አድባራተ ጥበብ

በአክሱም በር ሥር እንለፍ

የኢትዮጵያን ታሪክ እውነታ ከሴማውያንና ከምዕራባዊያን ትርጉም አሰጣጥ አንፃር በተቃራኒው መልኩ ቆመው የሚረዱትና የሚጽፉት አስረስ የኔሰው “ትቤ አክሱም መኑ አንተ” የሚል መጽሐፍ አላቸው:: “አክሱም አንተ ማነህ ትልሃለች” ነው ትርጉሙ:: ይህ ብቻ አይደለም የግዕዝ ቋንቋ ከነፊደሉ የያዘውን ሚስጥር እየተነተኑ “መለኮት ፍጥረታትን ሲፈጥር ልኬቱንና ሚስጥሩን የሰወረበት ፊደል ግዕዝ ነው::” ሲሉ የሚማጎትባትም “የካም መታሰቢያ የምትል ጥራዟ የቀጠነች እውነቷ የጠለቀች መጽሐፍ አለቻቸው:: አስረስ የኔ ሰው በእነዚህ ስራዎቻቸው ውስጥ ትውልዱ በተሳሳተ ታሪክ ተጠልፎ ከማንነቱ ጋር እንዳይጣላ አይኖቹ ወደ ቆሙበት የአባቶቹ ሐውልት እንዲያቀና ጽፈው አስቀምጠው ያለፉትን ድርሳናቶች እንዲመረምር ለዚህ ትውልድ “ትቤ አክሱም መኑ አንተ” እያሉ በአክሱም ሐውልት ሥር በቆመው መንፈሳቸው ይጣራሉ:: መግቢያው በሐውልቱ ሥር የሚገኘው የተቆለፈው በር ይመስለኛል::

 የተቆለፈው የአክሱም ሐውልት የድንጋይ በር ምንድነው?

 ዛሬም ቆመው ከሚታዘቡንም ሆነ ወድቀው ከሚያስለቅሱን የአክሱም ሐውልቶች ላይ በበር ቅርፅ የተሰሩ የድንጋይ በሮች እና በነሱም ላይ ተደራራቢ የሆኑ ፎቆች ሚስጥራዊ የቁጥር ውክልናን ይዘው በዝምታ ለሚያልፈው የትውልድ ጅረት የሚናገሩት ሚስጥር እንደነበር እናያለን:: እነዚህ የድንጋይ በሮች የተቆለፉ ይመስላሉ:: በበር ቅርፅ እስከተሰሩ ድረስ የሚከፍታቸው ሆነ በሥራቸው የሚያልፍ ትውልድን የሚጠብቁ ለመሆናቸው እርግጠኞች ልንሆን ይገባል:: ያለ ምክኒያት በር አይሰራም፤ ሕይወት እራሷ በር ፈላጊ ናት:: 9 ወር በሙሉ በእናቱ ማህፀን ውስጥ የኖረ ፅንስ ጊዜው ሲደርስ የተዘጋውን የእናቱን ማህፀን በር ከፍቶ በእሱ በኩል አልፎ ይህንን ዓለም ይቀላቀላል:: በር ያሳልፋል::

 “በ” በግዕዝ ፊደል ተ.ቁ ላይ 9ነኛውን ተራ ይዞ መገኘቱን አስቡ:: ሰው በዚህ የበር ቅርፅ ባለው 9ነኛው ቁጥር በኩል በእናቱ ማህፀን 9 ወር ቆይቶ በተከፈተው በር በኩል አልፎ ወደዚህ ዓለም ይመጣል:: ይህንን ሚስጥር አክሱማዊያን ተረድተውታል:: ባቆሙልን ሐውልቶች ላይ ተደራርበው ወደ ተሰሩት ፎቆች ለመውጣት እና ከሐውልቱ አናቱ ላይ ለመድረስ በበር በኩል ማለፍ እንዳለብን ይነግሩናል:: እየሱስ ክርስቶስም በምዋዕለ ስብከቱ እኔ የበጎች በር ነኝ ከማለቱ እስቀድሞ አክሱማዊያንም በመንፈሳዊ ማንነት ትውልዶች ሁሉ የሚያልፉበትን የሕይወት ሚስጥር በር ከእነ ሚስጥራዊ ቁጥራቸው እና ምሳሌያቸው ጋር አጣምረው በሥራቸው ላይ አስቀምጠውልናል:: በ9 ቁጥር ውክልና:: ይህንን 9 ቁጥር እየሱስም ይወደዋል በ6 ሰዓት ተሰቅሎ በ9 ሰዓት ተፈጸመ ብሏል:: ታላቁ ዩኒቨርስ በ9 ፕላኔቶች ምዕዋር 10ኛ የሆነችውን ፀሐይ ከቦ ያሽከረክራል:: በግዕዝ ፊደል “በ” የሚወክልበት 9 ቁጥር እጅግ ትልቅ ሚስጥር አለው::

 በአክሱም በር ሥር ማለፍ የት ያደርሳል? በአክሱም ከሚገኙት ሐውልቶች ውስጥ በአጥኚዎች ምዝገባ ቁጥር 1 ተብሎ መለያ የተሰጠው ሐውልት ርዝመቱ 33 ሜትር ሲሆን 520 ቶን ክብደት አለው ይባላል:: በዚህኛው ከአንድ ወጥ ድንጋይ ከተሰራ ሐውልት ላይ የተቆለፈ የድንጋይ በር እና በበሩ ላይ ተደራርበው የተሰሩ 13 ደረጃ ያላቸው ፎቆች ይታያሉ:: እነዚህ ቁጥሮች በፎቆቹ የተወከሉት ለምንድነው? አስረስ የኔሰው “ትቤ አክሱም መኑ አንተ” ይሉናል:: ይህንን ተከትዬ ሚስጥራቱን ከመተንተኔ በፊት የሌሎቹን ቀሪ ሐውልቶች ሁኔታ ላስረዳ:: ቁጥር 2 ተብሎ በሚታወቀው ሐውልት ሥር እንደ ቀደመው ሁሉ በር ሲኖረው እርዝመቱ 24.6 ሜትር እና 170 ቶን ክብደት ሲኖረው ከተቆለፈው የድንጋይ በር ቀጥሎ ወደላይ 11 የተደራረቡ ፎቆች ይዞ ይታያል:: ይህስ ቁጥር ውክልናው ምንድነው? በዚህ ቁጥር ሚስጥር ውክልና በበሩ በኩል ብናልፍ የት ያደርሰናል?

ቁጥር 3 ሐውልት ደግሞ 20.6 ሜትር ርዝመት እና 160 ቶን ክብደት ሲኖረው ከተቆለፈው የድንጋዩ በር ቀጥሎ ወደላይ 10 ድርብርብ ፎቆችን ይዟል:: ቁጥር 4 ሐውልት 18.2 ሜትር ሲረዝም 56 ቶን ክብደት አለው:: ከበሩ ቀጥሎ ወደ ላይ 6 ፎቆችን አደራርቦ ይዟል:: ቁጥር 6 የሚባለው ሐውልት 15.3 ሜትር ቁመትንና 43 ቶን ክብደት ሲኖረው ይህም ሐውልት 4 ፎቆችን ተሸክሞ ቆሟል::

የቁጥሮቹ ሚስጥር በግዕዝ ፊደል ሲፈታ ለዚህ ትውልድ ምን ይናገራል?

 የግዕዝ ፊደል ወደ ጎን 7 የተለያዩ ድምፅ የሚሰጡ ሆሄያትን ይዞ ወደ ታች ደግሞ ከ “ሀ” እስከ “ፐ” ሲቆጠር 26 ግዕዝ ተብለው የሚጠሩ ፊደላትን ይዞ ይገኛል:: (ቸ፣ ሸ፣ ኘ፣ ጨ፣ ጀ፣ ኸ) የሆኑትን የአማርኛ ድምፆች ሳንቆትር ማለት ነው:: እነዚህ ፊደላት 26 × 7 = 182 ሲሆኑ እያንዳንዳቸውም ሆሄያት የተሰጣቸው ቁጥር ተሰልቶ የመጨረሻው “ፖ”ፊደል ጋር ስንደርስ ቁጥሩ 5,600.00 ሲሆን በተለየ መልኩ የተደበቁ ሚስጥሮች የሚተነተኑበት ሚስጥራዊው ቁጥር ደግሞ 800 ቁጥር አለው:: ይህንን ሚስጥራዊ ቁጥር ለጠቅላላው የሆሄያት ቁጥር ስናካፍለው 5,600.00 ÷ 800.00 = 7 ይሆናል:: ይህንን በማካፈል ያገኘነውን የመጨረሻ ውጤት ከመጀመሪያው “ሀ” ፊደል ጋር ላሉት 7 ፊደሎች ስንደምረው 14 ቁጥር ይሰጠናል:: አጠቃላዩን የግዕዝ ፊደል 26 × 14 = 364 ይሆናል:: ይህ የአንድ ዓመትን ዙሪያ ክብ የሆነ የጊዜ ውጤት ሲያሳይ የዚሁ ግማሽ 182 የዓመቱን ግማሽ ወር ይዞ ይገኛል:: ይህም ቅርፅ ከሙሉ ክብ ይዞ የሚወጣ ግማሽ ቅርፅ ይሰጠናል:: ይህ የሙሉ ግማሽ ቅርፅ በአክሱም ሐውልት አናት ላይ ተቀምጦ የምናየው ነው:: 26 ለ2 ብናካፍለው 13 ቁጥርን ይሰጠናል:: ይህም በኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር የ13 ወራት የጊዜ ፅንሰ-ሀሳብን የሚያሳይ ሲሆን በቁጥር አንድ ሐውልት ላይ አክሱማዊያን ያቀመጡልንን ባለ 13 ድርድር ፎቅ ምንነት እንድንፈታበት እና እንድንረዳበት ይጠቅመናል::

 በሐውልቱ ላይ ያሉት ቁጥሮች በዚህ ሚስጥር ሲታዩ ምን ይመስላሉ? በቁጥር 1 ሐውልት ላይ የሚታየው ባለ 13 ድርድር ፎቅ በግዕዝ ፊደል ተራ አልፋውን “አ” የሚወክል ሲሆን የዚህ ፊደል ሚስጥራዊ ቁጥር 40 ነው:: በቁጥር 2 በሚታወቀው ሐውልት ላይ የሚታየው 11 ድርብርብ ፎቅ በግዕዝ ፊደል ኀይሉ “ኀ” ወይም ብዝኋኑን “ኀ” ሲወክል ሚስጥራዊ ቁጥሩ 20 ነው:: በቁጥር 3 ሐውልት ላይ 10 ድርብርብ ፎቆች ሲታዩ ይህም በግዕዝ ፊደል “ተ” ን ይወክላል:: ሌሎች ሐውልቶች 6 እና 4 ፎቆችን ይዘው የሚገኙት በፊደል ውክልና ሲገለፁ “ረ” እና “መ” ይሆናሉ:: የነዚህ ፊደሎች ሚስጥራዊ ቁጥር 4 እና 6 ነው:: እነዚህን በአንድ ላይ ሰብስበን ስንደምራቸው 40 + 20 + 10 + 6 + 4 = 80 ይሰጡናል:: ይህንን ውጤት በአንደኛው ሐውልት ላይ ላለው 10 ፎቅ ብናካፍለው ውጤቱ 8 ይሆናል:: 8 ቁጥር የፍትህ ቁጥር ነው ይባላል:: ለዚህም ይመስላል አክሱማዊያኑ 8 ማዕዘን ያለው የድንጋይ ገበታ ቀርፀው በዚያው ያስቀመጡልን::

 በግዕዝ ፊደል ተራ የአልፋው “አ” መጨረሻ የሆነው “ኦ” 280 ቁጥር ውክልና ተሰጥቶታል:: የብዙኋኑ “ኀ” መጨረሻ የሆነው “ኆ” የ140 ቁጥር ውክልና አለው:: የ“ተ” ፊደል መጨረሻ “ቶ” የ70 ቁጥር ውክልና አለው:: የ“ረ” ፊደል መጨረሻ “ሮ” 42 ሲሆን የ“ሐ” መጨረሻ “ሖ” 28 ቁጥርን ይወክላል:: እነዚህ ቁጥሮች ተጠቃለው ሲደመሩ 560 ውጤት ይሰጣሉ:: ይህንን ቁጥር ለሚስጥራዊ ቁጥሮች ደምረን ላገኘነው 80 ስናካፍለው 7 ቁጥር ይሰጠናል:: 7 ቁጥር የጥበብ መሰረት ነው:: “ጥበብ ቤቷ በ7 አምድ ላይ ሰራች” ይላል ጠቢቡ ሰለሞን:: ወደ ሌሎች ቁጥሮች ትንታኔ ላምራ፤

 13 ቁጥርና የአክሱማዊያን መልዕክት ይህ ቁጥር የተቀመጠው በቁጥር 1 ሐውልት ላይ ነው:: ይህ ሐውልት 9 ቁጥርን በሚወክለው በር በኩል አልፈን በመንፈሳዊው አካል ከፍተን እንድንገባ ይጠራናል:: “በ” በር ነው:: ሙሴ የመጀመሪያውን ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 መጽሐፍ ሲጀምር “በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድር” በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ብሎ በ9 ቁጥር የ“በ” ሚስጥራዊ ውክልና ስራውን ጀምሯል:: አስረስ የኔሰው የካም መታሰቢያ በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ይህንን አስፋፍተው በመተንተን ሙሴ ሲጀምር ብቻ ሳይሆን ይህንኑ የምዕራፍ አንድ ዘፍጥረት መጽሐፍ ይህንን እየሱስ ክርስቶስ ካስተማረው የመጀመሪያው የተራራው ስብከቱ ወይም አንቀፀ-ብፁሐን ጋር በማነፃፀር እየሱስም ልክ እንደ ሙሴ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5 ቁጥር 3 ጀምሮ እስከ ቁጥር 11 ድረስ 9 ብፁሐን የሚለውን ቃል መጠቀሙ የግዕዝን ቋንቋ እውነተኛነት ያረጋግጣል በማለት ይሟገታሉ:: እናም የ9 ቁጥር ውክልና የተሰጠው በር ራሱ ስጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ሚስጥራት ስላለው በበሩ በኩል የምናልፈው ትንሳኤ ልቦና በሚያገኘው መንፈሳዊው አካል ስንወለድ ብቻ መሆኑን አክሱማዊያን ባቆሙልን ሐውልት ለትውልድ ሁሉ ይናገራሉ::

በመንፈሳዊ ትንሳኤ ተወልደን በበሩ በኩል ስናልፍ ወደላይ መውጣት የሚጠበቅብን 13 ፎቆች ይጠብቁናል:: 13 ቁጥር በግዕዝ ፊደል ሚስጥራዊ ቁጥር ሲፈታ ሰላም የሚለውን ትርጉም፤ ሰ 7 + ለ 2 + መ 4 = 13 በበሩ በኩል ስናልፍ ይህንን ፍፁማዊ ሰላም ማግኝት የትውልዱ ኑሮ እጣ ፋንታ ነው:: ያለዚህ ፍፁማዊ ሰላም ስልጣኔም ሆነ ብልፅግና አይገኝም:: በጦር መሳሪያ የሚመጣ ሰላም ታላቅነት አይገኝም:: በቁሳዊ ብልፅግና ብቻ ሰላምና እረፍት አይገኝም:: የትውልዱ መንፈሳዊ አካል የተቀበረበት መቃብር በትንሳኤ ልቦና ካልተነሳ ኢትዮጵያም ሆነች ኢትዮጵያውያን ፍፁም ሰላምን አያገኟትም:: የአክሱም ስልጣኔ ታላቅነት የተገነባው ከዚህ ዓይነቱ ፍፁማዊ ሰላም ጋር በመደመሩ ብቻ ነበር:: ይህ ትውልድ ስለ ሰላም ያለው ትርጉም ከምዕራባዊያን አስተሳሰብ የተገለበጠ ነው:: በሚጨበጠው እና በሚታየው ቁሳዊ ነገር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሰላም ፍፁም እረፍት እና ብልፅግና የሚሰጠው መስሎት እየደከመ ነው:: የአክሱም ሐውልት ግን “ትቤ አክሱም መኑ አንተ” ይለናል:: “ሰላማችሁን የምታገኙት በትንሳኤ ልቦና ተወልዳችሁ ማንነታችሁን ስታገኙት ነው” ይለናል:: ጎሰኝነት አካላዊ ማንነት ነው:: ኢትዮጵያዊነት ደግሞ በትንሳኤ ልቦና የሚወለድ ከነፍስ ጋር የተደመረ ማንነት ነው:: የአክሱም ሐውልት የተቆለፈውን በር ከፍታችሁ በበሩ በኩል ወደ ከፍታው ካወጣችሁ ፍፁም የሆነውን ሰላም አታገኙትም ይለናል:: የገነባችሁት ያለዚህ ሰላም ይፈርሳል ይለናል:: የቋጠራችሁትም ይፈሳል፣ የወሰናችሁትም አይፀናም፣ የዘራችሁትም አይበቅልም ይለናል:: በቂምና በተንኮል መንፈስ ውስጥ ሆናችሁ የምትሰሩት ፖለቲካና የምትገነቡት ኢኮኖሚ የሰላም ሳይሆን የጦርነት ምክኒያት ይሆንባችኋል ይለናል::

 ሌላው ደግሞ 13 ቁጥር በግዕዝ “ሐመር” የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል:: ሐ 3 + መ 4 + ረ 6 + = 13 ይሆናል:: ሐመር ማለት መርከብ ማለት ነው:: በ9 ቁጥር ውክልና የተሰራው በር በኩል በትንሳኤ ልቦና ተወልዳችሁ ወደ ላይ ካልወጣችሁ ዘመኑም ካመጣባችሁ ከጥፋት ዶፍ ማምለጥ አትችሉም:: እነደ ኖህ ዘመን ሰዎች ከክፋታችሁ ጋር ሰምጣችሁ

በአክሱም በር ስናልፍ ወደ ላቀው ብልፅግና

ለመድረስ እጃችን ለሰላም ስራ ብቻ ማዋል

አለብን

ትጠፋላችሁ:: በዚያን ዘመን ምድርን ነበር የጠፋችው:: አሁን ግን ሀገራችሁ ናት የምትጠፋው:: ስለዚህ ከጥፋት ውሃ የምታመልጡበት ሐመር ወይም መርከብ ስሩ ይለናል:: ኢትዮጵያውያን ከዚህ ዘመን የዘርና የጎሰኝነት ጥፋት ለመዳን መርከብ መስራት ያስፈልጋቸዋል:: ይህ ትውልድ በአክሱም በር በኩል አልፎ ወደ ላቀው ልዕልና ጫፍ ለመውጣት የመዳን መርከብ መስራት ያስፈልገዋል:: በቁሳዊ ጥበብ ብቻ የተገነባ መርከብ የማናቋርጠው ብርቱ ፈተና ሀገራችንን አጋጥሟታል:: በትንሳኤ ልቦና ተወልደን በየምንሰራው መንፈሳዊ መርከብ ያስፈልገናል:: ኖህ ይህችን የዳነባትን መርከብ ለመስራት 50 ዓመት ፈጅቶበታል ይላል:: እሱ የሰራት መርከብ እሱንና ቤተሰቦቹን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ፍጥረታት ከጥፋት ውሃ እንዲድኑ ምክኒያት ሆናለች:: ኢትዮጵያውያንም ለሌላው ዓለም ሀዝብ መዳን ምክኒያት የሚሆኑት የተቆለፈውን የአክሱም ሐውልት በር ከፍተው ሲያልፉ ብቻ ነው:: ይህ ሐውልት በ13 ቁጥር ውክልና ደራርቦ በያዘው ፎቅ የሚናገረውን ሚስጥር ስንረዳ እና የመዳን መርከብን ስንሰራ ብቻ ነው::

እንደገናም 13 ቁጥር የፍቅር እራትን ይወክላል:: በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከ12ቱ ኃወርያት ጋር እርሱ 13ኛ ሆኖ በአርብ ዋዜማ በዕለተ ኃሙስ የፍቅር እራት በልቷል:: ይህ ቁጥር 13 መሆኑን ልብ እንበል:: በአክሱም በር ስናልፍ 100 ሚሊዮን ህዝቦች ብንሆንም የፍቅር እራት ግን 13 አድርጎ አሰባስቦ በፍቅር ገበታ ላይ ያስቀምጠናል:: ፍቅር እና እምነት ከመሪዎቻችን ጋር አዳምሮ የፍቅር እራት በአንድ ላይ እንድንጎራረስ ያደርገናል:: ህዝብ እና መሪ ሳይለያይ አንዱ ገዢ ሌላው ተገዢ፣ አንዱ ባርያ ሌላው ጌታ ሆነን ሳንተያይ የፍቅርን እራት ለመብላት በአክሱም በር ስር ማለፍ እንዳለብን ይህ ሐውልት ይነግረናል::

እንደገናም 13 ቁጥር የሰው ልጅን እጅ ይወክላል:: ማንኛውም የሰው ዘር በእጁ አራት ጣቶች ላይ 12 የተከፋፈሉ አፅቆች ይኖሩታል:: በአንዱ ጣት ያሉትን በ3 የተከፋፈሉ አፅቆች ለአራቱ ጣቶች ብናባዛው 12 አፅቆች እናገኛለን:: እነዚህን አራቱን ጣቶች ያለ አውራ ጣት በህብረት ብንጨብጣቸው የያዝነውን ነገር አያጠብቁም:: ነገር ግን በ4ቱ ጣቶቻችን ላይ አውራ ጣታችን ሲደመር 13ኛ ይሆናል:: ይህንን ጊዜ ብንጨብጥ እናጠብቃለን:: ብንመታ እናደቃለን፤ 100 ሚሊዮን ህዝቦች ብንሆንም በአ ክሱም በር ስናልፍ በ13ቱ ፎቆች በኩል ወደላይ ስንወጣ እንደ ተጨበጠው ጠንካራ እጅ እኛም በ13 ቁጥር ሚስጥር ጠንካሮች እንሆናለን:: ደግሞም እጃችን የ13 ቁጥር ውክልና ካለው ሰላም የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል:: በአእምሮአችን ያሰብነውን በተግባር የምንፈፅመው በእጃችን ነው:: ሰው ለመግደል አስቦ ግድያውን የሚፈፅመው በእጁ በጨበጠው የፀብ መሳሪያ አማካኝነት ነው::

ስለዚህ እጃችን የአስተሳሰባችን አስፈፃሚ ክፍል ነው:: በአክሱም በር ስናልፍ ወደ ላቀው ብልፅግና ለመድረስ እጃችን ለሰላም ስራ ብቻ ማዋል አለብን:: ይህ ትውልድ እጅን ማንፃት አለበት:: እንደ ጲላጦስ በውሃ ብቻ መታጠብ ሳይሆን በመንፈስ መወለድ ያስፈልጋል:: ወንድም በወንድሙ ላይ በሚያነሳው መሳሪያ ወደ ከፍታው ሳይሆን ወደ ዝቅታው ነው የሚወርደው:: የአክሱማዊያን እጅ የተዘረጋው ለሰላም ብቻ ስለነበር ያንን ገናና ሥልጣኔ ሰርተውትና ኑረውበት አልፈዋል:: ይህ ትውልድ ግን ከእነሱ በተቃራኒ መንገድ ላይ ቆሞ አገራችንን የምናፈርሳት በገዛ እጃችን ነው:: የምናድናትም እንደዚሁ::

የዚህን 13 ቁጥር ሚስጥር የተረዳው የተባበሩት የዓለም መንግስታት የስሙ ፊደል የተዋቀረው በ13 የላቲን ሆሄያት ነው:: እስቲ ቁጠሩት /UNITED NATIONS/:: ይህ ብቻ አይደለም የዚህ ዘመን ምሳሌ ተደርጋ የምትቆጠረው አሜሪካም ባንዴራዋን ስትሰራ በቀይ እና በነጭ መስመሮች ውህድ ላይ ያረፉት 52 ኮከቦች መሰረት ያደረጉት የ13ቱን ቀይ እና ነጭ ውሁድ መስመሮችን ነበር:: ለምን ይህንን ቁጥር የአሜሪካን መስራች አባቶች መረጡት፤ ከእኛ ቀድመው በአክሱም በር ሥር መንፈሳቸው አልፎ ይሆን? ኢትዮጵያውያንን ይህን ሚስጥር ለምን ተሰወረባቸው? ብዙ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል:: በሌሎቹም የሐውልቶች ውስጥ የተቀመጡትን ቁጥሮች በመተንተን ብዙ መነጋገር ይቻላል::

 የአክሱም መጠሪያ የሆነው የመጀመሪያ ፊደል አልፋው “አ” ሚስጥራዊ ቁጥሩ 40 ነው:: በግዕዝ “ንስሀ” የሚለው ቃል 40 ቁጥርን ይወክላል:: መ 30 + ሰ 7 + ሐ 3 = 40:: የንስሀ መሰረታዊ ዓላማ ሰዎችን ወደ ቀደመው ንፅህናቸው ሐጢአታቸውን በማስወገድ መመለስ ነው:: ንስሀ የቆሸሸውን ስብእና በማደስ መልሶ ንፁህ ያደርጋል:: የሰላምና የእርቅን መንገድ በነፍስና በስጋ መካከል ይሰራል:: እንደ ህዝብ እና እንደ ሀገር ሲታይ ደግሞ ንስሀ በህዝብ እና በአገራት መካከል የተፈጠሩና የተሰሩ መጥፎ ታሪኮችን ሽሮ አዲስ ታሪክን ያስፅፋል:: አክሱም በሚስጥራዊ ቁጥሩ ይህ ትውልድ ንስሀ እንደሚያስፈልገው ይሰብካል:: የንስሀ መግቢያ በር ከምናየው ሀውልት ሥር የተቆለፈው በር መሆኑን ይናገራል:: ይህንን በር በትንሳኤ ልቦና ማለፍ የቻለ ትውልድ እና ሀገር እና ህዝብ ወደ ላቀው የአክሱም ጫፍ ልዕልና መውጣቱ አያጠራጥርም:: አክሱም ብዙ ነገር ነው:: ለጊዜው ግን ነገሬን እዚህ ላይ እቋጫለሁ:: ከሞላው እና ከተረፈው ጊዜ ሰፍሮ የሚሰጥ አምላክ ለእኔም ጊዜ ከሰጠኝ በሚቀጥለው ሀሳቤ ሙግት ልገጥማችሁ ተዘጋጅቻለሁ:: ለነበረኝ ጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ!!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top