በላ ልበልሃ

ሕዝብ ለሕዝብ የማን ነው? ያልተቋጨው ውዝግብ

በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር አማካኝነት የምትታተመው ብሌን መጽሔት በቅጽ 9፣ ቁጥር 2 (ነሐሴ 2009) “የሕዝብ ለሕዝብ ዝግጅት ጅማሮ” በሚል በደራሲ አያልነህ ሙላት የተጻፈ ዘለግ ያለ ጽሑፍ አስነብባለች። የሕዝብ ለሕዝብ መነሻ ሀሳቡም ሆነ በሙዚቃዊ ድራማው ውስጥ የሚገኘው “አደይ አበባ” የተሰኘ ታሪክ የእሱ የፈጠራ ታሪክ መሆኑን ደራሲ አያልነህ ገልጿል። 

ይህን ጽሑፍ መነሻ በማድረግ፣ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በሹመታቸው ማግስት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በጽሕፈት ቤታቸው ጠርተው ስልጠና በሰጡበት ወቅት “የሕዝብ ለሕዝብ ዓይነት ሥራ መስራት እንዴት አቃታችሁ? እናንተ እያላችሁ በሲዳማና በወላይታ ሕዝብ መካከል እንዲህ ዓይነት እልቂት ይፈፀማል?” ማለታቸውን ተከትሎ በብስራት ሬዲዮ 101.1 ኤፍ. ኤም ዘወትር እሑድ ከ6 ሰዓት ጀምሮ በሚተላለፈው ‘ኪነ-ብስራት’ የሬዲዮ ፕሮግራም አያልነህ ሙላት እና ኃይሉ ፀጋዬ ተጋብዘው ሰፋ ያለ ሀሳብ ሰንዝረዋል። በዚህ ፕሮግራም ሁለቱም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አለመጋበዛቸውን ጨምሮ ስለሕዝብ ለሕዝብ የኪነት ቡድን አንዳንድ ጉዳዮችን አንስተዋል።

በወቅቱ እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎችን አቅርቤላቸው ጋሽ አያልነህ በብሌን መጽሔት ላይ የተናገረውን በራዲዮም ደግሞታል፡፡ ኃይሉ ፀጋዬ በበኩሉ በዚያን ጊዜ በአቶ አያልነህ ሥር ተቀጥሮ ይሰራ እንደነበርና የሥራው ባለቤት አቶ አያልነህ ሙላቱ መሆኑን እንደሚያውቅ መናገሩ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ታዛ መጽሔት በቅፅ 2፣ ቁጥር 20 (ሚያዝያ 2011 ዓ.ም) እትሟ “ታደሰ ወርቁ ብዙ የማያወራ ግን ብዙ የሠራ ጠቢብ” በሚል ደራሲና ተርጓሚ ዓለማየሁ ገ/ሕይወት ከታደሰ ወርቁ ጋር ያደረገውን ቃለ-መጠይቅ አነበብኩት። በዚህም ቀደም ሲል ብዙ ስላልተወራለት ዘርፈ-ብዙ የኪ-ነጥበብ ባለሙያ ታደሰ ወርቁ ሥራና የሕይወት ታሪክ ተገነዘብኩ። ወደሚኖርበት ሃገር አሜሪካ ቨርጂኒያ ደውዬም በጉዳዩ ዙሪያ አነጋገርኩት። የሕዝብ ለሕዝብን ትርኢት ወደ መድረክ ያመጣውም እርሱ መሆኑን ገለጸልኝ። አቶ ታደሰንም ሆነ አቶ አያልነህን ቃለመጠይቅ ባደረግኩበት ወቅት ሁለቱም እንደ እማኝ ያቀረቡት በወቅቱ የሕዝብ ለሕዝብ ብሔራዊ ኮሚቴ ጸሐፊ የነበረውን አቶ ባይለየኝ ጣሰው (ዛሬ ዶክተር) ነበር። የዚህ ቃለ-መጠይቅ ዓላማ አንባቢው የራሱን ግንዛቤ እንዲወስድ ማገዝ ነው።

*** ***

ከዶ/ር ባይለየኝ ጣሰው ጋር በሕዝብ ለሕዝብ ኢትዮጵያና ሌሎችም ተዛማጅ ሙያዊ ጉዳዮች ላይ አውርተናል። ዶ/ር ባይለየኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ነው። የትውልድ ስፍራው ጎንደር ሲሆን፤ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዚያው በጎንደር ተከታትሏል። ከዚያም ወደአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የመጀመሪያ ዲግሪውን በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ፣ የማስተርስ ዲግሪውን በእንግሊዝኛ ሥነጽሑፍ (ጥናቱን ደግሞ በፎክሎር ላይ አድርጓል) እንዲሁም የዱክትርና ዲግሪውን በባህላዊና ማኅበራዊ አንትሮፖሎጂ ተቀብሏል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህል አካዳሚ ውስጥ ተመራማሪ ሆኖ እየሰራ ነው።

*** ***

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀህ የት ተመደብክ?

ቢኤ ዲግሪዬን እንደተቀበልኩ በኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ቤት ነው የተመደብኩት። በወቅቱ እኛን ወደ ኢሠፓ ይወስዱናል ብለን አልጠበቅንም ነበር። ከዚያ ኢሕአዴግ ሲመጣ ወደባህል ሚኒስቴር ተመደብኩ። በባህል ሚኒስቴር ትንሽ ቆይቼ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዘዋወርኩ።

ወደ ውይይታችን አብይ ጉዳይ እንግባና ወደሕዝብ ለሕዝብ ሀገር አቀፍ ዝግጅት እንዴት ገባህ?

ኢሠፓ ውስጥ በርዕዮተ ዓለም ዘርፍ እንድሰራ ነበር የተመደብኩት። እዚያ እንደገባሁ የምስጋና ዝግጅት እየተዘጋጀ ነበር። ድርቅ በገጠመን ጊዜ የዓለም ህዝቦች ተረባርበው ስለታደጉን ኢትዮጵያን ለመወከል የሚችል እንዲሁም ባህላችንን ሊያሳይ የሚችል (ምክንያቱም ይህች ሀገር በባህሉ ዘርፍ ሀብታም ስለሆነች) የምስጋና ፕሮግራም ለማዘጋጀት ነው እንግዲህ ሕዝብ ለሕዝብ የተዘጋጀው። “ሕዝብ ለሕዝብ” የሚለው ስያሜ ከዚህ የመነጨ ይመስለኛል። ይህ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ በመንግሥት እና በፓርቲው ታምኖበት እግረ-መንገዱንም የገፅታ ግንባታ ተከሂዷል። የፖለቲካ ጉዳይም አለው፤ ለነገሩ እኔን የሚመለከተው ጉዳይ ግን የባህሉ ጉዳይ ነው። በዚህ ምክንያት ነው ከሕዝብ ለሕዝብ ጋር የተገናኘሁት።

በወቅቱ በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የተደረሰ “በኩር” የተሰኘ የተውኔት መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ወድቋል ይባላል። ለምን ወደቀ? እነማንስ ሳንሱር አደረጉት?

እንግዲህ እኔ መጀመሪያ በባህል ዘርፍ እንደተመደብኩ የቅርብ አለቃዬ አቶ አያልነህ ሙላቱ ነበር። በፓርቲው ጽሕፈት ቤት የባህል ጉዳይ በእርሱ ሥር ነው የነበረው። ከእሱ ጋር ተመድቤ ስሰራ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄንን ድርሰት “እስቲ እየው” ብሎ አያልነህ ሰጠኝ። አምስት እና ስድስት ገጽ ይሆናል። ያን “በኩር” የተባለውን ድርሰት መነሻ ሥራ በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ እንደጣለው ገልፆ ነው እንዳየው የሰጠኝ። በወቅቱ ማንበቤንና ጥሩ ድርሰት እንደነበር አስታውሳለሁ። በኔ ሚዛን ማለት ነው። በመድረክ እንዴት ይተረጎማል? የሚለውን የሙዚቃ ባለሙያ ስላልሆንኩ፤ የድርሰትም የኪሮግራፊ ሰውም ስላልሆንኩ ይከብደኛል። ግን ይዘቱ ኢትዮጵያን ጠቅልሎ የያዘ ነው። ሚስጥራዊነት ያለው እና ስሜትን የመያዝ ከፍተኛ ኃይል ያለው ነው። በወቅቱ ለአቶ አያልነህ ሙላቱ የሰጠሁት መልስም ይኸው ነበር።

በሬዲዮ ፕሮግራማችን ላይ ውይይት ስናደርግ ጋሽ አያልነህም ተገኝቶ ነበር። ለኛ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ሲቀርብ ጋሽ አያልነህ “አደይ አበባ” የሚለው ሙዚቃዊ ድራማ ደራሲ እሱ እንደሆነ ሲናገር ይደመጣል። “አደይ አበባን” በተመለከተ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር አማካኝነት በምትታተመው ብሌን መጽሔት ቅጽ 9፣ ቁጥር 2  (ጥር 2009 ዓ.ም) “የሕዝብ ለሕዝብ ጅማሮ” በሚል ርዕስ በአቶ አያልነህ ሙላቱ የተጻፈው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፣

“ታህሳስ 15 ቀን 1978 ዓ.ም የተካሄደው የባህል ንዑስ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ምን ዓይነት የኪነ ጥበብ ዝግጅት ይቅረብ? የሚል መወያያ ነጥብ ለቀጣዩ ስብሰባ ይዘው የሚመጡ ባለሙያዎች ተመደቡ። እነዚህ ባለሙያዎች ያቀረቡት ቢጋር ታህሳስ 1978 ዓ.ም. በኮሚቴው ስብሰባ ላይ ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ የዝግጅቱ ዓይነት ሙዚቃዊ ዳንስ ድራማ ይሁን ተባለ። ከዚያም ድርሰቱን መንደርደሪያ ሃሳብ አድርጎ የሚያቀርብ በባህል ንዑስ ኮሚቴ የሚመራ ቡድን ተቋቋመ። ይህ ኮሚቴም ታህሳስ 24 ቀን 1978 ዓ.ም. ቢጋሩን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ተወሰነ። ቢጋሩ በኮሚቴው እንዲዘጋጅ ቢወሰንም ድርሰቱን በስብሰባ መጻፍ አስቸጋሪ በመሆኑ ኮሚቴው ተነጋግሮ በተስማማበት መሰረት የአንድ ሙዚቃዊ ድራማ መነሻ ድርሰት በባህል ንዑስ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተዘጋጅቶ (ማለትም በአያልነህ ሙላት) ታህሳስ 24 ቀን 1978 ዓ.ም. ለውይይት ቀረበ”

ይላል። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ የምታውቀውን ንገረን?

እንግዲህ የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን “በኩር” የሚለው ድርሰት ከወደቀ በኋላ ሌላ ድርሰት ያስፈልግ ነበር። መነሻ ሀሳብ ማለት ነው። ሙዚቃዎቹ ተከታታይ ሆነው ሳያቋርጡ የሚቀርቡበት እንደዛ ዓይነት ነገር ነው የሚያስፈልገው። እኔ በወቅቱ በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ ቃለ-ጉባኤ ያዥ ነበርኩኝ። ሁሉንም አውቃለሁ። አንድ ሰኞ ቀን አቶ አያልነህ ጉባኤ አዳራሽ ስብሰባ ጠራን። 11 ሰዓት አካባቢ እኔ እዚያው ሰራተኛ ነኝ። ከውጭ አቶ ተስፋዬ ለማ፣ አቶ ሙላቱ አስታጥቄ፣ አቶ ታደሰ ወርቁ ነበሩ። ተከታታይነት ያለው ሙዚቃና የኢትዮጵያን ባህል የሚያሳይ ስራ እንዲቀርብ ስለሚፈለግ ሀሳብ አቅርቡ ተባለ። በዚህ ጊዜ እንዲህ ቢሆን እሚሉትን ሀሳብ ሲያቀርቡ እኔ ቃለ-ጉባኤ እይዛለሁ። ዋናው ኪሮግራፊ፣ ጭፈራው፣ እስክስታው ላይ የሚተረጎም ስለሆነ ድርሰቱ፣ ይሄ ደግሞ ያገባው የነበረው የበለጠ የኬሮግራፊ ባለሙያውን ነበር። ይህ ለአቶ ታደሰ ወርቁ ተነገረው። በዚህ አጋጣሚ የምትፈቅድልኝ ከሆነ የምናገረው ነገር አለ።

እፈቅድልሀለሁ መናገር ትችላለህ፡፡

ታደሰ ወርቁ ማለት እጅግ ኢትዮጵያን ያመለጣት ከያኒ ነው። በኔ ግምት እና አስተውሎት ኢትዮጵያ ካጣቻቸውና እንደዋዛ ወጥቶ በዛው ከቀረ ሀገሪቱ ልታጣቸው ከማይገቡ ሰዎች ትልቁ ነው። የእሱ ከሃገር ወጥቶ መቅረት ሁልጊዜ ይፀፅተኛል። ያኔ ታደሰ ወርቁ የተሰማውን ሃሳብ ይሰጥ ነበር። ሙላቱ አስታጥቄ “ከቅዱስ ያሬድ ይጀምር” በሚል ሀሳብ ሰጥቷል። አቶ ተስፋዬ ለማ ደግሞ ከባህል አኳያ ጥልቅ የሆነ አስተያየት ነበራቸው። ስብሰባው እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ ቀጥሎ መጨረሻ ላይ ሀሳቦቹ በጽሑፍ እንዲቀርቡ ለእኔ ተሰጠኝ። ታደሰ ወርቁ እና ሰዓሊ ታደሰ መስፍን በየክፍለ-ሀገሩ እየተዘዋወሩ የባህል ድምፃውያንና ጨፋሪዎችን በቪድዮ ጭምር ቀርፀው አምጥተዋል። ቪዲዮው ወደ 39 ሰዓት የሚወስድ ነው። ሕዝብ ለሕዝብን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ያደረገው እሱ ነው። ርዕሱ ብዙ ውይይት ከተደረገበት በኋላ “አደይ አበባ” እንዲባል ሆነ። “አደይ” ማለት በትግርኛ “እናት” ማለት ነው። “አበባ” የሚለው ልጅን ስለሚያሳይ፤ አደይ አበባ ማለት እናትና ልጅን የትናንትናዋን እና የዛሬዋን ኢትዮጵያ የሚገልፁ ስለሆነ ርዕሱ ተቀባይነት አገኘ። ቃለ ጉባኤው ተፅፎ መጣና ለአለቃዬ ለአያልነህ ሙላት ሰጠሁት። በጣም ደስ አለው፤ በሰማያዊ እስክርቢቶ አምስት ስድስት ቃላት ፃፈበት። የቃላት ለውጥ አድርጓል። ቃለ-ጉባኤው የቃላት ማስተካከያ ከተደረገበት በኋላ ለብሔራዊ ኮሚቴው ቀረበ።

ለብሔራዊ ኮሚቴው ከቀረበ በኋላ ወደ ነበረው ሂደት እንመለሳለን። ከዚያ በፊት ግን አንተ፣ ታደሰ ወርቁ፣ አያልነህ ሙላቱ፣ ተስፋዬ ለማ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ሆናችሁ በተነጋገራችሁበት ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ሲገልፅ ታደሰ ወርቁ “እኔ እየተናገርኩ ባይለየኝ ይጽፍ ነበር” ይላል። አያልነህ ሙላቱ ደግሞ ሀሳቡንም ሆነ “አደይ አበባ” የሚለውን ርዕስ ቀድሞ “እንቁጣጣሽ” በኋላ “ፋና” ከዚያም “አደይ አበባ” ብዬ ርዕሱን ያመጣሁት እኔ ነኝ ይላል። አንተ እዚህ ላይ ያለህ አስተያየት ምንድነው?

እኔ እንግዲህ የታሪክ ሽምያ ውስጥ አልገባም። አልፈልግምም። እውነታውን ግን ግልፅ ማድረግ አለብኝ። አቶ አያልነህ ለውይይት ዳብሮ በቀረበ ሀሳብ ላይ ያረመው አምስት ቃላትን ነው። ከዚያ በተረፈ ባለው ሀላፊነትም ጭምር ሕዝብ ለሕዝብ በዚህ መልኩ እንዲደራጅ ዲዛይን አድርጎ ሊሆን ይችላል። እኔ ሁሉ ከተሰናዳ እና ድርሰቱ ከመጻፉ በፊት ነው ወደዚያ ቦታ የገባሁት። በእርግጠኝነት ድርሰቱ ላይ አምስት ቃላትን እንደቀየረ ሀሳብም አምጥቷል። በጉባኤ አዳራሹ ውይይት ላይም እንደሌሎች ሁሉ ተመስጦ አስተያየት ይሰጥ ነበር። አብዛኛዎቹ ሀሳቦች ይቀርቡ የነበረው ግን ከኪሮግራፈሩ ታደሰ ወርቁ ነበር። አቶ አያልነህ ትልቅ ሰው ነው። ብዙ ሰርቷል። ለምን “የአደይ አበባ” ጉዳይ እንደሚያስጨንቀው ግን አላውቅም።

ባለፈው ሳምንት ከታደሰ ወርቁ ጋር በስልክ በነበረን ውይይት እና አሁን አንተም እንደምትለው ከሆነ አቶ አያልነህ “የአደይ አበባን” ድርሰት እንደራሱ አድርጎ ሲያቀርበው በወቅቱ የነበረውን ስልጣን ተጠቅሞ ነው ማለት ይቻላል? አቶ አያልነህ ባልጻፈው ድርሰት ላይ ስሙ እንዴት ሊፃፍ ቻለ?

እንግዲህ እኔም እንዳንተ ጥያቄ ነው ያለኝ። መልስ የለኝም። ታሪክን የመሻማት ጉዳይ ነው እንጂ እንደ እውነቱ ከሆነ ስራው ላይ ሁላችንም አስተዋጽኦ አለን። ስራው በጣም የተቀናጀ ነበር። ውስጡ የታደሰ ወርቁ፣ የአቶ ሙላቱ አስታጥቄ፣ 39 ሰዓት የፈጀው ቪዲዮ የብዙዎች ጥርቅም ሀሳብ አለ። የባህሉ ጉዳይ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እና በየክፍለ-ሀገሩ ተኪዶ የተጠናው ጥናት ላይ የተመሰረተ ነው። ከዚያ ለአያልነህ ሙላት የሰጠሁት አሥር ገጽ ቃለ-ጉባኤ ዋናው የሀሳቡ መሰረት ነው።

አንተ እንደገለፅከው ታደሰ ወርቁ እና ታደሰ መስፍን በየክፍለ-ሀገሩ እየተዘዋወሩ የሰሩት 39 ሠዓት የሚፈጀው ቪዲዮ ዋናው መነሻ ነው። ይህንን ወደ መድረክ አቀናጅቶ ለማምጣት ደግሞ ኪሮግራፊን ማወቅ ይጠይቃልና ከሚና አንፃር የታደሰ ወርቁን ደረጃ ግለፅልኝ እስቲ? ምክንያቱም ባለፈው ሳምንት ኃይሉ ፀጋዬ በስልክ ገብቶ ታደሰ ወርቁ ተወዛዋዦችን ቦታ ቦታ ከማስያዝ ባለፈ ድርሻ የለውም ብሎ ነበርና ነው ይህን ጥያቄ ማንሳቴ።

በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው። ታደሰ ወርቁን በትክክል ግለፀው ካልከኝ የሕዝብ ለሕዝብ የጀርባ አጥንት ነው። ዋናው አምድ ነው። ያለ ታደሰ ወርቁ ያ ሥራ በዚህ መልኩ ሊቀርብ በጭራሽ አይችልም። ከአርቲስቶቹ ጋር ታደሰ ወርቁ ያለው መጣጣም ልክ ከልጆች ጋር እንደመጫወት ያለ ነው። አርቲስቶችን የሚያግባባና አንድ አድርጎ ለስራ የሚያሳትፍ ሰው ነው። እነዛን ሁሉ ብዛት ያላቸው አርቲስቶች አንድ አድርጎ የሚያሰራቸው ታደሰ ወርቁ ብቻ ነበር። ሌላ ማንም አይችልም። እኔ ያለኝ ክብርም ከዚያ የተነሳ ነው። ታደሰ ወርቁ ሊሆን የማይችልን ነገር እንዲሆን ያስቻለ ሰው ነው። ይህን ስል ደግሞ ሙላቱ አስታጥቄ ግዙፍ አቀናባሪ ነው፤ እሱን ትቼ አይደለም። ሕዝብ ለሕዝብን በድጋሚ ለመስራት (ቁጥር 2ን) ከታሰበ ታደሰ ወርቁ ወደዚህ ሀገር ተመልሶ መምጣት አለበት። እንደ ሕዝብ ለሕዝብ ያለ ሁለት ሦስት ሥራ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የራሷን ባሌት ለመሥራት በቻለች ነበር። ሕዝብ ለሕዝብ ላይ የታደሰ ወርቁ ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነው። እዚህ አለመኖሩ ደግሞ የሚያስቆጭ ነው። ታደሰ ወርቁ አሜሪካ ገብቶ በመቅረቱ ልክ ሙያው እንደተሰደደ አድርጌ ነው የምቆጥረው።

ከሕዝብ ለሕዝብ ጉዞ ጋር በተያያዘ ብዙ ሸፍጥ እንደተሰራ ይነገራል። አንተ የቅርብ ሰው ሆነህም ጉዞው ላይ አልተካተትክም። ለምን? ታሪክ ስለሆነ እስቲ የምታውቀውን ንገረን?

በወቅቱ እኔ የፓርቲ አባል አልነበርኩም። ቀደም ባለው ጊዜ ኢህአፓ ውስጥ ነበርኩ። ሕዝብ ለሕዝብ ከመኬዱ በፊት ኢሠፓ ውስጥ ሦስት ጊዜ ፎርም መጥቶልኛል። ታደሰ ወርቁ፣ ተስፋዬ ለማና ሙላቱ አስታጥቄም አብሬያቸው ለመሄድ እፈልግ እንደሆን ጠይቀውኛል። የሰጠኋቸው መልስ አንድ ዓይነት ነው። የኔ ጉጉት የነበረው መማር ነው። አቶ ሺመልስ ማዘንጊያን እና እዚያ አካባቢ የነበሩትን በጣም የማስቸግራቸው ለመማር እንጂ ሕዝብ ለሕዝብ ለመሄድ አልነበረም። በወቅቱ ስለመሄዴ ጉዳይ ተነስቶ የተሰጠው ምላሽ “ይህ ሰው ወደ ሀገሩ ተመልሶ ይምጣ፣ ይቅር አናውቅም። የፓርቲ አባል አይደለም” የሚል ነው። ምንም ሥራ ውስጥ የሌሉ አንዳንድ ሰዎች በፓርቲ አባልነታቸው ብቻ ሄደዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ገፅታ ግንባታ፣ የሀገራችንን በጎ ጎን ከማሳየት፣ ከፖለቲካ ትርፍ አኳያ ለኢትዮጵያ የፈጠረው ምንድነው?

ሕዝብ ለሕዝብ ግቡን መቷል። ምስጋናውም ቀርቧል። ሀገሪቱም የህብር ሀገር መሆኗን አሳይቷል። ቡድኑ እንደሄደ በተለያዩ ሀገራት ጋዜጦች ላይ ተጽፎለታል። በጣሊያንኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በእንግሊዝኛ ብዙ ተጽፎለታል። አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ትርኢቱ ከሚቀርብበት አዳራሽ ውስጥ ሰብሰብ እያሉ ተቃውሞ ያቀርቡ ነበር። አስደሳች ውጤት ነው የተገኘበት። እኛን ያሳየንበት፣ ጥሩ ዕድል ያገኘንበት አጋጣሚ ነበር። የደርግ ጉዳይ የታወቀ ስለሆነ የፖለቲካውን ስሜት (ዲፕሎማሲ) የለወጠው አይመስለኝም። የባህላችን እሴቱና ብዛቱ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም የታየበት አጋጣሚ ነው ማለት እችላለሁ። የሚደገምም አይመስለኝም።

ከልብ አመሰግናለሁ!

እኔም አመሰግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top