ፍልስፍና

የእሳት ባህላዊ እና ሳይንሳዊ ትረካ

1.መግቢያ

ለምን ይህ ጸሑፍ አስፈለገ?

 የዚህ ጸሑፍ ዋና ዓላማ ሳይንስን ማኸዘብ ሲሆን፣ ይህን ዓላማ ለማሳካት እለት ከለት በምናያቸው ሂደቶች፣ ኩነቶች፣ እንዲሁም ለሰው ልጅ ጥቅምን የሚያበረክቱ የቁስ አካል ይዘት እና ሁኔታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መተንተን እና ለንባብ ማቅረብ አንድ ዓቢይ ዘዴ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ጽሑፍ የእሳት ታሪክ ሲሆን፣ የእሳትን እና የሰውን ልጅ ግንኙነት ከብዙ አቅጣጫ ይዳስሳል። የሰው ልጅ እሳትን እንዴት ሊቆጣጠር እንደቻለ ግምታዊ ትንተናዎችን ያቀርባል። እሳት በስነ ምህዳር እና በሰው ልጅ ሕያው ገላ ላይ ያስከተለውን ተፅዕኖ ይዳስሳል፣ እንዲሁም እሳት ለሰው ልጅ ያበረከተውን ጥቅም፣ ሊያደርስ የሚችለውንም ጉዳት፣ ያወሳል። በእሳት መጠቀም የሰው ልጅ የእለት ተለት ተግባር እንደመሆኑ፣ በአንፃሩ እሳትን መቆጣጠር ያሻል። አንዱ የእሳት ዋና መቆጣጠሪያ ውሃ ስለሆነ፣ ውሃ በእሳት መቆጣጠር ስለአለው ሚና ሳይንሳዊ ይዘት ይተነተናል። እንዲሁም የዘመናችን የአየር ቅጥ ለውጥ ከሰደድ እሳት ጋር ያለው ቁርኝት ይብራራል።

 2.ከእሳት ጋር የተዛመዱ እምነት ነክ እና ባህላዊ ኩነቶች

በእሳት ላይ የተመሰረቱ የእምነት ይዘት ያላቸው፣ እንዲሁም ከእሳት ጋር የተገናኙ ባህላዊ ስርዓቶችን በምሳሌነት እንዲያገለግሉ ጥቂቶችን አወሳለሁ። ዋናው በጥንት ዘመን ዓለማችንን ካዋቀሩት አራት አካላት አንዱ እሳት እንደሆነ መታመኑ ነበር፤ ሌሎቹ ውሃ፣ አየር እና አፈር ናቸው። በየትኛውም የዓለም ክፍል ከእሳት ጋር የተያያዙ አፈታሪኮች (ተረቶች) እና እምነቶች ነበሩ/አሉ። በጥንት ዘመን በእሳት አማልክት ማመን በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮጳ፣ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ፣ እንዲሁም በአውስትራሊያ እና በተለያዩ ደሴቶች አንሰራርቶ ይገኝ ነበር። እንደምሳሌነት እንዲያገለግሉ ጥቂቶችን አወሳለሁ።

እሳት ሙቀት እንዲሁም ብርሃን ስለሚያበረክት፣ እንደ ፀሐይ ወኪል፣ ወይም እንደ ፀሐይ አምላክ ወኪል ሆኖ ይታይ ነበር። ከሌላ አንፃር ስለ ዓለም ጥፋት የሚያወሱ አካባቢዎች፣ ዓለም በእሳት ነው የምትጠፋ ብለው ያምኑ ነበር። ሌሎች ደግሞ እሳትን እንደ ሕይወት መሰረት አድርገው የሚመለከቱ ነበሩ። አንዳንዶች ደግሞ እሳት የፀዳ ዓለምን እንድንጎናጸፍ ያስችለናል ይሉ ነበር። በክርስቲያኖች እምነትም እሳት ከኩነኔ ጋር ተያይዞ በገሃነብ ውስጥ እንደ መቅጫ መሳሪያነት ያገለግላል፣ ገሃነብ “እሳቱ የማይጠፋ ትሉ የማያንቀላፋ” አካባቢ ነው ይባላል።

በእሳት ላይ የተመሰረቱ ባህላዊ ስርዓቶች በብዙ አካባቢ ይታዩ ነበር፣ የስርዓቶቹ መሰረት እሳት ወይም የእሳት አምላክ ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ የነበረው “የአዝቴክ” መንግሥት ሕዝቦች፣ የእሳት አምላክ “ሁዊሁዊትል” (Huehueteotl) ሰማይ እና ምድር ባሉበት እንዲረጉ ያደረገ አምላክ ነው ብለው ያምኑ ነበር።

በብዙ አካባቢዎች፣ በተለይ በሩቅ ምስራቅ፣ አስከሬን ይቃጠላል። ለድርጊቱ የሚሰጠው ምክንያት፣ የሟችን የሕልፈተ ሕይወት ሁኔታ የጸዳ ያደርገዋል የሚል ነው። አስከሬን የሚቃጠል፣ እሳት ከምድራዊ ኮተት አላቅቆ ንጹህ ያደርገዋል ተብሎ ስለሚታመን ነው። እንዲሁም በአውሮፓ እና በሌሎች አካባቢዎች ጠንቋዮች የሸረቡትን ተንኮል፣ ያለሙትን ጥፋት ለማክሰም፣ እሳትን እንደ ተንኮል አውዳሚ አድርገው ይመለከቱ ስለነበረ፣ ጠንቋዮች ለእሳት ቃጠሎ ይዳረጉ ነበር።

በሰሜን ህንድ በአሰም አካባቢ፣ ስለ እሳት ባለቤትነት የሚወሳ አፈታሪክ አለ። እሳት ከውሃ ጋር በነበረው ጦርነት ተሸንፎ፣ መሸነፉን አምኖ ቀርቀሃ ውስጥ ተደብቆ ሳለ፣ ሲደበቅ ፌንጣ አይታ ኖሮ፣ ሂደቱን ለጦጣ ሹክ አለች። ጦጣም የእሳትን ጠቃሚነት ተረድታ ኖሮ፣ የእሳት ባለቤት ለመሆን ሞከረች። ሆኖም ነገሩን ሰው ስለሰማ፣ እሳትን ከጦጣ ነጥቆ የራሱ ንብረት አደረገ ይባላል። ግሪኮችም የእሳት ባለቤት የሰው ልጅ እንደሆነ የሚያወሳ አፈታሪክ አላቸው። አፈታሪኩም ፕሮሜቱስ (Prometheus) እሳትን ከአማልክት ሰርቆ ለሰው ልጅ ሰጠ ይላል። ከባህርይ ጋር በተያያዘ መንገድ ስለእሳት የማወሳ፣ የአማርኛ አባባሎችን፣ ዘይቤዎችን እንደምሳሌነት ወስጄ ነው። ደመራ እና እሳት በመስቀል በዓል ዋና መግለጫዎች ናቸው። በሀገራችን “ኅዳር ሲታጠን” ይባላል። ሰብሉ እንዲሠምር ይታጠናል። የሰው ተፈጥሮ ጠባዩን ከሚመሩ ከሦስት ነባር ኩነቶች አንዱ በእሳት ይመሰላል፣ ንባቡ እነሆ። በልጅነት እሳት ነው፤ በጎልማስነቱ ነፋስ ነው፥ ወዲያ ወዲህ እያለ ሕይወቱን ይረዳል፤ በሽምግልናው ውሃ ነው፤ ይቀዘቅዛል። እንዲሁም እሳት ተጨማሪ ባህርያት መግለጫ ይደረጋል። ለምሳሌ በጣም ተናደደ ለማለት “እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ”፤ ጮሌ ለጮሌ ተገናኙ ለማለት “እሳት ለእሳት”፤ አጥፊ እና ጠፊ ወይም የማይስማሙ ለማለት “እሳት እና ጭድ”፤ ነገር ቆሰቆሰ ለማለት “እሳት ጫረ”፤ ተወደደ ወይም ዋጋው ናረ ለማለት “እሳት ሆነ”፣ ወዘተርፈ። ከሌላ አንፃር ጎረቤት ለጎረቤት ያለውን መልካም ጉርብትና አመልካች ሆኖ ይወሰዳል (በጎረቤታሞች መኻከል እሳት መጫጫር የቅርበት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል)።

 3.የእሳት ሳይንሳዊ መሰረት

እፀዋት ወይም የእፀዋት ቅሪቶች (ቤንዚን፣ የድንጋይ ከሰል ወዘተርፈ) ‘እሳት የሚያፈልቁ እንዴት ነው?’ ‘እሳት ምንድን ነው?’ መልሱን የምናገኘው የእሳትን ሳይንሳዊ ይዘት ስንረዳ ነው። በቀን ተቀን ተግባሮቻችን እሳትን የምናየው ከእፀዋት (ከማገዶ) ጋር አቆራኝተን ነው። ይህንን ሁኔታ ለመገንዘብ በመጀመሪያ የእንጨትን አመጣጥ መገንዘብ ያሻል።

 እንጨት የካርቦን አቶሞች ውቅር ነው፣ የካርቦን አቶሞች እንጨትን የሚገነቡበት (የሚያዋቅሩበት) ስልት እነሆ።

አየር ውስጥ የካርቦን አቶሞች የሚገኙ ከኦክሲጂን አቶሞች ጋር ተዋህደው ሲሆን፣ ውሁዱ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ሞሌኪዩል (CO2) ነው። የካርቦን እና የኦክሲጅን ውሁድ የሚላቀቀው (የሚለያየው) በፀሐይ ብርሃን ኃይል ሲሆን፣ የመፈናቀሉ/ የመላቀቁ ሂደት በብርሃን አስተፃምሮ (photosynthesis) ይተገበራል። ካርቦን እና ኦክሲጂን ተፋተው (ተላቀው)፣ ካርቦን አቶሞች የእንጨት አካል ይሆናሉ። ይህም አረንጓዴ ሃመልሚል ወይም ክሎሮፊል (chlorophyll) በፀሐይ ጨረር ኃይል አጋዥነት፣ በውሃ አመቻችነት፣ ከአካባቢ አየር ካርቦንዳይኦክሳይድን ምጎ፣ እንጨት ስለሚገነባ ነው።

 በፀሐይ ኃይል የታገዘው መስተፃምሮ በመሰረቱ የውሃን ሞሊኪዩል (molecule) ወደ ኦክሲጅን (O2) እና ሃይድሮጅን (H) መንዝሮ፤ ኦክሲጅን ወደ ከባቢ አየር ሲለቀቅ፣ ሃይድሮጅኑ ግን በኬሚካዊ ውህደት ከካርቦን ጋር ተፃምሮ፣ የካርቦን ውህድ (carbon compound) ይገነባል። የፀሐይ ጨረር በራሱ ኃይል ቅጠሉ ውስጥ ሲገባ፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ግን ከአየር ተጠልፎ ነው የሚወሰደው። ካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO2) በመጀመሪያ በቅጠል ገላ ላይ ባሉ ትናንሽ ወንፊት መሰል ቀዳዳዎች፣ ስቁረቅጠል (ቅጠል ብስ/ Stomata) ከገባ በኋላ፣ እንደ ተሸካሚ/ ጋሪ በሚያገለግል ኬሚካላዊ እገዛ፣ በረቀቀ ኬሚካዊ ስርዓት/ ሂደት ወደ እንጨትነት ይቀየራል።

 እሳት የሚከሰተው፣ እንጨት ውስጥ ያሉ የካርቦን አቶሞች ከኦክሲጂን ጋር ሲቀላቀሉ ነው። ሂደቱም እንደሚከተለው ነው።

 ለምሳሌ እንደአጋጣሚ ሆኖ፣ በመብረቅ መንስዔ ወይም በእሳተገሞራ ፍሳሽ፣ ወይም ቀደም ሲል ከነበረ የእሳት ቃጠሎ፣ አካባቢው ከፍተኛ ሙቀትን ሲቀዳጅ (ሲያገኝ)፣ አየር ውስጥ ያሉት የኦክሲጂን አቶሞች እንጨት ውስጥ ካሉ የካርቦን አቶም ጋር ለማቀናጀት አጋጣሚው ይከሰታል።

 በሙቀት መንስዔ የተጀመረው የማያቋርጥ የአቶሞች ግጭት፣ ፍትጊያ፣ ሽኩቻ፣ በተገኘ ኃይል/ ኢነርጂ (energy) አካባቢው ሲግል፣ እንጨት አካል የነበሩ የካርቦን አቶሞች ከእንጨትነት ባህርያቸው ተፈናቅለው፣ ከኦክሲጅን ጋር ይዋሃዳሉ፣ ያም የቃጠሎ ሁኔታን ያስከትላል:: ኦክሲጂን አቀጣጣይ፣ ካርቦን ተቀጣጣይ ይሆናሉ። ስለሆነም እሳት ይፈልቃል ብሎም ቃጠሎ ይከሰታል፣ ቃጠሎውም ያካባቢውን (የእንጨት አካል የሆኑ) ካርቦን አቶሞችን ያግላል፣ ብሎም ያፈናቅላል።

 በዚህ መንገድ የተፈናቀሉ አቶሞችም፣ ሌሎችን የካርቦን አቶሞች ያፈናቅላሉ፣ ከኦክሲጅን ጋር እንዲገናኙ ሁኔታውን እያመቻቹ የቃጠሎው ሂደት ይቀጥላል፣ መጋል መፈናቀል፣ ከኦክሲጂን ጋር መገናኘት፣ ብሎም መቃጠል፤ ስለሆነም ተጨማሪ እሳት እንዲከሰት ይዳርጋል። በአካባቢው ኦክሲጅን እስካለ ድረስ እንጨቱም መንደዱ (መቃጠሉ) ይቀጥላል፤ ውጤቱም ካርቦንዳይኦክሳይድ (CO2) ይሆናል (ተመልካች በጢስ መልክ ነው የሚያየው)።

 ይህም እንደ ድንጋይ ናዳ ሊመሰል ይችላል። ከከፍተኛ ቦታ የጀመረ የድንጋይ ናዳ፣ ሲወርድ ታች የሚገኝን ድንጋይ አፈናቅሎ እንዲናድ ያደርጋል፣ የተፈናቀሉ ድንጋዮችም ከነሱ በታች ያሉ ድንጋዮችን ያፈናቅላሉ። ከፍታው እንደ ሙቀት ኃይል ቢመሰል፣ ሂደቱ (የካርቦን አቶሞች ከእንጨት አካል መፈናቀል) ተመሳሳይ ይሆናል። ሙቀት በመሰረቱ፣ ከፍ ካለ የሙቀት ይዘት ካለው አካባቢ፣ ዝቅ ያለ የሙቀት ይዘት ወዳለው አካባቢ ነው የሚዘምት። ስለሆነም ነው፣ በመንደድ ካለ እንጨት ገና ወደ አልነደደው አካል (አካባቢ) የሚሰራጭ። የዚህ ዓይነት አጋጣሚ ባልተከሰተበት አካባቢ (ማለት ከፍተኛ ሙቀት በሌለበት አካባቢ)፣ የካርቦን አቶሞችም የግንድ (እንጨት) አካል ሆነው፣ ኦክሲጂንም አቶሞች አየር ውስጥ ሆነው ጎን ለጎን በአንድ አካባቢ ይገኛሉ፣ ቃጠሎም አይከሰትም።

እሳት ሲነድ ሙቀት እንዲሁም ብርሃን ይገኛል። ያ የሚሆነውም ቀደም ሲል የካርቦን አቶሞችን ከኦክሲጂን ለመነጠል በተደረገው ሂደት፣ የፀሐይ ኃይል የነበረው (ብርሃንም

የስነ ምህዳር፣ የባዮጂኦግራፊ እንዲሁም የፖሎቦታኒ ምሁራን የአየር ቅጥ እና የአፈር ዓይነት የስነምህዳር ይዘትን ይወስናሉ የሚል እይታ አላቸው

ሆነ ሙቀት) ወደ ኬሚካዊ ግብዓትነት ተቀይሮ፣ የእንጨት አካል ሆኖ ቆይቶ፣ በዚህ አዲስ በተከሰተው ኃይል (ፍትጊያ፣ ሽኩቻ፣ ወዘተርፈ) ቀደም ወደ ነበረበት መመለሱ ነው። አንዱ የሳይንስ መርህ “ቁስ አካልን ለመፍጠር እንዲሁም ለማውደም አይቻልም” (matter is neither created nor destroyed) ይላል፣ ከፀሓይ በታች አዲስ ነገር የለም እንደሚባለው። ይህም “የሌለ አይገኝም፣ ያለም አይከስምም”፣ ባህሪውን ይቀይራል እንጂ እንደ ማለት ነው።

 4.እሳት በስነምህዳር እና በሰው ልጅ ህያው አካል ያስከሰተው ተፅዕኖ

በፀሐይ ኃይል አካላቸውን የሚገነቡ እፅዋት በገፀ ምድር ከማንሰራራታቸው በፊት ምድርን በከበበው አየር ውስጥ የነበረው የኦክሲጅን መጠን ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ ነበር። እፅዋት በብርሃን አስተጻምሮ ሂደት ኦክሲጅንን ማመንጨት ከጀመሩ በኋላ በህዋ ውስጥ የነበረው የኦክሲጅን መጠን ጨመረ፣ ብሎም ለእሳት ቃጠሎ አካባቢውን አመቻቸ። ምንም እንኴን እፅዋት በምድራችን ከ540 ሚሊዮን ዓመት በፊት ቢከሰቱም፣ እሳት ለማቀጣጠል በቂ ኦክሲጅን ማመንጨት የቻሉ ከ400ሚሊዮን ዓመት በፊት እንደነበረ ይገመታል፣ ግምቱን ተኣማኒ የሚያደርጉ በቂ ማስረጃዎች ተገኝተዋል።

 ስለሆነም እሳት ከ400 ሚሊዮን ዓመት በፊት ጀምሮ በምድራችን ታሪክ፣ በእፅዋትም ሆነ በእንስሳት ዝግመተ ለውጥ አቅጣጫ ቅየሳ፣ ጉልህ ሚና እንደነበረው ይገመታል። ያም ሊከሰት የቻለ እሳት የምህዳርን (የአካባቢን) ይዘት መቀየር በመቻሉ ነው።

 የስነ ምህዳር፣ የባዮጂኦግራፊ እንዲሁም የፖሎቦታኒ ምሁራን የአየር ቅጥ እና የአፈር ዓይነት የስነምህዳር ይዘትን ይወስናሉ የሚል እይታ አላቸው። እነኝህ ምሁራን ዓለምን ካለእሳት ተፅዕኖ መገንዘብ ይሳናል፤ ምክንያቱም እሳት የአካባቢውን ሁኔታ በመወሰንም ሆነ የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ላይ ከፍተኛ ሚና ስለነበረው ነው። እንዲሁም ሰው እሳትን መቆጣጠር ከጀመረም ወዲህ በእሳት በመጠቀም በብዙ አካባቢዎች የምድርን ገፅታ ለመቀየር ችሏል።

ምድራችን በተወሰኑ ሥርዓተ ምህዳር የተከፋፈለች ነበረች። በእያንዳንዱም ሥርዓት ምህዳር በዝግመተ-ለውጥ በተለያዩ አካባቢዎች እንደ አርማ የሚመስሉ እፅዋት እና እንስሳት ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። ለምሳሌ ካንጋሩ (Kangaroo) በአውስትራሊያ፣ ሌሙር (Lemur) በማዳጋስካር፣ ወዘተ። ከጊዜ በኋላ የሰው ልጅ እንቅስቃሴ የሥርዓተ ምህዳሩን አጥር ሰብሮ አንዱን ከሌላው ቀላቀለው።

የሰው ልጅ (Homo sapiens)፣ ከ45,000 ዓመት በፊት ነበረ አውስትራልያን የወረረ። የአውስትራልያን ምድር ከረገጠ በኋላ እና ጉዞውም ወደመሃል አገር ሲያቀና፣ የሰው ልጅ እግረ- መንገዱን ወሰን የሌለው ጥፋት በአካባቢው አስከትሏል። በሂደት በእሳት ታግዞ፣ የሰው ልጅ ተፎካካሪ የነበሩ ግዙፍ አዳኞችን (ስጋ በል እንስሳትን) በሙሉ ከምድር ገፅ አጠፋቸው። ይህም ኩነት ራሱን በምግብ ፒራሚድ ቁንጮ ላይ ለማስፈር አስችሎታል።

ቀደም ብሎ የሰው ልጅ የሚኖርበት አካባቢ፣ አፍሪካም ውስጥ ሆነ ኢሮእስያ፣ ከሌሎች እንስሳት ጋር አብረው ጎን ለጎን በዝግመተ- ለውጥ ስለተጓዙ፣ የህያው ዝግመተ ለውጥ ከአካባቢው ሁኔታ ጋር እያጣጣመ፣ እያሳለጠ ነበር የኖረ። አውስትራሊያ የነበሩ ግዙፍ እንስሳት ግን ይህ እድል አልገጠማቸውም። የሰው ልጅ አፍሪካም ውስጥ ሆነ ኢሮእስያ በዚያን ወቅት አውስትራልያ የደረሰውን የሚመስል አሰቃቂ ጥፋትን አላመጣም።

 የአውስትራሊያን መሬት ከረገጠ በኋላ ግን የሰው ልጅ እና የአካባቢ ግዙፍ እንስሳት ግንኙነት ተቀየረ። በዚህም ምክንያት (ጎን ለጎን በዝግመተ ለውጥ ስላልተጓዙ) ነበር ለጥፋት ለአደጋ የተጋለጡት ተብሎ ይገመታል። የሰው ልጅ ለአውስትራልያ እና ለአካባቢ ደሴቶች መጤ ነበር። ለአውስትራልያ ደሴት እንግዳ የነበረው የሰው ልጅ፣ እዚያ አካባቢ ቀደምት ከነበሩ ግዙፍ እንስሳት ጋር ሲነፃፀር አቅመ ውስን ኮሳሳ ነበር። ይህም የሰው ልጅ ረጃጅም ሹል ጥርሶች ወይም አስፈሪ ጥፍሮች ወይም ፈርጣማ ጡንቻ ስላልነበረው ነበር በአካባቢ ግዙፍ እንስሳት ከጉዳይ ያልተጣፈ።

 ግዙፍ የአውስትራሊያ እንስሳትም የሰውን ልጅ የጎሪጥ በንቀት ከተመለከቱት በኋላ፣ እንዳልነበረ ቆጥረውት፣ በነባር ተግባሮቻቸው ይሰማሩ እንደነበረ መገመት ይቻላል። ይህ መጤ የሰው ልጅ ግን ግዙፍ ነባር እንስሳትን በማጥቃት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአውስትራልያን ስነ ምህዳር ተቆጣጠረው፣ ብሎም ቀየረው። ለዚህ የበላይነት ያበቃው የአካባቢ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ፣ እሳት እንደነበረ ይታመናል።

 እሳትን ከበጎ ጎኑ እንመልከት። የሰው ልጅ ምግቡን በእሳት ማብሰል መቻሉ በአካሉ ላይ ለውጥ እንዳስከተለ ሳይንሳዊ ማስረጃ አለ። የሰው ልጅ ምግብ በእሳት ማብሰል በመቻሉ፣ ምግብ ማኘክ ይወስድበት የነበረውን ጊዜ በብዙ እጥፍ ለመቀነስ በቃ።

 ለመፍጨት ማብላላት ለእንሽርሽሪት (digest) ያዳግቱ የነበሩ ምግቦችን በቀላሉ መፍጨት (ማድቀቅ) ቻለ። ስለሆነም ቀደም ሲል ሳይበስሉ ለመብላት የማይችላቸውን ሰብሎች፣ በእሳት በማብሰል ለምሳሌ ሥራሥሮችን፣ ጠጣር አዝርእትን፣ ለመመገብ በቃ።

ምግብን አብስሎ መብላት፣ ሳያበስሉ ከመብላት ጋር ሲነፃፀር ለሰውነት ግንባታ ግብዓት በላቀ መጠን ያበረክታል ይባላል። ዘመዶቹ፣ ለምሳሌ ቺምፓንዚ (Chimpanzee)፣ ለማኘክ/ለመፍጨት ሰዓታት የሚወስድባቸውን ምግብ የሰው ልጅ ምግቡን አብስሎ በመብላት በደቂቃዎች ውስጥ ያን ተግባር ማጠናቀቅ ቻለ። ምግብ ላይ የሚገኙ ጥገኛ ትላትሎችንም (ለምሳሌ፣ የኮሶ ትል) ሆነ ሌሎች በሽታ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሕዋሳት እንዳይለክፉት ምግቡን ማብሰሉ ታደገው። እንዲሁም በጥሬው ቢበሉ መርዛማ የሆኑ ምግቦችን፣ ለምሳሌ ካሳቫ፣ ማብሰል ከመርዛምነታቸው ያላቅቃቸዋል።

 አንዳንድ ምሁራን አብስሎ መብላት የሰው ልጅን ጥርሳዊ መዋቅር እንደቀየረ ይገምታሉ፣ የጥርስ መጠነኛ መሆን፣ የመንጋጋ ጥርሶች ቅርጽ እና ግዝፈት (ማነስ)፣ የምንግጭል ስፋት እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል ይላሉ። የአንጀት ማጠር፣ እንዲሁም የጭንቅላቱ ግዙፍ (ትልቅ) መሆን ምግብን በእሳት ከማብሰል ጋር ግንኙነት አላቸው ብለውም ይገምታሉ። በመሠረቱ ረጅም አንጀትም ሆነ ጭንቅላት የሚጠቀሙት ኃይል (energy) ከሌላው የሰው አካል ጋር ሲነፃፀር በጣም የላቀ ነው። ምንም አወዛጋቢ ቢሆን፣ አንጀት በማሳጠር እዚያ መጠቀሚያ ሊሆን የነበረው የኃይል መጠን ወደ አንጎል (ጭንቅላት) ፍጆታ መጨመር አስችሏል ይባላል። በአጠቃላይ እሳት የተለያዩ ምግብ ዓይነቶችን (ጥራጥሬ፣ ፍራፍሬ፣ ሥራሥር፣ ሥጋ ወዘተ) ለመብላት የተለያየ የሰው ልጅን አካል (ጥርስ፣ አንጀት፣ ወዘተርፈ) ተግባሮች አቅልሎላቸዋል።

ሌላው የእሳት ዋና ተግባር አካባቢን መቆጣጠር ማስቻሉ ነው። እንስሳት ሁሉ ተግባሮቻቸውን የሚያከናውኑ በአካላቸው በመጠቀም ነው፤ በጡንቻ ፈርጣማነት፣ በጥርስ ግዙፍነት፣ በጥርስ እና በጥፍር ስልነት፣ በክንፍ (አእዋፍ) ርዝማኔ፣ ስፋት፣ ወዘተ ነው። ይህም ችሎታቸው ከአካል ቅርጽና መጠን ጋር የተገናኘ ስለሆነ ውስን ነው። የያንዳንዱ የአካል ክፍል እድገት የተወሰነ ስለሆነ፣ የማንም እንስሳ አካል ካለመጠን ሊያድግ አይችልም። የሚያከናውነውም ተግባር የሚወሰን ከእድገቱ ጋር ተጣጥሞ ነው።

 በተጨማሪ የአካል ተግባርን ለማስተናገድ የውጪው (ከአካል ውጭ ያለው ከባቢ) ወሳኝ ሚና አለው። ለምሳሌ ንሥር የሞቀ አየር ላይ ተሳፍሮ ወደ ሰማይ ይወጣል፣ ሆኖም ሙቁ አየሩ ወዴት እንደሚንቀሳቀስ ሊቆጣጠረው አይችልም። ሰው ግን እሳትን መሣሪያ አድርጎ፣ የትኛውን ጫካ እንደሚያቃጥል፣ የትኛውን ሜዳ እንደሚለበልብ ያውቃል። ስለሆነም የሰው ልጅ እሳትን በመቆጣጠር፣ ከአካሉ ውጭ የሆነ ግዙፍ የአካባቢ መቆጣጠሪያ አቅም ተጎናጸፈ። በእሳት ለመጠቀም ደግሞ ምንም ልዩ የሆነ ጉልበት (አቅም) አያሻም። ኮበሌ፣ ጎረምሳ፣ ኮረዳ፣ አዛውንት፣ ባልቴት፣ ወዘተ ይህንን ለማከናወን ይችላሉ። በዚህ ምክንያት እሳት የሰው ልጅ እድገት (የዓለም ገዢነት) ወሳኝ መሣሪያ ሆኖ ቀጠለ።

የሰው ልጅ ወደ አሜሪካ ክፍለ ዓለም ሲጓዝ፣ በበረዶ በተሸፈነ የብስ በብርዳማ ቦታ ማለፍ ነበረበት። በተጨማሪ በክረምት ወራት ፀሐይ በማትታይበት በበጋ ወራት ፀሐይ በማትጠልቅበት አካባቢ ነው ጉዞው የተደረገ። ጉዞውም በቴክኖሎጂ የታገዘ ነበር፣ ያም ብርድ ተከላካይ ልብስ፣ ጫማ፣ እና በስለት የታገዘ የአደን ዘዴን እንዲሁም በእሳት መጠቀምን ያካትታል።

 የሰው ልጅ አሜሪካ ከደረሰ ወዲያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጠቅላላ ከሰሜን አላስካ እስከ ደቡብ አሜሪካ ጫፍ ድረስ፣ ሁለት ሺ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነበር አህጉሩን (አሜሪካን) ከዳር እስከ ዳር የረገጠ። በአካባቢው የነበሩ ግዙፍ እንስሳት ለምሳሌ ማሙዝ (mammoth)፣ ማስቶደን (mastodens) ሌሎች የቀንድ እንስሳት፣ እንዲሁም ፈረሶች፣ ግመሎች፣ ድብ፣ ግዙፍ የድመት ዝርያዎች (አንበሶችን ጨምሮ)፣ እንደአውስትራሊያ እንስሳት ሁሉ፣ እነኝህም የአሜሪካ እንስሳት በዝግመተ ለውጥ ከሰው ልጅ ጋር ግንኙነት አልነበራቸውም። ስለሆነም ነበር በቀላሉ ለአደጋ የተጋለጡ።

ቅድመ ሰው እሳትን በመቆጣጠር ተግባር ጠላቶቹን መከላከል ስለቻለ፣ እንደዘመዶቹ ዛፍ ላይ ከመኖር ተላቅቆ፣ ሜዳ ላይ ሰፈረ ይባላል። መሬት ላይ መኖር ከተጀመረ ደግሞ፣ ሩቅ ስፍራን ለማየት በኋላ ሁለት እግሮች መቆም ግድ ይላል (ያሻል)። ከዛፍ ላይ ሆኖ በቀላል ይታይ የነበረን አካባቢ መሬት ላይ ሆኖ መቃኘት ቀላል አይደለም፣ ያዳግታል። ስለሆነም አንዳንድ ምሁራን ቆሞ መሄድን እሳትን ከመቆጣጠር ጋር ያዛምዱታል።

 ስነምህዳር ቅየራ (ምሳሌ የቦረና የግጦሽ መሬት)

የሰው ልጅ ዝቅተኛ ርጥበት የነበራቸውን አካባቢዎች በእሳት እገዛ ዛፎችን በማጥፋት፣ አካባቢው በሳር ብቻ እንዲሸፈን ለማድረግ በመቻሉ፣ ታዳኝ የቀንድ ከብቶች እንዲሰማሩበት አመቻቸ ይባላል። በአገራችንም ይህን ግምት የሚያጠናክር ሁኔታ አለ። የቦረና አካባቢ ለዚህ ተግባር እንደምሳሌነት ሊወሰድ ይችላል። ከዓመታት በፊት፣ አንድ በተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ላይ የተሰማራ ባለሙያ በወቅቱ ለነበረ የመንግሥት ሹም ምክር ሰጠ። ያም በየዓመቱ ይካሄድ የነበረ የግጦሽ መሬት ሳር ማቃጠል እንዲቆም፣ ሳሩ እንዳይቃጠል፣ በየዓመቱ በእሳት እንዳይጋይ ነበር። ምክሩም የተሰነዘረው የተፈጥሮ ሃብትን ከመንከባከብ አንፃር ታይቶ ነበር። ምክሩንም ሹሙ ተቀብሎ፣ የግጦሽ መሬቱ ሳር እንዳይቃጠል ለአካባቢው አስተዳደር ትእዛዝ አስተላለፈ። ሳሩም በየዓመቱ ሳይቃጠል ለጥቂት ዓመታት ቆየ። ከዚያም የአካባቢው ምድራዊ ገጽታ ተቀየረ።

 በመሠረቱ የግጦሽ መሬት ሳሩ በየዓመቱ የሚቃጠል፣ ለግጦሽ የሚስማማ አዲስ ሳር እንዲበቅል ሲሆን፣ አዲስ ሳር ሊበቅል የሚችለው ደግሞ አሮጌው፣ ለመብላት/ ለግጦሽ የማያመቸው ከቦታው ሲከላ ነው። ቃጠሎው አዲስ ሳር እንዲበቅል ቦታ ከማዘጋጀት ባሻገር፣ ሌሎች ጥቅሞችንም ይሰጣል-የከብት ጥገኞችን ማጥፋት (ለምሳሌ መዥገር)፣ ሰውም ሆነ ከብት ተጻራሪ የሆኑ ተርመስማሽ እንስሳትን ለማባረር፣ ለማጥፋት (ለምሳሌ እባብ)፣ ወዘተ. ነው። ከብቶች በግጦሽ ሜዳ ላይ ሲሰማሩ፣ በመብቀል ላይ ያሉ፣ ግን የማይፈለጉ እፀዋትን ስለሚረጋግጡ፣ ተፈላጊ ያልሆኑት ዛፎች (ለምሳሌ ግራር) አይበቅሉም። ግራር መሰል ዛፎች በግጦሽ ሜዳ አለመኖራቸው፣ የግጦሹን ሜዳ ለግጦሽ ተስማሚ ያደርገዋል (ያሰምረዋል)። በተጨማሪ ቃጠሎውም በማደግ ያሉ ወጣት የዛፍ ዝርያዎችን ያኮስሳል፣ ቅጠሎቻቸውን ያጋያል፤ ግንዱንም ይለበልባል፤ ስለሆነም በማደግ ላይ ያሉ ዛፎችን ምግብ ለመፈብረክ ያላቸው አቅም ይመነምናል፣ ስለሆነም አያድጉም።

ሳሩ በየዓመቱ ባለመቃጠሉ ምክንያት በግጦሹ ሜዳ ግራር አንሠራራበት። የቦረና አካባቢ ማህበረሰብ፣ አርብቶ አደር የሕልውናው መሰረት ተቃወሰ፤ ከብቶቹ፣ የሚበላ ሳር ማግኘት ተሳናቸው። አካባቢው ለሣር-በል ሳይሆን፣ ለቅጠል-በል እንስሳት አመች እየሆነ ሄደ፤ በቀንድ ከብቶች ፈንታ ለግመል መሰማሪያነት ያመቸ ሆነ። ይህም ሁኔታ ጎረቤት ያሉ የግመል አርብቶ አደሮችን ወደ ቦታው ለመንቀሳቀስ ጋበዘ። ይህም ሁኔታ የሁለቱን አርብቶ አደሮች በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም መንስዔ የሚነሳውን ግጭት አባባሰው።

የዘመናችን የአየር ቅጥ ለውጥ ከሰደድ እሳት ጋር ያለው ቁርኝት

በዘመናችን ለተከሰተው አየር ቅጥ ለውጥ ጋር ተዛምዶ፣ እሳት በብዙ አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። በእንግሊዝ ሮያል ሶሳይቲ (Royal Society-UK) እሳት እና የሰው ልጅ በሚል ርዕስ እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር፣ በሴፕቴምበር 2015 አንድ ኮንፈረንስ ተዘጋጅቶ ነበር። ኮንፈረንሱ ትኩረት የሰጠ በሰው ልጅ እና በእሳት ስላለው ቅርብ ግንኙነት እና ወደፊት ከአየር ቅጥ መለወጥ ጋር ተዛምዶ፣ እሳት ምን ሊያስከትል እንደሚችል ነበር። በብዙ አካባቢዎች የአካባቢ እርጥበት በመቀነሱ መንስዔ፣ ያንን ዓይነት አካባቢዎች ለሰደድ እሳት እየተጋለጡ መሆናቸው፣ ብዙ ውይይት የተደረገበት ጉዳይ ነበር። ለዚህ ኩነት ምሳሌዎች በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ እና በሌሎች አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱ የሰደድ እሳት ቃጠሎዎች እንደማስረጃነት ተወስደዋል።

5.እሳት እና የሰው ልጅ በእሳት መጠቀም መቼ እና የት ተጀመረ?

የሰው ልጅ በእሳት መጠቀም መቼ እና የት እንደጀመረ አርኪ ማስረጃ እስከአሁን አልተገኘም። የሰው ልጅ በእሳት መጠቀም የጀመረበት ጊዜ ጥርት ባለ መንገድ ባይታወቅም፣ ጊዜውን የተመኑ ብዙ መላምቶች፣ በተፈራረቁ ዘመናት ያሰፍሩታል፣ ዘመኑ ከ1.7 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ጀምሮ እስከ 200ሺ ዓመት በፊት ባሉት ጊዚያት መካከል ይዋዥቃል። የእሳት ቃጠሎ ከሰው ልጅ ቁጥጥርም ውጭ ሆኖ፣ በተፈጥሮ ስለሚከሰት ነው፣ ለምሳሌ በመብረቅ በእሳተገሞራ ፍሳሽ፣ በጠጣር ግዙፍ አካላት ግጭት፣ ወዘተረፈ አሳማኝ ማስረጃ ማግኘት ምሁራን ተሳናቸው።

 የሰው ልጅ በእሳት መጠቀም የጀመረ ከ800ሺ ዓመታት በፊት ነበር የሚል ግምት በብዙ አካባቢ ተቀባይነት አለው። አንዱ የሰው ልጅ ዝርያ ሆሞ ኢሬክተስ (Homo erectus)፣ ከአንድ ሚሊዮን ዓመት በፊት በእሳት ይጠቀም እንደነበረ ማስረጃ ተገኝቷል። በተለይ ከ200ሺ እስከ 125ሺ ዓመት በፊት ጀምሮ የሰው ልጅ በብዙ አካባቢዎች በእሳት ይጠቀም እንደነበረ የሚያመላክቱ ብዙ ማስረጃዎች ተገኝተዋል።

የሰው ልጅ እና የእሳት ግንኙነት ቀስ በቀስ የተካሄደ ይመስላል። ዋናው በሰደድ እሳት ከተቃጠሉ አካባቢዎች፣ በከፊል ያረሩ፣ በከፊል የበሰሉ የእንስሳት ቅሪቶች ሊገኙ ይችላሉ። በመጀመሪያ እሳት ባጋየው አካባቢ በእሳት ቃጠሎ የበሰለ ምግብን መቃረም፤ ወይም ሰደድ እሳትን ሸሽተው የሚወጡ እንስሳትን በማደን፣ የሰው ልጅ ከእሳት ጋር ቅርበት መሰረተ። ከሰው ልጅ ጋር የዘር ሃረግ የሚማዘዙት ጦጣዎች (Vervet monkeys/ Cercopithecus aethiops)፣ በሰደድ እሳት የተባረሩ ሦስት አጽቄዎችን፣ እንሽላሊቶችን፣ አእዋፍን፣ ወዘተርፈ ሲመገቡ ይስተዋላል። የሰው ልጅም በተመሳሳይ ተግባር ተሰማርቶ እንደነበረ ይገመታል።

በሰደድ እሳት በበሰሉ የምግብ ዓይነቶች የሰው ልጅ መጠቀም መቻሉ፣ የሰው ልጅ ምግቡን በእሳት አብስሎ መብላት በጥሬው ከመብላት የተሻለ እና ቀለል ያለ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተገንዝቦ ሊሆን ይችላል። ይህም ሁኔታ የሰው ልጅ ከእሳት ጋር ያለውን ግንኙነት እያጠናከረው ይሄዳል፣ ስለሆነም አብስሎ የመብላት ባህርይን አዳብሮ ሊሆን ይችላል።

የሰው ልጅ የምድር የበላይ ተቆጣጣሪ መሆን

 የሰው ልጅ በምግብ መረብ በእሳት እገዛ የመረቡ ቁንጮ ተዋናይ ለመሆን ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ይህን ለማድረግ እንዴት ቻለ የሚለውን መረዳት ያስፈልጋል። የምግብ ሰንሰለት፣ መረብ፣ እንደ ፒራሚድ የሚታይበትም ጊዜ አለ። ከታች ከፒራሚዱ ወለል (እፅ በሎች) ጀምረን ወደ ላይ (ስጋ- በሎች፣ አዳኞች) ስንጓዝ፣ የእንስሳቱ ቁጥር እየቀነሰ ይሄዳል፣ ፒራሚዱ ቁንጮ ላይ የሚቀመጡት በአማካይ አካለ-ግዙፍ ናቸው። ምግብ ፒራሚድ ቁንጮ ላይ የሚቀመጡ አዳኝ እንጂ ታዳኝ ያልሆኑ እንስሶች ብቻ ናቸው። የሰው ልጅ ምንም አቅመ-ውስን ቢሆን፣ በእሳት ተጠቅሞ የምግብ ፒራሚድ ቁንጮ ለመሆን በቃ።

 በተጨማሪ የሰው ልጅ እሳትን ለብዙ ተግባር ለማዋል በቃ፣ እሳትም ከፍተኛ አገልግሎት ማበርከት ጀመረ፣ ለምሳሌ ሙቀት፣ ብርሃን፣ በተጨማሪም የሰውን ልጅ በእንቅስቃሴ ፍጥነትም ሆነ፣ በጉልበት ብዙ እጅ ልቀው የሚገኙ እንስሳትን ለምሳሌ አንበሳን፣ በእሳት በመጠቀም አሸናፊያቸው ሆኖ ዘለቀ። ሊያጠቁት የሚችሉ እንስሳትን ሁሉ በእሳት ችቦ በማባረር፣ የሚኖሩበትን ቦታ ሳር፣ ደን፣ በማቃጠል፣ የሰው ልጅ መቆሚያ መቀመጫ አሳጣቸው።

የእሳት ማላመድ (መቆጣጠር) ረዥም ጊዜ እንደወሰደ ይገመታል። በመጀመሪያ እሳት ካለበት አካባቢ እሳት ጭሮ መውሰድ፣ ከዚያም ጠንከር ባለ እንጨት ለስላሳ እንጨትን በማፋተግ ወይም ባልጩት እና ባልጩትን በማፋጨት (በገጠር እንኩቶ ለመብላት አስቴ ቡል፣ ቡል ተብሎ በሚታወቅ ስልት እሳት ማግኘት እንደሚችል) እሳት አፍልቆ፣ መጠቀም እንደጀመረ ይገመታል:: ከዚያም እሳት ሳይጠፋ ለረዥም ጊዜ ማቆየት ቻለ፣ ያም እሳቱን አዳፍኖ ማቆየት ስልት እንደነበረ ይገመታል፣ አሁን በገጠር አካባቢ እንደሚደረገው ሁሉ። ከዚያም ቀስ በቀስ በእሳት ከመጠቀም ባለፈ (አስፈላጊነት በዘለለ)፣ የሰው ልጅ ካለእሳት መኖር እየተሳነው እንደመጣ ይገመታል።

እሳት ለጥንት ዘመን የሰው ልጅ ያበረከተው ጥቅም

 ሰዎች ይኖሩባቸው በነበሩ ዋሻዎች ውስጥ፣ በእሳት ይጠቀሙ እንደነበሩ በብዙ አካባቢዎች ማስረጃዎች ተገኝተዋል። ዋሻዎችን በእሳት ማሞቅ በመቻሉ በላቀ መልኩ፣ የሰው ልጅ ከምድረ ሠቅ በጣም የራቁ ቀዝቃዛ አካባቢዎች (ምሳሌ ሰሜን አውሮፓ) መኖር አዳጋች ሳይሆንበት ቀረ።

ቅድመ ሰው እሳትን በመቆጣጠር ተግባር ጠላቶቹን መከላከል ስለቻለ፣ እንደዘመዶቹ ዛፍ ላይ ከመኖር ተላቅቆ፣ ሜዳ ላይ ሰፈረ ይባላል። መሬት ላይ መኖር ከተጀመረ ደግሞ፣ ሩቅ ስፍራን ለማየት በኋላ ሁለት እግሮች መቆም ግድ ይላል

የዱር እንስሳትን ለማደን እንዲያመቸው በእሳት አጋዥነት አባሮ፣ ወደተወሰነ በረት መሰል ጠባብ አካባቢ አስገብቶ ማጎር ይችል እንደነበረም ይገመታል። በእሳት አጋዥነት በተወሰነ ቦታ እንዲሰበሰቡ ያስገደዳቸውን፣ እንደ በግ እና ፍየል ያሉ እንስሳትን ነበር። በዚህ መንገድ ከታገዱት እንስሳት ጥቂቶች መክበድ፣ መውለድ፣ መዋለድ ጀመሩ። በዚህ ስልት ከታጎሩት እንስሳት ቀስ በቀስ ቀናዎች፣ አመለ-መልካሞች፣ ረጋ ያሉት፣ የተረጋጉት (በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያመቹት)፣ ደልዳሎች ሰውነት ሙሉ ሴቶች እና አውራዎችን እየመረጡ በማላመድ፣ እንዲራቡ ብሎም የበግ መንጋ መመሥረት እንደተቻለ ይገመታል። በዚህ ሂደት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተመረጡ፣ ረጋ ያሉ ወፍራም፣ በቀላሉ የሚሰቡ በጎች ተራቡ። አስቸጋሪዎች፣ አመለ-ቢሶች ታርደው ተበሉ ብሎ መገመትም ይቻላል።

 ከዛሬ 164ሺ ዓመት በፊት ጀምሮ የሰው ልጅ በእሳት በመጠቀም እደጥበባትን ያከናውን እንደነበረ ብዙ ማስረጃዎች ተገኝተዋል፣ ከድንጋይ ወይም ከጥርስ የተቀረጹ ጥቃቅን ምስሎች፣ ጌጣ ጌጥ፣ ከሸክላ የተሰሩ ቶፋ፣ ዋንጫ መሰል ቁሳቁስ፣ ወዘተርፈ። አንዳንዶች ቅርጾች በስእል የተጌጡ ነበሩ። ሆኖም የሸክላ ስራ በጣም የተስፋፋ፣ ከግብርና ጋር ተያይዞ ከ10ሺ ዓመት ገደማ ወዲህ እንደሆነ ተረጋግጧል።

 ከ400ሺ ዓመት በፊት እንጨት አሹሎ በመለብለብ፣ ጠንከር ያለ ሹል ጫፍ እንዲኖራቸው አድርጎ የአደን መሳሪያ አበጅቶ ይጠቀም እንደነበረ በጀርመን አገር በምትገኝ አንድ መንደር መረጃ ተገኝቷል።

 በደቡብ አፍሪካ ከ164ሺ እስከ 72 ሺ ዓመታት በፊት በእሳት በመጠቀም፣ ሲልከሪት (silcrete) በመባል የሚታወቅ በእሳት የሚገራ ድንጋይ ማደኛ ቀስት እና ድግን ይሰራ እንደነበር ማስረጃ ተገኝቷል። በሰው ልጅ ረጅም የባህላዊ ለውጥ ጉዞ የእሳት ሚና በጣም ጉልህ ነው። እሳት የሙቀት ምንጭ፣ ከጠላት የመከላከል አቅም አጎልባች፣ ምግብ ለማደን ብሎም የአዳኝነት ባህልን ለማዳበር፣ ካለሙቀት ለመወረር የማይታሰቡ አካባቢዎች መውረር፣ እዚያ መኖር መቻል (የዓለም ቀዝቃዛ ቦታዎችን፣ በተጨማሪ እሳት በሚያበረክተው ብርሃን የስራ ጊዜን ማራዘም መቻል በባህላዊ ለውጦች ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው መገመቱ አያዳግትም።

እንዲሁም በሰው ልጆች ማህበረሰብ ውስጥ የስራ ድርሻን፣ ክፍፍልን ለመመስረት ከፈጠሩ ሁኔታዎች በእሳት መጠቀም አንዱ ሁኔታ እንደነበረ ይገመታል። በሂደት እሳትን የመቆጣጠር አቅም/ ክህሎት ያካበተ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ከሌሎች ክህሎት ካላካበቱ የተሻለ ስልጣን እንደነበረው ይገመታል። በተጨማሪ በእሳት መጠቀም መቻል ማህበረሰቡን በተወሰነ አካባቢ እንዲሰባሰብም ረድቷል ይባላል። አንድ አካባቢ ተሰባስቦ መገኘት ደግሞ፣ አብሮ በህብረት ተግባራትን የማስተናገድ ሁኔታ ያመቻቻል።

 በአጭሩ የዱር እንሳሳትን አባሮ በረት መሰል አካባቢ እንዲሰበሰቡ ማድረግ፣ ጦር መሳሪያ፣ ኪነጥበብ (የተጌጡ ማሰሮዎች፣ ምስሎች፣ ወዘተረፈ)፣ ምግብ ማብሰል፣ ቁሳ ቁስ መፈብረክ፣ በቀዝቃዛ አካባቢዎች መስፈር መቻል፣ አንድ አካባቢ መኖር መቻል፤ እሳት ለቴክኖሎጂ እመርታዎች ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደነበረው ማሳያ ምልክቶች ናቸው ብሎ ለመገመት ያስችላል።

እሳት እና የኢንዱስትሪ አብዮት ቅድመ ኢንዱስትሪ አብዮት የነበሩ የኃይል ምንጮችም ውስን ነበሩ፣ ለምግብ ማብሰያ፣ ለብረት ማቅለጫ፣ ለብርድ መከላከያ፣ ወዘተ፣ እንጨት ነበር የሚያገለግል። በቅርብ ጊዜ ማለት በ18ኛው ምዕተ ዓመት በተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮት እሳት ወሳኝ ሚና ነበረው።

አንድ ዓይነት ኢነርጂ ወደ ሌላ ዓይነት ኢነርጂ እንደሚቀየር ብንገነዘብም፣ ያንን ግንዛቤ ወደ እውቀትነት መንዝረን ለመጠቀም ሳንችል ብዙ ዘመናት አለፉ። ለምሳሌ አንድ ባህላዊ ምድጃ ላይ ውሃ ለማፍላት በአንድ በመግላሊት በተከደነ ቶፋ ውስጥ ብንጥድ፣ ውሃው ሲፈላ፣ የቶፋው መግላሊት (ክዳን) መዝለል እንደተመኘ ሁሉ፣ ከፍ ዝቅ፣ ብቅ ጥልቅ፣ ማለት ይጀምራል። መግላሊቱንም የሚያንረው (የሚያንቀሳቅሰው) በውሃ ሙቀት መንስዔ የተገኘ የእንፋሎት ኃይል ነው። ስለሆነም ከእንጨት ሙቀት (እሳት) የተገኘ ኃይል ወደ እንፋሎት ኃይል ተመነዘረ ማለት ነው። የእንፋሎቱን ኃይል ደግሞ ወደ መግላሊት ማንቀሳቀሻ ኃይል፣ ወደ እንቅስቃሴ (movement) ተቀየረ። እንግዲህ ይህንን አስተውሎ፣ አጢኖ፣ አንድ ዓይነት ኢነርጂ (ሙቀት) ወደ ሌላ ዓይነት ኢነርጂ (እንቅስቃሴ) መቀየር መቻሉን ያመለክታል። ይህን በማስተዋል ነበር በእንፋሎት የሚንቀሳቀሱ ሞተሮች (የእንፋሎት ሞተሮች) የተፈበረኩ እና ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ።

በእንፋሎት በሚንቀሳቀስ ሞተር በመጠቀም ፈርጀ-ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ስለተቻለ፣ የእንፋሎት ሞተር አገልግሎት እንደ ወረርሽኝ ከአንድ ዓይነት ተግባር ወደ ሌላ ዓይነት ተግባር በቀላሉ ዘመተ፣ ተሰራጨ። ለተለያዩ የሰው እና የዕቃ ማጓጓዣዎች (ትራንስፖርት)፣ ለሽመና ተግባር፣ ለድንጋይ ፈለጣ፣ ለመሬት ቁፈራ፣ ወዘተ፣ በእንፋሎት በሚንቀሳቀሱ ሞተሮች ያገለግሉ ጀመር። በእንፋሎት ኃይል የተንቀሳቀሰው የመጀመሪያው ባቡር እንግሊዝ አገር የተጓዘ ከድንጋይ ከሰል ማዕድን አካባቢ ሃያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ የባህር ወደብ ለዚሁ ተግባር በተዘረጋ የብረት ሃዲድ ላይ ነበር። የተዘረጋው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትም የድንጋይ ከሰል ማጓጓዝ ነበር። ከዚያም በባቡር ለተለያዩ ጉዞ እና የእቃ ትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲውል ለምን አይደረግም በሚል አሳብ ተጢኖ በ1830 በዓለም ላይ የመጀመሪያው የንግድ ባቡር መስመር ኩባንያ ተመሰረተ። ከዚያ ሃያ ዓመት በማይሞላ ዘመን ውስጥ በውሃ እንፋሎት ኃይል፣ ከእንፋሎት (በእሳት ከፈላ ውሃ) በተገኘ ኃይል፣ ባቡር በተለይ አውሮፓ ዋናው የትራንስፖርት አስተናጋጅ ተደረገ።

የሰው ልጅ እሳትን አላምዶ የሰው ልጅን ፍላጎት ለማሟላት ማብቃት ብቻ ሳይሆን፣ ያልተፈለገ አደጋ በእሳት መንስዔ ሲከሰትም የመቆጣጠር ስልት አዳብሯል፣ ያም በውሃ በመጠቀም ነው። ለመሆኑ እሳትን በውሃ የማጥፋት ሳይንሳዊ መሰረቱ ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ መልሱ እነሆ።

 የሰው ልጅ እሳትን ከሚቆጣጠርበት አንዱ እና ዋናው መንገድ፣ በውሃ ግብአትነት በሚተገበረው እሳትን የመቆጣጠር ዘዴ ነው። “ለመሆኑ እሳት ውሃን እንዴት ነው የሚያጠፋ?”

ውሃ በብዙ መንገዶች እሳትን ለማክሰም ይችላል። አንዱ እና ዋናው እሳትን ወደ እንፋሎትነት የሚያገለግለው የሙቀት መጠን፣ የእሳቱን ኃይል/ ኢነርጂ (energy ስለሚቀንሰው ነው። ውሃ ደግሞ ከመፍላቱ በፊት ከፍተኛ ሙቀት አምቆ መያዝ ይችላል፣ ያም ሌሎችን ፈሳሾች ከሚያፈላው ኃይል በጣም የላቀ ነው፣ ማለት ውሃን ለማፍላት የሚያስችለው ኃይል በጣም ከፍተኛ ነው።

 ውሃ ሲረጭ ውሃው ስለሚተን፣ ብዙ ቦታ ይይዛል፣ ስለሆነም ከእሳት ነበልባል ጋር የሚገናኘው እንፋሎት ከውሃ የላቀ ይዘት ይኖረዋል። እንዲሁም እሳት ለማጥፋት ውሃ በጉም መሰል መልክ ሲረጭ፣ ብዙ የውሃ ነጠብጣቦች ሆኖ ነው ወደ ነበልባሉ የሚላክ። ነጠብጣቦቹ፣ ከሚፈስ ውሃ በብዙ እጅ በላቀ መጠን ከእሳት ነበልባል ጋር ይገናኛሉ። የነጠብጣቦች ቁጥር በጨመረ መጠን፣ ከነበልባል ጋር የሚገናኘው እንፋሎት በጣም እየጨመረ ይሄዳል።

ከላይ እንደተጠቀሰው በመሰረቱ ውሃ ሲተን ወደ ጥቃቅን ነጠብጣቦች ተቀይሮ እንደ ጉም ሁሉ የአየር አካል ይሆናል፣ የውሃ ፈሳሽነት ባህሪው በሙቀት ኃይል ወደ ተናኝነት ባህሪ ይቀየራል። ይህም የሚሆነው የውሃ ሞሌኪውሎች በእሳት ኃይል ስለሚራራቁ ነው (ይገፋፉ እና ይራራቃሉ ብሎም ብዙ ቦታ ይሸፍናሉ)። የግፊቱ ኃይል የሚገኘው ከእሳት (ሙቀት) ነው። ሙቀቱ በጨመረ መጠን መገፋፋቱ ይጨምራል፣ ብሎም የሞሌኪዮሎች እየተራራቁ መሄዳቸው፣ ሲደመሩ የነጠብጣቦች (እንፋሎት) መራራቅ ይሆናል። ጥቃቅን ነጠብጣቦች በተራራቁ መጠን ደግሞ የሚሸፍኑት ቦታ በፊት ከሸፈኑት በብዙ እጅ እየላቀ ይሄዳል።

 ስለሆነም እንፋሎት በከፍተኛ ሙቀት አካባቢ እየተለጠጠ ይሄዳል (የሚሸፍነው ቦታ ይጨምራል)። ለምሳሌ 212°F (100°C) አንድ ሊትር ውሃ ብንወስድ፣ 1.7 ጊዜ ተለጥጦ ውሃ ከሚሸፍነው እሳት አካባቢ፣ በ1.7 እጅ የላቀ ይሆናል፣ ሰፋ ያለ በእሳት የሚጋይ ቦታ ይሸፍናል። ሙቀቱ 500°F (260°C) ከሆነ 2,400 ጊዜ ይለጠጣል፣ ማለት ውሃ ከሚሸፍነው 2,400 የላቀ በእሳት የሚጋይ ቦታ ይሸፍናል፣ ሙቀቱ ወደ 1,200°F (649°C) ከፍ ቢል፣ 4,200 ጊዜ በላቀ መጠን በእሳት የሚጋይ ቦታ ይሸፍናል።

 በዚህ መንገድ ለምሳሌ 600ሊትር ውሃ ጉም አስመስለን ወደ እሳት ብንረጭ፣ እና የእሳቱ ሙቀት 500°F (260°C) ቢሆን፣ በአንድ ደቂቃ ውስጥ 570 ሊትር ውሃ ይተናል፣ ይህም ወደ 1359 ሜትር ኩብ እንፋሎት ይቀየራል፣ ያም 1359 ሜትር ኩብ ቦታ ይሸፍናል ማለት ነው። ይህም 15ሜትር ወርድ፣ 3ሜትር ከፍታ እና 30 ሜትር ርዝመት ያከለውን ክፍል ሙሉ በሙሉ እንፋሎት ይሸፍነዋል ማለት ነው። ስለሆነም በ570 ሊትር ውሃ የመጠነኛ ክፍል እሳት በአንድ ደቂቃ ለማጥፋት ይቻላል ማለት ነው። እሳቱ የሚጠፋም፣ የሚቃጠለው አካል ከኦክሲጅን ጋር ለመገናኘት ሲሳነው ነው፤ የኦክሲጂንን ቦታ ውሃ ይወስደዋል፣ ውሃ በነዳጁ እና በኦክሲጂን መሃል ተጋርዶ ኦክስጅን እና ነዳጁ (እንጨት ሊሆን ይችላል) እንዳይገናኙ ያደርጋል።

በተጨማሪ ለእሳት የተዳረጉ ፈሳሾች፣ ውሃ ሲጨመርባቸው ይበረዙና፣ የመቀጣጠላቸው አጋጣሚ በጣም ይቀንሳል፣ የውሃ መጠን በጨመረ ቁጥር የፈሳሾች የመቀጣጠል እድል፣ አጋጣሚ እየቀነሰ፣ እየመነመነ ይሄዳል።

 6. መደምደሚያ

 የዚህ ጹሑፍ ዋና ዓላማ በእሳት ትረካ ውስጥ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን ማኸዘብ ነው። በጽሑፍ ውስጥ ሳይንሳዊ ሂደቶች ምን፣ ምን፣ እንደሚመስሉ አንዳንድ መረጃዎች፣ ትንተናዎች ቀርበዋል፣ ለምሳሌ እንጨት እንዴት የእሳት ምንጭ እንደሚሆን፣ እሳትን በውሃ ለማጥፋት እንዴት እንደሚቻል፣ ወዘተረፈ፣ ሳይንሳዊ ትንተናዎች ሰፍረዋል። ይህም ቀን ተቀን የምናያቸውን ኩነቶች ሳይንሳዊ ሂደት ለመረዳት ያስችለናል።

 ለየት ባለ መልኩ፣ የሰው ልጅ እንዴት ቀስ በቀስ እሳትን ለማላመድ፣ እንዲሁም የሰው ልጅ የዱር እንስሳትን በአንድ አካባቢ እንዲሰበሰቡ ማድረጉ፣ የተሰጡት ሎጂካዊ አስተያየቶች/ ግምቶች፣ ሳይንስ በቂ መረጃ ያልተገኘላቸው ኩነቶች እንዴት እንደሚገመቱ ያመለክታል።

 ትረካው አንዳንድ መረጃዎች እንዳሉ ይገልጥ እና መረጃዎቹ እንዴት እንደተገኙ አያብራራም፣ ሳይንሳዊ ትንተናን አያበረክትም። ያም ያንን ክፍተት የማወቅ፣ የመረዳት ጉጉት በአንባብያን ጭሮ፣ ተጨማሪ ሳይንሳዊ ግንዛቤን የመሻት ምኞት ግፊት ያደርግ ይሆናል የሚል በጎ ምኞት አለኝ።

 በተጨማሪ የሰው ልጅ በሩቅ ምስራቅ ውቅያኖስ አቋርጦ አውስትራልያን እና የአካባቢ ደሴቶችን እንደወረረ ይገልጣል። ያም ውቅያኖስን እንዴት ለማቋረጥ ቻለ፣ ምን ምን ዓይነት ጀልባዎች ነበሩት፣ የሚጓዝበትን አቅጣጫ እንዴት ነበር ለማወቅ የቻለው፣ የሚል መሰል ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። ስለሆነም ተጨማሪ መረጃ የማግኘት ምኞት ይጭር ይሆናል።

ብዙ ግለሰቦች ጽሑፎችን ለንባብ የማያቀርቡ፣ እተች ይሆናል የሚለው አባዜ እየገረገራቸው ይመስለኛል። ይህን እይታ አስወግዶ፣ በልዩ ልዩ ተግባራት የተሰማሩ ሁሉ እውቀታቸውን፣ ተሞክሮዎቻቸውን፣ ለአንባብያን የማካፈል/ የማበርከት ግዴታ አለባቸው የሚል አስተያየት አለኝ። በተጨማሪ ይህ ጽሑፍ ሌሎች ግለሰቦች በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲሳተፉ ይጋብዝ ይሆናል። በዚህ መንገድ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ዳብሮ፣ አላስፈላጊ ወይም ትክክለኛ ይዘት የሌላቸው አስተያየቶች፣ እምነቶች ሊወገዱ ይችላሉ። ይህንን በማጤን የተለያዩ የሳይንስ ባለሙያዎች የቀን ተቀን ሁኔታዎችን፣ ኩነቶችን፣ የሚያብራሩ፣ ሳይንስን ለማኸዘብ ያለሙ ፅሑፎችን በማዘጋጀት ለአንባብያን ሳይንሳዊ ትንተና የማቅረብ ፍላጎት ይጭር ይሆናል የሚል ቀና እምነት አለኝ። ያም ሳይንሳዊ አስተሳሰብን እንደሚያዳብር አያጠራጥርም።

 ሳይንሳዊ አስተሳሰብ እና የሳይንስ ውጤት የሆነው ቴክኖሎጂ፣ ለሰው ልጆች ብልጽግና ተለዋጭ (ተኪ) የሌላቸው ግብዓቶች ናቸው። ሳይንስ ይስፋፋ! ድህነት ይጥፋ ! ሳይንስ ይለምልም! ድንቁርና ይውደም!

ማስታወሻ፣ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የተጠቀሙባቸውን ዋቤ መጻሕፍት በዝርዝር አቅርበዋል። ይህም በአማርኛ የተዘጋጁትን ከየት ወደ የት (2011) እና የሕያው ፈለግ (2010)፣ የተሰኙትን የራሳቸው ሥራዎች የሚጨምር ሲሆን እንደ ጁሊ ፓውሳ እና ጆን ኪሊ፣ ጃሬድ ዲያመንድ፣ ዩቫል ሃራሪ የመሳሰሉትን ምሁራን ሥራዎችም በሚገባ አመልክተዋል።

የመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top