ጣዕሞት

የአክሊሉ ተመስገን የሥዕል ኤግዚቢሽን ለእይታ ቀረበ

አክሊሉ ተመስገንን የሥዕል ሥራዎች አክሊሉ ተመስገንን የሥዕል ሥራዎች የያዘ ኤግዚቢሽን ከመስከረም 23-30፣ 2012 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለእይታ ቀርቧል። በሠዓሊውና በጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል ትብብር የተዘጋጀው ይኸው ኤግዚቢሽን በርከት ያሉ የቀለም ቅብ ሥራዎችን ይዟል። አቶ ደመቀ ዘመነ፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስል፣ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የኢትዮጵያን ባህል የሚያሳዩና ገጽታዋን የሚገነቡ መሰል የፈጠራ ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ኤምባሲው እንደነዚህ አይነት ኤግዚቢሽኖችን ለሚያዘጋጁ ባለሙያዎች ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጨምረው ተናግረዋል።

 የጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል መሥራች የሆነችው አርቲስት ዓለምፀሃይ ወዳጆ በበኩሏ በስደት ዓለም ከኑሮ ፈተና ጋር እየተጋፈጡ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን ማበረታታት እንደሚገባ አሳስባለች። “ሕይወታችንና ማንነታችንን የሚያሳዩትን የአክሊሉ ተመስገን ሥዕሎች በመግዛት ለልጆቻችንና ለራሳችንም የደስታ ምንጭ ማድረግ” እንደሚቻል የገለጸችው ዓለምፀሃይ፣ ሠዓሊውንም “እንኳን ደስ አለህ” ብላለች። ሠዓሊ አክሊሉ ተመስገን በበኩሉ ለሥራው መቃናት አስተዋጽዎ ያደረጉ ግለሰቦችንና ተቋማትን አመስግኗል። ኤግዚቢሽኑ በተመልካቾች ከተጎበኘ በኋላ ደግሞ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል።

“ለመምቴ” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ
ተመረቀ

በክንፈ ባንቡ ተደርሶ የተዘጋጀው “ለመምቴ” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ መስከረም 29 ቀን 2019 ዓ.ም ፎልስ ቸርች፣ ቨርጂኒያ፣ በሚገኘው ብላክ ሮዝ ላውንጅ ተመርቋል። በሸገር ኤቨንት እና ፊልም ፕሮዳክሽን አቅራቢነት በአርትስ ቴሌቪዥን እንደሚተላለፍ የተገለጸው ይኸው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በአሜሪካ የተቀረጸ ሲሆን ሃገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑ በምረቃው ሥነሥርዓት ተጠቁሟል። “ለመምቴ” የሚለው ቃል ትርጉምም ውኃ ላይ አንድ ጠብታ ሲያርፍ የሚፈጠረው ክበብ (ክብ ነገር) መሆኑ ተገልጿል። በጎ ነገር ውኃው ውስጥ ሲገባ በክቦቹ አማካይነት በጎነቱ ለሁሉም እንደሚዳረሰው ሁሉ ክፉ ነገርም እንዲሁ የመዳረስ እድል እንዳለው አመላካች መሆኑ ተነግሯል። በድራማው የምረቃ ሥነሥርዓት በክብር እንግድነት የተገኘችው አርቲስት ዓለምፀሃይ ወዳጆ የባለሙያዎቹን ጥረትና የትብብር መንፈስ አድንቃ በዚሁ የአንድነትና የፍቅር ስሜት ጠንክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብላለች። ከልብ የተደከመበት አንድ የጥበብ ሥራ ዘመን ተሻጋሪ የመሆን እድል እንዳለውና ባለሙያዎቹም ከዛሬ ይልቅ ነገ የሚደሰቱበትና የሚኮሩበት እንደሚሆን ምሳሌ ጠቅሳ አስረድታለች። የፊልሙ ደራሲና አዘጋጅ ክንፈ ባንቡ “ወደው አይሰርቁ”፣ “ብላቴና” እና “ፍሬ” የተሰኙ ሥራዎቹን ከዚህ ቀደምም ለተመልካች አቅርቧል። የሸገር ፊልም ፕሮዳክሽን ማኔጀር ዮሐንስ ጌታቸውና ዳይሬክተሩ ክንፈ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በትጋትና በፍቅር አብረዋቸው የሠሩ ተዋንያንን፣ የካሜራና የቴክኒክ ባለሙያዎችን፣ ድጋፍ ያደረጉላቸውን ግለሰቦችና ድርጅቶች፣ ወዘተ አመስግነዋል። ሞገስ ቸኮል፣ መልካም ይደግ፣ ሜሮን ተክሌ ደስታ፣ ሳራ በፍቃዱ፣ ኤልሳቤጥ መኮንን፣ ታዬ አዳነና ሌሎች ተዋንያን ተሳትፈውበታል። በስተመጨረሻም ተዋንያኑና የቴክኒክ ባለሙያዎቹ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከእለቷ የክብር እንግዳ ተቀብለዋል። በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ በርከት ያሉ ከያንያንና የጥበቡ አድናቂዎች ተገኝተዋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top