ጥበብ በታሪክ ገፅ

ልጅ እንዳልካቸው መኮንን

በዛሬው የታሪክ ገጻችን ስለ ልጅ እንዳልካቸው እናወራለን። እኒህ ሰው በተለይ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ በሀገራችን ላይ ቁልፍ ሚና ነበራቸው። ኢትዮጵያ በ1963 ዓ.ም. ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊነት እጩ ባቀረበችበት ወቅት ወክለዋታል። ይህ ታሪክ ከተፈጸመ በያዝነው ዓመት በታህሳስ ወር 48 ዓመት ይሞላዋል። ይህንን ቀን መክንያት አድርገን ከታሪካቸው እና ከስራዎቻቸው ጥቂቱን እናወጋችኋለን። ሀገራችንን፣

በ1966 ለጥቂት ወራት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስለመሩት ስለ ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን እዝራ እጅጉ ያሰናዳልን ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል። መልካም ንባብ!

              የአቧሬው እንዳልካቸው…

በጷግሜ 4 1920፣ የዛሬ 92 ዓመት የተወለዱት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን አባታቸው ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፣ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ ዘውዲቱ መንገሻ ይባላሉ። የትውልድ ቦታቸው አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ‹አቧሬ›› ነው። ጠላት ሀገራችንን በወረረ ጊዜ አባታቸው መኮንን እንዳልካቸው ከዘመቱበት የኦጋዴን ግንባር ሲሄዱ ልጅ እንዳልካቸው ከአባታቸው ተነጥለው ስለቀሩ አምስቱን የመከራ ዓመታት ያሳለፉት ሰሜን ሸዋ ውስጥ ከአያታቸው ከወይዘሮ አቦነሽ ተክለማሪያም ጋር ነበር። አባታቸው በ1933 ዓ.ም. በድል ከገባው ሰራዊት ጋር እንደተመለሱ እንዳልካቸው መኮንን ከአያታቸው ጋር ወደ ትውልድ ከተማቸው መጡ። ሁኔታዎች ሲረጋጉም ልጅ እንዳልካቸው የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚሲዮን እና በቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሴ ትምህርት ቤቶች /በኮተቤ/ አጠናቀቁ።

ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ሀገራቸውን በበርካታ መስሪያ ቤቶች ያገለገሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአታሼነት ስራቸው ይጠቀሳል። ለ6 ዓመታት ያህል በዚሁ መስሪያ ቤት ካገለገሉ በኋላ ምክትል ሚኒስትር ሆኑ። ከዚህ ጊዜ በኋላም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለጉብኝት ባህርማዶ በሚሄዱ ወቅት አብረው እየተጓዙ የሀገራትን ሁኔታ የመጎብኘት እድል ገጥሟቸው ነበር።

በ1948 የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። በመቀጠልም በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ የካቢኔ ሚኒስትር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ፣ የፖስታ የመገናኛ እና የቴሌኮሚኒኬሽን ሚኒስትር በመሆንም አገልግለዋል።

አቶ በቀለ እንደሻው የ84 ዓመት ሰው ሲሆኑ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በልማት ኢኮኖሚክስ የተመረቁ አንጋፋ ምሁር ናቸው። ከልጅ እንዳልካቸው ጋር በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ አብረው የመስራት አጋጣሚ እንደነበራቸው ይናገራሉ። አቶ በቀለ ስለ ልጅ እንዳልካቸው ሲጠየቁ 57 ዓመታትን ወደ ኋላ መጓዝ ነበረባቸው። ነገሩም እንዲህ ነው። ግርማዊ ጃንሆይ በ1952 ሶቭየት ኅብረትን ይጎበኛሉ። ከጉብኝቱ መልስም የበርካታ ሚልዮን ብር እርዳታ ያገኛሉ። በወቅቱ አቶ በቀለ በንግድና ኢንዱስትሪ ስር ባለው የብድር አገልግሎት ውስጥ በከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ይሰሩ ነበር። ታዲያ አቶ በቀለ ይህን ብድር በሀገሪቱ ለሚገኙ ብድር ፈላጊዎች መስጠቱ ያለውን ችግር ዘርዝረው ለጃንሆይ ያቀርባሉ። በዛን ወቅት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩት ልጅ እንዳልካቸው አቶ በቀለን ደውለው ያስጠራሉ። ከግቢ ነው የምደውልልህ አሉ፡፡ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን። ራሳቸውን እያስተዋወቁ። “…አቶ በቀለ ጃንሆይ ራፖርህን ሰጥተውኛል። ይህንን ራፖር በትክክል የምታስረዳኝ አንተ እንደሆንክ ነግረውኛል። ነገ ቢሮ መጥተህ ብንነጋገር ብለዋቸው እንደነበር አይዘነጉትም።

ልጅ እንዳልካቸው አባታቸው ደራሲ ስለነበሩ መጽሐፍ ማንበብን ከምንም በላይ ይወዳሉ። አንባቢ ስለነበሩም ነገሮችን ምሁራዊ በሆነ መንገድ የማየት አቅማቸው ከፍተኛ ነው። አቶ አሸናፊ ሺፈራው የልጅ እንዳልካቸው ባለቤት የወይዘሮ እንከንየለሽ ሺፈራው ታላቅ ወንድም ናቸው። የልጅ እንዳልካቸው አእምሮ ብሩህ መሆኑን አቶ አሸናፊ ይመሰክራሉ። በውጭ ሀገራት አዳዲስ መጽሐፎች ሲታተሙ ልጅ እንዳልካቸው በቶሎ ያስመጣሉ። ልጅ እንዳልካቸው ከተባበሩት መንግሥታት ስራቸው ሲመለሱ ጥቁር ፔጆ 504 መኪና ይነዱ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት

ኢትዮጵያ፤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊነት የሚወዳደር አዲስ እጩ ማዘጋጀቷ የተሰማው በ1963 ነበር። ዘመኑ “ቀዝቃዛው ጦርነት” ያየለበት ነበር። በዛን ወቅት የዓለም ፖለቲካ የሚዘወረው በሁለቱ ኃያላን (በሞስኮና ዋሺንግተን) ፍላጎትና ጥቅም ላይ ተመስርቶ ነበር። ስለሆነም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዕጩ ገለልተኛ ከሚባል አገር ይመጣል የሚል ግምት ነበር።

የዋና ጸሀፊነቱን እድል አውሮፓ ሁለት ጊዜ፣ እስያ ደግሞ  አንድ ጊዜ ስላገኙ ተራውን ለሌላው ይለቃሉ ተብሏል። በዚህ ስሌት መሰረት ከሄድን ዋና ጸሀፊው የሚመረጠው ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከደቡብ አሜሪካና ከአፍሪካ አገራት መካከል ይሆናል። ይሁን እንጂ መካከለኛው ምሥራቅ በአረብ እሥራኤል ፍጥጫ ዘወትር የተወጠረ እንደመሆኑ ከዚያ አካባቢ የሚመጣ ዕጩ ለማሸነፍ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ያገኛል ተብሎ ተስፋ አይጣልበትም። ከደቡብና ከመካከለኛው አሜሪካ አገራት የሚመጣ እጩ ከኩባ ካልሆነ በስተቀር ለመቀበል አሜሪካ ችግር የለባትም። ሩስያኖቹ በበኩላቸው ግን ደቡብ አሜሪካ አገራትን በሙሉ የአሜሪካ ጋሻ ጃግሬ አድርገው ስለሚቆጥሩ ከዚያ አካባቢ ለሚመጣ እጩ ድጋፋቸውን ይከለክላሉ የሚል የተንታኞች ስሌት ነበር። በዚህ ጊዜ የተሻለ ግምት የሚሰጠው ለአፍሪካ ይሆናል፤ ብቃት ያለው ዕጩ እስከተጠቆመ ድረስ ሶቭየቶቹም ሆነ አሜሪካኖቹ በአንድ አፍሪካዊ ዕጩ ላይ ሊስማሙ ይችላሉ። ምክንያቱም በምሥራቅ ምዕራብ ፍጥጫው አፍሪካ ገለልተኛ ሆኖ የመቆጠር ተስፋ አለው ተብሎ በወቅቱ ፎርሙላ ሂሳቡ ተሰርቶ ነበር። የፖለቲካ አሰላለፉ ከዚህ በላይ በቀረበው የወቅቱ ትንተና መሠረት ከሆነ፤ በተለምዶ የአፍሪካ ወኪል ተደርጋ ለምትቆጠረው ለኢትዮጵያ ዕጩዋን ለማቅረብ በእርግጥም ከዚህ የተሻለ ጊዜ አልነበረም። ለዚህ ሥራ የታጩት ኢትዮጵያዊ የ43 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሲሆን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሀገሪቱ ዋና መልዕክተኛ ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል። የዘመኑ መገናኛብዙኃን “አገሩ በኦፊሴል ድጋፍ የሰጠችው የመጀመሪያው አፍሪካዊ ዕጩ የተ.መ.ድ ዋና ጸሐፊ›› ሲሉ የገለጧቸው እኚህ ሰው፤ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ነበሩ።

ለተመድ ዋና ጸሀፊነት መታጨት

የተመለከቱት በድርጅቱ የሀገራቸው ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው በተመደቡበት ጊዜ ነበር። በተለይ ከ1959 ዓ.ም እስከ 1961 ዓ.ም. በነበረው የ3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የጸጥታው ምክር ቤት ጊዜያዊ አባል ስለነበረች፤ ልጅ እንዳልካቸው ሁለት ጊዜ ተመርጠው የጸጥታውን ምክር ቤት በፕሬዚዳንትነት መርተዋል። በዚሁ የጸጥታው ምክር ቤት የፕሬዚዳንትነታቸው ዘመን በመካከለኛው ምስራቅ፣ በቆጵሮስ፣ በሮዴሽያ፣ በናሚቢያና በቼኮስሎቫኪያ የደረሱ ቀውሶችን አስመልክቶ የተጠሩ ስብሰባዎችን መርተዋል። እንዲሁም በእስራኤልና በግብጽ መካከል ጦርነት በተካሄደበት ጊዜ አስታራቂ መልዕክተኛ ሆነው ያገለገሉትን ሚስተር ጉናር ጃሪንግን የሰየሙት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ነበሩ። ልጅ እንዳልካቸው መኮንን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጉባኤ ላይ  ለሮዴዥያና ለደቡብ አፍሪካ ነጻነት ተሟግተው ነበር።

ወይዘሮ እታገኝ ወልደማሪያም ልጅ እንዳልካቸው የተባበሩት መንግሥታት በሰሩበት ዘመን አብረዋቸው መስራታቸውን ያስታውሳሉ። ወይዘሮ እታገኝ ከልጅ እንዳልካቸው ጋር አብሮ መስራት ያኮራኛል ይላሉ። በተለይ ልጅ እንዳልካቸው ከውጭ ሀገር ሰዎች ጋር ሲነጋገሩ የራሳቸውን ክብር የሚጠብቁና በራሳቸውም የሚተማመኑ ነበሩ።

እጩነት በሚድያ

በአፍሪካ ጆርናል እየተዘጋጀ በየወሩ ለንደን ላይ ይወጣ የነበረው “አፍሪካ” መጽሔት እ.ኤ.አ በየካቲት 1971 ዓ.ም. እትሙ ላይ ልጅ እንዳልካቸውን “አፍሪካዊው የዩታንት ተተኪ” በማለት ሰፊ ዘገባ እና ቃለ- ምልልስ ይዞ የወጣ ሲሆን “ንጉሥ ኃይለሥላሴ በዓለም ላይ ያላቸው ሥምና ዝና ለእንዳልካቸው የምርጫ ዘመቻ ትልቅ ጉልበት ሊሆናቸው ይችላል” ሲል ተንብዮ ነበር። የዚህ መጽሔት ዋና አዘጋጅ፤ ልጅ እንዳልካቸውን ለተመድ ዋና ጸሐፊነት ሥራ ለመወዳደር ምን እንዳነሳሳቸው ሲጠይቃቸው

“የቤተሰቤን ያለፈ ታሪክ ብትመለከት ከአገራዊ ወይም ዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ርቆ እንደማያውቅ ትመለከታለህ፤ አባቴ የተመድ ቻርተር ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ላይ ሲፈረም የኢትዮጵያ መልዕክተኞች መሪ ነበር። ሌላው የግል ትምህርቴ ታሪክ ነው፤ የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቅ እንደመሆኔ ፖለቲካ ይስበኛል- በተለይ ዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ” በማለት መልስ ሰጥተው ነበር።

ልጅ እንዳልካቸው ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊነት በእጩነት ራሳቸውን ማቅረባቸውን በይፋ ያስታወቁት ጥር 14 ቀን 1963 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነበር። በዚሁ መግለጫቸው፣ እጩ ሆነው እንዲወዳደሩ በንጉሠ- ነገሥቱና በመንግሥታቸው እንደተፈቀደላቸው ጠቁመው፤ እጩ ሆነው የሚቀርቡት ግን ዩታንት የሥራ ጊዜያቸውን ለማብቃት ያላቸውን ፍላጎት ያልቀየሩ እንደሆነ ብቻመሆኑን አስረድተዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊነት የምርጫ ዘመቻ አዲሱ የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት 1972 ዓ.ም. ከመግባቱ በፊት (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጥር 1964 ዓ.ም. አስቀድሞ) መጠናቀቅ አለበት። ከምርጫው ሦስት ወራት ቀደም ብሎ ሮይተርስ፤  የመመረጥ ተስፋ አላቸው ያላቸውን 5 እጩዎች ይፋ ያደረገ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ይገኙበታል። በዛን ወቅት ተስፋ አላቸው የተባሉት እጩዎች (1ኛ) ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ከኢትዮጵያ (2ኛ) ማክስ ጃኮብሰን ከፊንላንድ (3ኛ) ሺርሊ አሜራሲንግ ከሲሎን (4ኛ) ዶ/ር ኩርት ቫልዳሂም ከኦስትርያ (5ኛ) ዶ/ር ፊሊሻ ሄራከቺሊ ነበሩ።

መስከረም 20 ቀን 1964 ዓ.ም. ሮይተርስ ከኒውዮርክ በላከው ዘገባ፣ ከአምስቱ ኃያላን አገራት አንዷ የሆነችው የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሞሪስ ሹማን አዲሱ የተመድ ተመራጭ ዋና ጸሀፊ፣ ከእንግሊዝኛ ሌላ ፈረንሳይኛም የሚናገር መሆን አለበት ማለታቸውን ጠቅሶ በዚሁ መሰረት ውሳኔው ፈረንሳይኛ የማይናገሩ የሁለቱን እጩዎችን የመመረጥ ተስፋ አጨለመ። ሮይተርስ በዚሁ ዘገባው፤ የፊንላንዱ ማክስ ጃኮብሰንም ሆኑ የሲሎኑ ሺርሊ አሜራሲንግ ፈረንሳይኛ የማይናገሩ ሲሆን ኢትዮጵያዊው እንዳልካቸው መኮንን፣ ኦስትሪያዊው ኩርት ቫልዳሂም እና የቺሊው ተወላጅ ዶ/ር ፊልሻ ሄራ እንግሊዝኛም ፈረንሳይኛም ተናጋሪ በመሆናቸው ለመመረጥ ተስፋ ነበራቸው። ታህሳስ 9 ቀን 1964 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊን ለመምረጥ የጸጥታው ምክር ቤት መሰብሰቡን አጃንስ ፍራንስ

ፕሬስ ከኒውዮርክ አሰማ። ይሁን እንጂ በሚስጢር በተደረገው የምርጫ ሂደት በድምጽ ብልጫ ተፈላጊውን እጩ ለማስገኘት ሳይችል በመቅረቱ ምክር ቤቱ ያለውጤት ተበተነ። የጸጥታው ምክር ቤት በተከታታይ ካካሄደው ሁለት ተጨማሪ ያልተሳኩ የምርጫ ሙከራዎች በኋላ፤ ታህሳስ 13 ቀን 1964 ዓ.ም. ባካሄደው ምርጫ ኦስትሪያዊውን ዶክተር ኩርት ቫልዳሂምን 4ኛው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አድርጎ የመረጣቸው ሲሆን በማግስቱ የተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤም ምርጫውን አጽድቆታል። ልጅ እንዳልካቸው እንደተመኙት፤ የፖለቲካ ተንታኞችም እንደተነበዩት ከአፍሪካ ሳይሆን ከአውሮፓ ለሦስተኛ ጊዜ የተመድ ዋና ጸሐፊ ተመረጠ። ዶክተር ቫልዳሂም ሁለት ጊዜ ተመርጠው እ.ኤ.አ እስከ 1981 ዓ.ም. ድረስ ተመድን አገልግለዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊነት ስራ ከአውሮፓ ቀጥሎ የተጓዘው ወደ አፍሪካ ሳይሆን ወደ ደቡብ አሜሪካ ነበር። የደቡብ አሜሪካዋ አገር የፔሩ ተወላጅ የሆኑት ሀቪየር ፔሬዝ ዴኩየር 5ኛው የተመድ ዋና ጸሐፊ ሆነው እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም. የተመረጡ ሲሆን ድርጅቱንም እስከ 1991 ዓ.ም. ድረስ መርተውታል። ከልጅ እንዳልካቸው መኮንን የምርጫ ዘመቻ ልክ ከ20 ዓመት በኋላ ግብጻዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ እ.ኤ.አበ 1992 ዓ.ም. 6ኛው የተመድ ዋና ጸሐፊ በመሆን ሲመረጡ አፍሪካ የመጀመሪያውን ውክልና አገኘች፡፡ ከ5 ዓመታት በኋላ ደግሞ ኮፊ አናን ሁለተኛው አፍሪካዊ የተ.መ.ድ ዋና ጸሐፊ ሆነው ተመረጡ።

የልጅ  እንዳልካቸው የተመድ እጩ ሆኖ መቅረብ ጊዜው ያልደረሰ ሐሳብ ነበር ወይም ጊዜውን በ20 ዓመት የቀደመ ነበር ለማለት ይቻላል። የእንዳልካቸው ዘመቻ ያልተሳካው በዘመኑ ይካሄድ በነበረው የቀዝቃዛ ጦርነት ምክንያት አፍሪካ በኃያላኑ ስሌት ውስጥ ልትገባ ባለመቻሏ ነው እንጂ የእንዳልካቸው ልምድና ችሎታ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ አልነበረም። ልጅ እንዳልካቸው የጓጉለት የተመድ ዋና ጸሀፊ እጩነት ያልተሳካላቸው ቢሆንም ከሦስት ዓመታት በኋላ የካቲት 21 ቀን 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። ይህ ሹመት የመጣው የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በሁሉም አቅጣጫ በተቃውሞ ማዕበል በሚናጥበት ዘመን በመሆኑ የእንዳልካቸውን የሥራ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ አድርጎት ነበር።

         ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳልካቸው

ንጉሱ በየካቲት ወር ለሁለተኛ ጊዜ በቴሌቪዥን ቀርበው የጸሐፌ- ትእዛዝ አክሊሉን ካቢኔ የስንብት  ጥያቄ መቀበላቸውን ገለጹ። በምትካቸውም ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሌተናል ጀነራል ዐቢይ አበበን የመከላከያ ሚኒስትር፣ ሌተናል ጀነራል ወልደ ሥላሴ በረካንም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር አድርገው ሾሙ።

ልጅ እንዳልካቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው አንዳንድ ደጋፊዎቻቸውንና መሰል መሳፍንትን ያስደሰተ ቢሆንም በአብዛኛው ተራማጅ ምሁራን እና በተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ልጅ እንዳልካቸው ይህን ሀገራዊ ኃላፊነት ሲቀበሉ ሁኔታዎችን መልክ ለማስያዝና ለማረጋጋት የተቻላቸውን አድርገዋል።

ልጅ እንዳልካቸው በተቃውሞ ሰልፍ መካከል መጋቢት 11፣ 1966 ዓ.ም. የሕገ-መንግሥት አርቃቂ ጉባኤ አባላት ዝርዝር ይፋ አደረጉ። በዝርዝሩ የተጠቀሱት አባላት በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር አብዛኛዎቹ በዘውዳዊ ስርአት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወይም ከስርአቱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በመሆኑ በመምህራንና ተማሪዎች ዘንድ ዝርዝሩ ተቀባይነት አልነበረውም።

ተቃውሞ ሰልፉና ጥያቄዎቹ እየተጠናከሩና ውጥረቱ በተለይ በአዲስ አበባ እየተባባሰ በመምጣቱ ይህንኑ የሚያስደርጉት ከሥልጣን የለቀቁት ባለሥልጣናት ናቸው የሚል በሰፊው ይወራ ነበር።

የወታደሩ እንቅስቃሴ ረገብ ሲል ህዝባዊ ተቃውሞው ሲግል እንደገና ወታደሩ ተቃውሞውን ሲያፋፍም ህዝባዊው እንቅስቃሴ እየቀዘቀዘ ሲፈራረቅባቸው ውጥረት ውስጥ የወደቁት ልጅ እንዳልካቸው ነጋ ጠባ በቴሌቪዥን እና በሬድዮ ፋታ ስጡኝ እያሉ ህዝቡን ይማጸኑ ነበር።

ልጅ እንዳልካቸው ሚያዝያ 10 ቀን በ4ኛ ክፍለ-ጦር ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት “የቀድሞ ባለሥልጣናት እና የካቢኔ አባላት ለምን በቁጥጥር ስር አይውሉም?” የሚል ከጦሩ አባላት ጥያቄ ቀርቦ ነበር።

ከሥልጣን የወረዱት የቀድሞ ባለሥልጣናት እና የካቢኔ አባላት ለሀገሪቱ ጸጥታና ለእነርሱም ደህንነት ከፍተኛ ጥበቃ ወዳለበት አካባቢ እንዲሰባሰቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው ማሳሰቢያ እንዲተላለፍ በከፍተኛ ድምጽ ተወስኖ ነበር። በዚህም ምክንያት አዲሱ የተመሰረተው ወታደራዊ ኮሚቴ ጸሀፌ-ትእዛዝና ሌሎቹም ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለንጉሱ ጥያቄ አቀረበ። በዚህም መሰረት ሚያዝያ 18፣ 1966 ዓ.ም. ጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉና ሚኒስትሮቻቸው በድምሩ 25 ሰዎች በ4ኛ ክፍለ-ጦር ስር በነበረው ጎፋ በሚገኘው የ17ኛ ሻለቃ ክበብ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደረገ።

        ደርግ እና ልጅ እንዳልካቸው

ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ከደርግ ጋር መስራቱ አስቸጋሪ ሆነባቸው። ደርግም እንዳልካቸው አልተመቹትም። ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ማንሳት አስፈላጊ መሆኑን ስላመነበት ሊቀ-መንበር መንግሥቱ ሀሳቡን በደርግ ስብሰባ ላይ አቀረቡት።

“ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን አላማችንን በስራ ላይ ለመተርጎም አስቸጋሪ እየሆነብን መጥቷል። ዋናውን የመንግሥት ስልጣን የያዙት ጠቅላይ ሚኒስትር እኛ እንደምንፈልገው ሊሄዱልን አልቻሉም። በእርግጥ የተማሩ ናቸው። ነገር ግን የመሳፍንት ወገን በመሆናቸው የእኛን እንቅስቃሴ አልወደዱትም። ከእኛ ጋር ሳይመካከሩ ውሳኔ ይሰጣሉ። ይሾማሉ፣ ያዛውራሉ፣… ስለሆነም መንግሥታዊ አሰራሩንም ለመቆጣጠር ብሎም ለመምራት ተቸግረናል። ስለዚህ እንዳልካቸው ከያዙት የሥልጣን ቦታ መነሳት አለባቸው።” ብለው ሻለቃ መንግሥቱ ለተሰበሰቡት የደርግ አባላት ጠቆም አደረጉ።

ከዚያም ልጅ እንዳልካቸው ከሥልጣናቸው ወርደው በቤታቸው የቁም እስረኛ ሆኑ። ከውጭ ግንኙነት እንዳያደርጉም የስልክ መስመራቸው እንዲቋረጥ ተደረገ።

በ1966 ዓ.ም. የንጉሠ-ነገሥቱ መንግሥት በህዝባዊ ተቃውሞ ሳቢያ ከስር መሰረቱ በመናጋቱ፤ ወታደራዊ መኮንኖችም ቀስ በቀስ መንግሥቱን እየቦረቦሩ ነበር። እንዲሁም ህዝባዊው ተቃውሞ ባለመለዘቡ ምክንያት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ሥልጣን ላይ ከወጡ ከ144 ቀናት በኋላ ሐምሌ 15 ቀን 1966 ዓ.ም ከሥልጣን ተሰናበቱ። ልጅ እንዳልካቸው ከሥልጣን ከወረዱበት ጊዜ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል በመኖሪያ ቤታቸው በጥበቃ ሥር ሆነው ከቆዩ በኋላ፤ ከሐምሌ 24 ቀን 1966 ዓ.ም. ጀምሮ ቀደም ብሎ በአራተኛ ክፍለ ጦር ቅጥር ግቢ ውስጥ ታስረው ከነበሩት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ጋር እንዲቀላቀሉ ተደረገ። ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ደርግ ያለፍርድ ለብዙ ወራት አስሮ፤ በመጨረሻም  ህዳር 14  ቀን 1967 ዓ.ም. ምሽት በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት በጥይት ተደብድበው በግፍ እንዲገደሉ ካደረጋቸው 60 ንጹሀን ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው።

ልጅ እንዳልካቸው በትርፍ ጊዜያቸው ግለ-ታሪኮችን፣ መጣጥፎችን እና ግጥሞችን ይሰበስቡ ነበር። የሚወዱት ስፖርት ደግሞ የውሃ ዋና ነበር። በትዳር አብረዋቸው ከኖሩት ወይዘሮ እንከንየለሽ ሽፈራሁ ጋር በሕግ ተጋብተው 3 ወንዶችና 4 ሴት ልጆች ማፍራታቸው ታውቋል። እኒህ ኢትዮጵያዊ በደርግ ጥይት ተደብድበው በጅምላ መቃብር ሲጣሉ ገና 46 ዓመታቸው ነበር። ሥራቸውንና አገልግሎታቸው ግን ተገድሎ የማይጣል ስለሆነ ከመቃብር በላይ ህያው ሆኖ  በታሪክ ሲታወስ ይኖራል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top