አድባራተ ጥበብ

አባ ገዳ

አባ ገዳ

ሎሬት ፀጋዬ እጅ በተለመደው የወል ቤት በሚሉት ስንኝ የተቋጠረ ስነ ግጥም ይህም ከእንግሊዝኛው ስነ ግጥም በቀር የቀሩት ሁሉ ምሁራን በእርሳቸው ስም የሎሬት ፀጋዬ ምት/ቤት በሚሉት በባለ ስምንትዮሽ ስንኝ የተፃፈው ግጥማቸው በድምጽ ቀድተው ከሰጡን ቅርስ አንዱኛው ነው። ሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን ራሳቸው እያነበቡ በድምፅ ካስቀረጿቸው ግጥሞቻቸው ውስጥ አንዱም ይኼው ኢልማ ገልማ አባ ገዳ የተሰኘው ግጥማቸው ነው።

ይህንኑ ግጥም ከማንበባቸው በፊትም በመግቢያቸው ላይ ሎሬት ፀጋዬ “መርኤ ገልማ አባገዳን. . . በ1964ዓ.ም ደቡብ ቦረና ድሬ ሊበን ሄጄ ነው ያገኘሁት። ይህቺንም ስነ ግጥም የጫርኩት እዚያ ነው። በአጋጣሚ ካገኘኋቸው ታላላቅ ሰዎች ውስጥ በአንደበተ ርቱዕነቱ ያስደነቀኝ ሰው ነው። መርኤ ገልማ በእምነቱ የኦሮሞ ህዝብ ሁሉ አባ ገዳ ነኝ ብሎ ነው የሚያምነው። ህይወቱም በገዳ ስርዓት እና ህግጋት ብቻ የታጠረ እና የተወሰነ ነው። ነበር ልበል መሰለኝ አሁን አርፏል። ገዳ ኢልማ ገልማ አባ ገዳ በአሪት ሆነ በሐዲስ ኪዳን በቅዱስ ቁርዓን ሆነ በማርክሲስት ወይም የባዕድ ናቸው ከውጭ የመጡ መጤ ኃይማኖቶች ናቸው ብሎ በሚያምናቸው ነባርና ዘመናዊ ስርዓቶች ሁሉ አያምንም። ገዳ ስርወ ቃሉ ካ – አዳ ነው። ካ — እግዚአብሔር፤ አዳ — ስርዓት ነው። ኃይማኖት ነው። ህግ ነው። ባህል ነው። ልክ እንደ ኦሪት ህግ የእግዚአብሔር ስጦታ የካ መመሪያ ነው። ካ አዳ” ብለው ነው የሚጀምሩት።

ኢልማ ገልማ አባ ገዳ

ርቱዕ ጀማ ብፁዕ ጀማ

ለካ አንተነህ

አባ ገዳ- — – ኢልማ ገልማ

ያዳ ኦሮማ ሻማ

ዋቃ ጋዲኒ – – – ነማ ኦሊኒ ሱማ

አካ ሱማ

የተሰኘው እንደ አክሱማ

የተባልከው ፍፁም ጀማ

ለካ አንተነህ

አጋ ኡ —ጋ

ጂጋ ሎ——–ጋ

አባ ሰርዳ – – — አባ ገዳ

አባ ፈርድ ነበልባሉ

እም ቅድመ ኦሪት ባህሉ

ያኢ ቢያ አባ ቃ —-ሉ

ቃሉ የማይቀለበስ ቃሉ

ለካ አንተ ነህ

ስርአት አርካ ኦግ ገዳ

የአድባር ዋርካ

ያዴ እናቴ

ያዴ እሴቴ

ያዴ አቴቴ

ያዴ እቴቴ

ያቴ ሆራ የኩሽ ነዶ

አባ ቦኩ አካሚዶ

ባናትህ ፀሐይ ከለቻ

የምትጠልቅ አንተ ብቻ

የካም ኢድ ኢዶ ምድር

ተነባቢ አስር ምስጢር

አባ ወሮ አባ ወራ አባ ባሮ አባ በራ

አባ ከሮ አባ ከራ

የጅቡቲም ጀበጂሾ

የመቅዲሾም መቀዲሾ

የነሙቴሳ ከምበል—-አ

እንደ ብራሾ ካምፓላ

መነቅ–ደላ አከ መንደላ መቀደላ አከ መቅደላ

የፉላኒ ካኖ ደላ

የምትሰኝ የምታሰኝ

የጎና ቤት

አባ ወራ የላሊ ቤት ላሊ በራ፤ የከረዩ አባ ከራ

በጎፈሬህ ስሪት ላባ

አዶ አዶዬ ውብ ቀዘባ

አዳ —–የቀልቻ ተሸላሚ

ያዱ—– ግንባር ተቀዳሚ

ያዲስ ዘመን መፀው አደይ

አዳ አዱኛን እልል እሰይ የምታሰኝ

የምትሰኝ አዱ አዱኛ

አባ ቢሌ

ያአካ ኪሌ

የአባ ቢሌ

ለካ አንተ ነህ

ገዳ – – ገዳም

ያለም ሰላም

ገዳ ቢሊሱማ ሳቃ

ፈካ ቡራቻ አካ ዋቃ

የፀሐፍት አምላኩ አኒ

ያለበሰህ ድርብ ከኒ

የጥቁር ፈርኦን ልሳን

ያአዴ ኦዳ ፀሐይ ብርሃን

የአዱሊስ አዱኛ ኪዳን

አባ ገዳ አባ በዓል

የቅድመ አክሱማዊት ቃል

የአስርቱ በሮች መሰላል

የማለዳ ንጋት ፀዳል

የኦሩስ ኦሪሳ ተምሳል

ለካ አንተ ነህ

ኦጋ ኡጋ

ጂጋ ሎ — ጋ

ያኢ ቢያ ባ — ቃ –ሉ

የማይቀለበስ ቃሉ

ርቱዕ ጀማ

የተባልከው አጋ ሱማ እንደ አክሱማ

ያዳ ኦሮሞ ሻማ

አባ ገዳ ኢልማ ገልማ

ለካ አንተነህ

1964 ድሬ ሊበን

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top