በላ ልበልሃ

የፌደራሊዝም ‹ያኑሳዊ› ገጽታ

የሀገራችን የፌደራል የፖለቲካ ሥርዓት በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሷል። በመሆኑም አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል። ፍራንዝ ፋኖን እንደተናገረው “ፌደራሊዝም ፍቱን መድኀኒት ነው ባይባልም” የተሻለ ዘመናዊ የአስተዳደር ስልት መሆኑ አያከራክርም። ከልምድ እንደታየው የፌደራሊዝምን አስተዳደር ፍልስፍና ወይም መርሆ ተከትለው ፌደራላዊ የፖለቲካ ሥርዓትን የዘረጉ ብዙ ሀገሮች የእድገት ጎዳና እና የግጭት መቆጣጠሪያ ወይም የመፍትሔ ስልት ሆኖ አገልግሏቸዋል። እያገለገላቸውም ይገኛል። በአንፃሩ ደግሞ በተለይም እንደ አፍሪካ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች ቢሞከርም ውጤቱ ፍሬ አልባ ሆኖ መክሸፉ ብዙ የተፃፈበትና የተነገረለት ሀቅ ነው። በቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረትና በዩጎዝላቪያ ፌደሬሽኖችም ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ዋጋ ማስከፈሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በሀገራችን ያለው የፌደራል ሥርዓትም ከእነዚህ ጋር የሚፈረጅ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በተለይም የችግሩን ባሕርያት በማመልከት አስተያየቶችን መስጠት ይሆናል። ለዚህም ጽሑፉ የኢትዮጵያው የፌደራል ሥርዓት ወደ ተመሳቀለባቸው ገጽታዎች ከማምራቴ በፊት ለግንዛቤ እንዲረዳ በፌደራሊዝም ፅንሰ-ሀሳቦች፣ ዋና ዋና መርሆዎችና የፌደራል ሥርዓት አስፈላጊ ምክንያቶች ላይ አጭር ገለፃ ለመስጠት እሞክራለሁ።

በመጀመሪያ ‹ፌደራሊዝም›፣ ‹ፌደራል› እና ‹ፌደሬሽን› የሚሉ ፅንሰ-ሀሳቦች መሠረት ተደርጎ የተወሰደበትን ሥርወ- ቃል በአጭሩ እንመልከት። ለምሳሌ ኤላዛር (1980)፣ ቼን (1999) እና አሊፍ (2015 እንደገለፁት የፅንሰ-ሀሳቦቹ ሥርወ-ቃል ‹ፌዱስ› (‹foedus› ) የሚለው ጥንታዊ የግሪክ ቃል ነው። ሥርወ-ቃሉ በአፋዊ ትርጉሙ ወይም በቁሙ የሚሰጠው ፍች ‹ቃል- ኪዳን›፣ ‹ስምምነት›፣ ‹በቃል-ኪዳን› ወይም ‹በስምምነት፣ አመኔታ ላይ የተመሠረተ የትብብር ግዴታ መግባት› (በእንግሊዝኛው ‹ኮቬናንት›) የሚል ነው። ከዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው የቃል ኪዳን ስምምነቱ ሲከናወን የሚያካትታቸውን፣ ለምሳሌ፡- (ሀ) የስምምነቱ ፍሬ ነገር (ርዕሰ- ጉዳይ)፣ (ለ) ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ የህዝብ ውክልና ተቀባይነት ያላቸው የፖለቲካ ኀይሎች (የስምምነቱ ተዋንያን) መኖራቸውን፣ (ሐ) የእነዚህ የስምምነቱ ተዋንያን ታሪካዊ የአመጣጥ ዳራቸው ምን እንደሚመስል፣ (መ) በስምምነቱ ተዋንያን መካከል የሚኖር ፍላጎት፣ አቋም፣ ሚናና ድርሻ፣ (ሠ) የተደረሰበት የቃል ኪዳን ስምምነት አሳሪ ይዘት፣ (ረ) ተስማሚ ወገኖች የጋራ ዓላማቸውን በቁርጠኝነት ለማሳካትና በተግባር ለማዋል የፈጠሩት የመተማመን ደረጃ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ጉዳዮችን ጭምር ነው። ከዚሁ ጋር አብሮ መገንዘብ የሚያስፈልገው የስምምነቱ ተዋንያን ወደ ስምምነት ሲመጡ በአንድ ወይም በሁለት ኀይሎች ፍላጎት ግፊትና ጫና ሳይሆን የጋራ ጥቅምን መሠረት አድርገውና የጋራ መግባባት፣ መተማመን፣ የርስ በርስ ‹መተሳሰብ፣ መረዳዳት›፣ ‹ትብብር› እና ‹መደጋገፍ› ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው። በተለይም “የስምምነቱ ተዋንያን ታሪካዊ የአመጣጥ ዳራ” የሚለው ‹የፌዱስ› ወይም የቃል ኪዳኑ ዓይነተኛ ገጽታ ነው። ይህንም የመስኩ ምሁራን በሁለት ከፍለው ስያሜ ሰጥተውት ይገኛል። አንደኛው በታሪክ በአንድ ሉዐላዊ መንግሥት ጥላ ሥር ይተዳደሩ የነበሩ፣ ነገር ግን፣ የዚያን መንግሥት ሥርዓት መጥፎ የአስተዳደር ይዞታ በመቀየር የፌደሬሽን የፖለቲካ ሥርዓት መመሥረት የሚሹ ሲሆን “አዲሱን ሥርዓት በአንድነት/በህብረት ይዞ መቀጠል” (በእንግሊዝኛው አጠቃቀም “holding together”) በሚል እሳቤ ይጠቀሳል። ለዚህ በአንድነት ይዞ መቀጠል ለሚባለው የፌደሬሽን ዓይነት ምሳሌ የሚሆነው በኢትዮጵያ፣ በሕንድ፣ በቤልጂየም፣ በካናዳና በስፔን የታየውን ያመለክታል።

ሁለተኛው ወደ ስምምነቱ የመጡ ኀይሎች ስምምነት ከማድረጋቸው በፊት በየበኩላቸው የየራሳቸው ሉዐላዊ መንግሥት የነበሩ ወይም ከነበሩበት ሌላ ሉዐላዊ መንግሥት አፈንግጠው/ተገንጥለው በመምጣት ፌደራል መንግሥት መሥርተው አብረው ቢኖሩ ሁላችንም “ይበልጥ እንጠቀማለን” የሚል እምነት ይዘው ወደ አንድነት በመጡ ጊዜ “በአንድ አብሮ መምጣት”፣ በእንግሊዝኛው አጠቃቀም (“coming together”) ተብሎ ይጠቀሳል። ለዚህ አብሮ ወደ አንድነት መምጣት ለሚለው በምሳሌነት የሚጠቀሱት በአሜሪካ፣ በስዊዝላንድ እና በአውስትራሊያ የተደረገው ክላሲካል ፌደራሊዝም ይሆናል። እነዚህ ሁለቱ የአመጣጥ ታሪኮች ቁልፍ የሆኑ የፅንሰ-ሀሳብ አንድምታ ስላላቸው አንዱን ቃል የሌላው ተለዋጭ አድርጎ መጠቀም ትልቅ ስህተት መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ምሁራን ‹ፌዱስ› የሚለው ጥንታዊ ሥርወ-ቃል በሚሰጠው ፍች ላይ ተመሥርተው ‹ፌደራሊዝም› ለሚለው ፅንሰ-ሀሳብ በተለይም እንግሊዛዊው የሕገ- መንግሥትና አስተዳደር ባለሙያ ኬ.ሲ. ዌር (እኤአ) በ1946 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጠውን መሠረታዊ ብያኔ ተከትሎ ባለፉት 70 ዓመታት ውስጥ እጅግ በርካታ ብያኔዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል። ዌር የሰጠው ብያኔ፣ “ፌደራሊዝም በብሔራዊና በክልላዊ መስተዳድሮች/መንግሥታት መካከል የሥልጣን ክፍፍል የተደረገበት፣ እያንዳንዱ በአንድ ግዛት ውስጥ በሕግ በተደነገገ እኩልነት በተቀናጀ ሁኔታ ትብብር በነፃነት ተግባሩን እየተወጣ የሚገኝበት ዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት“ ነው ይላል። ብያኔው ከዚህ በኋላ ለተሰጡ ብያኔዎች የመሠረት ድንጋይ ሆኖ ቢያገለግልም ምሁራን ፌደራሊዝም ‹ሥርዓት› ተብሎ መገለፁን አያሌ ትችቶችና ሂሶች አቅርበውበት ነበር:: በመሆኑም (እኤአ) በ1963 ዓ.ም. ዌር ‹ሥርዓት ነው› ብሎ ገልፆት የነበረውን አሻሽሎ ‹መርህ›፣ ‹ዘዴ›፣ ‹ሥልት› ወይም ‹መንገድ› ማለቴ ነበር በሚል ማስተካከያ ሰጥቷል::

ዌር ከሰጠው ፈር ቀዳጅ ብያኔ በኋላ በተለያዩ የምርምር መስኮች በሚገኙ ምሁራን የተሰጧቸውን በርካታ ብያኔዎች የጋራ ጭብጦች አጠቃለን ስንመለከት ከሞላ ጎደል በሚከተሉት ጭብጦች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሆነው እናገኛቸዋለን። እነዚህም ፌደራሊዝም፣ “ራስን በራስ የማስተዳደር ውስጣዊ ነፃነትና የጋራ አመራር፤ በፌደራል መንግሥትና በክልል መስተዳድሮች መካከል የጋራ ሉዐላዊነት፤ በፌደራል መንግሥትና በክልል መስተዳድሮች መካከል በሕገ-መንግሥት የተገነባ እኩል የሥልጣን ክፍፍል፣ የጋራ ውሳኔ፣ የጋራ ኃላፊነትና ተጠያቂነት፤ የሚሉ ናቸው።“

ለምሳሌ አላዛር (1987) “ፌደራሊዝም ራስን በራስ ማስተዳደር ሲደመር የጋራ ሥልጣን ማለት ነው” ይለዋል::

 በሀገራችን ብዙ ሰዎች (ፖለቲከኞች እና ምሁራን) ‹ፌደራሊዝም ሥርዓት› ነው በሚል ሲገልፁ ይደመጣሉ። ይህ ትክክል አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህም የመስኩ ዕውቅ ምሁራን፣ ለምሳሌ፡ – ዋትስ (1994፣ 2000) እና ኦሌሪ (2003)፣ “እንደተለመደው ‹ፌደራሊዝም› የሚለው ፅንሰ-ሀሳብ በአጠቃላይ ፌደራላዊ የፖለቲካ ሥርዓቶች የምንላቸውን ተቋማዊ አደረጃጀቶች ተስማሚ የሆነ አጠቃቀም የሚገልፅ የአደረጃጀት መርሆን የሚወክል እሳቤ ሲሆን ይህም የፌደራሊዝም መርሆዎችን የሚያንፀባርቁ ፌደሬሽኖችን፣

ከልምድ እንደታየው የፌደራሊዝምን አስተዳደር ፍልስፍና ወይም መርሆ ተከትለው ፌደራላዊ የፖለቲካ ሥርዓትን የዘረጉ ብዙ ሀገሮች የእድገት ጎዳና እና የግጭት መቆጣጠሪያ ወይም የመፍትሔ ስልት ሆኖ አገልግሏቸዋል

የተወሰኑ የህብረት ዓይነቶችን ለምሳሌ ፌደሬሲዮኖችን፣ ህብረት የፈጠሩ መንግሥታትን እና ህብረት የመሠረቱ ድንበር-ዘለል ተግባራዊ ባለሥልጣኖችን የሚያካትትና ብዛት ያላቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚገልፅ ቃል ነው።“ ሲሉ በማያሻማ ሁኔታ ገልፀውታል። ሮበርት አግራኖፍም (2011) በበኩሉ፣ “ፌደራሊዝም የሚለው ፅንሰ-ሀሳብ የዘመናዊ አስተዳደር ሥርዓት ፍልስፍና ወይም መራሔ-ሀሳብ ወይም ርዕዮተ-ዓለም እንደማለት ነው።” ሲል በተመሳሳይ ገልፆታል።

 ይህን ካልን ሥርዓት የሚባለው የፌደራሊዝሙ ትኩረት የሆነው የፌደሬሽን የፖለቲካ ሥርዓት አደረጃጀት ነው። ዋትስ (1987) እንደሚያስረዳው፣ “ፌደሬሽን የሚለው ቃል በአጠቃላይ የፌደራል ፖለቲካ ሥርዓቶች ተብሎ በሚጠቀሰው ምድብ የሚካተት አንድ የተለየ ዓይነት ሥርዓት ነው (121)። እንደ ተጨባጭ ተቋማዊ የፌደራል እውነተኛ መርህ ፌደሬሽን የፌደራሊዝም መርሆዎችን ወይም ሀሳቦችን በተግባር ተቋማዊ ኅልውና በመስጠት በሥራ የሚተረጉሙ መዋቅሮችን፣ ተቋሞችን እና ቴክኒካዊ ስልቶችንና ዘዴዎችን ያካትታል።“ ይላል። ፌደሬሽኖች በቅርፅ የተለያዩ ናቸው። ለአንዱ ሀገር የተመረጠና በተዋጣ ሁኔታ የሚሠራ የፌደሬሽን ዓይነት በመርሆ፣ በመዋቅራዊ አደረጃጀት፣ በርዕዮተ-ዓለማዊ የፖለቲካ ፍልስፍና፣ በግብና በትብብሩ አካላት ፍላጎት ከሌላው የሚመሳሰልባቸው ገጽታዎች መኖራቸው ባይካድም ሰፊ ልዩነት አለው። የዚህ ምክንያትም ፌደሬሽኖች እንደየሀገራቸው ባህላዊና ሥነ-ልሳናዊ፣ ታሪካዊ፣ የማንነት ጥንቅር አውዶችና በወቅቱ ከሚኖረው ነባራዊ እውነታ፣ ወዘተ፣ ላይ ተመሥርተው የሚወሰኑና የሚቀመሩ በመሆኑ ነው። ስለዚህ በአንድ ሀገር አውድ ውስጥ ውጤታማ የሆነ ፌደራላዊ ሥርዓት በሌላው ሀገር አውዶች ውስጥ የመፍትሔ ሞዴል ይሆናል በሚል እንዳለ ቀድቶ ለመጠቀም መሞከር ከመፍትሔነቱ ይልቅ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ በኪሣራ የሚጠናቀቅ መሆኑን የብዙ ሀገሮች ልምዶች ያረጋግጣሉ (አሊፍ 2015)። ዲያመንድ እንደሚያስገነዝበው ሁሉም የፌደራላዊ ሀገሮች መንግሥታት የሥልጣን ክፍፍል ያላቸው አይደሉም። በተቃራኒውም ሁሉም የአንድነት መንግሥታት ማዕከላዊነትን የሚያጠብቁ አይደሉም። ለምሳሌ ካናዳ እጅግ በጣም የሥልጣን ክፍፍል ያላት ሀገር ናት። በአውስትራሊያና በጀርመን ደግሞ ሥልጣን በማዕከላዊነት የተያዘባቸው ፌደሬሽኖች ናቸው። ከአውስትራሊያና ከጀርመን ሲነፃፀር የኖርዲክ የአንድነት ሀገሮች የበለጠ ማዕከላዊነት ያላቸው ሆነው ይገኛሉ። የእነዚህ ሀገሮች የፌደራል መንግሥታት ከቤልጂየምና ከስዊዘርላንድ የተለየ የአደረጃጀት ቅርፅ አላቸው። በምዕራቡ ዓለም ከሚገኙት የብዝኀ-ባህል አገሮች ከህንድና ኢትየጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ከሚገኙት ይለያሉ።

 የፌደራሊዝም ቅድመ-ሁኔታዎች እና መሠረታዊ መርሆዎች በትውፊታችንም “አጥብቆ ያሠረ ዘቅዝቆ ይሸከማል” እንደሚባለው ዓይነት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርዓት ምሥረታ ከፌደራሊዝም አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎች መሟላትና ዝግጅት እንዲሁም ፌደራሊዝም ከሚከተላቸው መሠረታዊ መርሆዎች አኳያ እንዴት ይገለፃል? የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ወይም ጥያቄ ነው። የፌደራሊዝም ፓራዶክስ በሚል (እኤአ) በ2009 ዴቪድ ካሜሩን ባቀረበው ጥናት የፌደራሊዝም ቅድመ-ሁኔታዎችንና ቅድመ-ዝግጅቶችን በሚመለከት ምሁራን በተለያዩ ሀገሮች ልምዶች ላይ በመመሥረት ያቀረቧቸውን ጥናቶች መሠረት በማድረግ በተጠቃለለ ሁኔታ እንደሚከተለው ገልፆታል። ይኸውም በመሠረቱ በበሓውርት ሀገሮች የፌደራል የፖለቲካ ሥርዓት የሚያስፈልገው፣ የሚመረጠውና ተስማሚ መዋቅር የሚዘረጋው በተለይም በብሔረሰብ ግጭት ተጠምደው እድገታቸው ለተገታና በድህነት ለሚማቅቁ ህዝቦች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ይበጃል። ነገር ግን ፌደራሊዝም በባሕርይው መልካምና መጥፎ ውጤቶችን ሊያስከትሉ በሚችሉ ተፃራሪ ኩነቶች የተሞላ ነው። ከዚህ የተነሳም በርካታ ምሁራን “የፌደራሊዝም ፓራዶክስ” በሚል፣ ሌሎች “የያኑስ-ገፅ” (‘Janus-faced’) ስለምናዊ ተምሳሌት (ሜታፈር) ይገልፁታል። በመሆኑም በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለ አንድ የብዘኀ-ባህል ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ገና ከመነሻው (በቅድመ-ሁኔታ ዝግጅት ደረጃ) ምን ዓይነት ፌደሬሽን መመሥረት ያስፈልጋል? የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ መመለስ ሊፈጠሩ የሚችሉትን አደጋዎች ለመቆጣጠር አስፈላጊ ቅድመ- ሁኔታዎችን መለየት፣ ማጤንና ማሟላት ግድ ያደርገዋል። ከተሻለ ወይም ተስማሚ ከሆነ የፌደሬሽን የፖለቲካ ሥርዓት ምርጫ ላይ ለመድረስ፣ ለመወሰንና ለማቋቋም በቅድሚያ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን ማዘጋጀት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን በችኮላና በሆያ ሆዬ የሚታለፍ አለመሆኑን ካሜሩን አጥብቆ ያስገነዝባል። ቅድመ ሁኔታዎችም እንደሚከተለው የሰፈሩትን ይመስላሉ። በእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፌደራላዊ መንግሥት የፖለቲካ ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ በቅድሚያ መሟላት የሚኖርባቸውን አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎች በሚከተለው ሁኔታ ለይቶ ዘርዝሯል። እነዚህም፡-

1. የፌደራል ህብረት ምሥረታ አባልነትን ፈቃደኝነት ማረጋገጥ፣

2. የጋራ እሴቶችንና ዓላማዎችን ለመጠበቅና ለመጠቀም የጋራ መግባባት፣

 3. በፌደሬሽኑ አባላት መካከል መተማመንን መፍጠርና ማረጋገጥ፤

4. ሕገ-መንግሥታዊ ደንቦችና ተቋማዊ መዋቅሮችን የማክበር ዝግጁነት፣

5. ለሕግ የበላይነት ተገዥነትን ማረጋገጥ፣

6. የፖለቲካ ባህል እድገትን በጋራና በትብብር የማፋጠንና የማሳካት ቁርጠኝነትን ማረጋገጥ፣

7. ተደጋጋፊ የኢኮኖሚ ተግባራትን ጨምሮ ድጋፍ ሰጭ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን፣ የጋራ የኢኮኖሚ ፍላጎቶችንና የኢኮኖሚ ልዩነቶችን ለማጥበብ ዝግጁነትን ማረጋገጥ፤ የሚሉ ናቸው። ካሜሩን ከዚህ መቀጠል፣ “እነዚህ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ቀልብ የሚስቡ ቃል-ኪዳኖችን በመግባትና ድንቅ ተቋማዊ መዋቅሮችን በመዘርጋት ወደ ተግባር ማምራት ውሎ አድሮ የሚያስከትላቸውን ምስቅልቅሎች ተመልሶ ለማስተካከል አይቻልም። …. ቁም-ነገሩ ፌደራሊዝምን ከማስተዋወቁ ላይ አይደለም። መረዳት እንደተቻለው የችግሮ መንስዔ የፖለቲካ ሥርዓቱን ከማስተዋወቁና በሥራ ከመተርጎሙ ወይም ከመዋሉ በፊት ስምምነት ሊደረግባቸው ከሚገቡ ቅድመ-ተቋማዊ ሁኔታዎችና ቅድመ-ዝግጅቶች መሟላት ጉድለት ላይ የተመሠረተ ነው። በአንፃራዊ ደረጃ ሲታይ ተቋሞችን ማስተካከል ቀላል ሲሆን እጅግ ከባዱ ፈተና ግን ቅድመ- ተቋማዊ ሁኔታዎችንና ዝግጅቶችን ወደ ኋላ ተመልሶ ለማስተካከልም ሆነ ውጤታማ መፍትሔ ለማግኜት ፈፅሞ የማይቻል መሆኑ ነው።“ በማለት በአጽንኦት ያስረዳል። ይህን ካለ በኋላ የተለያዩ ፌደሬሽኖችን ውጤታማ ለመሆን ያበቋቸውን ጠቃሚ የፖለቲካ ሂደቶችና ተግባሮች መሠረት በማድረግ የተጠቀሙባቸውን የአሠራር መርሆዎችም እንደሚከተለው በዝርዝር አስፍሯቸው እናገኛለን። እነዚህም፣

1. ዲሞክራሲያዊ የአሠራር መንገድን በተግባር ማዋል፣

 2. ማዕከላዊነትን እንደ መርሆ ከመውሰድ ማስወገድ፣

 3. የሥልጣን ክምችትን ለመወሰን መቆጣጠሪያና መመዘኛዎች (checks and balances) በሥራ ላይ መዋል፣

4. በጋራ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ግልፅ የፖለቲካ ውይይት ማድረግ፣

5. በማዕከላዊ ደረጃ በሚገኙ ተቋማት እውነተኛ የጋራ የሥልጣን ክፍፍል መኖር፣

6. ሕግ-መንግሥትን ማክበርና የሕግ የበላይነትን ማክበር፣ የሚሉ ናቸው። እነዚህ የተጠቀሱት የአሠራር መንገዶች ፌደራላዊ መንግሥት ይሁንም አይሁን በአጠቃላይ ዘላቂነት ያለው መልካም አስተዳደር እንዲቀጥል መሠረት የሚሆኑ ሂደቶችና የአሠራሮች መርሆዎች ተደርገው ይታያሉ::

 የፌደራሊዝም አስፈላጊነት፡- ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከዓለማችን ህዝብ ውስጥ ወደ 2 ቢሊዮን የሚሆነውን ወይም 40 ከመቶ ያህሉን የዓለማችን ህዝብ የሚያስተዳድሩ ወደ 24 የሚሆኑ ፌደሬሽኖች ወይም ፌደራል መንግሥታት ይገኛሉ። ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደሞከርኩት እነዚህ ፌደሬሽኖች በሚከተሉት ፌደራላዊ መርሆ ሊመሳሰሉ ቢችሉም እንኳን በቅርፅ ወይም በዓይነት (type) የተለያዩ ናቸው። ይህ የሚሆንበት ምክንያትም እያንዳንዱ ሀገር ከሌላው ሀገር በታሪካዊ፣ በባሕላዊ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ አውድ ስለሚለያይና ይህም በአንድ ሀገር ውስጥ ሊሠራ የሚገባውን የፌደሬሽን ዓይነት ለመምረጥና ለመወሰን ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ የተነሳ ነው። በዓለማችን በሥራ ላይ ከሚገኙት የተለያዬ ቅርፅ ወይም ዓይነት ካላቸው ፌደሬሽኖች መካከል፣ ለምሳሌ፡

  • ካናዳና ራሽያ የአንድ አሕጉር መጠን ያህሉን የህዝብ ብዛት ይሸፍናሉ። ሕንድ እጅግ ብዛት ያለው ህዝብ አላት። አንዳንድ፣ ለምሳሌ ኮሞሮስን የመሳሰሉ፣ ሀገሮች በጣም ጥቂት የህዝብ ብዛት ያላቸውም ይገኛሉ። ከእነዚህ ፌደሬሽኖች መካከል አንጋፋ ወይም ‹ክላሲካል› ተብለው የሚገለፁ፣ በአስተዳደራዊ ሥርዓትና በልምድ በጣም የዳበሩና የደረጁ ሆነው ይገኛሉ። እነዚህም (እኤአ) በ1787 የተመሠረተው የአሜሪካ፣ በ1846 የተመሠረተው የስዊዘርላንድ፣ በ1867 የተመሠረተው የካናዳ እና በ1901 የተመሠረተው የአውስትራሊያ ፌደሬሽኖች ናቸው። ከላይ ከተገለፀው ቁጥር ውጭም በአሕጉረ-አፍሪካ ውስጥ አብዛኛዎች ሊያሰኝ በሚያስችል ሁኔታ በቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው ምርጫና ውሳኔ አማካይነት ፌደሬሽኖች ሆነው ነበር። ዳሩ ግን ከ70 ዓመታት በላይ ስሙን ይዞ እየተንገዳገደ ከቆየው ከናይጀሪያው በስተቀር ሁሉም በተመሳሳይ ምክንያቶች ከባድ ዋጋ ባስፈከለ ኪሣራ

ከተሻለ ወይም ተስማሚ ከሆነ የፌደሬሽን የፖለቲካ ሥርዓት ምርጫ ላይ ለመድረስ፣ ለመወሰንና ለማቋቋም በቅድሚያ አስፈላጊ ቅድመ- ሁኔታዎችን ማዘጋጀት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን በችኮላና በሆያ ሆዬ የሚታለፍ አለመሆኑን ካሜሩን አጥብቆ ያስገነዝባል

የከሸፉ በመሆናቸው ከቁጥር አይገቡም። (ምክንያቶቹን በሚቀጥሉት የታዛ መጽሔት ቅፆች በማቀርባቸው ተከታታይ ጽሑፎች ይከታተሉ::) ሮናልድ ዋትስ (1999) እንደሚለው እንኳን እነዚህ በአፍሪካና በሌሎች ሀገሮች ጨርሶ የከሸፉት ቀርቶ “እውነቱን ለመናገር ሁሉም ከላይ በቁጥር የተጠቀሱት ፌደራላዊ መንግሥታት ወይም ፌደሬሽኖች ናቸው ለማለት አያስደፍርም። በአሁኑ ጊዜ ፌደራል መንግሥታት ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉት 13 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው” ብሏል።

 እናም ከእነዚህ ‹13 ከመቶ ከሚሆኑት› ፌደሬሽኖች ልምድና ታሪክ መረዳት እንደተቻለው ፌደራሊዝም ተመራጭ ከሆነባቸው ምክንያቶች መካከል የጠበቀ ማህበራዊ ትሥሥርን የሚገልፁ የተለያዩ ቡድኖችን በመልክዓ-ምድር በማካለልና በማደራጀት እጅግ ጠቃሚ ከሆኑ ተቋማዊ ዘዴዎች አንዱ ተደርጎ ይታያል። ከእነዚህ አስፈላጊ ምክንያቶች መካከልም ጥቂቶችን እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል የሚከተሉት ይገኙበታል፣

1. እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝኀ- ብሔረሰብ ሀገሮች የባህልና የብሔረሰብ ውጥረትንና ግጭትን ለማስወገድ ይጠቅማል። ፌደራላዊ የመንግሥት ሥርዓት አካባቢያዊ ግጭትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር፣ ብሔራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ፣ ክልላዊ እኩልነትን ለማረጋገጥ፣ ውስጣዊ የጋራ ጥቅሞችን ለመጠበቅ ይረዳል።

 2. ፌደራሊዝም የሥልጣን ክፍፍልን ተቋማዊ በማድረግና በዚህም የክልልና የአካባቢ አስተዳደርን የውስጥ ነፃነት (ኦቶኖሚ) በማስጠበቅ እንዲሁም ለአናሳ ማህበራዊ ቡድኖች የተሻለ ውክልና በማስገኜት የዲሞክራሲ መብቶቻቸውን ለማጠናከር አስተማማኝ ሚና ይጫወታል። ከዚህ አኳያ ዲያመንድ (1999) እንዲህ ይላል፡ – “ፌደራሊዝም በብዝኀ-ብሔረሰብ መንግሥት ብሔረተኝነትንና ዲሞክራሲን በማስታረቅ፣ በየመልክዓ- ምድራዊ አካባቢዎች ለሚገኙ አናሳ ብሔረሰቦች የራሳቸውን የውስጥ ጉዳይ በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መብታቸውን በማስጠበቅ ታሪካቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና እምነታቸውን በነፃነት ለመጠቀም እንዲችሉ ዋስትና በመስጠት፣ በብሔራዊ ደረጃ በብዙኀን ብሔረሰቦች ዘንድ የመገለል ስሜት እንዳያድርባቸው ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ጥበቃ በማድረግ የብዝኀ- ብሔረሰብ ሀገሮችን ሰላምና አንድነት አስጠብቆ ለመያዝ ያስችላል።”

 3. ሌላው ፌደራሊዝምን ተመራጭ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ እሴቶችን/ መብቶችን በመጠበቅና በማጠናከር የአንድን ኅብረ-ባህል ሀገር ውስጣዊ መገለጫ ባሕርያትን ማለትም በአንድነትና በልዩነት (በዳይቨርሲቲ) መካከል ውጥረቶችን በማርገብና የእነዚህን መሠረታዊ ባሕርያት ሚዛን በማቻቻል እኩልነትንና ፍትኅን፣ ዘላቂ ሰላምን፣ ደኅንነትን፣ የፖለቲካ መረጋጋትን እና በሁሉም የእድገት መስኮች ዘላቂ ስኬታማነት ለማረጋገጥ ያስችላል።

4. አንድነታቸውን ለመጠበቅ የሚፈልጉ የብዝኀ-ብሔረሰብ ሀገሮች መንግሥታት ፌደራሊዝምን ተጠቅመው ልዩነቶችን አቻችሎ በማካተት በአንድ ሀገር ሰፊ ማህበረሰብ ውስጥ ኅብርነትን ለመፍጠርና ለማጠናከር ይጠቅማል፣ ወዘተ።

 ማጠቃለያ፡- ከላይ ከተገለፁት የፌደራሊዝም ቅድመ-ሁኔታዎች፣ መሠረታዊ መርሆዎች እና አስፈላጊነት አንፃር የኢትዮጵያው የብሔረሰብ ፌደራላዊ መንግሥት እንዴት ይታያል? በሚለው በአጭሩ ለማጠቃለል እሞክራለሁ። የኢትዮጵያው የብሔረሰብ ፌደራላዊ መንግሥት የፖለቲካ ሥርዓት ከላይ ለመግለፅ ከሞከርኳቸው የፌደራሊዝም ቅድመ-ሁኔታዎች እና መሠረታዊ መርሆዎች አኳያ ሲታይ በሚከተሉት ባሕርያት ሊገለፅ የሚችል ሆኖ ይገኛል። የኢትዮጵያው ፌደራላዊ የፖለቲካ ሥርዓት ከፌደራሊዝም አስፈላጊ ምክንያቶች አኳያ ሲታይ ደግሞ እንደሚከተለው በተገለፁት የአፍሪካ ሀገሮችን ወደ ክሽፈት ሊያመሩ በቻሉ ድክመቶች የሚገለፅ ሆኖ ይገኛል።

 ኢትዮጵያ የብዝኀ-ባህል ሀገር ናት። በመሠረቱ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በሓውርት (ብዝኅ-ባህል/ብሔረሰብ) ሀገሮች የፌደራል የፖለቲካ ሥርዓት የሚያስፈልገው፣ የሚመረጠውና ተስማሚ መዋቅር የሚዘረጋው በተለይም በብሔረሰብ ግጭት ተጠምደው እድገታቸው ለተገታና በድህነት ለሚማቅቁ ህዝቦች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሲባል ነው። ይህንም ምሁራን ለምሳሌ ዴቪድ ካሜሩን (2009) ሲገልፅ በአንድ የብዘኀ- ባህል ሀገር ነባራዊ ሁኔታዎች ውስጥ ምን ዓይነት ፌደሬሽን ያስፈልጋል? ለምን? እንዴት? የሚሉትን ቁልፍ ጥያቄዎች ለመመለስ፣ ከተገቢ ምርጫ ላይ ለመድረስና ለመወሰን በቅድሚያ የግድ መሟላት የሚገባቸው አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን መለየት፣ ማጤንና ዝግጅቶችን ማጠናቀቅ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው።

 ከልምድ እንደታየው “እነዚህ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ቀልብ የሚስቡ ወይም የሚያማልሉ ቃል- ኪዳኖችን በግብር ይውጣ፣ በቸልታና በችኮላ መግባትና ድንቅ ተቋማዊ መዋቅሮችን በመዘርጋት ወደ ተግባር ማምራት ውሎ አድሮ የሚያስከትላቸውን ምስቅልቅሎች ተመልሶ ለማስተካከል አይቻልም። … ፌደራሊዝም በተፈጥሮው በተቃርኖ በተሞሉ ሁነቶች የሚጓዝ “አይ- አዎ!” (‹ፓራዶክሳዊ›) ሂደት ነው።” ይልና በመቀጠል ለምሳሌ “ፌደራሊዝም በአንድ ሀገር ልዩ ሁኔታ ውስጥ ወደ መገንጠል ያመራል ወይስ ሥጋቱን ያስቀራል? ወደ መገንጠል ማምራቱ አይቀሬና እሙን ከሆነ ምርጫው ምን ቢሆን ይሻላል? ዝም ብሎ ፌደራሊዝምን መምረጥ ወይስ ከመበታተን አደጋ ለማምለጥ ፌደራሊዝም ከመምረጥ መቆጠብ? ይህን የመሰለ ሁኔታ ሲፈጠርና በአንድ ሀገር አውድ ውስጥ ወደ መበታተን የሚያመራ ሆኖ እስተገኜ ድረስ ፌደራሊዝም ሁለተኛ ምርጫ ይሆናል ማለት ነው” ሲል ያስጠነቅቃል።

ሁል ጊዜ የችግሮች መንስዔ ሆኖ የሚገኜው ፌደራሊዝምን ከማስተዋወቁ ላይ አይደለም – የፖለቲካ ሥርዓቱን ከማስተዋወቁና በሥራ ከመተርጎሙ ወይም ከመዋሉ በፊት ስምምነት ሊደረግባቸው በሚገቡ ቅድመ-ተቋማዊ ሁኔታዎችና ቅድመ-ዝግጅት ጉድለት ላይ ነው እንጂ! ስለዚህ ካሜሩን “እጅግ አስቸጋሪው ጉዳይ ተቋሞችን ማስተካከል በአንፃራዊ ደረጃ ሲታይ ቀላል ሲሆን እጅግ ከባዱ ፈተና ግን ቅድመ-ተቋማዊ ሁኔታዎችንና ዝግጅቶችን ተመልሶ ለማስተካከልም ሆነ ውጤታማ መፍትሔ ለማግኜት የማይቻል መሆኑ ነው።” በማለት በአጽንኦት ይመክራል።

በአጠቃላይ ከቅድመ ሁኔታ መሟላት አኳያ በኢትዮጵያ የብሔረሰብ ፌደራሊዝምን ለመመሥረት ከ1983 እስከ 1987 ድረስ በነበሩት አራት ዓመታት ውስጥ በተሰየመው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት በተከናወኑት አስፈላጊ ቅድመ- ዝግጅቶችም ሆነ ከዚያም በኋላ ፌደሬሽኑ በገቢር ላይ ከመዋሉ በፊት በሀገሪቱ ብሔረሰቦች ኅብረ-ማንነት፣ የምደባ እንዴትነትና የግልና የጋራ ማንነት የመለያ ባሕርያት ምን እንደሆኑ በጥናት ላይ በተመሠረተ ዕውቀት ተመርኩዞ ወደ ተግባር የመግባቱ ጉዳይ ፈፅሞ ሊታለፍ የሚገባው አጋጣሚ አልነበረም። የሽግግር መንግሥቱ በብሔረሰብ ላይ የተመሠረተ ፌደራላዊ መንግሥት ማደራጀት የጀመረውና ከዚያም ከሁለት ዐሠርት ዓመታት በላይ በጭፍን ሙከራ የቀጠለው ይህ አስፈላጊ ቅድመ- ሁኔታ ሳይከናወን በቂላቂል የፖለቲካ ሽኩቻ የተመራ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱን ከመሠረቱ ምስቅልቅሉን ካወጡት ተጠሪ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ሆኖ ይገኛል።

 ከዚሁ ጋር አብሮ የሚገለፀው በፌደራሊዝም መሠረታዊ መርሆዎች ላይ የግንዛቤ ግልፅነት ያለመኖሩ ችግር ነው። ይህ በብሔረሰብ ፌደራሊዝምና በዲሞክራሲ ተግባራዊነት፣ በሕገ-መንግሥት፣ በብሔረሰብ ፌደራል ሥርዓት ግንባታ መርሆ፣ በአከላለል፣ በአወቃቀርና በአደረጃጀት፣ በዲሞክራሲ ተቋማትና እሴቶች ሥርፀትና ተግባራዊነት፣ በመልካም አስተዳደር ይዞታ፣ በዘላቂ ሰላምና በፖለቲካዊ መረጋጋት፣ በተመጣጣኝ እድገት፣ በእኩልነት፣ በፍትኅና በሀገራዊ አንድነት፣ ወዘተ፣ ላይ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖዎችና አሉታዊ አንድምታዎች ማስከተል ችሏል። እነዚህ ዐበይት ጉዳዮች በኢትዮጵያ የብሔረሰብ ፌደራሊዝም አውድ ውስጥ ሲታዩ ተሟልተዋል ከማይባሉ ከሌሎች ዓይነተኛ ችግሮች መካከል ዋነኛ ናቸው።

 ሌላው ከዲሞክራሲ አሠራር መርሆ አንፃር ስንመለከት ሥልጣንን ላለማጋራትና የጋራ እሴትን ለማጠናከር ያለመቻል ድክመት ነው። በሀገሪቱ በብሔረሰብ የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች/ፓርቲዎች ‹እንወክለዋለን› ለሚሉት ብሔረሰብ የነፍስ አባትነት (‹ፓትሮኔጅ›) ሆነው የታዩበት ሁኔታ ብዙ ነው። ይህ ከፌደራሊዝም መርሆዎች አኳያ ሲታይ ፍናጅርቱ ክስተት ሆኖ ይገኛል። ኢትዮጵያ የብሔረሰብ ፌደራላዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ከተከተለች እነሆ ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። የፌደራል ሥርዓቱ ቅርፅም “የብሔረሰብ ፌደራሊዝም” የሚባልና በዓይነቱ የመጀመሪያው ቅርፅ መሆኑን ምሁራን በስላቅ ሲተቹት የቆየ ሀቅ ነው። ከፌደራሊዝም አስፈላጊ ምክንያቶችና ጥቅሞች አንፃር ሲታይ የዲሞክራሲ ሂደቶችን በማጠናከር አምባገነንነትንና መረን የለቀቀ የብሔረሰብ ፖለቲካን ለማስከንና ሰላምንና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ እንዳልተቻለ አይተናል። የሕግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር የሲቪል ማህበረሰብንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን መብቶች ማስጠበቅ አልቻለም። የግለሰቦችን ዘላቂ የኢኮኖሚ ብልፅግና፣ ማህበራዊና አእምሯዊ እድገት ያለማቋረጥ ለመገንባት የግለሰቦችና የማህበራዊ ቡድኖችን ነፃነትና ተሳትፎ ለማክበር፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊው መስክም ወደ ከፍተኛ እድገት ለማምራትና ከበለፀጉት ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ አልቻለም። ፌደራሊዝሙ በብሔረሰቦች መካከል የርስ በርስ መከባበርን፣ አንድነትንና ልዩነትን በማስታረቅ የመቻቻል እሴቶችን ለማጠናከር፣ የኅብረ-ባህል ጤናማ ግንኙነቶችን በማፋፋት የብዝኀ-ባህል የፈጠራ ምንጮችና የአዳዲስ የቴክኖሎጂ ጥበብ ግኝቶችን የማሳደግ ብቃት አላሰየም። እንዲያውም በተቃራኒው በብሔረሰቦች መካከል የመናናቅ፣ የጥላቻ፣ የማግለልና የግጭቶች፣ ወዘተ. መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም።

በአጠቃላይ የብሔረሰብ ፌደራሊዝሙ ተቋማት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት በጉርብትና አብረው በመኖር የገነቧቸውና የሚያስተሳስሯቸው ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብራዊ የግንኙነት ባሕርያት፣ በአጠቃላይም፣ የህዝቦችን የጋራ ሉዐላዊነትና አንድነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ታሪካዊና ትውፊታዊ እሴቶችን ከማጎልበትና ከዲሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር በማዋሀድ ከመጠቀም ይልቅ እነዚህን አደጋ ላይ የሚጥሉና የፌደራሊዝሙን ውድቀት የሚያፋጥኑ ሁኔታዎችን መፍጠሩ ግልፅ ሆኖ ይታያል። በዚህ ረገድ ሀገሪቱ ፌደራሊዝምን ተመራጭ ከሚያደርጉት አስፈላጊ ምክንያቶች ተጠቅማለች ለማለት አይቻልም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top