ታሪክ እና ባሕል

የአውደ ዓመት መዘክር

የአውደ ዓመት መዘክር

የበረዶ አባት

የዓለም ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብራቸውና ከሚዘክራቸው በዓላት መካከል አንዱና ተወዳጁ የዘመን መለዋጫ ነው። ዕለታት እየበረሩ፣ ወራት እየተቀመሩ አልፈው አዲስ ዘመን በባተ ቁጥር ሕዝብ ሁሉ ፍሥሐ ያደርጋል። ሰላምን፣ ብልጽግናን፣ ጤንነትን፣ ፍቅርን፣ ይመኛል። አዲስ የሥራ እቅድና ምኞት በስሜቱ ያሰርፃል። ወደ ተግባር ለመተርጐምም ሌት ተቀን ይኳትናል። ያለፈው ዘመን የጦርነት እና የረሀብ የነበረ ከሆነ አዲሱ ዓመት ዘመነ ሰላም፣ ዘመነ ጥጋብ፣ እንዲሆን መልካም ምኞት ይገልጻል።

 በተለይ አውሮጳውያንና አሜሪካውያን የጎርጎርዮሳዊው ዘመነ ስሌት ጥር አንድን የሚያከብሩት በእንግሊዝኛው ሳንታክላውስ፣ በሩሲያኛ ደግሞ ዴድ ማሮዝ (የበረዶ አባት) በሚል የሚታወቀውን የአርቲፊሻል ሽማግሌ ምስል በመሥራት ነው። ምስሉን በየቤቱ፤ በየመደነሻ ቦታና በየአደባባዩ በማቆም ነው። በመብራትና በልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት አዥጎርጉረው፣ በአለባበሱ፣ ከግግር በረዶ በተሠራው በረጅም ጢሙ፣ በለበሰው ቀይና ነጭ ልብስ ልጆችና አዋቂዎች ይዝናኑበታል።

 በበዓል ዋዜማ ሌሊት ለዳንስ መውጣት የተለመደ ነው። የታዋቂ ዘፋኞች የሙዚቃ ቅምር በኅብረ ዐውደ ዓመት ቀለማት በተብረቀረቀው አዳራሽ እየተንቆረቆረ የሻምፓኝ ቡሽ ሲተኮስ፣ ወይን ጠጁም ገንፍሎ ሲረጭና ሲፈስ ያድራል። የደስታ ብሥራት። ወጣት አረጋውያኑ በላብ እየተዘፈቁ በየአዳራሹ ያረገርጋሉ። ታላላቅ መሪዎች እንኳን ለአዲሱ ዘመን በሰላም አደረሳችሁ “ሃፒ ኒው ይር”፤ ‘’ስኖቪም ጎዶም’’ እየተባባሉ የደስታ መልዕክት ይለዋዋጣሉ።

በእንስሳት ተምሳሌትነት

 ይህንን በዑደት አንድ ጊዜ የሚመጣውን ዓመታዊ በዓል (እንቁጣጣሽ) ቻይናውያንም በታላቅ ስሜት ነው የሚያከብሩት። ዘመናቸውን በዐውደ ጨረቃ ቀመር እያስቀመጡ፣ በጥንቸል፣ በነብር፣ በድራጎን፣ በበሬ፣… እየሰየሙ የእንስሳቱን እና የአራዊቱን ምስል እየቀረጹ ምስሉ እንደሚወክለው ሐሳብ ሌሊቱን ሙሉ ደስታቸውን፣ እምነታቸውን እና ፍቅራቸውን፣… እየገለጹ ሲፈነጥዙ ያድራሉ። የበዓሉም ሥነ ሥርዓት በሰርከስ መልክ እየታየ በቴሌቪዥን በሬዲዮ እና በመሳሰሉት መገናኛዎች ለአድማጮችና ለተመልካቾች ሲተላለፍ ግማሽ ሌሊቱ ይወገዳል።

የዝንጀሮን እና የድራጎን ዘመን

የቻይና የአዲስ ዓመት ተምሳሌት የሆነው የዝንጀሮን እና የድራጎንን ዘመን የሚወክለው ፎቶ በቻይና 34ኛዋ ክፍለ ሀገር የሆነችውን ጉይጆን የተነሳ ነው። ይኸውም ሺያንግ ወረዳ የጥንት ቤተ መንግሥት አዳራሾች ያለበት ሲሆን በቤተ መንግሥቱ አደባባይ ላይ የቱሪስት መስህብ የሆኑ የልዩ ልዩ የዱርና የቤት እንስሳት ምስሎች ክብ ቅርፅ ይዘው ይታያሉ። እነዚህም በቁጥር ዐሥር ሲሆኑ የቻይናን ዘመን አቆጣጠር ተከትሎ ቻይናውያን በአዲስ ዓመታቸው በእንስሳቱ ምስል ዙሪያ እየዞሩና እየዘፈኑ በዓላቸውን የሚያከብሩበትና ፈንጠዝያ የሚያደርጉበት ቦታ ነው። ዘመናቸውም የዝንጀሮ፣ የጦጣ፣ የነብር፤ የድራጎን፣ የበሬ፣ የጥንቸል፣… በሚል እየተሰየመ በየዓመቱ ይከበራል።

በእምነት

ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመታቸውን በመስከረም አንድ የሚያከብሩት የብርሃን ምልክት የሆነውን ዳቦት ወይም ችቦ በማብራት፣ የሰላም ተምሳሌት የሆነውን የወይራ ዝንጣፊ በመቁረጥ፣ አበባና እንግጫ፣ ቄጤማና ሳር በመጎዝጎዝና የበግ መሥዋዕት በማቅረብ ነው። ይህም የደስታና የተስፋ ምልክት የሆነው አዲስ ዓመት ከኖኅ በፊትና በኋላ በተዘረጋው ስሌተ-ዘመን እንደሆነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሊቃውንት ጉሳኤ ሰብሳቢ የነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ በሕይወት በነበሩበት ዘመን አስረድተውኛል።

 የኢትዮጵያ ይዞታ መሠረተ ባሕርይ ከጥንት ጀምሮ ሃይማኖት ሲሆን በጽሑፍም በአፈ- ታሪክም እየተወራረሰ የመጣ ነገር ነው። በሹም ሽር ባለሥልጣናት ሲቀያየሩ፣ የመንበረ መንግሥት መቀመጫ ቦታ ልውውጥም ሲደረግ መጥቷል። ግና በሰው ፍልስፍና ወይም በመንግሥት ለውጥ ምክንያት የተናወጠ ነገር የለም። ጦርነቶችና ግጭቶች፣ ቢፈራረቁም መሠረተ እምነትን የሚነካ ለውጥ አልደረሰም። አዲስ ዓመት ከጥንት ከአዳም ጀምሮ የነበረ በዓል ነው።

 ከአዳም ጀምሮ የመጣውን የቁርጥ ዘመን በጽሑፍ ያስተላለፈው ሄኖክ ነው። ይኸውም ለሳምንት ለእሁድ እስከ ቅዳሜ 7 ቀናት፣ በዕለት 24 ሰዓታት፣ ለወር ቀናት 30፣ የዓመት ቀናት 364 ሲሆኑ 65ኛዋ መዛወሪያ ቀን ናት። ጳጉሜን በሦስት ዓመት 5 ስትሆን የሚዘለው ስድስተኛ ቀን ሠግር (የወር መባቻ) ይሆናል።

 ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር) ጥ በ ብ ና ባ ህ ል 20 ታዛ መጽሔት | ቅፅ 03 ቁጥር 25 | መስከረም-ጥቅምት 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ካላንደር ከጥፋት ውኃ በፊት ሦስት ትውልዶችን አሳልፏል። እነርሱም ሄኖክ፣ ላሜህ እና ኖኅ ናቸው። ኖኅ የሰው ልጆች ሁሉ አባት እንደሆነው እንደ አዳም የሚቆጠር ከጥፋት ውሃ በመጨረሻ የተረፈ አባት ነው። ኖኅ ከአባቶቹ የተቀበለውን ጥበብ ሁሉ ለልጆች አስተላለፈ። ዛሬ የምንጠቀምበት የኮሶ መድኃኒት የኖኅ ተረፈ ጥበብ ነው። ኖኅ ከመርከብ በሰኔ ወር በወጣ ጊዜ የበግ መሥዋዕት ሠውቶ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ። እግዚአብሔርም ያን ጊዜ ከኖኅ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን መሠረተ። ይኸውም የሰው ልጅ ልቡ ምንም ክፉ ቢሆንና ቅጣትም የማይቀርለት ቢሆን ጨርሶ እንደማያጠፋው ለኖኅ ቃል ገባለት። ምልክቱንም በደመና ላይ ቀስት ስሎ አሳይቶታል። ይኸውም የቀስቱን ደጋን ወደ ራሱ፣ ገመዱን ደግሞ ወስደው ልጆች አድርጐ።

ጌታ ‘’ከመዓልትና ሌሊት፣ በጋና ክረምት፣ ብርድና ሙቀት፣ ዘርና መኸር ጊዜያቸውን ጠብቀው ሲፈራረቁ ይኖራሉ። በምድር ላይ ይህ አይቀርም’’ እንዳለው በቃሉ መሠረት ክረምት ገባ። ከክረምት በኋላ የዓመት መሥፈሪያ 365 ቀናት በመሆናቸው መስከረም አንድ የአዲስ ዓመት መባቻ ሆኖ መጣ።

አዲስ ዓመት ከቶ ሥራውን ጨርሶ በሄደ ቁጥር፣ ዕለት ግን በየጊዜው እየታደሰ ይሄዳል። እስከ አዲስ ኪዳን ጅማሮ ድረስ አበው የተለያዩ ጊዜያት የተገለጹላቸውን ምልክቶች በመያዝ የየዘመናትን ብተት (መግቢያ) የእግዚአብሔርን ዙፋን ተሸካሚ በሆኑ በኪሩቤል መላእክት እያመሳሰሉ ገጸ ሰብእ (ሰው)፣ ገጸ ላህም (በሬ)፣ ገጸ ንሥር (አሞራ)፥ ገጸ አንበሳ እያሉ ዓመታትን ይመድቡ ነበር። ከስብከተ ሐዲስ በኋላ ግን ይህ ተሽሮ ወንጌልን በጻፉት አርድእት ስም ተተካ፤ ማቴዎስ፥ መርቆስ፥ ሉቃስ፥ ዮሐንስ፥ ሲጽፉም ዕለት ተቀደም ነውና ተራቸውን ጠብቀው ይመላለሳሉ። ይህም ማለት ዘመኑ ዘመነ ምሕረት መሆኑን ለማብሰርና ድኅነት (መዳን) የሚሰበክበት ዘመን መምጣቱን ለመግለጽ ነው።

 በገጸ ሰብእ የተተካው ማቴዎስ ነው። ጌታ ከሰማይ ወረደና ሰው ሆነ ብሎ ስለሚያስተምር ነው። በገጸ አንበሳ የተተካው ማርቆስ ነው። በግብፅ (ምሥር) ብላህም (በበሬ) ጣዕዋ (ጥጃ) ጣዖት ያመልኩ ስለነበር ያንን ምልክና አጥፍቶ፤ ሽሮ በክርስቶስ እንዲያምኑ ስላደረገ ነው።

 በገጸ አንበሳ (ላህም) የተተካው ሉቃስ ነው። ተምሳሌቱም የጌታን መሥዋዕትነት ስለሚያስተምር ነው። በገጸ ንሥር የየተካው ዮሐንስ ነው። ንሥር ከአዕዋፍ ሁሉ መጥቶ ይሄዳል። መሬትም ላይ ምንም ኢምንት ነገር ብትወድቅ አትሠወረውም ዓይኑ (ጽሩይ ነው። ይላል። ይህም ማለት ቅዱስ ዮሐንስ ዓለም ሳይፈጠር፥ዘመን ሳይቆጠር ወደ ነበረው ሁኔታ መጥቶ (በአስተሳሰብ) በመሄድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቀዳማዊ ቃል መሆኑን፥ እግዚአብሔርም ዓለሙን የፈጠረው በእርሱ ቃል እምነት መሆኑን፥ ያም ቃል ሰው መሆኑን ስለሚያስተምር ነው ገጸ ንሥር የተባለው። ‘’የሦስቱ ወንጌላውያን ትምህርት ታሪክ ጠቀስ ሆኖ ለሰሚዎችና አንባቢዎች ሁሉ በቶሎ ሲረዳ፥ የዮሐንስ አስተምህሮ ግን ጥልቅ የአእምሮ ብስለትና ምርምን ይጠይቃል።’’ ይላሉ አለቃ አያሌ ታምሩ። አያይዘውም፡-

 ‘’ዘመን በተለወጠ ቁጥር ከሰው ልጆች ስሜት ጋር አብሮ የሚንቀሳቀሰ ተስፋ አለ። በጥፋት ዘመን ሰማይ በደመና ተሸፍኖ፥ ከላይ ዝናም፥ ከታች የሚፈልቀው ጎርፍ የኖኅ ሰዎችን አስጨንቋቸው ነበር። በኋላ ግን ምድር ላይ ለውጥ ታየ። ነፋስ ነፈሰ። ብረሃንም ፈነጠቀ። አበባ አበበ። የኖኅ መልእክተኛ የሆነችው ርግብም ‘ማየ አይህ (የጥፋት ውሃ) ነትገ (ጐደለ) ‘እያለች ርጥብ ቄጠማ በአፏ ይዛ መጥታ ስታበስረው፤ የኖኅ ሰዎች ከመርከቧ ወደ መሬት ሲወርዱ በመጀመሪያ አበባ፣ እንግጫ፥ ቄጠማ የለመለመ ሣር፣… አገኙ። እግዚአብሔርንም በአንቃዕድዖ ልቡና አመሰገኑና በዓላቸውን (አዲሱን) አከበሩ።

በዚህም አምሳል ክረምት አልፎ መሬት በምታሸበርቅበት በምታብብበት ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ አዲስ ዓመታትን እናከብራለን። እንደ ዕፅዋትና እንደ አበቦች ሁሉ ከመሬት የተገኘ በመሆኑ በመስከረም ሰውም በተስፋ ስሜት ይለመልማል። አገኛለሁ፥ አሳካለሁ፣ እድናለሁ፣ አሸንፋለሁ ብሎ በቁርጠኝነት ይነሳሳል። በዘልማድም እምነቶች ይገለጻሉ ‘’በዮሐንስ እረስ፥ በማቴዎስ እፈስ’’፤ ‘’ጳጉሜ ሲወልስ ጎታህን አብስ’’፥ ‘’ጳጉሜ ሲበራ ስንዴህን ዝራ’’ እያሉ ገበሬዎች ይናገራሉ። ይተነብያሉ። ገበሬዎች ገና በግንቦት የክረምቱን አገባብ ለይተው የሚዘሩትን ዘር አስቀድመው የሚያውቁ ሜትሮሎጂስቶች ናቸው።

 እነዚህ ወንጌላውያን ዐውደ ዘመናችን በባተ ቁጥር በየአራት ዓመቱ ይመላለሳሉ። አሁን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ተሸኝቶ ቅዱስ ዮሐንስ ተሹሟል። በብዙዎች እምነት ግን አንዱን ወንጌላዊ የሰላም፥ የአንደኛውን የጦርነት፥ የብጥብጥ፤ የመዓት የቸነፈር፥ የረሃብ፥ የጥጋብ ተምሳሌት አድርጎ ማመን የተለመደ ነው። ሁሉ ነገር ግን በጌታ ፈቃድ የሚከናወን ነው። መ/መክ ምዕራፍ 3 ቁጥር 7 ‘’ፈቃዱን በጊዜው ውብ አደረገው’’ እንደሚል/እንዲል ነውና በአዲስ ዓመት የምቀኝነት አስተሳሰባችን፤ የኋላ ቀርነት ራዕያችን የፖለቲካ ውዝግባችን፤ እንደ ጉም በንኖ፥ እንደ ውኃ ተንኖ ውዲቱ ሀገራችን ሰላም የሰፈነባት፥ ሥጋት የራቀባት እንድትሆንና በሥራ እንድናሳድጋት የአምላክ ፈቃድ ይሁንልን።

 ከባህል አንጻር

የቅዱስ ዮሐንስ ዋዜማ መዓልት በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጎዘጎዛል። አደይ አበባ በሥርዓቱ እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል። ልጆችና አረጋውያን አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ። በአመሻሽ ላይ ችቦ አቀጣጥለው ‘’ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፣ ኢዮሃ የበርበሬ ውሀ። በሸዋ በጎንደር፣ በትግራይ በወሎ፣ በሐረርጌ፣ በሲዳሞ፣… ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ። እንኳን ከዘመን ዘመን (ከጨለማ ወደ ብርሃን) በሰላም አሸጋገራችሁ። እንጉሮ ገባሽ በያመቱ ያምጣሽ..’’ እያሉ ያቀጣጠሉትን ዳቦት ወይም ችቦ በአየር ላይ እየወረወሩ ሲጨፍሩ፣ ሲዘፍኑ የምሽቱም የችቦ እሳት ርቀት እስከወሰነው አድማስ ድረስ ከቀዬ ቀዬ ከአድባር እስከ አድባር፣ ከመንደር እስከ መንደር ሲበራ ይታያል። በሀገራችን ልዩ ልዩ ቦታዎች የሚገኙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች በአዳዲስ ልብስ ተውበው ስለ አደይ አበባ፤ ስለ ዕንቁጣጣሽ፤ ስለ መስከረም ወር የተፈጥሮ ውበት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ከንፈር ወዳጅነት እየዘፈኑና እየተጫወቱ ቀኑን በደስታ ያሳልፉታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top