ቀዳሚ ቃል

የ፪ኛው መቋጫ የ፫ኛው መጀመሪያ

የ፪ኛው መቋጫ የ፫ኛው መጀመሪያ

የጊዜ ቀመር ታዛ መጽሔት ፪ኛ ዓመቷን እንዳገባደደች አመልክቷል። ስፖንሰር ካደረጉን ተቋማት፣ በቋሚነት ሲከታተሉን ከነበሩ አንባቢዎቻችን፣ የጥናት እና ምርምር ጽሑፋቸውን እንድናትም ከፈቀዱልን ምሁራን፣ በታሪክ፣ በባህል እና በኪነ-ጥበብ ላይ ያተኮረ ሥራቸውን እንድናስነብብ ከሰጡን ጸሐፊያን ጋር ሆነን የሦስተኛ ዓመታችንን ጉዞ በዛሬዋ ቅጽ ፫ ቁጥር ፪፭ እትም ጀምረናል። እንኳን አደረሰን!

መንገዳችን በምቹ ምንጣፍ ያሸበረቀ ብቻ አልነበረም። ከወረቀት እና ከማተሚያ ቤት ዋጋ መናር ጀምሮ ከዝግጅት እስከ ስርጭት በርካታ ጎርበጥባጣ መንገዶች አጋጥመውናል። የበዙ ጠመዝማዛ መንገዶች ትዕግስታችንን ተፈታትነውታል። ነገር ግን ሁሉም ድቅድቅ አልነበረም። መሹለኪያ አቋራጮቻችን ዛሬ ላይ አድርሰውናል። የህትመት ቀናችንን ሳናከብር ስንቀር ምነው ዘገያችሁ የሚሉ አንባቢያን አቋራጮቹ ነበሩ። በይዘት ላላ ስንል ሐሳባችሁን አጠንክሩ የሚሉን መካሪዎቻችን አሻጋሪዎቻችን ነበሩ። ከስፖንሰር አጋርነትም በላይ ለሥራው ስኬት ተጨናቂ የሆኑት ደጋፊዎቻችን ምርኩዞቻችን ነበሩ። ድምር ውጤቱ “ታዛ” አሁን ያለችበት እድሜ ላይ፣ አሁን ባለችበት ቁመና እንድትገኝ አድርጓታል። ሁላችሁንም እናመሰግናለን!

 የባህል እና የኪነ-ጥበብ ጉዳዮችን ስናነሳ አላማችን ሰፊ ነበር። የተዛነፉ ትርክቶችን የሚያርሙ ምሁራንን ወደ አደባባይ ማምጣት ዋነኛው ነው። የኋላውን እንዴትነት አውቆ፣ የአሁኑን ነባራዊ እውነት ተረድቶ፣ ነገውን የሚተልም ትውልድ ማፍራት ደግሞ ግዙፉ ግብ ነበር።

በዝግታም ቢሆን ወደ ግባችን እየቀረብን እንደሆነ ይሰማናል። የሚድያ ተቋማትን ያጨናነቀው የምክንያታዊነት ጉድለት የወለደው መዛነፍ በንባብ እንዲታረም አንዲቷን ጡብ ለማስቀመጥ በትክክለኛው መስመር ላይ ተገኝተናል ብለን እናስባለን። በተለይ በኪነ-ጥበቡ መስክ ለዓለም የሚተርፍ ሐገራዊ ጀግና ለመውለድ በሚደረገው ጉዞ የድርሻችንን መወጣት የኩራታችን ምንጭ ነው።

 የንባብ ጉዞ የጥልቅ ምርምር ድጋፍ እንዲኖረው አንተጋለን። የባህል እድገት ቱባውን የቀደመ ሂደት እንዲከተል ከምንጩ የቀዳነውን ለመሰነድ መታተራችን አይቋረጥም። ታሪክ፡ – የዛሬ ኑሮ መሰረት፣ የነገ ሕይወት ጌጥ፣ እንዲሆን ትውልድን እናነቃለን።

 የዛሬው የታዛ መጽሔት መታሰቢያነቱ ለኤልያስ መልካ ነው። ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን አበርክቶ የተለየን ኤልያስ የዚህኛው ትውልድ ጉልህ ምልክቶች ከሆኑ ሙያተኞች ውስጥ አንዱ ነበር። ህያው ሥራዎቹን እና ግዙፍ ስብእናውን ሰፋ ባሉ ገጾች እናወሳለን። እግረ መንገዳችንን እንደ ኤልያስ ያሉ የሐገር ጡቦችን ለመውለድ የቀደምቶችን ታሪክ እንሰንዳለን።

 ኑ! በኪነ-ጥበብ ኃይል የተባበረ ኃያል ተውልድ እናፍራ። መልካም ንባብ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top