ታሪክ እና ባሕል

ክረምት በልጅነት

ክረምት በልጅነት

የልጅነት ትዝታዎች የሚያጭሯቸው አዝናኝ ሁኔታዎች አያሌ ናቸው። አሁን እንኳን ቡሄ ቢነሳ የየራሳችን ጨዋታ ተወርቶ ያልቃል?…

እንዴታ!

የሰፈር ልጆች ተሰብስበን በየዓመቱ ቡሄ የመጨፈር ባህል እና ግዴታ አለብን። ዱላ ያለው ዱላ፣ ግጥም ያለው ግጥም፣ እንደ ጸናጽል ዐይነት የሚንሹዋሹዋ ድምጽ የሚሰጥ በኮርኪ የሚሰራ መሳሪያ፣… እንይዛለን። በከፍተኛ ደስታ፣ በጥሩ ስሜት በጋራ ወደ የመኖሪያ ቤቶች እንዘምታለን።

 የተሰጠንን መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ሳይኖር እና ሳይሰጥም የማመስገን ጨዋ ሥርዓት አለን። የኛ ሰፈር ቡሄ ከሌላው ሰፈር ቡሄ የሚለይበት ነጥብ ያለው ይመስለኛል። በየዓመቱ ከምንሰበስበው ገንዘብ እና ሙልሙል በተጨማሪ ሳቅን የሚያጭሩ ገጠመኞችን እናሳልፋለን። አሳቂው ክስተት ሆን ተብሎ የተፈጠረ ወይም አጋጣሚዎች የወለዱት ሊሆን ይችላል። ዋናው ማስደረሱ ነው። መሳቅ፣ መሳቅ፣ መሳቅ… ብቻ።

ከዓመታት በአንዱ ቡሔ እንዲህ ሆነ። እንደተለመደው እየጨፈርን ነው። ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እየዞርን

 ‹‹መጣና በዓመቱ

ኧረ እንደምን ሰነበቱ››

አንላለን። ከአንዱ ግቢ ወደ አንዱ ግቢ እያንኳኳን

‹‹ክፈት በለው በሩን የጌታዬን››

እንላለን። በዚህ አካሄድ ሰብሰብ ብለን የሰፈር ጊቢ ውስጥ እየጨፈርን ገባን። ግርግሩ፣ ጫጫታው፣ ጩኸቱ፣ ዜማው፣ የእግር ኮቴው፣… ተደማምሮ ጉዟችን የሰዎች አይመስልም። ከብቶች ወደ በረት ለመግባት ሲጣደፉ የሚያሰሙትን ድምጽ ይመስል ነበር። ዜማ እና ግጥም አውጪው ልጅ ከፍ ብሎ ቆሟል። የቤቱን ግድግዳ ታኮ በተሰራው ውሃ ልክ ላይ ቆሞ ‹‹ሆ!›› እያልን ዜማውን የምንከተለውን እኩዮቹን እየተመለከተ ቀጥሏል…

እዚህ ቤቶች… ሆ!

እንደምናችሁ…ሆ

ዓመት ጠብቀን …ሆ…

መጣንላችሁ…..ሆ

እዚያ ማዶ….ሆ

አንድ ቲቸር…ሆ

እዚህ ማዶ…..ሆ

አንድ ቲቸር….ሆ

የኔማ እማማ….ሆ

ማርጋሬት ታቸር….ሆያ

ሆዬ …አብይ ማርዬ

መጨፈሩ ቀጥሏል። አውራጁ የሚችላቸው ግጥሞች አልቀው ተደገሙ። ድካሙን ለመቀነስ ሌላ አውጪ በቦታው ተተክቶ ግጥሞቹን ከለሳቸው። የሁላችንም ድምጽ መስለል ጀምሯል።

ኧረ በቃ በቃ

ጉሮሯችን ነቃ….. አለ።

እኛም ተቀበልን። ኧረ በልጅዎ ይራራ ሆድዎ…. እኛም ደገምነው። ከውስጥ ወፍ ዝር አላለም። አልሰሙ እንደሁ ብለን ባለን ድምፅ ጮኸን ጨፈርን። ምንም። ፀጥ። እርጭ። ግራ ገባን። ዝም አልን። ግቢውን ቃኘነው። ፀጥ ያለ ነው። እስር ቤት ይመስላል። ከወደ ጥግ ላይ ጥርሱን የሚፍቅ ዘበኛ አየን። ተጠጋነው።

“የሉም እንዴ?”

“አዎ!”

“ገበያ ሄደው ነው?”

“አይ አይደለም!”

“አሃ! የታመመ ሰው አለ?”

“ኧረ በፍፁም!”

“ታድያ ምነው ዝም አሉን?”

“የሚከራይ ቤት ነው! ውስጥ

ማንም የለም!” አለን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top