ጥበብ በታሪክ ገፅ

ዘመን አይሽሬው ብዕረኛ ሀዲስ ዓለማየሁ

ዘመን አይሽሬው ብዕረኛ

ሀዲስ ዓለማየሁ

በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ወደር የማይገኝለት የልቦለድ መጽሐፍ «ፍቅር እስከ መቃብር» ስለመሆኑ ይነገራል። የዚህ መጽሀፍ ደራሲ ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ደግሞ ከልቦለድ ደራሲነታቸው ባሻገር አንጋፋ ዲፕሎማትና አርበኛም ናቸው። በጎጃም ደብረማርቆስ የተወለዱት ደራሲ ሀዲስ ወላጅ አባታቸው የኔታ ዓለማየሁ ሰለሞን ሲባሉ እናታቸው ደግሞ ደስታ ዓለሙ ናቸው። የሀዲስ ዓለማየሁ አያት የዜማ መምህር ስለነበሩ ሀዲስም በ6 አመታቸው ፊደል መቁጠር ጀምረው ነበር። ጥቅምት 7፣ 2012 ዓ.ም. የተወለዱበት 110ኛ ዓመት መከበሩ የሚታወስ ነው።

 ሀዲስ ዓለማየሁ በ16 ዓመታቸው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን ከመጀመሪያዎቹ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች አንዱ ናቸው። ከተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ጎጃም ዳንግላ በማቅናት በመምህርነት አገልግለዋል። በተጨማሪም በዛው በጎጃም በጉምሩክ ባለሙያነት መስራታቸው ይነገራል። ጣሊያን ሀገራችንን በወረረ ጊዜ የ26 አመት ወጣት የነበሩት ሀዲስ አለማየሁ በግዞት ወደ ጣሊያን ለመሄድ የቻሉ ሰው ናቸው።

በ1929 ዓ.ም. በታህሳስ መጨረሻ ላይ ጌራ ላይ ከተደረገው ትልቅ ጦርነት በኋላ ጅማንና ከፋን በሚያዋስነው ጎጀብ ወንዝ ላይ ተከበው ተይዘው ወዲያዉኑ ወደ ጣሊያን አገር ተግዘው በ1936 ዓ.ም. በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጣሊያንን ድል አድርገው በያዙት በእንግሊዝና በካናዳ ወታደሮች እስኪፈቱ ድረስ ፖንዛና ሊፓሪ በሚባሉ ደሴቶች በኋላም በላይቤሪያ ዉስጥ ሎንግቦኮ በሚባል ተራራማ ገጠር ከሰባት ዓመት በላይ ታስረዋል።

 በ1936 ዓ.ም. ጣሊያን ተመልሰው በጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት፣ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ፣ ተቀማጭነታቸው እንግሊዝ አገር ሆኖ የእንግሊዝና የሆላንድ አምባሳደር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ አምባሳደር፣ ከዚያም መልስ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የሕግ መወሰኛ እና የብሔራዊ ሸንጎ አባል፣ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስትር ሆነው በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት አገልግለዋል።

 ሀዲስ አለማየሁ በድርሰት ዓለም የመጀመርያ የፈጠራ ድርሰታቸው ‹‹ያበሻና የወደኃላ ጋብቻ›› የተሰኘ ተውኔት ሲሆን በወቅቱ የተመልካችን ልብ የሳበ ነበር።

ደራሲ ሀዲስ ከግዞት ከተመለሱ በኋላ የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም ተረት ተረት፣ ፍቅር እስከ መቃብር፣ ወንጀለኛው ዳኛ፣ የልምዣት፣ ትዝታ የተባሉ ድርሰቶቻቸውን ለአንባቢ አቅርበዋል።

 ‹‹ማዕቀብ›› በተሰኘ የደራሲ እንዳለጌታ ከበደ መጽሐፍ እንደተወሳው ደራሲ ሐዲስ ደርግ ወደ ስልጣን በመጣ ማግሥት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር እንዲሆኑ ከታጩ ግለሰቦች አንዱ ነበሩ። እርሳቸው ግን ጥያቄዉን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

 ደራሲ ሀዲስ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተበረከተላቸው ሲሆን በ94 ዓመታቸው ኅዳር 26፣1996 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ኡራኤል ፕላዛ ሆቴል ገባ ብሎ የሚገኘው የሀዲስ ዓለማየሁ መኖርያ ቤት አሁን አቶ ሰኢድ ካሴ በሚባሉ ባለሐብት ባለቤትነት ይገኛል።

 ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ወደ ድርሰቱ አለም የገቡት በ1929 ሲሆን በዛን ወቅትም የጻፉት ቴአትር ሲሆን ርእሱም ‹‹የሀበሻና የወደኋላ ጋብቻ ›› የተባለ ተውኔት ነው።ሀዲስ አለማየሁ በ1948 ተረት ተረት የመሰረት የተባለውን መጽሀፍ የደረሱ ሲሆን ከ10 አመት በኋላ በ1958 የጻፉት ፍቅር እስከ መቃብር በጣም ታዋቂ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በ1974 በወጋየሁ ንጋቱ ለመተረክ የቻለው ይህ ልቦለድ ድርሰት ለ54 አመታት በተወዳጅነቱ እንደቀጠለ ነው። ፍቅር እስከ መቃብር እስካሬ 500 ሺህ ቅጂ እንደታተመ ይገመታል። የመጀመሪያው እትም በ1958 ሲወጣ ዋጋው 2ብር ከ45ሳንቲም ነበር። በአሁኑ ሰአት ይህ መጽሀፍ በ91 ብር እንደሚሸጥ ታውቋል።

 በእንግሊዝኛ የተተረጎመው የታላቁ ደራሲ የሀዲስ አለማየሁ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› አብዛኞችን በፍቅር የጣለ ልብ ወለድ መጽሐፍ ነው። ከዚያ በዘለለ በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጽሑፍ ዲፓርትመንት ውስጥ ላለፉት 50 ዓመታት የጥናትና ምርምር ጽሁፎች ሲሰሩበት የኖረ መጽሐፍ ነው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፋቸውን ሰርተውበታል፡ የሥነ-ጽሑፍ ተመራማሪዎች ፍቅር እስከ መቃብርን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተንተርሰው ጥናት ሠርተዋል።

 በአሁኑ ሰአት የአንትሮፖሎጂ ባለሙያ የሆነው አቶ ደስታ ሎሬንሶ የሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር አዲስ እይታ ያመላከተ ስራ መሆኑን ያምንበታል። በተለይ በ1940ዎቹ የነበረው የፊውዳል ስርአት ላይ የሰላ ሂስ በመሰንዘር መጽሀፉ ሚናውን ተወጥቷል፡ ይላል።

 ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ከ1949-1953 በአሜሪካ አምባሳደር ሆነውም አገልግለዋል። «አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ በዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ በቆዩበት ወቅት፤ የዓለም አቀፍ ሕግ« ኢንተርናሽናል ህግ» ተምረዋል። ነገር ግን አልጨረሱትም። ምክንያቱም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመቀየራቸዉ ነው። እርሳቸዉ እንደሚናገሩት ወረቀቱን ማለት ሰርተፊኬቱን ነዉ እንጂ ያላገኙት ትምህርቱን ተምረዉ ጨርሰውታል። ይህ ማለት በድሮ ጊዜ በኢትዮጵያ ዉስጥ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እንዲሁም የቅኔ ትምህርትን የተማረ ሰዉ አሜሪካ ዉስጥ ሄዶ ዓለም አቀፍ ሕግ ትምህርትን መከታተል መቻሉ የሚያሳየዉ፤ የጥንቱ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ተወዳዳሪ እንደነበር ነዉ። ሀዲስ አለማየሁ ከአሜሪካዉ ተልእኮዋቸዉ ተለዉጠዉ ወደ ሃገራቸዉ ከተመለሱ በኋላ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነዉ አገልግለዋል። እንደገናም በተመድ የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪ ሆነዉ አገራቸዉን አገልግለዋል። እዚያ በነበሩበት ወቅት በተለይም ኒዮርክ ሳሉ ይህ አሁን አዲስ አበባ ዉስጥ የሚገኘዉን «ECA» ማለትም «United Nations Economic Commission for Africa» የተባለዉን አዳራሽ እንዲሰራ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ዋና ሰው ናቸው።

ሀዲስ እንደ ዲፕሎማት

ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በተባበሩት መንግስታት ትልቁ አዳራሽ አንድ ትልቅ ቁምነገር ትተው ስለማለፋቸው ይነገራል። ይህም የኒኩሊየር ጉዳይ ነበር። ዛሬ የአለማችን ትልቁ ችግር የኒኩሊየር ስጋት መሆኑ ይታወቃል። ያኔ በ1950ዎቹ ይህ የኒኩሊየር መሳሪያ እንዳይስፋፋ እገዳ ተጥሎ ነበር። አንዳንድ ሀገሮች ለአለም ስጋት ይፈጥራሉ በሚል ኒኩሊየር እንዳይሰሩ ትላልቆቹ መንግስታት ሲጫኑ ነበር። የተባበሩት መንግስታት ሴኩሪቲ ካውንስል በዚህ ጉዳይ ብዙ ስብሰባ ተቀምጧል። ጭንቀቱም ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም፤፡ ህጉ ደግሞ መከበር እንዳለበትም የታመነ ነበር። አንዳንድ ሀገሮች ደግሞ ህጉ ሳይፈቅድላቸው ኒኩሊየር በድብቅ ከመስራት ወደ ኋላ አላሉም። ነገር ግን ኒኩሊየር ያልሰሩት እስኪሰሩ በይፋ ህጉን ሲቃወሙ አይታዩም። በ1950 ገና ከመጀመሪያው የኒኩሊየር የኬሚካል ጦር መሳሪያ የሚያግድ ህግ እንዲወጣ በተ.መ.ድ ላይ መጀመሪያ ሀሳብ ያቀረበችው ኢትዮጵያ ነበረች።

በ1950 ሀዲስ አለማየሁ በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ ሳሉ ሀሳቡን በደንብ አርቅቀው አቀረቡ። አለም የኒኩሊየር ቦንብን እንዳይሰራና እንዳይጠቀም መታገድ አለበት ብለው የዲክላሬሽን ፅሁፍ አቅርበው ውይይት እንዲካሄድ ጠየቁ። መሳሪያዎቹን የፈበረኩት እነ አሜሪካ እንግሊዝና ፈረንሳይ ያኔ ራሳቸው የጦር መሳሪያ የበለጠ በመገንባት ላይ ስለነበሩ በአቶ ሀዲስ ሀሳብ ተደናገጡ። ጥያቄው አግባብ አይደለም በማለትም ተቃወሙ። አቶ ሀዲስ ሀሳባቸውን እንዲያነሱ ተጠየቁ። ሀዲስም እምቢ አሉ። ትላልቆቹ መንግስታት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ሀሳቡን ውድቅ ማድረግ ቢችሉም እንኳን ጉዳዩ ለውይይት እንዲቀርብ አልፈለጉም ። ሀዲስ አለማየሁም በሀሳባቸው ጸኑ። ሀዲስ አለማየሁ ይህ የኒኩሊየር ሀይል ግንባታን የሚያግድ ድንጋጌ እንዲወጣ የፈለጉት ኢጣሊያ በመርዝ ጋዝ በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰችውን ጥፋት በአይናቸው ስላዩ ነበር።

አቶ ሀዲስ ብዙ ጓደኞቻቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲሞቱ ስለተመለከቱ ያስከፊነቱን መጠን ዋቢ አድርገው ነበር። የሀዲስ ሀሳባቸውን አላነሳም ማለት ለይፋ ክርክር የማይመች ስለሆነ ከትላልቆቹ መንግስታት ጉዳዩ ወደ አዲስአበባ ለንጉሰ-ነገስቱ ተነግሮ ሀዲስ ነገሩን እንዲተውት ትእዛዝ ተላለፈላቸው። ደራሲ ሀዲስም ያቀረቡትን ሀሳብ አልለውጥም ሆኖም ግን በጥያቄው አልገፋበትምና በሪኮርድ ፋይል ሁኖ ይቀመጥልኝ በማለታቸው ሀሳቡ ፋይል ተደርጎ ተቀመጠ።

ሀዲስ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ደርግ በ1966 በልጅ እንዳልካቸው ምትክ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ያጨው እውቁን ደራሲ አቶ ሀዲስ አለማየሁን እንደነበር ሌተናል ኮሎኔል ፍስሀ ደስታ ‹‹ አብዮቱና ትዝታዬ›› በተባለው መጽሀፋቸው ገልጸዋል። አቶ ሀዲስ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ መታጨታቸውን ጀነራል አማን እንዲነግሯቸው ተላኩ። ጀነራል አማን ግን አቶ ሀዲስን ጠይቀው ፈቃደኛ እንዳልሆኑ መግለጻቸውን ለደርግ አስረዱ። ደራሲ ሀዲስ ሹመቱን አልቀበልም ያሉበትን ምክንያት ለደርግ አልተናገሩም።

ፍቅረስላሴ ወግደረስ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ የሀዲስ አለማየሁ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ፈቃደኛ አለመሆን አሳዘነን ይላሉ። አቶ ሀዲስ ምናልባት የጤና ችግር ይኖርባቸው ይሆን? የእኛን አላማ አይደግፍ ይሆን? ሲሉ እነ ፍቅረስላሴ ሀሳብ ውስጥ ገቡ፡ ምናልባት ልጅ እንዳለካቸው ና ሌሎች ጓደኞቻቸው በመታሰራቸው ተቀይመው ይሆን? ከዕኛ ጋር ተግባብቶ መስራት አይቻልም የሚል ግምት ወስደው ይሆን እያሉ ደርጎች እርስ በእርስ ሲንሾካሾኩ አንዱ የደርግ አባል እኛ አምነናቸው እንዲረዱን ስንጠይቃቸው ፈቃደኛ ካልሆኑ ሌላ ሰው እንፈልግ አለ።

♠♠♠

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እዝራ እጅጉሙላት ለ20 አመት በጋዜጠኝነት ያገለገለ ሲሆን የ20 ሰዎችን ግለ- ታሪክ በዲቪዲና በኦድዮ ሲቲ ያሳተመ ነው። 3 መጽሀፎችንም ለህትመት ያበቃ ነው። በዚህ 2 ወር ውስጥ ተጨማሪ 4 ታሪኮች በዲቪዲና በኦድዮ ሲዲ እንደሚያሳትም ይጠበቃል። እዝራ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን የተሰኘ የራሱን ድርጅት የመሰረተ ሲሆን በዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ህይወትና ስራ ላይ ምርምሮችን ያካሂዳል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top