ፍልስፍና

ሰው የመሆን ጉዞ (በባህል-በፍልስፍና)

ሰው የመሆን ጉዞ (በባህልበፍልስፍና)

 መግቢያ በሰው ልጆች የሐሳብ ታሪክ ውስጥ የፍልስፍና፣ የሳይንስ፣ የሃይማኖት፣ የባህል ጥያቄዎች አንዱ፣ ምናልባትም ዋናው፣ ማጠንጠኛቸው ሰው ነው። ባንድ በኩል ስለ ተፈጥሮ ምሥጢር፣ ስለ ፈጣሪ ህልውናና ባህርይ፣ ስለ ፍጡሮች የርስ በርስ ግንኙነት እንዲሁም ስለ ራሱ ሰው የመሆን ምስጢር የጠየቀና ምላሽ ለማግኘት የሞከረ ራሱ ሰው ነው። በሌላ በኩል ራሱን ካገኘበት ህልው ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ሲፍጨረጨር የሚስተዋለውም ይኸው ሰው ነው። በዚህ ጽሑፍ ሰው የመሆንን ጉዞ በባህል እና በፍልስፍና መነጽር ዳሰሳ ተደርጓል። ሰው የመሆን የማያቋርጥ ጉዞ በአእምሮ መባተት እና በልቡና መሻት በዙሪያው ያለውን ዓለም ከመላመድ ጀምሮ እስከ መቀየር፣ ከመፍጠር ጀምሮ እስከ ማጥፋት፣ በልኩ ሰፍቶ እስከ ማበጀት የሚደርሱ ኅሊና-አእምሯዊ፣ ደመ ነፍሳዊ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል።

ሰው ራሱ ባለበት የማይረካ፣ ይኸው ይበቃኛል፣ ይኸ ነው ልኬቴ የማይል ሽንቁር አቁማዳ ይመስል በሥጋዊ እና ነፍሳዊ ፍላጎቱ የሚባትል፤ እንደማይነጥፍ ወንዝ እንዲሁ በጉዞ ላይ ያለ የጋራ እና የግል መንገዱን በማበጀት፣ ለዚያውም መንገድ ቁርጠኛ ተከታይ ወይም ይሁዳ ክሃዲ (ሌላ መንገድ ቀያሽ) በመሆን የሚናውዝ ፍጡር ነው። እናም ይህ ሰው የመሆን ጉዞ መነሻና መዳረሻውን የሚበይኑ የዕውቀት እና የእምነት መንገዶችን አበጅቶ ያለፈን ሲዘክር፣ ዛሬን ሲኖር፣ ነገን ሲያልም-ሲተነብይ በታሪክ ጉዞ ውስጥ ይገኛል። የነገረሰብ ጉዳይ የፍልስፍና አስኳል፣ የባህል ደም ሥሩ ነውና ሰውን በጋራም ሆነ በተናጠል ለመግራት ያደረጉትን ጥረት፣ ያስገኙትን ትሩፋት ባንድ በኩል፤ በይበጃል መርህ፣ “በብዙኃን ይመውዑ”፣ በከኔ/ከእኛ ወዲያ ላሳር ዘይቤ ያመጡብንን ቅያድ በሌላ በኩል ሚዛን ላይ እእያስቀመጥን እንመልከት። የማንጠሪያ ጥያቄዎቻችን ሰው መሆን ምንድን ነው? ሰው የመሆን ጉዞ መነሻው፣ መንገዱ እና መዳረሻው ምን ይመስላል? ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ ለማድረግ ባህል እና ፍልስፍና የጋራ እና የተናጠል ጡንቻቸው፣ ልዝብ ወይም ሸካራ ቀንበራቸው ምን ይመስላል? የሚሉት ናቸው።

 ባህል እና ፍልስፍና (ሥውር ስፍ ትስስር ወይስ የባላንጦች ሕብረት?)

 ባህልን በሁለት መንገድ መመልከት ይቻላል። አንደኛው፣ በቦታ እና ባንድ ማኅበረሰብ የተገደበ የአስተሳሰብ ካስማ፣ የዕውቀት ጥልፍልፍ፣ የጋራ ፍልስፍና እና ርእዮተ ዓለም የሚለው ነው። ሁለተኛው በዘመን መንፈስ የሚንጸባረቅ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ፣ ሁሉንም የሰው ልጆች ከጫፍ ጫፍ የሚያዳርስ ሰደድ እሳት። በዚህኛው ገጽታው ባህል ከአንድ ማኅበረሰብ አጥር ነጻ በመውጣት በፊታውራሪዎቹ አማካኝነት የቦታን ድንበር ተሻግሮ የእያንዳንዱን በር ያንኳኳል። በዘመን ተሻጋሪነቱ እና የትችትን በትር፣ የከንቱ ውዳሴን እብሪት በመቋቋሙ ወደ ገዥ ሐሳብነት ያድጋል። ሁሉም የሰው ልጆች በየራሳቸው መንገድ የጋራ ንብረት ያደርጉታል።

ዓላማችን ስለ ባህል ማተት አይደለም። ይልቁን በሰው ልጆች የሕይወት ጉዞ ውስጥ ባህል ያለውን ሥፍራ መዳሰስ ነው። Herbert J. Muller “The Uses of the Past” በተሰኘ ሥራው ስለ ዓለም ታሪክ ሲያትት “የሰው ልጅ ብቸኛው የባህል ሰሪ መሃንዲስ እንስሳ ነው። ባህልም ሰው ሰራሽ አካባቢ፤ በዋናነት ሚታዊ እና መንፈሳዊ ምኅዳር ነው። በባህል አማካኝነት፣ የአያት ቅድመ አያቶች ተሞክሮ በማስተማር በተፈጥሮ ደካማ የሆኑትን እድገት ያግዛል… በዚህም ግለሰቦች የባህል ውጤቶች፤ በዋናነት የማይታየው መንፈስ ውሉዳን ናቸው” ይለናል (ገጽ 41)። የዚህ ሙግት መሠረታዊ እሳቤ ባህል የጋራ ማንነት፣ የሕይወት ትርጉም መበየኛ መሳሪያ ሲሆን ግለሰቦችም የባህል ውጤቶች ናቸው የሚል ነው። በዚህ ላይ ሰዎች የባህል ውጤቶች ብቻ ሳይሆኑ ባህል ሰሪዎች እንደመሆናቸው ከነሱ መካከል ተጽእኖ ፈጣሪዎች የታሪክን ጉዞ ሊቀይሱ ይችላሉ። ሙሌር ወረድ ብሎ “ምንም እንኳን የሰው ልጆች የባህል ውጤቶች ቢሆኑም፤ የባህል ህልውናና ውጤታማነት በሰዎች ፈጣሪ ኅሊናና የእምነት ጽናት ይዘወራል።” ሲል ይደመድማል። በዚህም የባህል እሳቤዎች በሐሳብ መሃንዲሶቹ ቁርጠኝነት እና ትባት ወደ ፍልስፍና ያድጋሉ። በሁለቱም አረዳዶች ባህል አንድ ጠባይ አለው። የጋራነትን መሠረት ያደረገ መሆኑ። የአንድ የግለሰብ የሚባል ባህል ብዙም ትርጉም አይሰጥም። የእነ እከሌ፣ የዚህ ዘመን የጋራ አስተሳሰብ፣ የጋራ የኑሮ ዘይቤ ወይም የኅሊና ካርታ መባል የባህል መገለጫው ነው። ግለ ሰቦች ባህልን መልካም ፍሬ፣ ከሰውነት ጋር የማይጋጨውን ገጽታውን የዘመን እና ቦታን ድንበር እንዲሻገር ችቦውን ያቀጣጥሉታል፤ አጅበው ይሸኙታል። ከእነዚህ ውስጥ ፈላስፎቹ ይገኙባቸዋል።

 ፍልስፍና ደግሞ የማሰብ የበኩር ልጅ፣ የምክንያታዊነት ፊታውራሪ፣ የጭፍን እምነት ባላጋራ፣ የአይነከኔትን (Taboo) የሚፈትሽ፣ የሚታየው እና የማይታየውን ዓለማት ለመዳሰስ ዜግነት ያላት ነች ማለት ይቻላል። ፍልስፍና አመጽ ነው። አመጹ ግን በአፈንጋጭነት፣ በደምሳሽነት የሚገለጥ አይደለም። የኢምክንያታዊነትን፣ ያጋራ መሰረተቢስ አስተሳሰብን፣ የተቃርኖን እና የድንቁርናን ሰንኮፍ የሚነቅል፤ የጨቋኝ ተጨቋኝነትን ገዥ ሐሳብ እርቃኑን የሚያስቀር ትችት ነው። በሌላ በኩል ለዘመናት ሳንፈትሽ የተቀበልነውን ኑባሬ፣ ወይም ሳንመረምር የዋጥነው “እውነት” ላይ የሚነሳ የተመስጦ መግነጢሳዊ ኃይል የወለደው አመጽ ነው። አመጽ በባህል ላይ ወይም በሃይማኖት ላይ እንደሚስተዋለው ክህደት፣ ምንፍቅና ወይም እብደት አይደለም። ይልቁን የምንኖረው ኑሮ የተመረመረ፣ ለሰው ልጆች ክብር የሚመጥን፣ ወደ ሰውነት ክብር ከፍ የሚያደርግ የዕውቀት መሰረት፣ ሥነ ምግባራዊ መገለጫ ተግባራዊ ቅቡልነት ያለው ነው ወይ? ብሎ የሚጠይቅ፣ ጠያቂ ኅሊናዎችን የሚቀሰቅስ፣ የጎኸ ጽባሕ ወፍ ነው። በዝማሬ ድምጹ ያንቀላፋውን ዓለም ወደ ንጋቱ ብርሃን ወደ ውጋገኑ የሚጠራ የበገና ቅኝት ድምጽ ልንለውም እንችላለን።

 ይህ ድምጽ ነው ያንቀላፋውን የግሪኩን ዓለም በአደባባይ የሰበሰበ። ሶቅራጥስ አጎራ ላይ “ያልተመረመረ ሕይወት እንደተኖረ አይቆጠርም” የሚለውን መፈክር አንግቦ ፍልስፍናን ከሰማየ ሰማያት ወደ ምድር ሲያወርዳት ሁለት መሠረታዊ ሚናዎችን ተጫውቷል። በአንድ በኩል ምንም እንኳ በፍልስፍናቸው ባነሷቸው ጥያቄዎች እና ምላሽ ለመስጠት ባደረጓቸው ሙከራዎች የፍልስፍና ታሪክ ፀሐፊዎችን አድናቆት መደበቅ ያልቻሉትን የሶፊስቶችን ሸቀጥ በፍልስፍና ስም በትችት ጅራፉ ገርፏል። በሌላ በኩል በMyth/አማህልሎ ወይም በተረት የዶለዶመውን የወጣቶችን ጭንቅላት በአዋላጅ ነርስ ጥበብ ተፈጥሯዊ የማሰብ ክህሎቱን ሲቀሰቅስ እግረ መንገዱን ሰው የመሆን ጉዞ (በባህል-በፍልስፍና) ኢያሱ ባሬንቶ ታዛ መጽሔት | ቅፅ 03 ቁጥር 25 | መስከረም-ጥቅምት 2012 ዓ.ም. 29 በሚኖሩት የኢዲሞክራሲያዊ ሕይወት እና በሚደሰኩሩት የዲሞክራሲ ቃላባይነት መካከል ያለውን ተቃርኖ መሪዎችን፣ የማያውቁትን እንደሚያውቁት አስመስለው ራሳቸውን ያሳመኑትን “ጠቢባን” ነን ባዮች፤ ባጠቃላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ የነበረውን የአስተሳሰብ እና የአኗኗር ተቃርኖ አደባባይ አውጥቶ ጸሐይ እንዲመታው አጋለጠ። ይህ ነው አመጽ ማለት። ይኸው እና የሶቅራጥስ ፍልስፍና የምዕራባውያንን የሐሳብ ታሪክ ጉዞ መንገድ ቀየሰ። ባለቤቱ ደግሞ መርዝ ጠጥቶ የሞት ጽዋን እንዲጎነጭ ምክንያት ሆነ። የዘመኑ መንፈስ የጋራ አስተሳሰብን በማጎልበት፣ ማኅበረሰቡን እንደ ጋሪ ፈረስ በአንድ አቅጣጫ ሲመራው፤ ፈላስፎቹ የረጋውን በማደፍረስ እንዲጠራ፤ በመንሽ እያበራዩ ምርቱን ከግርዱ ለመለየት ይኳትናሉ። እነዚህ የታሪክን ጉዞ ይቀይሳሉ።

 የባህልና ፍልስፍስናን ግንኙነት እና ትስስር ማዕከላዊው ሥፍራ ማኅበረሰብ፤ ግለሰብ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው ቦታ እንዲሁም የጋራ እና የተናጠል ጉዳዮች ላይ መፍትሔ የሚያሻቸው ምሥጢሮች ናቸው። የባህሉ ባለቤት የማኅበረሰብን የጋራ እሴት ለማስጠበቅ ሲታትር ፈላስፋው ደግሞ ቅቡል በሆነው የማኅበረሰብ እሴቶች ውህድ ውስጥ የሰው ልጅን ባህሪያዊ ፍላጎቶች ሊገቱ የሚችሉ እንከኖችን በመንቀስ፤ በጎ እሴቶችን በማስቀጠል ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ለመምራት መንገድ ይቀይሳል።

ማሽላ ጠባቂ ከፍ ካለ ማማ ላይ ሆኖ መልካም ፍሬ ያፈራውን ሰብል ከወፎች ይጠብቃል። በአዝመራው ማማር የተደሰተው ገበሬ ከማማው ወርዶ ወይም ወደ ማማው ከመውጣቱ በፊት ሰብሉን ከአረም ያጸዳዋል። ይኸው ገበሬ ሌሊት አያንቀላፋም። ቀበሮ፣ ከርከሮ፣ ጃርት እንዳይበላበት የሰብል እርሻውን ያስሳል። ቀን ከቤት እንስሳት፣ ከዱር አራዊት (ጦጣ እና ዝንጀሮ)፣ ለመከላከል አንድም በአጥር አልያም በበትር ይጠብቃል። ከአረም እና ከሌሎች ተባዮች ይጠብቀዋል፤ ይኮተኩተዋል፤ የውሃውን ምጣኔ ይከታተላል። በአስተራረሱ ጥበብ፣ በአዘራሩ እና በዘር ምርጫው ባህርይ፣ በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ጣልቃ ገብነት እድገቱን የቀጠለው ሰብል፤ በአንድ ዓይነት የእድገት ደረጃ ያለው ማሽላ፣ ያማረ ምርት ለማስገኘት ጥሩ ሁኔታ (Potential) ላይ ነው ያለው። ድምጽ ሳያሰማ፣ በጉልህ በማይታይ ሥውር የዕድገት ጉዞው የጋራ ፍሰቱን ቀጥሏል። ይህንን ያማረ ማሳ የባህል ተምሳሌት አድርገን እንውሰደው። በአበው ተረት፣ በሽማግሌዎች ምክር ወተግሳጽ፣ በተመረጡ መሪዎቻቸው ጥብቅ ክትትል፣ በምሳሌያዊ አነጋገር፣ በዘይቤ እና በቅኔ ሽንቆጣ፣ በህዝቡ የጋራ ቁጣ እና ፈገግታ የበለጸገውን የጋራ አስተሳሰብ ባህል እንበለው። ኅብረተሰባዊ ውሕደት እና መስተጋብር የተቃና፤ ሰላማዊ የጋራ እና የተናጠል ሕይወት ፍሬያማ ይሆን ዘንድ የባህል ጠበቃዎች ትልቁን ሚና ይጫወታሉ። ከነዚህ ገበሬዎች ውስጥ በልቡና ትባት፤ በኅሊና ርቀት ራመድ ያሉት ደግሞ ከነበረው ዘዴ የተሻለ ደህንነቱን የሚያስጠብቅ መላ የሚፈጥሩ አሉ። እነዚህ የማሳውን የተፈጥሮ የማምረት አቅም እንደሚያግዙት የግብርና ባለሙያዎች በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም በሚናቸው ግን ግዙፋን ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ነው ፈላስፎቹ የሚመደቡት።

 የሰው ልጅ ባህል በተቋማቱ አማካኝነት የሕይወትን ትርጉም ለመበየን በሚያደርገው መጣጣር የሰዎችን ነጻነት ሊጨቁን ይችላል። ከዚህ ማኅበራዊ ጭቆና ለማፈትለክ ጥረት የምታደርግ ነፍስ የፈላስፎችን ድጋፍ ትፈልጋለች፣ ወይም ራሷ ፈላስፎችን ትወልዳለች። የባህል ትልቁ ዓለማው ግብረ ገብነትን እና አንድ ዓይነት የሕይወት መርህን ማረጋገጥ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ትልቁ መሳሪያው ማኅበራዊ ማዕቀብ (Social Control) ነው። የእውነት፣ የበጎነት እና የውበት መበየኛ መስፈርቶች በባህሉ ባለቤቶች የተቀመጡ እና አይነኬ መመሪያዎችን የሚጥስ አባል አካላዊ ወይም ስነ ልቡናዊ ወይም ሁለቱም ቅጣት ይደረግበታል። ሰው ሁሉ እንደ መስኖ ውሃ በአንድ የተቀደደለት ቦይ እንዲፈስ ይደረጋል። ከዚህ ማኅበራዊ ማዕቀብ ለመውጣት በሚደረግ መፍጨርጨር ውስጥ ፍልስፍና ሊጸነስ ይችላል። የባህል እና የፍልስፍና መስተጋብር የሚጀምረውም ለሰው ልጆች ይበጃል የሚሉትን መላምቶች እና ተግባራዊ እርምጃዎች በሚያውጁበት ጊዜ ነው። በባህል ብዙ ጊዜ ያረጀ፣ ያፈጀ፣ ዘመን ያለፈበት የሚባል ነገር የለም። ምንም እንኳ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ሕይወት እንደ አካባቢያዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ክስተቶች የሚለወጡ ቢሆንም ባንዴ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት የሚለው መርህ የባህል ጠበቃዎች አምርረው የሚቃወሙት ጉዳይ ነው። ይህ ዶግማቲዝም በባህል ጠበቃዎች ብቻ የሚስተዋል አይደለም። የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የሳይንስ ርእዮተ ዓለም አራማጆችም የሚስማሙበት ነው። ፈላስፎቹ ከዚህ በተቃራኒ ንቡርን በመፈተን እና በመፈተሽ ከዘመኑ መንፈስ ጋር እና ከሰው ልጆች የተፈጥሮ ፍላጎት ጋር አይስማማም የሚሉትን ሐሳብ ይሰነዝራሉ። የሰውን ልጅ ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ ለማድረግ ይሆናል ያሉትን ሐሳብ በሥነ አመክንዮ በማቅረብ ይሞግታሉ።

 እንደ Redfield ባህል ወይም ልምድ በሁለት ይከፈላል። ትልቅ እና ትንሽ ባህል (High Culture and Low Culture or Great and Little Tradition) በመባል ይመደባል። በትምህርት ደረጃ፣ በዕድሜ ወይም በጥበብ ብዙም ያልሰለጠኑትን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚመሩበት ተራ ባህል ሊባል ይችላል። በተቃራኒው ትልቅ ባህል የሚባለው በአስተሳሰብ ራመድ ላሉ ሰዎች ብቻ የሚረዱት እና የሚመሩበት ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ባህል የሰው ልጆችን ከምድራዊ እና ደመነፍሳዊ ከሚመስለው የእለት ተዕለት ኑሮ ባሻገር እንዲያስቡ እና የሰው ልጆችን የማሰብ ልዕልና ከፍ በማድረግ ትክክለኛውን የሰው ልጆች ባህርያዊ ምንነት እንዲጎናጸፉ የሚያድርግ ነው ይለናል ሌቪን። ታላላቅ ባህሎች ምድራዊውን ሕይወት በመሻገር ከፍ ያለ ስልጡን ሰውን ለማፍራት እንደ መመሪያ ወይም መወጣጫ መሳልል ያገለግላሉ። እንደ ሌቪን አገላለጽ Great Traditions serve us “as guides to transcending worldly habits and thereby producing a higher, “civilized” type of humanity.”

በተደጋጋሚ የጠቀስናቸው ኢትዮጵያዊ የባህል ተመራማሪ ፈቃደ አዘዘም የሰው ልጅ ከመወለዱ አስቀድሞ በሕይወት ዘመኑ እና ከሞቱም በኋላ የሚደረጉ ባህላዊ ክዋኔዎች ጥቅል መጠሪያ ነው ይሉናል። ሰው መሆን ጉዞው አያልቅም እና ከሞት በኋላ ያለ ሕይወት አንዱ ያልተፈታ ጣጣ ነው። ለዚህ ነው ከሞቱ በኋላም አለቀ ተከተተ የማይባልለት። ከዚህ ሐሳብ ጋር ስምሙ የሆነ አነጋገርም በጥንታዊ የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጥስ አንደበት ይገኛል። ፕሌቶ ፌዶ በተባለው መጽሐፉ እንዳስነበበን ለሶቅራጥስ ፍልስፍና የሞት መሰናዶ ነች። ያልተመረመረ ሕይወት ከተኖረ አይቆጠርም ሲለን የፈላስፋው ሕይወት ወደሞት መንገድ የምትደረግ ዝግጅት ናት። ሞት ደግሞ ወደ ተሻለው ዓለም መሸጋገሪያ የሰላም ድልድይ ተደርጋ ተስላለች። ፍልስፍና እንደዚህ ከሆነች እነ ሬድፊልድ “ታላላቅ ባህሎች” ካሏቸው ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ያስመድቧታል።

እንደዚህ ዓይነቶቹን ባህሎች በዋናነት የሚመሯቸው እነማን ናቸው? እዚህ ላይ ነው እንግዲህ በባህሉ ባለቤቶች ዘንድ ጠቢባን (Sages) የሚባሉት ፊታውራሪዎች የሚመደቡት። ከነሱ ውስጥ ፈላስፎቹም ይመደባሉ። የበጎነትን፣ የእውነትን እና የውበትን መርሆዎች የሚያሟሉ፤ በሥነ ምግባር የተከበሩ፣ በዕውቀት እና በጥበብ አንቱ የተባሉት ናቸው። እነዚህን ፊታውራሪዎች እጓለ ገብረ ዮሐንስ የዘመንን ፈተና ለመሻገር፣ በትውልዶች መካከል ድልድይ ለማበጀት የሚጣጣሩ የልብ ትባት፣ የኅሊና ንቃት የተቸራቸው ይሏቸዋል። ሰው የመሆንን ጉዞ በቀን ጸሐይ፣ በጠፍ ጨረቃ እየመሩ ከድንቁርና እና ከጭቆና ማዕበል አላቀው ሥጋዊ ፍትወቱ እና ለኅሊናዊ ትፍስኅቱ ብስራት ነጋሪዎቹ ናቸው። እነዚህ ባህልን ከፈጠሩት፣ ባህልን ከለወጡት፣ ባህልን ካበጁት እና ባህልን ከቀየሩት ወይም በተቃራኒው ባህል ራሱ ከወለዳቸው ጠቢባን ውስጥ በሰው ልጆች ታሪክ “እከሌ እንዳለ” የሚባልላቸው የዘመንና የቦታን ድንበር የተሻገሩ በርካታ ናቸው። ሰው የመሆን ጉዞ ፍለጋው አያልቅም።

 ሰው የመሆን ጉዞ በባህል እና በፍልስፍና ብቻ የተገደበ አይደለም። ሰው ሃይማኖት፣ ሳይንስ፣ ፖለቲካ፣ እንዲሁም ሌሎች ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ሁነቶች፣ ክስተቶች፣ ተቋማት… የሚያላጉት ፍጡር ነው። የምድራዊ እና ሰማያዊ (ስጋዊ እና መንፈሳዊ) ዓለማት የጋራ ዜጋ፣ አማካኝ ፍጥረት ነው እና የረቂቁ – መንፈሳዊ እንዲሁም የግዙፉ ሥጋዊ ዓለማት ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የጸኑ ናቸው። ሰው የመሆን ጉዞ በሃይማኖት እና በሳይንስ ምን ይመስላል? የፖለቲካው እና የቴክኖሎጂው ዓለም የሰውነትን ጉዞ እንዴት እየቃኘው ነው? ቀጣዩ ርእሰ ጉዳያችን እነዚህን ጥያቄዎች ማዕከል ያደረገ ይሆናል። ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top