አድባራተ ጥበብ

ማን ምን አለ?

ማን ምን አለ?

ታላቁ ባለሙያ / እዝራ እጅጉ (በሙዚቃና ኪነጥበባት ኮሌጅ የኤልያስ መልካ መምህር)

ጥበብን ለተደራሹ ሊደርስ በሚችል የቋንቋ ጥበብ (ድምፅን ሙዚቃን) በመጠቀም ሲጠበብ የኖረን ታላቅ፤ ግን ደግሞ በእድሜ ገና ወጣት የነበረን ይህች ሀገር ያበቀለችው ታላቅ ባለሙያን የመጨረሻ ስንብት ላይ ንግግር ማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ነው።

ኤልያስ መልካ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ካፈራቸው ምርጥ የት/ቤቱ ፍሬዎች አንዱ ሲሆን ከት/ቤቱ ከተመረቀ በኋላ በሀገሪቱ በጊዜው በነበሩ የሙዚቃ ቡድኖች ውስጥ በመዲና፣ በዜማ ላስታስ፣ በአፍሮ ሳውንድ ሌሎችም ቡድኖች ውስጥ በሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነትና በሙዚቃ አቀናባሪነት ድንቅ የሆነ የሙያ ችሎታውን አበርክቷል።

በሙዚቃ ጥበብ ድምፅን በተገቢው ሁኔታ መጠቀም እነዚህንም የድምፅ አሰካኮች በጥበብና በእውቀት መደርደር (ማቀናበር) የኤልያስ ምርጥና ድንቅ ችሎታው ነበር። ለዚህ ደግሞ ኤልያስ በተለያየ ጊዜ የሰራቸው ስራዎች በምስክርነት የሚቆሙ ናቸው።

በሙዚቃ የቅንብር ስራ በተለይ በኮመርሻል ሙዚቃ ኤልያስ ይዞት ብቅ ያለው አዲስ እይታና የቅንብር ቴክኒክ በሙያው የምር ፈር ቀዳጅ ሀሳብ ነው።

ኤልያስ ምርጥ ችሎታው በየጊዜው እራሱን በአዳዲስ ሀሳቦች የሚያጎለብትና ይሄንንም ሀሳብ በጥበብ ሙያው ሲጠቀምበት የነበረ መሆኑ ነው።

ጥበብን በድምፅ ከሸኖ አስውቦ ሀሳቡን በሚፈልገው መልኩ በቀላሉ አድማጩ እንዲረዳው ሙያው የሙዚቃ ጥበብን የተጠቀመ ድንቅ ባለሙያ ኤልያስ መልካ ነው። …ብሔራዊ ቲያትር

የትውልዱን ክስ ያሰረዘ ባለሙያ ተዋናይ ግሩም ዘነበ

 አንዱ “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወደቀ አፈር በላ ብሎ ሊወቅስህ ሲነሳ… የኤልያስ መልካን ስም ጠርተህ የትውልድህን ክስ ታሰርዝበታለህ…. የእኔን ትውልድ ክሶች ካጣፉልን ባለሙያዎች መካከል ኤልያስ መልካ አንዱ ነው”

እኔ የማውቀው ወንድሜ ኤልያስ መልካ ሔኖክ (መሐሪ ብራዘርስ)

 እኔ ኤልዬን የማውቀው ቀደም ሲል ቤተክርስትያን ውስጥ ሆነን፣ እኔም ወንድሞቼም፣ እሱ፣ ዮሀንስ ጦና፣ ቢንያም በድሩ፣ ዳዊት ጥላሁን፣ ዳንኤል ክንደያ፣… አብረው የመሰረቱትን ጽዮን የቤተክርስትያን ባንድ አልበም እየሰማን በዝና የሙዚቃው አድናቂ ሆነን ነበር። ከዛ በኋላ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ትውውቃችን ጀመረ። ከያሬድ ከወጣን በኋላ የመቅረዝ የመዝሙር ኮንሰርቶች፣ በሸራተን፣ በብሄራዊ ቴአትር፣… በነበረን አስደሳች የመዝሙር ኮንሰርት ግዜያት ነበር። ህይወቱ እስካለፈበት ግዜ ደግሞ ወንድሜ፣ መካሪዬ፣ ሙዚቃዬን አራሚ፣ ወዳጅ፣ መንፈሳዊ አመላካች፣ አንቂዬ፣… ነበር። ኤልያስ ብዙዎች እንደሚያስቡት ትልቅ የሙዚቃ ሰው ብቻ አልነበረም። ኤልያስ የህይወት፣ የእውነት፣… ሰው ነበር። ኤልያስ ስቱድዮ ተገብቶ ሙዚቃ ተሰርቶ ብቻ አይወጣም። ታላቁን ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ሰምቶ፣ አጥንቶ፣… ነው የሚወጣው። እኔ እስከማውቀው ኤልያስ ስቱድዮ ሙዚቀኛ ብቻ ሆነው ገብተው ሰው ሆነው የወጡ ብዙ ወንድም እህቶች አሉ ምስክር ነኝ። ኤልያስ በስሙ፣ በችሎታው፣ በእውቀቱ፣… ብዙ መጠቀም ይችል ነበር፤ ግን እሱ ጉዳዩ ይህ አልነበረም። ለሱ ቁምነገር ሰውን ሰው ማድረግ፣ የሚወደውን የእግዚአብሔር ቃል ለሰው ማካፈል፣ እውነትን መግለጥ ሰውን ማዳን ነው።

♣♣ እኔ የማውቀው ባለበገናው ኤልያስ መልካ

 ኤልያስ በሙዚቃ ስላለው ብቃት ብዙ ተብሏል፤ እኔ ስለሱ ትንሽ ልጨምር። በምሰራው ሙዚቃ አስተያየት፣ እርማት፣ ስፈልግ የማቀናው ወደ ኤሊ ነው። የማልረሳው ግን በአንድ ምሽት ከኤሊ ጋር የኔን ሙዚቃ ለመስማትና የሚሰጠኝን ሀሳቦች ለመክተብ ደብተሬንና ሙዚቃዬን ይዤ ሄድኩ። ምሽቱን ሁሉ በእያንዳንዱ ሙዚቃዬ ግጥም ዜማ ቅንብር ዙርያ ከ20 በላይ ሥራዎች ዝርዝር ሀሳብ ካስረዳኝ በኋላ ጨርሰናል ብዬ ለመሄድ ስነሳ ‹‹ቆይ እንጂ አንዴ ከላይ እንድገማቸው›› ብሎ ሌላ 2 ሰዓት ያደርነው ቀን አይረሳኝም። ከኔ በላይ ለኔ ተጨንቆ የሰጠኝ ግዜው፣ አቅሙ፣ መሰጠቱ፣ የሰዋው እንቅልፍ፣… ይሄንን ደግሞ ለብዙዎች ሲያደርገው ማሰብ፣ ማየት፣ ከግምት በላይ ነው።

ኤልያስ ትህትናው ወደር የለውም። እንደ እርሱ ዝናና ክብር መጠን ትህትናው ያስደነግጣል። በዛው ልክ ደግሞ ፈር ለሚለቅ ጋጠ-ወጥ ፊት ለፊት የሚገባውንና የሚያስፈልገውን ከመናገር ፈራ ተባ ብሎ አያውቅም። ለምሳሌ የዘመናችን ምሁራንና ሳይንቲስቶች ኢትዮጵያን የዝንጀሮ መገኛ መሆኗን እንደ ትልቅ ቁምነገር እየተሯሯጡ ሲለፍፉ ብቸኛው ነብይ እውነቱን በድፍረት የገለጠ ቤተክርስትያን ተብየዎቹ የዝንጀሮ አጥንት ለሀገር ሰላም ያመጣል ብለው እሺ ይሁን ብለው ሲስማሙ ኤልያስ ብቻውን የጮኸ: ሰው በአምላክ አምሳል የተፈጠረ ነው ያለ አርበኛ ነው። ለኤልያስ ሙዚቃ ክቡር ነች አላማዋም ዘልአለማዊ መልእክትን ማስተላለፍያ ነች።

♣♣ ለእኛ ለምናውቀው

 ኤልያስ ግሩም ሰው ነበር ትዳር ሳይኖረው የወዳጆቹን ትዳር አቅንቶአል እሱ ግድ ሳይለው ብዙዎች ሀብታም እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል ብዙዎቻችን ደንዝዘን የሙዚቃ መብታችንን ማንም ሲቀልድበት መፍትሄ ግራ በገባን ሰአት ስብስቦ ያነቃን አደራጅቶ ታታሪ ያረገን መብትና ግዴታችንን እንድናውቅ ያስተማረን መሪያችን ነው። ኤልያስ ታሪኩን ጽፏል ከሁሉም በላይ ባመነው አምላኩን አገልግሏል ሌላው ሁሉ አላፊ ነው።

♣♣ ለግብዞች ለፈሪሳውያንና ለመሳሰሉት

 በእናንተ የጠበበ ጭንቅላት ምክንያት ለዘመናት ሰው እንደገደለ ተሰደበ፣ ተብጠለጠለ። በእናንተ የጠበበ አይምሮ ምክንያት ያልሆነውን እንደሆነ ስእል ሳላችሁበት። ይሄንን ለእናንተ እያፈርኩ ነው የምጽፈው። ኤልያስ እናንተ እንደምታስቡት አለማዊ አለመሆኑን ደግመን ደጋግመን እናስተምራችኋለን። ለናንተ ክርስትያን ማለት እሁድ እሁድ ክብ ሰርቶ የሚንጫጫ ብቻ አይደለም። የሚያጨስ፣ የሚቅም፣ የሚጠጣ፣… ሁሉ በእናንተ ሚዛን ወደ ሲኦል ነው የሚወርደው። እሱን ኤልያስና አምላኩ ይምከሩበት። እኔንም እናንተንም አይመለከትም!

ግብዞች ሆይ መጀመርያ የራሳችሁን ኮተት አጽዱ። ኤልያስ ወደ አምላኩ እቅፍ እንደገባ አትጠራጠሩ። ይልቅ የራሳችሁን ዞር በሉን አስተውሉ። ኤልያስን ለመተቸት የሞራል ብቃቱ የላችሁም። ዓለም እንዲህና እንዲያ አደረገችው ለማለት ከመቸኮል መጀመርያ በእግዚአብሔር ስም የምታጧጡፉትን ከፍተኛ ንግድና ገበያ ገምግሙ። እንደ ጋሽ ንጉሴ ቡልቻ ካሉ የሰከኑ፣ የተረጋጉ፣ እግዚአብሔርን የእውነት ከሚያውቁ አፋቸው ሳይሆን ህይወታቸው ወንጌልን ከሚሰብክ አባቶች ቁጭ በሉና ተማሩ። ኤልያስ ሰው ነበር። እንደ እኔና እንደ እናንተ ይሳሳታል። ግን ንስሀ ይገባል። ክርስትያን ነዋ! ለሀገሩ ይጸልያል፣ ለህዝቡ ይጸልያል፣ ወንድሞቹን ይወዳል፣ ይቆጣል፣ ይመክራል፣ ይገስጻል፣… የኤልያስ ጥፋት ራሱን መጥላቱ ነው። የኤሊ ጥፋት ብልጣ ብልጥ አለመሆኑ ነው። የኤልዬ ጥፋት የዋህነቱ ነው። የኤልያስ ጥፋት ክፉ መሰሪ አለመሆኑ ነው። ጥፉት ከተባለ… ውሀ ሳታጠጡት፣ ሳትጸልዩለት፣ ሳትወዱት፣ ዳር ቆማችሁ ማብጠልጠል ነውር ነው። እሱ ሞቶ እንኳን የበለጣችሁ ብዙ ባለኮንፈረንሶችና ባለበራሪ ነብያት ባይገርማችሁ የቀብሩ ስንብት ፕሮግራም የወንጌል መድረክ ነበር። ለማንኛውም የኛ ህይወታችን ነው የሚዘምረው! እንደ ኤልያስ መልካ! ያገናኘን ደግሞ ሙዚቃ እንዳይመስላችሁ እየሱስ ነው!

ኤልያስ ተጠራ ተስፋዬ ማሞ መስከረም 25/2012

በበገናው አውታር በጅማት ወጥሮ

ዜማ እያፈለቀ ድምፅን አሰባጥሮ

ከባዶ አምድ ዘግኖ በአውድማ እየዘራ

ሲይፈራ የኖረ የሙዚቃ አዝመራ

በጭረት ምልክት በቅናት ከፍታ

ታትሞ የኖረ ትኁት ምሉዕ ሆኖ በድፋት ዝቅታ

በዕዝልና አራራይ መዋስዕት ዝማሬ

ከያሬድ ተቀድቶ ተዘርቶ ባ’ገሬ

ድርሻውን ያነሳ ዘመኑን የዋጀ

በእንቅልፍ እልባ ህይወት ለጥበብ የባጄ

የልጅነት መልኩን ለሙያው ገብሮ

አገሩን ያወዛ እሱ ከስቶ ጠቁሮ

ከእድሜው እጥፍ ልቆ አዝምሮ ያፈራ

የእሱን ስም ደብቆ እልፎችን ያስጠራ

ገና በማለዳው ዜማውን ጨርሶ ኤልያስ ተጠራ::

ይሂድ አትከልክሉት በእንባ ጎርፍ አጥራችሁ

ታልቦ ከጨረሰ ቢኖር ለምናችሁ!!

በጭለማ ወደ ቤት ተመልሰናል ሰርፀ ፍሬስብሀት

“ከባዷን ሰዓት እንደምንም አለፍናት። በብሔራዊ ቴአትር ኮከባችንን ወደ ሰማይ ሸኝተን፣ በጭለማ ወደ ቤት ተመልሰናል። ከጥንቱም የኮከብ መኖሪያው ሰማይ ነው። ሳይገባን አብሮን የቆየው ጻድቅ፣ በክብር ሊያሳርፈው ወደጠራው አባቱ ሔዷል። ሙሽራችን ኤልያስ በሕመም የተዳከመውን ሥጋውን ብቻ አልቅሰን እንድንቀብረው ትቶልን፣ የነፍሱን የደስታ ሙሽርነት ሊሠርግ፣ በአምላኩ ፊት ለዘለዓለም ሊቆም ትቶን ሔዷል። ማኅሌታይ ነበረና ወደ ሰማያዊው የመላእክት ማኅሌት አርጓል። ማኅሌት በምድር የምትጠናቀቅ ጥበብ አለመኾኗ ደስ ይላል።

 ዛሬ ገና በሞት ጥሪ ቀናሁ። ዛሬ ከዚህ ደግ ሰው ጋር አብሮ መጠራትን ተመኘሁ። ግን ሥራውን የጨረሰ እና ምንም ያልሠራ፣ ደግ ሰው እና ኃጢአተኛ ሰው አብረው ሊሔዱ ስለማይችሉ፣ ለምድሪቱ መከራ እኔ ቆይቼያለሁ። “ወትሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ” መጓዙ አይቀርምና! ኤልያስ በንፅሕና ባሸነፋት ዓለም እየተፈተንን እንቆያለን። ይኸው ነው። ሕይወት እንዲህ ነቻ!

ለሙዚቃ የመነነው ኤሊያስ! መአረግ ጌታቸው

 በዓሉ ግርማ ከሀዲ ደራሲ መሆኑን የነገረኝ የቀድሞ መምህሬ ቴዎድሮስ ገብሬ ነበር። “ከአድማስ ባሻገርን” ካነበብኩ በኋላ እኔም የእሱ ጭፍራ ሆንኩኝ። ታላቁን ደራሲ በክህደት ወነጀልኩኝ። ተስፋ ያጣውን አበራ ወርቁ ለምን ሲል በልቦለዱ መቋጫ ላይ በጉልበት ብሩሽ አስጨብጦ ከብርሃን አገናኘው አልኩኝ። ፍርሃቱን እረገምኩኝ። እርግማኔ ግን በጊዜ ሂደት ተረታ። ከበዓሉ በላይ ከሀዲ ከሆነ የጥበብ ሰው ጋር ተዋወኩ።

 ምናኔው ያስፈራል። ከዓለም ርቆ መኖሩ ያስደነግጣል። አብነት ተወልዶ አዲስ አበባን ዘንግቷታል። ዳርማርን ረስቶታል። ልደታ ሰፈርን ይናፈቀው ይዟል። ምን ጉድ ነው? አልኩ። ከተማ እየኖሩ መመነን እንደሚቻል ከእሱ ተማርኩ። የጥበብ ምንኩስናው አንቱ ቢያስብለውም እኔ ግን ኤሉ ለማለት አላንገራገርኩም። ኤሊያስ መልካ ከሃዲ የጥበብ ሰው ነበር። ክህደቱ ፅልመትን ነው። ሽሽቱ ከጨለማ ነው። ስራዎቹ ላይ የምታዘበውን እውነት አንድ ቀን በድፍረት ጠየኩት። በሚያስፈራ ሀገር እና ዓለም ውስጥ እየኖሩ ሁሌም ብርሃንን ማዜም ውሸት አይደለም ወይ? አልኩት። ማዕረግ ውሸታም ነህ እያለኝ ነው ብሎ ፊቱን ወደ ሃይሌ ሩትስ አዞረ። ሰራዊቱ በተጠንቀቅ እየጠበቀኝ ነው።

ጌቴ አንለይ ሙዚቀኛ ከተሰፋ ውጭ ሌላ መዝፈን የለበትም ብሎ ብዙ ነገር ዘረዘረ። አልበም ያላወጡት ሁለት ወጣቶች ጥበብ ከጨለማ ሽሽት መሆኑን ሊያብራሩልኝ ሀሳቤን ተቀባበሉት።የልጆቹ መልስ እዮብ መኮንን በወቅቱ ስለሙዚቃ ከሰጠው ቃለ-መጠይቅ ጋር መመሳሰሉን ሳስብ ነገርዬው የኤሊያስ የህይወት ፍኖት ውጤት መሆኑ ተገለጠልኝ። ውሸታም አልከኝ ? አለ በድጋሚ ። ፈገግ አልኩ ። እጁ ላይ ያለችውን ሲጋራ አሻሽቶ ለኮሳት። ሁለት ጊዜ ከማገ በኋላ። ሀገር ምን ማለት ነው ? የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ ። ሀገር ሰው ነው አልኩት ። መራሄ ተውኔት አባት መኩሪያ ያዘጋጀው ቴአትር ላይ ያለውን “ሀገር ማለት ሰው ነው ”የሚል መዝሙር እንደሚወደው ስለማውቅ ብዙ አልተጨነኩም። ቀጠለ። የሀገር ተስፋ ማለት የሰው ተስፋ ማለት ነው። የእኔ እና አንተ ተስፋ ማለት ነው። ኢቢሲ መስራትክን እርሳው። ኢትዮጵያዊነትን ሩቅ አታድርገው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት የጥንዶች፣ የባላትዳሮች፣ የአንድ ቤተሰብ ፍቅር የወለደው ነገር ነው። ለእነዚህ ጉዳዮች የምንሰጠው ቦታ ነው ትልቋን ኢትዮጵያ የሚፈጥረው። እኔ በስራዎቼ ስለ ፍቀረኞች መለያዬት እንዲዜም አልፈቅድም። ቀኑ ጨለመብኝ የሚል እንጉርጉሮ አልወድም። ምክንያቱም የፍቅረኞች መለያየት ነው የሀገርን መለያዬትን የሚወልደው። የግለሰቦች ጨለምተኛ መሆን ነው የሀገርን ጨለምተኝነት የሚፈጥረው። እኔ የካድኩት ፅልመትን ነው። እኔ የካድኩት ጨለማን ነው። …የቤት ሰራተኛው ኤሊ ሰው ይፈልግሃል አለችው። ተነስቶ ወጣ። ተመስገን አልኩ ! አያያዙ እኔንም ሊያጠምቀኝ ከጫፍ ደርሶ ነበር።

የኤሊያስ ሀዲድ ብርሃን ነው። የኤሊያስ ኢትየጵያ እኔና አንተ ነን። የአብነቱ ብላቴና ክህደት ከክህደት ጋር ነበር ።በጊዜ ሂደት ከሃዲነቱን ወደድኩት። እንኳን ውሸታም ሆንክ አልኩት። ሰውነት ህይወትን ዳግም መተርጎም፤ በተፍጥሮ ላይም መሰልጠን ነው። የኤሊያስ መልካ ስኬት ምንጩም ህይወትን መተርጎሙ፣ ተፈጥሮ ላይም መጎርመሱ ይመስለኛል። ኤሊያስ የአንተን ጎርናና፣ ቀጭን፣ አስቀያሚ ድምፅ ወስዶ አዲስ ውብ ድምጽ ይለግስሃል።

የሚኪያ በኃይሉ የመጀመሪያ ዓልበም ዓመታትን ወስዶ የመጨረሻ ሰራው እየተካሄደ እያለ አንድ ልብ ያላልኩትን ውብ ድምፅ ገና አሁን ሰማሁብሽ ብሎ ሙሉ አለበሟን እንዳስፈራት ሰምቻለሁ። የጌቴ አንለይን ድምፅ ከባህል አላቆ ሲያሻው ብሉዝ ፣ደስ ሲለው ችክችካ እንዲጫወት አድርጎታል። ኤሊያስ መልካ ከሳህሌ ደጋጎ (ኮለኔል) እና ሙላቱ አስታጥቄ በኋላ ተፈጥሮን በውሉ መግራት የቻለ ኢትዮጵያ የሙዚቃ ሰው ይመስለኛል። ማኅሌት ገብረ-ጊዮርጊስ ጋር የሰራውን የትግረኛ ሙዚቃን ልብ ብሎ የሰማ ሰው የምለው ይገባዋል።

 የአብነቱ ብላቴና የሙዚቃ ችሎታ ልምድ የወለደው ነው ብዬ ለመቀበል ይቸግረኛል። የኤሊያስ መልካ የመጀመሪያ ስራ “ሁሉም ይስማው” የተሰኘው የማሀሙድ አህመድ ዜማ ነው። መግቢና መሸጋጋሪዎቹን ደጋግሜ ስሰማቸው የበኩር ስራው እንዲህ የተዋጣለት የሙዚቃ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ብዬ በድፍረት እሟገታለሁ። የቴዲ አፍሮ የመጀመሪያ አልበም እንዴት የጀማሪ አቀናባሪ ስራ ነው ብዬ ላምን እችላለሁ። ለዛውም ክርስቲያን ስቱዲዎ ውስጥ ሰው አየኝ አላዬን ተብሎ ተደብቆ የተሰራ። ነዋይ ደበበ በአንድ ወቅት የነካው ሁሉ ይመርልህ የተባለ ሰው ነው ሲል ገልፆታል። እውነት ነው የኤሉ ጣቶች ታዓምረኛ ናቸው። እንደ ሚኪያ ድምፅ ታች አውረድው እንደ እዮብ ሬጌ ላይ ያወጣሉ። ፕሮዲውሰሮች ከኤሊያስ ስቱዲዮ የሚወጣን አልበም በውድ ለመግዛት አይሰስቱም። አድማጩም የጌቴ አንለይን አልበም አርባ ብር ገባ ብሎ አልተወውም።

ኤሊያስን ለስራ ከመጨነቁ አንፃር በሰው እድሜ ቀላጅ አድርገው የሚያዩት ብዙ ናቸው። ግን ስህተት ነው። አረጋሃኝ ወራሽ ያወጣው “በቃ በቃ ” አልበም እኮ አንድ ወር ብቻ ነው የወሰደው። ይርዳው ጤናውን በጥቂት ወራት ውስጥ ሙዚቃ አስተምሮ ለአልበም ማብቃት ታዓምር ይመስለኛል። ኤሊያስ መልካ ቀጥታ የሚሉት ዓይነት ሰው ነበር። ካመነበት የሌላውን ድጋፍ አይፈልግም። ብቻውንም ሆኖም ቢሆን ይፋለማል። የቅጅና ተያያዠ መብቶችን በተመለከተ በሸራተን ሆቴል በተካሄደው ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያበላሹ ያላቸውን ሰዎች ስም እየጠራ በአደባባይ ተችቷል። አንድ ወቅት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ጋር ልታገኛኝ ትችላለህ? አለኝ ።ምነው በሰላም አልኩት።

አዲሱ የቱሪዝም ሞቶ ምደረ ቀደምት የሚሉት ነገር ሀገር እንደሚያዋርድ ልነግራት እፈለጋለሁ እለኝ። ምክንያቱን ጠየኩት። ምዕራባዊያን የሰው ልጅ በዝግመተ ለውጥ መጣ ብለው የሚያምኑ ህዝቦች ናቸው። ሀገራችንን ምድረ ቀደምት ብለን ማስተዋወቃችንም ኑ ዝግመተ ለውጡን ያልጨረሰ ህዝብ ታገኛላችሁ ብሎ ከመቀስቀስ አይተናነስም አለኝ። እንዲህ ያለው የኤሊያስ ነገሮችን በሌላ መንገድ መመልከት ለሙዚቃችን ትልቅ ገፀ በረከት ነበር።

 ኤሊያስ መልካን ነበር እያሉ ማውራት ይከብዳል። ከቀናት በፊት እፈልግሃለሁ ብሎ ደወለልኝ። ሲ.ኤም ሲ የሚገኘው የአውታር ቢሮ ሄድኩ። ኤሊያስ በቦታው አልነበርም። ደወልኩለት፤ ዲያሊስስ ሲሰራለት ቆይቶ ናፕ እያደረገ እንደሆነ ነገረኝ። ከአፍታ በኋላ ደረሰ። አጎንብሷል፤ መራመድ ተስኖታል። ኃይሌ ሩትስና ጆኒ ራጋ አብረውት አሉ። መብራት በመጥፋቱ የህንፃው ሊፍት አይሰራም። አራተኛ ፎቅ ለመድረስ ደረጃዎችን መውጣት ጀመረ። ሦስት ደረጃዎችን ከወጣ በኋላ አቀተው። ቁጭ አለ። ተፈጥሮ ላይ የሚያምፀው ኤሊያስ እንደተረታ ገብቶኛል። አራት ፎቅ ለመውጣት ከ20 ደቂቃ በላይ ወስዶበት ቢሮ ተገናኘን። ስለአውታር አወራን። ድምፁ ይቋራረጣል። እረፍት አድርግ አልኩት። ሞትን ለመተባበር አለኝ?

 ደነገጥኩ። በመሃል አንድ ማየት የተሳነው ሰው ወደ ቢሮው ገባ። ለመነሳት ቢያቅተውም ተቀምጦ አልጠበቀውም። አጎንብሶ ሄዶ እየመራ ወንበር ሰጠው። ኤርፎኑን ከኪሱ አወጣ። የልጁ ሞባይል ላይ ሰክቶ ሙዚቃ መስማት ጀመረ። የአንተን ድምፅ ነው የምፈልገው የአንተን ዘፈን ነው የምፈልገው አለው። ልጁ የእኔ ድምፅ አኮ ነው ሲል መለሰለት። እንዳልወደደው ፊቱ ላይ ያስታውቃል። ታገሰኝ በደንብ እናወራለን ብሎት ወደእኔ ተመለሰ።

 ሁኔታው ልብን ይሰብራል። ዓለምን ጥሎ የመነነላት ሙዚቃ እስካሁን የነፍሱ ገዥ መሆኗ ይገርማል። አሁንም ስቱዲዮ ትገባለህ? አልኩት። አዎ አለኝ። ለእሱ ባልነግረውም ከሞት ጋር እልህ እንደተጋባ ተረድቻለሁ። ተፈጥሮን የማሸነፍ ልክፍቱ እዚህ ድረሰ መሆኑ ቢያስገርመኝም ምንም ልለው አልፈለኩም። የቢሮውን ደረጃ ቅልቁል ስጀምር ለምን እንደሆነ ባላውቅም አጋፋሪ እንደሻው ትዝ አለኝ። አጋፋሪ እንደሻ በስብሃት ገብረእግዛብሄር ልቦለድ ውስጥ ያለው ዋና ገፀ ባህሪ። ያ ሞትን ሽሽት በቅሎውን ጭኖ ሩቅ የሚሄደው አጋፋሪ እንደሻው። ከሞት ሊርቅ ፈረሱን ሽምጥ የሚጋልበው አጋፋሪ እንደሻው። ለኤሊያስ ያን ፈረስ ተመኘሁለት።

 የአብነቱን ብላቴና አፍንጫው ስራ ከሚገኘው ሞት የሚያርቀው አንዳች ነገር አሰብኩ። ከሙዚቃ ውጭ ምንም እንደሌለ ተረዳሁ። የኤሊያስ አልጋ ጠልቶ ሙዚቃ ውስጥ መሸሸግም ትክክል ነው አልኩ። ግን የኤሊያስ ሙዚቃ እንደ አጋፋሪ እንደሻው ፈረስ ለጊዜው እንጅ ለዘላለሙ ከሞት ለማምለጥ የሚረዳ አልነበርም። ጠዋት ጆኒ ረጋ አዎ አጣነው ሲለኝ ማመን አልቻልኩም። ተፈጥሮን የሚረታው ወዳጄ ኤሊያስ መልሶ ተራታ። ወደማይቀረው ዓለም ለመሄድ በተሰለፍንበት ፌርማታ ላይ የማውቀው ቅኑ ኤሊያስ ተራው ደርሶ ጥሎኝ ሄደ። ደና ሁን ብርሃን የምትናፍቀው ወንድሜ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top