በላ ልበልሃ

ውህደቱ እና የፖለቲካ ባህላችን

ውህደቱ እና የፖለቲካ ባህላችን

በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ትኩረትን ለመሳብ ከበቁ ሰሞነኛ ጉዳዮች መካከል “የኢህአዴግ ፓርቲዎች ውህደት” እና በቀጣይ ሊመሰረት የታሰበው “የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ” ተጠቃሾች ናቸው። የውህደቱም ሆነ የአዲሱ ፓርቲ ሐሳቦች እውን እንዲሆኑ የሚጎተጉቱ እንዳሉ ሁሉ፤ በጥርጣሬ የተመለከቱት፣ ጊዜው አሁን አይደለም ብለው የሚያምኑ፣ እንደ ሀገር የነበረንን ቁመና ያፈርሳል ብለው የሰጉ፣… እና መሰል ግብረ-መልሶችን አስተናግዷል። ለሩብ ክፍለ ዘመን አገሪቱን ያስተዳደረው የኢህአዴግ እጣ ፈንታ የሀገሪቱን ቀጣይ እርምጃ እስከመወሰን ድረስ የተራዘመ ተጽዕኖ እንዳለው እየተስተዋለ የሚገኝ ሀቅ ነው። የኢህአዴግ ፓርቲዎች ውህደት እና የአዲሱ ፓርቲ ምስረታ የተቆራኘ ዕድል ይዘው በመድረኩ እንዲሰየሙ የተደረገበት ሁኔታ ግራ አጋቢ ነው።  የአንዱን ትንሳኤ የሚወልደው የሌላኛው ሞት ሆኗል።  

ውህደትን እንደ መዳኛም ሆነ መጥፊያ መመልከት ስህተት እንደሆነ የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። ምሁራኑ ሁለቱንም ወገን የተቃረነ ሐሳብ አላቸው። ተፈትሾ ሳይረጋገጥ ውጤቱን ከጅማሬው መበየኑን አይቀበሉም። እንደ አባባላቸው ጥሩም መጥፎም ለማለት ጊዜው ገና ነው። አብዝተው የደገፉም ያለ ምክንያት እየተቃወሙ የሚገኙም ስተዋል።

የዕቅድ፣ የፕሮግራም፣ የፖሊሲ፣ የህግ፣… እና መሰል ረቂቆች አስፈላጊነት ይህንን ውዥንብር ማጥራት ነው የሚሉት ወገኖች ደግሞ ግለሰብን ከመውደድ እና ከማመን የዘለለ ድርጅታዊ ቁመና ያስፈልጋል ሲሉ ይሞግታሉ። የሚያሰባስብ ሀሳብ ያለው ድርጅት ተፈጥሮ በምክንያት የሚቃወም ወይም ስብስቡን ለመቀላቀል የማይፈልግ ካለም ከምንም ነገር ጋር ሳይጣበቅ ሀሳቡ ሊከበርለት እና ሊታመን ይገባል፤ የሀሳባቸው መቋጫ ነው።

የዴሞክራሲ ስርዓት ምሳሌ ተደርጋ የምትቆጠረው ልዕለ-ኃያሏ አሜሪካ ከምስረታዋ ጊዜ አንስቶ ስድስት ዓይነት የፓርቲ ዘይቤዎችን አስተናግዳለች። ዘይቤዎቹ እንደ ማኅበረሰቡ ወቅታዊ ጥያቄ፣ እንደፖለቲከኞቹ አጀንዳ እና ሌሎች ገፊ ምክንያቶች የሚቀያየር ቢሆንም፤ ከ3ኛው የፓርቲ አሰራር ስርአት በኋላ (1854-1890) ሁለቱ ትላልቅ ፓርቲዎች ዴሞክራቲክ እና ሪፐብሊካን ከብዙ ፓርቲዎች ጋር ተዋህደው ጥንካሬ አበጁ። ከ1856 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመሃላቸው ንፋስ ሳያስገቡ አሜሪካንን በምርጫ እየተፈራረቁ እየመሩ እንደሚገኙ Donald T. Critchlow የተባለ ምሁር American Political History: A Very Short Introduction በሚል መጽሐፉ አስነብቧል።  አሜሪካ ውስጥ ከታዋቂዎቹ የዲሞክራቲክ እና ሪፐብሊካን ፓርቲዎች በተጨማሪ ሌሎች አነስተኛ ፓርቲዎችም ይገኛሉ። ከእነሱም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ሊብሪቴሪያን ፓርቲ (Libertarian Party)፣ ግሪን ፓርቲ (Green Party) እና ኮንስቲቲዩሽን ፓርቲ (Constitution Party) ይጠቀሳሉ።  

ከዚህ የስኬት ታሪክ የውህደትን ውጤታማነት እንመለከታለን። አለመዋሀድ የጎዳቸው ፓርቲዎች መኖራቸውም ሌላ ሀቅ ነው። ለምሳሌ ከአሜሪካ በላይ ብዙ ቁጥር ያላቸው ፓርቲዎች ያሏት ታላቋ ብሪታንያ፤ 3 ጠንካራና ለመንግሥት ስልጣን ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሏት። ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ያገዘፉት እና ደጋፊዎቻቸውን ያበረከቱት በውህደት አይደለም። ኮንሰርቫቲቭ (Conservative)፣ ሌበር (Labor) እና ሊብራል (Liberal) ይባላሉ። ባለፉት 20 ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የቻሉት ቶኒ ብሌር፣ ጎርደን ብራውን፣ ዴቪድ ካሜሮን እና ተሬዛ ሜይ ሁሉም የሌበር እና ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አባላት ናቸው። ይኼኛው የእንግሊዝ ተሞክሮ ደግሞ ቁምነገሩ ያለው መልእክቱ እና ህዝብን ማገልገሉ ላይ እንደሆነ ያስረዳናል።

በኢትዮጵያ ሁኔታም ውህደት፣ ግንባር፣ ቅንጅት፣ የጋራ ስምምነት፣… እንግዳ ተግባር አይደሉም። ‹ቅንጅት› እና ‹ሕብረት› የቅርብ ጊዜ ተጠቃሽ ናቸው። ከ1980ዎቹ ጀምሮ ያለውን ለመመልከት ብንሞክር ‹ሳውዘርን ፍሮንት አጌንስት ኖርዘርን ሄጂሞኒ› ከሚለውን የሌንጮ ለታ ስብስብ ጀምሮ እስከ ኢዜማ ውህደት ድረስ ብዙ እንቆጥራለን። የኢዴፓ እና የመድህን ውህደት፣ የደኢህዴን እና የኢህአዴግ ግንባር መሆን ለሁለት አሰርት ዓመታት የቆዩ ናቸው። አብዛኛዎቹ መጀመሪያቸውም መጨረሻቸውም የሚታወቅ ናቸውና ዝርዝሩን እንዝለለው።  

በጠቃቀስናቸው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የፓርቲዎች ጥንካሬ የሚመሰረተው ርዕዮታቸው እና አካሄዳቸው ላይ መሆኑን ተመልክተናል። መዋሃድ ሊጠቅምም ላይጠቅምም ይችላል። እንከኑ እና ጥንካሬው የሚለካው ከውህደቱ በኋላ በሚያስመዘግበው ውጤት ነው።

ርዕዮተ ዓለምም ብቸኛ መዳኛ አይደለም። ፓርቲዎች በተለያየ ምክንያት ርዕዮተ-ዓለማቸውን ይቀይራሉ። ለዚህ ትልቅ ምሳሌ የሚሆነው የቻይናው ሲሲፒ (Chinese Communist Party) ነው። በማኦ ዘመን ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ይከተል የነበረው ሲሲፒ በተለይም ከቻይና የባህል አብዮት በኋላ፣ የካፒታሊዝም አስተሳሰቦችን ወደ ፕሮግራሙ አስገብቷል። ምንም እንኳ የቻይና መንግስት አሁንም በኮሚኒስት ስርዓት ውስጥ ነን ቢልም፤ ነፃ ገበያን በመተግበር እና ባለሃብቶችን የሚጠቅም ፖሊሲ በመቅረፅ ከካፒታሊስት ሃገሮች በላይ የካፒታሊዝም አስተምህሮዎችን ሲተገብር ተስተውሏል።  

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ‹የኢህአዴግና የአጋር ድርጅቶች የውህደት ሂደት እና ያለበት ደረጃ› በሚል ርዕስ የተሰጠው ማብራሪያ፣

 “ …የውህደት ሂደቱ በአሁኑ ሰዓት ወደ መጨረሻው ደረጃ እየተጠጋ ነው።… እንደሚታወቀው የኢህአዴግ የውህደት ሃሳብ እና ጥያቄ ታሪካዊ ዳራን ስንመለከት ረዘም ያሉ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። ጥያቄው በኢህአዴግም ደረጃ እንዲሁም በአጋር ድርጅቶችም ሲነሳ ቆይቷል።… በውህደቱ ዙሪያ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከሁሉም አካባቢ የተውጣጡ ከፍተኛ ምሁራን ጥናት ሲያደርጉበት ነበር። ጥናቱ አንደኛ ከኢህአዴግ አኳያ፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአጋሮች አካባቢና በህዝቡ ምን ዓይነት ፍላጎት አለ? የሚሉት የጥናቱ አጀንዳዎች ነበሩ። በዛ ላይ ተመስርቶ በለውጡ ሂደት አምና ሃዋሳ ላይ በተደረገው 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ይሄንን ጥያቄ በተመለከተ በባለፉት ጉባኤዎች ጥናቱ ተጠቃሎ እንዲቀርብ ተወስኖ በመቆየቱ እና ለጉባኤው ሊደርስ ባለመቻሉ “ለምን?” የሚሉ ጥያቄዎች በርከት ብለው ተነስተው ነበር። በዛም ተመርኩዘን በሁሉም የኢህአዴግ ፓርቲዎች ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ውስጥ የምሁራኑ ጥናት እንዲቀርብ ተደርጎ ተመክሮበት በአጋሮችም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ተመክሮበት፤ አሁን በስራ አስፈፃሚ ፓርቲ ደረጃ ከውሳኔ ሊደርስ በቅቷል”

ማለታቸው አይዘነጋም።  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ በሁሉም የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተላለፈው በዚህ ማብራሪያቸው አዲስ የሚመሰረተውን የብልጽግና ፓርቲ በተመለከተም እንዲህ ብለዋል።

“…የብልፅግና ፓርቲ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚሰራ ፓርቲ ነው። አዲሱ ፓርቲ አሁን የሚታዩትን የተካረሩ ፅንፎችን በማለዘብ ልዩነትን ባከበረ መልኩ ብሔራዊ አንድነትን የሚፈጥር ነው። ፓርቲው ብሔራዊ የጋራ ማንነትን በኢትዮጵያ ደረጃ ለማምጣት እና ያለፉ ስህተቶችን ለማረም የሚሰራ ነው…”

ከጋዜጠኞች ከቀረበላቸው ጥያቄዎች መካከልም “ህወሓት ለምን በስራ አስፈፃሚው ስብሰባ ላይ በተነሳው የውህደት ሃሳብ ከሌሎች ተለይቶ ተቃውሞውን በአባላቶቹ አሰማ?” የሚል ይገኝበታል። ለዚህም ሲመልሱ፡-

“ልዩነቶች በፓርቲዎች ውስጥ ሁሌም አሉ። በህወሓት በኩልም በዚህ ጉዳይ ላይ ስላላመኑበት የተቃውሞ ድምፅ ሰጥተዋል። ቢሆንም ግን አብላጫው በሰጠው ድምፅ ተወስኗል። መለያየት ማለት መጣላት አይደለም… በውህደቱ ላይ ጥያቄ እና ጥርጣሬ ያላቸው በሂደት ሃሳባቸውን ይቀይራሉ የሚል ተስፋ አለኝ” ብለዋል።

        የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው ከኢ.ቴ.ቪ. ዜና ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ በስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ውስጥ ስለተደረገው ስብሰባ እና ስለተደረሰበት ውሳኔ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከማብራሪያው ውስጥም “…ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች እና ብሔረሰቦች በሚመሰረተው ፓርቲ ውስጥ በኢህአዴግ ከነበረው በተሻለ ውክልና ይኖራቸዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።  

        የህወሓት ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ከቪኦኤ የትግርኛ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ የሚከተለውን ብለዋል፡-

“የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ማድረግ የነበረብን ነሐሴ ላይ ነበር። የየፓርቲው ስብሰባ ተደርጎ ለኢህአዴግ ሪፖርት መደረግ ነበረበት። እኛም ስብሰባ አድርገን ለኢህአዴግ ሪፖርት ያደረግን ቢሆንም፤ ሌሎች ፓርቲዎች ባለማድረጋቸው ስብሰባው ወቅቱን ጠብቆ መደረግ እያለበት (እንዲደረግ ስላልተፈለገም ጭምር) እስካሁን ድረስ ቆየ። ውህደቱን በተመለከተ የፓርቲው ሊቀመንበር የሚመራው ቡድን ያጠናውን ሪፖርት በዚህ ስብሰባ እንደምንወያይ ቀድሞ የታወቀ ነው። እኛ ግን የየፓርቲዎቹ ሪፖርት በሃገራዊ ሰላምና ደህንነት ዙሪያ እንዲሁም ቀጣዩን ምርጫም በሚመለከት መወያየት እንደሚገባን በስብሰባው ገለፅን። በእነዚህ ሁለት ርዕሶች ላይ በቂ ሪፖርት በተቀሩት ፓርቲዎች ላይ ያልቀረበ ስለሆነ ለቀጣይ ስብሰባ ይተላለፍ የሚል ሀሳብ በሊቀመንበሩ ተሰጥቶ በአብላጫ ድምፅ ተቀባይነት አገኘ። ከዛም ውህደቱን በተመለከተ በጥናቱ ላይ እንድንወያይ እንጂ ውሳኔ ለመስጠት አይደለም የተሰበሰብነው፤ ያም ሆኖ ግን ሁለቱም ሃሳቦች ይቅረቡ ብንወያይባቸውም ችግር የለውም ብለን ውይይቱ ቀጠለ። ፊዚካል ብቻ ውህደት ሳይሆን የአስተሳሰብ ውህደት ሊኖር እንደሚገባም አንስተን ተወያየን። ቀጥሎ ወደ ድምፅ መስጠት እንተላለፍ ሲባል ችግር መጣ። ውህደት ላይ የተነሱ የምሁራን ጥናቶች ድምፅ ተሰጥቶባቸው ልንወስን እንችላለን። ውህደት ግን የፖለቲካ ውሳኔ ነው። በእያንዳንዱ የውህደቱ አወቃቀሮች፣ ሂደቶች እና ነጥቦች ላይ በየእርከኑ ባልተወያየንበት አሁን ልንወስን አይገባም የሚል ሀሳብ እኛ አቀረብን። ሃሳባችን ውድቅ ተደርጎ ድምፅ ወደመስጠት ሲገባ የህወሓት አባላት ሙሉ በሙሉ ውህደቱን እንደማንቀበል የተቃውሞ ድምፅ አሰማን።” ብለዋል። ውህደቱን ያልተቀበሉበትን ምክንያት ሲገልጹም፣

“ሲጀመር በውህደቱ ጥናት ላይ እንጂ በውህደቱ ላይ ድምፅ ለመስጠት አልነበረም ስብሰባው ላይ የተገኘነው። ቀጥሎ ደግሞ በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እና ችግሮች ላይ ለመወያየት ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌለው አመራር፤ ለሚዲያ ማራገብ እና ሥልጣን ለማስረዘም ተብሎ ብቻ ከግል ጥቅም አንፃር ለመዋሃድ መሞከሩን ስለማንቀበለው ነው።”

የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ፍቃዱ ተሰማ የአካሄድ እንጂ የመርህ ልዩነት በውህደቱ ዙሪያ የለም  ማለታቸውን በመንተራስ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ጌታቸው ሲመልሱም፣

“በውህደቱ ላይ ምንም ዓይነት ስምምነት የለም። ለምሳሌ አቶ ፍቃዱ ራሳቸው የሚያስታውሱ ከሆነ ‹በምን ፕሮግራም ነው የምንዋሃደው?› የሚል ጥያቄ አንስተን፤ ሊቀመንበሩ ‹በመርህ ደረጃ ተስማሙ እንጂ የፕሮግራም ድራፍት በጥቂት ቀናት ውስጥ ጨርሼ አሳያችኋለሁ እመኑኝ› ብሎ ለምኖናል። እኛ ደግሞ ከማመን ካለማመን ጋር ይህ እንደማይያያዝ እና ይህ ከቆምንለት ዓላማ ጋር እንደሚፃረር አስረግጠን ነግረናቸዋል። መዋሃድ ለእኛ ችግር የለውም። ሃገር እስከጠቀመ ድረስ ትግራይን፣ አማራን፣ ኦሮሞን፣… ሁሉንም ብሄር እስከጠቀመ ድረስ ችግር የለብንም።  ቀድሞውንም በኢህአዴግ ፕሮግራም ውስጥ የነበረ ነው። እኛ የምንፈልገው ውህደት ግን በዓላማ፣ በአስተሳሰብ እና በርዕዮት አንድ በምንሆንበት ጊዜ ነው መሆን ያለበት። ጥናቱን ራሳችን ነው ያደረግነው። ሊቀመንበሩ ግን ያኔ ወስነን ወይም በመርህ ተስማምተን እንድንወጣ ፈልጓል።  እኛም ለሚዲያ ወሬ እና ርካሽ የስልጣን ፍላጎት ተብሎ የሚደረግን ውህደት እንደማንቀበል ነው የነገርናቸው። ከድምፅ መስጠቱ በኋላና በነጋታውም ልመናዎች እና ማባበሎች ነበሩ። የእኛን ሃሳብ ሊያስቀይር የሚችል ነጥብ ግን አልተነሳም” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በበኩላቸው የስብሰባውን መጠናቀቅ ተከትሎ ባስተላለፉት መልእክት፣

“ባለፉት 3 ቀናት የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲዎች እና የስራ አስፈፃሚ አባላት ውህደታችንን በሚመለከት እንዲሁም አዲሱን የፓርቲያችን ፕሮግራም ሕገ-ደንባችንንም በመወያየት በ3ቱም አጀንዳ ላይ ጥልቅ የሚያግባባ እና የሚያቀራርብ፤ እንዲሁም በአቀራረቡ እጅግ ዴሞክራሲያዊ የሆነ፣ ሁሉም ሀሳብ በነፃነት የተንሸራሸረበት ውይይት በማድረግ ውሳኔዎች አሳልፏል።›› ብለዋል።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማስከተል፣ 

‹‹ይህ ለፓርቲያችን አባላት እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ድል ስለሆነ፤ እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ።›› ያሉ ሲሆን የፓርቲውን ውሳኔዎች በማድነቅ ያስገኛሉ ያሏቸውን ጠቀሜታዎች ዘርዝረዋል።  

1ኛ/ እያንዳንዱ እርምጃችን ህግን የተከተለ እንዲሆንና በውይይት በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈፀም በማድረግ የተሳካ ውጤት ማምጣት ተችሏል።  

2ኛ/ የፌደራል ስርዓቱ አዳጊ፣ በየጊዜው የሚሻሻልና የሚያድግ በመሆኑ እስካሁን የነበሩበትን ስህተቶች በሚያርም ብዝሃ-ቋንቋ፣ ብዝሃ-ካልቸር፣ ብዝሃ-ፍላጎቶች ያሉባትን ሃገር ወጥ በሆነ መንገድ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዕውቅና በሰጠ እና ባከበረ፣ ሁሉንም ባሳተፈና በሚገባቸው ልክ፣ የሚያስፈልጋቸውን ማቅረብ በሚያስችል ማንነት የሚደራጅ ፓርቲ ሆኖ ተወስኗል። በዚህም አግባብ ፓርቲያችን ከአማርኛም በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛን የስራ ቋንቋ አድርጎ ከመወሰኑም በላይ እነዚህ ቋንቋዎች የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ እንደሚሰራም ወስኗል። ይህ ኢትዮጵያውያን አንዱ ከአንዱ ተምሮ በጋራ የጋራ ሃገራቸውን ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት ይበልጥ የሚያጠናክር እና እስካሁን ከነበረው በእጅጉ የላቀ ዕድገት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱ ህዝብ በልኩ የሚሳተፍበት እና ሌላውን የሚያከብርበት የዲሞክራሲያዊ አውድ ለመፍጠርም ከመግባባት ላይ ተደርሷል። ውይይቱ በጥቅሉ ለኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ያመጣ፣ ኢትዮጵያን በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ወደብልፅግና ተርታ ለማሸጋገር የነበረንን ትልም ለማሳካት በእጅጉ የሚያግዘን በመሆኑ በታላቅ ደስታ ያጠናቀቅን ሲሆን፤ መላው የድርጅታችን አባላት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እፈልጋለሁ።›› ሲሉ ንግግራቸውን በምስጋና ደምድመዋል።  

የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ የአጋሮች ተሳትፎ ነውን?

      በእርግጥም አጋር ፓርቲዎች እኩል የመወሰን ስልጣን በኢህአዴግ ውስጥ እንዳልነበራቸው ሁሉም የሚያውቀው እውነት ነው። ይህንንም ለመለወጥ እንደሚፈልጉ ያሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተለያዩ መድረኮች ላይ ገልፀዋል። ልብ ብለን መመልከት የሚጠይቀን አዲሱ መዋቅር ለአጋር ፓርቲዎች የሚያስገኘው ተጨባጭ ለውጥ ምንድነው የሚለውን ነው። 

የአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲ የህዝቦች ውክልና በህዝብ ቁጥር ነው ይላል። አብዛኛዎቹ አጋር ፓርቲዎች አነስተኛ የህዝብ ቁጥር ያላቸው ናቸው። ይህ መሆኑ ውክልናቸው አነስተኛ እንዲሆን ያደርጋል። እንደቀድሞው ሁሉ ተጽዕኖ የመፍጠር ዕድላቸው ጠባብ ነው። ስለዚህ የተሻለ አማራጭ የማግኘት ዕድላቸው በቀጣይ ሂደቶች ላይ ቢወሰንም እስካሁን ባለው ግን የፊት መለዋወጥ ካልሆነ የተወራለትን ያህል ለውጥ አያስከትልም ብለው የሚያምኑ አሉ።

የቁጥር ውክልናው አንድን ብሔር ከሌሎቹ በበለጠ መወከሉ የበፊቱ ኢሕአዴግ ይታማበት የነበረውን የአንድ ብሔር የበላይነት በአዲሱ ፓርቲም በሌላ ስም እንዲቀጥል እንዳያደርግ ትልቅ ስጋትም አላቸው። ይህንን ያስተዋሉ ሰዎች ውህደቱ ‹ኢህአዴግን ማፍረስ ወይስ በአዲስ ቅርፅ መድገም?› የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።

ተስፋ እና ስጋቶች

         በም/ጠ/ሚ/ሩ አቶ ደመቀ መኮንን፣ በጠ/ሚ/ሩ ዶ/ር አብይ አህመድ እና የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ አባል በሆኑት አቶ ፈቃዱ ተሰማ  የተሰጡት መግለጫዎች እና ማብራሪያዎች ውህደቱ ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተዋል። ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ሊያሳትፍ የሚችል ውክልና እንደሚኖርም ገልፀዋል። አጋር ፓርቲዎችም ከበፊቱ ኢህአዴግ የተሻለ በአሁኑ ውህደት ውክልና እንደሚኖራቸውም አስረድተዋል።

        በአንፃሩ የህወሓት እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ውህደቱ በአስተሳሰብ አንድነት፣ በፕሮግራም አንድነት፣ በብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት እና የኢህአዴግን አሰራር ተከትሎ እስካልሄደ ድረስ ለኢትዮጵያ ሊጠቅማት እንደማይችል አሳውቀዋል።  

      እዚህ ላይ ነገሮችን በገለልተኛ መነፀር ማየት ተገቢ ይሆናል። “ለምሳሌ አጋር ፓርቲዎች ለምን ሙሉ አባል አልሆኑም?” የሚለውን ጥያቄ የኢህአዴግ ቀደምት መሪዎች የመለሱበትን አግባብ እንመልከት።

     በ2003 ዓ.ም. በተካሄደው ጉባኤ የያኔው የድርጅቱ ሊቀመንበር የቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ እንዲህ ብለዋል፡-

“አብዮታዊ ዲሞክራሲ ማኅበራዊ መሰረቱ ግብርና እና የከተማው ታችኛው ማኅበረሰብ ነው።  በእነዚህ ክልሎች ግን ይሄ ስለሌለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለችግሮቻቸው መፍትሄ አይሰጥም።  ምክንያቱም ማኅበራዊ መሰረቱ በሌለበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ አይሰራምና ነው። አሁን ግን ዘመኑም ተቃርቦ ስላለና ዕድገት እየታየ ስለሆነ እነዚህ አጋሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተቻለ ሙሉ አባል ቢሆኑ ምንም ችግር የለውም”

       ይህንን ንግግር ሰሞኑን ከዚህ በፊት በተለይም ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ለወትሮው የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስቴርን ንግግር ማሳየት የማይፈልጉት የመንግስት ሚዲያዎች ባልተለመደ መልኩ በተለይም ኢቴቪ ውህደቱ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ ሀሳብ መሆኑን ለማሳየት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

       የቀድሞ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው በ1996 ዓ.ም. በደኢህዴን ድርጅቶች ውህደት ጊዜ ያደረጉትና  በመንግስት ሚዲያዎች ተደጋግሞ እየታየ የሚገኘው ንግግር

የደኢህዴን ከተለያዩ ፓርቲዎች ተዋህዶ አንድ ሆኖ መውጣት በትልቁ ለኢህአዴግ አርኣያ ሊሆን ይገባል” የሚለው ነው።

      ውህደቱ ላይ እየታየ ያለው የቁጥር ውክልና ለኢትዮጵያ እንደስጋት ሊታይ ይችላል።  ለዚህም ዋናው ምክንያት ከቁጥር ውጪ ያሉ መስፈርቶች በትክክል አለመታየታቸው ነው።  ለምሳሌ በሀገሪቱ የሃገረ-መንግስት ምስረታ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ የአዳል ሱልጣኔት እና የአክሱም ስልጣኔ መሰረት የሆኑ ህዝቦች ከ10 በመቶ በታች መወከላቸው በእነሱ ላይ ቅሬታን ሊፈጥር ይችላል።  

     ይህንንም ህወሓት የኢህአዴግን ስራ አስፈፃሚ ውሳኔ እንደማይቀበለው እና በማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባ ላይም እንደማይሳተፍ ህዳር 10 ባወጣው መግለጫ ላይ በመንገር አሳይቷል።

     የወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ ተስፋ ሊያጭሩ የሚችሉ ንግግሮች ከጠ/ሚ/ሩ እና ከም/ጠ/ሚ/ሩ ተሰምተዋል። ም/ጠ/ሚ/ሩ እንዲህ የሚል ንግግር በማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል።

“ውህደቱ የብሔርም ይሁን የሃይማኖታዊ ማንነቶችን ሳይረግጥ ሁላችንንም አንድ በሚያደርግ ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚጠቅም ነው።”  

ከፖለቲካ ባህላችን አንጻር

    ውህደቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀሬ ነው። የጊዜው ጥያቄ ነባሩን የመገዳደል፣ የመጠፋፋት እና የሴራ ፖለቲካ ይደግመዋል ወይስ አዲስ ባህል ይፈጥራል የሚለው ነው። የጥያቄው ምላሽ እንደቆምንበት ጽንፍ ተለያይነት አለው። ባለ ተስፋዎችም ሆኑ ግራ ዘመሞቹ የሚግባቡበት የሀሳብ ሙግት ላይ የቆሙ አይመስልም። በተቃራኒ መግለጫዎቻቸው እንዳደመጥነው ‹‹እመኑኝ ቀድመን እንስማማ እንጂ ፕሮግራሙ ነገ ይመጣል›› ከሚሉት ጀምሮ፤ ‹‹ከስምምነቱ በፊት መተዳደሪያ ደንብ ተጽፏል፤ ከሐሳብ እና ከፕሮግራም በፊት ግለሰብን ማመን ገዝፏል›› እስከሚሉት ድረስ ሁሉም ሐላፊነቱን እየተወጣ አይመስልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመድረክ ንግግሮቻቸው ደጋግመው የሚያነሱት በሀሳብ የመሸናነፍ፣ በሀሳብ ብልጫ የማመን፣… እሳቤ በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሊታመንበት ይገባል።  ሀገር የማዳንም ሆነ አዲስ ባህል የመገንባት ሂደቱ መሰረት ይህ ነውና።

ከአዘጋጁ፡- አንባቢዎቻችን የፓለቲካ ባህልን በተመለከተ ሊያደርሱን የሚፈልጉት ሐሳብ ካለ በደስታ ተቀብለን የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን፡፡   

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top