አድባራተ ጥበብ

የኤሊያስ መልካ ብዕር

የኤሊያስ መልካ ብዕር

ኤልያስ መልካ የሚለው ስም በኢትዮጵያ የሙዚቃ አቀናባሪዎች ዝርዝር ውስጥ የገባው በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው። ብላቴናው የአንጋፋው ድምጻዊ መሐሙድ አህመድን “ሁሉም ይስማ” የተሰኘ ሙዚቃ በማቀናበር በዓለማዊ ሙዚቃ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ አንድ አለ። በሙሉ ባንድ ከተቀናበረው የመሐሙድ አልበም በኋላ በእነ ሙሉጌታ አባተ የተጀመረውን የአንድ ሰው የቅንብር ዘዬ በሚገባ አሳድጎ ተከታይ ለማፍራት ችሏል። በሐገራችን የዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ የዱላ ቅብብል ውስጥ የራሱን ግዙፍ ቀለም በጉልህ ለማተም ቻለ። የቲያትር ቤቶቹ፣ የኦርኬስትራዎቹ የነ ኮረኔል ሳህሌ ደጋጎ ዘመን ለሌላ ዘመን ተረኛ ቦታውን ለቀቀ። የሮሃ ባንድን ወርቃማ ዘመን አሞራው የሙዚቃ ቡድን ተረከበ። አቀናባሪ መሐመድ ጥቂት መስመሮች አስጉዞ ለሙሉጌታ አባተ አቀበለው። በ1993 ዓ.ም. የቴዎድሮስ ካሳሁን “አቡጊዳ” የተሰኘ አልበም ደግሞ ጉዟቸው የረዘመ ሁለት አዳዲስ ሙያተኞች ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ አበረከተ። በበኩር ሥራው አስገድዶ የሙዚቃ አድማጭን ቀልብ ተቆጣጠረ።

 ሙዚቃን የጀመረው በቤተክርስቲያን ውስጥ ነው። ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በመማር ደግሞ ይበልጥ አዳብሮታል። በባንዶች ውስጥ ድምጻዊያንን በማጀብም ሰርቷል። ጽዮን መንፈሳዊ የሙዚቃ ባንድ፣ መዲና ባንድ፣ 3ኤም ባንድ፣ ዜማ ላስታስ፣ አፍሮ ሳውንድ ባንድ ከተጫወተባቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ።

 የኤሊያስ ስም በቅንብር ተደጋግሞ ይነሳ እንጂ የግጥም ሥራዎችም አሉት። ከኢዮብ መኮንን ጋር “እንደ ቃል” ሲሉ የሰየሙት የድምጻዊው የበኩር ሥራ የአብዛኛዎቹን ግጥሞች እና ዜማዎች ከቅንብር ጋር ሰርቷል። በበርካታ የሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው “እንደ ቃል” ኤልያስን በአዲስ ተሰጥኦ እንድናውቀው ብቻ ሳይሆን እንድናደንቀው አስገድዷል።

 ግጥም እና ዜማ ሰርተው የስቱዲዮውን ደፍ የረገጡ የሙያ ጓደኞቹ እንዲህ ይላሉ።

 ግጥም ይዘህ፣ ቅንብር ፈልገህ ኤልያስ ጋር ስትሄድ መጀመሪያ ሥራውን ደጋግሞ ይሰማዋል። ቀጥሎ ጥያቄ ይጠይቅሃል። ይህንን ቃል ባትለው ምን ይመስልሃል? መልእክቱን ወደ ቀና መንፈስ ብንወስደው ይበልጥ አይዋብም?… ይልሐል። በዚህ ጊዜ ባነሳቸው ነጥቦች አለመስማማት አትችልም። ወደ ቤትህ ገብተህ ጨረስኩት ብለህ ያሰብከውን ሥራ አፍርሰህ ከ-ሀ ትጀምራለህ።

 ከሙዚቃ ባሻገር በርካታ ሐሳቦች የሚነሱባት፣ የውይይት የክርከር እና የሐሳብ ማፍለቂያ የሆነችው የኤልያስ መልካ “በገና” ስቱዲዮ በርካቶች ተመላልሰውባታል። በሙያቸው አንቱታን ካተረፉ አንጋፋዎች ጀምሮ እስከ ጀማሪዎች ድረስ አስተናግዳለች። ለ19 ዓመታት ከሰማናቸው ድምጾች ጀርባ የእርሱ አሻራ አርፎባቸዋል። ከኤልያስ ጋር መስራት የብቃት መለኪያ እስኪሆን ድረስ የጠነከሩ ሐሳቦች፣ ጨለምተኛ ያልሆኑ ስሜቶችን ያዘሉ ሙዚቃዎችን ሰጠን፤ ሙዚቃን ከስሜት በላይ እንድንገነዘብ መንገድ ከፈተልን።

 ብዙዎችን ለማስማማት የበቃው ኤልያስ በሙዚቀኛው እና በሙዚቃ ባለሙያው መካከል ያለውን ቀጭን መስመር ማግኘት ችሏል። አብዝሀው አድማጭ ሳይደናገር በጥሩ ስሜት የሚያደምጠው፤ ባለሙያው እጅግም ተራ ሳይሆንበት እጅግም ሳይከብደው እንዲደነቅበት ማድረግን ችሎበታል።

 የአብነት አጎናፍር- “ድብቁን ውበት”፣ የፍቅር አዲስ ነቅአጥበብ- “ልዑል አስወደደኝ”፣ የማዲንጎ አፈወርቅ- “አይደረግም”፣ የአረጋኸኝ ወራሽ- “በቃ በቃ”፣ የግርማ ገመቹ- “ትመቺኛለሽ”፣ የደረጄ ዱባለ- “ዐይኔን አላሽም”

ከቅንብር ሥራዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ከነባሮቹ ይልቅ አዳዲስ ወጣቶችን የማብቃት ሥራ ላይ ሕይወቱን ሙሉ የተጋው ኤልያስ በመጀመሪያ ሥራቸው አድማጭ ልብ ውስጥ እንዲቀሩ ካደረጋቸው የወቅቱ ጀማሪዎች መካከል ቴዎድሮስ ካሳሁን “አቡጊዳ”፣ ትግስት በቀለ “ሳቂታው”፣ ኃይልዬ ታደሰ “ሁሌ ሁሌ”፣ ዘሪቱ ከበደ “ዘሪቱ”፣ ኢዮብ መኮንን “እንደቃል”፣ ሞኒካ ሲሳይ “ሸክሽክ”፣ ኃይሌ ሩትስ “ቺጌ”፣ ሚካያ በኃይሉ “ሸማመተው” ተጠቃሾች ናቸው።

 ከድምጻዊያን ጀርባ ያሉ ሙያተኞችን ማድነቅ ባልተለመደበት ጊዜ የሥራዎቹ ጉልበት “ይህ ሰው ማን ነው?” እንዲባል አስገደደ። አጠር ካለ ቁመናው፣ ዝግ ካለ ንግግሩ በላይ ድንቅ ተሰጥኦው ጎልቶ ተደመጠ። ቀርበው ያነጋገሩት፣ አብረውት ውለው ያደሩ ደግሞ ራሱን ለሙያው ያስገዛ ለመሆኑ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ስለ ስብዕናው ግዝፈት መስክረዋል።

ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ “እምባዬ” የሚለውን ዜማዋን ቅንብር ስትሰማ እንዳለቀሰች፣ ከርሱ እድሜ መሰል ሥራ እንዳልጠበቀች መናገሯን አስታውሳለሁ። የግጥሙን ሐሳብ ከዜማው ፍሰት ጋር የማዋሀድ ችሎታው የላቀ ስለመሆኑ በርካታ ሙዚቀኞች ብዙ ብለዋል።

በአንድ ወቅት በሸገር ኤፍ ኤም ይተላለፍ በነበረው “የጣዕም ልኬት” የተሰኘ የሙዚቃ ሒስ ፕሮግራም ላይ እንዲህ ተጠየቀ። ለቅንብር ዘዬህ እንደምን ያለ መላ ትጠቀማለህ? ጥቂት ሙዚቀኞች ቀላል ናቸው ይሉሀል።

መልሱ እንዲህ የሚል ነበር። “ለዘፈኑ ሙዚቃ ስሰራ ሙዚቀኞችን አላስብም። ሙዚቀኛ ከብዶት እንዲሰማው፣ ተጨምቆ እንዲጫወተው እያልኩ አልሰራም። የዘፋኙን ድምጽ፣ ዜማውን እና ግጥሙን ነው የማስበው”

በተለይ እስከ ኢትዮጵያ ሚሊንየም ድረስ  ያሉትን ዓመታት በብቸኝነት ለማለት  በሚያስደፍር ሁኔታ እጅግ የበዙ አልበሞች  ሰርቷል። ለትራፊክ አደጋ፣ ለኤች አይ ቪ፣…  እና ሌሎችንም ማኅበራዊ ጉዳች አንስተው  ግንዛቤ የሚሰጡ ዘፈኖችን ቅንብር ሰርቷል።  ከአንድ በላይ ድምጻዊያን የሚሳተፉበት  የሕብረ ዝማሬ ቅንብሮች ላይም ኤልያስ አለ።

 ማለባበስ ይቅር- ዓለማየሁ እሸቴ፣ ምኒልክ  ወስናቸው፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ኢዮብ መኮን፣  ዘሪቱ ከበደ፣ እና ሌሎችም የተሳተፉበት፤  ኑር- አብነት አጎናፍር፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ጆኒ ራጋ  የተሳተፉበት፤ አሽከርክር ረጋ ብለህ- ምናሉሽ  ረታ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ግርማ ተፈራ፣ ሞገስ  ተካ እና ሌሎችም የተሳተፉበት፤ የአፍሪካችን  ህብረት- ትግስት በቀለ፣ ሳምቮድ፣ እና  ሌሎችም የተሳተፉበት ሥራዎች ቀድመው  ከትውስታ የሚገቡ ናቸው።

 ኤልያስ በዘፈን ግጥም ሐሳቦች ዙሪያ በዘፋኞች  ላይ ቀላል የማይባል ተጽእኖ አሳድሯል። ዘፈን  ስሜት የወለዳቸውን ሐሳቦች ማንጸባረቂያ  ቢሆንም ኤልያስ የተለመደ ጥያቄ አለው።  “የዚህ ዘፈን ፋይዳ ምንድ ነው?” የሚል  ኤልያስ ዘፈኑን እንዲሰራልህ መክፈል ብቻ  አይበቃህም። መውደድ አለበት ከድምጽህ  ጀምሮ ዜማ እና ግጥምህ ሊማርከው ይገባል።  ካልሆነ ስሜቱ እሺ አይለውም። ታዋቂ ከሆኑ  ድምጻዊያን ጋር በሐሳብ ያልተስማማባቸውን  ዘፈኖች አልሰራም ያለባቸው ተጨባጭ  ማስረጃዎች አሉ። የተከፈለውን ቀብድ መልሶ  ያውቃል።

  የኤልያስ ግጥሞች ብርሀን አመላካች ናቸው።  ከጨለማ መውጣትን ይዘምራሉ እንጂ በቀቢጸ  ተስፋ አያላዝኑም። በዘፈን ግጥሞቻችን ውስጥ  የተለመደው የውበት ገለጻ የለባቸውም።  የተቃራኒ ፆታ ፍላጎት አይቀሰቅሱም። የመልከ  ጥፉን ሴት ስሜት አይበድሉም። የመልከ  መልካሟን ሴት ባዶ ኩራት አያሞካሹም።  በተፈጥሮ የተሰጠ ነገርን ከማሞካሸት ይልቅ  በኑሮ ሂደት የመጣ ህጸጽን ይተቻሉ። ከፍ  ያሉትን ሐሳቦችን ቀለል ባለ ቋንቋ ይገልጻሉ።  ዋናው ዓላማቸው ሐሳቡን ማስተላለፍ እንጂ  ስነ-ጽሑፋዊ ደረጃው አይደለም። አብዛኛውን  ጊዜ አጫጭር ስንኞች ያዘወትራል። ተቀዳሚ  ትኩረቱ መልእክቱን ማስተላለፍ ላይ በመሆኑ  እያንዳንዷን ቃል እንድናደምጣት የሚያስችል  የቅንብር እና የዜማ አካሄዶችን ይጠቀማል።

  የሙሉ አልበማቸውን ግጥም እና ዜማ  ከሰራላቸው ድምጻዊያን ውስጥ የኢዮብ  መኮንን- “እንደ ቃል”፣ የጌቴ አንለይን-  “መልክሽ ካንቺ አይበልጥም”፣ የቤሪን “ከምን  ነጻ ልውጣ”፣ የኃይሌ ሩትስን “ቺጌ”፣ የልዑል  ኃይሉን “እሳቱ ሰዓት” በመውሰድ በምሳሌ  እንመልከት። በዚህ አጭር ምልከታ ውስጥ  የስንኞቹ መልእክት ላይ ትኩረት እናደርጋለን።

 ሐይማኖታዊ  የኤልያስ መልካን የዘፈን ግጥም ሥራዎች  በመልእክት ደረጃ ከፋፍለን ለመመልከት  ስንሞክር አንዱ ዘውግ የሚሆነው ሐይማኖታዊ  ይዘት ነው። ሁሉም ግጥሞቹ ሞራልን

የሚሰብኩ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮን  የሚደግፉ ቢሆኑም የኃይሌ ሩትስ “ያላለው  ላይሆን”፣ የኢዮብ መኮንን “እንዳጠፋሽ”፣  የቤሪ “ማዝመር እንዲህ መዝፈን እንዲያ”  እና “ከምን ነጻ ልውጣ” ለየት ባለ መልክ  ሊታዩ የሚገቡ ናቸው። ከፊሉ የሐይማኖቱን  አስተምህሮ ተቀብለው በፈጠሩት ታሪክ  ውስጥ መልእክት ለማኖር ጥረት ያደርጋሉ።  ገሚሱ ደግሞ አስተምህሮውን ትተው በግል  ፍልስፍናቸው ባመኑበት አቋም ይሞግታሉ። 

ያላለው ላይሆን

ሰው ዝም ይበል ባይሆን

ከጥንት ያልነበረ

ሰው ደፈረ ተመራመረ

ብሎ የሚጀምረው የኃይሌ ሩትስ ዘፈን። የሰው ዘርን አመጣጥ በተመለከተ ያሉ አስተሳሰቦችን አንስቷል። ከሐይማኖተኛ ወገን በመሆንም ያመነበትን ለማጋባት ይጥራል።

 ዝንጀሮ ዘር ነው ሰው ማንነቱ

ብሎ ራስ ንቆ ሰው ባንደበቱ

ሰው ከዘፍጥረቱ ካዳም ነው ውበቱ

ካለም ይቀራል ሰው

ሀዋ ነበረች ሰው

ሰው አርጎ እንደኔ በክብር ፈጥሮት

ወንድሜ ሳተ ያወቀ መስሎት

እያየ ሲገራ ፍጥረት በሰው ሥራ

ካላመነ ራሱ አይደምረኝ ከሱ

የዝግመተ ለውጥን አስተምህሮ የሚቃወመው ዘፈን መልእክቱ ሐይማኖታዊ ነው። የጥቅስ እና የፈጣሪ ስም አልገባበትም። የመጽሐፍ ቅዱሱ አዳም ከቁርአኗ ሀዋ ጋር ተጠቅሰዋል። ሁለቱም ሐይማኖቶች በዘፍጥረት ላይ ያላቸውን ቀኖና ተመሳሳይነት በመጠቀም መልእክቱን ለሁሉም ሊያጋባ ይጥራል።

 ስልጣኔ እያለ

ራሱን ያታለለ

አይበል ነን ከእንስሳ

እንበልጣለን ከዛ

“እንዳጠፋሽ” ወደሚለው የኢዮብ መኮንን ዘፈን ስናልፍ የሁለት በዳዮች ታሪክ እናገኛለን። በአምላካቸው ፊት ጥፋት የፈጸሙ ሁለት ሰዎች በዘፈኑ ውስጥ በገጸ ባህርይነት ተስለዋል። ወንድየው ተራኪያችን ነው። እነዚህ ወንድ እና ሴት ነውራቸውን ተያይተዋል። በደል ተጋርተዋል። ፈራጁ ግን ፍርዱን እኩል አልሰጠም። እሷ ላይ ፈረደ። ያልተፈረደበት ሰው የሷን ፍርድ ተመለከተ። እሱ አልተፈረደበትም። ለምን ሲል ጠየቀ

 ዘፈኑ እዚህ መስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመውን ገጸ ባህርይ ሐሳቦች ይዟል።

እንዳጠፋሽ አጥፍቻለሁ

እንደሸፈትሽ ሸፍቻለሁ

ያለጽድቄ ያለፍርድ ቆሜአለሁ

ያለ ጽድቅ ያለ ፍርድ

 መቆም ከባድ ነው። ሥራውን ያውቃልና በጽድቅ ጎዳና እንደማይጓዝ ደመ ነፍሱ ነግሮታል። ግን ፍርዱስ

ቸኩሎ ቅጣቱን ካንቺ የጀመረው

ሊታዘበኝ ነው ወይ የኔን ያሳደረው

ዋጋ ልክፈል ብሎ ካበዛው ቅጣቴን

ይደምርብኛል አንድ የዳኝነቴን

አብረን ካጠፋነው በላይ በተፈረደብሽ ባንቺ ላይ የምሰጠው ዳኝነት ሌላ ጥፋት ሆኖ ሊደመርብኝ ነው ይላል። ሙሉ ለሙሉ ሐይማኖታዊ መልእክት ቢሆንም ማንንም በማይጎረብጥ መልኩ ተሰናድቷል።

ማነው ጻድቅ ሰው ሁሉም ሰው ሞኚ

እራሱ ሳይሰርቅ ሌላ እሚዳኝ

ኤልያስ ግጥም የሰራላቸው ድምጻዊያን በሲዲው ሽፋን ላይ ሙሉ ግጥሙን አትመውታል። ቤሪ እና ልዑል ለዚህ ይጠቀሳሉ። የድርጊቱ ሰበብ መልእክቱ ሳይሸረፍ እንዲደርስ ለማድረግ ነው ብንል ያስኬደናል። አንዳንድ ሐሳቦቹንም ጽፎ አይጠግባቸውም እናም በሌላ ቅርጽ ይመለስባቸዋል። ከላይ የተመለከትነው የኢዮብ ዘፈን ላይ ያለው ሐሳብ በልዑል ኃይሉ አልበምም ይደገማል።

ባንቺ ስላቅ በጥፋቴ

ምንም አፍ የለኝም እስኪሽር ቅጣቴ

በኔ የሳቀች ጥርስ ትከደናለች

ይብላኝ እንጂ ላንቺ ነፍሴስ ጨክናለች

ይብላኝ እንጂ ላንቺ ነፍሴስ አምልጣለች

በቀጣይ የምንመለከታቸው ሁለት ዘፈኖች ቤሪ አልበም ውስጥ የተካቱ ናቸው። ነባሩን ሐሳብ ለመሞገት ተነስተዋል። በሀይማኖቱ ጥላ ስር ሆነው ልክ ያልመሰላቸውን ሊቃወሙ የተነሱ ናቸው። ይህንን ሐሳብ ኤልያስ መልካ በልዩ ልዩ ቃለ መጠይቆቹ ላይ ተናገሯቸዋል። በአደገበት የፕሮቴስታንት ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድም በጥሩ አልታየለትም። ሙዚቀኛ ዮናስ ጎርፌ “ቤት ያጣው ቤተኛ” ሲል መጽሐፍ አሰናድቶለታል። “ማዝመር እንዲህ መዝፈን እንዲያ”

 በፍቅር ሕግ አምላክ በንጹህ ቅን ጨዋታ

ፍጹም በዘፈን ድምጽ የለም ከልካይ ጌታ

ክፉ ግን ክልክል ነው እሱማ መቼ ጠፋን

በቀልድም በዜማ መዝሙር አሉትም ዘፈን

 የዘፈንን ሐጥያትነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተዋል። ክፋትን ብቻ ነው የተከለከልነው እንጂ ዘፈንን አይደለም ይላል። ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ዘፈን ከዚህ በፊት አላደመጥንም። ክፉ ነገር ከሆነ በቀልድም፣ በዜማም፣ በመዝሙርም፣ በዘፈንም ቅርጽ ቢመጣ ሐጥያት ነው። ጥሩ ነገር በዘፈን መምጣቱም ጥሩነቱን አያሳጣውም የሚለው ዋናው የዘፈኑ ጭብጥ ነው።

እልልታማ ንጹህ ሆታ

በረከት ነች ለሰው ልጅ ደስታ

እምቢልታ ነው ዘፈን መካሻ

የእንባ ካሳ ያዘን ማስረሻ

በፍቅር ሕግ አምላክ በንጹህ ቅን ጨዋታ

ፍጹም በዘፈን ድምጽ የለም ከልካይ ጌታ

መልክ

የበዛ ቁጥር ባላቸው የዘፈን ግጥሞች ውስጥ ተፈጥሯዊ ውበት ተደንቋል። ደምግባት፣ ወዘና፣ ቁመና፣ ዐይን፣ ጥርስ፣ በፍቅር ለመውደቅ ምክንያት ሆነው ቀርበዋል። ቁንጅና የፍቅር መግቢያ በር የሆነባቸው ዘፈኖች ብዙም ማሰብ ሳያስፈልግ፣ እጅግም ሳንቆፍር እናገኛለን።

                        ኤልያስ መልካ ጽፎአቸው ቤሪ፣ ጌቴ አንለይ እና ኢዮብ የዘፈኗቸው ዘፈኖች ግን ባልተሄደበት መንገድ የተጓዙ ናቸው። የቁንጅናን (የላይ ውበትን) የፍቅር መስፈርት ማድረግን አሽቀንጥረው ይጥላሉ። ለዚህ ምድብ ቀዳሚ ተጠቃሽ የኢዮብ መኮንን “ደብዝዘሽ” የሚለው ዘፈን ነው። በእውቀት የሚበልጧትን፣ በውበት የሚበልጧትን፣ ቀልዳቸው የሚያስቀውን፣… በልጣ በዝምታዋ ልቡን ያሸነፈችውን እንስት ጥያቄ የሚጠይቅ ገጸ ባህርይ ተስሎበታል።

                                 መልክን የሻረ

አንቺ ጋር ምን ተሻለ

ከሩቅ ሳትስቢ

ዐየሁ ልቤ ስትገቢ

ካንቺ በላይ ቆንጆ ሞልቶ

ያውቃል ልቤ ቀርቦም አይቶ

ግን በምን በለጥሻቸው

ቆንጆዎቹን አስናቅሻቸው

ዝምታሽ በለጣቸው

ደብዝዘሽ አጋለጥሻቸው

ስብሀት ገብረ እግዚአብሄር በአንድ ወቅት “ሁሏም ሴት ላይ ለወንድ ልጅ ውበት አስቀምጦለታል” ሲል ተናግሮ ነበር። ይህ ንግግር የመልከ ጥፉነትን መስፈርት የሚያፈርስ ነው። በኤልያስ ግጥም ውስጥም ተመሳሳይ ድምፅ ይሰማል።

 ጌቴ አንለይ ባቀነቀነው “መልክሽ ካንቺ አይበልጥም” የሚለው ዘፈን ላይ ያለችው ገጸ ባህርይ ደግሞ በኢዮብ ዘፈን ላይ ካለችው ትለያለች። እጅግ በጣም ውብ ናት። ይሁን እንጂ የአፍቃሪዋ መለኪያ ከመልክ በላይ ነው።

                     መች እተውሽ ነበር ዐይኔ እስኪያይሽ ዞሮ

ባይኖር እንኳን መልክሽ ውብ ባትሆኚም ኖሮ

ቢደምቅም ባይደምቅም ቢበርደው ቢሞቀው

ላይሽ ብቻ አይደለም ልቤን የደነቀው

ከላይ እዩኝ ባለች ባደባባይቷ

አንቺ አትመዘኝም በብልጭልጪቷ

ጥቁር ነጭም ቢሆን የጸጉርሽ ቀለሙ

መች እሱ ሆነና ለኔ ብርቅ ዓለሙ

አይደንቅሽም አንቺ ሆኖ አይሰለቸኝም

ጉዳዬ ውስጥሽ ነው ካንቺ አይበልጥብኝም

ምናልባትም ኤልያስ በህይወት በነበረበት

ወቅት የተለቀቀ የመጨረሻ አልበም የሆነው “እሳቱ ሰዓት” ተመሳሳይ ሐሳብ ተነስቶበታል። አውታር በሚሰኘው የኢንተርኔት ግብይት እና በሲዲ ለገበያ የቀረበው የልዑል ኃይሉ ዘፈን “አስቤው መጣሁ” ይሰኛል። ከስንኞቹ ጥቂት እንመልከት።

                            ስንቱ የሚያምር ባየ ቁጥር

ሁሉን አርጎ ቆጥሮ እንደፍቅር

ሮጦ ገብቶ አድሮ ኋላ

ተጠዳድፎ ወጣ ሻረ ማላ

ድምጻዊት ቤሪ “ከምን ነጻ ልውጣ” በሚል አልበሟ ላይ “መልኩስ ልቡ ነው” የሚል ዘፈን አላት። አሁንም የግጥም እና የዜማ ደራሲውን ጨምሮ ያቀናበረው ኤልያስ መልካ ነው።

ልቡን ሲያበራ- ውስጡን ሲያጠራ

ሰው ሁሌም ውብ ነው- ድንቁ ውብ ሥራ

ላይን ነው ሁሌም ሲፈጠር

ውብ ቢነጣ ቢጠቁር

ሁሉም የፈጣሪ እጅ ሥራ ነው። ቢነጣም ቢጠቁርም ውብ ነው። የሚል የአማኝ መልእክት አለው። በዚሁ ከምን ነጻ ልውጣ የተባለ አልበም ላይ “ህሊና” የሚል ርዕስ የተሰጠው ዘፈን ከላይ ያሉትን በመልክ እና ደምግባት ዙሪያ የተነሱ ሐሳቦች ከፍ አድርጎ ማሰሪያ ያበጀለት ይመስላል።

ማን ቀድሞ ዐይቶ

መልኩን አውቆ በልጦ

መርጦ መጣ

ጠቁሮ ወይ ነጣ

በሚል ጥያቄ የሚጀምረው የዘፈኑ ስንኝ፣ ሰውን በዘር ለመኮነን፣ በቀለም ለመፈረጅ የዳረገን ህሊናችንን አለመጠቀማችን ነው በሚል ድምዳሜ ያጠናቅቃል።

ህሊና ይህን ካላስተዋለ

ሰውን በዘር ኮናኝ ብዙ አለ

ህሊናን ጥሎ ከታለለ

የጠቢብ ዘር ነኝ ባይ ከንቱ አለ።

ፍቅር

ብዙዎቹ የኤሊያስ መልካ የፍቅር ግጥሞች ፍቅርን እንደ ማዋዣ ይጠቀሙበታል። በፍቅር ውስጥ ያሉት ሰዎች እንቅስቃሴ ዋነኛ ትኩረታቸው ነው። የእለት ተእለት እንቅስቃሴአቸው ውስጥ ያለውን እንከን መቅረፍ ወይም በጎ ነገርን ማጉላት ላይ ያተኩራሉ። “የፍቅር ዋጋ” የሚለው የቤሪ እና “በቃ በቃ” የሚለው የኢዮብ ዘፈኖች ግን ፍቅርን ራሱን ያብራራሉ። ፍቺ ይፈልጋሉ።

                              ልፈልገው ከዋለበት

ንጹህ ፍቅር ከሞላበት

መቼ ተሞኘ ብልህ ነው ፍቅር

ክብሩን አይጥልም ከውሸት መንደር

ከቅብዝብዝ ጋር መች ይረጋጋል

አይታለልም ሸንጋዩን ያውቃል

የተራበ ልብ ፍቅርን የጓጓ

ከእውነት ቤት ሄዶ የእውነት ያንኳኳ

ንጹህ ፍቅር ጨለማ ላይ በፈዘዘ

 ዐይን አይገኝም ብሎ ብርሃኑ ላይ ለመፈለግ ይታትራል። በቤሪ “የፍቅር ዋጋ” ላይም ተመሳሳይ ሐሳብ በተለየ መንገድ ተገልጾአል።

የከበረ የውዱን አፍቃሪ

ለሚወደው አፍቃሪ ነዋሪ

ወዶ ሲሰጥ ራሱን ነውና

የእጁን መአዛ የነፍሱን ቃና

ተስፋ

የኤልያስ ስንኞች እርጋታን የሚያላብሱ ሐሳቦች የተሸከሙ ናቸው። በቃላቱ ውበት ተወስደን መልእክቱን እንዳንዘነጋው ይጠነቀቃሉ። በጠጣር ቃላት ታጭቀው ትርጉም ፍለጋ እንድንባዝን አያደርጉም። ተስፋ ከሚያጭሩት መካከል ሁለቱን ተመልክተን እናብቃ! “ቀኑ መጣ” የዘፈኑ መጠሪያ ነው። በውጣ ውረድ ውስጥ የነበረች ገጸ ባህርይ ተስላበታለች። ጨርሳ ከችግሯ ባትላቀቅም ለመሆን የተቃረበ ተስፋ ላይ ናት። ደረሰ፣ መጣ፣ ልይዘው ነው፣… ትከላለች።                   ያንዱን ምዕራፍ መወጣጫው ቀኑ መጣ

የእቅፍ ነዶ መቆረጫው ቀኑ መጣ

የተከልናት ዘር ወይናችን ቀኗ መጣ

ቀልታ ተጠምቃ ጽዋችን ተራዋ መጣ

ኩርፊያው አልፎ የፍቅር መንገድ ተራው መጣ

ልዑል ኃይሉ በቅርብ ያወጣው የመጀመሪያ አልበሙ ውስጥ ከተካተቱት 13 ዘፈኖች ውስጥ አንዱ የሆነው “አውቀህ አትጨፍነው” የተስፋን ፍንጣቂ የሚያሳይ ነው። የትም ብትሆን ምንም ነገር ውስጥ ብትገባ እስከመጨረሻው ታገል፤ ራሱ ይጣልህ እንጂ ተሸንፈህ እንዳትወድቅለት የሚል መልእክት አለው። እነዚህን ስንኞች ኤልያስ በገሀዳዊ ሕይወቱ ኖሯቸዋል። ከጤናው በላይ ለስራው ያስብ ነበር። እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ሞትን ሳይፈራው ተጋፍጦታል። ስራውን እየሰራ በጸጋ ተቀብሎታል። የ18 አዳዲስ ሥራዎች ጅምር ስቱዲዮ ውስጥ መኖሩ ለዚህ ምስክር ነው።

                               በቃ አትበል ምሽት መጣ

ጥልቁ አይሞቅም ተነስ ፍጠን ውጣ

በቃ አሁን ና አምልጥ ጽና

ቆይ እንዳትል መስሎህ ገና

የፍቅሬን እና የስሜቴን እንዲህ ተነፈስኩ እንጂ ኤልያስ ይህ ብቻ አይደለም። ከዚህ በጠለቀ እና በሰፋ ሊታዩ የሚችሉ ዘልአለማዊ ሥራዎችን አበርክቷል። ነፍሱን በገነት ያኑረው ብለን እንሰናበትና አቅም እና ጊዜ ሲፈቅድ በሌላ ዕይታ ለመገናኘት ተስፋ እናድርግ። ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top