ቀዳሚ ቃል

ቅን ልቡና ይዘን ዘመኑን እንሻገር

አሮጌውን ሸኝተን አዲሱን ዓመት ለመቀበል ቀናቶች ቀርተውናል:: እኛም ሁለተኛ ዓመታችንን ጨርሰን ወደ ሦስተኛው ለመሸጋገር የመጨረሻ ደግሳችንን እነሆ ይዘን ብቅ ብለናል:: በባለፉት አመታት ጉዟችን በንባብም ይሁን በተሳትፎ አብራችሁትን የነበራችሁ ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን::

በዚህ በ24ኛ ዕትማችን የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ወደናንተ አድርሰናል:: ጽሑፎቻችን የተለያየ ስሜትና ፍላጎት ያላቸው አንባቢያንን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ መጣራችንን ስታነቡት ትረዱታላችሁ ብለን እናስባለን:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሙዚቃው ኢንደስትሪ ብቅ ብቅ ማለት ከጀመሩት ወጣቶች ውስጥ አዲስ ነገር ይዞ የመጣው ሮፍናን ኑሪ የዚህ ዕትም እንግዳችን ነው:: ሙዚቃ ምን ያህል ከማንነቱ እና ከግል ሕይወቱ ጋር የተሳሰረ መሆኑን የሚናገረው ሮፍናን ገና ብዙ ትልሞች እንዳሉት ያወጋናል::

 በተመሳሳይ አዝማሪ ቤት እና ባህላዊ ጭፈራ ቤቶች ክብር ሊሰጣቸው ይገባል እያለ የሚሟገተው የፈንዲቃ መስራች መላኩ፤ አንድነታችንን፣ ውበታችንን እና ሁለንተናዊ ባህላችንን ለዓለሙ ማህበረሰብ እያስተዋወቀ መሆኑን ይነግረናል:: በስርሖተ ገፅ ላይ ሃሳቡን፤ ስሜቱን ያጋራናል:: ከፍልስፍናው፣ ከታሪኩ፣ ከሙግቱ፣ ከቀልዱ፣ ከወጉም ጨለፍ ጨለፍ ያደረግነውን ትቋደሱልን ዘንድ እነሆ ብለናል::

 በዚህ መልኩ የዓመቱንጉዞ ጨርሰናል:: በቀጣዩ ዓመት ዕቅዳችን በእቅድ መልክ የሰነቅናቸው በርካታ ጉዳዮች አሉን:: እናንተ አንብቡ፤ ተሳተፉ፣ በሃሳብና በአስተያየት ከጎናችን ሆኑ እንጂ ከጥበቡ፣ ከፍልስፍናው፣ ከባህሉ፣ ከታሪኩ፣ ከቅርሱ፣ ከማህበራዊ ጉዳዩ ከሌላ ሌላውም ብዙ እውቀትና ቁምነገር የሚያስጨብጡ ስራዎች ይኖሩናል::

በአዲስ አመት በመጣ ቁጥር በግለሰብ፣ በተቋምም ሆነ በአገር ደረጃ ሊተገበሩ የሚፈለጉ እቅዶች ይወጣሉ:: የሚሳካው ይሳካል፤ የማይሳካው አይሳካም:: እኛ ግን እቅድ እንዲሳካ እንተጋለን::

 ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ አገሪቱ በመልካም እና በመጥፎ ዜናዎች ስትናወጥ እንደነበረ እናስታውሳለን:: በዚህ ምክንያት ያልተሳኩ በርካታ እቅዶች እንዳሉ ይታሰበናል:: አገር ሰላም ስትሆን ነው መልካም እቅዶች የሚሰምሩት:: ያለፉትን እኩይ ተግባራት ታሪክ መሆኑን ተገንዝበን ዛሬንና ነገን በሰላም ለመኖር ቅን ልቡና ይዘን ወደ አዲሱ ዓመት እንሻገር:: ሰላማችን፣ ህብረታችን፣ አንድነታችን፣ መከባበራችን፣ መፋቀራችን ነው የሚያምርብን:: መልካም አዲስ ዘመን!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top