አድባራተ ጥበብ

ኪሮስ ዓለማየሁ ሲዘከር

ኪሮስ ዓለማየሁ ሲዘከር

ኪሮስ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ትልቅ ስም አለው፡፡ በተለይ የትግርኛ ሙዚቃ በመላው ሐገሪቱ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍ ያለ ድርሻ ነበረው፡፡ ድምጻዊ፣ የዜማ እና ግጥም ደራሲ የሆነው ኪሮስ ጥቅምት 3፣ 1986 ዓ.ም. በ42 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ሰለሞን ገብረእግዚአብሄር በአርቲስቱ የግጥም ስራዎች ላይ ያደረገውን ጥናት እና ከሌሎቹም ምንጮች ያገኘናቸውን መረጃዎች፣ ታዋቂ ሰዎች እና የስራ ባልደረቦቹ የተናገሩትን በማጠናቀር ሕይወት እና ስራዎቹን ባጭሩ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ መልካም ንባብ!

** ** **

‹‹ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ዮናስ ነው›› አሉት፡፡

የሦስተኛ ክፍል ተማሪያቸው የስም ለውጡን እንዳልተቀበለ በኩርፊያው የተረዱት መምህር

‹‹ለመሆኑ ዮናስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?››

ጥያቄያቸውን በአሉታዊ ንቅናቄ መለሰ፡፡

‹‹ዮናስ እግዚአብሄር የሚወደው ነቢይ ነው፡፡ በአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት ቆይቷል…›› ሕጻኑ መምህሩን አልሰማም፡፡ አሁንም የቀደመው ጥያቄው ላይ ነው፡፡

‹‹መጠራት የምፈልገው እናት እና አባቴ ባወጡልኝ ስም ነው፡፡ ስሜ ኪሮስ ነው፡፡ ኪሮስ ዓለማየሁ ነኝ››

መምህሩ የስም ለውጡ ያስፈለጋቸው ጥያቄ ለመመለስ በተደጋጋሚ ‹‹እኔ እኔ›› እያሉ የሚያስቸግሯቸውን ሞክሼ ሕጻናት ለመለየት ነበር፡፡

አርቲስት ኪሮስ ኃይለሥላሴ እና ድምጻዊ ኪሮስ ዓለማየሁ፡፡ ኪሮስ ኃይለሥላሌ ትረካውን ቀጥሏል፡፡ የአብሮ አደጉን የግራዝማች ዓለማየሁን ልጅ የልጅነት ትዝታ እየተረከ ነው፡፡ በትግርኛ ማልቀስ እንኳን በማይቻልበት በዚያ ዘመን ‹‹አንጉዐይ ፍስስ›› ብሎ መቅኒ ስለሚያስፈስስ ፍቅር ስላዜመው፣ በሙዚቃ ኃይል መላ ኢትዮጵያን አዳርሶ በአንድ የፍቅር ቋንቋ ስላነጋገረው፤ በወኔው፣ በአለባበሱ፣ በአዘፋፈኑ፣ በአጨፋፈሩ፣ በጸጉር አበጣጠሩ፣… በሁለመናው የኢትዮጵያዊያንን ቀልብ ስለገዛው፤ የትግርኛ ሙዚቃ ቋንቋውን በማይናገሩ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንዲወደድ ለማድረግ የራሱ ትልቅ አሻራ ስላኖረው አብሮ አደጉ አውርቶ አይጠግብም፡፡

ኪሮስ ዓለማየሁ እስከ አራተኛ ክፍል የተማረባትን ‹‹ፍረወይኒ›› ለቆ ወደ ‹‹ውቕሮ›› በማምራት ትምህርቱን ቢቀጥልም የሦስተኛ ክፍል መምህሩ ‹ቲቸር ዮናስ› ያወጡለትን ስም አይዘነጋም፡፡ የደርግን ማእከላዊ እስርቤት ደጋግሞ በጎበኘ ጊዜ የአሳ ነባሪውን ሆድ ያስታውሳል፡፡ ዮናስነቱን ባለመቀበል ኪሮስነቱን የማጥበቅ ትግሉ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ተከትሎታል፡፡

ሐምሌ 19፣ 1944 ዓ.ም. ተወለደ፡፡ የስለት ልጅ ነው፡፡ ግማሽ ጸጉሩን እየተላጨ፣ ግማሽ ጸጉርን እየተሾረበ የአንድ ብዙ ሆኖ አደገ፡፡ የስለት ልጅ እንደሚያድግበት የአካባቢው ልማድ ተቀማጥሎ አደገ፡፡ ሎቲ እያንጠለጠለ፣ ንቅሳት ተነቅሶ፣ የሚጠይቀው ተሟልቶለት፣ አጠፋህ ተብሎ ሳይገረፍ አደገ፡፡ በ‹ሳዕሲዕ ፃዕዳ እምባ› ወረዳ ‹ሰንደዴ› ጣቢያ ‹እንዳ ወይዘሮ› ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የሕጻንነት እና የልጅነት ጊዜውን አሳልፎበታል፡፡

ወንድሙ ኃይላይ ዓለማየሁ ወደኋላ ተመልሶ ትላንትን ሲያስታውስ ‹‹እኛ ቤት ኪሮስ በጣም ተወዳጅ ነበር፡፡ ሌሎቻችን በአንድ ማዕድ ስንበላ እሱ የነጭ ጤፍ እንጀራ በተለየ ወጥ ይሰጠዋል፡፡›› ይላል፡፡

‹‹አባታችን በምክር ነው ያሳደገን፡፡ ኪሮስ ግን ከሌሎቻችን የተለየ ነጻነት ተሰጥቶት ነው ያደገው፡፡ በራስ መተማመንን ያዳበረው ከዚያ ይመስለኛል››

ኪሮስ ዓለማየሁ በቤት ውስጥ ፈለገ-ሕይወት ተምሯል፡፡ ዘመናዊ ትምህርትን የጀመረው ግን በቀድሞ አጠራሯ ‹ስንቃጣ› በአሁኑ ‹ፍረወይኒ› በተባለችው ከተማ ነው፡፡

ለእናቱ ለወ/ሮ ቀለብ ገብረመስቀል ከፍተኛ ፍቅር አለው፡፡ ‹‹ገዛና›› (ቤታችን) በሚለው ዘፈኑ እንዲህ አንስቷቸዋል፡፡

ትሽዓተ ወርሒ ብጥንሲ አብ ከብዳ

ካሕሳ ናይ ወላዲት ዘይኽፈላ ዕዳ

(ዘጠኝ ወር አርግዛ በሆዷ

የእናት ካሳ የማይከፈል ዕዳ)

ግራዝማች ዓለማየሁ መለስ ሰፊ የእርሻ መሬት፣ በርከት ያሉ የቀንድ ከብቶች እና የቤት እንስሳት ያላቸው ባለጸጋ ነበሩ፡፡

የትምህርት ቤቱ ግቢ በሁለቱ ኪሮሶች ተሰጥኦ እየደመቀ ሰባተኛ ክፍል ደረሱ፡፡ ከእጁ የማትለየውን ዋሽንት በመጫወት በትምህርት ቤት ጓደኞቹ ታዋቂነትን ያተረፈው ኪሮስ ዓለማየሁ ከመድረክ መሪው ኪሮስ ኃይለሥላሴ ጋር የተለያዩት ስምንተኛ ክፍል ነው፡፡ የኃይለሥላሴ ልጅ ወደ አስመራ የዓለማየሁ ልጅ ወደ መቐለ አጼ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ተጓዙ፡፡

የትግራይ የባህል ቡድንን በመቀላቀል ዋሽንት የተጫወተው ኪሮስ 5ኛ ክፍል ሲደርስ ሌሎች መሳሪያዎችን መጫወት ጀመረ፡፡ ውቕሮ ከተማ ሲማር በነበረበት ጊዜ ከዋሽንት በተጨማሪ መሰንቆ መጫወት ጀመረ፡፡

በስለት የተገኘው ልጃቸው አዝማሪነትን ማዘውተሩ ያልተዋጠላቸው አባቱ ግራዝማች ዓለማየሁ ‹‹መሰንቆ ከዘራችን የለም!›› ብለው መቆጣት ጀምረዋል፡፡ በትምህርቱ በመጎበዝ ፋንታ ጊዜውን ሙዚቃ ላይ በማጥፋቱ ተበሳጭተው መሰንቆውን ሰብረውበታል፡፡ የሙዚቃ ፍቅር የተጣባው ብላቴና ግን መሰንቆው ሲሰበር እንዴት ቶሎ የማይሰበር መሰንቆ መስራት እንደሚችል ያስብ እንደሆነ ነው እንጂ የነፍሱን ጥሪ ከቤተሰቡ ተደብቆ ማስታገሱን አላቆመም፡፡

‹‹ንሰለስተ ዓመት እኖ ተሓዘለት

አቦ ዶ ይምኖ እኖ ተወለደት››

(እናት ለሦስት ዓመት በጀርባ ብታዝልም

ለሚወደው ልጁ አባት አይሰለችም)

በማለት በአንድ ዘፈኑ ውስጥ አንስቷቸዋል፡፡

ዘውዳዊው ስርዓት አክትሞ ደርግ ስልጣን ላይ ሲወጣ፤ የእድገት በኅብረት ዘመቻ ሲታወጅ ኪሮስ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ኪሮስም እንደ ዘመነኞቹ ወጣቶች ሰኔ 9፣ 1967 ዓ.ም. በትውልድ ሀገሩ አቅራቢያ በሚገኝ ‹ሸኸት› ተብሎ በሚጠራ ቦታ ግዳጁን በማስተማር መወጣት ጀመረ፡፡ 100 ብር እየተከፈለው ‹‹ማሪያም ቀያሕ›› እና ‹‹ደቤን›› በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አስተማረ፡፡ ይሁን እንጂ ብርቱ አስተማሪነቱ በደርግ ካድሬዎች አልተወደደለትም፡፡ ‹‹ሕዝብን እያነቃሕ ነው›› በሚል ተወንጅሎ ወደ መቀሌ ተወሰደ፡፡ በ1970 ዓ.ም. የእስር ስቃይን እና እንግልትን ቀመሰ፡፡

ኪሮስ ኃይለሥላሴ ትረካውን ቀጥሏል፡፡

‹‹ከአስር ዓመት በኋላ አዲስ አበባ ተገናኘን ለማውራት በቃን፡፡ እኔ ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በቲያትር ተመርቄ ሐገር ፍቅር ስመደብ፣ ኪሮስ ዓለማየሁ ከደርግ ዩንቨርሲቲ (እስር ቤት) ተፈቶ ራስ ቲያትር ተመደበ፡፡ ያኔ ነው የተገናኘነው፡፡ አመጣጣችን ይለያያል፡፡ እሱ ታስሮ ተገርፎ፤ እኔ በሰላም ትምህርቴን ተምሬ፣››

የሕይወት ባህር ባሻችው መንገድ ያስጓዘቻቸው የልጅነት ጓደኛሞች በጥበቡ መድረክ ዳግም ወዳጅነታቸው ቀጠለ፡፡

ኪሮስ ዓለማየሁ ከእስርቤት እንደተፈታ ቤት አልነበረውም፡፡ አምፒር ቲያትር ቤት ውስጥ መኖር ጀመረ፡፡ የሚኖርባት ክፍል ጠባብ እና ጨለማ ነበረች፡፡ ኪሮስ ብቻውን መኖሩ ያስጨንቀው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ከቤት በወጣ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ቤቱ በእሳት ጋይቶ ከሞት ተርፏል፡፡

ወቅቱ ትግራዊያንና እና ኤርትራዊያን የወያኔ እና የሻቢያ አባላት ናችሁ ተብሎ የሚታሰሩበት ዘመን ነው፡፡ ኪሮስም ከዚህ የወቅቱ እውነታ አላመለጠም፡፡ የልጅነት መምህሩ ‹ዮናስ› ያሉትን እያስታወሰ፣ በአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሆኖ ግጥም እና ዜማ ይጽፍ ነበር፡፡ ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀችውን ‹አንጉዐይ ፍስስ›› የጠነሰሰው እስር ቤት ሆኖ ነው፡፡

‹‹ውነይ ክምስ – አንጉዐይ ፍስስ

ልሳነይ ልጉም – ስነይ ክምስ››

(ወኔዬ ፈገግ- መቅኒዬ ፍስስ

ልሳኔ ዝግት – ጥርሴ ፈገግ)

አብዛኛው የግጥም ሐሳቡን ከእውነተኛ ታሪኮች የሚቀዳው ኪሮስ በፍቅር መስሎ ያቀረበው ግጥም የስርአቱን ጥላቻ ያንጸባረቀበት ይመስላል፡፡

አንድ አብሮት የታሰረ ሰው በተደጋጋሚ ሲያለቅስ እና ሲተክዝ የታዘበው ኪሮስ “ምን ሆነህ ነው ወንድሜ” በማለት ቀረብ ብሎ አዋራው፡፡ እስረኛውም ስሙ ጌታቸው እንደሆነና በሰርጉ ቀን ተይዞ እንደታሰረ ሲነግረው በጣም አዘነ፡፡ አዝኖም ዝም አላለም፤ ወዲያውኑ በእንጨት እጁ ላይ ግጥሙን ፅፎ ዜማ ደረሰ፡፡

“ዛቐያሕ ቖልዓ ከይመነኹዋ

ካብ ቤት ምሕፃነይ ተፈለኹዋ

ካብ ቅድሚ ዓይነይ ተፈለኹዋ

ኢሉ ዛንትኡ እንተዋግዓኒ

ከቢድ ሓዘን እዩ ዝተሰመዓኒ

ኣብ ልዕሊ ሓዘን ሓዘን ኮይኑኒ”

(ቀይዋን ልጅ ሳልጠግባት

ከጫጉላ ቤቴ ተለየኋት

ከአይኔ ፊት ተለየኋት

ብሎ ታሪኩን ሲያወራኝ

ከባድ ሀዘን ነው የተሰማኝ

በሀዘን ላይ ሀዘን ነው የሆነብኝ)

ብሎ ዘፈነለት፡፡ ጌታቸውም ከሀዘኑ በኪሮስ ዘፈን ተፅናና፡፡ በ1979 ዓ.ም. ከእስር እንደተለቀቀም በ“አንጉዐይ ፍስስ” አልበሙ ውስጥ አካተታት፡፡

የአዲስ ተጋቢዎቹ ፍቅረኞች ታሪክ መጨረሻው አሳዛኝ ነው፡፡ ሙሽራው ሲረሸን ሙሽሪት ሌላ ላለማግባት ወስና ብቻዋን እንደቀረች ይነገራል፡፡

ኪሮስ ከወጋህታ መጽሔት ጋር በነበረው ቆይታ

“እኔ መከራዬን፣ ስቃዬን እና ስሜቴን በዘፈን ነበር ምገልፀው፡፡ የግሌን ብቻ ሳይሆን የአገሬንና የህዝቤን ግፍ ጭምርም ነው፡፡ በነዚህ ዘፈኖቼ የሚነኩ የያለፈው ስርዓት ቡችላዎች ይከታተሉኝ ነበር፡፡ እኔም “ብዙ መስራት እንደምችል እያወቅኩ ዝምብዬ አፌን ከድኜ ነው እንዴ ምሞተው?” ብዬ፤ ጭንቀትም ስለነበረኝ ዘፈንን እንደ አንድ አማራጭ ወስጄ እስከ መስዋዕትነት በሚል ውሳኔ ቆርጬ ተነሳሁ፡፡

እስር ቤት እያለሁ ሳላቋርጥ ሙዚቃ እደርስ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹን ግጥሞቼን ከማዕከላዊ ወደ ዓለም በቃኝ ስወሰድ ቀዳድጄ ጣልኳቸው፡፡ ትንሽ በቃሌ ያጠናኋቸውን ብቻ ከርቸሌ በነበርኩበት ጊዜ ይዤያቸው ቆየሁ፡፡ ቢሆንም በማንኛውም ቦታ ላይ ተስፋ ሳልቆርጥ በቋንቋዬ፣ የስሜቴን እና የህዝቤን ስሜት እደርስ እና እዘፍን ነበር፡፡ ጊዜ አላፊ ነውና ያሁሉ ስቃይና መከራን አልፌ ዳግም ከሞት በር አምልጬ ከእስር ተፈታሁ” ብሏል፡፡

በመቐለ እስር ቤት

ታጋይ ብርሃኑ አባዲ ኪሮስን የሚያውቀው በ1968 ዓ.ም. ነው፡፡ ዕድገት በኅብረት ዘመቻ ላይ ክራሩን እየደረደረ ብሔራዊ ስሜቶቻቸውን ያነሳሳው ነበር፡፡ በኋላ ላይ “ቀይ ሽብር” ተብለው በመቐለ ወኽኒ ቤት ተገናኝተው የበለጠ ተዋወቁ፡፡

ብርሃኑ ስለ ኪሮስ ዓለማዬሁ ሲናገር “ኪሮስ በጣም ተሰቃይቶ ነው እስር ቤት ውስጥ ያገኘሁት፤ በድብደባ ምክንያት ቆስሎ ነበር፡፡ ቁስሉ ገና ሳይደርቅ ነው ያገኘሁት” ሲል ያስታውሳል

“ዋይ ይኸውን ዶኾን

ብርሃን ክሪእያ ንዓይነይ”

(ይሆናል ወይ

ብርሃን በዓይኔ አያለሁ ወይ)

እያለ የእስር ቤቱን አሰቃቂነት በመግለጽ አዚሟል፡፡

ብርሃኑ አባዲ ከ1000 በላይ የሚሆኑ እስረኞች በአንድ ላይ በሚኖሩበት ግቢ ከኪሮስ ዓለማዬሁ ጋር ጎን ለጎን ይተኙ ነበር፡፡

“ኪሮስ ከሙዚቃ ችሎታው በላይ ተጫዋች እና ወገኛ ነው፡፡ ተገርፈን እንዳበቃን በምንሰቃይበት ጊዜ ጨዋታና ቀልድ እያመጣ ስቃያችንን ያረሳሳን ነበር፡፡ መቶ አለቃ ደስታ የሚባል የደርግ ሰው ነበር፡፡ ሰውየው የሚያውቃቸውን ሰዎች ሁሉ ቅጣታቸውን ያከብድባቸዋል፡፡ ኪሮስንም አልማረውም፡፡ ሞት ተፈርዶባቸው መዝገብ ውስጥ ከሰፈሩት እስሮኞች አንዱ ነበር፡፡ በአንድ አጋጣሚ የዓድዋ ድል ክብረ በዓል ዋዜማ አንድ ግጥም ጽፎ ለጓደኞቹ አነበበላቸው…

‘ንዘክሮም ናይቀደም ወለዲ

ሓፂራቶም ዘፅንሑልና ዓዲ

ንሓልዋ ብግዲ ብውዲ’

(እናስታውሳቸው የጥንት አባቶቻችን

አጥረው ያቆዩልንን አገራችንን

እንጠብቃት በግድም በውድም)

በማግስቱ ሁሉም የእስርቤቱ ኃላፊዎች በዓሉን ለማክበር ባሎኒ እስቴድዮም እንደሄዱ ‘ይህ የኛም በዓል ነው፤ እኛም ማክበር አለብን’ ብሎ እስረኞቹን አነሳሳ፡፡ ግጥሙን አነበበላቸው፡፡ እስር ቤቱን በጭብጨባ እና በፉጨት አናጉት፡፡ ኃላፊዎች እና ካድሬዎች ይህን ጫጫታ እንደሰሙ የጻፈውን ግጥም እንዲያሳያቸው ጠየቁት፤ ሲያሳያቸው አልጠሉትም፡፡ ከዛ በኋላ እስር ቤቱ ውስጥ አንድ የኪነት ቡድን አቋቁሞ ቅስቀሳ እንዲያደርግ ጠየቁት፡፡ ኪሮስም ፈቃደኛ ሆነ፡፡ ክራሩን አመጡለት፡፡ እስረኛ ሆኖ በጠባቂዎች እየታጀበ በመቐለ እየዞረ በህዝባዊ በዓሎች እና መድረኮች ላይ እየተገኘ ይቀሰቅስ ነበር፡፡ በዚህ ተግባሩ ከሞት አመለጠ፡፡

ኪሮስ ለደርግ የሚሰራ ቢመስልም፣ ደርግ እንዲቀሰቅስለት ከእስር ቢለቀውም፤ ኪሮስ ግን ደርግን ሚደግፍ በመምሰል የነጻነት መልዕክት ያላቸው ግጥሞች በማስተላለፍ ተቃውሞውን ይገልጽ ነበር፡፡

 ‘ጎንደራ ናይ ከብዲ’ (የሆድ ወስፋት) የሚለው ዘፈኑ በዛን ሰዓት የደርግን ስርዓት በደምብ ይገልፀው ነበር…

‘ማርክሲዝም ሌኒንዝም ከየንበብካያ

ቲኦሪ ብተግባር ከየንበብካያ

ናበይ ናበይ ናብ ወንበር ጉያ’

(ማርክሲዝም ሌኒንዝም ሳታነብ

ቲኦሪን በተግባር ሳታነብ

ወዴት ወዴት ስልጣን ላይ ጉብ)

ዘፈኑ በቀጥታ የስርዓቱ መሪዎችን በሚመለከት ነው፡፡ ኪሮስ በጊዜው ከነበሩት ዘፋኞች ልዩ የሚያደርገው የትግራይ አካባቢዎችን በሙሉ በዘፈኑ ማካለሉ ነው፡፡ ከወልቃይት እስከ ራያ በለዛቸውና በዘያቸው ዘፍኗል፡፡

ኪሮስ በሙዚቃ ስራው ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፤ ዳሩ ምን ዋጋ አለው፡፡ “ሂድ አትበለው ግን እንደሚሄድ አድርገው” እንደሚባለው ሁሉ፤ ነጋ ጠባ የካድሬዎች ትንኮሳና ማስፈራራት ሲበዛበት ተለዋጭ ሥራ እንዲያገኝ ብሎ በፃፈው ደብዳቤ መሠረት የሚወደውን ህዝቡንና አገሩን ወደ ኋላ ትቶ የካቲት 20፣ 1973 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ራስ ቴአትር አመራ፡፡

“ፀወታ ትግርኛ ዝነበሮ ለዛ

አሎ ዶ ከም ቀደም ናይ ወግዒ መዓዛ”

(የትግርኛ ጨዋታ የነበረው ለዛ

እንደ ድሮው አለ ወይ ያወግ ያመዓዛ)

የአገሩን ናፍቆት ከገለፀበት የግጥም ስንኝ የተወሰደ፤

ያን ጊዜ ራስ ቴአትር ተወዳጅ የሙዚቃ ቡድን በመሆኑ ኪሮስም ተለዋጭ የዝውውር ወረቀቱን ይዞ በጊዜው የሃገረሰባዊ የሙዚቃ ጨዋታዎች ክፍል ኃላፊ ለነበረው ሙሉ ገበየው ሰጠው፡፡ ቴአትር ቤቱ ትግርኛ ተጫዋች ያስፍልገው ስለነበር ሳያቅማሙ ተቀበሉት፡፡

ራስ ቴአትር ገብቶ ከሁሉም የቡድኑ አባሎች ጋር ባጭር ጊዜ ተዋውቆ ጓደኝነት መሰረተ፡፡ በቴአትር ቤቱ የመጀመሪያ ጓደኞቹ ከነበሩት ውስጥ ነዋይ ደበበና ፀሐዬ ዮሐንስ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ ከነዋይ ደበበ ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ነበራቸው፡፡

ታዋቂ ሰዎች ስለ ኪሮስ

ድምጻዊ፣ የዜማ እና ግጥም ደራሲ ነዋይ ደበበ በአንድ ወቅት

“ኪሮስ ክራር ይጫወታል፣ ግጥምና ዜማ ይሰራል፣ እኔም ልክ እንደሱ ድርሰት እጽፋለሁ፣ ዜማ እሰራለሁ፡፡ ከዛም አልፎ ብዙ የሚያመሳስለን ነገር ስለነበር በፍጥነት ጓደኛሞች ሆንን፡፡ ኪሮስ በተደጋጋሚ በሲኒማ አምፒር የሚዘፍናት ፖለቲካዊ ይዘት የነበራት ዘፈን ነበረችው፡፡

“እታ መራር ቃልሲ ከይፈተንካያ

ማርክሲዝም ሌኒንዝም ከይጨበጥካያ

ቲኦር ብተግባር ከይፈተሸካያ

ናበይ ናብ ወንበር ጉያ

ናበይ ናብ ስልጣን ጉያ”

(መራሯን ትግል ሳትሞክራት

ማርክሲዝም ሌኒንዝም ሳትጨብጣት

ቲኦሪ ብተግባር ሳትፈትሻት

ወዴት ወዴት ወደ ወንበር ሩጫ

ወዴት ወዴት ወደ ሥልጣን ሩጫ)

የምትለውን ዘፈን በተደጋጋሚ ሲዘፍናት ስሰማ ‘በናትህ እኔም በትግርኛ እንድዘፍን እንዲህ ዓይነት ግጥምና ዜማ ስጠኝ’ ብዬ ስጠይቀው ‘እሺ’ ብሎ በማግስቱ ይህን የመሰለ ግጥም ፅፎ ዝፈነው ብሎ ሰጠኝ፡፡

“ተስኡ በሉ ጉቦ ኮይኑ ሓዊ

ስራሕ ንምቑፃር ወገን ኮይኑ ዓሌታዊ

ብማዕረ ደሞዝ ስራሕ ተቖፂሩ

ብቐለም ብቋንቋ ነዞም ዝፃረሩ

ጊዜ ምሃብ ይትረፍ ሀዚ ይጎርጎሩ”

(በሉ ተነሱ ጉቦ እሳት ሆኗል

ስራ ለመቀጠር በዘር ወገን ሆኗል

በእኩል ደሞዝ ስራ ተቀጥሮ

በቀለም በቋንቋ ለሚከፋፈሉ

ጊዜ መስጠት ይቅር በቃ በሉ፡፡)

በማለት የሀገሪቱን ቢሮክራሲ የሚነቅፍ ዘፈን ሰጠኝ፡፡ ክለብ ውስጥ አልፎ አልፎ እዘፍነው ነበር፡፡ ኋላ ግን ስለ ሰጋሁ “አንተ ልጅ ታሳስረኛለህ ብዬ ዘፈኗን ተውኳት፡፡ ሌላው የኪሮስ ነገር የሚያስገርመኝ መጽሐፍ ለማንበብ የነበረው ፍቅር ነው፡፡ አብረን ስራ ላይ አምሽተን እኛ ደክሞን ስንተኛ፤ ኪሮስ ግን ሲያነብ ያድራል” በማለት ከኪሮስ ጋር የነበረውን ትውስታ በሀዘን ይናገራል፡፡

ኪሮስ ለሦስት ዓመታት ያህል 230 ብር እየተከፈለው ከቆየ በኋላ ብዙዎቹ የአብዮቱ 10ኛ ዓመት ሊከበር በዝግጅት ላይ በነበረበት ጊዜ ታኅሳስ 23፣ 1976 ዓ.ም. ከሚሰራበት ራስ ቴአትር ታስሮ ወደ ማእከላዊ ተወሰደ፡፡

“ፍቕሪ ውላድ እዩ ለዛ መለስለሲ

ፅልኢ ፍረ የብሉን ፀኒሑ መጣዓሲ”

(ፍቅር ልጅ ነው ለዛ ማለስለሻ

ጥል ፍሬ የለውም ከርሞ መጸጸቻ)

ራስ ቴአትር እያለ የዘፈነው ነው፡፡

 “በክለባችን በየዓመቱ የኪነጥበብ ወድድር ሲኖር ኪሮስ አንደኛ ነበር የሚወጣው፡፡”

ሻምበል በላይነህ

“ኪሮስ ማይክ ሲይዝ መድረኩን ግርማ ነው የሚያላብሰው፤ በተለይም እሱ የሚመርጠው ከበሮ ትክክለኛው እና ረጋ ያለው ምት በመጠቀም ተወዳጅ ስራ ሰርቷል”

ክቡር ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ

“ኪሮስ ከሌሎች አርቲስቶች በበለጠ በተሰጠው ተሰጥኦ አድርጎ በማንሰማው ቋንቋ ሁላችንንም በአንድ ድምፅ ያስዘመረ ነበር”

ክቡር ደ/ር ጥላሁን ገሠሠ

‹‹ኪሮስ በአጭር ጊዜ የሙዚቃ ህይወቱ ተአምር የሚባል ሥራ ሰርቶ ወደፊት ብዙ በሚሰራበት ዕድሜ ላይ ያጣነው ከያኒ ነው”

ክብር ዶ/ር ዓሊ ቢራ

“እኔ ከኪሮስ ብዙ የወረስኩት ነገር አለ፡፡ አርአያ ከሆኑኝ አርቲስቶችም አንዱ ነበር፡፡ ውዝዋዜው፣ ፈገግታው፣ ዜማው ድምፁ ልዩ ነው፡፡ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የሚኖር ልዩ ችሎታ የነበረው ተፈጥሮአዊ ነፃነት የታደለ ከያኒ ነበር”

ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)

“ኪሮስ በዓለም አቀፍ ዝና ከነበራቸው እንደነ ሳሌፍ ኬታ፣ የሱን ዱር፣ ማማ ግብፂ፣ ማርያም ማኬባ የመሳሰሉት ዕንቁዎች ጋር የሚስተካከል አቅም የነበረው ከያኒ ነው፡፡ ልክ እንደነሱ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዳያገኝ የሆነው በኛ ስንፍና ነው፡፡ ባጭሩ የ100 ዓመት ጀግና ብዬዋለሁ”

ሠርጼ ፍሬሥብሐት

መቋጫ

በኪሮስ ዓለማየሁ የዘፈን ግጥሞች ላይ ጥናት ያካሄደው ሰለሞን ገብረ እግዚአብሔር የቋንቋው ተናጋሪዎች ሳይቀሩ የዘፈኑን ሐሳቦች አልተረዷቸውም፡፡ ለጭፈራ ብቻ ነው የሚጠቀሙባቸው›› ብሏል፡፡

‘አለኹ እየ ዝብልየ

የለኹን ዓይጥዑምን

ምቕናይ ጥዑም ‘ዩ

ዋላ ሓደ ሰሙንየ’

(አለሁኝ ነው እምለው

የለሁኝም ማለት ጥሩ አይደለም

መሰንበት ጥሩ ነው

አንድ ሳምንትም ቢሆን)

ብሎ እንደዘፈነ፤ በዚች ዓለም ኗሪ ሰው የለምና ዘፈኖቹን በህዝብ ልብ አስቀምጦ እስከወዲያኛው አሸልቧል፡፡ ከመሞቱ በላይ ግን የአሟሟቱ ሁኔታ በምን እንደሆነ ሳይታወቅ እንሆ 26 ዓመት ሆኖታል፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top