ጣዕሞት

የ‘ቅምሻ’ ጣዕሞች

አንድ ሁለት እያልን ከሁለት ወራት በላይ ላገባደድንለት 2012 ዓ.ም. መቀበያ የሚሆኑ በርካታ የሙዚቃ አልበሞች ከ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ለአድማጭ ደርሰዋል። ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ቴዎድሮስ ሞሲሳ፣ አስቴር አወቀ፣ ዘሩባቤል ሞላ፣ አቡሽ ዘለቀ፣ ፀዲ፣… የአልበም ሥራዎችን ካበረከቱት ውስጥ ይጠቀሳሉ። ሙሉ የአልበም ሥራቸው እጃችን ከገባ ድምጻዊያን መካከል አንዷ የሆነችው ሐመልማል አባተን ሥራዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች በወፍ በረር ለመቃኘት እንሞክር፡፡

ሳጣው ነው እኔስ የሚከፋኝ

ሳጣው ነው ቅር ቅር የሚለኝ

ሐሳብ የሚገለኝ

ወዴት ይሆን ዘንድሮስ የራቀኝ

ያ የማውቀው ቁምነገር ናፈቀኝ

የነበረንን ሐገራዊ እሴት የሚንዱ ሲበረክቱ የታዘበ፣ ጨዋነታችን፣ ሕብረታችን፣ አንድነታችን ሲሸረሸር ያስተዋለ የቋጠረው ስንኝ ነው። ሐመልማል አባተ በውብ ድምጽዋ ያቀነቀነችው ይህ ዜማ ግጥም- እና ዜማው በሰኢድ መሐመድ ተሰርቷል። ቅንብሩ የአዲስ ፍቃዱ ነው።

የጎደለኝ አንድ ነገር አለ

ያደግንበት ቁምነገር የት ዋለ

.

የታል ሽማግሌው አስታራቂው

እድሜ ያስተማረው ብዙ አዋቂው

.

አንተ ትብስ አንቺ መባባሉ

ኧረ ወዴት ጠፉ ወዴት ዋሉ

ድምጻዊያንን ለግጥም እና ዜማ ስራ ማመስገን ተገቢ አይደለም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ እምነት ግን ከሐሳቡ ጋር አይሰምርም። አሁን የምንገኘው ዘፈን በግለሰብ ጥረት ብቻ የሚሰራበት ጊዜ ላይ ነው። የሚዘፍናቸውን ግጥሞች የሚመርጠው፣ ዜማ የሚሰበስበው፣ አቀናባሪ ፈልጎ ከፍሎ ቅንብሩን ገምግሞ የሚያጸድቀው ድምጻዊው ነው። የዘፋኙ ሚና በመዝፈን ብቻ አያበቃም፤ ሁሉም ውስጥ እጁ አለ። ማከፋፈል እና ማስተዋወቅ ድረስ ዘፋኙ አለበት። ለገጣሚያን ሐሳብ ሰጥቶ የሰጠውን ሐሳብ እስከማጻፍም ይለጠጣል፡፡ ስለዚህ ድምጻዊያን ግጥም እና ዜማ ባይሰሩም የተባለውን ሐሳብ ወደው፣ መርጠው፣ በሐሳቡ አምነው ስለሚያቀርቡልን ምስጋና ይገባቸዋል። ሐመልማል በ‹‹ቅምሻ›› አልበሟ ሽፋን ላይ ካሰፈረችው የምስጋና ቃል ለአባባላችን ማስረጃ የሚሆን ቃል እንጥቀስ

 “አብረን ለፍተን፣ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ስራችሁን እዚህ አልበም ውስጥ ስላላካተትኩት፣ የግጥም እና የዜማ ደራሲዎችን እጅግ በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ።”

ለዚህ ነው የሰማናቸው የግጥም ሀሳቦች ተሰርተው ለኛ ከማይደርሱት ውስጥ ባለመካተታቸው ምስጋናችንን ልንቸር የወደድነው፤ ሐመልማል አባተን ለዚህ ዘፈን ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም ከፍ ያለ ሐሳብ ላዘሉት ዘፈኖቿ እናመስግናትና ነገራችንን ከመቀጠላችን በፊት የበዛው ምስጋናችን እያንዳንዱን ከሐሳብ እስከ ሽያጭ ባለው ሰንሰለት ያሉትን ተሳታፊ ባለሙያዎች ያልዘነጋ መሆኑን እናሳውቅ፡፡

በዓላት በመጡ ቁጥር “እንኳን አደረሳችሁ!” በሚለው ዜማዋ ዕለቱን የምታሳምረው ሐመልማል በዛ ያሉት አልበሞቿ የወጡት በበዓላት ጊዜ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህ ለምን ሆነ የሚል ጥያቄ ተጠይቃ ተከታዩን ምላሽ መስጠቷ አይዘነጋም።


“አጋጣሚ ነው። ከዚህ በፊት “አውደ ዓመት” የሚል ካሴት ለአዲስ ዓመት አውጥቼ ነበር። ከዛ በኋላ ሠው ሁልጊዜ ለአዲስ ዓመት ካሴት የማወጣ ይመስለዋል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የአሁኑም አልበሜ ሄዶ ሄዶ አዲስ ዓመት ጋ ደረሠ። በዚህ ደሞ ደስተኛ ነኝ።” (ይህ ንግግር ከመጨረሻው አልበም በፊት የተደረገ መሆኑን ልብ ይሏል።)

በቅርብ ሳምንታት እጃችን ገብቶ እያጣጣምነው የምንገኘው “ቅምሻ” አልበምም ለህዝብ ጆሮ የደረሰው በዐዲስ ዓመት ዋዜማ ነው። የቅምሻ አልበም የሐገር ውስጥ አከፋፋይ ‹‹አርዲ ኢንተርቴይመንት›› ሲሆን ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰሩ “አመል ፕሮዳክሽን” ነው።

“በሙዚቃው መገስገስ ነው የምፈልገው፤ ከራሴ ስራ አልፌ የሌሎችን ፕሮዲዩስ ማድረግ እፈልጋለሁ። ‘አመል ፕሮዳክሽን’ የተባለ ድርጅት አቋቁሜያለሁ፤ በዛ በኩል የሌሎችን ስራዎች ለማሳተም እቅድ አለኝ።” ሰትል ከአሁኑ አልበሟ በፊት የተናገረቸው ሐመልማል የሌሎችን የማሳተም እቅዷ የሰመረ ባይመስልም “ቅምሻ” ከሚለው አልበሟ ጋር በድርጅቱ በኩል ሁለተኛውን አልበሟን ለአድማጭ አድርሳለች።

አሰበ ተፈሪ ጭሮ ያደገችው፣ በቤተክርስቲያን ዝማሬ ድምጽዋን ያሟሸችው፣ በትርፍ ጊዜዋ ማብሰል እና አትክልቶችን መንከባከብ የምትወደው ድምጻዊት ሐመልማል የድሮ እና የዘንድሮን የአልበም ስራ እንዲህ አነጻጽራዋለች።


“የመጀመሪያ ካሴቴ የወጣ ጊዜ እኮ እንደ አሜሪካ ሰለብሪቲ ነበር የምንሠራው። ሁሉም ነገር በአሳታሚው በኩል ነው የሚያልቅልሽ። አሁን ግን በኮፒራይት ጥሰት የተነሳ ነጋዴው ከስራው ወጥቷል። ያሉትም ቢሆኑም በጣም እየከበዳቸው ነው። ብዙ ብር ካወጡ በኋላ ስራው ኮፒ ስለሚሆን አይደፍሩትም። አሁን ትንሽ ለውጥ አለ። እስከዛው ግን በግላችን እየሞከርን ነው። አልበም ሲሰራ ብዙ ወጪዎች አሉ። አልበሙን ካስደመጥን በኋላ ከኮንሠርት እናገኛለን በሚል ነው የምንሰራው።”

ቅምሻ የተሰኘው የሐመልማል አባተ አልበም 14 ቀፈኖች ተካተውበታል። ታደሰ ገለታ፣ ተስፋ ብርሃን፣ አብዲ፣ ሰኢድ መሐመድ እና ድምጻዊ እሱባለው ይታየው (የሺ)ን ጨምሮ 6 ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል። አዲስ ፍቃዱ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ወንድሜነህ አሰፋ በቅንብር የተሳተፉ ናቸው። ዳዊት ፍሬው ክራር፣ እንድርያስ መሐመድ ማሲንቆ ተጫውተዋል።

ከዚህ ቀደም ባሉት የዘፈን አልበሞቿ የኦሮምኛ እና የጉራጊኛ ዘፈኖችን መጫወቷ ይታወሳል። በዚህኛው አልበምም “ሸጎዬ” እና “ጋዲሴ” የተሰኙ ሁለት ዘፈኖች አካታለች። “የኔ ቢጤ” የተሰኘው ዘፈን ደግሞ  ለአምላክ የቀረበ ልመና እና ምስጋና ነው። “ደሞ መሸ” ተደጋግመው ከተዘፈነባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ነው። “ከላይ ነው ትዕዛዙ” ደግሞ በዘወትራዊ ንግግራችን ውስጥ ያሰለቸ ቃል በመሆኑ ለዘፈኑ በጠሪያ ቃልነት ባያገለግል መልካም ነበር ብዬ አስባለሁ።

አብዛኛዎቹ የሐመልማል አባተ “ቅምሻ” ውስጥ የተካተቱ ዘፈኖች በወንድ እና ሴት የፍቅር ግንኙነት ውስጥ እንዲያጠነጥኑ ተደርገው ተሰርተዋል። ይሁን እንጂ የሚያስተላልፉት ከሁለት ሰዎች የፍቅር ውጣ ውረድ በላይ የሆነ መልእክት ነው። ተደጋመው ሲደመጡ ፖለቲካዊ ቅርጽ እንዳይዙ በማሰብ ሆን ተብሎ በሴት እና ወንድ ግንኙነት ሰበብ እንዲገለጹ የተደረገ ይመስላል።

የጥበብ ሥራዎችን ብያኔ ውስጥ ለመክተት ከምንጠቀምባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ የቀረቡበት ጊዜ ነው። አርቲስቱ ምን አስቦ፣ እንደምን ያለ ከባቢያዊ ሁኔታ ላይ ሆኖ ሰራው የሚለው አንዱ የብያኔ ገፊ ሰበብ ነው። በአጠቃላይ አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ፣ ዘፈኑ የተሰራበትን እና ለአድማጭ የደረሰበትን ጊዜ ስናስብ ከሰሙ በላይ እንድናደምጠው፣ ወርቁን ፈልፍለን እንድናወጣ ያስገድዶናል።

በዚህ አውድ ውስጥ ሆነን “ራሴን ነኝ”፣ “እንታረቅ”፣ “ተው ስማኝ” የተሰኙትን ዘፈኖች እያነሳን እንጨዋወት።

 የ“እንታረቅ”ን ግጥም የጻፈው ፍሬዘር አበበወርቅ ነው።  ዜማውን የሰራው ማስተዋል እያዩ ሲሆን ቅንብር እና ማዋሃዱን አዲስ ፍቃዱ ከውኖታል። ሐመልማል አባተ ውብ አድርጋ ተጫውታዋለች።

አስታራቂ ጠፍቶ አንድ እኛ ላይ ባይ

ቀረን ባዋጅ ወጥተን በያ’ደባባይ

ቂም ውስጥ የሚገኝን ገጸ ባህርይ የምታዋይ ገጸ ባህርይ አለችበት። ወዳጇን- ሊያውም የተጣላችውን ሰው እንታረቅ የምትል የፍቅር ሰው፤ ጸጸቷን ለመንገር ድፍረት ያላት ሴት፣…

ሁሉን ቻይ ጠፍቶ እንጂ ጥርስ ነክሶ ከንፈር

የሚያደርሰን እዚህ ነገሩስ አልነበር

ጠብ እና ክርክር የዘወትር ዜና እየሆነ በምንኖርባት ሐገር ይህንን ዘፈን ለሁለት ሰዎች ብቻ የተዘፈነ አድርጎ ማሳነስ በደል ነው። እንዲህ በዋዛ ሳይጎረብጠን፣ ሳያስቆጣን ምክር ቢጤ ጣል ማድረግ ደግሞ የጥበበኛ ተግባር ነው።

አይለያዩም መስከረም እና አደይ

እስኪ እኛም ታርቀን እንሁን አንድላይ

ከፋ ብዬ አልከፋም ወዳጅ ጨከነብኝ አሳዘነኝ ብዬ

ይቅር ከኔ ይለፍ ማንነቴን ልውደድ የያዝኩትን ይዤ

መጽሐፍ “ክፉን በክፉ አትቃወሙ” እንዲል የዚህ ዘፈን ሐሳብ ክፋትን በሌላ ክፋት አትመልስ ነው። የተበደለች ሴት ይሁን ብላ የዛሬን በደል ጎንበስ ብላ ስታሳልፍ ያሳያል። ጊዜ ሁሉን እንደሚፈታ አምና ታንጎራጉራለች።

ይሁን ብዬ ቀን እውነቱን እስኪያወጣው

እኔ አልከፋም በሰው ምግባር በሁኔታው

የበደለ መካስ፣ ያጠፋ ጥፋቱን ማመን ብቻ ሳይሆን፡- ማሳለፍ፣ ዝም ማለት፣ የሆነን እንዳልሆነ ማየት፣… አሁን ላለንበት ጊዜ የሚያስፈልገን ክህሎት ነው። ራስን ብቻ መወከል፤ በራስ ሐሳብ ብቻ መቆም፤ ማንነትን መውደድ፤…

ገፉኝ ብዬ ላልገፋ

ከፉ ብዬ ላልከፋ

ሰው አለ ብዬ ላልልህ

እንደራሴ ነው እምውልህ

ሄዱ ብዬ ላልሄድ

ወደዱ ብዬ ላልወድድ

እኔ ነኝ ሁሉን የምለምድ

እንደራሴ የምራመድ

የዛሬው ኑሯችን፣ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም የሚያስፈልገን ምክር በዜማ ሲቀመር ይህንን ይመስላል። ግጥም ሆኖ፣ ዜማ ለብሶ ሲቀርብ….

ነገር አላሳድር ቻል አድርጌ ልርሳ

እኔን እንዳልጥለው የሌላን ሳነሳ

ቀጣይ ማረፊያችን “ተው ስማኝ” ይሰኛል። በአብዛኘው ዘፈን ውስጥ ያለችው ሴት (እኔ ባይ ገጸ ባሕርይ) ተሸናፊ ናት። በደሏን ውጣ፣ መገፋቷን ቸል ብላ ፍቅርን ታስቀድማለች። “ተው ስማኝ” ላይም ተመሳሳይ ድምጽ ይሰማል። ዋናዋ የዘፈኑ ተዋናይ ይቅር እንባባል የምትል ናት። “በፊት እንዴት ነበርን አሁን ወሬ ሰምተን እንዲህ የሆንነው?” ትላለች። የትላንቱን ፍቅር እንመልሰው፤ እንዲህ አልነበርንም መስማማት ይሻላል ትላለች። አስጨፋሪ ዘፈን ቢሆንም በትከሻ ብቻ ሳይሆን በልቦናችን እንድናደምጠውም ያስገድደናል።

ከመቼ ወዲያ ነው ከመች ወዲህ ደግሞ

በኔና አንተ መሐል አስታራቂ ቆሞ

.

መጣላታችንን ዞረን ብናወራ

ያ’ስታራቂ ያለህ ብለን ሰው ብንጣራ

እውነት ነው የሚለን ማን ይኖራል ከቶ

በዚህ አያውቅም እና ስማችን ተነስቶ

ሊነገር የተፈለገው ነገር ቃል በቃል ሳይጠራ መልእክት እንዲህ መተላለፍ ይችላል። የሚለውን አስረግጠን የተመለከትንበት የሐመልማል አባተ አልበም ያሉት በረከቶች እነኚህ ብቻ አይደሉም። ሌሎቹን ደግሞ በሌላ ጊዜ እንዳመቸን እንመለስባቸዋለን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top