ጥበብ በታሪክ ገፅ

ፖለቲካ የጋረደው አሸንዳ

ፖለቲካ የጋረደው አሸንዳ

 አሸንዳ፣ ማሪያ፣ ዐይኒ ዋሪ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣… በተለይ በትግራይ እና በዐማራ ክልሎች እንዲሁም በጎረቤት ሀገር ኤርትራ የሚከበሩ የሴቶች የአደባባይ በዓላት መሆናቸው ይታወቃል። ጨዋታዎቹን ለትዳር ያልደረሱ ልጃገረዶች ብቻ የሚጫወቱባቸው መሆኑ፣ የአለባበስ እና የአጊያጊያጥ ተመሳሳይነት መኖሩ፣ ከሚያመሳስሏቸው ክዋኔዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። የጅማሬ እና የፍጻሜ ቀኖቻቸውን ጨምሮ አነስተኛ ልዮነትም አይጠፋቸውም።

ተሳታፊያችን ንጓቸ አሸንዳን መሸረት ያደረገ ትዝታቸውን አካፍለውናል፡፡ ጸሐፊው የግል እይታቸውን እና ትዝታቸውን ባለሙያዎች በመገናኛ ብዙኃን ካስተላለፉት የተሳሳተ ብያኔ ጋር ቀይጠው አቅርበውታል፡፡ ጽሑፉ አሸንዳ ላይ ትኩረት ያድርግ እንጂ ሌሎቹንም አሸንዳ መሰል የሴቶች ዓመታዊ ጨዋታዎች የሚመለከት መልእክት ያስተላልፋል ብለን እናምናለን፡፡ መልካም ንባብ! ***

 የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑኝ ሁለት ጉዳዮች ናቸው። የመጀመሪያው በአሸንዳ በዓል ላይ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን የደረሱበት ድምዳሜ ነው። አጥኚዎቹ ጥናቱን ያካሄዱት በራሳቸው ተነሳሽነት መሆኑ ያስመሰግናቸዋል። የአሸንዳን ባህላዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ስነ- ማኅበረሰባዊ ፍቺ እንድንረዳ፣ በዚህም የተሰነደ የታሪክ ማጣቀሻ እንዲኖረን፣… ያደረጉት ጥረትም የሚደነቅ ነው። በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ላይ በጋራ እና በተናጠል ጥናት ያካሄዱት ምሁራን በትግራይ ቴሌቪዥን ቀርበው የሰጡት ትንታኔ ግን ፖለቲካዊ እሳቤ የተጫነው ሆኖብኛል። በተጨማሪም በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የአከባበር ስነ-ስርአቱ ላይ እየተስተዋለ ያለው ከቀደመ ትውፊት የማፈንገጥ ዘዬ ከግል አስተውሎቴ በመነሳት የቢሆን ሃሳቤን ለማጋራት ያስችለኝ ዘንድ ነው።

ታሪካዊ እና ሐይማኖታዊ መነሻዎች

 አጀማመሩን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ እንዳለው ይነገራል። የአዳምን ከገነት መባረር፣ የኖኅ ዘመኑን የጥፋት ውሃ፣ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቆረጥ፣… ተንተርሰው የሚነገሩ ታሪኮች ቢኖሩም ተደጋግሞ የሚነገረው እና በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ከቅድስት ድንግል ማርያም ትንሳኤ (ፍልሰታ ማርያም) ጋር የተያያዘው ታሪክ ነው። የጥቂቶቹን እንመልከት…

 ልጃገረዶቹ የሚያገለድሙት የአሸንድዬ ቅጠል እና ‘ቆጽሊ አሸንዳ’ በመባል የሚታወቀው ረጅም ቄጠማ አዳም ከገነት ሲባረር እርቃኑን ለመሸፈን የተጠቀመበት ቅጠል ምሳሌ ነው። አዳም እና ሔዋን ከገነት የተባረሩበትን ዕለት እና ያገለደሙትን ቅጠል ያስታውሳል። ጨፋሪዎቹ ያላገቡ መሆናቸው ደግሞ አዳም እና ሔዋን ከገነት ከመባረራቸው በፊት የግብረ-ስጋ ግንኙነት የማያውቁ ደጋግላን እንደነበሩ የሚያሳይ መሆኑን ስለ ጨዋታዎቹ የተጻፉ መዛግብት ያብራራሉ።

ከኖኅ ዘመን ጋር የተሳሰረውን ታሪክ የሚያስረዱት ደግሞ፡- የሴቶቹን አለባበስ በተመለከተ የኖህ መልእክተኛ የሆነችው እርግብ ምሳሌ እንደሆነ ያስረዳሉ። የሴቶቹ ባህላዊ ነጫጭ አልባሳት በኖህ ተልካ የለመለመ ቅጠል በመያዝ ሰላምን ያበሰረችው ነጭ እርግብ ምሳሌ ነው ይላሉ። የጥፋት ውሃውን መጉደል ክረምቱ ከማብቃቱ፣ ፀሐይ ከመውጣቷ፣ ብራ ከመሆኑ ጋር ያገናኙታል። የሚያገለድሙትን ቄጠማ ይዛ ከመጣችው ለምለም ጋር ያገናኙታል።

 ከመስፍኑ ዮፍታሔ ጋር ግንኙነት አለው የሚለው አፈ ታሪክ ደግሞ እንዲህ ይላል። ዮፍታሔ ወደ ጦርነት በሔደ ግዜ ለአምላኩ እንዲህ ሲል ተሳለ። ‘‘በድል የተመለስኩ እንደሆን መስዋእት አቀርባለሁ’’ አለ። ‘‘ወደ ቤቴ ስመለስ በመጀመሪያ የሚቀበለኝን ለክብርህ እሰዋለሁ’’ ሲል ከአምላኩ ጋር ቃል- ኪዳን አሰረ። ከድሉ በኋላ የገጠመው ግን ቀድሞ የገመተውን አይመስልም። አዘውትሮ ከደጅ የሚቀበለው በግ አልተቀበለውም። ድል አድራጊውን ንጉስ እየዘፈነች ልትቀበለው ቀድማ የወጣችው ሴት ልጁ ነበረች። ያልጠበቀው ስለገጠመው አዘነ። ሐዘኑን ያየች ልጁ ግን ለነፍስዋ አልሳሳችም። ለአምላኩ የገባውን ስለት እንዳያስቀር አብዝታ ወተወተችው። ከሁለት ወራት ቁዘማ እና ማሰላሰል በኋላ ስለቱን በልጁ ላይ ፈጸመ። ለሀገር፣ ለሕዝብ፣ ለአባቷ፣ ለፈጣሪዋ የታመነችው ጀግና በየዓመቱ ለአራት ቀናት ሙሾ በማውጣት መታሰብ ቀጠለች። በማለት በዓሉ ላይ የሚፈጸሙትን ተግባራት ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ጋር ያዛምዱታል።

 የበዛ ተቀባይነት ያለው የአሸንዳ አፈ ታሪክ- የድንግል ማርያም ከሞተ ስጋ መነሳት ላይ የሚያተኩረው ነው። በሔዋን ምክንያት የተዘጋው በር በድንግል ማርያም መከፈቱን፣ እርገቷን መላእክት ነጭ ለብሰው በእልልታ፣ በሽብሸባ እና በጭብጨባ ማጀባቸውን፣… ምሳሌ እንደሚያደርግ ምሁራኑ ይናገራሉ።

‘‘ድንግል ማርያም አካላዊ ሥጋዋ ከጌተሰማኔ ወደ ገነት መፍለሱን እንዲሁም በገነት በዕፀ-ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ምክንያት በማድረግ ነው። መመኪያቸው ስለሆነች ልጃገረዶች በዓሉን ያከብሩታል ድንግልናቸውንም አደራ የሚሉት በእርሷ ነው። ዕለቱን ፍስለታ ብለን የምንጠራውም ማርያም ከሞት ተነሥታ ማረጓን፣ ሙስና መቃብር አፍልሳ መነሣትዋን ወይም ዕርገቷን በማሰብ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን በነሐሴ 16 ቀን በመላዕክት ሽብሸባ፣ እልልታ፣ ዝማሬና ዝማሜ ታጅባ ከምድር ወደ ሰማይ ስታርግ በታላቅ ፍስሃ ይመለከቱና በተዓምራቱ ይደነቁም ነበር። ከዚያን ዕለት ጀምሮ ደናግል ቅዱሳን ከመላእክቱ በተመለከቱት ሥርዓት መነሻነት ባህላዊ ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው፣ አምረውና አጊጠው፣ የወቅቱ መታሰቢያ የሆነውን ለምለሟን፣ ከምድር ሳሮች ሁሉ ረዘም ያለችውን ቅጠል በወገባቸው አስረው እንደ መላአክቱ አክናፍ ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ በማሽከርከር እያሸበሸቡ፣ በአንደበታቸው እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በአንድነት ተሰባሰባስበው በፍቅርና በሐሴት ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ በመጾም ጾሙ ከሚፈታበት ከዳግም ዕርገቷ ነሐሴ 16 ጸሎታቸው ተሰምቶላቸው የፈለጉትን ማየታቸውን ምክንያት በማድረግ እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ በየዓመቱ ማክበር ተጀመረ ሲሉ አዋቂዎች ያስረዳሉ።

 በዚህም መሠረት አሸንዳ፣ ማሪያ፣ ዐይኒ ዋሪ ጨዋታ የፍስልታ በዓል መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እንደተጀመረና በምእመኑ ለረጅም ጊዜ እየተከበረ የኖረ ሐይማኖታዊ በዓል እንደሆነ ይታመናል።

 ስሁት ድምዳሜዎች

 ሀ. ፋይዳዎች

 የአሸንዳ በዓልን ጠቀሜታ ለመዘርዘር የሞከረው ጥናቱ፣ “አሸንዳ ሴቶች የዴሞክራሲ ምንነትን የሚማሩበት፤ ‘ሜሪቶክራሲ’ን የሚገነዘቡበት ነው” ይላል። አክሎም ሰብአዊ መብት (human right) የሚንጸባረቅበት፣ ሴቶች እኩልነታቸውን የሚገልፁበት፣ የግጭት አፈታትን፣ እኩልነትን፣… የሚማሩበት፤ የተጻፈ ሕግ ሳይኖር በሕግ የሚገዙበት መድረክ እንደሆነ አብራርቷል። በ“አሳታፊ”ነቱም የምርጫ ስርዓት (electoral process) እንዳለበት ገልጿል።

በእርግጥ አሸንዳ የሴቶችን በራስ መተማመን ያሳድጋል፤ በጋራ ለመስራት የሚችሉበትን ክህሎት ያድላል፤ ይሁን እንጂ “ዴሞክራሲ የሚማሩበት፣ ሜሪቶክራሲ የሚገነዘቡበት፣ እኩልነት እና ሰብአዊ መብት የሚረጋገጥበት ነው” የሚለው ድምዳሜ በዓሉን ፖለቲካዊ ገጽታ ያላብሰዋል፤ ከቱባው ባህል ጋር ያጣርሰዋል ብዬ አምናለሁ።

 አሸንዳ ምንም ዐይነት ፖለቲካዊ ገጽታ የለውም። እርግጥ ነው ዩኔስኮ የሰው ልጅን ሰብአዊ መብት ማስከበር የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በተለይ የንዑሳን (minority) ህዝቦችን ባህል እንደሚጨምር ደንግጓል። በዚህ መነፅር ሁሉም ባህል ሰብአዊ መብት ነው። ራስን በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር ይገናኛል። አሸንዳም ባህላዊ ውርስ እንደመሆኑ ከሰብአዊ መብት ጋር ልናገናኘው እንችላለን። ነገር ግን አሸንዳ በሰብአዊ መብት የሚገለፅ፣ የሚያብራራ (Defined) የሚደረግ አይደለም።

አሸንዳ የተለያዩ እሴቶች (Significance or Values) አሉት። ባህላዊ እሴቶቹ ደምቀው ይታዩ እንጂ መሰረቱ ሐይማኖታዊ ነው። ልጃገረዶች ተሰባስበው በየቤቱ እየዞሩ በዘፈን፣ በከበሮና በጭብጨባ “እንኳን አደረሳችሁ!” እያሉ ዓመታዊ ሥዕለቶች (ቃል መግባቶች) የሚለምኑበት ክርስቲያናዊ ክብረ- በዓል ቢሆንም የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ልጃገረዶችንም ያቅፋል ማኅበራዊ ቁመናው ሐይማኖታዊ ገደቡን ያልፋል። ይህ መሆኑ ባህላዊነቱን ያጠናክራል። ባህል ብቻ ነው ስንል ሐይማኖታዊውን፣ ሐይማኖት ብቻ ነው ስንል ባህሉን እንዘነጋለን፤ የሁለቱ ውህድ ነው።

 በኔ ግምት አሸንዳ ከሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች በተጨማሪ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ቱሪዝማዊ ፋይዳዎች አሉት። ከአልባሳቶቹ እና ጌጣጌጦቹ ጋር በተያያዘ ዕደ-ጥበባዊ መልኮቹ ብዙ ናቸው። ከፀጉር አሰራር ጀምሮ ኩል፣ ቅቤ እና ሽቶዎቹ ደግሞ የሥነ-ውበት ፋይዳዎቹ ናቸው። ልጃገረዶች የሚዝናኑበት መሆኑ የተዝናኖት ፋይዳ እንዲኖረው ያደርጋል።

 ዩኔስኮ የአሸንዳ ክብረ በዓልን ዓለም አቀፋዊ ቅርስ አድርጎ ለማስመዝገብ ጥያቄ ሲቀርብለት የዘርፉ ባለሙያዎችን ልኮ ምን ምን ዓይነት እሴቶች አሉት የሚሉትን ጥያቄዎች ያነሳል። ለዚህም ተጨባጭ እና አርኪ የሆነ መልስ ማግኘት ይገባዋል። የጥንቱን ነባር ባህል አስቀጥሎ፣ ከዓለም የሚለይባቸውን መልኮች አጉልቶ ማሳየት የባህሉ ባለቤት ወይም ህዝብ እና መንግሥት ሐላፊነት እና ፈተና ነው። ባህላዊ ክዋኔውን ሳይበረዝ እና ሳይሸራረፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ ካልቻልን ብርቅነቱንም ሆነ ከዓለም ልዩ የሚያደርገው ቅንጣት ይመናመናል።

አሸንዳ የሴቶች እኩልነት የሚገለፅበት መድረክ አይደለም። ሃይማኖታዊና ባህላዊ መነሻዎች ያሉት ራሱን የቻለ ውርስ ነው። የባህላዊ እቶች ባህርይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተለዋዋጭ ቢሆንም አሸንዳ እኩልነትን ያረጋገጠበት፣ ሰብአዊ መብትን ያስከበረበት፣… ጊዜ ኖሮ አያውቅም።

 ሴቶች ዓመታዊ ሥለቶቻቸውን የሚያደርሱበት፣ ሠናይ ዘመን የሚመኙበት፣… የጨዋታ ጊዜ እንጂ ሰብአዊ መብት የሚያከብሩበት ወይም እኩልነትን የሚያውጁበት የፖለቲካ መድረክ አይደለም። ተሰባስቦ መጫወት፣ ፈጣሪን ማመስገን እና እንኳን አደረሳችሁ እያሉ የመልካም ምኞትን መግለጽ እንደምን ብሎ ከመብት ጋር ይዛመዳል? ወቅቱ የአዝመራ እንደመሆኑ አዝርዕት የሚያሽቱበት ነው። የአሸንዳ ልጆች ሰብሎቻቸው እንዲያሽትላቸው፣ ወይፈኖቻቸው እንዲደልቡ ይመኛሉ። ለህዝባችን ጤና እና ለኪዳነምህረት ምስጋና ያቀርባሉ። ስለዚህም የአሸንዳ ክብረ በዓልን ከማይዛመደው “ዘመን አመጣሽ” የፖለቲካ አጀንዳ ጋር ማዛመድ ያልተገባ ነው።

 ለ. የአከባበር ልዩነት

 የጥናት ባለሙያዎቹ በትግራይ ክልል የሚከበረውን አሸንዳ ዋና መሰረት አድርገው ባጠኑት ጥናት አሸንዳ፣ ማሪያ፣ ዐይኒ ዋሪ በተለያየ ጊዜ እንደሚከበሩ አንስተዋል። የጊዜ እና የስያሜ ተለያይነቱም በየ-አከባቢው የተለያዩ አድባራት ወገዳማት ስላሉ ነው የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ከ4 ሺህ በላይ አድባራት እና ገዳማት ባሉበት ሐገር የተሰጠው ምክንያት አሳማኝነት አይኖረውም። ይልቁንም ለተጨማሪ ጥናት እና ምርምር በር የሚከፍት አጋጣሚ ይሆናል እንጂ…

TIGRAY, ETHIOPIA – AUGUST 21: Orthodox Christians observe the Ashenda Festival marking the end of a two-week-long fast known as Filseta, in Mek’ele city, Tigray region of Ethiopia on August 21, 2016. (Photo by Minasse Wondimu Hailu/Anadolu Agency/Getty Images)

 የቀደመው አከባበር

 የአሸንዳም ሆነ የሌሎቹ የሴቶች የአደባባይ የጭፈራ በዓላት የቀደመ አከባበር ይህንን ይመስላል። የጨዋታው ተሳታፊ ልጃገረዶች ከበዓሉ ቀደም ብለው ቡድን ይመሰርታሉ። የቡድኑ አመሰራረት ደብርን (ሰፈርን) መሠረት ያደረገ ነው። አልባሳታቸውን እና ጸጉራቸውን አስተካክለው፣ ከበሮ ይዘው፣ አውራጅ እና ገንዘብ ያዥ መርጠው መሰናዷቸውን ያጠናቅቃሉ። በመጀመሪያ ወደ አጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው ያመራሉ። ደጀ ሰላሙን ከተሳለሙ በኋላ ዝማሬ እያሰሙ ቤተክርስቲያኑን ሦስት ጊዜ ይዞራሉ። ለዓመት ያደረሳቸውን አመስግነው፣ ለከርሞ እንዲጠብቃቸው ጸልየው ይወጣሉ።

 ከዚያም በየሰፈሩ፣ በየመንደሩ እየዞሩ እንኳን አደረሰን ይላሉ። ሳምቱን ሙሉ ተመሳሳይ ተግባር ይፈጽማሉ። በጭፈራ እና በጨዋታ ሲደሰቱ እና ሲያስደስቱ ሰንብተው፣ አሮጌውን ዓመት ሸኝተው፣ አዲሱን ይቀበላሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተስተዋለ የሚገኘው አከባበር ግን የተለየ መልክ በመያዝ ላይ ነው። በጥቂቱ እንመለከታቸው፡-

 ሀ. የፖለቲከኞች ያልተገባ ጣልቃ ገብነት

 በክብረ በዓሉ ላይ ፖለቲከኞች ንግግር ያደርጋሉ። ይህ የማይገባ እና ከበዓሉ ጋር የማይሄድ ባህርይ ነው። የዘንድሮው አሸንዳ “የአንድነታችንና የሰላማችን” (ንሓድነትናን ንሰላምናን) በሚል መሪ ቃል ነበረው። ማነው መሪ ቃሉን የሰየመው? መንግሥት? መሪ ቃል ያስፈለገበት ምክኒያትስ ምንድነው? “አሸንዳ ራሱ አንድነት ነው! በባህርዩም ሰላም ነው!” ከሚለው ጋር አይጋጭም? ሌላ ተጨማሪ ተቀጽላ ያስፈለገው ለምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች አሸንዳ የሙዚቃ ምድረካ (concert) አድርገው ቆጥረውታል። አሸንዳ የሙዚቃ ኮንሰርት ከሆነ ዩኔስኮ ለምን በዓለም ቅርስነት ሊያስመዘግበው ይገደዳል? በሌሎች ሀገሮች ዳንኪራና ጭፈራ የሚደለቅበት ኮንሰርት ስለሌለ ነው?

መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ናቸው። የአሸንዳ ክብረ በዓል በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ ይኑርልን የምንልበት ምክንያት

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top