ታዛ ስፖርት

ሰውየው

    1975 ዓ.ም ለሙሉጌታ ከበደ  ጥሩ ዓመት ነበር።  በዚያኑ ዓመት ለብሔራዊ ቡድን ተመረጠ።  የደሴ ከተማ ነዋሪ በሙሉጌታ መመረጥ ተደሰተ።  በዚያን ዓመት ፔፕሲ የኢትዮጵያ ሻምፒዮናነትን ክብር ተቀዳጀ። የወሎ ምርጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ትቅደም ዋንጫን አነሳ።  የማሸነፊያዎቹን ግብ ያስቆጠረውና ለድሉ ማማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ሙሉጌታ ነበር።  ቡድኑ ወደ ከተማው ሲገባ የጀግና አቀባበል ተደረገለት።  ሙሉጌታ የደሴ ንጉስ ተባለ።  ለብሄራዊ ቡድን በመመረጡ የሀገር ጥሪ ስለመጣለት ለአዲስ አበባው ጉዞ የሽኝት ግብዣ ቤተሰቦቹ  አዘጋጁለት።  ጓደኞቹና አድናቂዎቹ እንዲሁም የእናቱ ማህበርተኞች በተገኙበት ሞቅ ባለ ሁኔታ ተደገሰ።  ምርቃቱም ተዥጎደጎደ።

ትልቅ ቦታ ያድርስህ!

አገር የምታስጠራ ሁን!

ዕድሜና ጤና ይስጥህ!

ወልደህ፤ ዘርተህ፤ ከብደህ ለትልቅ ደረጃ ያብቃህ!!

እናቱ እንዲለያቸው ባይፈልጉም የሀገር ጥሪ በመሆኑ ከልባቸው መርቀው ሸኙት።  ከተማዋን በስፖርት እያስጠራ በመሆኑ አድናቂዎቹ “የደሴ ንጉስ” ብለው ሰይመውታል።  እነርሱም የሽኝት ጋበዙት።  መልካሙን ሁሉ ተመኙለት።  የክፍለ ሀገሩ አስተዳዳሪ ቢሯቸው ጠርተው ካበረታቱት በኋላ ከሽኝት ደብዳቤ ጋር 500 ብር ሰጡት።  ክለቡ ፔፕሲ 200ብር ለጉዞና ለአንዳንድ ነገር በሚል ኪሱ ውስጥ ሸጎጠለት።  በጥቅሉ ከሁለቱ ቦታ 700ብር አገኘ።  700 ብሩን ለብቻ አስቀመጠና ደመወዙን ተቀብሎ ጓደኞቹን ጋበዘበት።  በነጋታው ምርቃቱን ታቅፎ 700 ብሩን ለብቻው ሸጉጦ ወደ አዲስ አበባ ተጓዘ።

   ሙሉጌታ በአውቶብስ ረጅም መንገድ ሲሄድ ላቡ ፊቱ ላይ ችፍ ይላል።  ቆይቶም ቁልቁል ይወርዳል።  ከዚያም ፊቱ ውሀ ውስጥ የተነከረ ይመስላል።  በመሀረብ ቢጠርገውም ተመልሶ ያው ነው።  አውቶብሱ  የደሴውን “የኳስ ንጉስ” አዲስ አበባ ሊያደርስ እያስገመገመ ነው። ፡ ከሚሴ መድረሻ ላይ ድንገት አንድ ሰው

“እሪሪሪሪ! ያገር ያለህ! ተዘረፍኩ! ጉድ ሆንኩ!”

እያለ መጮህ ጀመረ።  አውቶብሱንም  በጠበጠው… አመሰው።  ተሳፋሪው ተደናገጠ።  “ምንድ ነው! …ምንድነው!” ብሎ ሰውየውን መጠየቅ ጀመረ።  ሰውየውም ብር እንደጠፋው ተናገረ። አውቶብሱ ፍተሻ ላይ  ቆሞ ፊናንስ ፖሊሶች ጉዳዩ ተነገራቸው።  መንገደኛው  ወርዶ እንዲፈተሽ ተደረገ።  ተሳፋሪው እየተጠራ አንድ በአንድ ተፈተሸ…. ኪሱ፤ ቦርሳው፤ ጫማው ሳይቀር እየተበረበረ ነው።  የሙሉጌታ  ተራ ደረሰ።  አለባበሱም ደህና አይደለም።

    ሰውየው ከፈታሾቹ ጋር አብሮ በመሆን ነው ብርበራው የሚካሄደው።  ሙሉጌታን ሊፈትሹት ተዘጋጁ።  ፖሊሶቹ ሰውየውን “ስንት ብር ነው የጠፋህ?” አሉት።  ሰውየውም “700 ብር” አላቸው።  የዚህን ጊዜ ሙሉጌታ በጣም ደነገጠ።  ላቡ እንደውሃ በፊቱ ላይ ይሄድ ጀመር።  መናገር አቃተው።  ሰውየው የሙሉጌታን መደንገጥና ፊቱ በላብ መዘፈቁን አይቶ ለፖሊሶቹ “እንደውም ይሄ ሳይሆን አይቀርም የሰረቀኝ።  ደንግጧል።  ደግሞም ፊቱን አልቦታል።  “በደምብ ይፈተሽ”  አለ።  

     ሙሉጌታ ሲፈተሽ ኪሱ ውስጥ ብር ተገኘ።  ሲቆጠር 700 ነው።  በቃ “ሌባው ተያዘ” ተባለ።  ተያዘና ታሰረ።  በሁኔታው በጣም ስለተደናገጠ የሚናገረው ጠፋው።  “ብሩ የኔ ነው” ብሎ ማስረዳትና  ከየት እንዳመጣው መናገር እንኳን አቃተው።  በሁኔታው በጣም ስለተናደደ የሚናገረው ጠፋው።  ብቻ ዝም ብሎ ያልበዋል።  እጁ በድንጋጤ ይንቀጠቀጣል።  ላብ ሽቅብ የሚወጣ ቢሆን ሙሉጌታ ላይ ይታይ ነበር።

      አውቶብስ ውስጥ ያለው ተሳፋሪ አብዛኛው ሙሉጌታን  ያውቀዋል።  ሌባ እንዳልሆነ መስክሮ  ሊያስጥለው አልቻለም።  ምኪኒያቱ ኪሱ ሲፈተሽ ሰውየው ጠፋኝ ያለው ብር ሳይጨምር ሳይቀንስ ተገኝቷልና።  ከመፈተሹ በፊት ሰውየው “ይሄ ሳይሆን አይቀርም የወሰደው “ብሎ ተፈትሾ ብሩ እርሱ ኪስ በመገኘቱ ነገሩ ያለጥርጥር ተጠያቂ አድርጎታል።  አውቶብሱ ታስሮ በመቆየቱ ተሳፋሪው ተጉላልቶ ነበር።  ብሩ መገኘቱ ሲነገር አንዳንዶቹ አልሰሙም ነበር።  አንዱ ተሳፋሪ ሌላኛውን መጠየቅ ጀመረ “ብሩ ተገኘ?”

“አዎ”

“ከየት”

“ልጁ”

“የትኛው”

“ስፖርተኛው”

“ማን የሚባለው?”

“ሙሉጌታ”

“ያያ እከሌ ልጅ?”

“አዎ”

“ጉድድድ! ጉድ!.. ጉድ!..”

የእናቱ እድርተኞች ሰምተው ተገረሙ “ለካ ይሄ ልጅ የእጅ አመል አለበት” ብለው አዘኑ።  ሰሞኑን እነርሱ ቤት የሽኝት ግብዣ ላይ ተገኝተው መርቀውታል።  አሁን ደግሞ በሌብነት ተወንጅሎ ከፊት ለፊታቸው ቆሟል።  አፋቸውን በነጠላ ሸፍነው “አይ የሰው ነገር!” የሚሉ ይመስላሉ።  

      ሙሉጌታ በጣም ተደናግጧል።  መሬት ተሰንጥቃ ብትውጠው ደስታውን አይችለውም።  የሚያደርገው ነገር ጠፋው።  ድንገት ሮጠና ወደ ገደል ሄዶ ተፈጠፈጠ።  ግን በሀሳቡ ነው።  እንደዚያ ሆኖ እራሱን ቢያጠፋ ደስ ይለዋል።  ምክኒያቱም ተዋርዷላ።  በተከበረበት እና በነገሰበት ሀገር እንዲህ ዓይነት ነገር ይፈጠራል ብሎ አልገመተም።  የባሰ ያስደነገጠው ደግሞ ከዚህ በኋላ የሚመጣው ነገር ነበር።  በኢትዮጵያ ሬድዮ በዜና እወጃ “ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተመረጠው ተጫዋች አውቶብስ ውስጥ 700 ብር ሰርቆ ተያዘ” ተብሎ ሲነገር ታየው።  እረረረረረ!! አይደረግም።  ግን ተወንጅሎ ተይዟል።  ወሬውን ሀገር ሁሉ ይሰማዋል።  “ምነው በዚህ አውቶቡስ ባልመጣሁ” ብሎ ዕድሉን አማረረ።   ከዚህ በኋላ ወደ ደሴም አይመለስም።  ምን ያረጋል?  ከእንግዲህ ኳስ መጫወት አይችል።  የ700 ብር ሌባ ስለሚባል ደሴን አይረግጣትም።

     ገንዘቡ ያለአግባብ መወሰዱ ብቻ ሳይሆን እርሱም ቤተሰቡም እንዲሁም አድናቂዎቹ መዋረዳቸው  ሊቀበለው የማይችል ነገር ሆነበት።  ለኢትዮጵያ ቡድን ተመርጦ በክብር ከደሴ እንዳልተሸኘ እንዲህ ዓይነት ቅሌት ውስጥ መግባቱ አስደንግጦታል።  ሰውየው ጠፋኝ ያለው 700 ብር እርሱ ኪስ ሲገኝ ይሄ ሁሉ ተሳፋሪ  አይቷል።  ከነርሱ የበለጠ ምስክር  የለም።  ተሳፋሪውስ ቢሆን 700 ብር ያህል ሙሉጌታ ኪስ ይገኛል ብሎ እንዴት ይመን? ያን ጊዜ ኳስ ተጫዋች ደሞዙ 100 ብር እንኳ አይሞላም።  ነጋዴ ነው ትልቅ ብር የሚይዘው።  እናም  700 ብር  ሙሉጌታ ኪስ ከተገኘ ሊሆን የሚችለው ከሰውዬው ወስዶ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ተደረሰ።

 ሙሉጌታ እንደታሰረ ቆየ “ከዚህ ብፈታ ለብሄራዊ ቡድን አልሄድም ወደ ደሴም አልመለስም” ብሎ ወሰነ።  ምን ሊሆን እንዳሰበ አያውቅም።  ብቻ እዚህ ጉድ ውስጥ እንዴት እንደገባ ማሰብም አቅቶታል።  እርሱ ከነስጋቱ ራቅ  ብሎ ቆሟል።  ተሳፋሪው  ተሰብስቦ ያየዋል።   “ንጉሳችንን ስጡን” አይነት ይፈልጉታል።  ግን ንጉሳቸው ሌባ ተብሎ ተይዞባቸዋል።  አንዳንድ ተሳፋሪ “እርሱ ይታሰርና እኛ እንሂድ” በሚል እንድምታ እየጠየቀ ነው።  

        ገንዘቡ በኤግዚቢትነት ተይዞ እርሱ ይከሰሳል።  ምስክር አያሻውም።  ድፍን ተሳፋሪ ያየውና ያረጋገጠው ጉዳይ ነው።  ፖሊሶቹ በጣም ተጨነቁ።  ብዙዎቹ የሙሉጌታ አድናቂ ናቸው።  በችሎታው ገዝቷቸዋል።  ትላልቅ ጨዋታ ሲኖር ደሴ እየሄዱ ተመልክተዋል።  ብዙ ጊዜ  ሙሉጌታ በሚያስቆጥረው ግብ ተደንቀዋል።  የትናንቱ የኳስ ሜዳ ጀግና አሁን ግን በምስክር ፊት ሌባ ተብሎ ተይዟል።  ፖሊሶቹ ከሙሉጌታ የበለጠ ተጨንቀዋል።  ግን የሚያረጉት ነገር ጠፋቸው።  ሙሉጌታ ታሰረ።  ተሳፋሪው ወደ አውቶቡሱ እንዲገባ ተነገረው።  ምክኒያቱም እዚህ ቆይቶ ከሄደ አውቶብሱ መንገድ ላይ ለማደር ይገደዳል።  ተሳፋሪው “ንጉሳችንን መልሱልን” ብሎ ቢጠይቅም በሌብነት ስለተያዘ እንደማይሰጥ ተነገራቸው።

   መንገደኛው ተስፋ ቆርጦ ወደ መኪና ውስጥ ገባ።  ሹፌሩ ሞተሩን አስነሳው።  ተሳፋሪው  በመስታወት ከውጭ የቆመውን ዝነኛ ተጫዋች በሀዘን እየተመለከተው ነው።  የሚያደርገው ጠፍቶት መንገድ ላይ የተገተረው ወጣት “ወይኔ ሙሌ ጉድ ሆንኩኝ!!” በሚል ቁጭት ፈዝዞ ቆሟል።  አውቶብሱ ተንቀሳቀሰ።  ጎማው መሽከርከር ጀመረ።  ዝነኛው ጥሎት መንገዱን ተያያዘው።  ከፖሊሶቹ አንዱ ድንገት ሀሳብ የመጣለት ይመስላል።  እየሄደ ያለውን መኪና፡-

“ቆይ!… ቆይ! ቆይ…ብየሀለው!”

አንደኛውን ማርሽ ከሌላው እየቀያየረ ሊበር የነበረው መኪና  ሹፌር በመስታወት እያየ “ምን ቀረ ደግሞ?” ብሎ ፍሬን ያዘ።  ፖሊሶቹ መኪናው ጋር ደረሱና ተሳፋሪውን በሙሉ አስወርደው መኪናውን መፈተሽ ጀመሩ።  አለ የተባለ ቦታ ሁሉ በረበሩ ግን ምንም ሊያገኙ አልቻሉም።  ሰውየውም “ብሬ ተገኝቷል አይደል? ሌላ የጠፋ ነገር አለ እንዴ?” ብሎ በመገረም ይጠይቃቸው ጀመር።  መልስ ሳይሰጡት ፍተሻቸውን ቀጠሉ የሚገኝ ነገር ጠፋ።

   ፈታሾቹ ተስፋ ቆርጠው እየወረዱ ሳለ አንደኛው ፖሊስ ሰውየው ተቀምጦበት የነበረውን ወንበር  ትኩር ብሎ አየው።  መደገፊያው ከታች ቀዳዳ አለው።  እዚያ ስር የሆነ ነገር ተወትፎ አየ።  የተወተፈውን ነገር በሽቦ ስቦ አወጣው።  የኪስ ቦርሳ ነው።  ቦርሳውን ፖሊሱ ሲፈትሽ 715 ብር ተገኘ።  ብሩ መገኘቱን ሲሰማ ሙሉጌታ ፖሊሱ ላይ ጎል እንዳገባ ተጫዋች አቅፎና ተጠምጥሞ ይስመው ጀመር።  

  ሙሉጌታ ነፃ በመውጣቱ ሰው ሁሉ ደስ አለው።  የሚያደንቁት፣ የሚወዱት፣ በምርቃት ወደ ብሄራዊ ቡድን የሸኙት፣ ለትልቅ ደረጃ የሚጠብቁትና ደሴን ያስጠራል ብለው ተስፋ ያደረጉበት ልጅ  ከውርደት ተላቆ ነፃ ሆኖ በመገኘቱ ደስታቸው ወሰን አልነበረውም።  ፖሊሶቹ “ሰውየው መታሰር አለበት አንለቀውም” አሉ።  ምክኒያቱም ሰውየው በደምብ ሳይፈልግ ነው ጠፋኝ ያለው።  በዚያ ላይ 715 ጠፍቶበት ለምን 700 ይላል?   ተሳፋሪውንስ ለምን ያጉላላል? በሚል ነበር።

    ሙሉጌታ ቶሎ እንዲሄዱ ብሎ ሰውየው እንዳይከሰስ ተከራከረ።  ሰውየው ሙሉጌታን “ገንዘብ ጠፍቶብኝ ተደናግጨ አንተ ስትርበተበትና ላብ በላብ ሆነህ ሳይ የወሰድክብኝ መስሎኝ ነው” ብሎ ይቅርታ ጠየቀው።  በጭንቀት ተወጥሮ የነበረው ተሳፋሪ በደስታ እያወካካ አዲስ አበባ ገባ።  ከዓመት በኋላ ደሴን ለቆ አዲስ አበበ ከተመ።  የጊዮርጊስን 2 ቁጥር ማሊያ ለበሰ።  ለ12 አመት ያህል በክለቡ ነግሶ የብዙ ዋንጫ ባለቤት አደረገ።  ሙሉጌታ አሁን ኑሮውን በአሜሪካ አድርጎ እዚያው ከትሟል።  ያኔ ብሩ ባይገኝ ኖሮ እጣ ፈንታው ምን ይሆን ነበር?

የጄኔራሉ ቤት (ማሞ ወልዴ ደጋጋ)

የቢቢሲ ጋዜጠኞች ከሜክሲኮ ኦሎምፒክ የማራቶን አሸናፊው  ማሞ ወልዴ ጋር ቃለ ምልልስ እያደረጉ ነው።  ከርሱ ጋር ለሶስት ቀን ይቆያሉ።  የኢትዮጵያ አትሌቶች  በአበበ ቢቂላ ጀማሪነት ሶስት ጊዜ በተከታታይ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘታቸው አለም ስለተገረመና በሀገራቸው ጥሩ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል ተብሎ ስለተወራ “የአትሌቶች አያያዝ እንዴት ነው?” በሚል ዘገባ ለመስራት ፈልገው ነው የመጡት።  ማሞ ከሜክሲኮ ሜዳሊያውን ይዞ እንደተመለሰ  በአስራ አምስተኛው ቀን ነበር ጋዜጠኞቹ የመጡት።  አሁን በማሞ ህይወት ዙሪያ ዶክመንተሪ ፊልም እየሰሩ ነው።

     ጋዜጠኞቹ ትላንትና በልምምድ ሜዳ ላይ ነው የቀረፁት።  ዛሬ ደግሞ መኖሪያ ቤቱ እየቀረፁት ነው።  ቤቱ በጣም ምርጥ ነው።  ከኢትጵያ ህዝብ ኑሮ አኳያ  ጋዜጠኞቹ የማሞን ቪላ ቤት አይተው  ከውጤቱ አንፃር “ይገባዋል” ብለው ደምድመዋል።  ግቢው ሰፊ ነው።  ቤቱም የተለያዩ ክፍሎች አሉት።  ጋዜጠኞቹ ማሞ ቤቱን እያዞረ እንዲያሳያቸው ፈለጉና ጉብኝቱ ተጀመረ።  ስለእያንዳንዱ ክፍል እየጠየቁት ነው።  አስገራሚው ነገር ማሞም እንደጋዜጠኞቹ ቤቱን ያለማወቁ ነው።  አስጎብኚና ጎብኚ በቤቱ ሁኔታ ግራ ተጋብተዋል።  

ጋዜጠኞቹ የማሞን ታሪክ በፊልም ቀርፀው በቴሌቪዥን ሊያስተላልፉ ቢፈቀድላቸውም መንግስትን ያሰጋው ነገር አንድ ጉዳይ ነበር።  ማሞ የሚኖርባት ቤቱ ደሳሳ ነች።  እዚህ ቤት ውስጥ ፊልም ከተቀረፀና ለዓለም ከተላለፈ የኢትዮጵያን ገፅታ ያበላሻል ተብሎ ስለታሰበ የአንድ ጄኔራል ቤት  ተሰጠው።  ትዕዛዙ የመጣው ከላይ በመሆኑ ሰውየው ቤቱን ለማሞ በፍጥነት አስረከበ።  ነገሮች በጥድፊያ ስለተደረጉ ጄኔራሉ እቃቸውን ከቤት አላወጡም።

አንድ ቀን ከሰዓት ማሞ ከእንግዶች ጋር ሆኖ ደሳሳ ቤቱ ውስጥ እየተጫወተ ሳለ ሰዎች እንደሚፈልጉት ተነገረው።  ከአንደኛው በስተቀር ሌሎቹን አያውቃቸውም።  ሰውየው ትልቅ ባለስልጣን ናቸው።  “ሰለም ነህ ማሞ” አሉት።

“ደህና ነኝ…..ቤት ግቡ”

ሰዎቹ ወደ ግቢው ዘለቁ።  እኚህ ባለስልጣን ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ማሞ እንዴት እንደሚያስተናግዳቸው ግራ ገብቶታል።  ሶፋ ቢኖር እዚያ ላይ ያስቀምጣቸዋል።  ቤቱ ውስጥ ደህና ወንበር እንኳን አልነበረውም።  የግቢውን አጥር እንኳን ያጠሩለት የክብር ዘበኛ ወታደሮች ናቸው።  አቀባበል ካደረጉለት በኋላ ቤቱን ቀለም ቀቡለት አጥሩንም አስተካከሉት።

   ማሞ አሁን ግቢ ውስጥ የዘለቁትን ሰዎች ምን እንደሚያረጋቸው ግራ ገባው።  ለነርሱ የሚመጥን የተዘጋጀ ነገር የለም።  ግን ዝም ማለት የለበትም።  በድጋሚ “ወደ ቤት ግቡ” አላቸው።

“አንገባም”

“ቡና ይፈላል ምሳም ትበላላችሁ”

“ችግር የለም እዚሁ እናናግርህ”

“አሺ”

“በንጉሱ ትዕዛዝ የተሻለ ቤት እንዲሰጥህ ተወስኗል”

“ለእኔ?”

“አዎ ላንተ”

“በጣም ደስ ይለኛል”

“አሁን ከኛ ጋር ትሄዳለህ”

“የት?”

“ቤቱን ልታይ”

ማሞ እውነት አልመሰለውም።  ይዋሻሉ እንዳይል ባለስልጣን ናቸው።  ከሰዎቹ ጋር ወደቦታው ሄደ።  ቤቱን ሲያየው በፍፁም አላመነም “ይሄ ለኔ ነው?” ብሎ በመገረምና ባለማመን ጠየቃቸው።  እነርሱም የቤቱን ቁልፍ እየሰጡት።  “እዚህ ቤት አንድ ጀኔራል ይኖር ነበር።  ለጊዜው ሌላ ቦታ እስኪሰጠው ላመጣኸው ውጤት ቤቱ ላንተ በሽልማት መልክ ተሰጥቶሀል።  ውስጥ ያለውንም ዕቃ ተጠቀምበት” አሉት።  ወዲያውኑ ቤቱ በአስቸኳይ ቀለም እንዲቀባ ተደረገና ማሞ ገባ።  እርሱ እንደገባ በነጋታው የቢቢሲ ጋዜጠኞች መጡ።  ጉብኝቱ ቀጥሏል።  ማሞ ይሄ ነገር ይመጣል ብሎ ስላልጠበቀ አልተዘጋጀም።  ሳሎን የጀኔራሉ ፎቶ ተሰቅሏል ጋዜጠኞች “ይሄ ፎቶ የማነው?” አሉት።

“አርበኛ ናቸው”

“በህይወት አሉ?”

“ጦርነት ላይ ሞተዋል”

“በየትኛው ጦርነት”

“ማይጨው”

 የመጣለት ሀሳብ ይሄ ነበር።  ጄኔራሉ በህይወት አሉ።  ጥያቄው ድንገት ስለመጣ ሞተዋል ለማለት ተገደደ።  የጄኔራሉ የወታደር ጫማ ተደርድሯል ስለጫማዎቹ ጠየቁት አድርጎ እንዲያሳያቸው ጠየቁት አደረገ።  ጨማው ሰፊ ነበር ለርሱ የሚበቃው አልሆነም።  ልብስ እየቀያየረ ሊቀርፁት ፈለጉ።  ሰውየው ወፍራም ስለሆኑ ልብሱ ከማሞ ጋር የሚሄድ አልሆነም።  ነገሩ ለማሞ አስጨናቂ ሆነ።  ጋዜጠኞቹና ማሞ ግቢ ውስጥ እየተዘዋወሩ ነው።  የጄኔራሉ መኪና ቆማለች “ይህች መኪና ገዝተህ ነው ተሸልመህ?” አሉት።

“ገዝቼ ነው”

“ስንት ገዛሃት?”

“በቅናሽ ነው”

“እስኪ ግባና እየነዳህ እንቅረፅህ?”

ማሞ መኪና መንዳት ችግር አለበት “ዛሬ የመኪና መንዳት ፕሮግራም የለኝም” ብሎ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ።  

       የጄኔራሉ ወንድም ራቅ ወደ አለ ክፍለሀገር ሲሄድ መኪናውን እዚህ ግቢ ነበር የሚያቆማት።  አሁን ከጉዳዩ ስለተመለሰ ግቢ ውስጥ ያቆመውን የራሱን መኪና ሊያወጣ መጣ።  በሩን አንኳኳ፤ ማሞን ለማስተናገድ ከተመደቡት ሰዎች አንዱ  በሩን ከፈተ።  ሰውዬው ወደ ውስጥ ሲገባ “ማንን ፈልገህ ነው?” አለው።

“መኪና ልወስድ ነው”

“የምን መኪና?”

“መኪናዬን ነዋ !!!”

“የትኛው?”

“ይሄኛው”

“ይሄማ የማሞ መኪና ነው”

“እንዴት ሆኖ?”

“ንጉሱ ነው የሰጡት”

“የኔን?”

“አዎ”

“እኔ ሳልጠየቅ?”

 ሰውዬው በነገሩ ግራ ተጋባ ለማን አቤት ይባላል ብሎ ግራ ተጋባ።  በሁለተኛው ቀን የጄኔራሉ ሚስት ዕቃ ልትወስድ መጣች።  ከአስተናጋጁ አንዱ ተደብቆ በሬድዮ ለአለቃው ነገረው።  ከግቢው ውጭ ለዚህ የተዘጋጁ ሰዎች ስላሉ ሴትየዋ በአክስትነት አዘጋጇትና ለጋዜጠኞቹ  ተነገራቸው።  ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ ጋዜጠኞቹ ስለማሞ አስተዳደግ አክስት ተብዬዋን ጠየቁ።  ወተት እየጠጣ እንዳደገ።  ሩጫ ጎበዝ እንደሆነ አስረዳች።  የተነገራትም እንደዚህ እንድትል ነበር።  ወዲያውኑ ከግቢ አስወጧት።  ከ3 ቀን በፊትም ድንገት መጥተው ነው ሴትዬዋን ከነባለቤቷ “በአስቸኳይ ልቀቁ የተባሉት “አሁን ደግሞ የማታውቀውን ምስክርነት ሰጥታ ቶሎ ከግቢ ሸኟት።  ሴትዬዋ “እዚህ ግቢ ምን እየተደረገ ነው?” ብላ አሰበች።  ማሞንም ልታናግረው ፈለገች ግን አልተሳካላትም።

   በሶስተኛው ቀን ጋዜጠኞቹ ተጨማሪ ቀረፃ ያደርጋሉ።  ስለ ማሞ የሚያውቁ አንዳንድ ሰዎችን ያነጋግራሉ።  ከምሳ በኋላ ነው የሚሄዱት።  በጠዋት አትክልት ሲያጠጣ  ግቢ ውስጥ ያሉትን ውሻና ከብት ሲንከባከብ ተቀረፀ።  ጄኔራሉ ሁለት ፈረሶች ግቢ ውስጥ ነበራቸው።  አንዱ ያልተገራ ነው።  ማሞን ፈረሱ ላይ ሆኖ ሊቀርፁት ፈለጉ።  ሌጣውን ፈረሱ ላይ ፈንጠር ብሎ  ጀርባው ላይ ወጣ።  ነገር ግን ፊልሙ ሲቀረፅ ማሞ ፈረሱ ላይ አልነበረም።  ፈረሱ ያልተገራና አስቸጋሪ በመሆኑ እዚህና እዚያ ተንፈራግጦ ማሞን አንስቶ አፈረጠው።  ባለቤቱ ፈረሱን ገና ያልገራው መሆኑን ማሞ አላወቀም ነበር።  ቢጎዳም “አንዳንዴ ይሄ ፈረስ ያስቸግረኛል።  ግን ከምወደው አንዱ ነው።  በልጅነቱ ነው የገዛሁት” አላቸው።  በሌላኛው ፈረስ እንዲቀረፅ ነገሩት።  ከዚያ ይልቅ የሚበላ ነገር እየሰጣቸው ተቀረፀ።  ያኛውን ግን ብዙም አልተጠጋውም።

     የምሳ ሰዓት ደረሰና እየተበላ ቀረፃ ተካሄደ።  የፈረንጅና ሀበሻ ምግቦች በቡፌ መልክ ቀረበ።  ለዚሁ ሲባል የማሞን መስተንግዶ የሚመሩት ሰዎች አቅርበውለታል።  ወጥቤቶቹም ከትላልቅ ሆቴል የመጡ ናቸው።  ማሞ ፈረንጆቹን ለማስተናገድ ምንም አቅም የለውም።  ላድርግ ቢል እንኳን ይሄን ሁሉ ወጪ እንዴት ይችለዋል? ማን እንደሸፈነ ባይነግሩትም ከበላይ አካል ነው ስለተባለ ነገሩን በፀጋና በደስታ ተቀብሎታል።  ምሳ እየተበላ ሰሞኑን የተቀረፀው የማሞ ፊልም እየታየ ነበር።  በእንግሊዝ ሀገር ስለእርሱ በጋዜጣ ላይ የወጣውን ፎቶግራፎችን ተመለከተ። ፎቶዎቹ እነርሱ አንስተው የላኩት ነበሩ። ጋዜጠኞቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ጥሩ እንክብካቤ ስለተደረገላቸው ነው ውጤት የሚያመጡት በሚል እንደማሳያነት ተመለከቱና ሌሎችንም አትሌቶች በዚህ ዓይነት እንደሚንከባከቧቸው አመኑ።

የከሰዓቱ ቀረጻ ወደተለያየ ቦታ ሄደው  ማሞ ከህብረተሰቡ  ጋር ያለውን ግንኙነት ለመቅረፅ ቀጠሮ ይዘዋል።  ለሚቀረፁት ሰዎች መባል ያለበትን አስተናጋጆቹ በቅድሚያ ይነግሯቸዋል።  ማሞ ወደ ቀድሞ ሰፈሩ ሲሄድ አስተናጋጆቹ ከለከሉት።  አስተናጋጆቹ ከማሞ ወገን ሆነው ነገሮችን የሚቆጣጠሩ ናቸው።  ማሞን አጣድፈው ነው ወደ አዲሱ ቤቱ ያስገቡት።  ከቀድሞ ቤቱ ዕቃውን አላወጣም ነበር።  በቀረፃና በሌላም ጉዳዮች ሲዋከብ ወደ ቀደሞ ቤቱ አልሄደም።  አሁን ግን በዚህ አጋጣሚ ወደ ቤቱ ደረስ ሊል ፈለገ።  ከአስተናጋጆቹ ለአንዱ “ዕቃዎቼን ከቤት ላምጣ?” አለው።

“ምን ያደርግልሃል? የተሟላ ነገር አለህ”

“አንዳንድ የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ”

“ለምሳሌ ምን”

“ፎቶዎች….ሌላም”

“ሌላ ፎቶ ትነሳለህ”

ነገሩ ለማሞ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም አሁን  በሽልማት የተሰጠው ቤት ከምንም ነገር ይበልጥበታል።  ነገር ግን የቀድሞ ቤት ውስጥ ያሉት ከበፊት ጀምሮ የተነሳቸው ፎቶዎች፣ የስፖርት ትጥቆች፣ ሌላም የሚፈልጋቸውን ዕቃዎች ብወስድ ምን ችግር አለበት ብሎ አሰበ።  እቃውን ለመውስድ  አንድ ዘዴ መጣለት ለአስተናጋጆቹ “ጋዜጠኞቹ የቀድሞ ቤቴን ማየት ይፈልጋሉ” አለ።

“አይቻልም”

“ለምን”

“ካሳየህ ወይም ከነገርካቸው አሁን የተሸለምከውን ቤት ታጣለህ”

“ምን ችግር አለው?”

“ምንም”

“ላሳያቸዋ!!”

“ቤቱ የለም”

“እንዴት”

“ለሌላ ተሰጥቷል”

“ዕቃዬስ?”

“ሌላ ቦታ ስለተቀመጠ በተመቸህ ጊዜ ትወስዳለህ”

ማሞ በነገሩ ቢስማማም እነዚህ ጋዜጠኞች የድሮ ቤቱን ቢቀርፁለት ጥሩ እንደሆነ አሰበ።  ቤቱ ያለመቀረፁ ምን ያህል ጉዳት እንዳለው  አልተገነዘበም።  ጋዜጠኞቹ በማሞ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነውን ፊልም ቀርፀው ጨረሱና በስፖርተኞች አያያዝ  የኢትዮጵያ መንግስትን አድንቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።

    አንድ ቀን ጠዋት ማሞ በአዲሱ ቤቱ ገንዳ ውስጥ በሞቀ ውሃ ሰውነቱን እየታጠበ ነው።  በሚያምረው ገንዳ እየተንፈላሰሰ ብዙ ነገር አሰበ።  በእንዲህ ዓይነቱ ገንዳ የሚጠቀመው ውጭ አገር ለወድድር ሲሄድ ነው።  ከዚያ ውጭ የገንዳ ሻወር አያገኝም።  ገንዳ ውስጥ ሆኖ ያችን ደሳሳ ቤቱን አሰባት።  ሻወር ሲፈልግ በባልዲ ውሃ አምጥቶ ብረት ምጣድ ላይ በጣሳ ሰውነቱ ላይ እያፈሰሰ ነው የሚታጠበው።  ዛሬ ያቺ ቤቱ ትዝ አለችው።  እዚያው ገንዳ ውስጥ ሆኖ  ማሞ ስለቤቱ አሰበ።  ከአቅሙ በላይ የሆነ መኖሪያ ነው የሰጡት።  የክፍሎቹ ብዛት፣ የግቢው ስፋት፣ የቤቱ ውበት የሚያስገርም ነው።  ይሄን ቤት ሽጦ መለስተኛ ቤት ሰርቶ በቀረው ገንዘብ ሊጠቀምበት ፈለገ።  ይሄን ሀሳቡን ቀየረና ማከራየት እንደሚቻል ወሰነ።  ሊያከራየው ፈለገ።

   ለማንኛውም የሚቀርቡትን ጓደኞቹ ነገ ስለቤቱ ሁኔታ ያዋያቸዋል።  ዛሬ ቤቱ ትልቅ ግብዣ ጠርቷል።  በስጦታ ያገኘውን ቤት የሚያስመርቀው ዛሬ ነው።  ጓደኞቹንና የቅርብ ዘመዶቹን እዚህ ግብዣ ላይ እንዲገኙለት ጠርቷል።  ክቡር ዘበኛ ያሉት በቅርቡ የሚያውቃቸው ወዳጆቹ ሙዚቃ ሊጫወቱለትና ግብዣውን ሊያደምቁለት እንደሚመጡ ነግረውታል።

   ቤቱን ከትናንት ጀምሮ እያሰማመረ ነው።  የጄኔራሉ ፎቶ ተነስቷል።  ይሄ ትልቅና ዘመናዊ ቤት የማሞ መሆኑ ተረጋጧል።  አሁን  ግድግዳዎች በማሞ ፎቶዎች ተሞልተዋል።  በሜክሲኮ ኦሎምፒክ አሸንፎ ሜዳሊያ ሲቀበል፣ ከንጉሱ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጥ፣ በአዲስ አበባ አቀባበል ሲደረግለትና  ሌሎችም የማሞን ድል የሚገልፁ ፎቶዎች  ቤቱን አድምቀውታል ሜዳሊያውንም በሳሎን ግድግዳ ላይ ተሰቅሏል።

     ዛሬ ግን ሜዳሊያውን ያወርደዋል።  እንግዶች ከመምጣታቸው በፊት የማዕረግ ልብሱን ይለብስና ሜዳሊያውን በደረቱ ላይ ያኖረዋል።  ከዚያም በማራቶን እንዴት እንዳሸነፈ ለተጋባዦቹ ገለፃ ያደርጋል።  ይሄን ግብዣ እርሱ ቢጠራም አብዛኛው ወጪ በጓደኞቹ ተሸፍኗል።  ሽንጥ ስጋ ገብቷል።  ተጨማሪ በጎች ተገዝተዋል።  ከምግብ በኋላ ለማወራረጃ የሚያስፈልግ ነገር ሁሉ ተሟልቷል።  አንዳንድ ወዳጆቹ በጊዜ መጥተው ምሳ እስኪደርስ ከማሞ ጋር እየተጫወቱ ነው።  ቤቱን እያዞረ አስጎበኛቸው።  እነርሱም በጣም ተደነቁ።  አንደኛው ባልደረባው።  “በኦሎምፒክ ስላሸነፍክ ነው ይሄን የመሰለ ቪላ ቤት የተሰጠህ?” አለው።

“አዎ”

“ለአበበ ለምን አልተሰጠውም?”

“መስጠታቸው አይቀርም”

“እንደርሱ ነው?”

“ይመስለኛል ወይምን መሸለም ከአሁን ጀምረው ይሆናል”

“እኔ ብሮጥና ባሸንፍ እንዲህ ዓይነት ቤት ይሸልሙኛል?”

“አዎ”

“በል እንግዲህ ነገ ሩጫ ጀምራለሁ”

 የምሳ ሰዓት እየተቃረበ እንግዶችም በብዛት ወደ ቤት እየገቡ ነው።  ጭፈራውን የሚያደምቁ ሰዎች መጥተዋል።  ሁለት ሰዎች ከውጭ ሆነው እያንኳኩ ነው።  አንድ ሰው ከፈተላቸው “ግቡ” አላቸው።

“አንገባም”

“ሌሎች እንግዶች እኮ እየገቡ ነው”

“እዚሁ እንሆናለን”

“ምሳ ደርሷል እኮ”

“ማሞን ጥራልን”

“ከእንግዶች ጋር ነው”

“ፈልገነው ነው”

“ግቡና አናግሩታ”

“ግድ የለም እዚህ  ጥራልን”

ሰውዬው እንዲገቡ ቢጎተጉታቸውም ወደ ውስጥ አልዘለቁም።  ማሞን ሊጠራው ሄደ።  እርሱ ግን በመስተንግዶው ተወጥሮ ስለነበር ፈላጊዎቹን ገብተው እንዲያነጋግሩት ላከባቸው እነርሱም ለመግባት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው አንደኛ ስሙን ሰጠውና ለማሞ እንዲነግረው ላከው።  ማሞም  ስሙን ካየ በኋላ ይሄን ሰውዬ ያውቀዋል።  ምን ፈልጎ ነው የመጣው? በግብዣው ጥሪ አልተደረገለትም።  ይሄን እያሰላሰለ በር ላይ የቆሙትን ሰዎች ሊያናግር ወጣ አንደኛው “ልናናግርህ ፈልገን ነው” አለው።  

“ቤት ግቡና እናውራ”

“እዚሁ መነጋገር እንችላለን”

“ምንድ ነው ጉዳዩ?”

“ቤቱን ልቀቅ ተብለሃል”

“እየቀለዳችሁ ነው”

“አልቀለድንም”

“ማነው ልቀቅ ያለው”

“ተወስኗል”

“ቤቱ እኮ የኔ ነው”

“ማነው የሰጠህ?”

“ንጉሱ”

“እንኳን ለአንተ ለአበበ ቢቂላም አልተሰጠም”

“ቤቱ ለእኔ እንደተሰጠኝ ምስክር አለኝ”

“ምንም ምስክር አያስፈልግም።  ቤቱ ያንተ ለመሆኑ በሰነድ የተላለፈ ነገር አለ?”

“ጋዤጠኞቹ ምስክር ናቸው”

“የሚበቃህን ያህል ቤቱ ውስጥ ተንፈላሰሀል።  አሁን ውጣ”

“ወጥቼስ? “

“ወደ ቀድሞ ቤት ትገባለህ”

“ቤቴ እኮ ለሌላ ሰው ተሰጥቷል”

“ለማንም አልተሰጠም”

“እቃዬም እንደወጣ ተነግሮኛል”

“ስትሄድ ሁሉንም ነገር ታገኛለህ።  አሁን ይሄን ልቀቅ”

“አለቅም!”

“ችግር ውስጥ እንዳትገባ”

 ማሞ ማስጠንቀቂያውን ሰምቶ ለጊዜው ከቤቱ ባይወጣም የደህንነት ሰዎች መጥተው “ቤቱ ለአስቸኳይ እንግዳ ስለሚፈለግ በቶሎ ውጣ” የሚለው ትዕዛዝ ስለመጣ ከዚህ በኋላ ምን እንደሚከተል ስላወቀ በድራማው እያዘነ ወደ ደሳሳው ቤቱ ተመለሰ።  በነገሩ በጣም ተከፋ።

በሌላ ቀን ጓደኞቹ አገኙት።  በተለይ አንደኛው ይቀርበዋል።  ብዙ ሀሳብም የሚያማክረው ለእርሱ ነበር።  ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ተገናኝተው አያውቁም።  ጓደኛው “አለፈልህና እኛንን ረሳኸን አይደል ?” አለው።

“ምን ተገኘና ረሳሀለሁ”

“ምን የመሰለ ቤት አገኘኽ”

“የምን ቤት?”

“የተሰጠህ”

“ቲያትር ሊሰሩበት ነው”

“የምን ቲያትር?”

“በነፍሴ ተጫወቱብኝ”

“እንዴት ?”

“አሳይተው ነሱኝ”

ጓደኛው ተገረመ እንደገናም አዘነ።  የተደረገውን ነገር አንድም ሳያስቀር ማሞ ለጓደኛው አጫወተው።  ጓደኛውም፡-

“ለምን አትጠይቅም?”አለው

“ማንን? “

“የበላይ አካል”

“የሰጡኝ እነርሱ ናቸው”

“እና”

“የወሰዱትም እነርሱ ናቸው”

“ለንጉሱ ለምን አትናገርም?”

“ምን ብዬ?”

“ተወሰደብኝ ብለህ”

ጓደኛውና ማሞ ለንጉሱ የሚፁፉበትን ደብዳቤ ማዘጋጀት ጀመሩ።

ደብዳቤው ውስጥ ከተፃፉት ነገሮች ውስጥ “…..ቤቱን ተነጥቂያለሁ፣ ተለዋጭ ቤት ይሰጠኝ፣ ግማሹ ቤት ይሰጠኝ፣ በሚቀጥለው ኦሎምፒክ በትጋት እንድሮጥ ተመጣጣኝ ቤት ይሰጠኝ…..” የሚሉ ተካተውበታል።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች እንደሄዱ በነጋታው አንድ ባለስልጣን ቤቱ መጥቶ ነበር “ማነው ይሄን ቤት የሰጠህ?” አለው።

“ንጉሱ ናቸው”

“ለሌሎች ለምን አልተሰጠም?”

“እርሱን አላውቅም”

“ይሄ ቤት ይፈለጋል”

“ምን ማለት ነው?”

“ቤቱን መልቀቅ አለብህ”

“ለምን?”

“ሌላ ቤት እኔ አሰጥሃለሁ”

“ሌላ ቤት አልፈልግም ይሄኛው ተስማምቶኛል”

   ማሞ በሁኔታው ግራ ተጋብቶ የርሱ አስተናጋጅ ለነበሩት በስልክ ደውሎ “አንድ ሰው መጥቶ ቤቱ ይፈለጋል አለኝ” ብሎ ነገረው።

“ማነው?”

“ባለስልጣን ነው”

“ስሙ ማን ይባላል”

(ማሞ ስሙን ነገረው)

ሰውየው እንዳትወጣ ብሎ ነገረው።  አሁን ያንን ባስልጣን አሰበ እርሱ “ይሄን ልቀቅና ሌላ ቤት ልስጥህ ነው” ያለው።  ያኔ እርሱን እሺ ብዬው ቢሆን ጥሩ ነበር ብሎ አሰበ።  ሌላም ነገር አሰበ።  ጋዜጠኞቹ የድሮውን ቤት አሳይቷቸው ቢሆን ኖሮ ሌላ ጥያቄ ስለሚያነሱ ምናልባት ይሄን ፍራቻ ትልቁን ቤት አይነጥቁትም ነበር።  አሁን ሁሉ ነገር አልፏል።  የደህንነት ሰዎችም ከቤቱ ሲያስወጡት አስጠንቅቀውታል።  ስለዚህ ጉዳይ ለማንም ቢያወራ ችግር እንደሚፈጠርበት አስረግጠው ነግረውታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top