አድባራተ ጥበብ

ጥቂት ስለ ዘመናዊ የክዋኔ ጥበብ

እንበል እና በመንገድ ላይ እየተጓዛችሁ ነው። ሰው በሚሰበሰብበት ዋና መንገድ ወይም ጎዳና መሃል አንድ ብቻውን የቆመ ሰው አንዳች አይነት ነገር በእጁ ይዞ ወይም ልብስ ለብሶ ወይም የተለየ እንቅስቃሴ እያደረገ ልትመለከቱት ትችላላችሁ። ይህንን ሁነት ጥቂት ሰዎች ብቻ ሊከታተሉት ይችላሉ። ወይም የስነ- ጥበብ ስራዎች በሚቀርቡባቸው የዓውደ ርዕይ አዳራሾች ውስጥ ሆነው አንድ ወይም ሁለት ተዋንያንን ብቻ ያካተተ፤ ምናልባትም ንግግር የሌለበት የጥበብ አይነት ሊመለከቱ ይችላሉ … ይህ ዘመናዊው የክዋኔ ጥበብ ከሚከተላቸው መንገዶች አንዳንዶቹ ናቸው!! በዘመናዊው የክዋኔ ጥበብ የክዋኔ ቦታ ይለወጣል፣ የተመልካች ቦታ ይቀየራል፣ የጊዜ ሁኔታ ይሻራል … በቴአትሩ ዓለም የለመድነው አኳኋን ሁሉ እዚህ የለም። ለዛሬ ጥቂት ስለዚህ ጥበብ እናውራ!

 ዘመናዊው የክዋኔ ጥበብ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት የአውሮፓ ቴአትር አሁን ያለውን ቅርፁን መያዝ የጀመረው ከአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ አስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ነው። በተለይ በአውሮፓ በዚሁ ዘመን የተቀሰቀሰው የኢንዱስትሪ አብዮት ሰፊውን ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ሁናቴ ለውጧል። የኢንዱስትሪ አብዮቱ ካመጣቸው ለውጦች ዋነኞቹ ደግሞ የማህበረሰብ የአኗኗር እና የሀብት ልዩነት ናቸው። ሰዎች የሀብት ልዩነታቸው በሰፋ ቁጥር ሁኔታዎችን የሚመለከቱበት መነፅር፣ የኑሯቸው አኳኋኋን እንዲሁም የፍልስፍና አካሄዳቸው ይለያያል። በመሆኑም ኢንዱስትሪው ካመጣው መጠነ ሰፊ የሆነ ለውጥ ጋር በተያያዘ የኪነጥበብ መስመሩም እንዲሁ ሰፊ ለውጥ ማምጣት ጀመረ። አዳዲስ አካሄዶች፣ አጻጻፎች እና የትወና መንገዶች መፈጠር ጀመሩ። እነዚህ የኪነጥበብ ስራዎች (ማለትም በስነ-ፅሁፍ፣ ስነ-ግጥም፣ ቴአትር እና ሙዚቃ) የየወከሉበትን ማህበረሰብ ህይወት በማሳየት ላይ ትኩረት ያደረጉ ነበሩ። ለምሳሌ ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት የነበሩት አብዛኞቹ የኪነጥበብ ስራዎች በተለይ የከፍተኛውን መደብ (bourgeois) ህይወት እና የአኗኗር ሁኔታን በማሳየት እና በማዳነቅ ላይ የተጠመዱ ነበሩ። ከአብዮቱ በኋላ ግን ይህንን ሁኔታ በሚገባ የሚገነዘቡ እና ኪነ-ጥበብ የከፍተኛውን መደብ ህይወት ብቻ ሳይሆን የዝቅተኛውን እና የድሃውን ማህበረሰብ ህይወት ማሳየት አለባት በሚል የሚሞግቱ ባለሙያዎች ተፈጠሩ። እነዚህ የኪነጥበብ ሰዎች በሰፊው የኪነ-ጥበብ አተያይ ላይ አዲስ የሆነ መንገድ ከፈቱ።


በ 1960ዎቹ የዘመናዊ ክዋኔ ጥበብ ጀማሪ እና ዝነኛ ከነበሩት መሃል አንዱ አለን ካፕሮው በክዋኔ ላይ

የቴአትር ጥበብም ከዚህ አብዮት እና ለውጥ አላመለጠም። በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መቋጫ እና በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ ቴአትርን በልዩ መነፅር መመልከት እና በአዲስ መንገድ መፃፍ፣ ማዘጋጀት እና መተወን የዘመኑ ሁነት መገለጫ ሆኑ። በተለይ በቴአትር ስራ ላይ ያሉትን ባለሙያዎች ግንኙነት ከአጠቃላዩ ማህበረ ፖለቲካዊ ግንኙነቶች አንፃር በመመልከት እና በመተንተን ለዘመናት ከተለመደው መንገድ ወጣ ያለ የአፃፃፍ እና አዘገጃጀት መንገዶችን መከተል ጀመሩ። ለምሳሌ አንድ ቴአትር በሚዘጋጅበት ጊዜ በቴአትሩ ፀሃፊ እና አዘጋጅ መሀል ያለው ግንኙነት የገዢ እና የተገዢ ግንኙነትን ያሳያል ሲሉ ይሞግታሉ። እንበልና ፀሃፊ ተውኔቱ ፅሁፉ ያለሱ ፍቃድ ምንም እንዳይነካ እና እሱ ካለው በቀር እንዳይሰራ መከላከሉ የእሱን እና የሌሎች ባለሙያዎችን ያልተገባ የገዢነት እና ተገዢነት ግንኙነትን ያሳያል፤ እናም መቀየር አለበት ይላሉ።

በሌላ በኩል በቴአትሩ አዘጋጅ እና ተዋንያን መሀል ያለውም ግንኙነትም እንደዚሁ ሊተነተን የሚገባው ነው ይላሉ። የቴአትሩ አዘጋጅ ተዋንያንን “እንዲህ ሁኑ”፣ “እንዲህ ተውኑ” እያለ ሲያዝ በሁለቱ ባለሙያዎች መሃልም እንዲሁ የገዢ እና የተገዢ ግንኙነት ጎልቶ ይታያል። ስለዚህም ለነዚህ ግንኙነቶች መፍትሄ መሆን የሚችለው ሁሉም በጋራ በእኩልነት የሚሳተፍበት የቴአትር ፅሁፍ፣ ዝግጅት እና ትወናን መከተል ነው ይላሉ። በመሆኑም በዚህ ፍልስፍና ተመርተው የሚሰሩ ቴአትሮች በአብዛኛው ሃሳብ እና ታሪካቸው በቴአትሩ ቡድን አባላት በጋራ ተፅፎ፣ በጋራ ተዘጋጅቶ እና በጋራ ተተውኖ ለተመልካች ይቀርባል።


ዝነኛዋ ማሪና አብራሞቪች በክዋኔ ላይ

 ከዚህም ባሻገር በቴአትሩ አቅራቢዎች እና በተመልካች መሃል ያለው የአቀማመጥ ሁኔታ ይህንኑ የገዢ እና የተገዢ ሃሳብን ያመላክታል፤ ይኸም ሊቀየር ይገባዋል ሲሉ ሞግተዋል። ለምሳሌ አንድ ተዋናይ በመድረክ ላይ ከፍ ብሎ ቆሞ፣ ቀና ብሎ አንጋጦ የሚመለከተውን ተመልካች ወደታች እየተመለከተ ሲተውን፣ ሊያስተላለፍ የሚችለው መልክት “እኔ ካንተ እሻላለሁ” የሚል እና የበላይነትን ካባ ለተዋናዩ የበታችነትን ደግሞ ለተመልካቹ የሚያቀብል በመሆኑ ይህም ተስተካክሎ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት ሊዋሃድ የሚችል አቀራረብ መከተል ይገባዋል ይላሉ። ለዚህም መፍትሄ እንዲሆን ክብ መድረክ እንዲሁም ልዩ ልዩ ስልቶችን በመፍጠር ወደ ተመልካች የሚቀርቡብት መንገድ አስልተዋል። ተመልካችም አንዳንድ ጊዜ የቴአትር ስራውን በመክበብ፣ ሌላ ጊዜ የቴአትሩ አካል በመሆን ከተዋንያን ጋር እጅግ የቀረበ ግንኙነት በመፍጠር አዲስ ቴአትርን የመመልከቻ ስልት ፈጥሯል።

ይህ ተግባር እና ንቅናቄ በአውሮፓ እና አሜሪካ ሲመጣ እጅግ

የበዙ የቴአትር አቅርቦት ስልቶች መፈጠር ጀመሩ። የቴአትር አቅርቦቶቹ በአፃፃፋቸው፣ በአዘገጃጀታቸው እና በትወናቸው አዲስ አቀራረብን ይዘው በመምጣታቸው እና ለተመልካችም አዲስ በመሆናቸው ሰፊ ተቀባይነትን ለማግኘት በቅተዋል። ከነዚህ አዳዲስ የቴአትር ጥበቦች አንዱ ዘመናዊው የክዋኔ ጥበብ ነው። ይህ የክዋኔ ጥበብ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ጠቅላላውን የቴአትር አዘገጃጀት እና አተዋወን ስልት በመቃወም የተፈጠረ ጥበብ ነው። ባልተለመደ መልኩ የቴአትር ጥበብን የሚመስል ግን ያልሆነ፣ ከቴአትር ጥበብ ዋና ዋና ስልቶችን በመዋስ የራሱን ቀለም ፈጥሮ ያደገ ጥበብ ነው።

 ዘመናዊው የክዋኔ ጥበብ በተለይ በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ በአውሮፓ እና በአሜሪካ በሰፊ መታወቅ የጀመረ ሲሆን ዋና ዋና በሚባሉ የጥበቡ አራማጆች ምክንያት ሰፊ የሆነ የምርምር እና የጥናት ምንጭ ሆኗል። አሜሪካዊው ታዋቂ የዘመናዊ ክዋኔ ምርምር መሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ሸክነር ዘመናዊውን የክዋኔ ጥበብ በሁለት መንገድ እንዲህ ይፈታዋል፦

 “ክዋኔ ማለት በአንድ በኩል ታሪካዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ሁኔታዎች/ውርሶች አንድን ተግባር ክዋኔ ነው ብለው ሲፈርጁ ወይም ስም ሲሰጡ ሲሆን በሌላ በኩል ሀይማኖታዊ ተግባራት፣ ጨዋታዎች እና የዕለት ተዕለት የሰው ልጅ እንቅስቃሴዎችን በሞላ ክዋኔ ብለን ልንጠራቸው እንችላለን። ነገር ግን ይህ አጠራር እንደየአጠቃቀሙ እና ባህላዊ ሁኔታው የሚለያይ መሆኑ ከግምት ሊገባ ይገባዋል።” (ሸክነር፣2006)

ይህ ሃሳብ ስለ ዘመናዊው የክዋኔ ጥበብ ስናወራ ሁለት ነገሮችን ከግምት እንድናስገባ የሚያሳስብ ነው። አንደኛው የክዋኔ ጥበብ ዋነኛ መነሻው የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ማህበረ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ይህ እንቅስቃሴ እና ከዚህም እንቅስቃሴ የሚመነጨው የክዋኔ ጥበብ እንደየሁኔታው ባህል እና የማህበረሰብ ስነ-ልቦና አረዳዱም ይለያያል። በመሆኑም ይህን ሰፊ የሆነ የአረዳድ መንገድ መክፈት ዘመናዊውን የክዋኔ ጥበብ ሃሳብ ለመረዳት እና እንደየባህሉ ለመተንተን እድል ይሰጣል። ዘመናዊው የክዋኔ ጥበብ እንደተለመዱት የቴአትር እና ሌሎች የክዋኔ ጥበቦች ተለምዷዊ የአፃፃፍ እና የአዘገጃጀት መንገድን አይከተልም። እንደ ቴአትር የግድ ብዙ ባለሙያዎችም እንዲሳተፉበት አያስገድድም። አንድ ባለሙያ እንደጸሐፊም፣ አዘጋጅም፣ ተዋናይም ሆኖ መከወን ይችላል። በዚህም የሚፈልገውን/የምትፈልገውን ሃሳብ ለማስተላለፍ ይችላል። ከዚህም ባሻገር ዘመናዊው የክዋኔ ጥበብ የሰዎችን የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ መሰረት በማድረግ የሚሰራ ሲሆን ቀላል በሆነ መንገድ ሰፊ ሃሳብን ማስተላለፍ ላይ ትኩረት ያደርጋል። የክዋኔ ጥበቡ ባለሙያ የዕለት ተዕለት መጠቀሚያ ቁሳቁስን ብቻ ተጠቅሞ ኪነጥበባዊ መንገዱን በጠበቀ መልኩ ሰፊ የሆነ የመነጋገሪያ እና የመወያያ መነሻ የሚሆን ሃሳብ ማስተላለፍ ይችላል።

የክዋኔ ጥበብን በሰፊ ትርጓሜው ስንረዳው የሚከተሉት ተግባራት ይኖሩታል፦

 – ማዝናናት

 – አንድን ሃሳብ/ተግባር ውብ አድርጎ ማቅረብ

 – ማነንትን ለመቅረፅ/ ለመቀየር

 – ማህበረሰብን ለመፍጠር (የሃሳብ ተጋሪን ለመፍጠር)

– ለደህንነት

– ለማስተማር ወይም ለማሳመን

 እነዚህ ተግባራቱ ዘመናዊውን የክዋኔ ጥበብ እንደሌሎቹ የኪነ-ጥበብ አይነቶች ለመረዳት እና ለመተንተን ዕድል ይሰጣሉ። ከአስራ ዘጠኝ መቶ ስልሳዎቹ ጀምሮ ዝነኛ ከነበሩ የዘመናዊ የከዋኔ ጥበብ ባለሙያዎች መሃል ዩጎዝላቪያዊቷ ማሪና አብራቮሚች ዋነኛ ተጠቃሽ ነች። ማሪና በስልሳዎቹ ከባለቤቷ ከጀርመናዊው ኡላይ ጋር በመሆን በጋራ እና በተናጠል ልዩ ልዩ ዘመናዊ የክዋኔ ጥበቦችን ለህዝብ አቅርበዋል። ከታወቁት ስራዎቿ መሀል፡ Rhythm 10, (1973), Rhythm 5, (1974) Rhythm 2, (1974) Cleaning the Mirror, (1995) Spirit Cooking, (1996) ተጠቃሽ ናቸው።

ከማሪና ባሻገር በአሜሪካ እና አውሮፓ በዚሁ ዘመናዊ የክዋኔ ጥበብ ዝነኛ የሆኑ በቡድንም በግለሰብም ደረጃ ብዙ ተፈጥረዋል። እነዚህ ባለሙያዎች ዘመናዊውን የክዋኔ ጥበብ ከጀማሪ የአውሮፓ ጥበብነት ወደ ዓለም ዓቀፋዊ ተቀባይነት አሸጋግረውታል። በዩኒቨርሲቲዎች ይህንን የኪነጥበብ አይነት ለብቻው የሚያጠና የትምህርት ዘርፍ (አሁን አሁን በመላው ዓለም) ተከፍቶ ይህንን ጥበብ ይመረምራል።

 በሀገራችን ይህ ጥበብ ያን ያህል አልታወቀም። ተቀባይነቱም ሰፋ ተደርጎ ተስርቶ አልተመረመረም። ነገር ግን በዚህ ሁኔታም ቢሆን ጥበቡን ለማስተዋወቅ እና ለራሳቸውም ኪነ ጥበባዊ እርካታ ይህንን ጥበብ ለመሞከር የዳዱ እጅግ በጣት የሚቆጠሩ ባለሙያዎች አሉ። ከነዚህም መሀል ሄለን ዘሩ፣ ሙሉጌታ ገብረኪዳን፣ ዮሃንስ ሙላት እና ሌሎችም ይገኙበታል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲው የባህል ማዕከል አባላትም በተለያዩ ጊዜያት ጥቂት ሙከራዎችን ለተወሰኑ ተመልካቾች አቅርበዋል። እነዚህ ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ልዩ ልዩ ሃሳቦቻቸውን ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች፣ በታሪካዊ ማስታወሻ ስፍራዎች፣ በመካነ መቃብር እንዲሁም በሰዕል መሳያ ስቱዲዮዎች ውስጥ ስራዎቻቸውን ለተመልካች አቅርበዋል። በዚህ ስራዎቻቸውም የክዋኔ ጥበብን ለሀገራችን ተመልካች ለማስተዋወቅ ሞክረዋል። ከሚሰጠው ጠቀሜታ እና ኪነጥበባዊ ውበቱ አንፃር ወደ ፊት በዚህ ጥበብ ላይ በሰፊው የሚሰሩ ባለሙያዎች ተፈጥረው ጥበቡ ይበልጥ እንደሚስፋፋ ተስፋ አለኝ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top