አድባራተ ጥበብ

የከተማው መናኝ!

የከተማው መናኝ!

የእድሜውን እኩሌታ ያህል ስቱዲዮ አሳልፏል። እስከ ሦስት ቀናት ለተራዘመ ጊዜ ያለ እንቅልፍ የሚቆይባት ስቱዲዮ የሙዚቃ መፍለቂያ ብቻ አልነበረችም። የሐሳብ ጡብ እየተደረደረ ሰው የሚገነባባትም ጭምር ነበረች። ሸውራራ ምልከታ የሚወልዳቸው ስንኞች በንስሃ ራሳቸውን ወደ ቀና መንገድ መርተዋል። የተጣመመ መልእክት ያላቸው ግጥሞች በቀና ሐሳብ ፍላጻ ተቀጥቅጠው ስሙር መልክ ይዘዋል። የነበረውን እንዳልነበረ ያልነበረውን ህልው የማድረግ አቅሙ የገዘፈ ነበር።

 ከተማ ተወልዶ ከተማ የራቀው፣ ብዙዎች ዓለምን የሚዞሩበትን መክሊት አዋልዶ በስቱዲዮ የታጠረው ብላቴና ለፍልስፍናው ታምኖ ኖሮ እንደታመነ ተለይቶናል። ለመሆኑ ወዳጆቹ እንደሰው ሲያዩት እንዴት ነበር? ተደጋግሞ ከተወራለት የቅንብር ብቃቱ ባሻገር በብዕር ተወልደው በንጉርጉሮ ዓለምን የናኙት ግጥሞቹ እንደምን ያለ ፍልስፍና ተሸክመዋል? መልሱ እንደ ጥያቄው ቀላል አይደለም። 19 ዓመታትን በአግባቡ መፈተሸ ይጠይቃል። ከ400 በላይ ሙዚቃዎችን በጥንቃቄ ማድመጥን ይፈልጋል። ከ40 በላይ ድምጻዊያንን ማግኘት ግድ ይላል።

 ኤልያስ የሚድያ ሰው አይደለም። ስራው ላይ የበለጠ ያተኩራል እንጂ ራሱን ለመሸጥ የሚያደርገው ጥረት የለም። ለሞቱ ቀረብ ባሉት ዓመታት ግን ባልተለመደ መልኩ በሚድያዎች መቅረብ ጀምሮ ነበር። በወቅቱ በልዩ ልዩ ሐሳቦች ላይ ከተናገራቸው መካከል ጥቂቶቹ እንዲህ ይነበባሉ።

የሙዚቃ አሰራር አሁን እና ድሮ

 እኔ ከገባሁ ወዲህ በጣም ብዙ አጋዥ ነገሮች መጥተዋል። ቴክኖሎጂውም ያግዘናል። ሙዚቃ መስራት እንደ ድሮ ከባድ አይደለም። አሁን ብቻህን ሆነህ ምን ዐይነት ሙዚቃ እንደሰራህ መስማት ትችላለህ። ድሮ እንደዚህ አይደለም። ቤዙን የሚይዝልህ ሰው ያስፈልግሃል፣… ሌላም ሌላም። ይህ ነገር ኪቦርድ የሚባለው መሳሪያ ከመጣ በኋላ የመጣ ቢሆንም አሁን ግን የበለጠ በኮምፒውተር የፈለከውን ነገር የምትሞክርበት እድል ተፈጥሯል። ቴክኖሎጂው በራሱ ሙዚቃው እንዲያድግ አግዞናል። ቴክኖሎጂውንም ለማግኘት ብዙ ከባድ አይደለም።

የዐዲስ ልጆች ትኩረት

ዐዲስ ዘፋኝ ነጻነት ይሰጥሀል። አዲስ ዘፋኝ ነው፤ ገና መስመሩ አይታወቅም፤ ስለዚህ ምንም መስመር የምትሞክርበት ነው። አንድ ታዋቂ ዘፋኝ፤ ተቀባይነቱ በጣም የተረጋገጠ ዘፋኝ፤ ብትነካካው የተወደደበትን ነገር ልታፈርስ ትችላለህ። ሰው የወደደለት ነገር አለው ስለዚህ እሱን ጠብቀህ እዚያ ነገር ላይ ነው ሰውየው መሔድ የሚፈልገው። እኔ እፈራለሁ። ዝም ብዬ አልነካካም። አዲስ ዘፋኝ ከሆነ ግን ትሞክራለህ። ነጻነት አለው። ከዚህ በፊት ይሔ ያዋጣኛል የሚለው ነገርም የለውም። ያ ትልቁ ዘፋኝ እሺም ላይልህ ይችላል። ከዚህ በፊት ያዋጣኛል የሚለው አካሄድ ስላለው ስንዳትነካበትም ይገድብሀል። አዲስ ሲሆን ግን መስመሩን መለየት ይጠበቅብሀል። የሆነ ዘፋኝ መስመሩን አግኝቼ፣ ከኔ ቀጥሎ ሌላ ቦታ ሲሰራ ምን መስራት እንዳለበት አውቆ ሲሄድ ደስ ይለኛል።

ከገበያው እና ከስሜት

 አንዳንድ ዘፋኝ ሲመጣ ከዚህ በፊት ራሴ ሰርቼው የተወደደ ሥራ ይዞ መጥቶ የእሱ ዐይነት ይለኛል። የመጣበት ምክንያት ያኛውን ወዶት ሊሆን ይችላል። እኔን ግን አያስደስተኝም። የዚህ ዐይነት ሲለኝ የመስራት ፍላጎቴን ያጠፋዋል። ዐዲስ ነገር ነው ደስ የሚለኝ። ብዙ ዘፋኝ ሲመጣ ያችን ዘፈን እንደሚወዳት በነገደምዳሜ ይነግርሃል እንጂ አያስገድደኝም። አምነውኝ ነው የሚሰሩት፤ የፈለኩትን ስሞክር ይታገሳሉ። የሆነ ጥሩ ነገር ይመጣል ማለት ነው ብለው ይጠብቁኛል በዚህ እድለኛ ነኝ።

 ሰው ወደደው አልወደደው ግድ የለኝም የሚባል ነገር የለም። ሰው መውደድ አለበት። ሰው ካልወደደው ካሴቱ ወድቋል ማለት ነው። ወደ ህዝብ ሲወጣ ሰው መስማት አለበት። ካልሰማው መጥፎ ነው ማለት ነው።

የሚሰማ በሙሉ ጥሩ መልእክት ስላለው ነው ማለቴ አይደለም። እንደ ሙዚቃ ከመልእክቱ ውጭ የተሳካ ሲሆን፣ የቃላቱ ውበት፣ ዜማው፣ የሰውየው ድምጽ ስክትክት ሲል ሰው ሲሰማው ያ ዘፈን ተሳክቷል ማለት ነው። የሚሰራው ሰው እንዲሰማው ነው። ነገር ግን በተደጋጋሚ ድምጽ ሰውንም እንዳታሰለች፣ አንተ ደስ ሲልህ ሰውንም ደስ ይለዋል ብለህ ማመን ነው። ሳይሰማ ሲቀር ሰው አልገባውም እኔ መጥቄ ሔጄ ነው የሚል ጨዋታ ውስጥ አልገባም።

ሙዚቃ አዋጭ ነው?

ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቃ አዋጭ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሙዚቃ በጣም ይወዳል። የራሱን ሙዚቃ በጣም ይሰማል። ከአፍሪካ ውስጥ የራሱን ሙዚቃ አብዝቶ የሚሰማ ብቸኛው ህዝብ ይመስለኛል። አንዳንዶቹ የፈረንሳይን፣ አንግዚዝን በብዛት ይሳማሉ። ከቅኝ ግዛት አንጻርም ይመስለኛል። የኛ ሰው የውጭ ዘፈን ቢሰማም አብዛኛው ግን የሐገሩን ነው የሚሰማው፤ ቋንቋው የፈለገውን ቢሆን የሐገር ውስጥ ይሰማል። የሕዝብ ቁጥሩም ብዙ ነው። የትም ሐገር ብታገኘው አጠገቡ የሐገሩን ዘፈን አታጣም። በዚህ ነገር እየተጠቀመ ያለው ሙዚቀኛው ነው አይደለም ግን ሌላ ጥያቄ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top