊያዬ ኒያላ ሆቴል ነው። ኒያላ በኦሮማይ መጽሐፍም ይሁን ኤርትራ በኢትዮጵያ ስር በነበረችበት ጊዜ የትልልቅ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች መዝናኛ ነበር…

ባለ 10 ፎቅ ህንፃ አጠገብ እንገኛለን። ኒያላ ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻውም። ሰቀላውን በግርምት እያየሁ በመግቢያው በኩል ወደ ሆቴሉ ዘለቅኩ። ዩኒፎርሟ ወደ እርጅና ያጋደለ ወጣት “እንታይ ክእዘዝ?” አለችኝ። ምን ልታዘዝ ማለቷ ነው። “ቢራ! ቀዝቃዛ ቢራ!” መልሷ ግን አስደንጋጭ ነበር “የለም!” ሰዓቴን ተመለከትኩ። 8፡00 ላይ ያመለክታል። ከረፋዱ 8 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ከሌሊቱ 8 ሰዓት የማልሰማውን በመስማቴ ግር ብሎኛል።  

የከተማዋ ትልቁ ህንፃና ትልቁ ሆቴል፣ ባለ ብዙ ታሪኩ ሆቴል፣ ቢራ ሲያልቅበት በፍጥነት መተካት ተስኖታል። የሆቴሉ አብዛኛው ሠራተኞች በኃይለ ሥላሴም፣ በደርግም፣ በኢሣያስም ነበሩ። ልጅነታቸውን ወደ ጉልምስና ያሸጋገሩት በዚህ ቤት መስተንግዶ ነው። የማዕድን ውሃ አዘዝን፣ በድሮው የአዋሽ ጠርሙስ በሚያክል መጠን  የተፈጥሮው ውሃ መጣልን::

ሽርሽር በእግር

ፅብቅቲ እንዳማረባት ነበረች። አሁንም እንደተኳለች ነው። እንዳነበብናት፣ በፊልም እንደተመለከትናት አገኘኋት። አስመራ በኮረዳነትዋ ጎረምሳ ጩቤ የተማዘዘላት፣ ሁሉም የኔ እያለ የሚፎካከርባት ነበረች። ዛሬ በትዝታ ባህር ወደኋላ አሻግራ ደማቅ ዘመኗን በማሠብ የምታሰላስል እመቤት ትመስላለች። የዘምባባ ቅጠሎቿ የተስፋ ፀዳል ይምነሸነሽባቸዋል። አስፓልቶቿ ቢያረጁም ንፁህ ናቸው።

ምፅዋ

ከአስመራ ወደ ምፅዋ ስነጉድ ብዙ ትዝታዎች፣ ብዙ መጻሕፍት፣ የሀገሬ ጀግኖችን በምናቤ እየሣልኩ  ነበር። መኪናዋ ተራራውን ተከትሎ የሚወርደውን ቀጭን መንገድ እየተከተለች ከ2,440 ሜትር ከፍታ ወደ 0 የባህር ጠለል ነፋሲትን፣ ጊንዳዕን፣ ደንጎሎን፣ ጋሕተላይን እያለፈች ነው። እንደ አብዛኛው የኤርትራ መኪና ያለንበትም መኪና አማርኛ ዘፈን ይንቆረቆራል፤ ከዓመት በፊት አማርኛ ዘፈን መክፈት ከፍተኛ ነቀፋና እስራት ያስከትል ነበር። ዛሬ በኤርትራ ምሽት ክበቦች፣ ካፌዎች፣ ሱቆችና የመዝናኛ ቦታዎች ኤፍሬምን ማድመጥ፣ ታምራትን ማድመጥና ጎሣዬን መስማት ከሄለን መለስና አብርሀም አፈወርቂ ይልቅ ይደመጣል።

ሙዚቃው ይንቆረቆራል፣ አማርኛ ተናጋሪ መሆናችንን ያጤኑ የባፅዕ ተጓዦች ለመንገድ የሸመቱትን ዳቦ ቆሎ እያካፈሉን ነው። በስባሪ ትግርኛችን የቐንየልና (እናመሠግናለን) እያልን ከማናውቃቸው ኤርትራውያን ጋር ወጎቻችንን ኮመኮምን፡፡ አንዳንዱ “አቢይ ይመረጣል? ይለሀል። ሌላው እርግጠኛ ነው። ድንበሩ የተከፈተ ጊዜ ያየውን ፍቅር ሲዘጋ ስለናፈቀ “አሳይታችሁ ነሣችሁን፤ ባትመጡ ይሻለን ነበር” ይሉሀል። ሳወራቸው፣ ሲያወጉኝ ዐይናቸው ውስጥ ፍቅር ነበር። እንደ በፊቱ የምትል ሀረግ ጣል እያረጉ ስሜትህን ያገማሽሩታል። ዶግዓሊን ተሻግረን ምፅዋ ገባን።

አባቶቻችን ቢሞቱላትም ሀቅ አላቸው የሚያስብል ውበት አላት። ባህሩን ለሁለት የሚከፍለውን “ቀጢን ሰገለት” ድልድይ ተሻገርነው፤ በዓሉ ግርማ ኦሮማይ ላይ የምፅዋ ፌስቲቫል የተከወነባት እና ኢሳያስ እና አቢይ በጫጉላ ሽርሽር ጊዜ የዋኙበት አጠገብ የሚገኝ ጉርጉሱም ሆቴል ገባን። ባህሩ ያገሣል እንደ አንበሣ፣ ታጥፎ እንደሚዘረጋ የቱርክ ምንጣፍ የባህሩ ሞገድ ወደረገጥኩት አሸዋ እየተዘረጋ መልሶ ይጠቀለላል። በዐይነ ህሊናዬ ወደ ኋላ ነጎድኩ።

ለብዙ ሠዓት ወደባህሩ ቆዘምኩ። አባቶቼ የሞቱላት መሬት አሸዋዋን በእግሬ ቆሰቆስኩ። አቧራው ጤሰ። አባቴ ይሙት ኦሮሞ ኦሮሞ ይሸታል (ሮሪሳ ዳዲ ምፅዋን አልሰጥም ቦንብ በጥርሱ መንቀሉን ልብ ይሏል)፣ አማራን አማራን ይሸታል (ኮረኔል አስጨናቂ በላይ የመጀመሪያው ጥቁር ሰቃይ በሳንደርስ College of Royals የአባቶቼ ርስት ብሎ እንደ ወንድሙ ሮሪሳ ፊቱን ለምፅዋ ሰጥቶ ጭንቅላቱን በጥይት መንደሉ…) የትግራዋይን (አሉላና ልብ ቀጥ የሚያደርጉ ወታደሮቹን ጩኸት አደመጥኩኝ። የወገኖቼን ደም ይጮሀል። ዐይኔን ጨፍኜ ማግሁት፣ ድንገት ስነቃ እምባዬ ገነፈለ። ወደ ጉንጮቼ ተንከባለለ። ከዚያም ወደ መሬት… የፈሰሰውን ከአፈሩ ጋር ለወስኩት፣ የለወስኩትን እምነት አደረኩት፤ አዲስ አበባ ስመጣ ከምይዘው እምነት ማንም የመቆንጠር መብት አለው፤ ምክንያቱም እዛ አፈር ውስጥ የሁላችንም አባቶች አሉ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top