አድባራተ ጥበብ

ዘመነ ግሎባላይዜሽን አብቅቶለት ይሆን…

ዘመነ ግሎባላይዜሽን አብቅቶለት ይሆን

 ግሎባላይዜሽን በሀገራት መካከል በኢኮኖሚ ውህደት እየፈጠረና የካፒታል፣ የሸቀጥና የ አ ገ ል ግ ሎ ት እንቅስቃሴ ድንበር በተሻገረ መልኩ እንዲካሄድ ያስቻለ እድገት ነው። የመልክአ ምድር፣ የባህልና የኢኮኖሚ መራራቅ የጠበበትና በአንዱ ሀገር የተፈጠረ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር ያስከተለ ክስተት እንደሆነ ይታወቃል። እንደኛ ያሉ ሀገራት ግሎባላይዜሽንን በአግባቡ ተረድተው እየተጠቀሙበት ባይሆንም እየተጠናከረ የመጣ ስለሚመስል ወደፊት አንድ ቀን ከትሩፋቱ ይደርሰናል ብለው በተስፋ እየጠበቁት ነበር። ይሁንና ይህ በአለማቀፍ ማእከላዊነት ላይ አተኩሮ አለምን መንደር እያደረጋት ነው ተብሎ የተወራለት ግሎባላይዜሽን እያበቃለት ነው ቢባሉ ምን ይላሉ?

ሚካኤል ኦሱሊቫን በፕሪሲተን ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰርና የኢንቬስትመንት ባንከ ባለሙያ ሲሆን በግሎባላይዜሽን እጣ ፈንታ ላይ ‘ዘ ሌቭሊንግ፤ ዋት ኢዝ ኔክስት አፍተር ግሎባላይዜሽን’ በሚል ርዕስ ያሳተመው በጣም አነጋጋሪ መጽሀፉ የግሎባላይዜሽን መጨርሻው ቀርቧል ይላችኋል። እንደዚህ ሰው አባባል የግሎባላይዜሽን ዘመን እያበቃ አለማችን ወደ ብዝኃፅንፍ (multi polarity) በመሸጋገር ላይ ነች። በዚህ ጉዳይ ላይ ኦሱሊቫን ብቻውን አይደለም እንደ ፕሮፌሰር ስቲቨን ጊሮድ፤ ቢል አሞት፤ ፈንገር ሊቭሴይ እና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግሎባላይዜሽን እያከተመለት መሆኑን በማስረዳት ላይ ይገኛሉ።

እንደ ምሁራኑ ገለፃ በአለም ላይ ያሉ ሀያላን ሀገራት በኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በማህብረሰብ ጉዳዮች ላይ በሀሳብ ከመቀራረብ ይልቅ በጣም የሚቃረኑ አመለካከቶች እና አሰራሮች እየተከተሉ መጥተዋል። እንግዲህ ይህ ከፋፋይ ፅንፍ የተፈጠረው የብዝሀጽንፉ ዋንኛ አባላት ለግሎባላይዜሽን ምቹ የሆነ አንድ የፖሊሲ ቋንቋ ከመነጋገር ይልቅ የተለያየ ቋንቋ መናገር ሲጀምሩ ነው። በአሁኑ ሰአት ብዙ ላለመግባባት የተግባቡ ጽንፎች በአለማችን ተፈጠረዋል። በዚህ የተነሳ የሀሳብ፣ የገንዘብና የሰዎች ዝውውር አለማቀፍ ከመሆን ይልቅ አካባቢያዊ (regional) እየሆነ እየመጣ ይገኛል። እንደ አለን ቢአቲ አስተያየት ከግሎባላይዜሽን ጋር ጥቃት እየደረሰበት ያለው የሊብራል አመለካከትም ጭምር ነው። ቢአቲ እንደሚለው ከ2017 መጨረሻ ጀምሮ አለማቀፋዊ የሆነው የአለም ኢኮኖሚና የሊብራል ስርአት መፍረስ ጀምሯል።

እንደሚካኤል ኦሱሊቫን አባባል አዲሱ ብዝሀጽንፍ በሶስት ትልልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት የሚመራ ነው። እነዚህም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረትና ቻይናን እና ህንድን ማእከል ያደርገው ኤሺያ ናቸው። እንደምሁራኑ አስተያየት በዚህ ብዝሀፅንፍ ውስጥ ያልተካተቱት ሀገራት እጣ የሚሆነው ወይ በእድገት ወደ ኋላ ይቀራሉ፣ አሊያም ከነዚህ ቀዳሚ ሀገራት ጋር ጥምረት ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና ግን በዚህ የጽንፈኛ ምድብ ውስጥ በአግባቡ ያልተካተቱ እንደ እንግሊዝ፤ አውስትራሊያ፤ ሩሲያ እና ጃፓን ያሉ ሀገራት ማንነታቸውን ለመፈለግ በአለምአቀፍ እንቅስቃሴው ላይ የሚያደርሱት ጫናም ቀላል እንደማይሆን ይፈራል። እንደ እስካንዲኔቪያን ሀገራትና በባልቲክ ሀገራት የጽንፉን ጫና ለመቋቋም አዲስ ጥምረት መመስረት ሊጀምሩ እንደሚችሉም ይጠበቃል። በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ድርጅቶች ማለትም የዓለም ባንክ፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የአለም ንግድ ድርጅት (WTO) የመሳሰሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሚና ቀዝቅዞ አቅመ ቢስ እየሆኑ በመሄድ ላይ ይገኛሉ። በነዚህ ፈንታም በየአካባቢው ዓለም አቀፋዊ ባህሪ የሌላቸው እንደ ብሪክስ (BRICS) ያሉ የተለያዩ ድርጅቶች እየተከፈቱ መሆናቸውን እናያለን።

 ግሎባላይዜሽንን በማዳከም የነዚህን ጽንፎች መፈጠር ያስከተለው ምንድነው ለሚለው ምሁራኑ በርከት ያሉ ምክንያቶችን የስቀምጣሉ። ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የሚያነሱዋቸው የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚና ንግድ ከ2008ቱ ቀውስ ማገገም አለመቻሉና በአለም ላይ በአማካኝ በጣም ዘገምተኛ እድገት እየታየ መምጣቱ ነው። ለቀውሱ ምላሽ ይሆናል ተብሎ የተሰጠው መፍትሄ ሁኔታዎችን አባብሷል የሚሉ ባለሙያዎች ብዙ ናቸው። የአለም ምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ በየሀገራቱ ያለው እድገት በገንዘብ የሚደጎም እንዲሆን አስገድዷል። በዚህም ምክንያት መንግስታት በእዳ ከመዘፈቃቸውም አልፎ ባንኮቻቸው በርካታ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዲረጩ፤ እሴቶችን በመግዛትና እንደ ቦንድ ባሉ ዘዴዎች አለም አቀፍ ሚናቸውን ለማስቀጠል እንዲፍጨረጨሩ አስገድዳቸዋል። ሌላው ምክንያት የግሎባላይዜሽኑ የጎንዮሽ ጫናዎች ናቸው። ለምሳሌ ግሎባላይዜሽን በሀገራትና በህዝቦች መካከል ያስከተለው የሀብት አለመመጣጠን፣ በዚህ ስርአት ውስጥ ተዋናኝ የሆኑ አንዳንድ አለምአቀፍ ኩባንያዎች ሁሉንም ነገር የመቆጣጠር አባዜ ውስጥ መግባታቸው እና የአለማቀፉ የአቅርቦት መስመር ወይም አቅጣጫ መበታተን ናቸው። በሌላ በኩል ለግሎባላይዜሽን መዳከም እንደአመላካች ሊጠቀሱ የሚችሉ ነባራዊ ክስተቶችም አያሌ ናቸው። አንደኛው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቬስትመንት (FDI) በኢኮኖሚው ቀውስ ምክንያት መቀዛቀዙ፣ በምእራባውያን ዘንድ የኢኮኖሚ አለመመጣጠን መከሰቱ እና በዚህም ምክንያት ሀገራት ክልከላ የበዛበት (protectionist) የንግድ ግንኙነት ማራመዳቸው ነው። ይህ በሀገራት መካከል ቀደም ሲል የነበረውን መተማመን በከፍተኛ ደረጃ ሸርሽሮታል። ለምሳሌ ከየካቲት እስከ ነሀሴ 2016 መካከል ብቻ የG20 ሀገራት ወደ 350 የሚደርሱ የክልከላ እርምጃዎችን የሚያስፈጽሙ ህጎችን አውጥተዋል።

 ነገር ግን በዚህ ወቅት ውስጥ ያወጧቸው ለሊብራል መርህ ወይም ለነፃ ገበያ የሚጠቅሙ ህጎች 100 ብቻ ነበሩ። በተለይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቬስትመንትን በተመለከተ የG20 ሀገራት ነፃ ገበያን ከሚያበረታቱት ህጎች 10 እጥፍ የሚልቅ ከልካይ ህጎችን አውጥተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ሀገራት በታዳጊም ሆነ ባደጉት መንግስታት በነጻ አስተሳሰብና በህግ በመገዛት ጎዳና ለረጅም ዘመናት ከተጓዙ በኋላ ይህን አካሄድ ቀዝቀዝ እያደረጉት የመጡ ይመስላል። እንደ ዜጎች ሉአላዊነት፣ ዲሞክራሲና ነፃው ፕሬስ በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ብዙ የኋልዮሽ ሄደዋል። ለዚህም ምሳሌቹ እንደ ቱርክና ሀንጋሪ ያሉ ሀገሮች ናቸው። አሜሪካም የነዚህ ጉዳዮች ጠባቂነቷ የሰለቻት ትመስላለች። ጥረቶቿም በሩሲያና በቻይና እየተጨነገፉባት ናቸው።

 ኃያላን የነበሩ ምዕራባዊያን ሀገራት በአሁኑ ወቅት ከባባድ በሆኑ በየራሳቸው ችግር ውስጥ እየገቡ ይታያሉ። በዚህም የችግር ጊዜ ግሎባላይዜሽን እየጠቀማቸው እንዳልሆነ እየተሰማቸው ይገኛል። በነዚህ ምእራባዊያን አስተያየት ግሎባላይዜሽን መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎቻቸውን እያደኸየ መጥቷል። ይህም የሆነው የዜጎቻቸው ስራዎችና ገቢዎቻቸው በስደት ወደ ሀገራቸው በመጡ በቅናሽ በሚሰሩ የሌላ ሀገር ዜጎች መወሰዱ እንዲሁም ኩባንያዎች ወጪን ለመቀነስ ሲሉ ማምረቻዎቻቸውን ወደ ሌሎች ሀገሮች ማዛወራቸው ነው ይላሉ።

 በየሀገራቱ ያለው የፖለቲካ የሀይል ሚዛን መለወጥም ፖለቲከኞችን አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተ ይገኛል። ፖለቲከኞቹ አሁን የህዝብን ስሜት ወደ መከተል አተኩረዋል። ለምሳሌ አሜሪካውያን የሀገራቸውን ዓለም አቀፍ ሚና ሊደመስስ ታጥቆ የተነሳ የሚመስል መሪ መረጡ። የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ ለየት ባሉ የህዝብ ክፍል መመረጥና በእንግሊዝ ለአውሮፓ ህብረት መለየት የተሰጠው የህዝብ ድምጽ ፖለቲከኞቹን አቅጣጫ ያስቀየረ ነው። ከአህጉሩ ሁለተኛ ኢኮኖሚ ያላት ከመሆኗ የተነሳ የእንግሊዝ ከህብረቱ የመልቀቅ ሀሳብ (BREXIT) የአውሮፓ ህብረት በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል። እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የምትለይ ከሆነ በአውሮፓ ሀገራት መካከል የኢኮኖሚ አለመመጣጠን ስለሚፈጠር የህብረቱን ፖለቲካ፣ ፋይናንስና በጀት ትልቅ ችግር ውስጥ እየከተተው ስለሚሄድ በዓለም ትልቁ የንግድ መስመር የሆነው የአውሮፓ ህብረት እንዳይፈራርስ ስጋት እንዳላቸው ብዙ ምሁራን ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት በምእራባውያን ዘንድ የሚታየው ዝቅተኛ የሆነ እድገት፤ የኢኮኖሚ አለመመጣጠን፤ የቻይና መግነንና በነፃ ገበያው ላይ ያለው የእኩልነትና የፍትሀዊነት ችግር በጥንቃቄ ካልተያዘ የብዙ የምዕራብ ሀገራት ህዝቦች ድምፃቸውን በጣም ፅንፈኛና የክልከላ ህጎችን ለሚደግፉ መሪዎች በመስጠት ወደ ስልጣን እንዳያመጡዋቸው ይፈራል።

 ከዚህም ሌላ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ አለመመጣጠን ጀርመን ብቻዋን ገዝፋ እንድትወጣ ቢያደርጋትም ሌሎች የህብረቱ ሀገራት ኢኮኖሚያቸው ከመቀዛቀዙ የተነሳ የገንዘቦቻቸውን የመግዛት ዋጋ እንዲቀንስ (devaluate) ማድረግ ግድ ሆኖባቸዋል። ይህ ደግሞ በእነዚህ ሀገራት በሚኖሩ ህዝቦች ደመወዝና የመግዛት አቅም ላይ ጫና በማሳደሩ ብዙ የመንገድ ላይ ነውጦችንና አመጾችን እያስተናገዱ ይገኛሉ። የብሄረተኝነትና የማንነት ጥያቄዎችም ባልተለመደ መልኩ በአውሮፓ መግነን ጀምረዋል። ችግሩም ከስደተኞች ጋር በመያያዙ የብዙ ሀገራት መንግስታት የስደተኛ ፖሊሲዎቻቸውን መፈተሸ የህልውና ጉዳይ ሆኖባቸዋል። የአውሮፓ የስደተኛ ችግር የኃይማኖት ጽንፈኝነት ተደምሮበት የመንግስታትን ተባባሪነት የተፈታተነና መረር ያሉ እርምጃዎችን እየጋበዘ ነው።

 እንደ ቢል አሞት ያሉ ምሁራን እንደሚሉት በየሀገራቱ እያቆጠቆጠ የመጣው የፖለቲካ ህዝበኝነት (populism) ኢኮኖሚንና የአስተዳደር ህጎችን በተመለከተ የሚታወቁትን የሊብራል አስተሳሰቦች በከፍተኛ ጫና ስር እንዲወድቁ አድርጓል። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ሰአት እንደ ጣሊያን፣ ፈረንሳይና ኔዘርላንድስ ያሉ ሀገራት በጣም ከባድ በሆነ ፈተና ውስጥ ናቸው። ለዚህም እንደምሁራኑ አስተያየት የአውሮፓ ህብረት ወይ በጣም ጠንከር ወዳለ ፌዴራሊዝም ማቅናት አለበት ካልሆነ ግን ወደ መፈረካከስ መሄዱ እንደማይቀር ተንብየዋል።

 ለግሎባላይዜሽን ያለው አምሮት በአብዛኛው የምእራብ ሀገራት እየተፈተሸ ቢሆንም በአዳዲስ ወደ ገበያው በመጡ ሀገራትና በቻይና በኩል ፍላጎቱ ገና በማደግ ላይ ነው። በትላልቅ ገበያዎች ያለው ጭንቀት እያየለ ሲመጣ በአዲሶቹ ገበያዎች ዘንድ ያለው ተስፋ እየበረታ መታየቱ አስገራሚ ነው። በቻይና እና ገና ብቅ ብቅ እያሉ ያሉ ሀገራት ከግሎባላይዜሽን ሌላ አማራጭ ማየት የሚችሉ አይመስሉም። ምክንያቱም ከ1990 ጀምሮ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ከድህነት ወደ መካከለኛ ገቢ የገቡት በዚሁ ግሎባላይዜሽን በፈጠረው ዕድል ነውና። እንደ ቻይና እና ህንድ ያሉ ምስራቃውያንን ስንመለከት የግሎባላይዜሽንን በረከቱን ማጣጣም የጀመሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመሆኑ የተነሳ ሱሱ አልወጣላቸውም ማለት ይቻላል። በተለይ ቻይና ከ2001 ጀምሮ በግሎባላይዜሽን መርሆ ላይ ተንተርሳ ብዙ ተግባራትን ፈጽማለች። የባህር ላይ ያላት ገናና የኢኮኖሚ መስመር ሳያንሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጧጧፈች ያለችው የየብስላይ የንግድ መስመር ዝርጋታ( Silkroad) ፤ የኤሽያ ኢንቨስትመንት ባንክን መፍጠሯና በዓለም አቀፍ ገበያ ዶላርን የሚተካ ገንዘብ ወደ መፍጠር የምታደርገው ጉዞ ሲታይ በእርግጥም በግሎባላይዜሽን ላይ ተስፋ እዳልቆረጠች ይጠቁማሉ። በተጨማሪም በኒኩለር ኃይል ግንባታ ላይ፣ በእግር ኳስ፣ በሆሊውድ ፊልም እንዱስትሪ ላይ እና በአፍሪካ የምታስፋፋው የግብርናና የመሰረተልማት ስራ የሚያሳየው ሀገሪቷ ገና ብዙ የግላባላይዜሽን በረከቶችን ለመሰብሰብ እቅድ እንዳላት ያሳያሉ።

መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በዚህ ሂደት ቻይና ከግሎባላይዜሽን ከብዙ ሀገራት በላይ ተጠቃሚ ሆናለች። ነገር ግን የIMF ዘገባ እንደሚያሳየው የቻይና ንግድ ዓለም አቀፋዊ ከመሆን ይልቅ ወደ አካባቢያዊነት ያደላል። ከ2011 ከነበረው ጋር እንኳ ሲነፃፀር በአሁን ወቅት ካምቦዲያ፣ ላኦስ፣ ማሌዢያ፣ ባንግላዲሽ እና ፓኪስታንን የመሳሰሉ ሀገራት ከቻይና ጋር የሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ በከፍተኛ መጠን ማደጉን ማየት ይቻላል። በተቃራኒው አሜሪካ ከነዚህ ሀገራት ጋር ያደረገችው የንግድ ልውውጥ እዚህ ግባ የሚባል ሆኖ አልተገኘም። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ቻይና ራሷ ዓለም አቀፋዊ (globalized) አይደለችም ተብላ ትታማለች። ለዚህም ምልክቱ የብዙ ምእራባውያን ሀገራት ኩባንያዎች ከቻይና ጋር መስራት አዳጋች እየሆነባቸው መቀጠሉ ነው። ወደ ቻይና የሚደረግ የሀሳብም ሆነ የገንዘብ ወጪና ገቢ ብዙ ቁጥጥር ይደረግበታል። ምንም እንኳ አሁን ለመቀየር ያሰቡ ቢሆንም፤ በሰዎች ዝውውርም ላይ ተመሳሳይ ቁጥጥር ነው ያለው። የሌሎች ሀገራት ዜጎች ወደ ቻይና የመፍለስ ሁኔታ አይታይም። የቻይናውያን ወደ ውጭ መፍለስ ሂደት ግን በሰፊው ይታያል። ስለዚህ ቻይና ዋንኛው ጽንፍ ሆና ብዙ እየጠቀማት ያለውን ግሎባላይዜሽንን ህልፈቱን እያፋጠነች ነው በማለት የሚከሷት ምሁራን አሉ።

ቻይና ከዓለም አቀፍ ይልቅ ለአካባቢያዊ የንግድ ግኑኝነት አትኩሮት መስጠቷን ብዙዎች አልወደዱላትም። ለምሳሌ በ2012- 2017 ባለው ወቅት ከቻይና ወደ አውስትራሊያ የተደረገ የውጭ ቀጥታ ኢንቬስትመንት (FDI) በ21 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ይህ በ6 በመቶ ብቻ ዕድገት ካሳየው የአሜሪካ እና አውስትራሊያ ኢንቬስትመንት ጋር ሲነጻጸር እውነትም አውስትራሊያ ከኤሽያ የምትስበው ኢንቬስትመንት እያየለ መምጣቱን ያሳያል። ይህም የኢኮኖሚ ግንኙነቱ ከአለማቀፋዊነት ይልቅ አካባቢያዊነት ላይ እያደላ ስለመሆኑ ጥሩ ምልክት ነው። በዚህ የተነሳ ቻይና ከግሎባላዜሽን ወደ ብዝኃፅንፍ የመሸጋገር ምሳሌ ነች ትባላለች። ምክንያቱም በአካባባቢው ባሉት ሀገራት ላይ የኢኮኖሚ መሪ ለመሆን የምታሳድረው ጫና እና የአካባቢዋን ሀገራት በክልላዊ ትብብር ስም ከሌላው ዓለም እንዲነጠሉ ማድረጓ ግሎባላይዜሽን ከሚመራባቸው መርሆች ጋር የተፋለሰ ድርጊት እየፈጸመች እንደሆነ ያሳያል። በሌላ በኩል በዓለም ላይ የሚታየው የቴክኖሎጂ ሽግግርም የማይናቅ ፈተና ይዞ ብቅ እያለ ነው። እንደ ፈንገር ሊቭሴይ አዳድስ ቴክኖሎጂዎች ግሎባላይዜሽንን ከማጠናከር ይልቅ ፍጻሜውን እያቀረቡት እንደሆነ ይነገራል። ባለፉት 30 ዓመታት የነበረው በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ የታየው ግሎባላይዜሽን በተለይ ያተኮረው የሰው ሀይል ወጪን በመቀነስ ላይ ስለነበረ የሰው ሀይል የሚፈልጉ የማምረት ሂደቶች ወጪያቸው ዝቅተኛ ወደሆኑ ሀገራት በመውሰድ ማሰራት የተለመደ ነበር። ዲጂታል ቴክኖሎጂውም መረጃን በፈጠነ ሁኔታ ከተፈለገው የዓለም ክፍል መቀባበል ማስቻሉ ለነዚህ ድንበር ዘለል ካምፓኒዎች ሁኔታዎችን አመቻችቶላቸዋል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ሮቦቶች ዋጋቸው ዝቅተኛ እየሆኑና ውጤታማነታቸውም እጨመረ ከመምጣቱ አምራቾች ርካሽ የሰው ጉልበት ፍለጋ ማምረቻዎቻቸውን አርቆ መውሰድ አላስፈላጊ እንደሆነ እየተገነዘቡ መጥተዋል። ስለዚህ የምርቱ ተጠቃሚዎች ወዳሉበት ሀገር ቀረብ ብሎ ማምረት አማራጭ የሌለው ይሆናል ማለት ነው። ለምሳሌ ርካሽ የሰው ጉልበት ፍለጋ ወደ ኤሽያ ሀገራት ሄደው የነበሩ የአሜሪካ ካምፓኒዎች አሁን እዛው አሜሪካ ውስጥ ከደንበኞቻቸው ሳይርቁ ማምረትና መሸጥ ያስችላቸዋል ማለት ነው። እንደ ዶናልድ ትራምፕ ዓይነት ፖለቲከኞችም በነዚህ ድንበር ዘለል ኩባኒያዎች ላይ እያሳደሩት ያለው ጫናም የዚህን አሰራር ዕድሜ የሚያሳጥሩ ይሆናሉ። በዚህ ሂደት ግሎባላይዜሽንን ተማምነው የነበሩ ታዳጊ ሀገራት ክፉኛ ይጎዳሉ። ምክንያቱም ባላቸው የህዝብ ብዛት በሚፈጠር የሰው ጉልበት ሽያጭ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ያላቸው ህልም እየጨለመ የሚሄድ ይመስላል። ይህንንም ተገንዝበው ሌሎች አማራጮችን እንዲያስቡም ይመክራሉ።

ወደ ብዝኃፅንፈኝነት (multi polarity) የሚወስደው መንገድ ብዙ ፈተናዎች እንደሚጠብቁት ይገመታል። የእነዚህ ፅንፎች መጠናከር ዲሞክራሲን ወደ ማማው ጫፍ በማድረስ በሀገራት መካከል ለተወዳዳሪነት የሚቀርብ የዲሞክራሲ እይታ እንዲፈጠር ያደርጋል። ስለዚህ ጽንፎቹ የኔ የሚሉት የዲሞክራሲ፤ የህዝብ አስተዳደርና የነፃነት ትርጓሜ ይዘው ይወጣሉ ማለት ነው። ሌላኛው ፍራቻ በእነዚህ ፅንፎች መካከል ያሉት የፖሊሲ ልዩነቶች እየሰፉ ሄደው ወደ ከባድ ግጭት እና ጦርነት እንዳይወስዳቸው ያሰጋል። በቻይናና አሜሪካ መካከል እንዲሁም በራሺያና በአውሮፓ ህብረት መካከል የሚታዩ መቃቃሮች የዚሁ መላምት ማጠናከሪያ ይሆናሉ። አንዳንዶች እንደሚሉት ግሎባላይዜሽንን ለመታደግ ቻይና የማታደርገው ነገር አይኖርም። ይህን የምታደርገው ብዙ እሴቶችን በአውሮፓ በመግዛት፣ አፍሪካንና ኤሽያን በበላይነት በመቆጣጠር፣ በምእራባዊያን የኢኮኖሚ ድክመት በመጠቀም፣ እንዲሁም በአሜሪካ በራሺያና በአውሮፓ መካከል እየተፈጠረ ያለውን ተቃርኖ ለራሷ በሚመች መልኩ ለመጠቀም ትሞክራለች ተብሎ ይጠበቃል።

የሆነው ሆኖ ብዙዎቻችን በተለይም የዘርፉ ባለሙያዎቻችን አሁን ማሰብ የሚኖርብን የእንደኛ ዓይነት ሀገራት እጣ ፈንታ በግሎባላይዜሽን ማብቂያ ላይ ምን ሊሆን እንደሚችል በመተንበይና ለዚያ የሚያዘጋጁ ፖሊሲዎችን መቅረጽ እንደሚያስፈልግ ይሰማኛል። ይህን ለማድረግ በርግጥ በቂ ጊዜ ይኖረናል ወይም አይኖረንም ብዬ መናገር ባልችልም ጉዳዩ ግን መፍትሄ የሚሻ መሆኑ አይታበልም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top