ፍልስፍና

ሰው የመሆን ጉዞ (በሳይንስ- በሃይማኖት)

መግቢያ

ባለፈው እንዲሁ እንደዋዛ ሰው የመሆን ጉዞ ብለን የጀመርነው ጉዞ አቅጣጫው የበዛ ስለሆነ መንገዶቹን መመርመር ቀጥለናል። ሰው የመሆን ጉዞ ትብታቡ የተወሳሰበ ንውዘት እና የጠራ መስመር ለማግኘት የሚደረግ ፍሰት ነው። ባህል እና ፍልስፍና ሰውነትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ለማየት ተሞክሯል። የባህሉ ባለቤቶች ሰዎች ከመወለዳቸው በፊት ጀምሮ ከሞቱም በኋላ ስላለው ዘመናቸው እና ጉዟቸው ይበጃል ያሉትን ክዋኔዎች ይፈጽማሉ። ፈላስፎቹ ደግሞ ለአንድ ዘውግ አባላት ብቻ ያልተመጠነ፣ የአንድ ማኅበረሰብ ብቻ ያይደለ፤ ለአንድ አካባቢ ያልተወሰነ በጥቅሉ የሰው ልጆች የሆኑ ሁሉ በተፈጥሮ የተቸራቸው ወይም በተፈጥሮ የሚፈልጉት፣ በእውቀት እና በምርምር የሚደርሱበት፣ ቢያደርጉት መልካም ነው የሚሉትን በዲበ አካል፣ በነገረ ዕውቀት እንዲሁም በሥነ-ፋይዳ (Axiology) እውቀት ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ (Universal) ህግ እና ይሁንታ ለመመስረት ይኳትናሉ። በዚህም ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ ለማድረግ ለዘመናት ገዥ ሐሳቦችን እየፈጠሩ ኖረዋል፣ አሁንም በመፍጠር ላይ ናቸው። ነገር ግን ሰውነት ለባህል እና ለፍልስፍና ብቻ የተተወ አይደለም። ሳይንስ እና ሃይማኖትም የሰውነትን ምሥጢር፣ ሰው የመሆንን ጉዞ ስንክሳር፣ የጉዞውን ትብታብ ሰንሰለት ለመበጠስ እና መንገዱን ለማቅናት የየራሳቸውን መፍትሔ ወይም ይበጃል ያሉትን ዘዴ ይዘዋል። በዚህ አጭር ጽሑፍ የሁለቱን የሰውነትን መብረሪያ አክናፎች መነሻና መዳረሻ ዓላማዎች፣ የመንገዳቸውን ሁናቴ ለማየት እንሞክራለን። በጉዳዩ ላይ የተሻለ ዕውቀት ያላቸውን ሰዎች ለመጥራት የተደረገ የመነሻ ውይይት እንጂ ይኸው በቂ እና ምሉዕ ነው የሚል ሐቲት ወይም ብያኔ አይደለም።

ሳይንስና ሃይማኖት (ሰው – የምድራዊው እና የሰማያዊው ዓለማት አማካኝ ፍጥረት)

ሳይንስና ሃይማኖትን ሊያገናኛቸው የሚችል አንድ ነጥብ ቢኖር ሰውነት ነው። ለዚች ድምዳሜ መነሻ የሆነን እጓለ ገብረ ዮሐንስ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ በተሰኘው መጽሐፋቸው ያቀረቡት ሐሳብ ነው። እንዲህ ይላል:- “ሰው በሁለት ዓለማት መካከል የሚገኝ አማካኝ ፍጥረት ነው። በአካሉ የጉልሁ ዓለም ተካፋይ ነው። በመንፈሱ የረ[ቂ]ቁ የዘላቂው ዓለም ተሳታፊ ነው። በሥነ ፍጥረት ላይ የሚጸናው የግዴታ ሕግ በእሱም ላይ ይጸናል። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚጸናው የነጻነት ሕግ በሱም ላይ ይጸናል። ስለሁለቱም ዓለማት አግባብ አለው። ስለዚህ የምርማራውን አቅጣጫ ወደሁለቱም ይመራል።” (ገጽ. ፲፪) እንደ እጓለ አስተያየት የፍልስፍና ምርመራ ሁለቱንም ዓለማት ባንድ ላይ አስተባብሮ በመያዘ እና ስለመላው ዓለም እና ስለሰው ልጆች ይበጃል ያለውን በሕግ ምክንያት የተመሰረተ አስተያየት ያቀርባል። ሰው የምድራዊ እና የሰማያዊ ዓላማት ዜጋ ከሆነ ሁለቱን ዓለማት በአግባቡ ተረድቶ የዜግነት ግዜታውን የሚወጣበትን እና መብቱን የሚያስከብርበትን ሕግጋት ነድፏል ማለት እንችላለን። በዚህም ሰው ግዙፉ ምድራዊ ሕይወት እና ኑሮ ግድ የሚለው፣ ረቂቁ ሰማያዊ ወይም የማይጨበጥ-‘ማይዳሰሰው መንፈሳዊ ዓለም ያገባኛል እና ይገባኛል የሚል ፍጥረት በመሆኑ ሁለቱንም ዓለማት የሚመረምሩ የሳይንስ እና የሃይማኖት ርዕሰ ጉዳይ ሊሆን ችሏል። ሁለቱን በተናጠል ለማጥናት ደግሞ ሳይንስና ሃይማኖት የየራሳቸውን ፊታውራሪነት ይይዛሉ ማለት እንችላለን።

ሳይንስ ሰውን ምድራዊ ዜጋ እንደሆነ በመፈረጅ ከተፈጥሮ አካላት አንዱ አባል አድርጎ ሲያስቀምጠው፣ ሃይማኖት ደግሞ ምድራዊውን ሕይወት ጊዜያዊ አድርጎ በመፈረጅ የሰው ልጅ ትክክለኛ ህላዌው የሚረጋገጠው በሰማያዊ ወይም ከሞት በኋላ በሚኖረው ሕይወት እንደሆነ ይበይናል። ሁለቱ የሚገናኙት ሰውነት ላይ ሲሆን የሚለያዩትም ሰውነትን በሚወስዱበት አቅጣጫ ነው ማለት እንችላለን። ሁለቱ ፍጹም ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ይጓዛሉ ማለት አይደለም። ይልቁን ሳይንስና ሃይማኖት የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወቱ የተስተካከለ ይሆን ዘንድ ሁለቱም ሲጥሩ ሳይንስ ሰውን ከሞተ በኋላ ብዙም ግድ የማይሰጠው ሲሆን ሃይማኖት ግን ሰው ከመሞቱ በፊት እና ከሞቱ በኋላ ስለሚኖረው ሕይወት እያሰበ እንዲኖር የማንቂያ ደወሉን ኪልል እያደረገ ያስባትተዋል። ሳይንስ በተቻለው መጠን ሰው ረጅም ዕድሜ እንዲኖረው እንዲያውም ቢሳካለት ሰው በዚህ ምድር ላይ ዘለዓለማዊ ሕልውና እንዲኖረው ጥረት ሲያደርግ፣ ሃይማኖት ደግሞ ዘለዓለማዊው ሕይወት በሰማይ እንደሆነ በመስበክ ሰው በምድር የሚኖራት የተመጠነችለት እድሜው እስክታልቅ ድረስ በፈጣሪው ሕግ ተወስኖ ወደ ፈጣሪው በፍጥነት ቢጓዝ ይበጀዋል የሚል አስተያየት ይሰጣል።

ሳይንስ ሰውን የማሰብ እና የመፍጠር ክህሎቱን ተጠቅሞ በተፈጥሮ ላይ ነግሶ የተደላደለ ምድራዊ ሕይወት እና ገደብ የለሽ የሥጋ ፍላጎቱን እንዲያረካ ሲመክር፣ ሃይማኖት ደግሞ ሰውን ከሥጋዊ ፍላጎቱ በመነጠል ወይም ሥጋዊ ፍላጎቱን በመገደብ መልአካዊ ሕልውና እንዲኖረው ጥረት ያደርጋል። ሰውን በዚህ መልኩ የሚበይኑት ሳይንስና ሃይማኖት ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ የሚያነግሱበት መንበርም እንዲሁ ይለያያል። ሁለቱ ሰውነትን ዘርተው የሚያበቅሉበት፣ አርመው የሚያሳድጉበት፣ አጭደው የሚወቁበት፣ ፈጭተው አቡክተው የሚጋግሩበት መንገድ እንደምን ያለ ነው?

የሳይንስ መንገድ

ሳይንስ በባህርይው ለነገሮች እርግጠኛውን መልስ ማግኘት ይቻላል የሚል አቋም አለው። ሳይንስ መቼ እና እንዴት እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም ከጥንታዊ የሰው ልጆች እውቀት ቀስ በቀስ ወደ ዘመናዊ በመሳሪያ የተደገፈ የቴክኖሎጂ ዘመን እንደተሸጋገረ በድምዳሜው መናገር ይቻላል። የሰው ልጅ ወደ መሬት ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ አካባቢያዊ እውነታዎችን ለመፈተሽ፣ ምድራዊ ችግሮችን ለመፍታት እና በተፈጥሮ ላይ አንዳች ለውጥ ማምጣት ሲፈልግ ከሚከተላቸው መንገዶች አንዱ ሳይንስ ነው። ሳይንቲስቱ የተፈጥሮን ሕግ በመመርመር የራሱን መላምት በማስቀመጥ የሰው ልጅ ለዚህ የተፈጥሮ ሕግ ምላሽ በመስጠት እንዴት ስኬታማ ምድራዊ ሕይወትን መኖር እንደሚችል ይበጃል ያለውን ቲኦሪ ያስቀምጣል። በዚህም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በርካታ የሚያስደነግጡ እና ደስ የሚያሰኙ ሳይንሳዊ ግኝቶች እና ድምዳሜዎች ተስተውለዋል። ከነዚህ ውስጥ የኒውተን የመሬት ስበት ሕግ፣ የኮፐርኒከስ መሬት እና ሌሎች ዓለማት በጽሐይ ዙሪያ ይሽከረከራሉ የሚለው፣ የዳርዊን የሰው ልጅ ከትል መሳይ ነገር በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት የመጣ ነው የሚለው እና የኤንስታይን ግኝት ማንሳት ይቻላል።

የሳይንስ ጠንካራ ጡንቻ የተስተዋለው ግን ቤከን የተባለው ሳይንቲስት የሰው ልጅ የሳይንስን መንገድ እና መሳሪያ በመጠቀም ተፈጥሮን ማስገበር እና ለሰው ልጆች ጥቅም እንድትውል ማድረግ አለበት የሚለውን አዋጅ ባወጀበት የሳይንሳዊ አብዮት (The Scientific Revolution) በ17ኛ ክፍለ ዘመን ነው። “እውቀት ኃይል ነው” በሚለው  መርህ የሚታወቀው ቤከን የሰው ልጅ የተፈጥሮ አንድ አካል ሲሆን ማንኛውንም መሳሪያ በመጠቀም ተፈጥሮን ድል መንሳት እና ለፍላጎቶቹ ሁሉ ማስገበር አለበት የሚል አቋም አለው። በዚህም የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ውጭ ስላለው የልዕለ ተፈጥሮ ወይም የማይታየው ዓለም ምንም ግድ ሳይሰጥ እና ስለሱም ማወቅ ስለማይችል የሳይንስን መንገድ ወደ እርግጠኛው እውቀት መምራት አለብን በማለት የመካከለኛውን ዘመን የሃይማኖት፣ እንዲሁም ቀደም ሲል የነበረውን የፍልስፍና ሐተታዎች በመተቸት አዲሱን የእውቀት መንገድ ለመቀየስ ይሞክራል።  ለስሜት ህዋሶቻችን ትልቁን ቦታ በመስጠት ስለ’ሚታየው፣ የሚዳሰሰው ዓለም  እርግጠኝነት ላይ የምንደርሰው በሳይንሳዊው የInductive መንገድ ነው ይለናል። እስከዛሬ በተሄደበት መንገድ እውነት ላይ መድረስ አይቻልም የሚለን ቤከን ሰውን ከተበተቡት አራት ቅያዶች (Idols ደንቃራዎች፣ “ዓይነ ጥላ”) ነጻ ማውጣት አለብን ይላል።

እነዚህ ቅያዶች አንደኛው Idols of the tribe (ከሰው ዘር፣ ከሰው ተፈጥሮ፣ ከሰው ዓርሰ-መረዳት የሚመጣ ስሁት ግምት) ከሰው ከራሱ ተፈጥሮ የሚመነጭ ሲሆን ሰው የራሱን ተፈጥሮ  በሌላው ተፈጥሮ ላይ በመጫን ተፈጥሮን በደንብ እንዳንረዳት በመጋረጃ እንድትሸበብ የሚያደርገው ነው። ሁለተኛው Idols of the cave (ከግለሰቦች የግል ዋሻ፣ የተናጠል ገጠመኝ፣ ወይም የትምህርት ዳራ የሚመነጭ) ሲሆን ግለሰቦች ዓለምን በራሳቸው ጠባብ ጎጆ ልኬት የሚረዱበት ስሁት መነጽር ነው። ሦስተኛው Idols of the Market Place የሚለው ሲሆን ሰዎች በጋራ በሚገናኙበት ወቅት በሚያደርጉት ዝብርቅርቅ ጫጫታ፣ ከገበያ ዳር ተቁሞ ወይም በዳስ ውስጥ እንደሚሰማው ትርጉም እንደሌለው ጉርምርምታ መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ሐሳቦች ሰው ተፈጥሮን እንዳይረዳት ይጋርዱታል። አራተኛው Idols of the Theatre የሚለው ደግሞ በሰው ልጅ የታሪክ ሂደት ውስጥ በርካታ የእውቀት እና የእምነት፣ የተረት እና የትረካ፣ የፍልስፍና ወዘተ ዲስኩሮች ልክ እንደተለያዩ የመድረክ ትእይንቶች የራሳቸውን ዓለማት በመፍጠር ሰው ትክክለኛውን ዓማናዊ ዓለም (Objective World) ማየት እንዳይችል አድርገውታል ይለናል።

እንግዲህ በቤከን ፊታውራሪነት የሚመራው የሳይንሳዊው አብዮት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ትክክለኛውን እና ምሉዕ የሆነውን እውነት ማግኘት ይቻላል የሚል መሠረት ጣለ። Logical  Positivism የሚባለው የቅርብ ዘመናችን የፍልስፍናን ጥንታዊ መንገድ የሚተቸው አንድን ነገር በሳይንሳዊ የሙከራ ወይም በሎጅካዊ የማስረገጫ እስካላረጋገጥን ድረስ እውነት ነው ልንለው አንችልም የሚለው ክንፍ ተፈጥሯል። በዚህም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሚታወቀው የሳይንሳዊነት (Scientism)፣ እንደ ግሎክ ሐተታ አንዳንዶቹ የሳይንስ አምባገነንነት (Scientific Imperialism) ወይም የሳይንስ እብሪት ተንጸባርቋል። በሌላ አገላለጽ ሳይንስ ሁሉን ነገር በሳይንሳዊ መንገድ በቻ መረዳት አለብን የሚል ጠቅልልነት ደረጃ ላይ ደረሰ። በዚህም የሥነ ተፈጥሮ፣ የሥነ ሰብ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች በሙሉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መፈተሽ አለብን፣ ሳይንስም ያንን ለመረዳት ያስችለናል የሚል ድምዳሜ የሚያደርሰው ነው። እንደ ሥነ-ኅሊና (ሥነ-ልቡና) ዓይነቶቹ የትምህርት ዘርፎችም የሰውን ማኅበራዊ ጉዳዮች ከኅሊናው ሥሪት ለመረዳት የሚደረጉ የሳይንሳዊነት መንገድ የወለዳቸው ናቸው። ይህ አስተሳሰብ በርካታ ትችቶችን ያስተናገደ ሲሆን ለምሳሌ የእነ ሀከር የሰው ልጅ እንደ ታሪክ፣ ባህል፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችን ለመረዳት የፍልስፍና፣ የአንድምታ የትርጓሜ (Hermeneutics) እና ሌሎች የማኅበረሰብ ጉዳዮችን መመርመሪያ መንገዶችን ተከትሎ እንጅ ሳይንሳዊ መንገድ ትክክለኛው እና ብቸኛው አማራጭ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።

እንግዲህ የሳይንስ መንገድ እና ዓላማ ምድራዊውን ዓለም መነሻው እና መዳረሻው በማድረግ፣ ሰውም የዚሁ ዓለም ዜጋ እንደመሆኑ ስለሌላው ስለማይታየው ሰማያዊ ዓለም ግድ ሳይሰጠው ራሱን በዚሁ ምድር ላይ እንዴት ደልቶት መኖር እንዳለበት የሚያስችለውን የእውቀት ትጥቅ ማስታጠቅ ነው። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ሰው ካለው የተፈጥሮ ድካም እና ጉድለት ሻገር በማድረግ፣ አካሉን በመቀየር ሊሆን ይችላል፡፡ ሊያበለጽገው የሚያስችለውን የሳይንስ ግኝት ሊገጥምለት ይችላል። የሰው ሰራሽ አእምሮ (Artificial Intelligent) እና የኒውሮ ሳይንስ ፈጠራዎች የሚያመላክቱትም ይህንኑ ነው።  ከሥነ ምግባራዊ፣ ከሰው ልጆች ነጻነት እና ገመና (Freedom and Privacy) አኳያ ሲታይ የቴክኖሎጅው ዓብዮት በርካታ የሚተቹ ነገሮች ቢኖሩትም የሰው ልጅ ዓለምን እንዲገዛ እና በተፈጥሮ ያሉትን ገደቦች እንዲሻገር በማድረግ አኳያ ያስመዘገበው ተራምዶ አለ የማይባል ነው። ሰውነትን ከነበረው የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ ፈተናዎች ነጻ እንዲወጣ በማስቻል ረገድ የሳይንስ አስተዋጽኦ ተዘርዝሮ የማያልቅና በርግጥም ተፈጥሮን የመቀየር ያክል የሚተካከል ነው ማለት እንችላለን። በዚሁ ልክ የሳይንስ መንገድ የዘነጋው ጉዳይ፣ ያልዘጋው ቀዳዳ እና የከፈተው አንጋዳ (አዘቅት) መኖሩንም ማጤን ይገባል። ይህንን የሳይንስ ተቃርኖ በሌላ ጽሑፍ በሰፊው የምመለስበት ይሆናል።     

ወደፍጹማዊው ዓለም የምትወስደው “ጠባቧ” የሃይማኖት ጎዳና

ሰው የሰማያዊ እና የምድራዊ ዓለማት አማካኝ ፍጥረት ነው ብለናል። የምድራዊ ውን ዓለም የሚመራበት የሳይንስ እና የሰው ህጎችን ደንግጓል። ስለ ሰማያዊው ዓለም ሁኔታ የሚያትቱ ደግሞ በዋናነት ሃይማኖት ፈጥሯል። ሃይማኖት ስለ ሰው ተፈጥሮ፣ ስለ ፈጣሪ ምንነት፣ ስለሰው እና ስለ ፈጣሪ ግንኙነት እና ሰው ወደ ፈጣሪ ወይም ከሞት በኋላ ስለሚያደርገው ጉዞ የሚያትት ነው። ምንም እንኳ በዓለም ላይ በርካታ ሃይማኖቶች ቢኖሩም ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ራሳቸውን ብቸኛዋ እና ትክክለኛዋ መንገድ አድርገው በመሳላቸው ነው። የሃይማኖት ሌላኛው መገለጫ ደግሞ የዓለምን ምሉዕ ስእል በማሳየት የሰውን ልጅ ምድራዊ እና ሰማያዊ ሕይወት በመምራት ወደ ዘለዓለማዊነት የሚያሻግር መንገድ ሆኖ መቅረቡ ነው። የሚታየውን እና የማይታየውን ዓለም በሚስልበት መንገድ ደግሞ ትልቁ የእውነታን ግንብ በመስራት የግዙፉን ዓለም ተምሳሌታዊ ሥዕል ያስቀምጣል። ለዚህም መነሻው የሰው ልጅ ዓለም የሚታየው የሚጨበጠው ብቻ ሳይሆን የማይታይ የማይዳሰስ መንፈሳዊ አካላትንም ያካትታል የሚለው ነቁጠ ነገር (Thesis) ነው። ሙለር ስለዚህ ጉዳይ ሲጽፍ እንዲህ ይለናል:-

All human reality is in some sense a spiritual reality, since it perforce includes things that are not seen. Religion is only the clearest example of controlling symbolism. Call it mythology and it is still not a primitive way of misinterpreting or escaping the facts of life, but a comprehensive way of organizing and accepting the facts (p. 80). (የሰው ልጅ ስለ በግዙፉ ዓለም ብቻ ሳይሆን ስለ መንፈሳዊው ዓለም ውስጥም ግድ የሚሉት እውነታዎች አሉት። ሃይማኖት ደግሞ እንደዚህ ዓይነቶችን እውነታዎች ተምሳሌታዊ በሆነ መልኩ በማቅረብ የተሻለው መንገድ ነው። ይህም ከእውነታ የሚያሸሽ የተረት መንገድ ሳይሆን እውነታዎችን በተሰበሰበ መልኩ የሚያቅፍ ግዙፍ ጉያ ያለው ውስብስብ ሂደት ነው።)   

ሃይማኖት ግዙፉን እና ረቂቁን ዓለማት በአንድ ላይ ሰብስቦ በመያዝ ሰራኤ መጋቢውን አንድ ፈጣሪ አድርጎ ያስቀምጠዋል። የሥነ ምግባር በጎነትን በማበረታታት እና የሰውን ልጅ ኃጢአት በማስወገድ ወደ ፍጹማዊው ፈጣሪ እንዲጠጋ ንጽሐ ልቡና እና ቀና ኅሊና እንዲኖረው ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን ይቀርጻል። በፈተና በተሞላው፣ በማዕበል በሚላጋው ዓለም ውስጥ ሰው ከራሱ ከተፈጥሮው (ከሥጋው) እና ከአካባቢው ከሚመነጩ ፈተናዎች የሚያመልጥበትን ትዕግስት እና ብልሃት፣ እንዲሁም የመዋኘት ጥበብ ተጠቅሞ ከማዕበሉ ነጻ የሚወጣበትን ጠባብ መንገድ ይነድፋል። በዚሁም ሰው የራሱን ፍላጎት ገዝቶ፣ በዋጋ ወደማይገዛው ፍጹማዊ እና ዘለዓለማዊ ገነት እንዴት መጓዝ እንዳለበት የሚጠቁሙ የተጻፉ እና ያልተጻፉ ሕግታትን ይነድፋል።

በሰው  ልጆች ታሪክ ውስጥ ግዙፍ ከሚባሉት ሃይማኖቶች ውስጥ ክርስትናን እና እስልምናን እንደ ምሳሌ ብንወስድ እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ እና በቅዱስ ቁርዓን በእነሙሴ አማካኝነት የተሰጡት ዓሥርቱ ትዕዛዛት፣ በቁርዓን እና በወንጌል የተላለፉ ሕግጋት፣ በአብያተ እምነቶቹ ዶግማና ቀኖና የተበየኑ የሕይወት መርሆዎች በሙሉ ምዕመናቸውን ከምድር ወደ ሰማይ የሚያደርጉት ጉዞ የተስተካከለ እንዲሆን የሚያሳዩት ቁርጠኝነት ወደር የለውም። የሰውን ልጅ ከዝብርቅርቁ፣ በፈተና ከተሞላው ዓለም፣ ከሰይጣን ጉሮሮ መንጥቆ ወደ ሰላማዊው ቦታ ለመውሰድ የሚደረገው ግብግብ በምድራዊ ሕይወት ውስጥ ሰውን ከትልቅ የጦር ሜዳ ውስጥ በልዕለ ተፈጥሮ ረድኤት አማካኝነት ነጻ የማውጣት ምስል ሲሳል ባንድ በኩል ሰማያዊ ትፍስኅት በሌላ በኩል ደግሞ ምድራዊ ሕይወት ምን ያክል ረብ የለሽ እንደሆነ የሚያመላክቱ በርካታ ስብከቶች፣ ተረኮች እና ማስጠንቀቂያዎች ይዥጎደጎዳሉ። ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት፣ ትዕግስት፣ ራስን አሳልፎ መስጠት፣ እና ሌሎች የብጽእና ሥራዎች በሙሉ የጠባቧ መንገድ መገለጫዎች፣ ሰው የመሆን የነጻነት ሃይማኖታዊ ጉዞ ሰንሰለታማ ትብታቦችን ማለፊያ በሮች ናቸው። ስስት፣ ጭካኔ፣ ያልተቆጠበ ሥጋዊ ፍላጎት እና ፍትወት፣ ጥላቻ እና ጭቅጭቅ፣ እና ሌሎቹን በዓሥርቱ ትዕዛዛት የተገለጹትን ሕግጋት ማጓደል ደግሞ ሰውን ወደ ገሃነም እሳት የሚወረውሩ የምድር ላይ ማነቆዎች ተደርገው ተቀምጠዋል። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ እያንዳንዱ ሃይማኖት የራሱ ልዩ ሕግጋትን በመቅረጽ የሰው ልጅ ወደ ገነት የሚገባባቸው ወርቃማ ቁልፎች አሉት። ለምሳሌ የክርስትናው ጥምቀት እና የኢየሱስን ሥጋና ደም መቀበል የመጨረሻዎቹ የገነት በር መክፈቻ ተደርገው ተቀምጠዋል። የሰው ልጅ ጉዞ መቋጫው ደግሞ በምድራዊ ሕይወት ይህ ነው ተብሎ የማይበየን ሲሆን በመጨረሻው ቀን ጌታ በሚሰጠው ፍርድ ላይ ይወሰናል።

የሳይንስና የሃይማኖት መፋጥጥ

ከሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች አንጻር የሰው ልጅ በዘመን ሂደት ውስጥ የሚገጥሙት አዳዲፈተናዎች፣ የሚፈጥራቸው የሳይንስ እና የቴክኖሎጅ ግኝቶች አልታረቅ እያሉ ወይም ተቃርኖ እየፈጠሩ ሰው የመሆንን ጉዞ ሲገቱት፣ ሲያደናቅፉት፣ ወይም ሲያዋልሉት ይስተዋላል። ይህም በዘመናዊ ዓለማቀፋዊ ርእዮተ ዓለሞች እና በአንድ ወገን ዕምነት ላይ በተመሰረቱ ሃይማኖቶች መካከል ተቃርኖ ይፈጥራሉ። በሳይንስ ለሰው ልጅ  ምቾት የተባለ ነገር በሃይማኖት ኃጢአት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ እንደ ጽንስ ማስወረድ እና የጽንስ መከላከያ ዓይነቶቹ ገጠመኞች ወይም ምክረ ሃሳቦች በአንዳንድ ሃይማኖቶች ውጉዝ ናቸው። ለዚህም ሃይማኖት ምንም እንኳ ዘመንና ቦታ የማይገድበው፣ የሚታየውና የማይታየውን ዓለም ባንድ ማዕቀፍ በመጠርነፍ የተሳካለት ነው ቢባልም እንደዚህ ዓይነቶቹን ጉዳዮች እንደ ኃጢአት የሚመለከትበት መንገድ ከምዕመኖቹ ጋር ሲያጋጨው ማየት የተለመደ ነው። ለዚህም ነው የሃይማኖት መንገድ ጠባብ ናት የምትባለው። ጠባብነቷ አንድ ነገር ላይ ብቻ በማተኮሯ ሳይሆን ሁሉንም ፈተናዎች በድል ለማለፍ ንጽሐ ልቡናን እና ፈቃደ እግዚአብሔርን በቸኛዎቹ አማራጮች አድርጋ በመውሰዷ ነው። ሳይንስ ደግሞ ለእያንዳንዱ ችግር የራሱ የሆነ ምድራዊ መፍትሔ አለኝ የሚል መንገዱ የሰፋ፣ ባለ ብዙ አማራጭ ጎዳና ነው። የሁለቱን መንገዶች ተቃርኖ ማስታረቅ ሰው የመሆንን ጉዞ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ይመራዋል። ያንን ለማድረግ ደግሞ ቴክኖሎጅው በፈሪሃ እግዚአብሔር ለሚያምኑት እንዴት ምቹ መሆን ይችላል? የሰው ልጅ ያልተገደበ ሥጋዊ ፍላጎት እና የኅሊና ነጻነት እንዴት በሳይንስ እና በሃይማኖት መሰረታዊ መርሆዎች ሊመለስ  ይችላል?

አንዳንዶቹ ሃይማኖት ጨቋኝ ነገር ስለሆነ፣ ፈጣሪም ሰው በፍርሃት የፈጠረው ምስል እንጅ ከዚህ ሕይወት ውጭ ሌላ ዓለም የለም የሚል ድምዳሜ ይደርሳሉ። ሌሎቹ ደግሞ ይህ ዓለም ግዜያዊ እና አላፊ ጠፊ ስለሆነ “ሕደግዎ መንንዎ” ብለው ገዳም ይገባሉ። በዚህም ሰው የመሆን ጉዞ በአጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃል። እውነታው ግን ሃይማኖቶች ለሰው ልጅ በጎነት፣ ባህርያዊ ቀናነት፣ ማኅበረሰባዊ ሰላም ያበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ሳይንስ ደግሞ የሰውን ልጅ ምድራዊ መሰናክሎች ለማለፍ ያበጃቸው ዘዴዎች ሁለቱም እንዲሁ አንዱ ለአንዱ የሚተካ ልዋጮች አለመሆናቸው ነው። በርግጥም የሰው ልጅ በዚህ ምድር በሚኖርበት ጊዜ ከሳይንስ መጠቀም አለበት፣ የሃይማኖት ኃይልም እንዲሁ በዋዛ የሚተች፣ ልናጣጥለው የሚገባ አይደለም። ለመሆኑ በምድራዊ እና ሰማያዊው ዓለማት አማካኝ ላይ የሚገኘውን የሰው ልጅ ከዚህ አጣብቂኝ ነጻ የሚያወጣው ምን ይሆን? ይቆየን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top