ከቀንዱም ከሸሆናውም

የእቴጌ ስጦታ

የእቴጌ ስጦታ

በህዳር 4 ቀን በ1879ዓ.ም አፄ ምንሊክ ወደ ሀረር ዘመቱ። እቴጌ ጣይቱም በበኩላቸው ከእንጦጦ ወርደው ፍልውሃ አቅራቢያ የዛሬው ታላቁ ቤተመንግሥት የሚገኝበት ከፍ ያለስፍራ ላይ ከትመዋል። ወደ ሀረር ያቀኑት ዳግማዊ ምኒሊክም ከአንድ ወር በላይ ሆኗቸዋል። ቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልዴ ጣይቱ ብጡል በሚለው መፅሐፋቸው የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ገልፀውታል።

በምኒሊክ መጥፋት የህዝቡን መጨነቅ እቴጌ ጣይቱ በሰሙ ጊዜ ከዚያች ፍል ውሃ አጠገብ ከተሰራች ቤት ወርደው ተቀመጡ፤ ከተማ መስራትም ተዠመረ፤ መኳንንቱም ቦታውን እየተመራ ቤቶችን ይሰራ ዠመረ። ህዝቡም እቴጌ ጣይቱ ከተማ ወርደው ከተማ ማሰራታቸውን ባየ ጊዜ የምኒልክን ደህንነት በዚህ አውቀናል ብሎ ዳር እስከ ዳር ረካ። ሀገሩም እጅግ ያማረ ሆነ። ሰራዊቱም ወደደው፤ እቴጌ ጣይቱም ይህንን ከተማ ስሙን “አዲስ አበባ” በሉ ብለው አዘዙ።

 አፄ ምኒሊክ ሐረር ዘመቻ ላይ ቢሆኑም የእቴጌ ጣይቱ ደብዳቤ በየወሩ ይደርሳቸው ነበር። አብዛኛው ደብዳቤም “ተፃፈ ከእቴጌ ጣይቱ እንጦጦ” ወይም “ዲልዲላ” የሚል መደምደሚያ ነበረው። ከአዲስ አበባ ስም መሰየም በኋላ ግን ለአፄ ምኒሊክ የሚደርሷቸው ደብዳቤዎች ተፃፈ ከአዲስ አበባ ይል ጀመር። ለምኒልክ ስለ አዲስ አበባ የተነገራቸው ምንም ነገር አልነበረም። ይህም በንጉሡ ዘንድ አግራሞትን እንዲያጭር እቴጌይቱ ሆን ብለው ያደረጉት መሆኑን የታሪክ መፃህፍት ያወሳሉ። እቴጌ እንዳሰቡት “የት ሆና ይሆን?” የሚል አግራሞት በምኒልክ ዘንድ ተፈጥሯል። በሌላ ደብዳቤ ታዲያ “እቴጌ ያቺን የምንፈልጋትን ቦታ አግኝቼ አዲስ አበባ ብያታለሁ” የሚል የምስራች ላኩባቸው። ንጉሡም ከሀረርጌ ዘመቻቸው በድል ከተመለሱ በኋላ የእቴጌ ጣይቱን ውሳኔ በማፅናት አዲስ አበባ የርዕሰ መዲናቸው ዋና ከተማ እንድትሆን ወሰኑ። አዲስ አበባ ርዕሰ መዲና ሆነች። በተለያዩ ጉዳዮች በርካታ ሰዎች ከየጠቅላይ ግዛቱም ሆነ ከውጭ ሀገር ይመጡ ጀመር። እነዚህ እንግዶች ወይም ባለጉዳዮች ታዲያ የሚያርፉበት ስፍራ አስፈለገ። አራት ኪሎ በሚገኘው ቤተመንግሥት ግቢ ገብርኤል አጠገብ የእንግዶች ማረፊያ ተሰራ። ይህ የእንግዶች ማረፊያ በርካታ ክፍሎች ያሉት ነበር። እንግዶች በቆይታቸው ወቅት ምግብ፣ መጠጥም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን ከንጉሡና ከእቴጌ ጣይቱ ነበር የሚያገኙት። እቴጌ ጣይቱም በውጭ ሀገር የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ እንግዶች እየከፈሉ ሊስተናገዱበት የሚያስችል ሆቴል መኖሩን ሰሙ። በ1900 ዓ.ም. እርሳቸውም ሆቴል አቋቋሙ። ስሙንም ‘እቴጌ ጣይቱ’ ሆቴል አሉት። ይህ ሆቴል ዛሬም ድረስ ስሙን ይዞ ይገኛል።

በነሐሴ ወር በ1900 ዓ.ም. በፆመ ፍስለታ ውስጥ አንድ ቀን ጠዋት ጃንሆይ ለፀሎት ቤተመንግስታቸው አጠገብ ወደምትገኘው ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ሄዱ። ቀኑ ዝናብና ውሽንፍር የበዛበት ነበር። ፀሎት ካደረሱ በኋላ ወደ ቤተመንግሥታቸው ሲመለሱ ከእልፍኛቸው አጠገብ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው የዝናብ ውሃ የሸፈነው የወለሉ ጥርብ ድንጋይ ወይም ደረጃ አዳልጧቸው ይወድቃሉ። የተከተሏቸው ሰዎችም ደጋግፈው ከእልፍኝ አስገቧቸው። ከዚህ ቀን ጀምሮ ታመው ከእልፍኝ ዋሉ።

 አፄ ምኒሊክ አንበታቸውም አካላቸውም ተይዞ አልጋ ላይ ናቸው። የሸዋ መኳንንቶት ወይንም የውጭ ኃይሎች ደግሞ የእቴጌን አለመኖር ይፈልጉታል። ምክንያቱም የሸዋ መኳንንቶች ሥልጣኑ ወደ ሰሜን ቤጌ ምድር ይሄድብናል በሚል ስጋት የውጪ ኃይሎች ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ እንደልባችን እንዳንሆን እንቅፋት የሆኑት እቴጌይቱ ናቸው የሚል ምክንያት ስለነበራቸው ነው። እቴጌም ይህን ዘመን የመጨረሻ የተማረሩበት ዘመን ነበር ይባላል። ከ1902 እስከ 1906 ዓ.ም. እቴጌጣይቱ ከአፄ ሚኒልክ ልጅ ከወ/ቶ ዘውዲቱ ጋር ሆነው በታላቁ ቤተመንግሥት አፄ ምኒልክን ሲያስታምሙ ነው የቆዩት።

በዚህ መካከል የእቴጌ ጣይቱን ስነ ልቦና የሚጎዳ ክስተት ተፈጠረ። ባለቤታቸውን ብቻ በማስታመም ብቻ እንዲወሰኑ የተደረጉት እቴጌ አፄ ምኒልክን መርዘዋቸዋል የሚል ወሬ በስፋት ነፈሰ። መነሻውም የጀርመኖቹና የፈረንሳዮቹ ሀኪሞች አለመዋደድ፤ ለዝና መሯሯጥና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሰሚ ለመሆን የነበራቸው ፍላጎት…መሆኑና፤ ፈፅሞ ሀሰት እንደሆነ የታሪክ መጻሕፍት አስፍረውታል።

ዳግማዊ አፄ ምንሊክ ህመም ፀንቶባቸው ነበርና ታህሳስ 03 ቀን 1906ዓ.ም በእለተ አርብ ቀን በ69 ዓመት ከ3 ወር እድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ወ/ሮ ዘውዲቱ

‹‹ምልክቱ ይህ ነው የንጉሥ ሞት ሀዘን

 ጣይቱ ስትጨልም ጨረቃ ደም ስትሆን

ወልደውኛል እንጂ እኔ አልወለድኩዎ

 አንጀቴን ተብትበው ምነው መያዝዎ››

 እቴጌ ጣይቱም ሀዘን በርትቶባቸው ነበርና

 ‹‹እምቢልታ ማስነፋት ነጋሪት ማስመታት ነበረ ስራችን

ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን›› ብለዋል።

‹‹ተወድዶ ከመኖር ተጠልቶ መውለድ

ማን ያይብኝ ነበር ይህን ሁሉ ጉድ››

 የሚለውንና እቴጌ ቋጠሩ የሚባለው ስንኝ የመጨረሻ ዘ መ ና ቸ ው ን በግዞት ያሳለፉባት ወደ እንጦጦ ማሪያም በግዞት ሲያመሩ ነበር። እቴጌ ከእንጦጦ በምሽት ቁልቁል እያዩ ያቺ እንደዚያ በ መ ብ ራ ት የ ደ መ ቀ ች ው ከተማ ማን ናት ብለው ጠየቁ አሉ፤ የእርሶ አዲስ አበባ ናት አሏቸው። ጣታቸውን ወደ ቤ ተ መ ን ግ ሥ ቱ አቅጣጫ አድርገውም ያኛው እዚያ ጋ የማየውስ ሲሉ የእርሶ ቤተመንግሥት የነበረው ነው ቢሏቸው ለካስ ነበር እንዲህ ቅርብ ኖሯላ ብለው ነበር ይባላል። እቴጌ ጣይቱ በየካቲት 10 ቀን 1910 ዓ.ም. በተወለዱ በ78 ዓመታቸው አረፉ። አስከሬናቸውም በግዞት በነበሩበት እንጦጦ ማሪያም ቅፅር ለተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ በክብር ወደታእካ ለነገስት ባዕታ ለማሪያም ቤተ ክርስቲያን ተዛወረ።

 አዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው ታላቁ ቤተመንግሥት ጋር ተያይዞ የታእካ ለነገስት ባዕታ ለማሪያም ቤተክርስቲያን ይገኛል። ቤተክርስቲያኑ ንግስት ዘውዲቱ ለአባታቸው መታሰቢያነት ያሰሩት ነው። ታላቁ ቤተመንግሥት አጠገብ ከቤተመንግስት ቀጥሎ በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት የተሰራ ነው። አፄ ሚኒሊክም ከአ.አ መቆርቆር ጀምሮ ህይወታቸው እስከሚያልፍም የኖሩት በዚህ ቤተመንግሥት ነው። ወደ ባእታ ቤተክርስቲያን ሲገቡ ከዋናው የቤተክርስቲያን ክፍል ወለል ቁልቁል ወርደው አንዲት መጠነኛ ክፍል ያገኛሉ። ክፍሏ ፭ አስክሬኖች አርፈውባታል። ፭ኛው የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ልጅ የልዕልት ፀሐይ። ፬ተኛው የአቡነ ማቲዎስ አስክሬን ነው። ፫ኛው አስከሬኖች ደግሞ በተመሳሳይ ዲዛይን በታነፁ ሐውልቶች ጎን ለጎን ተደርድረዋል። 3ኛው ዳግማዊ ምኒሊክ ን/ነ/ዘኢትዮጵያ ፪ኛው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘኢትዮጵያ ፪ኛው ዘውዲቱ ምኒሊክ ሦስቱም በተለያየ ወቅት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል። (ቀኝአዝማች ታደሰ ዘወልዴ የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ህይወት በሚያሳየው አጭር መፅሐፋቸው ካሰፈሩት ገለፃ እና በሸገር ኤፍ ኤም ከቀረበ ትረካ ላይ የተቀነጨበ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top