ስርሆተ ገፅ

ዓለም አቀፍ እውቅና – ለኢትዮጵያ ፈንድቃ!

ከአገር ውስጥ አልፎ በተለያዩ አገራት በሚያቀርባቸው ኮንሰርቶች ተደናቂነትን ያተረፈ የአገር ባህል የጭፈራ ቡድን ነው – ፈንድቃ። የፈንድቃ ባለቤትና የቡድኑ መሪ ወጣት መላኩ በላይ የሙዚቃ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ጥበብ በአግባቡ ከማስተዋወቁ ባለፈ፤ ታሪኳን፣ ባህሏን፣ አልባሳቷን፣ የብሔረሰቦች ስብጥር፣ ህብር ያላት መሆኗን፣ በአጠቃላይ በውዝዋዜና ጭፈራ ውስጥ የተዋበች አገር መሆኗን አሳይቷል። በዚህም ታዋቂነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር እያደነቁ ጽፈውለታል። “አዝማሪ ክብር ሊሰጠው ይገባል” ባይ ነው። ለምን? ከምን አንጻር? በዚህ ጥያቄ መነሻነት ስለ ፈንድቃ አጠቃላይ ጥበባዊ እንቅስቃሴ እንዲያወጋን እነሆ ጋብዘነዋል።

መላኩ፦ ፊት አዝማሪ ቤት በሽልማት ነበር የሚሰራው እንደ ኮንሰርት ያሉ ትላልቅ መድረኮች አይዘጋጁላቸውም። ህዝቡ ከስራም ሆነ ከቤቱ ከፍቶትም ሆነ ተደስቶ ለመዝናናት ሲመጣ ለአዝማሪ በሚሰጠው ግጥም ደስታውንም ሆነ ብስጭቱን ወይም ሃዘኑን ይወጣል። ቁጭቱን ይገልጻል። የታመቀ ስሜቱን ፈታ ያደርጋል። አዝማሪና ተዝናኙ ልዩነት የላቸውም። ለብቻ የተከለለ መድረክ የለም። እየተቀባበሉ “ያዝ እንግዲህ …” ነው። ጥፋትም ይሁን ልማት ሁሉም ስሜቱን በነጻነት የሚጋራበት ነው። ስለዚህ አዝማሪ ቤትና አዝማሪ ሊከበሩ የገባል። ዛሬ ዛሬ ደግሞ እየዘመነ የመጣ ጥንታዊና ባህላዊ መዝናኛ ነው- ለኔ።

ታዛ፦ እንዴት ማለት?

መላኩ፦ ያለፈው፣ የአሁኑ እና የወደፊቱ ብቻ የማይባልበት የሚገርም ሳይንስ ያለበት ስጦታችን ነው። ባህላዊ ይባል እንጂ ለእኔ የረቀቀ ዘመናዊነት ያለበት ጥበብ ነው። ያለፈን ሳይረሳ፣ የአሁኑን ሳይፈራ፣ የወደፊትን ተንብዮ የሚኖር የመዝናኛ ጥበብም ነው። በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት ደግሞ የሚገርም ነው። እየተጠቀመበት፣ እየተደሰተበት ግን እየናቀው ያለ ነው። ባህላዊ ጭፈራ /አዝማሪ/ ቤት ትልቅ የጥበብ ማእድ ነው።

 ታዛ፦ ፈንድቃን መቼና እንዴት ጀመርከው?

መላኩ፦ እስክስታ ወይም ጭፈራ የጀመርኩት በእናቴ ሆድ ነው። ህብረተሰቡ ተቀበለኝ። ከህብረተሰቡ ጋር እለት በእለት ባለኝ መስተጋብር ከሚያገናኘኝ ስሜት ጋር በማዋሃድ እንደ አጋዥም፤ እንደ ስራ ፈጠራም እንደ ባህልም እንደ ህክምናም እየሆነኝ ጥበቡ ዛሬ ያለሁበት ላይ አድርሶኛል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተጉዤበት ጥበቡን እዚህ ደረጃ አድርሼዋለሁ። ፈንድቃን ከጀመርኩኝ ወደ 21 ዓመት ሆኖኛል። እዚሁ አሁንም እየሰራሁበት ያለሁበት ቤት ነው ፈንድቃ። ባለቤቶቹ ሌሎች ናቸው። ስሜቴን አይተው አስገቡኝ። ደመወዝ የለም። ማታ ማታ በሽልማት ነው እሰራ የነበረው። በጭፈራ ነው የገባሁት። አባቴን በልጅነት በሞት ስላጣሁ፣ እናቴም በቅርብ ስላልነበረች የሚንከባከበኝ አልነበረም። አንድ በጣም የምወዳቸው አሳዳጊዬም አረፉ.። በቃ ጎዳና ወጣሁ። እናም በረንዳ በማደር መራር ህይወቴን በጥበቡ እያዋዛሁ ገፋሁት። እስክስታዬን እየሰራሁ የማገኘውን የሽልማት ገንዘብ አብረውኝ በረንዳ ከሚያድሩ ጋር እየተካፈልኩ ነበር ህይወቴን መምራት የቀጠልኩት። ቀስ በቀስ ከፈንድቃ እድምተኞች ጋር እየተላመድኩ ስመጣ፣ ጭፈራዬም እየተወደደ ሲመጣ በቤቱ ማደር ይቻል እንደሆነ ባለቤቶቹን ጠየኳቸው። ፈቀዱልኝ። ማታ ቤቱ ሲዘጋ ባንኮኒ ስር ሳር ፍራሽ አንጥፌ መተኛት ጀመርኩ። ለሰባት ዓመት በዚያ ሁኔታ ኑሮዬን ገፋሁ። ከጭፈራ ስራዬ በተጓዳኝ ከ9ኛ ክፍል ያቋረጥኩትን የማታ ትምህርት ቀጠልኩ። ገቢዬን ለማሳደግም ቀን ቀን ሌሎችን እስክስታ የማስጠናት ስራ እየሰራሁ ቀጠልኩ። ከ12 ዓመት በኋላ ቤቱን ተከራየሁት። የዛሬ 11 ዓመት ማለት ነው። በቃ ህይወት ተለወጠ።

ታዛ፦ ቤቱን ገዛኸውና መስራት ቀጠልክ? በምን መልክ ተጓዝክ?

መላኩ፦ አዎአ! የውስጥ ህመሙን አውቀዋለሁ። ባህሉን፣ የህዝቡን አመለካከት እረዳለሁ። እንደገባሁበት አልከበደኝም። እዚሁ እየሰራሁ አሜሪካም ሆነ ሌሎች አገራት እየሄድኩ መመለስ ጀመርኩ። በነፃ እያጨበጨብኩ ነው የምሰራው። “ምናባቱ ሊሰራ መጣ?! ቤተሰብ የለው፣ ደመወዝ የለው፣ ምን ይሰራል?…” እያሉ የሚያንጓጥጡኝ ነበሩ። በዚያ ሰዓት ህልሜን መናገሩ መዳረቅ ነው። በፈረንጆቹ 2008 ቁጭቴንና ህልሜን የማሳካት ሄደቴን ጀመርኩ። “ሀ” ስልም ለአዝማሪው ደመወዝ መክፈል ጀመርኩ። በሌሎች ያልተደረገ ነው ይህ። የሰዉ ባህሪ ብዙ ነው። አዝማሪ ቤት ውስጥ “ስደበኝ” ብሎ የሚመጣ አለ። “እኔ ክብሬ ከፍ ያለ ነው” የሚል አለ። የሚሳደብ አለ። እዚህ ላይ አዝማሪው በሽልማት ነው የሚተዳደረው። የቤት ኪራይ አለበት። የሚያስተዳድራቸው ቤተሰቦች ሊኖሩት ይችላል። ለዚያ ደግሞ ሽልማት ማግኘት ይኖርበታል። ምን ቢተጋ ልግስና ያለው ከተዝናኙ ዘንድ ነው። ካልሰጠው አልሰጠውም ነው። ይህ ሃሳብ ሳይኖርበት በነጻነትና በፍቅር ሙያው ውስጥ እንዲዘልቅ ያደረኩት ነገር ነው ደመዎዝ። ደመወዟ ትንሽ ነች፤ ዓላማው ግን ተወደደ። ጨፋሪዎቹም ሆነ መሳሪያ ተጫዋቾቹ ውስጣዊ አቅማቸውን ማውጣት ጀመሩ። እኔም ኬሮግራፍ ማድረግ ጀመርኩ፣ ኮምፖዝ ማድረግ ቀጠልኩ፣ ኢንትሮ ብሪጅ የሚባለውን ነገር እየተካንኩት መጣሁ። ቅንብሩን፣ አንዱ ጭፈራና ዘፈን ከሌላው ጋር ተዋዝቶ የሚቀርብበትና ተከታታይነት ያለው የውህደት ሰንሰለት የሚፈጥርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቻልኩ። ቀጠልኩና ለቤቱ ህግ አወጣሁ። ቤት ውስጥ ሲጋራ ማስጨስ አቆምኩ። ለምን የሚል ጠያቂ ፈተና እየሆነብኝ እንደመጣ ሁሉ ይህንን የሚፈልጉ በዝተው ቤቱን መሙላት ጀመሩ። ይህ በሆነ በዓመቱ ኢትዮ ከለር የሚል ባንድ አቋቋምኩ። በፈረንጆቹ 2009 መሆኑ ነው። ዓላማው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ጭፈራ ማሳየትና ማዝናናት ነው።

ታዛ፦ ተቀባይነቱስ?

መላኩ፦ በጣም ቆንጆ። ፈንድቃ የህዝብ ነው፤ የእኔ አይደለም። በካሳንችስ 17 አዝማሪ ቤቶች ነበሩ። በልማት ምክንያት ሁሉም ፈርሰዋል። ፈንድቃ ብቻ ነው ያለው። ካሳንችስ ደግሞ ከጥንትም ጀምሮ መታወቂያዋ አዝማሪ ቤት የበዛባት መሆኑ ነው። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጭምር እየጠሩ የህዝቡን የልብ ትርታ የሚያደምጡበት ነበር። ሕዝቡ ራሱ ጥርጣሬውን በነጻነት የሚገልጽበት፣ ከሰላዮች ፍራቻ ራሱን ነጻ የሚያደርግበት፣ ሌላው ቀርቶ እህትና ወንድም ጭምር የማይተማመኑበትን ጉዳይ ጥበቡ መፍትሄ የሚሰጥበት ቦታ ነው። የህክምና ቦታ እንደማለት ነው። እሱን ነገር ለመጠበቅ ብዙ መስዋዕትነት ከፍያለሁ። መስዋዕትነቱ በረንዳ ከማደር ይጀምራል። ዛሬም ኮንዶሚኒየም ተከራይቼ ነው የምኖረው። ህልሜ ትልሜ ገና ነው። በልጅነት ልቦናዬ ጥበብን እግዚአብሔር ስለገለፀልኝ እሱን ጠብቄ መኖር ነው ፍላጎቴ።

 ታዛ፦ ከሌሎች ታዋቂ ባለሙያዎች ጋር የመስራት እድሉም ነበረህ?

መላኩ፦ በጣም። ከኢትዮ ከለር ባንድ በተጓዳኝ ያዘጋጀሁት “ፈንድቃ” የሚል ባንድ ለጉዞ የሚመች አይነት ነው። ነፍሳቸውን ይማረውና ከታዋቂው ሳክሲፎኒስት ጋሽ ጌታቸው መኩሪያ ጋር ብዙ አገር እየተጓዝን ሰርተናል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከጋሽ መሐሙድ አህመድ፣ ከጋሽ አለማየሁ እሸቴ፣ ከጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር ብዙ ሰርተናል። ከተለያዩ የውጭ ሰዎች የኮንተምፐራሪ ዳንስ ቫሌስ፣ ፎክ፣ ፍላሚንጎ ተጫዋቾች ጋር ሰርቻለሁ። ከኤምባሲዎች ጋር በትብብር በመስራት የሀገሬን ባህል አስተዋውቂያለሁ። ከጃዝ ጋር ተዋህዶ በመስራት ብቸኛው እኔ የሆንኩ ይመስለኛል። ዘመናዊነት ማለት ለእኔ ማንነትህን ጠብቀህ የሌሎች ጫና ሳያርፍብህ ተጋብተህ መውለድ የመቻል ስሜትን ማዋሃድ ነው። ያንን በጥሩ ሁኔታ ሰርቻለሁ ብዬ አስባለሁ። መርካቶ ምናለሽ ተራ የሰራሁት ስራ አለ። ሚስ አንደርስታንዲንግ የሚል ስራ አለኝ ፖለቲካቸውን፣ ሙስናውን የሚተች ስራ ሰርቻለሁ። የማህበረሰቡን ስሜት በጥበብ የሚያስተጋባ ስራ ነው። ጥበብ ነጻነቷን ማንም ሊወስድባት እንደማይችል አሳይቼበታለሁ።

ታዛ፦ ያንተን ቤት ፈንድቃን ከሌላው የባህል ጭፈራ ቤት የሚለየው ምን ነገር አለው?

መላኩ፦ 28 ዓመቱ ነው። አንድም ቀን ተዘግቶ አያውቅም። ዛሬ የሉም እንጂ ካሳንችስ ውስጥ የነበሩ አዝማሪ ቤቶች በየምክንያቱ ይዘጉ ነበር። ለምሳሌ በፆም ወቅት። ዘመናዊው ጃዝ ባንድ “ኢትዮ ከለር” ከተመሰረተ ወዲህ በቤቷ ሦስት ትውልድ ታይበታለህ። በጣም የተረሱ የጥበቡ ባለሟሎች የሚጫወቱበት ቤት ነው። ለምሳሌ ዘሪቱ ጌታሁን፣ ኃይሉ ዲሳሳ፣ ባለ ዋሽንቱ ዮሐንስ አፈወርቅ (ዛሬ ሁሉም የሉም)። ተረስተው የነበሩ እያዩ ማን ያዘዋል፣ ደረጀ ዘመዱ፣ ሃዋ፣ ኪዳኔ፣ ሌሎችም ሰርተውበታል። እየሰሩበትም ነው። እነ ፋንቱ ማንዶዬ፣ ታደለ በቀለ፣ ስዩም ጥላሁን ስንቱን ልጥቀስልህ? እነዚህ ድምጻውያን ከመጫወታቸው በፊት ለአንድ ሰዓት ያህል በሸክላ የሚደመጡ ቆየት ያሉ ዘፈኖች አሉ። ቀደም ባለው ዘመን አልበላም አልጠጣም ብዬ ከተለያየ ሁኔታ ያሰባሰብኳቸው ኦርጅናል ስራዎች ናቸው። አሁን እነሱን ማግኘት ይከብዳል። በዚህ በዚህ ፈንድቃ ከሌሎች ይለያል። አዝማሪ ላይ በሚያተኩረው ፈንድቃ 33፣ በኢትዮ ከለር ደግሞ 23 የሚሆኑ ተጫዋቾች አሉ። በተለያየ ዘርፍ። ቢራ 60 ብር ጠጅ 80 ብር፣ መግቢያ 50 ብር ሆኖ የሰጥቶ መቀበልን ስራ እየሰራን ነው። በአዲሱ ዓመት መግቢያ 100 ብር የማድረግ ሃሳብ አለ። ይህ የሚሆነው የአዝማሪ ቤት ጥበብ ምን ያህል ከበሬታ እንደሚኖረው ለማሳየት ነው። የሰጥቶ መቀበል መርሃችን እንደተጠበቀ ነው እንግዲህ።

 ታዛ፦ ቀደም ብለህ እንደጠቀስክልኝ ከዚህ ሙያህ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አገሮች እንደሄድክ ይታወቃል፤ የት የት ሄደሃል?

መላኩ፦ ብዙ አገራት። ወደ ስምንት ፓስፖርት ጨርሻለሁ። ከፈረንሳይ መንግስት የክብር ሜዳሊያ በማግኘት የዩኔስኮ ግራንት በማሸነፍ፣ ከ800 ተወዳዳሪዎች አሸንፌ ከ50 ሺ ዶላር በላይ አግኝቼ ቤቴን አሻሽዬበታለሁ። በዚሁ ገንዘብ ከየክልሉ አዝማሪዎችና ተወዛዋዦችን እያስመጣሁ ደንበኞቼ እንዲዝናኑ አድርጊያለሁ። እና አዝማሪ ማለት መሸማቀቂያ ሳይሆን መከበሪያ ሙያ መሆኑን ለማሳየት ጥረት አድርጊያለሁ። ወደአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አፍሪካ እና ሌሎች የዓለም ክፍሎች የሙዚቃ ቡድኑን እየወሰድኩ መልሻለሁ። ከተለያዩ ቴአትር ቤቶች ወደ ውጪ አገር የመሄድ እድል የገጠማቸው አብዛኞቹ አይመለሱም። የኔዎቹ ግን ያ ሃሳብ የላቸውም። ደስ የሚለው በፈንድቃ የባህል ቡድንም ሆነ ኢትዮ ከለር ውስጥ የሚሰሩ አብዛኞቹ ራሳቸውን እየቻሉ ይወጣሉ። ሌሎች አዲሶችን አሰልጥኜ ከኔ ጋር ሲሰሩ ተክነው እነሱም ይሄዳሉ። ይህ ለእኔ ደስታ ነው የሚሰጠኝ። ጥበቡ ላይ ሰው እያፈራሁ መሆኔን እረዳለሁ። በአሁኑ ወቅት 13 ልጆች ደመወዛቸውም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞቻቸው ተጠብቀው ፈንድቃ ውስጥ ቤት ተሰጥቷቸው ይኖራሉ። እነ ሄኖክ ተመስገን፣ እነ ላይን ላቭ የጃዝ ባንድ፣ ሳሙኤል ይርጋ፣ እነ ተፈሪ አሰፋ (ውዳሴ ባንድ) አብረውኝ ይሰራሉ። ውጤታማ ናቸው። ስለዚህ በዚህ በዚህ በአሁኑ ወቅት አፍሪካ ውስጥ ምርጥ አስር ከሚባሉ ባንዶች አንዱ ፈንድቃ ነው። በአገር ውስጥ ደግሞ ቀዳሚ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።

ታዛ፦ በውጭ ጉዞህ ስለኛ ምን ሰማህ ወይ ታዘብክ?

 መላኩ፦ በዋናነት ችግረኞች፣ ረሃብተኞች ስለሆን መዝናናትና የፈጠራ ነገር የማይገባን እንደሆን የሚያስቡ መኖራቸውን ነው። ያንን ለመስበር ውበታችንን በጭፈራችን፣ በአልባሳታችን፣ በፈጠራ ችሎታችን ለማሳየት ሞክሪያለሁ። ፈጠራውም ዘመናዊነቱም እኛ ዘንድ እንዳለ ያሳየሁበት ሁኔታ አለ። ተሳክቶልኛልም። ቢቢሲም አፍሪካ ውስጥ ወደ 30 ቻናል ላይ ያሳየው ስራዬ አለ። ስራው የህዝብ ስለሆነ ከህዝብ ወስጄ ለህዝብ በተለይም፤ ለሌላው አገር ሰው ያሳየሁት ነው። ወዲያውኑ ዩ ቲዩብ ላይ ተለቀቀ። ይህን ያህል ሰው አየው፣ በዚህ አተረፍኩ የምል ሰው አይደለሁም። ዩ ቲዩብ ላይ በእኔ አካውንት የተለቀቀ አይደለም። የህዝብን ጥበባዊ ስራ ውበቱን እንደጠበቀ ለህዝብ ማሳየት ነው የኔ የስራ መመሪያ። የተለየ ጥቅም የለኝም። ስራዬ ያመጣው ከማህበረሰቡ የተለየ ኑሮ የለኝም። ብዙ የሰራኋቸው ሊወራላቸው የሚገቡ ነገሮች ቢኖሩም፤ የሚያመጻድቀኝ የተለየሁ እንደሆንኩ የሚያደርገኝ ነገር የለም። ግን የገጽታ ግንባታ የሚለውን ተግብሬዋለሁ ብዬ እናገራለሁ። በነገራችን ላይ በተለያዩ አገራት እየሄድኩ ልምዴን አካፍላለሁ። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጭምር እየተጋበዝኩ ስለ ውዝዋዜ ስልጠና እሰጣለሁ። በቅርቡም ወደ አሜሪካ እሄዳለሁ።

ታዛ፦ በአገር ደረጃ ያለንን የሙዚቃ ባህል በሚገባ ተጫውተነዋል፤ ለሌሎችም አስተዋውቀነዋል የሚል እምነት አለህ?

መላኩ፦ የለኝም። ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ማሲንቆና ክራር ወይም ከበሮ ማይነር ናቸው። የቅዱስ ያሬድን የሚያክል ግዙፍ ስም ይዘን ሞዛርት እና ቤትሆቨንን ነው በሜጀር የሚያስተምሩት። ይህ መጥፎ ነው ማለቴ አይደለም፤ ግን ከዚያ የወጡት አዝማሪዎችን ይዘው ማስተማር ሲችሉ አንዳንዶች ንቀታቸው ይጎላል። “እኔ ውጪ አገር ተምሬ መጥቼ…” የሚሉ ናቸው እንጂ ገጠር ውስጥ ከገበሬው ጋር ያለውን የእውቀት ጥግ አላወቁትም። እውነቱን ለመናገር እንዲያውም ያንን የማጣጣል አባዜ ነው የተጠናወተን። ፈረንጅ ካልተናገረልን፣ ከውጪ ተምሮ ወረቀት ተይዞ ካልተመጣ፣ የአነጋገር አክሰንት ካልተቀየረ የተማረ ተብሎ አይታመንም። በማህበረሰባችን ውስጥ ይህ የአብዛኞቻችን አስተሳሰብ ነው። ምን ያህል የጥበብ ሃብት እንዳለን እንኳ አላወቅነውም። በዚህ ጉዳይ በብቻነት መሞገት ወይም መብሰልሰል ዋጋ የለውም። ጥበቡ ውስጥ ለመቆየት የራስን ዓለም ፈጥሮ ጠንክሮ መቆየት ነው። ለምሳሌ እኔ እራሴ አራቱም ቴአትር ቤቶች ተፈትኜ የተለያዩ ሰበቦችን እየፈጠሩ ሳይቀጥሩኝ ቀርተዋል። በሚገርም ሁኔታ ከ12 ዓመት በኋላ አራቱም ቴአትር ቤቶች በባህላዊ ጭፈራ ሲወዳደሩ አንዱ ዳኛ እኔ ነበርኩ። ልል የፈለኩት ራስን ይዞ ለመቆየት የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ከተጋፈጥክ የኋላ ኋላ ጥበቡ ራሱ ይከፍልሃል።

ታዛ፦ ከጭፈራው የማዝናናት ስራ በተጓዳኝ የሰዓሊያንን ስራ ታበረታታለህ ልበል?

መላኩ፦ አዎ የተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ተያይዘው ቢያድጉ መልካም ነው። ባለኝ አቅም አሁን ያለሁበትን ቤት ተበድሬ ገዝቼዋለሁ። አንዱን ክፍል የስዕል ጋለሪ አድርጌዋለሁ። ሰዓሊያን በነጻ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ነው። እየተወደደ እየተለመደም ነው። ምሽት ሊዝናና የመጣ በእግረመንገድ ይጎበኘዋል። ዘወትር ቀን ከ7 ሰዓት ጀምሮም ለጥበብ አፍቃሪዎች የነጻ ጉብኝት ፕሮግራም አለ። በወር በወር ይቀያየራል። ጀማሪው፣ አንጋፋው እኩል እድሉን ያገኛል። ምንም ክፍያ የለውም። በአሁኑ ወቅት እያሳየ ያለው ሰዓሊ 52 ስራዎችን ሸጧል። ወደፊት ገና የ2 ዓመት ስራ ተይዟል። በወር አንድ ጊዜ የግጥም ዝግጅትም አለ። በቀጣዩ ዓመት ከአፍሪካ የተለያዩ አገራት የተመረጡ ገጣሚያን ግጥሞቻቸውን የሚያቀርቡበት መርሃግብር ተይዟል። በዚህ በዚህ ፈንድቃ ይወደዳል። የተለያዩ አገራት ቱሪስቶች ጭምር ኢትዮጵያ ሲመጡ ፈንድቃን ለመጎብኘት ይጓጓሉ። በውጪ አገር ሚዲያዎች የተሰራው ስራ ከፍተኛ ስለሆነ ነው እንዲህ የተወደደው። በአጠቃላይ የወደፊት ህልሜ ብዙ ነው። ፈንድቃን ከቱሪዝሙ፣ ከባህሉ ጋር አገናኝቼው የተጎዳውን ጥበብ መደገፍ ነው ዓላማዬ።

ታዛ፦ ባህላችን እንደሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ብዛት ሰፊ ነው። ይህንን በፈንድቃ መዝናኛ ማእከል ውስጥ እንዴት ማእከላዊነቱን ጠብቆ ማስኬድ ይቻላል? በውዝዋዜውም ሆነ በአዝማሪነት ስራው ቱባ ባህሉን ከመጠበቅ አንጻር የምታደርጉት ጥንቃቄ እስከምን ድረስ ነው?

መላኩ፦ በእኔ እምነት ባህል አንድ ቦታ ተሰፍቶ የተቀመጠ ነገር አይደለም። እንደዛ ከሆነ ይሞታል። እንዳልኩህ ከፈረንጆች ኮፒ በማድረግ አላምንም። ግን ህብረተሰቡ ባለው ላይ በሚጨምረው መልካም ነገር አምናለሁ። ያንን በጋራ ማጎልበቱ ላይ እስማማለሁ።

ታዛ፦ ብዙውን ጊዜ አንተ በመድረክ ስትታይ በጭፈራዎችህ ሁሉ ተመስጥኦ ይታይብሃል፤ ፈገግተኛ ነህ። የአማርኛ፣ የኦሮምኛ፣ የትግርኛም ሆነ ሌሎች ባህሎች ጭፈራ ላይ ሰውነትህን ትንጣለህ። አካልህ በኃይል ነው የሚንቀሳቀሰው። ይህ ከየት መጣ?

 መላኩ፦ ራሱ ጭፈራው የሚፈልገው ሳይንሳዊ ክዋኔ ነው። እንዳልኩህ ጭፈራን ከእናቴ ሆድ ነው የተማርኩት። ስጦታዬ ነው። መኖሪያዬ፣ ጸጋዬ። ሙዚቃ ለእኔ ህክምናዬ ነው። እንደ እምነት እንደ ፀሎትም ነው የማየው። ከብዙ ነገር ይጠብቀኛል። በሞራል፣ በስነ ምግባር ያንፀኛል። ስሜታዊ ሆኜ ሰው እንዳልጎዳ፣ በሰው መጎዳት እኔ እንዳልጠቀም፣ ጥቅማም እንዳልሆን ይገራኛል። ፈሪ እንዳልሆን፣ ግልፅ እንድሆን ያግዘኛል። በመድረክ የተዝናኙ ስሜትና የህብር ሙዚቃ መሳሪያዎች ቅኝት ህብረ ዜማ ውስጣዊ ስሜቴን ይፈነቅለዋል። ያኔ እኔ ውስጥ ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ። ከልብ እደሰታለሁ። ለምንም አልጨነቅም። ህብረ ሙዚቃው ቁጥጥር ውጪ ያለ መንፈስ ውስጥ ይከተኛል። ሙዚቃን ከልብ ስዋሃደው ነው ያ ሁኔታ የሚታይብኝ። ላለፉት 12 ዓመታት ዕለት በዕለት ነበር የምጨፍረው። አሁን ግን በሳምንት ሁለት ቀን ሰኞና አርብ አድርጌዋለሁ። ኃላፊነቱ፣ ማስተባበሩ ስራ ሲበዛ ነው እንደዚያ ያደረኩት። ቀኖቹ ይናፍቁኛል።

 ታዛ፦ ካስቀመጥከው የሕይወት ግብ አንጻር በእስካሁኑ ጉዞህ ምን ያህል ስኬታማ ሆኛለሁ ትላለህ?

መላኩ፦ ውስጤ ያለው ስሜት፣ ውስጤ ያለው ምኞት ታፍኖ አልቀረም። አገር አወቀልኝ። ዓለም አወቀልኝ። አቅምን የማሳየት መድረክ ማግኘት ዕድለኝነት ነው። በምወደው ሙያ ውስጥ ውጤታማ ሆኜ ስዘልቅ ደስ ይለኛል። ለዚያ ነው አንዱ አልበሜን “ቢራ ቢሮ” ያልኩት። ጥረቴን ያሳየሁበት ነው። አምስተርዳም የተቀዳ ነው። የአዝማሪ እና የኢትዮ ከለር ሁለት ሲዲ እና ሁለት ሸክላ ነው የተቀዳው። የኢትዮጵያ ተዋዛዋዦች ጥበብ ማህበር መስራች መሆኔም ስኬታማነት ነው።

ታዛ፦ የሙዚቃን ሳይንሳዊ ዕውቀት ተምረኸዋል? ለምሳሌ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመግባት።

መላኩ፦ በፍፁም። እኔን ሊማሩ ካሉ ነው እንጂ እስካሁን አልተማርኩም። ወደፊት ሳይንሳዊ መንገዱን ለማጥናት የሚፈልጉ ካሉ እኔን ማጥናት ነው የሚችሉት። ለእኔ እንደዚያ ያለ ትምህርት ቤት መግባት ማለት ራስን ሳጥን ውስጥ መክተት ማለት ነው። መጥፎ ነው እያልኩ ሳይሆን በተፈጥሮ ያገኘሁት ዕውቀት ሳይንሳዊ ከሚባለው ዕውቀት አያንስብኝም ማለቴ ነው። ይህ ለእኔ ነው።

ታዛ፦ ቅድም ጠቅሰኸዋል፤ መርካቶ ምናለሽ ተራ በቆርቆሮ ኳኳታ የሙዚቃ ስሜትን ፈጥረሃል።

መላኩ፦ ለመጀመሪያ ጊዜ በምናለሽ ተራ ሳልፍ በጣም ነው የደነገጥኩት። ኳኳታው፣ ጫጫታው፣ በግዢና ሺያጭ ሂደት የሚፈጠረው ወከባ ብዙ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩት ሁኔታው መንፈስን ያውካል። እዚያ የሚሰሩትን ተጠግቼ ሳወራቸው ምን ያህል ሩህሩህ እንደሆኑ፤ ደጎች እንደሆኑ፣ የፈጠራ ሰዎች፣ የስራ ሰዎች እንደሆኑ ተረዳሁ። በጣም ነው የማደንቃቸው፣ የማከብራቸው። እነሱ ባይኖሩ ኖሮ አዲስ አበባ የቆሻሻ ክምር የሚውጣት ትሆን ነበር። እነሱ ናቸው የወደቀውን እያቃኑ፣ የተበላሸውን እየጠገኑ ዳግም አገልግሎት ላይ እንዲውል የሚያደርጉት። ስለዚህ መንግስት ባያስነሳቸው እንዲያውም በአገልግሎታቸው እንዲገፉ ቢያበረታታቸው ነው ፍላጎቴ። ይህንን ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ የምናገረው ነው። እና እነሱ ሲሰሩ እዚያው ኳኳታውን የሙዚቃ ሪትም ፈጠርኩበት። ባህላዊ ጭፈራውን አስነካሁት። እነሱ ተደሰቱ፣ ተገረሙም። ይህ በቴሌቪዥን ተላለፈ። መልዕክቴና ስሜቴም ታወቀልኝ። ሙዚቃ ስራ ውስጥም፣ ውሃ ውስጥም፣ ተራራ ውስጥም መኖሩን፤ ከእለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር ቁርኝት እንዳለው ለማሳየትና የሙዚቃ ረቂቅነትና የመንፈስ ህክምናነቱ ምን ያህል እንደሆነ ለማሳየት የተጠቀምኩበት ክስተት ነው።

ታዛ፦ ለጥበቡ ባለህ የቀናኢነት ስሜት ከአገር አልፎ በውጪ ደረጃ ለማስተዋወቅ ጥረትህን እንደምትቀጥል ገልፀህልኛል። ምናልባት በወደፊት ጉዞህ ያቀድካቸው የተለያዩ ተግባራት ካሉ?

መላኩ፦ ቅድም እንደገለፅኩልህ ይህ ባንኮኒው ስር ፍራሽ አንጥፌ አድርበት የነበረውን የወቅቱ ታዋቂ አዝማሪ ቤት ሰፊ ግቢ በብድር ገዝቼዋለሁ። ሰው ሃብታም ያደርገኛል እንጂ አብሮ ለማደር የማካፈልን መርህ የምከተል ነኝ። ሃብታም አይደለሁም። አምስት መቶ ካሬሜትር ቦታ ላይ የሰፈረ ነው። አሁን እያገለገለ ባለው መልኩ የሚጠበቅበት ነገር አለ። ባለው ቦታ ትልቅ ግንባታን ይጠይቃል። ቤቱን የጥበብ ማዕከል የማድረግ አላማ አለኝ። ለዚህ ደግሞ አጋዥ እፈልጋለሁ። በመንግስት ደረጃ ምን እንርዳህ፣ ምን እንደግፍህ የሚሉ አካላት ቢኖሩ በበለጠ ሞራል እተጋለሁ። ያሰብኩትን መከወኔ አይቀርም፤ እገዛው ቢኖር ግን ሂደቱን ያፈጥነዋል። አገር ውስጥ ያለው እንዳለ ሆኖ በፈረንሳይ ፓሪስ፣ በበርሊን፣ በሮም፣ በኒው ዮርክ እና በቶኪዮ ፈንድቃን የማቋቋም ህልም አለኝ። ከእነዚህ አገራት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለኝን ስምምነት ለመፍጠር በማደርገው ጥረት መልካም ምልክቶች እያሁ ነው። ዓለም አቀፍ እውቅና ለኢትዮጵያ ማስገኘት ነው አላማና ግቤ። ግን ወደዚያ ለመጓዝ “መጀመሪያ የመቀመጫዬን” አይደል ያለችው ዝንጀሮ?… እንደዚያ ነው።

ታዛ፦ የአርት ማዕከል አደርገዋለሁ ስትል አሁን እየሰጠ ካለው አገልግሎት በተጨማሪ ምን አስበህ ነው?

መላኩ፦ ብዙ ነገሮች አሉ። ከቱሪዝም ጋር፣ የኢትዮጵያ የባህል ምግቦች አቅርቦት፣ የቀረፃ ስቱዲዮ፣ ፌስቲቫሎች፣ ሌሎችም ጥበባዊና ባህላዊ ክዋኔዎች ይሰሩበታል። ሲጀመር ወጪ ቢኖረውም ውስጥ ሲገቡበት ግን በአንዴ በእጥፍ የሚክስ ነው። እዚያ እንደምደርስ አውቀዋለሁ። የመፍጠን ጉዳይ ነው አሳሳቢው። ይህንን የሚሰማ አካል ልብ ይላል ብዬ አስባለሁ። በነገራችን ላይ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር አሁን አሁን መቀራረብ ጀምረናል። ተናድጄ “ሌሎች አገሮች እንዲያ ሲያውቁኝ እናንተ አታውቁኝም፤ የእናንተን ስራ እየሰራሁ ችላ ብላችሁኛል…” ብዬ የተናገርኩበት አጋጣሚ ነበር። የእነሱን ስራ አቅልዬላቸዋለሁ። ቢሮክራሲው የጥበብ እድገትን ይገታል። ከዚያ እንዲወጡ ነው ሃሳብ የምሰጠው። ብቻዬን መሮጥ የለብኝም፤ እገዛ ያሻኛል። ለእኔ ብቻ ሳይሆን ላሉን ቴአትር ቤቶች የጥበብ ሙያተኞች ከደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጀምሮ መብታቸውና ስሜታቸው መጠበቅ አለበት። እዚያ አካባቢ መሳሳት ይታያል። ከዚያ ይልቅ የምሽት ክበቦች በአቀራረብ፣ በችሎታና ተቀባይነት ደረጃ እየተሻሻሉ መምጣታቸው እየታየ ነው። ይህ የውድቀት መንገድ ስለሆነ መጠንቀቅ ይገባል። የቴአትር ቤቶችን በዘመናዊ መንገድ ለማራመድ ሳይሆን ያለውንም መጠበቅ እንደተሳነን እየታየ የመጣ እውነታ ነው። ስለዚህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቆም ብሎ መፍትሄውን ማሰብ ይኖርበታል።

ታዛ፦ ብዙውን ጊዜ በግለሰቦችም ሆነ በተቋም ደረጃ በአዲስ ዓመት አዲስ እቅድ አለ። በፈንድቃ ምን ታስቧል?

መላኩ፦ እኔ ተቃራኒ ነኝ። አዲስ ዓመትን ጠብቆ አዲስ ነገር መልቀቅ ማሻሻጫ ነው የሚመስለኝ። ሁሌ በዓል ነው – ለኔ። በዚያ መሸወድን ስለማልፈልግ የለሁበትም። ይህ የእኔ ሃሳብ ነው። ለሌሎች ሊሰራ ይችላል። ያንን አልተችም። በዓላት የሚከበሩ እሴቶቻችን እንደሆኑ ይታወቃል። ጭፈራው ግን ከእነዚያ ቀናት ሌላም ሊሆን ይችላል፤ ነውም።

ታዛ፦ ሙሉ ጊዜህን ለጥበብ የሰጠህ እንደሆንክ ይታወቃል፤ እንዲህ ያለ ሰው ቤተሰብ ማፍራት ይቻለው ይሆን?

መላኩ፦ በጥሩ ትዳር ውስጥ ነኝ። ሁለት ወንዶች ልጆች አሉን። ባለቤቴም በእኔ ሙያ ውስጥ ስላለች ተግባብተን፣ ተደጋግፈን እየተጓዝን ነው።

ታዛ፦ ከመሰነባበታችን በፊት እኔ ያላነሳሁትና መቅረት የለበትም የምትለው ነጥብ ካለህ?

መላኩ፦ ፈረንጆች ምን ይፈልጋሉ ብሎ መስራት ያናድደኛል። እኛ ስናምር፣ እኛ ስንስቅ፣ በጨዋታው፣ በፍልስፍናችን ስንኖረው ፈረንጆች ይወዱናል። እንጂ እነሱን ለመምሰል ስንጥር አይደለም እነሱ የሚወዱን። በኛነታችን እንዲወዱን፣ እንዲያከብሩን፣ እንዲቀርቡን ማድረግ ነው መልካሙ ነገር። አሁን እኔ ቤት ከሀበሻው ይልቅ ፈረንጁ ነው አገር አቋርጦ ሲመጣ ለመጎብኘት የሚፈልገው። እዚሁ አዲስ አበባ ያለ አያውቀውም። መጀመሪያ እራሳችንን እንወቅ፣ በራሳችን እንደሰት። ሰላማችን ይብዛ ነው የምለው። ሰላም ሲኖረን ነው ሁሉም ነገር የሚኖረው። መልካም አዲስ ዘመን ይሁንልን።

ታዛ፦ ላንተም መልካም አዲስ ዘመን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top