አድባራተ ጥበብ

እያለን እንደሌለን የምንሆነው ለምን

እያለን እንደሌለን የምንሆነው ለምን

 “የዛሬን አያድርገውና ድሮ እኮ ዶክተር ሲባል ሌላ ነበር” አሉ አንድ በዕድሜ የገፉ ሸበቶ ለጨዋታቸው ጅማሮ ጥቂት እንደ ማሟሻ ለመጠቀም ፈቅደው።

 እርሳቸው እንዳሉት በሀገራችን በርግጥም “ዶክተር” ሲባል በሸመገለው ዘመን እንደ አሁኑ ጊዜ በማንኛውም የዕውቀት ዘርፍ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚሰጠውን ከፍተኛ የሆነ “የመጨረሻ ደረጃ” ተብሎ ሊቆጠርም የሚሻውን “ሦስተኛ ዲግሪ” የምርምር ወረቀት ካቀረበ እና ያም ሰነድ በምሁራን ጉባኤ እንዲጸድቅ ተደርጎ የተቀበለው ሰው ሊጠራበት የበቃ አልነበረም ማለት ይችላል።

 እንዲህም ሲሆን በዚያ ለጊዜ አዛውንትነት ምስክር ሊሆን በቻለ ሰዓት “ዶክተር” ከተባለ ያንኑ የሕክምና ሳይንስን ምሩቅ ብቻ የሚመለከት ነበር ማለት ያሰደፍራል። ይህ ስመ ማዕረግ የሚባል ጉዳይ በየወቅቱ ሰዎችን ሲያጣላ የኖረ እንደመሆኑ ዶክተር ላንዳው ከተባሉ አንድ የነምሳ (ኦስትሪያ) ተወላጅ ጋር በረዳት የሕክምና ተግባር ተቀጥሮ አብሮ የመጣ አንድ ጀርመናዊ ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።

 ለዶክተር ላንዳው በረዳትነት ያገለግል ዘንድ ከባሕር ማዶ የመጣው “ሳእን” በመሰኘት የሚታወቀው ያ የጤና ረዳት (ድሬሰር) ውሎ አድሮ ከቀጣሪው ጋር ይጣላና የሚደርሰውን ሒሳብ ተቀብሎ ይሰናበታል። ውላቸውም ወደ ሀገሩ ተመልሶ ሊሄድ እንደነበር ይነገራል። እርሱ ግን በውላቸው መሠረት የተቀበለውን የባሕር መጓጓዣ ገንዘብ ከነሥራ መፈለጊያው ወሰዶ እዚሁ ለመቅረት ወሰነና የራሱን ሥራ ለመክፈት ወዲያ ወዲህ ይል ጀመር። እንዳሰበውም ተሳከቶለት “የራሱ ጌታ” ሆነ። “ቅዱስ ጊዮርጊስ መድኃኒት ቤት” በሚል የፋርማሲ መጠሪያ ከፍቶ ገበያው ደራ። ብዙ ደንበኞችም አፈራ። በድፍን ኢትዮጵያችን የመድኃኒት ቤት ታሪክ ሁለተኛው መሆኑ የሚነገርለትን የዚያን ጊዜውን “ቅዱስ ጊዮርጊስ መድኃኒት ቤት” የማያውቀው ሰው አልነበረም ማለት ይቻላል። ሀገር ያወቀው፣ ፀሐይ ያሞቀው ገበያ እንደነበረውም በስፋት ይነገርለታል።

ከተራ ረዳትነትም አልፎ ወደ “በሰል መድኃኒተኝነት” ራሱን ያሸጋገረው ያ የጀርመን ተወላጅ ብዙ መሰንበትም ሳያስፈልገው ‹‹ሐኪም ሳእን›› እየተባለ “ብር በአካፋ” ሆኖለት ቆይቶ ያንን ሕክምና የተባለውን ነገር እንደገና ይተወዋል። ለጥቂት ጊዜ ያህልም በአዳሚ ቱሉ የግብርና ተግባር ሲያካሂድ ከራርሞ ኢትዮጵያን ለቆ እንደሄደ ይተረካል።

 መማር፣ መመራመር፣ መጠበብ መቸገር መውጣትና መውረድ ሳያሻው ራሱን በራሱ ሾሞ፣ ለራሱ ስመ ማዕረግ ሸልሞ ሲቆፋጠን ለጊዜ አዛውንትነት ምስክር ሊሆን በቅቶ ሄደ። እኔ እንኳ ይህን ያነሣሁት የዚያን ፈረንጅ አጉል ‹‹ቀልድ›› ለመተረክ ሳይሆን ወደ ሌላ ሻገር ለማለት እንድችል ያህል በማለት ነው።

 በተለይ “ሐኪም” ሲባል በዚያን ወቅት የቱን ያህል ታላቅ ስም እንደነበር መዘንጋት አይኖርብንም። ኢትዮጵያዊው ዶክተር ማርቲን ወርቅነህ በብዙዎች “ሐኪም ወርቅነህ” እየተባሉ የሚጠሩበት ማዕረግ ስም ነውና!! ሐኪም ወርቅነህ ከሕክምና ክህነታቸውም በላይ ዲፕሎማት የነበሩ ታላቅ ሰው መሆናቸውን ልብ ይሏል። በውኑም በጽሑፌ መግቢያ ላይ “ዶክተር” ሲባልና ሲጠራ “ሌላ ነበር” ሲሉ አረጋዊው የተናገሩት እንደ ዋዛ ሊታለፍ አይገባውም።

 ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ተደጋግሞ አይጥመው፣ አያጣጥመው፣ አይውጠው የሆነበት ነገር በራስ ቋንቋ ውስጥ የባዕድ ቃል ተሰንቅሮ የመገኘቱ ጉዳይ ነው። እጅግ የሚገርመው ደግሞ በሀገር ልሳን እንደ ልብ የሚገኘው ቃል የግድ በባዕድ ቋንቋ ተተርጉሞ መደመጥ አለበት ወይ? ይህ እጅግ ብዙ የሚያጠያይቅ ነው።

 ለምሳሌ “ሐኪም” የሚለውን ርቱዕ ግሥ ብንወስድ “ብልኃተኛ ሆነ፣ አከመ፣ ፈወሰ፣ አገመ፣ በጣ፣ መድኃኒት ሰጠ…..” ሲል አማርኛችን ከልሳነ ግእዝ ወደ አማርኛ ተርጉሞት እናነባለን። “ሐኪም” ሲል ደግሞ “ብልኃተኛ፣ ወጌሻ፣ ፈላስፋ …” የሚለውን ቃል ይሰጠናል። እንግዲህ በዚያን ወቅት የነበሩ ማእምራን “ዶክተር” የተሰኘውን እንዴት “ሐኪም” ወደሚለው ቃል እያለን እንደሌለን የምንሆነው ለምን? አሸናፊ ዘደቡበ መማር ፣ መመራመር ፣ መጠበብ መቸገር መውጣትና መውረድ ሳያሻው ራሱን በራሱ ሾሞ፣ ለራሱ ስመ ማዕረግ ሸልሞ ሲቆፋጠን ለጊዜ አዛውንትነት ምስክር ሊሆን በቅቶ ሄደ። እኔ እንኳ ይህን ያነሣሁት የዚያን ፈረንጅ አጉል ‹‹ቀልድ›› ለመተረክ ሳይሆን ወደ ሌላ ሻገር ለማለት እንድችል ያህል በማለት ነው።

ዛሬ ግን የቀረው ቀርቶ “ኮብልስቶን” እንኳ የግድ እንዲያ ተብሎ መጠራት አለበት የተባለና በዚህ ካልተጠራ በቀር ለንጣፍም፣ ለምንጣፍም “እምቢኝ” ይል ይመስል ኮብልስቶንን የአማርኛ ቃለ ልሳን እንዲሆንን ማስገደዱ ታይቷል። ሽማግሌውም ባልቴቷም የግዳቸውን እየተንገዳገዱ “ኮብልስቶን” ማለቱን እንዲያውቁበት ተደርጓል።

 በመሠረቱ በአራት ማዕዘን አጠራረብ እንዲስተካከል የተደረገ፣ ተድቦልቡሎም መልክ እንዲይዝ የሆነ ወይም በሌላ ገጽታ የታየ “ኮብልስቶን” ያው “ጥርብ ደንጊያ” ወይም “ጥርብ ድንጋይ” እንጂ ሌላ ስመ ማዕረግ በመሰጠቱ የሚለውጠው ነገር የለም። ታዲያ ይኼ ሁሉ ድካም ለምኑ ነው?

እኔ የዚህ የባዕድ ቋንቋ አለቦታው መደንጎር ፈጽሞ ሊገባኝ የሚችል ሆኖ አላኘሁትም። ምክንያቱ ምን እንደሆነም ባወጣ ባወርደው መሠረተ ነገሩን ልደርስበት አልበቃሁም። አንድ ወዳጄ እንዲያውም በጉዳዩ ላይ ስንወያይ እንዲያው “የሚጠማን የባሕር ማዶኛው ቋንቋ ይሆን?” ያለው ሳይጠቀስ አይታለፍም። እንግዲህ የሚናፍቀን ያ ልሳን ነው ማለት ነው። ስም ለማውጣት ስንፈልግ አማራጩ እያለ ግን የምንፈልገው ያንን “የውጭውን” ነው፤ ያውም የምናውቀውን ሲሆን። የቀረው ቀርቶ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚቀርቡልንን ዝግጅቶችም ብናስተውል ከዚህ ርቀው የሚገኙ አለመሆናቸው ሊያሳዝነን ይበቃል።

ለምሳሌ “የቢዝነስ ዘገባ” የሚለውን ብናይ ከዚህ የተለየ አይደለም። “ቢዝነስ” ለሚለው አማርኛ ጠፍቶ ነው ወይስ እንዳባባሉ “አይገልጸውም” ሊባል ነው? በዚያ “በቢዝነስ ዘገባ” የሚቀርቡትን መሰናዶዎች እናውቃለን። እውን ንግድ፣ የንግድ ነክ ተግባራት የምርትን ወይም ሸቀጥን በሸቀጥ የመለወጥ ሥራ መካሄድ፣ በሀገሮች መሀከል የሚካሄዱ የተለያዩ ምርቶችን የመሸጥና የመግዛት ተግባር፤ ….. ራሱ “ንግድ” የሚለው አይደለምን? ሌላ ምንድን ነው? . . . አያምርም? ወይስ ረዥም ነው? ነው ወይንስ የግድ እንግሊዝኛ መኖር አለበት? ታዲያ “ዘገባ” የሚለውንስ ለምን ዘነጉት “ሪፖርት” ብለው ሊቀጥሉበት ይችሉ አልነበረምን? ለምን ለዘገባው ታዘነለት?

 በየግል ትምህርት ቤቶች ያለውንማ ብንመለከት “የሚመለከተው አካል ብርቱ ቁጥጥር የማያደርገው ለምንድን ነው እስከ ማለት ያደርሳል። ለምሳሌ በመንግሥትና በሕዝብ ትምህርት ቤት ካሉት ውጪ ግን ‹‹ሚስተር፣ ሚስ፣ ሚስስ›› ብለው ይድረሳቸውን ማሳመር የግድ ነው። እንኳን ተማሪውንና የተማሪውን ወላጆችም ቢሆን ‹‹እንዲህ ብላችሁ ጥሩ›› ተብሎ የተነገረባቸውን ቦታዎች አይተናል። የተጀመረበት ጊዜና የአጀማመሩ ሁኔታም አይረሳን።

 “ሚስተር፣ ሚስ፣ ሚስስ” ማለት ምናልባት የተለየ የክብር አሰያየም መስሎ ታይቷቸው ይሆን? ይህ እንዳይባል ደግሞ ይድረሱ እንዲያ የተጣረለት ሰው ምኑም ምኑም ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላ ሆኖ አልተገኘም። “ሚስተር አዝብጤ፣ ሚስተር ጎንጤ፣ ሚስ ሐበሻ፣ ሚሲስ አልሻ” ሲባሉ ሰምተናል። እንዲያው ምክንያቱ ምን ይሆን? ምናልባት ሚስተር፣ ሚስስ፣ ሚስ ሲባል ከሰማየ ሰማያት የወረደ “ቅዱስ ክብረ ማዕረግ” መስሎ ታይቷቸው ነው ወይስ እንደተባለው የሚናፍቀን ያው የባሕር ማዶው ብቻ ነው? ሌላው ቀርቶ ሕፃናት የገበታ ጸሎት በእንግሊዝኛ እንዲያደርሱ መደረጉስ አይገርምምን?

ሀገራችን እኮ የራሷ የሆነ ባህል፣ የራሷ የሆነ ታሪክ በአኩሪነቱም በአስከባሪነቱም ልዩ ቦታ የሚሰጠው የተለየ ወግ ያላት ታላቅ ሀገር ናት። ይህንን ለተተኪው ትውልድ ከማስተማርና “በእርሱነቱ” በታወቀ ግንዛቤ እየጸደቀ እንዲራመድ ከማበረታታትና ሌት ተቀን ከመልፋት ይልቅ ያላወቀውን እንዲያውቅ፣ ያወቀውን እንዲንቅ የማድረጉ ነገር ሊያሳስበን ይገባል ባይ ነኝ። ይህ ካላሳሰበን ሌላውም የሚያሳስበን አይመስለኝም።

ይህንን መሰሉ አካሄድ ውሎ አድሮ የሚያመጣውን ሀፍረት “ይህ ነው” ማለት ለእኔ ይቸግረኛል። ሀፍረት ሲባል ደግሞ ውርደት፣ ቅሌት እንጂ ሌላ አይደለምና በቅጡ ሊታሰብበት የግድ እንደሚል መካድ አንችልም።

እንደ “ሃይድሮጅን፣ ኦክሲጅን” ያሉትን መቼም በቋንቋችን የለንምና ከውጭ ቋንቋ ተውሰን፣ አስገብተን ብንገለገልበት ክፋት የለውም። ግን ያለንን ጥለን የሰው አንጠልጥለን የግድ እንድንጓዝ የተደረገበት ሁኔታ እጅግም ደስ አይለኝም። እንዲያውም የባዕድ ቃላት ደንጉሮ፣ አንዳንዴም አለቦታው ሰንቅሮ ካልተናገረ በቀር “ምሁርነቱ” እንደማይታይ እስከማመን የተደረሰበትን ሁኔታ ለማስታወስ ያስደፍራል።

በእርግጥ በቋንቋ ዓለም መዋዋስ ፍላጎትንና አቅምን የተመረኮረ ወይም የተዋሹን እጦትና የአዋሹንም ሀብታምነትን የሚያመላክት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ምሉዕ ካለመሆን የቋንቋ ተፈጥሯዊ ባህሪ የመነጨ እንጂ። ይህ ማለት ግን መበረዝ ሊያውም ያለአግባብና ያለምክንያት ልቅ የሆነና የራስን ጥሎ የሌላን አንጥለጥሎ ሲሆን ደግሞ፤ የቋንቋን ህልውና ጥያቄ ውስጥ አይጨምርም ማለትን አያመጣም።

 ከራስ ባይኖር ከጎረቤት እንኳ መዋስ ያባት ነው። ኢትዮጵያ፣ የበርካታ ብሔር ብሔረበሶችና ሕዝቦች ሀገር ሆና የቃላት ደሀ ነች ብለን ብንናገር ለሰሚው ግራ ነው። አማርኛ ከግእዝ፣ ከትግርኛ፣ ከሲዳምኛ፣ ከኦሮሚፋ፣ ከከምባትኛ፣ ከወላይታና ከሌሎችም ልሳናት አለወለድ መበደር ይችላል። ቃሉ ካለን የግድ የፈረንጆችን ቋንቋ ወስደን በማናውቀው ስልተ ልሳን መቸገራችን ለምን ይሆን? ቃሉ ከሌለን ይሁን። እያለን የምንቸገር ከሆነ ግን “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” ከማለት በቀር ሌላ ማለት አይቻልም። በተረፈ ግን እያለን እንደሌለን ሆነን የሰውን ልሳን እያከበርን የራሳችንን እያዋረድን መገኘት ከብልኅነት ያስቆጥረን ዘንድ አይበቃም።

 ፈጣሪ አምላክ የ2012 ዓ.ም. ዘመነ ሰላም ያደርግልን ዘንድ የሁላችን ጸሎት ይሁን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top