አድባራተ ጥበብ

ሁለገቡ ሙያተኛ ካህሳይ ገ/እግዚአብሄር

የበዛውን የእድሜአቸውን በመምህርነት እና በጋዜጠኝነት አሳልፈዋል። ትግራይ፣ ሐረር፣ ጅጅጋ፣… እና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክልሎች በመዘዋወር በመምህርነት አገልግለዋል። ለሕትመት ከበቁት ሥራዎቻቸው መካከል ኅብረ-ብዕር በሚል ስያሜ የታተሙት ሦስት ቅጾች ከዚህኛው ትውልድ ጋር ይበልጥ ያስተዋወቋቸው ሥራዎቻቸው ናቸው። “ብጹአን እነማን ናቸው?”፣ “ባህል እና ክርስቲያናዊ ትውፊት በኢትዮጵያ”፣ “ምስጢረ-ፊደላት” የተሰኙ መጻህፍትንም ለንባብ አብቅተዋል። ሕዳር 24፣ 2011 ዓ.ም. በ66 ዓመታቸው በሞት ከመለየታቸው በፊት ለሕትመት የተዘጋጁ አራት ያህል መጻሕፍት እንደነበሯቸው መረጃዎች አመላክተዋል። “ኅብረ-ብዕር ቁጥር ፬ን” እና “ብጹአን እነማን ናቸው? ቁጥር ፪ን” ጨምሮ “ንግሥና በኢትዮጵያ”፣ “ሐገር በቀል እጽዋት” የተሰኙት ያልታተሙ ሥራዎቻቸው ናቸው።

የተወለዱት መጋቢት 5፣ 1946 ዓ.ም. በትግራይ ማእከላዊ ዞን ልዩ ስሙ ሙዘና የተባለ ስፍራ ነው።  ከ1970 ዎቹ ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ ከ40 ዓመታት በላይ በራዲዮ እና በቴሌቪዥን ስራዎቻቸውን ሲያቀርቡ የቆዩት መምህር ካህሳይ ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ የዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ በመሆን ህይወታቸው እስካለፈበት እለት ድረስ አገልግለዋል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ራዲዮ “የእሁድ መዝናኛ” ፕሮግራም እና “የአፍሪካ ቀንድ” መጽሔት የሐረር ከተማ ወኪል ሆነው በሰሩባቸው ጊዜያት አዝናኝ እና አስተማሪ ጽሑፎችን በማቅረብ አድናቆትን አትርፈዋል።

ከሐረር መምህራን ተቋም ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በቀጥታ ያመሩት ወደ ትውልድ መንደራቸው ነው። ‹ዳዕሮ› የሕዝብ ትምህርት ቤት ከ1967-1969 የነበራቸው ቆይታ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉበት ነበር። ጂግጂጋ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ከ1976-1982)፣ ሐረር የሚገኘው ‹ጉርሱም› ትምህርት ቤት፣… ከመምህርነት እስከ ርዕሰ መምህርነት ካስተማሩባቸው ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ። ከመምህርነቱ ጎን ለጎን የሚከውኑትን ጋዜጠኝነት ለማሳደግ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በማምራት ጋዜጠኝነትን ካጠኑ በኋላ ፊታቸውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ጋዜጠኝነት ማዞራቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

በ1970 ዓ.ም. የጊዜው የሐገሪቱ ፖለቲካ የተሻለ ለውጥ እንዲያመጣ በማሰብ ከኢሕአፓ ጎን በመሰለፍ ታግለዋል። በ1974 ዓ.ም. ከመሰረቱት ትዳርም ሦስት ሴት እና ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተዋል።

ምስክርነቶች

ሁለገብ ሙያተኛ ነበር

ደራሲ ጌታቸው በለጠ

ከካህሳይ ጋር ዘለግ ላለ ጊዜ እተዋወቃለሁ። ትልቁ የካህሳይ ጥንካሬ ሁለገብ መሆኑ ነው። በጋዜጠኝነቱም በኢትዮጵያ ባህላዊ ጉዳዮች ላይ በተለይ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ባህል ላይ ከሃይማኖት ጋር በተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮችም ደፍረው ከሚፅፉ ጸሐፊዎች መካከል ነው። ደራሲያን ማኅበረሰባዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ ጫና አለባቸው፤ ካህሳይ ግን ይህንን ሁሉ ማለፉ ከሁኔታዎች በላይ ለህሊናው እና ለሞያው ታማኝ እንደሆነ ያሳያል።

ሞቱ ለሃገር ትልቅ ጉዳት ነው

ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ

“እውነተኛ እና ሐቀኛ፤ ለጋዜጠኝነት፣ ለመምህርነት እና ደራሲነት የሚገባ ሰው ነው። ካህሳይ ከሚያምንበት ጉዳይ ውጪ የማይጽፍ፣ የማይናገር ሰው ነበር። ቤተክህነት ውስጥ ሆኖ የሚያያቸውን ስህተቶች ሁሉ በመፃፍ ለንባብ ያበቃ ጎበዝ ደፋር ጋዜጠኛ ነው። ካህሳይ ሳይንቲስትም ነው። በስነ-ህይወት (ባዮሎጂ) ያለው ዲፕሎማ ቢሆንም ለስነ-ጽሁፍ ሲዘዋወር በእፅዋት ላይ ጥናት ያደርግ ነበር።

ከየትኛውም የሃገራችን ክፍል ተዎላጆች ጋር ብሄር እና ቋንቋን መሠረት ሳያደርግ በስምምነት መስራት ይችላል። ከ40 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሬድዮ ‘እሁድ መርሃግብር’ ካህሳይ በጽሑፍ እኔ ደግሞ በድምፅ እንሳተፍ ነበር። ሞቱ ለሃገር ትልቅ ጉዳት ነው።

ደፋር ጸሐፊ ናቸው

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

“አሁን ባለንበት ዘመን፤ የኢትዮጵያን ትውፊቶች፣ በገበሬው ዘንድ ያሉትን በተለይ በአማራና በትግራይ አካባቢ የሚነገሩትን ጥንታዊ ትውፊቶች እና በትውፊቶች ውስጥ ያሉትን እውቀቶች፤ የመምህር ካሕሳይን ያህል የሚያውቃቸው አለ ብሎ ማለት ያስቸግረኛል። በፎክሎር እና ባህል ጥናት ላይ የተሠማሩ ምሁራን የጥናት ዘዴውን ያውቁት ይሆናል ይዘቱን ግን በእሳቸው መጠን እና ዝርዝር የሚያውቅ አለ ማለት ይከብዳል።

ካህሳይ ላመኑበት ነገር ወደኋላ የማይሉ፣ የትኛውንም ጉዳይ ከብሔርም ሆነ ከሃይማኖት ጋር ሳይፈርጁ፣ እውነት ብቻ ይዘው የሚሄዱ፣ ላመኑበት ነገር ቆራጥ እና የሃሳብ ሰው ናቸው። ደፋር ጸሐፊ ናቸው።

ሦስቱም የኅብረ-ብዕር ቅፆች በያዙዋቸው እውቀቶች ከስራዎቻቸው ሁሉ ገዝፈው ይታያሉ። ቃላዊና ትውፊታዊ መረጃዎችን በጽሑፍ በማስቀረታቸውና ያንን ትልልቅ እውቀት ለትውልድ በማሸጋገራቸው ሲታወሱ ቢኖሩ ደስ ይለኛል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top