የታዛ ድምፆች

ስሜት እና ተሰጥኦ

አያሌ ሊቃውንት “ተሰጥኦ” “ከስሜት” ጋር ብርቱ ጉድኝት ያለው መሆኑን ይናገራሉ። “ምነው?” ቢሉ ተፈጥሮ የለገሰው ችሎታ “ተሰጥኦ” ካለ በዚያ በተለየ ችሎታ ላይ የጋለ ስሜት ሊኖር እንደሚችል ይመሰክራሉ።

ምንም እንኳ ዘመናት በአዛውንትነት ሲመደቡና የጊዜ ሽረትና ሹመት ሲሰርጽ የሊቃውንት አስተሳሰብም በዚያው ልክ መንገዱን አቅንቶ የሚገኝ ቢሆን “ተሰጥኦ”ን ከ”ስሜት” ጋር በእጅጉ አራርቆ ማሳለፍ እንደማይቻል ያመኑ ጥቂት አይደሉም።  

የቋንቋ ትምህርት እንደ ማለፊያ ምሳሌ ሊወሰድ ቢበቃ ተሰጥኦ የሚያሻው እንጅ የቀለም ትምህርት ብቻውን ሊደግፍ እንደማይችል አሌ የማይባል እውነት ነው። እዚህ ላይ እንግዲህ ሀገርኛውን በብሔራዊነት የሚነገርበትን ቋንቋ ወይም ብሔረሰብኛውን ቋንቋ ለማለት ሳይሆን ከባህሉ ውጭ የሆነውን “የውጭ ሀገር” ቋንቋ ማለታቸውን ነው። አንድ ሰው ከልደት እስከ ጉልምስና ወይም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ቋንቋዎች የመግባባት ጸጋ የተላበሰ ሊሆን ይችላል።

አንድ ሰው በስተጉልምስና ሊያጠና የሚሻው ቋንቋ ካለ ተስጥኦ ቢኖረውም ባይኖረውም ተምሮ ሊግባባበት ይችል። ቁም ነገሩ ለመማር የፈጀበት ጊዜና “የቱን ያህል ይፈላሰፍበታል?” የሚለው ላይ ነው። አንዳንድ ሰዎች የበቃ ትምህርት ሊያገኙ ሳይችሉ ቢቀሩም በገዛ ጉልበታቸው ተጣጥረው በአጭር ጊዜ ውስጥ የውጭ ሀገር ቋንቋ ሊያውቁ የቻሉ አሉ።

“ለምን እንዲህ ተቸገሩ?” ተብሎ ቢጠየቅ የተሰጥኦና የስሜት ጉድኝት እንዳለ ያበሥርልናል። ተሰጥኦ ስላለቸው ያለ መምህር በአጭር ጊዜ ለማወቅ በመብቃታቸው “ተሰጥኦ” ያበረከተውን ሰፊ ድርሻ ሲያመለክተን በትግል ተምሮ ለማወቅ ያደረባቸውን ፍላጎት ስናጤን ደግሞ “ስሜት” የተጫወተውን የራሱን ሚና ያሳየናል።  

የቋንቋን ትምህርት በምሳሌነት ልንጠቅስ የሻነው የተነሳንበትን ርእስ እናስተነትን ዘንድ ብርታት ለመቸር ያህል ሲሆን “ተስጥኦ”  እና “ስሜት” መልካም ተጓዳኞች ሊሆኑ የበቁበትን እንድንገዘብም ጭምር ነው።

በአኳያው ደግሞ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ጠበኞች ሆነው እናገኛቸዋለን። ተስጥኦ ያልቸረውን ጸጋ በስሜት ግለት ብቻ ለመወጣት ሲባል የሚደረግ መውተርተር አለ። አንድ መልኩ ‹ተሰጥኦ  በተፈጥሮ አልተቸረኝም።” በማለት በቀቢጸ ተስፈኝነት እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ ይልቅ ሙከራ ማድረጉ የሚደገፍ መሆኑን ለመረዳት ነው።

ግና ዳሩ ሙከራው ሳይሳካ ቢቀር ተሰጥኦው ወዳለበት መስክ ፊትን አዙሮ በስሜት እንዲጎለብት ማድረጉ ይመረጣል እንጂ በእኝኝ ባይነት ደንድኖ መቸጋገሩ አይመከርም።  

እንግዲህ “ሥምሪት” ወይም “የሙያ ምርጫ” ወደሚለው የርእሳችን ጣምራ ነጥብ ብንሻገር ተሰጥኦና ስሜት በአንድነት ሆነው የሥምሪቱን ስኬት ወይም ክሽፈት በወሳኝነት ሊመሰክሩልን የሚችሉ ይሆናሉ። አንዳንድ ወቅት የሥራ ባልደረቦች ሲጨዋወቱ “እገሌ እኮ ታታሪ ነው፣ በእጅጉ ይጥራል… ግን አይሳካለትም” ሲሉ ይሰማል። ይህ አባባል የሚጠቁመን ምን ይሆን? “የባልደረባቸውን ጥረት አድንቀዋል፣ ታታሪነቱን በእጅጉ አወድሰዋል፣…” ይሁን እንጂ የጥረቱን ያህል እንዳልተሳካለት አልሸሸጉም።  

አሰኛኘቱ ከቅን ልቡና የመነጨ እንደሆነ ተቀብለን እንቀጥል። በርቱዕ አገላለጹ ብቻ ወስደን እንመርምረው። “ይጥራል ይግራል ለምን አይሳካለትም” ብለን ራሳችንን ጠይቀን የምርምር ውጤት ለማግኘት ብንሞክር የሚከሰትልን አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ። ይኸውም “እገሌ”  ተሰጥኦ ሳይኖረው በስሜታዊ ግለት ብቻ የተሠማራ መሆኑን ነው።

“እገሌ የተሸከመው ዕውቀት ይህ ነው አይባልም። ግን ምን ያደርጋል አይጥርም፣ ንቃት ይጎድለዋል፣ ወዘተረፈ…” ሲባል ደግሞ ሌላ ቁም ነገር እናገኝበታለን። በሙያው የተጠበበ ለመሆኑ የሚያጠራጥር ሐረግ አልታሰረበትም። እንደውም የአእምሮውን ብስልነት በማያወላውል ሁኔታ መስክረዋል። “ታዲያ ለምን ንቃት ይጎድለዋል ለምንስ አይጥርም?”  ብለን እኛም አእምሮአችን ውስጥ እንዲጉላላ ብንፈቅድ ስሜቱ እንደ በረዶ ቀዝቅዞ ሥምሪቱን ያቆፈነነው መሆኑን ይነግረናል።

“ለምን ስሜተ በራድ ሆነ?” ብለን ብንጠይቅ አያሌ ምክንያቶች ሊደረደሩ ይችላሉ። በግል ከሚሰርጽ ትዳር ችግር እስከ ሥነ ቁጠባዊ ውጥንቅጥ ድረስ በተዋረድ ምከንያቶች ይዘረዘሩም ይሆናል።

ይሁንና በተፈጥሮ የተገኘ ተሰጥኦ፣ እንዲያ ሲልም ትምህርት፣ በጋለ ስሜተ ስምሪት ላይ ሊውል ካልበቃ የዘገምተኝነት ባህርይ ደንድኖነበት እንቅስቃሴውን ሊደብት እንደሚችል ለመረዳት አላዳገተንም።

በአንድ መልኩ ይህን መስሎ ሲታይ በሌላ ገጽታው ደግሞ ልዩ ሥዕል የሚኖርበት ጊዜ አለ። “እገሌ እኮ በውኑ ጠቢብ ነው። ፈጠራውን ማንም አይደርስበትም። የሚሠራው እንደ ግል ቤቱ እንጅ እንደ መሥሪያ ቤቱ እንኳ አይደለም። ለአንድ አፍታ ከሥራ ገበታው ቢለይ አይወድም። ግን ምን ያደርጋል ቤቱ ሰው አያስመሰግንም… ወዘተ” የሚለው አነጋገር ለጊዜው ጆሮ ሲመታ ቀላል ምላሽ የሚያገኝ ይመስላል።

ይህ የተጠቀሰው አባባል ግን በእጅጉ የጠለቀ ፍተሸ የሚያስፈልገው እንጅ በላእላይ ዳበሳ ብቻ ሕመሙ ሊገኝ የሚችልበት አገላለጽ አይደለም።

ሰውየው ጠቢብነቱ ለፈጠራው ችሎታ ሞገስ ሆኖለት ወደር የለሽ ክንውን ማከናወኑ ተነግሮለታል። አንድ ቤቱ እነብጅ እንደ መሥሪያ ቤቱ የማይቆረጥረው መሆኑን ተረድተናል። ሌላው ይቆይና እሑድን እንኳ ከቤተሰቡ ጋር በዕረፍት ማዘከር ሲገባው ለሙያው ባለው ፍቅር የዕለቱን ትርጓሜ እጅግም እንዳላወቀው ተገልጾልናል።

ለአፍራሻው ግን እንዲህ ለፍቶና በትጋት ሠርቶ ሊመሰገንበት እንዳልበቃ እናያለን። “ቤቱ ሰው አያስመሰግንም”  የተሰኘው የሸመገለ የአነጋገር ዘይቤ ልዩ ትርጓሜ ያለው መሆኑን በዚህ ረገድ ይጠቁመናል። “ለምን አያስመሰግንም?” የተሰኘውን ጥያቄም ይደቅናል። እዚህ ላይ  እንግዲህ  “ሥምሪት” በተገቢው የአሠራር ብልኃት ያልተቀነባበረ መሆኑን ወይም ተሰጥኦንና ስሜቱን አቀናጅቶ ለተገኘ ማለፊያ ጉልበት መጥበቡን ያበሥርልናል።

የሥምሪትን ጥበትና የአሠራር ብልኃትን ያለመቀልጠፍ ስናነሳም የተቋሙ ባሕርይ እንዲህ የሆነበትን ምክንያት ለመመርመር እንቃጣለን። የሥራው ጠባይ ውሱን በመሆኑ አርቡ ሊሰፋ፣ ቁመቱ ሊረዝም የማይችል ሊሆን ይችላል። የአሠራር ብልኃቱም በተለያዩ ምክንያቶች ሸጋ ቅንብር የጎደለው መሆኑን አምነን እንቀበላለን። በዚያም አለ በዚህ ተሰጥኦና ስሜት ያለ ቦታቸው ተዘፍቀው ሥምሪትን ያስጨነቁ መሆናቸውን ያስረዳናል።

አንድ ምሳሌ ብንጠቅስ ደግሞ “መሬቱ ድንጋይ ቢዘሩበት ያበቅላል። ታዲያ ምን ያደርጋል “ጦም አደረ እንጅ!” የተሰኘው አነጋገር የሸበተ ነው። እውን አፈር ድንጋይ አብቅሎ ነው? ምላሹን በአሉታ እንለፈውና ሕብውዕ አገለላጹን ስንፈትሸው  ግን ተሰጥኦና ስሜት በባህል ያለመደርጀት በስንፍናና በመሳሰሉት ጎታች ባሕርያት ተውጠው  ሥምሪትን ያጎሳቆሉ መሆናቸውን ለመገንዘብ እጅግም መቸገር አያሻንም።  

ይህንን ያህል አስተንትኖ የጠለቀ ግንዛቤ ለመግዛት ከበቃን ዘንድ አንዳንድ ሁኔታዎችን ለመጠቃቀስ ብንሞክር ማለፊያ ይሆናል።  

ወደ ጽሕፈቱ ታሪክ ለአፍታ ጎራ ብንል ድሮ  ከረምረም ባለው ዘመን በጽሕፈት መኪና ትየባ መጠበብ እንደ ብርቅ መታየት በጀመረበት ወቅት በየመንደሩ ጥጋጥግ የጽሕፈት መኪና ትምህርት ቤቶች ተቆርቁረው ነበር። እነዚያ “የማሥልጠኛ ማእከላት” ዛሬ ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይድረሰውና በኮምፒውተር ተተክተዋል።

ወደ ግብርና፣ ጥበበ እድ፣ ኪነትና የመሳሰሉቱ አኩሪ ሙያዎች ዘወር ብንል ደግሞ እነዚያ ሞያዎች እንዲናቁና እንዲጠሉ ያደረገው  የጥንት  አስተሳሰብ ተሰጥኦ ስሜትና ሥምሪት ተጣልተውና እርስ በእርሳቸው ተደባድበው “አቶ ወድቀት” በገላጋይነት እንዲቀመጥ የፈቀደበት ወቅት ነበር ለማለት ያስደፍራል።

አሁን በምንገኝበት ወቅት ያለውን ሁኔታ ብንመለከት ግብርና፣ ጥበበ እድ፣ ኪነትና ሌሎችም የሙያ ሜዳዎች በሚገባ ተሰናድተውና ተደራጅተው የሥራን ክቡርነት በየምሥራች ሊያበሥሩልን በቅተዋል።

በተለይም ቀለምና ወረቀቱን ሊያዛምድ የቻለ ማንኛውም ሰው ቢሆን ሊዘነጋው የማይገባውና ለአንድ እፍታ እንኳ ከብዕሩ ለይቶ ሊያስቀር የማይገባው ጉዳይ ባህልን የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል በሕግ ተቋቁሞ ይገኝ ዘንድ ለሞያው ከበሬታን መፍጠሩም ነው። ይህም በመሆኑ የኪነቱም ዓለም ዛሬ በእጅጉ ተከብሮና ተወዶ ኢትዮጵያዊው ከያኒ በሀገሬነቱ ሊኮራ ችሏል።

“ኪነት” ብለን ስናነሳ ግን የዜማ (የዘፈን) ጉዳይ አብሮ ብቅ ማለቱም የግድ ነውና  አንዳንድ አሳሳቢ ሁኔታዎችን ሳይደቅንብን አያልፍም። ድሮ የነበሩ (በዚያን ዘመኑ አጠራር) “አዝማሪዎች” እና በየማታ ክለቡ ያስጨፈሩ የዳንኪራ አስረጋጭ ኦርኬስትራ አባላት በጊዜው በነበረው የወግ አጥባቂነት ሳቢያ አመዛኞቹ ከቤተሰባቸው የተቀያየሙ፣ ከኀብረተሰቡ የተገለሉ፣ የተናቁ፣ ቢሆንም ተሰጥኦን ከሰሜት ጋር ተላቅለው ሥምሪቱን ማለፊያ በማድረግ ለሙያው ያላቸውን ፍቅር አጎልብተው አስከብረዋል።  ብርቱ ትግል አድርገዋል።

የዚያ የዘመናት ትግል ዛሬ አክትሞ አያሌ ሙዚቀኞች፣ ድምጻውያን፣ ዘማርያን አፍርተናል። ብሎም ቢሆን ሁኔታው ገደብ የለሽ ወደ መሆን ደረጃ ሊደርስ የተቃረበ ሰለሚመሰልና የሙያውን ክቡርነት በፍቅረ ንዋይ ጀቡነው በፍጹም የገቢ ምንጭነት ብቻ እንዲያገለግሉ የሚሹ ሰላልጠፉበት አሳዛኝ ገጽታውን ለማየት ዳር ዳር እያልን መሆኑን ለመደበቅ አንሻም።

ማዜምና መሞዘቅ “እንደ ልብ ሆኗል” በሚል አጉል አስተሳሰብ ያም ያም “ቅኔ ዘራፊ፣ ስንኝ አሳሪ” ሊሆን የተመኘበቱ ነገር ተሰጥኦ ስሜትና ሥምሪት በገንዘብ ተለውጠው የሙያውን ውርደት በአደባባይ ከማጋለጥ በቀር ክብረቱን አይነግሩንም።

በመሠረቱ በዚህች ምድር የሠፈረ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ ሠርቶ ለማግኘት፣ ነግዶ ለማትረፍ፣ በልቶ ለመጥገብ እንጅ ለፍቶ ለማጣት፣ ነግዶ ለመክሰር፣ ጉርሶ ለመራብ ሲል እንደማይደክም እናውቃለን።

ብሎም ቢሆን በሙያ ረገድ ሲጤን የሙያውን ክቡርነት በቅድሚያ አዘክሮ የድካም ዋጋ መቀበል እንጅ ገንዘብን በእልቅና ሾሞ ሙያውን በጭፍራነት ማሳጀብ ተሰጥኦና ስሜት ሞተው ሥምሪትም (ሙያ) እንዲከተል ለማድረግ መሆኑ አንድና ሁለት አይባልም። በአሁኑ ዘመን ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ዘፋኝና ዳንኪራተኛ የሆኑ እንዳሉ ይነገራል። ይህን ጉዳይ ግን በሙያው ክቡርነት ያመኑ ምስጉን ከያንያን ሊያስቡበት ብቻ ሳይሆን ሊታገሉበት የተገባ ነው እንላለን።

በርግጥ ሰው ሁሉ ተሰጥኦውና ስሜቱ እንዳሰበው ሥምሪቱን አደላድሎ ይገኝ ለማለት አንችልም። ይህ እንኳንስ በእኛ አቅምና “በልጽገናል” ብለው በትዕቢት በሚደነፉት የባሕር ማዶ ሥልጡኖች ዘንድም ቢሆን ተግባራዊነቱ ሙሉ በሙሉ እውን ሊሆን አልቻለም። ቢሆንም አንድ ሰው ለሚሠራው ሥራ በቅድሚያ የሚያገኘውን ገቢ ካሰበ ተሰጥኦውና ስሜቱ ከገንዘቡ አኳያ ብቻ ይመዘኑና ይቀራሉ። የዚህ ዓይነቱ አመለካከት በተለይ በኪነቱ ዓለም (ሥነ ጽሑፍን ጨምሮ) ጭርሱን በተግባር ሊውል የማይገባው ኩንን ባሕርይ መሆኑን ከጠዋቱ ተረድቶ መቀመጥ የግድ ነው። በዚያም አለ በዚህ ተሰጥኦ፣  ስሜት፣ ሥምሪት ምን ጊዜ ቢሆን መለያየት የማይችሉ፣ ከተለያዩ ደግሞ ብርቱ ግድፈት የሚያስከትሉ መሆኑንም በጣምራነት መረዳት የእያንዳንዱ ባለሙያ ተግባር ነው።

ለግድፈቱም ሆነ ለጉድለቱ ግን “ፍቅረ ንዋይ” ዋና ተጠያቂ መሆኑ አይካድም። የፍቅረ ንዋይ መዘዝ እጅግ ብዙ ነውና!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top