አድባራተ ጥበብ

የግብጹ የቲያትር ፌስቲቫል

በቅርቡ የካይሮ ዓለም ዓቀፍ የዘመናዊ እና ሙከራዊ ቴአትር ፌስቲቫል (Cairo International Festival for Contemporary and Experimental Theater) ተካሂዷል፡፡ ፌስቲቫሉ በካይሮ ከተማ ሲዘጋጅ ከሩብ ክፍለዘመን በላይ አሳልፏል። የዘንድሮውን ለሀያ ስድስተኛ ጊዜ የተካሄደ ነው፡፡

በፌስቲቫሉ በመላው ዓለም የሚገኙ የቴአትር ባለሞያዎች፣ መምህራን፣ ሀያስያን እና ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል። ከስድስት እስከ አስር ቀን በሚቆየው ፌስቲቫል በየዕለቱ ከአምስት ያላነሱ ቴአትሮች በተለያዩ ማሳያ ቦታዎች ለዕይታ ይበቃሉ። ከቴአትሮቹ ባሻገርም ልዩ ልዩ የጥናት ወረቀቶችም ይቀርባሉ፣ ውይይትም ይደረግባቸዋል። ከዚህ ሁሉ ጎን ለጎን ለወጣት የቴአትር ባለሞያዎች እንዲሆን ከተለያዩ ሃገራት የመጡ የቴአትር ባለሞያዎች ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን ይሰጣሉ። ወጣቶችም አዳዲስ ከሆኑ የቴአትር ስልቶች ጋር ይተዋወቃሉ፤ ይማራሉ። ፌስቲቫሉ በዋናነት በግብፅ የባህል ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ ይዘጋጃል።

በዚህ ፌስቲቫል ከሚቀርቡት እና ውይይት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ብቻ በላይ፣ የግብፅ መንግሥት እና የቴአትር ባለሞያዎች እንዲህ ያለውን ታላቅ ትዕይንት ለማዘጋጀት የሄዱበት እጅግ አስደናቂ ነው። ከመላው ዓለም በተለይ በሙከራዊ የቴአትር ስራቸው የሚታወቁትን የቴአትር ቡድኖችን ከመጋበዝ ጀምሮ በዘርፉ አንቱ እስከተባሉ ታላላቅ ፕሮፌሰሮች ድረስ ግብጽ ምድር ካይሮ ከተማ ይከትማሉ፡፡

ዝግጅቱ የዓለማችን ዋነኛ የዘመናዊ ቴአትር ጥበብ መገናኛ እና መወያያ መድረክ ነው። ይሕንን ትጋት አለማድነቅ ፍርደ-ገምድልነት ይመስለኛል፡፡

በተለይ በዚህ ሞያ ላይ ለምንገኝ ሰዎች እንደሩቅ የሚታዩ ባለሞያዎች በፌስቲቫሉ እንደልብ በዝተው ማነጋገር፣ መከራከር፣ መማማር፣… የሚቻልበት መድረክ ሲፈጠር ማየት የአዘጋጆቹን ልፋት እና የሥራቸውን ታላቅነት ለመመስከር ከበቂ በላይ ማሳያ ነው።

የጥናት ፅሁፎች አቅርቦት እና ለወጣቶች ስልጠናዎችን መስጠት ዋነኛ ተግባራት ነበሩ።

በፌስቲቫሉ የተሳተፉት የቴአትር ቡድኖች ስራዎቻቸውን በፋላኪ፣ ኤል ጋድ፣ ባሉን፣ ፍሎቲንግ፣ ማያሚ እና በሌሎች ቴአትር ቤቶች አቅርበዋል። ቴአትሮቹ ከኩዌት፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ብራዚል፣ ኮሶቮ፣ ኮንጎ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ቱኒዚያ፣ ሶርያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄርያ፣ ኢራቅ ወዘት የመጡ ናቸው። በፌስቲቫሉ በቴአትር ብቻ ግብፅን ጨምሮ ከ17 በላይ ሀገራት ተሳትፈዋል።

ፌስቲቫሉን በአካል በታደሙበት ጊዜ በርካታ አንጀት አርስ ቲያትሮች ተመልክቻለሁ፡፡ ስለተመለከትኳቸው ቴአትሮች ዝርዝር ጉዳይ ከማቅረብ ይልቅ እነዚህ ቴአትሮች የቀረቡባቸውን ቴአትር ቤቶች ከእኛ ጋር አነፃፅሬ የተመለከትኩትን ላጫውታችሁ።

ቴአትር ቤቶቹ ለአንድ ዘመናዊ ቴአትር ማሳያ የሚሆን የድምፅ፣ የመብራት እና ልዩ ልዩ ግብዓቶች ተሟልተውላቸዋል፡፡ የአየር ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በተወሰነ ርቀት የአየር ማቀዝቀዣ መሳርያዎች አሉ፡፡ ቅንጡ ባይባሉም ለቴአትር ተመልካች ምቾች ያላቸው ናቸው። የመድረክ ዝግጅቶቹ በድምፅ እና በመብራት ግብዓት ሳይቸገሩ ሃሳባቸውን በአግባቡ ማስተላለፍ እንዲችሉ የቴአትር ቤቶቹ ልከኛ አሰራር እንደረዳቸው መታዘብ ችያለሁ። ሁኔታው በሐገሬ ምድር ስለሚገኙት ቲያትር ቤቶች መብራት እና ድምጽ ሁኔታ እንዳስብ አስገድዶኛል፡፡ የጎላው ልዩነት ሀዘን እንዲገባኝ ቢያደርግም፤ ባለሙያዎቻችን ይህንን ችግር ተቋቁመው በየሳምንቱ ቴአትር ማሳየታቸውን ሳስብ በብርታታቸው እደነቃለሁ።

በፌስቲቫሉ ከምርምር አቅርቦት፣ ከቲያትር ምድረካ፣ እና መሰል ተሳትፎዎች ባሻገር አጫጭር ስልጠናዎች ለቴአትር ተማሪዎች እና ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡ በስልጠናው በልዩ ልዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል። በኒው ዮርክ የታወቀው የሙከራዊ ቴአትር አዘጋጅ ሊ ብሩየር፣ የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ፕሮፌሰሩ ፒተር ኢከርሳል፣ ዩጋንዳዊቷ የቴአትር ለልማት መምህር እና አዘጋጅ ፕሮፌሰር ጄሲካ ካህዋ፣ ጃፓናዊቷ የዳንስ አሰልጣኝ ሺሚ ፉኩኦርጂ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከአስራ ሁለት በላይ ከመላው ዓለም የተጋበዙ ባለሞያዎች እና መምህራን ስልጠናዎችን ሰጥተዋል፤ ልምዳቸውን አካፍለዋል። የአንጋፋዎቹ ልምድ ለወጣት የቴአትር ባለሙያዎች ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።  የዘንድሮውን የቴአትር ፌስቲቫል ለየት የሚያደርገው ግብፅ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር በምትዳክርበት እና “አፍሪካዊነቷን” ለዓለም ለማስመስከር በመትሞክርበት ጊዜ መሆኑ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት በዚሁ ፌስቲቫል ላይ ተሳታፊ በነበርኩበት ወቅት፤ የፊስቲቫሉ መሪ ቃል እና የጥናታዊ ፅሁፎች ማቅረቢያ ርዕስ “Theatre between Heritage & The City (ቴአትር በቅርስ እና በከተሞች መሀል)” ነበር። የዚህኛው ዓመት ሙሉ ትኩረቱን ለአፍሪካ የቴአትር እና የክዋኔ ጥበብ ሰጥቶ ርዕሱን “Contemporary African Theatre (ወቅታዊው የአፍሪካ ቴአትር)” አሰኝቶ ተገኝቷል። በመድረኩም በአፍሪካ ቴአትር ላይ ልዩ ልዩ ጥናቶችን የሰሩ ግለሰቦች ጥናታቸውን አቅርበዋል። እኔም ስለ ሀገራችን ቴአትር አሁን በመድረክ ላይ ያሉ እና ታይተው የወረዱ ቴአትሮችን እንደማሳያ በመውሰድ ጥናቶቼን በሁለቱም ተሳትፎዬ አቅርቤአለሁ።

በተለይ ሉላዊነት በተጫነው የዘመናዊው የዓለም ከፌስቲቫሉ ጎን ለጎን ይህ የግብፅ “አፍሪካዊነትን” ለማስመስከር የሚደረግን መዳከር ለሌሎች ሐሳቦች ይገፋናል። በፖለቲካ ከአንድ ወገን ጋር ብቻ የሚደረግ ቋሚ ወዳጅነት እንደማይሰራ የግብፅ ተግባር ማሳያ ይመስላል። ሀገሪቱ ለረዥም ጊዜ ስትከተለው የነበረው የግብፅ “ዓረባዊነት”፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተሻሽሎ “አፍሪካዊነቷ”ን ለማሳየት እየጣረች ነው። ይህ የፖለቲካ ለውጥ በቴአትሩ ፌስቲቫል ላይ ገብቶ ስለ “አፍሪካ” ቴአትር ለመወያየት መንገድ ከፍቷል። በተለይ በጥናታዊ ወረቅት አቅርቦቴም ሆነ ሌሎች ሲያቀርቡም በተደረጉ ውይይቶች እንደታዘብኩት፤ የግብፅ ሰፊው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከአፍሪካ ተገላይነትን ላለማቀንቀን እና አፍሪካዊነትን ለማቀፍ ሙከራ ለማድረግ እንደሚታትር የሚያሳይ ነበር። ከዚህ ጎን ለጎን አብዛኛው የግብፅ ህዝብ ከሰሃራ በታች ስላሉ አፍሪካዊያን የህይወት እውነታ ይልቅ ስለ መካከለኛው ምስራቅ የአረብ ህይወት እና ዕውነት የተሻለ እውቀት እና ግንዛቤ አለው። የግብፅ መንግሥት የፖለቲካ አቅጣጫ የፌስቲቫሉን ዋና ጭብጥ ከመምራት ባሻገር ፌስቲቫሉን እና የቴአትርን ጥበብ ለፖለቲካው ዓላማም በሰፊው ተጠቅሞበታል። ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተጋበዙ የቴአትር ቡድኖች የሀገራቸውን ባህል እና እውነታ የሚያሳዩ ቴአትሮችን ሲያቀርቡ አስደሳች በሆነ ሁኔታ አጅግ የበዙ የቴአትር ተመልካቾች፣ የቴሌቪዥን፣ የሬድዮ እና የህትመት ሚዲያ ጋዜጠኞች የየቀኑን ሁኔታ በሰፊው ዘግበውታል። በዚህም ለግብፅ ህዝብ በቴአትሮቹ እና በመላው ፌስቲቫል ስም በተለይ ከሰሀራ በታች ስላለው የአፍሪካ ክፍል ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። የጥናታዊ ፅሁፎች አቅርቦትም የሚያሳየው ይህንኑ ነው። በመሆኑም የቴአትርን ጥበብ በሚገባ በመጠቀም የፖለቲካ ሀሳቡን በማስረፅ ረገድ የግብፅ መንግሥት በሚገባ ተሳክቶለታል።

የካይሮ ዓለም ዓቀፍ የዘመናዊ እና ሙከራዊ ቴአትር ፌስቲቫል ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት “ወሰንን መሻገር” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር እና የተለያዩ ባለሙያዎች (አዜብ ወርቁ፣ መዓዛ ወርቁ፣ ሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) እና ሌሎችም) በመተባበር የተዘጋጀውን ፌስቲቫል ያስታውሳል። በፌስቲቫሉ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ምሁራን፣ የቴአትር ባለሙያዎች እና የስልጠና ባለሙያዎች የተሰባሰቡበት ነበር። እኛም ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን እና ከባህል ማዕከሉ የቴአትር ባለሞያዎች ጋር “የብርሀን መንገድ” የተሰኘ ሙከራዊ ቴአትር በብሄራዊ ቴአትር አቅርበን ነበር። ፌስቲቫሉ እንደታሰበው በየዓመቱ አለመደረጉ የካይሮው ፌስቲቫል ያመጣውን (እንዲያም ሲል ከፍ ባለ ሁኔታ!) በረከት ለአዲስ አበባ የቴአትር ተመልካቾች ማምጣት በቻለ ነበር። ምናልባት የ ‘ወሰንን መሻገር’ አዘጋጆች ጉዳዩን በሚገባ አስበውበት እና ተገቢ የሚሆን ድጋፍም ካገኙ ዳግም የሚያጤኑት ይመስለኛል። ወይም እንዲያጤኑት እመኛለሁ!

የቴአትር፤ በሰፊው ደግሞ የኪነ-ጥበብ እና ስነ-ጥበብ ፌስቲቫሎች ዝግጅት ለጥቂት ሙያውን ለሚወዱ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ሰፊው የከተማው ነዋሪ፣ ከዚያም ከፍ ሲል ለአዘጋጅ ሀገራት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የተለያዩ ሀገራት ባለሙያዎች ወደ ከተማው (ሀገሪቱ ከመምጣታቸው ባሻገር፣ የሀገሪቱን የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ለዓለም ዓቀፍ ዐይን ይፋ በማድረግ ባለሙያዎች የዓለም አቀፍ ተመልካችነት እና ታዋቂነት ዕድል ያገኛሉ። ከዚህም ባሻገር ወጣቶች ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሚመጡ ባለሙያዎች እውቀትን በመሸመት አዳዲስ የጥበብ አሰራር እና አመለካከትን ያዳብራሉ። አዘጋጅ ሀገራት ከፍ ያለ የመታየት እድል ያገኛሉ፡፡ ስራው በራሱ የሚፈጥረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት ሐገሪቱን ጨምሮ ሥራው ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ዕድል ይፈጥራል። የካይሮውን ዓይነት ተመሳሳይ ዓለም ዓቀፍ የዘመናዊ እና ሙከራዊ ቴአትር ፌስቲቫል ኪነ-ጥበባዊ እና ህዝባዊ ትዕይንቶች ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው።

በእኛም ሀገር “ወሰንን መሻገር” የመሰሉ የቴአትር ፌስቲቫሎች ቢበረታቱ እና ቢደገፉ የግብፁን የካይሮ ዓለም ዓቀፍ የዘመናዊ እና ሙከራዊ ቴአትር ፌስቲቫል የመሰሉ ወይም የተሻሉ ሆነው ሀገሪቱም ከኪነ-ጥበብ ዘርፉ ልታገኝ የሚገባትን ጥቅም ልታገኝ የምትችልበትን ዕድል ይፈጥራሉ። ከሁሉ በላይ ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከሀገራቸው ወጥተው ዓለም ዓቀፍ ልምድ እና ተጨማሪ ዕውቀት እንዲሸምቱ ድጋፉ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የሀገራችን መንግሥት እና በዘርፉ የሚሰሩ ተቋማት ለእንዲህ ያለው ድካም ዋጋ በመስጠት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top