ጥበብ በታሪክ ገፅ

ጥቁር እና ነጭ በኢትዮጵያ

ጥቁር እና ነጭ በኢትዮጵያ

አየለ አትናሽ እና ጆርጅ ዱካስ አብሮ አደግ ጓደኞች ናቸው። ገና ታዳጊ ናቸው። ሁለቱ ልጆች በጧት ተነስተው ሁለት በጎች እየነዱ ጣሊያኖች በብዛት በሚገኙበት ቦታ እየተዘዋወሩ ነው። ልጆቹ በጎቹን የሚነዱት ሳር ለማብላት ወይም ሊሸጧቸው አልነበረም። ጣልያኖች ያሳደሩባቸውን ስሜታቸውን የጎዳ፤ ጓደኝነታቸውን የሚለያይ መጥፎ ስሜት ለመቃወም ነበር።

 አየለ እና ጆርጅ ጎረቤታሞች ናቸው። ጊዮርጊስ ክለብን የመሰረቱት እነርሱ ናቸው። ጆርጅ ነጭ ነው (ግሪካዊ) አየለ ደግሞ ሀበሻ ነው። ሁለቱ ኳስ ለመጫወት ሲሄዱ አንድ ጣሊያናዊ ጓደኛሞቹን ከሚጓዙበት መንገድ ላይ አስጠራቶ አስቆማቸው። ይህ ሰው ሲኞር ማርቲኔሌ ይባላል። (በኋላ ጣሊያን ባቋቋመው ፌዴሬሽን ውስጥ ሰርቷል)፤

 “ወዴት ነው የምትሄዱት?” አላቸው

“ኳስ ለመጫወት”

“የት?”

“ወደ ሜዳ”

“ከእንግዲህ ሁለታችሁ አብራችሁ መጫወት

አትችሉም”

“ለምን?”

“ሕጉ ያግዳችኋል”

“የምን ሕግ?”

“ሰሞኑን ተግባራዊ ይሆናል”

ያን ጊዜ ጣሊያን ጥቁር እና ነጭ አንድ ላይ መጫወት አይችሉም የሚል ሕግ ለማውጣት በሂደት ላይ ነበር። ሁለቱ ልጆች በቀለማቸው ልዩነት አብረው እንዳይጫወቱ ታገዱ።

 በዚህን ጊዜ ነበር አየለ እና ጆርጅ ለጊዜው ምንም ነገር መፍጠር ባይችሉም ነጭ እና ጥቁር በግ ይዘው መዘዋወር ጀመሩ። እነዚህ በጎች የሚለያቸው የቆዳ ቀለም እንጂ ሁለቱም በግ ናቸው የሚል መልእክታቸውን በማስተላለፍ ሃሳባቸውንና የተጎዳውን ስሜታቸውን በዚህ መንገድ ለመግለጽ ተገደደዱ። ይህንኑ ሃሳባቸውንም ለሌላው በማካፈል ቅስቀሳ ጀመሩ።

ጆርጅ ነገሩን ይበልጥ አጠንክሮ ገፋበት። በትምህርት ቤት ያሉ ጓደኞቹም ትግሉን ተቀላቀሉ። ትምህርት ቤት ውስጥ ይሄንን ውሳኔ እና ሕግ የሚቃወም ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ተለጥፎ ተገኘ። ማን እንዳደረገው ባይታወቅም ጆርጅ ላይ ስለተሳበበ ቡሉቅባሽ የሚባል ማዕረግ ያላቸው ወታደሮች ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲሄዱ ነጭ ሆኖ ዙሪያውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ያለበት ማሊያ ተሰቅሎ አገኙ።

 ይህ ማሊያ ጊዮርጊስ ለሁለተኛ ጊዜ ያሰራው ነበር። የክለቡ ማሊያ የሚቀመጠው እንደ ጽህፈት ቤት እንዲጠቀሙት የጆርጅ አባት ለቡድኑ በሰጡት አንዲት ክፍል ነበር። ጆርጅም በወታደሮቹ ተያዘና ታሰረ። ብዙ ሳይቆይ ቢለቀቅም በሌላ ግዜ ሰላይ ነው በሚል ከነቤተሰቡ ታሰረና ኮረም አስር ቤት ተከተተ። ወዲያውም ጣሊያን ሕጉን አወጣ። ጥቁር እና ነጭ አንድ ላይ መጫወት የለባቸውም፤ አይችሉምም ብሎ በአዋጅ አስነገረ። ደንቦችን አወጣ። ጥቁሮች መሳለሚያ አካባቢ ባለው ኳስ ሜዳ እንዲጫወቱ፤ ነጮች ደግሞ አሁን ሳንጆሴፍ የሚባለው ትምህርት ቤት ባለበት ቦታ ላይ እንዲጫወቱ ተደረገ።

 ለጥቁሮች ከወጡት ሕጎች አንዱ ለእንግዳውና ለዳኛው የፋሽስት ሰላምታ መስጠት ግዴታ ነው። ጎል ያገባ ተጨዋች ለዳኛ የፋሽስት ሰላምታ ካልሰጡ ግቡ አይጸድቅም፤ ቡድኖች በጣሊያን ሀገር ያሉ ቡድኖችን ዐይነት ማለያ እንዲለብሱ ይገደዳሉ፤ እያንዳንዱ ተጫዋች ተያዥ ካላመጣ አይጫወትም።… ሕጎቹ ብዙ ናቸው። ጣሊያን ከመግባቱ በፊት ጥቁሮች ቆረጡ፡፡

ሁለቱም ተፈራረሙና 5 ሰዓት ላይ ሲኒማ ኢትዬጵያ ገቡ (እነዚህ ነገሮች በሌላ ግዜ በዘርዝር ይጠቀሳሉ) ከሰዓት በኋላ ኳስ ሜዳ ሄዱ። በወቅቱ በአንዳንዶቹ ዘንድ ተቃውሞ ቢኖርም አላማውን ከግብ ለማድረስ ጨዋታው ተደረገ። ተጫወቱ። ጊዜው 1934 ነበር። እለቱም ግንቦት አምስት ነው። በግጥሚያው ጊዮርጊስ 4ለ1 አሸነፈ።

 በዚህ ግጥሚ ያየጎሉ ውጤት እንጂ ሁለቱም አሸናፊ ነበሩ። ዋናው አላማ ጥቁር እና ነጭ አብሮ እንዳይጫወት የሚገድበውን ሕግ ሽረው በአንጻሩ እንዲጫወት የሚፈቅደውን ሕግ አጽድቀው ግንኙቱን የሚያበስረውን ግጥሚያ ማድረጋቸው ነው። ሁለቱ ክለቦች የተፈራረሙበት ወረቀት ለሁሉም የውጭ ቡድኖች ተላከ። በ1935 ሌሎች ቡድኖች የተካተቱበት የሙከራ ጨዋታ ተደረገ። ነጭ እና ጥቁር አንድ ነው የሚለውን ደንብ አሻሽለው ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ላኩ። በወቅቱ ፌዴሬሽን ባለመቋቋሙ እግር ኳሱን እንደፌዴሬሽን ሆኖ ለመምራት የተዘጋጀው ይሄው መስሪያ ቤት በመሆኑነበር። ማስታወቂያ ሚኒስቴር (በወቅቱ ማስታወቂያ መምሪያ) ወድድሩን ለመምራት የሙከራ ግጥሚያ አዘጋጀ። አላማውን አሳወቀና ጊዮርጊስ ያወጣውን ደንብ ተነጋግረውበት ሁሉም ክለቦች ባሉበት አጸደቁት።

ማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚመራው የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በ1936 ዓ.ም. ተጀመረ። የተካፈሉት የጣሊያኑ ፎርቲቲዲዮ፤ የእንግሊዙ ቢ.ኤም.ኤም፣ የግሪኩ ኦሎምፒያኮስ፣ የአርመኑ አራራት፣ ከኢትዮጵያ ጊዮርጊስ ነበሩ። ሁሉም ቡድኖች የቀለም ልዩነት ሳይኖር ለመጫወትተስማሙ። ህንዶች ቡድን ባይኖራቸውም በዳኝነት ይሳተፉ ነበር። በናይሮቢ ህንዱ እና ኬንያዊው ለእንግሊዙ ጥቁር ነበር። በኢትዮጵያ ግን ህንዱ ከእንግሊዙ ጋር እኩል መብት ነበረው። የእንግሊዝ ደጋፊዎች በህንድ ዳኛ ላለመመራት ቢያንገራግሩም ፈርመዋልና ተቀበሉት። ህንዱና እንግሊዙ እዚህ እኩል መብት ነበራቸው። ጊዜው በ1936 ዓ.ም. ሲሆን ህንድ ከእንግሊዝ ነጻ የወጣው በ1940 ዓ.ም. ነበር። እዚህ ቀድሞ ነጻ ወጥቷል። በማን? ጊዮርጊስ ባወጣው ሕግ!

በዳኝነት፣ በኮሚቴነት፣ በክለብ የተመዘገቡት የውጭ ኮሚኒቲዎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጠቅላላ ጉባኤ አባል ሆነው ይሰራሉ። በድምጽ ይወስናሉ። የፈረሙት ሕግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደንብ ሆኖ ጸደቀ። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በ1949 ዓ.ም. ሲቋቋም የኢትዮጵያ ተወካዮች በምስረታው ላይ ክለቦች ያወጡትን ሕግ አቀረቡ። ግብጽ እና ሱዳን የቀለም ልዩነትን ሕግ በተመለከተ ብዙም ባይገፉበትም የኛ ተወካዮች “ሞተን እንገኛለን ይሄ ሕግ መካተት አለበት” በማለታቸው በብዙ ክርክር ጸደቀ። የደቡብ አፍሪካ ቡድን በአፓርታይድ ሕግ ስለሚተዳደር ነጭ እና ጥቁር ተጫዋች አብሬ አልቀላቅልም በማለቱ በሕጉ መሰረት ከውድድሩም ከካፍም ተባረረ። ደቡብ አፍሪካ አየለ አትናሺ እና ጆሪጅ ዱካስ ታዛ መጽሔት | ቅፅ 03 ቁጥር 25 | መስከረም-ጥቅምት 2012 ዓ.ም. 25 የፊፋ አባል በመሆኗ ፊፋ “የኔን አባል አንድ አህጉራዊ ፌዴሬሽን ማገድ አይችልም” በማለቱ ሌላ ችግር መጣ።

በወቅቱ ፊፋን የሚመሩት እንግሊዛዊ በደቡብ አፍሪካ ድርጅት ያላቸውና የጥቅም ተጋሪ ስለነበሩ ካፍ ላይ ጫና አሳደሩ። ይሄን ሕግ በመተዳዳሪያ ደንቡ ውስጥ እንዲካተት ያደረገችውና ባለጉዳይዋ ኢትዮጵያ በመሆኗ ጫናው እኛ ላይ አረፈ። ፊፋ እኛን አስወግዶ የደቡብ አፍሪካ አከባቢ ያሉትን እነ ማላዊና ዛምቢያን በመጨመር ሌላ “የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን” ለማቋቋም መዘጋጀቱን እነ አቶ ይድነቃቸው ደረሱበትና አጋለጡ። ደቡብ አፍሪካ የፊፋ አባል በመሆኗ ካፍ ያወጣው ሕግ እንዲፈርስ ብዙ ጥረት አደረገች። ኢትዮጵያም ሕጉ እንዲጸድቅ ለአስራ ስድስት ዓመታት በፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ታገለች። በየጉባኤው ሲያነሱ ውድቅ ሲደረግባቸው ከቆየ በኋላ እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም. ፍራንክፈርት በተካሄደው የፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ጸደቀ።

ኢትዮጵያ ያቀረበችውና የጸደቀው የደንብ ረቂቅ “በኢንተርናሽናል ፉት ቦል ፌዴሬሽን እንቅስቃሴ ውስጥ ባንድ አገር ወይም ባንድ ሰው ላይ በዘር፣ በሀይማኖት፣ በጎሳ የተነሳ ልዩነት ማድረግ አይፈቀድም። የዘር፣ የሀይማኖት፣ የጎሳ ልዩነት በሕግ በመሰረተ ሀገር የሚገኝ ብሄራዊ ፌዴሬሽን ከፊፋ አባልነት ጨርሶ ይታገዳል” የሚል ነበር። ኢትዮጵያ በፊፋ ስብሰባ ለረጅም ዓመታት ስታነሳ በድምጽ ብልጫ ሲወድቅባት ያለ አንዳች ተስፋ መቁረጥ ተራማጅ የሆኑትን በማሳመንና ድጋፍ በማሰባሰብ ጠንክራ ስትታገል የኖረችለት ሕግ በመጨረሻ ሊጸድቅ ችሏል።

ይሄ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነበር። ውሳኔው በአፓርታይድ ሕግ የሚተዳደረውን የደቡብ አፍሪካ ፌዴሬሽንን ከፊፋ ያሳገደ ሲሆን በዓለም ያሉ ጥቁር ተጨዋቾች በፈለጉበት ሀገር በነጻነት ለመጫወት የሚያስችል ሕግ ነበር።

የዚህ ሕግ መጽደቅ ኢትዮጵያ ለሰው ልጅ መብት፣ እኩልነት እና ነጻነት ያደረገችውን ተጋድሎ ያመለክታል። ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል ሲሆን ይሄኛው ደግሞ በዓለም ላሉ ጥቁር ተጫዋቾች ነጻነትን ያጎናጸፈ ነው። ጉዳዩን አቶ ይድነቃቸው በየስብሰባ ላይ ያቅርቡት እንጅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌረዴሬሽን የወሰነው ነው። ነገር ግን ይሄ ጉዳይ አንድም ቀን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያለመነሳቱ ነገር እንደጉዳት የሚታይ ነው። ብሄራዊ ቡድኑ ደቡብ አፍሪካ ለአፍሪካ ዋንጫ በሄደ ጊዜ ትንሽ አዳራሽ ተከራይተው ጋዜጠኞችን ጠርቶ መጠነኛ የፎቶ ኤግዚቢሽን አዘጋጅቶ “እኛ ለአፍሪካውያን ስፖርተኞች ነጻ መውጣት ብዙ ታግለናል። ነጭ እና ጥቁር በአንድ መድረክ እንዲጫወቱ ትልቅ አስተዋኦ አድርገናል” ቢሉ ሀገራችን በዓለም ስፖርት አደባባይ ያበረከተቸው አስተዋጽኦ ይታወሳል።

ትልቅ ቦታ ያገኛል። የአንድ ሀገር እግር ኳስ የሚለካው በውጤት ብቻ ሳይሆን ለስፖርቱ በሚያበረክተው ቁም ነገር ነው። ይሄ ጉዳይ የሀገራችንን ስም በከፍተኛ ጉዳይ የሚያስጠራ ሆኖ ሳለ ትልቅ ታሪካችን ደብዝዞና ተረስቶ መቅረቱ ያሳዝናል። አሁን ያለው ትውልድ ስለዚህ ነገር እምብዛም አያውቅም። እንዳያውቅ ያደረግነው እኛው ነን። ጭንቅላቱ ውስጥ ስለ አውሮፓ ፉት ቦል እንዳይረሳ እየጨቀጨቅነው ትልቁንና ሀገራዊ ድርሻችንን ቦታ አሳጥተን አስረስተነዋል። ደቡብ አፍሪካ ነጻ ስትወጣ ማንዴላ ለኛ ሰዎች ሽልማት ሲሰጡ ድካማችንን አስታወሰው ነው። እኛ ግን ይሄን ትልቅ ታሪክ ቦታ አልሰጠነውም። ይሄንን ያደረጉት ኬንያ ወይም ሌላው ሀገር ቢሆን ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ያወራሉ፤ ያስወራሉ ዓመታዊ በዓል አዘጋጅተው ያከብራሉ።

 ሕጉ ፍራንክፈርት ላይ ሲጸድቅ አቅራቢዋ ሀገራችን ትሁን እንጂ እዚህ የነበሩት ኮሚኒቲዎች ትልቅ ሚና ነበራቸው። በወቅቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይሰሩ የነበሩ የውጭ ዜጎች ማለትም የሀንጋሪ፣ ግሪክ፣ አርመን፣ የመን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን እና የሌላ ሀገር ዜጎች የሀገራቸውን እግር ኳስ ፌዴሬሽን በማግባባትና በመጫን በፊፋ ድል እንዲገኝ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የእነዚህ ሀገር ዜጎች ገና ትግሉ ሲጀመር አብረው የነበሩ ናቸው። ትግሉ የተጀመረው ኳስ ሜዳ በመሆኑ ከዚያ የተነሳው ነገር ተቀጣጥሎ በፊፋ ሕግ ሆኖ ወጣ። ይሄ በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለው ነገር እንዴት በዋዛ ዝም ይባላል?

 አሁንም ጊዜው አልረፈደም ይሄ ትግል የተጀመረበት ቦታ አንድ መጠነኛ ሀውልት ቢቆም በሀውልቱ ላይ ይድነቃቸው ተሰማ፣ አመለወርቅ ተክለዜና፣ ገብረ ሥላሴ ኦዳ፣ ዲሚትሪስ ጎሎምቢስ፣ ኦኔኒስከን፣ ፒየርኮንቲ፣ ሙሴ ሌንታኪስ፣… ቢኤምኤም፣ ፎርቲቲዲዮ፣ ኦሎምፒያኮስ፣ ጊዮርጊስ የሚሉ ጽሁፎች ቢቀመጡ ትልቅ ማስታወሻ ነው። ሀውልቱን የሚያዩ ሁሉ ምክኒያቱን ይረዳሉ። የሀገራችን የስፖርት ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያደረጉትን ትግል ይገነዘባሉ። ከዚሁ ጋር ተያያዞ በየዓመቱ ግንቦት አምስት ቀን የቀለም ልዩነት ትግል የተጀመረበት(ፎርቲቲዲዮ እና ጊዮርጊስ ተፈራርመው የተጫወቱበት) በሚል ቢከበር

1ኛ.ሀገራችን በዓለም እግር ኳስ ያበረከተቸውን አስተዋጽኦ አመላካች ይሆናል

2ኛ. ለአዳዲስ ስኬቶች የሚገፋፋ ብርታት በመሆን መጪው ትውልድ ታሪኩን ይዞ እንዲያስቀጥል ያስችላል፤

 3ኛ. ትላንት ለዚህ ትልቅ ዓላማ የታገሉትን እናስታውሳለን፤

 4ኛ. ትልቅ የቱሪስት መስህብ ከመሆንም አልፎ/በላይ ቱሪስቶች እንዲጎበኙ እና አላማውን እንዲረዱ በማድረግ

የሊቨርፑሉ ታዋቂ ተጫዋች የነበረው ጆንባርነስ አዲስ አበባ መጥቶ በነበረ ጊዜ ናይት ክለብ ወስደው አዝናኑት። ባርነስ በጥቁርነቱ በባለጋራ ደጋፊዎች በአሽሙር ከሚሰደቡ ተጨዋቾች አንዱ ነበር። “በዓለም እግር ኳስ ጥቁሮችን ከነጮች ጋር በእኩል መብት እንዲያጫወቱ ያስቻለና ነፃ የወጡበት ሕግ የተገኘው እዚህ ቦታ በተጠነሰሰ ትግል ነው” የሚለውን ታሪክ በቦታው ላይ ሄዶ ቢያይ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ቢያንስ እንደ ናይት ክለቡ የሚረሳው አይሆንም። “ጥቁር ተጫዋቾች ነፃ የወጡበትን ቦታ አየሁ” ብሎ ለሌች የሚናገረው ነገር ሰጠነው ማለት ነው። የስዊድን፣ ሆላንድ፣ ፈረንሳይ፣… ዜጎችም ሲመጡ ሀውልቱን በማሳየት “እዚህ የነበሩት የእናንተ ሰዎች ከኛ ጋር ታግለው ይህ ሕግ እንዲጸድቅ አድርገዋል” ብሎማስተዋወቅ ቢቻል እና ቢሰራበት ትልቅ ዋጋ አለው። ይሄ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትልቅ ማስተዋወቅ ከመሆኑም በተጨማሪ ትላንት ለዚህ ጉዳይ ለታገሉት ሁሉ የሚገባቸውን እውቅና መስጠትም ይሆናል። ከዚህ በላይና ባሻገር ደግሞ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በሀገራችን ላሉት የእግር ኳስ ተቋማት መሪዎችና ተዋናዮች የኃላፊነት ፅንፋቸውን ማሳየት፤ የተጋረደውን የድል ዐይነጥላ የሚገፍፍ፣ ብሎም በስፖርቱ አፍቃሪያን ደጋፊዎች ዘንድ የላሸቀውን የዛለውን ስፖርታዊ ፍቅርና የተሰበረውን ስሜት የሚጠግን ትልቅ ነዳጅ ነው።

ታዲያ ምንድነው ዝምታው?

 ትላንት ጊዮርጊስ ሀሳቡን አንስቶ ሌሎችን ክለቦች እና አካላት አሳትፎ ከብዙ ጥረት በኋላ ይሄ ሕግ ከሀገር አልፎ በአህጉር ተሻግሮ በዓለም ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ጥረት አድርጓል። ትላንትም ከሌሎች ጋር በጋራ ሰርቶ ዳር አድረሷል፤ ዛሬ ይሄ ታላቅ ሀገራዊ ታሪካችን ተዳፍኖ እንዳይቀር ጥሪውን ያቀርባል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top