አጭር ልብወለድ

የምፅዓት ቀን ዘጋቢው

አዲስ አበባ በውርጫማ ቀዝቃዛ አየር ቆፈን ያሲዛል:: ዝናብ ያዘለው ደመና እንደ ፊኛ ከህዋው ላይ እየተንገዋለለ የማለዳዋን ጀንበር መጋረድ ችሏል:: እየተቆራረጠ የሚወርደው ካፊያ የአየር ሁኔታ ተንባዮችን ሳይቀር ሳያሳስት አይቀርም:: ብራ ሲባል የሚዘንበው፣ ይዘንባል ሲባል ብራ የሚሆነው የአየር ሁኔታ ለይቶለት አዲስ አበባን ጭፍና ጋርዷታል::

የቀጣዩን ቀን የአየር ትንበያ ባልሰማም ነዝናዛ እያሉ የሚጠሩት ችክ ያለ ካፊያ ዝናብ የሚቆም አይመስልም:: ከትንበያ ውጭ የሆነው የአየር ሁኔታ ውቧን ከተማ አፍዝዟታል፤አደንዝዟታል::

በየምስራቅ ኢትዮጵያ ጠረፍ ዶሎ አዶ እንደ አዲስ አበባ በጭጋግ የተከበበ ሰማይና ችክ ያለ ነዝናዛ ዝናብ እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ:: ከአዲስ አበባ 950 ኪሎ ሜትር ርቀት የሀሩር ክልል ቆዳን የሚያደርቅ ጠራራ የፀሀይ ሙቀትና እንደረመጥ የሚያቃጠል የአሽዋ አቧራ እንደሚጠብቀኝ አውቅ ነበር:: ለዶሎ ኦዶ እንግዳ ብሆንም የደቡብ ምዕራብና የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያን ለሰሀራ ሀሩር የተጐራበቱ ጠረፋማ አካባቢዎች ለፀሀይ እጅግ የቀረቡ ናቸው::

 ከምስራቅ አፍሪካ የርግብ አዙሪት ጋር የሚራገበው ሰሞነኛ ዜና በዶሎ ኦዶ ምን ሊመስል እንደሚችል አንሰላሰልኩ:: የምስራቅ አፍሪካ አዙሪት ማሳያ ሀሩር ምድረ በዳ ዶሎ አዶ ጦርነትና ርሃብ የሚያሳድዳቸው የሶማሊያ ስደተኞች ደሴት ነው:: የሰው ልጅ ሰቆቃ ተዘርቶ እንደበቀለ ቀድሞ ተነግሮኛል:: የሰው ልጅ ስቃይ የማይቆመው ለምንድን ነው? ብለው የሚጠይቁበት የሙከራ ትዕይንት በዶሎ ኦዶ እንደወረደ መገናኛ ብዙሃን ባለማቋረጥ እያናፈሱት ነው::

ጊዜ እየጠበቀ ሳይታክተው የሚመላለሰው ድርቅና ርሃብ፣ ድንገት የሚፈነዳው አይታሰቤ ጦርነትን ደጋግመው የመዘገብ አጋጣሚ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እኔም ተረኛ ሆኜወደ ዶሎ ኦዶ ለመዝመት ተዘጋጅቻለሁ:: የርሃቡን ቀጠና እንደ ምዘግብ ከሰማሁ ጀምሮ ጉዞው እንደ እዳ ከውስጤ ይመላለሳል::

 ሁኔታው አንጋፋ ባልደረቦች በሻይ ቡና ወግ የሚተርኩልንን፣ ይፋ ያላደረጓቸውንና ያልፃፏቸውን የዘገባ ታሪኮች አስታወሰኝ:: በይፋ ከሚዘገበው ዜና ጀርባ በሳቅ ልብን የሚያፈርሱ አጋጣሚዎች በሻይ ቡና እያወራረዱ የሚተርኩት ጋዜጠኞቹ ጉድ የሚያሰኙ እውነት ያዘሉ ገድሎችን ለግላቸው አድርገዋቸው እንደቀሩም ይናገራሉ:: ብዙ ህዝብ መስማት ያለበት የታሪክ እፍታ የሆነ ዜና በየሻይ ቡናው ስብሰባ እንዲሁ እንደዋዛ ተበትነው ይቀራሉ:: የመዘገብ ነፃነት ደዌ ምክንያት ሁኖ አንጋፋ ጋዜጠኞች እያዩና እየሰሙ ያልዘገቧቸው የኢትዮጵያ ታሪክ አንኳር ጉዳዮች በእርግጥም አስደማሚ ናቸው:: ይህ ሲታሰብ በአንባገነኖች ዙሪያ እንደሚገኙ ጋዜጠኞች ያኽል በህሊና ዕዳ የተያዘ አይኖር ይሆናል::

ከእለታት በአንድ ማለዳ ከተለመደው የሻይ ቡና ስብስባችን፣ ጋዜጠኞች ከዘገባ የተረፉ ገጠመኞቻችንን በደርዘን እየቸረቸርን ስላልተዘገቡና በሻይ ቡና ውይይታችን ስለሚነሱት እፍታ ዜናዎች አስፈላጊነት አንስተን አወራን:: አንድ ትውልድ ያኽል በጋዜጠኝነት ሙያ የዘለቀው ባልደረባዬ በፌዝ ሳቅ እየተመለከተኝ እንዲህ አለ:: “ባይዘገብም ጊዜ የሰጠው ሀበሳውን ያየ፤ የሰማውን ሀጢአት አንድ ቀን ይፅፈው ይሆናል:: ዜና ባይሆን ለታሪክ ግብአት መዋሉ ያፅናናል:: ከዜና መማር የሚኖርብንን ከታሪክ ለመማር ከተገደድን ምን እናደርጋለን? ያውም ከታሪክ ለመማር ከቻልን! አለመታደል ሆኖ ዜና ስራ ላይ የማይውልበት አገርና መንግስት ባለበት አገር ጋዜጠኞች ሆነን ከእውነት ጋር ተጣልተናል:: አንዳንዱን ዜና በብዙሃን መገናኛ ሳይሆን እንደዋዛ በየክበቡና መሸታ ቤቱ ባክኖና ተልከስክሶ ሰምተነው ያልፋል:: እውነትን የመደበቅ አባዜ የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ታሪክ ሳይሆን ይቀራል?!

 “አንድ እውነት የማረጋገጥልህ የእኛ ጋዜጠኝነት ጥቂቶች ናቸው እንደ ተልዕኮ ቆጥረው የተሰውለት:: ሌሎቻችን ግን ሸሚዝ እንኳ መቀየር ተስኖን፣ በየኮክቴሉ እያንጦለጦልን የገዥዎቻችን ሎሌ ሆነን ከራሳችን ጋር ሳይቀር ተጣልተናል::

 የአምባገነኖች ቃል አቀባዮች ከሌሎች ቀድመው ራሳቸውን ይመራመራሉ :: ከእምነቱ እና ከሙያ ስነ – ምግባር ውጭ በሆነ ኤዲቶሪያል ታስሮ አልንቀሳቀስ ያለውን ጋዜጠኛ ቤቱ ይቁጠረው::

 ብዙው ነገር በሙያ ስነ ምግባር መመሪያ ይመካኛል:: በህብረተሰብ ግንባታ መሰማራቱን ዘንግቶ የአምባገነኖች መማሪያ፣ የሀቅና የዕውነት ቀበኛ የሆነው ጋዜጠኛ ነኝ ባዩ እውነተኛ ጋዜጠኞችን መወከሉ ጥያቄ ሆኖ አብዛኛው በሙያው ውሰጥ የተሰማራ ከሙያዊ ተልዕኮ የበለጠ “እንጀራ” ከሙያ ተልዕኮና መመሪያ በላይ ትኩረት ይሰጠዋል::

እርግጥ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዘውዳዊው ስርዓት ጀምሮ ጋዜጠኛ የነፃነት ጠበቃ እንደሆነ አይታመንም:: እውነት፣ ፍትህ እና ነፃነትን ለማንሣት ዳርዳር ያሉ ጋዜጠኞችም ተጉዘዋል:: ብርሃኑ ዘሪሁንና በዓሉ ግርማ ለሙያው ዘብ መቆማቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ይታወቃል:: ስለ ነፃነት ማንሳት በስለት እንደመጫወት በሚቆጠርባት አገር እውነትና ርትዕን የፈለገ ጋዜጠኛ ነውረኛ ተደርጐ ነው የሚታሰበው:: ነፃነትን ፍለጋ በሽምቅ ውጊያ ስልጣን የያዘው መንግስት የነፃነት ጥያቄ የሚጐረብጠው፣ የፕሬስ ቀበኛ መሆኑ የዚህች አገር ጋዜጠኝነት እንቆቅልሽ ነው:: ብዙ ተስፋ፣ ብዙ ተመኘን፤ ነፃነት ተዘርቶ አልበቅል አለ:: ወይም ነፃነትን ዳዋ ውጦታል:: ለነፃነት የተከፈለው መስዋዕትነት እንደመከነ እንሰማለን:: ትክክለኛው በፍትህ የመዘገብ ቀን እስካልመጣ ጥያቄው ምላሽ አያገኝም::

 “እኛ የጦር አለቆችና አምባገነን መሪዎች ፀሀፌ ትዕዛዝ ሆነን እንጅ እንደ ጋዜጠኛ በምንሰራበት ብዙሃን መገናኛ በህዝቡ ውስጥ ያለውን እምነት ገለፀናል፣ ሙያችን በአግባቡ ተውጥተናል:: የሚል እምነት ያለው የለም:: እርግጥ ነው፤ ጋዜጠኝነት ነፃነትና ፍትህን የመፈለጊያ መሣሪያ ነው:: እኛ ግን ከፍትህ ጋር ለማበር አጋጣሚ አልነበረንም:: ምክንያቱም የአምባገነኖች ተላላኪና ነፃነት ከልካዮች ነን:: ይህ ሁኔታ አብዛኞቻችን እንደንስሃ የምንናዘዘው ነው::

 የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት እንዲህ አሉ ይባላል:: “ፍትህ የሚገኘው በትክክለኛው እና ስህተት በሆነው መካከል መሀል ሰፋሪ በመሆን አይደለም:: ከዚያ ይልቅ ትክክል የሚሆነውን ነገር ከማንኛውም ሁኔታ ፈልጐ በመያዝ ግፍን በመዋጋት ነው::” እኛ ግን በተቃራኒው ትክክል የሆኑ ፍትህን የሚያመጡ ዘገባዎች የማንገዋለል ተግባር እናከናውን ነበር:: ፀጉሬን የጨረስኩበት ከአንድ ትውልድ በላይ የለፋሁበት ሙያ ራሱ ከነፃነትና ከእውነት ጋር ድብብቆሽ የተጫወትኩበት፣ ህሊናዬ እየከሰሰኝ ጊዜየን የገፋሁበት የሙከራ ዘመን ነበር:: ለዚያውም ቁሳዊ ሀብት የተነፈግሁ ድሃ ሁኘ::

 የኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ አጭር ታሪክ ይኽው ሳይሆን አይቀርም:: ጋዜጠኝነት ከተቀደሰ ህዝባዊ ተልዕኮው በተቃራኒ “እንጀራነቱን” እና ለአምባገነኖች አድረን ኑረን አርጅተንበታል:: ከጥቂት ሰማዕታት ውጭ ብዙዎቻችን የማይሸጥ የማይለወጠውን ነፃነት ተነጥቀን ነው የኖርነው፤ ነፃነት ብሎ ዘራፍ ያለ ደግሞ እንደመፅናኛ የሚቆጥረውን በዋጋ ርካሹን ኒያላ ሲጋራና ካቲካላውን እየኰመኰመ መኖርን እንኳ እንደሚከለከል ያውቀዋል::

ቀለድክ አትበለኝ እና ለድሃው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ትልቁ ትርፍ ካቲካላ ፣ ርካሾቹ ኒያላና ግስላ ሲጋራ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂት ቢሆኑም ከማንም ይልቅ ስለነፃነት ጠንቅቀው የተረዱ ባለራዕይ ጋዜጠኞች ነበሩ:: ነፍሳቸው ለሙያው ያደረች ብፁእ ጋዜጠኞች ነበሩን:: ብርሃኑ ዘሪሁን በአፓርታይድ ጊዜ ስለደቡብ አፍሪካዊያን ሰቆቃ በጋዜጣ ኢ – ፍትሀዊነትን ይዋጋ የነበረ ጋዜጠኛ ነበር:: ነፃነትን እንደ ፅንስ ያረገዙ ነፃነት ናፋቂ ጋዜጠኞችም ጥቂት አልነበሩም::

ወደ ዶሎ ኦዶ የሰቆቃ ቀጠና እንደ ምጓዝ ለውዷ ሚስቴ መንገር ነበረብኝ:: የሆዴን ሁሉ አንድ ሳላስቀር ዝርግፍ አድርጌ ነው የማካፍላት:: “እየቃዥህ ነው?” በማለት እንደ መሳቅ እያለች አፌዘችብኝ:: እርግጥ ነው፤ ድርስ ነብሰጡር የሆነችውን ሚስቴን ብቻዋን ጥዬ መሄድ በተለይ አልተዋጠላትም:: ለእርሷ ውሳኔዬ ትክክል አልነበረም::

 ጉዞ ህይወት ነው ብሎ እንደሚያስብ ጋዜጠኛ የእኔ ውሳኔ የሚቀለበስ አልነበረም:: የልጅ በረከት በእርሷ አማካኝነት እንደሚያደርሰኝ ሳስብ ለሚስቴ ያለኝ ፍቅርና ክብር ይጨምራል:: ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አባት መሆኔን ሳስብ በምጐናፀፈው የአባትነት ተፈጥሯዊ ምስጢር አማካኝነት ይመስላል ለተከታዩ ትውልድ ማሰብ ጀምሬአለሁ::

“እንደ ወፍ በየቦታው እየበረርክ ለቤተሰብህ ጊዜ የሚኖርህ መቼ ነው?” የሚደጋገመው የሚስቴ ጥያቄ ከውስጤ እያቃጨለ ወደ ዶሎ ኦዶ እንደምሄድ መናገሬን ተከትሎ ራሴን እስኪያዞረኝ ሁኔታው አጅግ አሳስቦኛል:: ከውብ ቁንጅናዋ በተቃራኒ ቁጣዋ አስፈሪ ገፅታ የሚያላብሳትን ሚስቴን በእንደዚህ አይነቱ ቅፅበት ስታዘብ እተክዛለሁ:: ሚስቴ ደጋግማ እንደምትለው እንደ ወፍ በየቦታው በውዴታ ግዴታ የሚበኑበት ሙያ ለቤተሰብ አብሮነት አዳጋች ቢሆንም መቸም ሁለት ወዶ አይሆንም እንዲሉ ነገሩ አስቸጋሪ ነው፡ ሆኖም ተልእኮ ነው:: “እንጀራም” ነው::

 እንደ ደመናማው የአዲስ አበባ የአየር ሁኔታ ሚስቴ ተቀዛቅዛለች:: አኩርፋለች:: እንደ ማለዳ ጀንበር ቤቱን ልዩ መንፈሳዊ ብርሃን የሚረጭበት ፈገግታዋ ከስሟል:: በሚስቴ ፈገግታ እንደሃይል እንደምሞላ የተገነዘብኩበት ወቅት ነው:: ቤታችን በአየር ሁኔታው ጋር ተደማምሮ ይበልጥ ቀዘቀዘ:: በኩርፊያ ወስጥ እንዳለች የቤት ኪራይ መድረሱንና የቤት አስቤዛ ማለቁን አስገነዘበችኝ:: የእኔ ሁኔታውን የማስረዳት ችግር ይሁን የእርሷ ሁኔታውን አለመቀበል የስራየን ፀባይ ደጋግሜ ባስረዳትም አልተግባባንም::

 ወደ ደሎ ኦዶ እንደምጓዝ ከተነገረኝ ጊዜ ጀምሮ ስለዚያ መከራን ስለተሸከመ ምድር አንሰላስያለሁ:: ወደ ስፍራው ከሚጓዘው የጋዜጠኞች ቡድን በአንድ ተሽከርካሪ እንደምንጓዝ ተነግሮኛል:: እኔ ጋዜጠኛ ሁኘ ከምስራበት ሬዲዮ ጣቢያ ሌላ አንድ የሱማሌኛ ቋንቋ ክፍል ባልደረባዬ አብሮኝ ይጓዛል::

ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በምድራችን ታይቶ የማይታወቀው ቸነፈርና መቅሰፍት በእርስ በእርስ ጦርነት በተጐዳው የሶማሊያ ህዝብ ላይ መከሰቱን ቢቢሲ ካወጀው ጊዜ ጀምሮ የዓለም መገናኛ ብዙሃን እምብዛም የማትታወቀውን የዶሎ ኦዶ ወረዳ የርሃብ መቅሰፍት ጋር ደጋግመው አንስተውታል:: በዚያ የርሃብ ሰቆቃ ምድር በእርግጥ ምን እውነት ይኖር ይሆን? ጥቂት እንዳሸለብኩ እየደጋገመ የሚቀሰቅሰኝ የመኪናው መንገራገጭ እረፍት ነስቶኛል:: በኩርፊያ የሸኘችኝ ሚስቴ ሁኔታ ምቾት አልሰጠኝም::

ባልደረባዬ ሰኢድ ቀድሞ የሚያውቀውን ተሽከርካሪው የሚያልፍበትን አካባቢ ስያሜ ይነግረኛል:: እኔ ግን ልብ ብዬ አልሰማውም ነበር:: የምዕራቡ ዓለም ዘጋቢዎች የሽልማት ምክንያት እንዲህ አይነቱ ክስተት ነው:: ጋዜጠኛነት በእርግጥ ሰብአዊ ቀውስ ሲከሰት ቀድሞ ማሳወቅና መፍትሄ ማፈላለግ ነው:: ሚሊዮኖችን የታደጉ ዘጋቢዎች ለምን አይሸለሙ? በሚያንገራግጨው የመኪና ጉዞ ሰመመን ውስጥ ከራሴ ጋር እያወጋሁ ነው:: ባልደረባዬ ሰኢድ ያወራኛል:: የሚለውን ሁሉ አልሰማውም:: የሶማሊያ የእርስ በእርስ ግጭት ተጠቂ ስለ ሚሆኑ ጐሳዎች የራሱን አስተያየት ጨምሮ ያወራኝ ነበር:: በተጫጫነኝ እንቅልፍ ውስጥ ሆኜ ከራሴ ጋር ነበር ብዙውን ጊዜ ያሳለፍኩት:: እኔ የምዘግበው ሽልማት አስቤ አይደለም:: ስለርሃብና ሰቆቃው፣ ስለተፈጠረው ችግር የመዘገብ ኃላፊነት አለብኝ:: ራሴን የሸለምኩባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ::

 የዶሎ ኦዶ ሰማይ የበራ ምጣድ መስሏል:: ይህ የርሃብ ቀጠና ነው የሚል ፅሁፍ የበራ ምድጃ ከመሠለው ሰማይ ላይ በምናብ ፃፍኩበት:: ሀሮራማውን ሰማይ አትኩሬ አየሁት፤ ለረዥም ጊዜ ዝናብ ያልዞረበት ሰማይ ጭው ብሏል:: ደመና ያልተጓዘበትና ያላለፈበት ሰማይ ስር ርሃብ መንደሩን ቀልሷል:: የዘገባዬ ርዕስ የእኔ አይደለም:: የምዘግብበት አቅጣጫ ተጠቁሞኛል:: የባልደረቦቼ የክበብ ጨዋታ፣ የሻይ ቡና ወግ፣ ከዘገባው በስተጀርባ ያልተነኩ ታሪኮች ሁኔታን አስታወሰኝ::

 በታዘዝኩት መሠረት የዘገባዬ ማዕዘን የዱቄትና ዘይት ራሽን እየታደለ ነው መሆን ነበረበት:: የርሃብ አዙሪት ተጨባጭ ታሪክ ግን እንደዚያ አይደለም:: እርዳታ ለመቀበል ርሃብ ቅስማቸውን ስለሰበራቸውና አቅም ስለነሳቸው፣ በርሃብ ስለዛሉ ሰዎች፣ ርሃብ በራሱ መንገድ አጐሳቁሎ ስለቀረፃቸው ህፃናት መናገሩ ነው ተጨባጭ…:: ርሃብን ዘጋቢ የመሆን እዳ ሸክሙ ከበደኝ፤ ሆኖም የማልናገረው እውነት መኖር እንደሌለበት ከራሴ ጋር ቃል የገባሁትም በዚሁ አጋጣሚ ነበር::

 በርሃብ አፅማቸው ስለቀረ፣ በቆዳቸው ብቻ በቆሙና ጉሮሯቸው ርሃብ ስላነቀው ህፃናት ምን ማለት ይቻላል? ራሴን ጠየቅኩ:: ከእናቶቻቸው ጉኛ የነጠፈ ጡት ጋር ስለሚታገሉ እንቦቀቅላዎች፣ ከንፈራቸው እንደ ኩበት የደረቀባቸው የቸነፈሩ ሰለባዎች… የተሳበ አንጀት፣ የተሰረጐደ ጉንጭ፣ የሚቆጠር የጐን አጥንት… አፅማቸው በቆዳቸው ብቻ ተያይዞ ርሃብ አንድ አይነት ቅርፅና ገፅታ የሰጣቸው ሰዎች ከዚህም- ከዚያም ይታያሉ:: የሚገርመው የሰው ልጅ መልክና ቅርፅ በስጋው የተገነባ መሆኑ ነው:: አንዳንዶች በዶሎ ኦዶ በድንኳን የተመሠረተ የበረሃ አይናቸው አትኩረው የሚማፀኑ ርሃብተኛ አይኖች፣ የሚንቀሳቀሱ አፅሞች ሁኔታ ያስጨንቃል::

 በቅዱስ መጽሐፍ የዮሃንስ ራዕይ የመጨረሻው ዘመን መቅሰፍት የተወከለበት ፈረስ ትንቢት በዶሎ ኦዶ እየጋለበ ይሆን? ስል አሰብኩ:: የሚገርመው ደግሞ ይህን ጉደኛ የምፅአት ቀን ትንቢታዊ ክስተት ከቦታው ተገኝቼ እየዘገብኩ ነው:: …

የአምላክን የቁጣ ጽዋዎች በምድር ላይ መፍሰስ ጀመረዋል:: ሰዎች ከስቃያቸው ብዛት ምላሳቸውን ያኝኩ ነበር:: ከህመማቸውና ከቁስላቸው የተነሣ የሰማይ አምላክን ተራገሙ…:: ከአህዛብ ከተሞች መፈራረስ የቀድሞው መቅሰፍት ርሃብ የሰውን ልጅ እንደ ትንኝ ሲያረግፈው መዘገብ ይረብሻል:: መዳኛ መድሃኒት የሚያገኝ ሳይሆን በሽታን የሚነግር ሃኪም፣ መፍትሄ የሚጠቁም ዘጋቢ እንደመሆን ያለ ቆሽት የሚያሳርር ባዶነት የለም አልኩት ለራሴ:: የአፍሪካ ቀንድ ርሃብና ጦርነት፣ ከምድር የሚፈሰው የእግዚአብሄር የቁጣ ፅዋዎች ምሳሌ ናቸው ማለት አይቻል ይሆን?

 አዲስ አበባን ከለቀቅኩ ነብሰ ጡሯን ሚስቴን ከተሰናበትኩ ሶስተኛ ቀኔን ይዥለሁ:: የሶስት ቀን ኑሮዬ ደግሞ ከምንጊዜውም በላይ በድብርት የተከበብኩበት የፅልመት ጊዜ ነበር:: ስለመከረኞች ለመዘገብ በመካከላቸው መገኘቴ አስጨንቆኛል:: ለቃለ መጠይቅ ዶሎ ኦዶ በሚገኙ የእርዳታ ሰራተኞች በኩል ሁለት ለሚራመዱ አፅሞች ጋር ተገናኘሁ:: እንደ ደከመውና በቆዳ ብቻ እንደተያያዘው አካላቸው ርሃብ ድምፃቸውንም ሰልቦታል:: ርሃብ ድምፅንም ሃይል ይነሳዋል? ለራሱ ያቀረብኩት ጥያቄ ነበር:: የሶማሌኛ ቋንቋ ክፍል ባልደረባዬ ሰኢድ ነበር አስተርጓሚዬ:: እነርሱ የሚሉትን እንዳላጋነነው እርግጠኛ ነበርኩ:: “ርሃብ ጉሮሯችን አንቆናል፤ አንደበታችን ዘግቶናል፤ እንዴት እንንገርህ? የእርዳታው እህል ዘግይቶ ነው የደረሰው:: አሁንም ምግብ በጉሮሯችን አይወርድም:: ስለገደለን ርሃብ ቅድመ ታሪክ ብንነግርህ ምን ትፈይድልናለህ?…” ደነገጥኩ:: ጠያቂው ሲጠየቅ ይከብዳል::

 “ከእንግዲህ አንኖርም፤ ሞትን እየጠበቅን ነው:: አንበላም፤ ከእንግዲህ አንራብም:: ሞት ከዚህ ሰቆቃ እንደሚገላግለን ተስፋ እናደርጋለን::” ሞት ከዶሎ ኦዶ የርሃብ ቀጠና መብለጡን፣ መሻሉን ማን ይነግረን ይሆን? የእኔ ጥያቄ ነበር::

በፖርሳዬ የያዝኩትን ደረቅ ብስኩት መቅመስ ተሳነኝ:: ለህይዎቴ ማቆያ ውኃ ከመጠጣቴ ውጭ አልራበኝም:: በእርግጥም በርሃብ ቀጠና እህል ትዝ አይልም:: አካሌም መንፈሴም ዝሏል:: ሰው የሚባለው ፍጡር በአካባቢው ክስተት ተፅእኖ ስር ይውላል ያለው ፈላስማ ማን ይሆን? በእውነትም በሀሩሩ ሙቀት የዛለው፣ በርሃብተኞች ሰቆቃ የተሰላቸው መንፈሴ ታውኳል:: የራሴ ፊት ገፅታ ከመመለከታቸው ከምመለከታቸው የአፀም ገፅታ የተለየ ለመሆኑ በአንዲት የዕርዳታ ሰራተኞች መኪና ስፖኪዮ መስተዎት ያረጋግጥኩበት አጋጣሚ ለራሴም አስገረሞኛል::

ለምሽት ዜና በተሟጠጠ ተስፋ የቆሙ ሁለት ርሃብተኞችን ቃለ ምልልስ ለይቼ አዘጋጀሁት:: ከእንግዲህ አንኖርም፤ አንበላም፤ አንራብም… ህዝቡን ከርሃብ መታደግ አልተቻለም::

የሰው ህይወት እያለፈ ዕርዳታ ብሎ ነገር “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኽ” አይነት ብሂልን የሚያስታውስ ነው:: የዶሎ ኦዶ ሰማይ እንደ ህዝቡ ተርቧል፤ እንደ ሀሩሩ ደረቅ ምድረ በዳ ቀዬ የደረቀ ነው:: ርሃብ እንዴት እየገደለ እንደሆነ ስመለከት ነው የዋልኩት…:: እኔም ራሴው የርሃብ ገፅታ የተዋረስኩና የተላበስኩ፣ አፅም የሆንኩ ያኽል ተሰምቶኛል:: በእርግጥ የርሃቡ ፈረስ ሲጋልብ ነው የዋለው:: የአምላክ የመጨረሻው ዘመን የቁጣ ጽዋ በአፍሪካ ቀንድ በእርግጥ እየፈሰሰ ነው?…::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top