መጽሐፍ ዳሰሳ

ጦረኛው መናኝ አሌክሳንደር ሰርጌይቪች ፑሽኪን

መናኝ መነነ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ የዓለምን ነገር ሁሉ የናቀ፤ የነቀፈ፤ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ 100) ፤ በቤተ ክርስቲያን አባቶች ትንታኔም መናኝ ሚስቴ፤ ቤቴ፤ ትዳሬ የማይል፤ ሥጋውን በድሎ ለነፍሱ ያደረ፤ የሥጋ ጉዳይ ሁሉ የማያሳስበው፤ ያነሰ፤ የጎደለ፤ በብሕትውና የሚኖር፤ የጣመ፤ የላመ የማይቀምስ፤ ዳባ ለብሶ፤ ዳዋ ጥሶ፤ ጤዛ ልሶ፤ ደንጋይ ተንተርሶ የሚኖር ነው ይባላል። እናም የመናኝ ጦረኛነት የዓላማው አሳሳች ከሆነው ከሰይጣን ጋር እንደሆነ ማንም ይገምታል። በእርግጥ ሀገር በውጭ ጠላት ስትወረር፣

ደኅና ሰንብች ዜማ ደኅና ሰንብች ቅኔ፤

 ወንዶች በዋሉበት እውላለሁ እኔ::

በማለት ከጉባኤያቸው፤ ከየባዕታቸውና ከየገዳማቸው፤ ከየምናኔ ቦታቸው እየወጡ ለነጻነት ከጠላት ጋር የተጋደሉ መናንያንና መምህራን ብዙዎች ናቸው። ለዚህም በሀገራችን እንደነ አባ እንድርያስን የመሳሰሉ ጀግኖች መነኮሳትን ለመጥቀስ ይቻላል። ሩሲያዊው መናኝ ግሪጎሪ ኦትሪፒየቭ ግን ከዚህ የተለየ ዓላማ የነበረው መነኩሴ ነበር። ይህ መናኝ በብሕትውና በሩሲያ ገዳማት ውስጥ በመኖር ላይ እንዳለ አንድ ዓለማዊ ሐሳብ አውጠነጠነ። ይኸውም የንግሥና ሽሚያ በነበረበት አንድ ወቅት የሩሲያ ነገሥታት የዘር ሐረግ ከሆነው ከሮማኖቭ ሥርዎ መንግሥት እወለዳለሁና የሩሲያ ንጉሠ ነገሥት መሆን ይገባኛል በሚል የራሱን ሠራዊት አደራጅቶ ከፍተኛ ውጊያ ማድረግ ጀመረ። የዚህን መናኝ እውነተኛ ታሪክ መነሻ አድርጎ አሌክሳንደር ፑሽኪን «ትራጀዲ ቦሪስ ጎዱኖቭ» በሚለው ሥራው ላይ አቅርቦታል።

 ፑሽኪን በሰሜኑ የሩሲያ ክፍል በግዞት ላይ በነበረበት ጊዜ ‹‹የቭጌኒ ኦኔጊን›› የተሰኘ ድራማዊ ሥራውን ለማጠናቀቅ አስፋፍቶ ይጽፍ ነበር። እ.ኤ.አ በ1825 በሚሃይሎቭስክ የገጠር መንደር በነበረበት ወቅት ደግሞ ‹‹ቦሪስ ጎዱኖቭ›› የተባለ ሌላ ታሪካዊው ትራጀዲ ደርሶ ለኅትመት አብቅቷል።

ትራጀዲ ቦሪስ ጎዱኖቭ የእውነታዊ ሥነ ጽሑፍ /የሪያሊዝም/ ውጤት ነው። በዚህ ሥራው ፑሽኪን በዐሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻና በዐሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረቺውን ሩሲያ ያንጸባርቃል። የትራጀዲው ታሪክ የሚጀምረው በንጉሠ ነገሥቱ በቦሪስ ጎዱኖቭ ግጥም መነሻነት ሲሆን አስመሳዩና ባስማኖቭ የተሰኙ ገጸ ባሕርያት ከዛር ጎዱኖቭ ጋር ተፋጥጠው እናስተውላለን። ለአብነትም ከሰባተኛው ገቢር ከሩሲያኛ ወደ አማርኛ የተረጎምኩትን ቃለ ተውኔት እንደሚከተለው አመለክታለሁ።

ዛር ቦሪስ ጎዱኖቭ፡-

ንጉሠ-ነገሥት ተብየ ለስድስት ዓመት ስገዛ፣

ሰላም ነበረ ሀገሩ እኔም ነበርኩኝ ወሬዛ ፣

ደስታ ግን አልነበረኝም ነፍሴ በጉጠት ተይዛ።

በልጅነት ዘመኔ በእኔነቴ ላይ ታዝዞ፣

ስላደከመኝ አይደለም የፍቅር ጠኔ በዝብዞ።

እኛ ለፍቅር አልወደቅንም ለጊዜው ስሜት ደስታ፣

የሴትን ከንፈር ለመሳም ወይም ለወሲብ ርካታ፣

የልባችንን ፍላጎት ለመሙላት ብለን ቀጥታ፣

እንበለ ፃማ ወድካም የምንማስነው ጠዋት ማታ፣

ለግርማዊነት ሕይወት ነው ልዕልና ላለው ከፍታ።

ነገር ግን አሁን ቀዝቅዟል አሰልቺ ሆኗል ደባሪ፣

ጠውልጎ ታየ ከአበባ እንዳልነበረ ተፈሪ?

በነገሥኩበት ዕለት ላይ አስማተኞቹ በሙሉ፣

ሺህ ዓመት ገና ይገዛል ኃያል ብርቱ ነው እያሉ፣

በግብዝነት ተነሳሥተው ተንብየው ነበር ስለእኔ፣

እንደሚረዝም አስበው የሥልጣን እድሜ ዘመኔ።

በንጉሥነት ሥልጣኔ ጌታ በሰጠኝ ሕይወት፣

ከማዘን በቀር ፈጽሞ አልተደሰትኩም ቅንጣት።

መብረቃዊ ነው ኀዘኔ የገነት ዋጋ ስጦታ፣

ይህ ነው ለእኔ የተረፈኝ አሁን ሳስበው በእርጋታ፣

የመከራ ማቅ ለበስኩኝ ለእኔ አልተሰጠኝ ደስታ።

መተርጉማን የማይፈቱት ሕልም ነበረኝ ለሕዝቤ፣

ላበለጽገው ነበረ ኃያል ላደርገው አስቤ፣

ታላቅ ስጦታ በመስጠት ጸጥ ላሰኘው ከልቤ፣

ከአሸናፊነት ኑባሬ ፍቅሩን ልገዛው ሰብስቤ።

ነገር ግን ግዴለሽ ሆንኩኝ ሳልከፍል ቀረሁ ውለታ፣

ስለተጠላ ሥልጣኔ በተራ ሕዝቦች ምልከታ።

የሞተውን ሰው ለማፍቀር ይህንን ብቻ ያውቃሉ፣

የአውሬ ጩኸት ነው ምሳቸው ለጭብጨባ ነው የሰሉ፣

ግልብ በሆነው ግብራቸው ልባችንን ይንጣሉ።

ይህን ከሠራን እብዶች ነን የምናሳዝን ለቀባሪ፣

ረሃብ በቶሎ ይልካል ወደ ምድራችን ፈጣሪ፣

ይተላለቃል በሜዳ ሕዝቡ ይቀራል ከእዳሪ፣

እያንዳንዱ ሰው ይጠቃል በዚያ ቸነፈር አስፈሪ።

ጎተራየንም ከፍቼ፣

ብርና ወርቄን አውጥቼ፣

በሰዎች መኻል ስበትን እንዲበሉበት እንጀራ፣

እየገረሙኝ ያን ጊዜ ይራወጣሉ ለሥራ።

ቤታቸውንም ቢያቃጥል እሳት ነበልባል አይሎ፣

አዳዲስ ጎጆ ሠርቼ ተካሁላቸው በቶሎ፣

እኔንም ማማት ጀመሩ በዚህ ውርጅብኝ ቃጠሎ።

ባጎረስክ ትነከሳለህ ጽድቅ በሠራህ ኩነኔ፣

እስከዚህ ድረስ ይዘልቃል የተራ ሰዎች ብያኔ፣

ሌላውን ሁሉ ተውኩና እንደ አስተናጋጅ አደግድጌ፣

ፍቅርን ለማምጣት ተመኘሁ ከቤተሰቤ ፈልጌ።

የደስታየ ፈለጌ ምንጬ ቤተሰብ ነውና፣

ልቧ እንዲረካ በሐሴት ልጄን ልዳራት ለገና።

እንደ ማዕበል ሞት መጥቶ ሙሽራ ባልዋን ሲነጥቃት፣

ሴተኛ አዳሪ ተብላ ልጄን ሐሜት እንዳይገርፋት፣

እኔንም ደስታ ርቆኝ እንዳልባል ርጉም አባት።

እኔ እንኳን ብሆን መዋቲ ስለበዛብኝ ምቀኛ፣

የምሥጢር ገዳይ እኔ ነኝ የምቆራርጥ ሰይፈኛ፣

ቶሎ ማፋጠን አለብኝ የፌዎዶርን ፍጻሜ፣

በቃ አሁን ጊዜው ደረሰ ላሳጥራት የእርሱን

እድሜ።

እቴንም ልግደላት በቃ ያቺን የንግሥት መነኩሴ፣

ይህን የማደርግ እኔ ነኝ የቋያ እሳት ነኝ ለራሴ።

በመከራና በኀዘን አጽናኝ የለንም በዓለሙ፣

ንጹሕ ኅሊና ብቻ ነው የሚደርስልን እንደዓቅሙ።

ከዮርዳኖስ ምንጭ ልቆ ኅሊና ነጽቶ ከጠራ፣

በጽልመት ውስጥ ተለኩሶ በጨለማ ውስጥ እያበራ፣

ማሸነፉ የት ይቀራል የሰይጣንን ዕኩይ ሥራ።

ከምንሠራው ብዙ ነገር እንከንማ መቼ ጠፍቶ፣

ነፍስህን ሲያቃጥል ያድራል ታላቁን ኀዘን አምጥቶ፣

በመጣው ሥቃይ መከራ በወረርሺኙ ተመትቶ፣

በመመረዙ ምክንያት ልብም ያለቅሳል ተጠቅቶ።

ምስማር ጆሮ ውስጥ ተደርጎ በፋስ አናቱ ሲመታ፣

ዋይ ብሎ ሰው እንደሚጮህ የሥቃይ ኀዘን በርክታ፣

ራሱን እንደሚያዞረው በደሙ ጆሮው ጨቅይታ።

ስሜቱ ሲያጥወለውለው ስትዞርበት ምድሪቱ፣

ልብሱ ሲጨቀይ አንዳፍታ በደም ነጠብጣብ ደረቱ።

ብረር ብረር ያሰኘዋል ግን አይችልም የትም ጉዞ፣

እንደመጣበት አበሳ ከዚያው ይቀራል ደንዝዞ።

ሥቃይ በዝቶበት ኀዘኑ አካሉ በደም ተሳክሮ፣

ኅሊናው ንጹሕ አይሆንም ከዛች ዕለት ቀን ጀምሮ።

ስለ ቦሪስ ጎዱኖቭ በበለጠ ለመረዳት የሚከተለውን ታሪካዊ ክሥተት ማወቅ ይጠቅማል። እ.ኤ.አ በ1584 ለሥልጣን ስስት ሲል ልጁን የገደለውና በጨካኝነቱም ኢቫን ግሮዝኒ ( ነፍሰ ገዳዩ ኢቫን) የተባለው ንጉሠ-ነገሥቱ ኢቫን ግሮዝኒ ሲሞት ፌዎዶርና ዲሚትሪ የተባሉ ሁለት ትናንሽ ልጆች ነበሩት። ወዲያው የመጀመሪያ ልጁ ፌዎዶር በአባቱ ምትክ የሩሲያ ንጉሠ ነገሥት ተብሎ ነገሠ። ዲሚትሪ ደግሞ በወቅቱ ሕጻን ነበር። ፌዎዶር በሽተኛና ደካማ ባሕርይ ያለው ሰው ስለነበር መንግሥቱን ለመምራት ተቸገረ። ስለሆነም አጠቃላይ የሀገሪቱ ሥልጣን የፌዎዶር ሚስት ወንድም በሆነው በመስፍኑ በቦሪስ ጎዱኖቭ እጅ ገባ። ቦሪስ ብልህ፣ ሸረኛ ፤ ተንኮለኛና ኃይለኛ ሰው ነበር። እ.ኤ.አ በ1591 በኡግሊቼ ከተማ የ17 ዓመቱ ልጅና ወራሴ መንግሥት የሆነው ዲሚትሪ ሞተ። ሕዝቡ ደግሞ አልጋ ወራሹ ዲሚትሪ የተገደለው በቦሪስ ጎዱኖቭ መሆኑን ስለተረዳ ውስጥ ውስጡን ማማት ጀመረ። እ.ኤ.አ በ1598 ለይስሙላ በንጉሠ ነገሥትነት የተቀመጠው ፌዎዶር ሲሞት ቦሪስ ጎዱኖቭ የሩሲያ ንጉሠ ነገሥት ሁኖ ነገሠ።

 እ.ኤ.አ በ1605 ‹‹የዲሜትሪን ዘውድ ለመመለስና ለመውረስ የሚገባኝ ንጉሥ እኔ ነኝ። ስሜም ንጉሠ-ነገሥት ግሪጎሪ ኦትሪፒየቭ ይባላል።›› የሚል ጦረኛና መናኝ መነኩሴ ከብሕትውናው ወጥቶና ተዘጋጅቶ ወደ ፖላንድ ተጓዘ። የፖላንዱ ንጉሥ ደግሞ ሊረዳው ስለፈለገ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ጦር ሠራዊት ሰጠው። ጦረኛው መናኝ ግሪጎሪ ከፖላንድ ዋርሶው ከተማ ተነሥቶና ሠራዊቱን መርቶ ሞስኮ ከተማ ሲገባ ውጊያ ሳይካሄድ ባልተጠበቀ ሁኔታ ቦሪስ ጎዱኖቭ ሞቶ ተገኘ። መሳፍንቱና መኳንንቱ ‹‹ሕጋዊው ወራሴ መንግሥት መጣልን›› እያሉ ራሱን ንጉሠ-ነገሥት ነኝ ያለውንና ጦረኛውን መናኝ ግሪጎሪን በክብር ተቀበሉት። ወዲያው ጦረኛው መነኩሴ የቦሪስን ሚስትና ልጁንም አስገደላቸው። ራሱን ‹‹ወራሴ መንግሥት ነኝ›› ያለው ግሪጎሪ ኦትሪፒየቭ ሞስኮ እንደደረሰ የሩሲያ ንጉሠ- ነገሥት ተብሎ ነገሠ። በንግሥና ላይ የቆየው ግን ለአንድ ዓመት ብቻ ሲሆን በታሪክ ‹‹የቀዳማዊው ዛር የዲሚትሪ ወራሽ›› እየተባለ ይጠራል። እናም ፑሽኪን ይህንን ትራጂዲ የጻፈው ከላይ የሠፈረውን ታሪክ መሠረት አድርጎ ነው።

አሌክሳንደር ፑሽኪን በዚህ ትራጂዲያዊ ሥራው እንዳሳየው ቦሪስ የ17 ዓመቱን ልጅ ዲሚትሪን በምሥጢር ያስገደለው ወራሴ መንግሥት እንዳይሆን ስላሰበና ስለተመቀኘው ነው። ብድር በምድር አትቀርምና ቦሪስ ነግሦ ሀገር ሲያስተዳድር ሌላ ተቀናቃኝ ተነሣበት። ይኸውም መነኩሴው ግሪጎሪ ኦትሪፒየቭ ነው። ጦረኛው መናኝ በሩሲያ መነኩሴ ነግሦ አገር ይገዛል የሚለውን የቆየ ተረት እውነት አስመስሎና በንግግር መልክ የተጻፈውን ታሪክ መሠረት አድርጎ ለመንገሥ የተነሣው ልክ በእኛ ሀገር ነገሥታቱና መሣፍንቱ ከንጉሥ ሰሎሞን ዘር እንወለዳለን ወይም በምሥራቅ በኩል ቴዎድሮስ የሚባል ንጉሥ ይመጣል እያሉ ለንግሥና ሲራኮቱ እንደኖሩት ሁሉ እርሱም ከሮማኖቭ ሥርዎ መንግሥት የምወለድ እውነተኛው የሩሲያ ንጉሠ ነገሥት እኔ ነኝ ብሎ ነግሷል።

 ፑሽኪን ስለቦሪስ ጎዱኖቭ ሲጽፍ ‹‹ብልህ፣ ሥልጣን ወዳድ፣ እውነተኛውን የሩሲያ አልጋ ወራሽ ገድሎ ንጉሠ ነገሥት የሆነ ተንኮለኛ ሰው ነው›› ብሏል። ዕኩይ ተግባሩም እስከ መጨረሻ ደስታ ያጎናጸፈው መሆኑን በቦሪስ አንደበት የሚከተለውን ስንኝ የተናገረ መሆኑን እናጤናለን።

‹‹ለስድስት ዓመታት፣ በዘዴ ነግሼ ገዛሁ በጸጥታ፣

 መንፈሴ ግን ያዝናል የለኝም ደስታ።››

 ስለ ቦሪስ ወንጀለኛነት የሩሲያ ሕዝብ በገሐድና በሥውር፣ በሹክሹክታ ሲናገር ንጉሠ-ነገሥቱ ጎዱኖቭ ግን ሕዝቡን ጸጥ ረጭ ለማሰኘት አልቻለም። እናም ዝም ብሎ ታሪካዊ ፍርዱን ይጠባበቅ ጀመር። ሽማግሌው መነኩሴ ስለቦሪስ ወንጀለኝነት ደፍሮ ጽሑፍ በጻፈበት ወቅት ‹‹የሩሲያ ንጉሠ-ነገሥት ነኝ ብሎ የነበረው ሌላ ሰው እንደሚነሣበት ቦሪስ ተረዳ። “መነኩሴው ንጉሥ ጦሩን እየመራ ወደ ሞስኮ በተጠጋበት ወቅት ደግሞ ቦሪስ ሞቶ ተገኘ” ብሏል።

 ይህ ታሪካዊ ክሥተት ለፑሸኪን ጽሑፍ መነሻ ሆኖታል። በቦሪስ ጎዱኖቭ ትራጀዲ በዋናውና በወሳኙ ሚና ተዋናይ ሁኖ የሚጫወተው ሕዝብ ነው። በፑሽኪን አምነት ሕዝብ በታሪክ ውስጥ የማይደፈር ታላቅ ኃይል ነው። በሩሲያ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚኬድበት መንገድ ኋላቀር መሆኑን አሳይቶናል። የፖለቲካው ኋላቀርነት የግፍና የመከራ አገዛዝን እንደሚያራዝም ጭምር ይጠቁመናል። ለዚህም ቦሪስ ጎዱኖቭና ግሪጎሪ ሥልጣነ መንግሥት ለመያዝ የተጠቀሙበት ዘዴ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይሆን ጉልበት ነው። ፑሽኪን ሁለቱም የየግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ሰው እየገደሉ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ማሰባቸው ኋላቀርነታቸውን ያመለክታል ይለናል። ነገር ግን በመጨረሻ ሕዝብ እንደሚያሸንፍና የጉልበት ገዢዎች አወዳደቅ ትራጄዲያዊ እንደሚሆን ፑሽኪን በብዕሩ አጉልቶ ያስረዳናል።

 ፑሽኪን እንደሚለው የፖለቲካ ሥልጣን ከአንድ ወንጀለኛ ወደ ሌላው ጥፋተኛ፣ ሸረኛ ወይንም ከቦሪስ ጎዱኖቭ ወደ ጦረኛው መነኩሴ ግርጎሪ ቢተላለፍም የተጨበጠ ለውጥ ግን ሊመጣ አልቻለም። መናኙ መነኩሴ ግሪጎሪ ጦሩን ይዞ ወደ ሞስኮ ሲገባ ቦሪስ በመሞቱ ሕዝቡ እሰይ ብድር በምድር እያለ ቢናገርም ግሪጎሪ የቦሪስን ባለቤትና ልጁን ጭምር በግፍ ባስገደላቸው ጊዜ በከፍተኛ ኀዘን ተዋጠ። የሩሲያ ሕዝብ ‹‹የዛር ዲሚትሪ ኢቫኖቪችን ነፍስ ይማር፣ ዐፈሩን ገለባ ያድርግለት›› እያለ የኅሊና ጸሎት አደረሰ። በዚህም ግሪጎሪና ሕዝቡ ሆድና ጀርባ ሆኑ። ዝምታ ሰፈነ። በዝምታም አማካኝነት ሕዝቡ ለግሪጎሪ ያለውን ጥላቻና ተቃውሞ ገለጠ። ቦሪስ ጎዱኖቭ በሩሲያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ በሪያሊዝም መሠረተ ሐሳብ ላይ የተነሳ የመጀመሪያው ሥራ ነው። ፑሽኪን በዚህ ትራጄዲያዊ ሥራው በዐሥራ ስድስተኛውና በዐሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሩሲያ ማኅበረሰብ ልክ እንደ አሁኒቱ ኢትዮጵያ በሐሳብ የተከፋፈለና አልተረጋጋ ሁኔታ ሥልጣን ለእኔ ይገባኛል በሚል የተመሰቃቀለ ነበር። እናም ይህ ትራጄዲያዊ ተውኔት የሩሲያ ሕዝብ የነበረበትን የፖለቲካና የአስተዳደር ብልሽት፤ ብሶትና ችግር ያመለክታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top