ስርሆተ ገፅ

“የኢትዮጵያ ባህል እንደ ጥቁር ቀለም ነው”

ሁለገቡ ሙዚቀኛ ሮፍናን ኑሪ መሳሪያ ይጫወታል። ሙዚቃ ያቀናብራል። ፕሮዲዩሰርም ነው። በግንቦት /2010 “ነፀብራቅ” የተሰኘ አልበም አውጥቷል። በ2011 ዓ.ም የተሳካ የሙዚቃ ጉዞ አድርጓል። ‘ አፍሪካን ፎርቭስ ‘ በ2019 ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ተፅእኖ ፈጣሪ ብሎ ከመረጣቸው 30 ወጣቶች መሃል አንዱ ትሁቱ ሙዚቀኛ ሮፍናን ነው። ይህ ወጣት የአዲሱ ዓመት የታዛ እንግዳችን ሆኗል።

ታዛ፡- ካሁን ቀደም ተናግረኸውም ቢሆን እንኳ ድገምልንና የስምህ (ሮፍናን) ትርጉም ምንድነው?

ሮፍናን፡- እንዳልከውም ይህን ነገር ደጋግሜ ተናግሬዋለሁ። ( ይህን ብትጠቅስልኝ ደስ ይለኛል። ) አባቴ ነው ስሙን ያወጣልኝ። ለእናትና አባቴ እኔ ወደ መጨረሻ ላይ ነው የተወለድኩት። ወላጆቼ ትልልቅ ሰዎች ናቸው። አባቴ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነው። የራሱ የፀሎት ጊዜዎች አሉት። እኔ እናቴ ሆድ ውስጥ ሆኜ አባቴ በፀሎት ላይ እንዳለ “ሮፍናን” የሚለው ቃል በተደጋጋሚ አዕምሮው ላይ ይመጣበታል። አባቴን ጠይቄው እንደነገረኝ ይህን ቃል ከዚያ በፊት ሰምቶት አያውቀም ። የሚገርምህ ጎግል ላይ፣ ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ ላይ ስፈልግ “ ሮፍናን “ የሚባልን ቃል ትርጉም ላገኝ አልቻልኩም። በሽታም፣ ቫይረስም፣ የመኪና ዕቃም፣ ምንም የለም። እሱ ነው የሚገርመኝ። አባቴ የእምነት ሰው ስለነበረ ይህ ቃል ደጋግሞ ሲመጣበት አለምክንያት አይደለም በማለት “ይህ ቃል የሚወለደው ልጅ ስም መሆን አለበት” ብሎ ወሰነና ስወለድ ሮፍናን ተባልኩ ።

ታዛ፡- የተወለደችው ሴት ብትሆንስ ኖሮ ?

ሮፍናን፡- እሷም ሮፍናን ትባል ነበር። የሚገርምህ አባቴ ይህ ቃል ሲመጣለት እጁ ላይ እስክሪብቶ ስላልነበረ እንዳይረሳው የቤታችን ግድግዳ ላይ ነው ፈቅፍቆ በመጻፍ ያስቀመጠው።

ታዛ፡- ከዚያስ በኋላ እያደግህ ስትመጣ፣ ከሌሎች ጋር በመወያየት ለስምህ ትርጉም ለመስጠት አልሞከርክም? (አንተም ባትሆን ሌሎች ትርጉም ሊሰጡት አልሞከሩም? )

 ሮፍናን፡- የተለየ የሚሆነው ስለ እኔ ነው። እኔ የማደርገው ነገር ነው የስሜ ትርጉም የሚሆነው። የስሜ ትርጓሜ እኔ ራሴ ነኝ።

ታዛ፡- ምን ማለት ነው?

ሮፍናን፡- አንድ ሰው የራሱ መንገድ ሊኖረው ይገባል። የራሱ ህይወት ሊኖረው ይገባል። በዚያ መንገድ ውስጥ ራሱን ይገልፃል። ለምሳሌ አንተ ስምህ ኤሊያስ ሊሆን ይችላል። ኤሊያስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤልያስ ያደረገውን ላታደርግ ትችላለህ። ግን ኤሊያስ የሚል ስም ተሰጥቶሀል። በሌላ መንገድ ደግሞ አንተ ራስህ እንደ ኤሊያስ ብትሆንስ? አንተ የራስህ ታሪክ ባለቤት ብትሆንስ? ያ ነው ሮፍናን። እኔ የሆነ ቦታ ደርሼ ለሀገሬ ወይም ለራሴ ወይም ለቤተሰቤ እግዚአብሔር የፈቀደውን ማድረግ ከቻልኩ (አሁንም የቻልኩትን አድርጌያለሁ ብዬ አስባለሁ) ግን ከሆነ ህይወትህ በኋላ ስምህ ሲነሳ እነዚያ ምግባሮችህ ናቸው አብረው የሚነሱት። እና “ሮፍናን ማነው?” ቢባል ሮፍናን ያ ሰው ነው። እና ስሜን እየናፈቅኩት ነው ያለሁት። የስሜን ትርጓሜ እየፃፍኩት ነው። እስከ ህይወቴ ፍፃሜ ድረስ የስሜን ትርጓሜ እያበጀሁ ነው የምሄደው።

ታዛ፡- “አፍሪካን ፎርብስ” መጽሔት ላይ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ሆኖ በአህጉር ደረጃ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጥቂት ሰዎችን ሲመርጥ አንተ ከእነሱ መሀል አንዱ ነህ። ለመሆኑ ዕድሜህ ስንት ነው?

 ሮፍናን፡- 29።

ታዛ፡- ከ29ኙ ዓመትህ ውስጥ ምን ያህሉን ሙዚቃ ውስጥ አሳለፍክ?

 ሮፍናን፡- ከ10 ዓመቴ ጀምሮ ከበሮ ስቀጠቅጥ እና ስዘፍን አውቃለሁ። ግን በወቅቱ እኔ ጋ የተለየ ነገር ያለ ሳይሆን ሁሉም የሚችለው ነበር የሚመስለኝ። 12 ዓመቴ ላይ እኔ መቅጃ ቴፕ አለኝ። ስራዬ መቅዳት ነው። እናቴን፣ ወንድሞቼን፣ የጎረቤት ልጆች እያስዘፈንኩ መቅዳት፣ የኮምፒውተር አጋጣሚው ሲገኝ ደግሞ እዚያ ላይ የራሴን ነገሮች መደርደር እና መደበላለቅ ነው። 14 እና 15 ዓመቴ ገደማ ላይ ነው ጉዳዩ የተሰጥኦ መሆኑ እየገባኝ የመጣው። “ሙዚቀኛ እሆናለሁ” ብዬ አላውቅም። ለካስ መጀመሪያውኑም ነበርኩ።

ታዛ፡- መዝፈንና መሳሪያ ለመጫወት መሞከር በየቱም ዕድሜ ላይ ቢሆን መኖሩ የተለመደ ሊሆን ይችላል። ግን ድምፅን የመቅዳት ዝንባሌ ያልተለመደ ነው። ከየት አገኘኸው?

ሮፍናን፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ። ምክንያቱም እኔን በደንብ ይገልፀኛል። ለእኔ መዝፈን አይደለም ትልቁ ነገር። ጭንቅላቴ ውስጥ ድምፅ ነው ዋናው ጉዳይ። ድምፅ ነው ያለው።

 ታዛ፡- የምን ድምፅ?

ሮፍናን፡- የብዙ ነገር ድምፅ። የከበሮ ድምፅ፣ የክራር፣ የእንጉርጉሮ እና የእናቶች እሽሩሩ ድምፅ፣ ራሴ የምሰራውም ሆነ የሌላ ድምፅ። እኔ ሙዚቃ ስሰራ የራሴን ድምፅ እንደ ገፀባህሪ ነው የምጠቀምበት። እንደ ድምፃዊ ሳይሆን እንደ መሳሪያ ነው ልጠቀምበት የምፈልገው። ድምፅ ነው የምፈልገው። ሀገሬን መቆፈር እፈልጋለሁ። ድምፆቿን መፈተሽ እና ማጥናት እፈልጋለሁ። እናቴ ለምንድነው አዝማሪ የምትወደው?

ታዛ፡- አዝማሪ ይወዳሉ?

ሮፍናን፡- ለእናቴ በዓለም ላይ ከአዝማሪ በላይ ሙዚቀኛ የለም። እናቴን ማስደሰት ከፈለግኩ ይዤው የምሄደው አንድ ከበሮ፣ ወንድና ሴት አዝማሪ ነው። ይህ ለምን ሆነ? አዝማሪ ለአንድ ሰው ለምን ይህን የሚያክል ትልቅ ስሜት ሆነ? ለእናቴ ማይክል ጃክሰንን ባመጣላት ለእሷ ምኗም አይደለም። ይህ በጣም ይደንቀኛል። አዝማሪ ደግሞ ከልጅነቷ ጀምሮ የምታውቀውን ሙዚቃ ነው የሚጫወተው። ያንን ለምንድነው ያልሰለቸችው? ለምንድነው ሁልጊዜ አንድ ምግብ የምትፈልገው?

ታዛ፡- ዘፈኖችህን ስናይ በአንድ በኩል ዘመናዊ ከሚባለውም በጣም ፈጣንና የቅርብ ዓመት ቴክኖሎጂ ውስጥ የገቡ ናቸው። እዚያ ውስጥ ደግሞ ባህላዊ መሳሪያዎችን የመጠቀም እና በቋንቋ ረገድም ቅርባችን ያሉ እና የዕለት ተዕለት መግባቢያዎቻችን ላይ ያተኮሩ ሆነው ይገኛሉ። በስራዎችህ ምን ለመግለጽ ነው የፈለግከው?

 ሮፍናን፡- ራሴንና አካባቢዬን፣ ሀገሬን መግለፅ እንጂ ሌላ አይደለም። የምኖርበት ፍልስፍና በለው፣ ሎጂክ በለው ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት ቢከብደኝም ልለው የምፈልገው ነገር አለ። ለእኔ ኢትዮጵያዊ እንደ ኢትዮጵያዊ ነው መኖር የሚችለው። ቀላል ምሳሌ ልሰጥህ የምችለው ብሔራዊ ባንክ ሲሰራ አርክቴክቱ ከመስራቱ በፊት በየክ/ሀገሩ እየተዘዋወረ አጥንቶ ነበረ። ከዚያ ውስጥ የተረዳው ነገር ቢኖር ክብ ሰርተን የምንኖር ሕዝቦች መሆናችንን ነው ። ክብ ሰርተን እሳት እንሞቃለን። ክብ እንጀራ እንበላለን። ክብ ምጣድ አለን። ክብ ምድጃ አለን። አምባሻችን ክብ ነው። ቆጮው ክብ ነው። ድፎ ዳቦው ክብ ነው፣ ጎጆ ቤቶቻችን ክብ ናቸው። ክብ ሰርተን እንጨፍራለን። ክብ ቤተ ክርስቲያን አለን። ክብ መስጊድ አለን። መቀጠል ትችላለህ። ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ሀገራችንን ስናይ በማንነታችን ውስጥ ክብ ቅርጽ ትልቅ ቦታ አለው። ስለዚህ ከክብ ነገር ተነስቶ ያንን ህንፃ ሰራው። ህንፃው በጣም ዘመናዊና በአውሮፓውያን ደረጃ የተሰራ ነው። በዘመኑ አለ የተባለውን ቴክኖሎጂ የተጠቀመ ነው። ግን ቅርጹ ፍፁም ኢትዮጵያዊ የሆነ ህንፃ ነው። ያ ነገር ትክክለኛ ስልጣኔ ነው ብዬ አስባለሁ። አንድ ኢትዮጵያዊ ከሰለጠነ እንዲህ ነው መሰልጠን ያለበት። ማንነትህን ይዘህ ነው መሰልጠን ያለብህ ።

 እኔም ይህንን ነው በስራዬ ማሳየት የፈለግኩት። ፍፁም የውጭ የሆነ ኤሌክትሮ ድምፆችን ልጠቀም እችላለሁ። ግን ይህ ድምፅ የሰለጠነበት መንገድ የአዲስ አበባ ዓይነት ሳይሆን በጣም የገጠር አነጋገር፣ ቃላት፣ ስልት፣ ምት፣ ውስጡ ታገኛለህ። ባህላዊ መሳሪያ፣ ሀሳቡ አገላለፁም በጣም ገጠሬ፣ በጣም ዘመናዊ የሆነ ነው። ክብ ሰራልኝ  ማለት ነው። መጀመሪያና መጨረሻ ሳይሆን የምትፈልገው ሲሽከረከር ነው የምታገኘው። እሱን ፍልስፍና እፈልገዋለሁ ሀገሬ ላይ። ለእኔ ምንም ዓይነት ጥበብ ከእውነት መጀመር አለበት። ሙዚቃ ስሰራ ውስጤ ያለውን ሀሳብ እንደ ንግግር ነው አውጥቼ የምደፋው። እንደ ታሪክ ነገራ ማለት ነው። የፈለገ ጠንካራ ቃል እንኳን ብጠቀም ግልፅነት ውስጡ አለ። የግጥሜ ሀሳብ አድማጩ ላይ እንዲደበቅበት አልፈልግም። ግጥም መስማት ፈተና መሆን የለበትም። ለህፃኑም ለአዋቂውም ግልፅ መሆን አለበት።

ታዛ፡- ድምፆችን የመቅዳት ልምድህ መቼ ድረስ አብሮህ ቀጠለ?

ሮፍናን፡- አሁንም ድረስ አብሮኝ አለ። በቅርብ ጊዜ ባህርዳር ነበርኩ። በጣም ገጠር ውስጥ ነበር የገባሁት። በምንም ምክንያት የትም ብሄድ ድምፅ መቅዳቴ አይቀርም። ለምሳሌ አንድ ዕለት ስቱዲዮ ውስጥ እንቅልፍ ወስዶኝ ተኝቼ ከጎን በር ላይ (በተለምዶ ላሊበላ የሚባሉት) አንዲት ሴት በጣም በሚገርም ድምፅ ስታዜም እንዴት ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ ሳላውቀው አጠገቧ ቆሜ እየቀዳኋት ነው ራሴን ያገኘሁት።

ታዛ፡- “አፍሪካን ፎርብስ” መጽሔት “ ተፅእኖ ፈጣሪ “ ብሎ ሲመርጥህ የተፅእኖ መለኪያው ምንድነው?

ሮፍናን፡- መጀመሪያ የሚያደርጉት ያንን ሰው በተለያየ መልኩ መከታተል ነው። የተናገርከው፣ የዘፈንከው፣ ስፖርተኛም ከሆንክ ለስኬት ያበቃህን መንገድ ያጠኑታል። ባንተ ስኬት ውስጥ ሌሎች ሰዎች ራሳቸውን ምን ያህል ያያሉ? በነገራችን ላይ ሁሉም ሰው ምንም ስራ ይኑርህ፣ ወይም አይኑርህ፣ እምነትም አጥባቂ ሁን፣ ወይም እምነት አይኑርህ በየትኛውም አቅጣጫ አንድ ሰው ላይ፣ ሺህ ሰው ላይ፣ ሚሊዮን ሰው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ጨዋውን ልጅ እልም ያለ ሌባ ሊያደርገው ይችላል – ተፅእኖ አሳድሮበት። ግን የአንተ ተፅእኖ ከመቶ ሺህ ሰው ከሀገር ወጣ ብሎም ወንዝ መሻገር ሲጀምር ትኩረት ይሰጡሀል። አፍሪካ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተጽዕኖ ይፈጥራሉ የሚሏቸውን ሰዎች መርጠው የራሳቸውን ዳታ ይሰበስባሉ። ከዚያም ያንን ሰው ያገኙታል። ከራስህም መረጃ ያገኛሉ። በመጨረሻ እርግጠኛ የሆኑባቸውን ይመርጣሉ። መጽሔቱ የቢዝነስ መጽሔት እንደመሆኑ ያ የተመረጠው ሰው…..

ታዛ፡- ለምሳሌ አንተን ማለት ነው?

ሮፍናን፡- ያው በለው። ከተወሰነ ዓመት በኋላ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊሰራ ይችላል ብለው ይተነብያሉ። እጅህ ላይ ከምትይዘው ዋንጫ በላይ ትልቅ ዕውቅና ይሰጡሃል። ያስተዋውቁሃል። ስብሰባቸው ላይ ሄደህ የምትጨብጣቸው ሰዎች በሙያ፣ በስኬት ፣ በሀብት ካንተ በጣም ብዙ የራቁ ሰዎች ናቸው። እነሱን ማግኘቱ ራሱ የሚፈጥርልህ ዕድል አለ።

 ታዛ፡- ይህ አንተ ሙዚቃህን የሰራህበትን የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ስልት እንዲሁም አዘፋፈንህ ለሀገራችን ሙዚቃ ሰሚ አዲስ አቀራረብ ነው ። ስድስት ዓመት ስቱዲዮ ውስጥ እንደመቆየትህ “ሰዎች ባይቀበሉትስ?” የሚል ስጋት አልነበረብህም?

ሮፍናን፡- “ሰቆቃወ ጴጥሮስ” ሰዎች ይቀበሉታል ተብሎ አልተሰራም። ሰውን አትስደብ። አታንቋሽሽ። ሰውን መጥፎ ተፅእኖ ውስጥ የሚከት ነገር አታድርግ እንጂ የራስህን እውነት ሌላውን በማይጋፋ መልኩ፣ ስነስርዓት ባለው መልኩ፣ ሀላፊነት በሚሰማው መልኩ፣ ሰርተህ ከራስህ ጋር መሆን ነው። ስለ መሰማት እና አለመሰማት አይደለም። ብትሰማ እሰየው ነው። ካልተሰማህ ደግሞ ትልቁ ድል ያለው መጀመሪያ አንተ ራስህን አሸንፈህ፣ ከተፅእኖዎች ተላቀህ እዚያ ቦታ ላይ ተገኝተህ መስራት መቻልህ ነው። በዓሉ ግርማ ያስተማረኝ ይሄንን ነው። የመሰለውን ከውስጡ የፈለቀውን እንባውን ነው መጽሐፉ ላይ የማነበው። እንጂ “ይሄ ነገር ከወጣ በኋላ …. “ የሚል ስሜቱን አይደለም። በሰው ልክ ቆርጦ መስፋትን አይደለም።

 ቤተሰቦቼ ነጋዴዎች ናቸው። ሁሉም የቤተሰባችን አባል መርካቶ መሀል ነው ያደገው። እኔ ሄጄ አላውቅም። አባቴ ልጅ ሆነህ ጀምሮ ወደዚያ ነው የሚወስድህ። ገንዘብ ከሆነ ከእኔ በላይ ዕድለኛ ሰው አልነበረም። በትምህርትም ከሆነ ፓይለት ትምህርት ቤት ልገባ ሁሉም ነገር ከተመቻቸልኝ በኋላ ነው የተውኩት። ውጭ ሀገር ለመሄድም ከአንድም ሁለት ጊዜ ተሞክሮልኝ “ እዚያ ሄጄ ሙዚቃ የማልማር ከሆነ አልሄድም “ ብዬ ነው የቀረሁት ። ስመጣ ራሴን ለመሆን ነው የመጣሁት። መንገዴን መርጬ ነው የመጣሁት። ራሴን ፣ እኔን ፣ ሮፍናንን ለመሆን ነው የመጣሁት። ማንንም ለመሆን ፣ እንደማንም ለመሆን አይደለም ። ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ተመርቄያለሁ። ለእናቴ ስል ነው የተማርኩት። እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ወረቀቱን ዞር ብዬ አይቼው አላውቅም።

ታዛ፡- “ነፀብራቅ” አልበምህ እንዴት ነው የተሰራው?

ሮፍናን፡- ጥናት ውስጥ ነው ያለሁት። በፊትም፣ አሁንም ። መጀመሪያ “ዶርዜን” ከመስራቴ በፊት ስለ ዶርዜ ሙዚቃ ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንዲኖረኝ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ለማጥናት እሞክራለሁ። እዚያ አካባቢ ተወልዶ ካደገ ሰው ጋር ያለምንም ችግር መጫወት እስከምችል ድረስ። አርባ ምንጭ በሄድኩበት ጊዜ መቅዳት፣ ማውራት ነበር ስራዬ። እዚህ ሽሮ ሜዳ ከማገኛቸው ሰዎች ጋር አያቶቼ ከሚሆኑት የ80 ፣ የ90 ዓመት ሰዎች ጋር ቆም ብዬ፣ ስቱዲየም እያመጣሁ የደስታውንም፣ የለቅሶውንም፣ የምርቃቱንም ስርዓት እና አፈፃፀም ለማወቅ ጥረት አድርጌያለሁ። እሱን ማጥናቱን በደንብ ጊዜ እወስድበታለሁ። ወደ እኔ ትውልድ ለማምጣት ደግሞ ሌላ ስራ እሰራለሁ።

 ታዛ፡- የራስህን ሙዚቃ ትሰማዋለህ?

ሮፍናን፡- እጅግ በጣም እንጂ። እየሄድኩ መስማት ነው። ደስ ብሎኝ መስማት። በቃ እየተመሰጥኩ አብሬው እጠፋለሁ። ሌላ ሰው የሰራው እስኪመስለኝ ድረስ ነው የምሰማው። ሙዚቃዬ ከመውጣቱ በፊት በቁጥር እስከማላውቀው ድረስ ነው የሰማሁት። ሰምቼው ሰምቼው አልጠግብ ስለው በቃ ይሄን ነገር ቢወጣ ብዬ ወሰንኩ።

ታዛ፡- አልበምህ ውስጥ 15 ስራዎችህ ተካተዋል። ሌሎች ስራዎችም ይኖሩሃል ብዬ እገምታለሁ። እና በምን መመዘኛ ተመርጠው ነው 15ቱ “ነፀብራቅ” ውስጥ የገቡት?

 ሮፍናን፡- እኔ መስራቴን እንጂ ሰው የቱን እንደሚወደውና ሊወደው እንደሚችል አላውቅም። ለምሳሌ እዚህ አልበም ላይ “የሰው ቅኔ”፣ “ፒያሳ ላይ” እና “ልንገርሽ”ን አልበሙ ውስጥ እንዳይገቡ ያወጣኋቸው ነበሩ ። “ ልንገርሽ “ን ለእናቴ ነው የፃፍኩት። እንድወደው እና እንድደሰትበት እንጂ ለአልበም አልነበረም የሰራሁት። “እኔ ለእናቴ በሰራሁት ሰው ለምን ይሄን ስማ ይባላል ? ብዬ ፣ “የሰው ቅኔ” ምናልባት ከብዶ “ሰው ላይረዳው ይችላል” ብዬ ነው ያወጣሁት። “ ልንገርሽ “ን ወንድሜ ነው “ ሰው ሁሉ እኮ እናት አለው ? “ ብሎ ያስገባው ። ሌሎቹንም ጓደኞቼ ናቸው ገፍተውኝ ያስገቡት። አልበሙ ከወጣ በኋላ ግን ሦስቱ ስራዎች ከምርጥ አምስቱ (TOP 5) ውስጥ አሉበት። ስለእኔ ከጠየቅከኝ ለምሳሌ “ጨረቃ”ን አልበሙ ውስጥ የሚያክለው የለም። እንደ ዋጋ ከጠየከኝ “ልንገርሽ” ትልቅ ነው። ስጦታ ስለሆነ። “ጨረቃ”ን ግን ተጠብቤበታለሁ ብዬ ነው የማምነው።

 ታዛ፡- በቀን ምን ያህል ሙዚቃ ትሰራለህ?

ሮፍናን፡- ከመተኛት ውጪ ያለውን አብዛኛውን ሰዓት ስቱዲዮ ልሆን እችላለሁ። አልበሙ የወጣ ሰሞን 20 እና 22 ሰዓትም በተከታታይ እሰራም ነበር ። ስቱዲዮ በማልሆን ጊዜም የሚረብሽ ስልክም ሆነ አጠገቤ ሰው ከሌለ መኪና ውስጥ ሆኜም ጭንቅላቴ ላይ አዲስ ሀሳብ ወይም ዜማ ይመጣል። ወዲያው ስልኬን አውጥቼ መቅዳት ነው። ሞባይሌን የሚሞላው በሚቀዳው ድምፅ ነው።

ታዛ፡- ድምፆቹን ተጠቅመህ ስትጨርስ ምን ታደርጋቸዋለህ?

ሮፍናን፡- “ትደመስሳቸዋለህ ወይ?” ልትለኝ እንዳይሆን ። የተጠቀምኩባቸውንም ሆነ ያልተጠቀምኩባቸውን ድምፆች የማከማችበት የድምፅ ባንክ አለኝ። እዚያ አስቀምጣቸዋለሁ። እግዚአብሔር ዕድሜ ከሰጠኝ የዛሬ 20 ዓመት የምጠቀምበት ድምፅ ሊሆን ይችላል።

ታዛ፡- ብዙ ሰዎች በሚፈልጉትና በሚኖሩት መሀል ልዩነት ይመጣባቸዋል። በዚያም ደስታቸውን ይነጠቃሉ ። በቀን አብዛኛውን ሰዓት በምትወደው ሙያ ላይ መኖር ላንተ ምን ትርጉም ይሰጥሀል?

ሮፍናን፡- ደስተኛ ነኝ። ደስታዬ ግን ሙዚቃ ውስጥ በመኖሬ ሳይሆን የምፈልገውን ለማድረግ ባለኝ ብርታት ነው። ከገንዘብም፣ ከዝናም፣ ከሹመትም በላይ ሰላሜን አስቀድማለሁ። ስቱዲዮ ስከፍት የነበሩኝን ዕድሎች (ፓይለት መሆንን፣ ውጭ ሀገር መሄድን፣ ነጋዴ መሆንን) ትቼ ስቱዲዮ ስከፍት ደመዎዜ 3,000.00 ብር ደረሰ። ሶስት ሺህ ብሩንም ስቱዲዮ ነው የተከራየሁበት። ቤተሰቦቼን የታክሲም ሆነ የምንም ብር መጠየቅ አልፈልግም። ስቱዲዮ ገብቼ የታክሲ አንድ ብር ኪሴ ላይኖር ይችላል። ጉዳዬ አይደለም፤ የምትፈልገውን ለማግኘት መስዋዕትነት ይፈልጋል። ሰው በሚወደው ቦታ ላይ ለመቀመጥ መሰናክሎቹን መሻገር አለበት። መወሰን አለብህ። ሁለት ቦታ ላይ እግርህ እንዲረግጥ ከፈለግህ ችግር ነው። መምረጥ አለብህ። ህይወት ላይ ደስታህን ነው የምትፈልገው ወይስ የሰዎችን ፍላጎት? “ሰው የሚያከብረው ይሄንን ነው” ብለህ እሱን ለመሆን ከጣርክ ለእሱ ትኖራለህ። እዚያ ውስጥ ደግሞ ሰላም የለም። ይሄ የዕድል ጉዳይ አይደለም። የመሆን ጉዳይ ነው። ገንዘቡን አታስብ። ዝም ብለህ ስራ። ከራበህም ይራብህ። ከተቸገርክም ተቸገር። በቃ ስራ።

ታዛ፡- አልበም ማውጣትህ የጨመረልህና የቀነሰብህ ነገር ምንድነው?

 ሮፍናን፡- የጨመረውም የቀነሰውም ነገር አለ። የጨመረው አንዱ ገንዘብ ነው። ሌላው አካባቢዬ ላይ ያሉና የሚወዱኝ ሰዎች ደስ እንዲላቸው አድርጓል። “ጂም ባንተ ዘፈን ነው የምሰራው”፣ “ለእናቴ የምሰጣት ነገር ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ” የሚሉህ አሉ። አንድ ህፃን ልጅ ደግሞ ትርጉሙን ባይረዳውም መጥቶ ያቅፍሃል። ይህ መባረክ ነው።

ታዛ፡- የቀነሰብህስ ነገር?

 ሮፍናን፡- የቀነሰብኝ ነገር አንዱ ከራሴ ጋር መሆንን ነው። ከእኔ ጋር መሆንን እወዳለሁ። ይህን ያህል ዓመት ስኖር ዲጄ ሆኜ ሆቴል ውስጥ ስሰራ ፣ ሬዲዮ ላይ ስሰራ አንድም ቀን ፎቶዬን አውጥቼ አላውቅም። ከልጅነቴ ጀምሮ ሌላ ነገር አላውቅም። ሙዚቃ ውስጥ ነው ስንከባለል የኖርኩት። ድንገት ስነቃ ሁሉም ሰው እያየኝ መሆኑን ሳስብ እረበሻለሁ። የማልክደውና የማልወደው ተፅእኖ አለ። ግን ደግሞ በሌላ መልኩ ሰው ወደ አንተ የሚመጣው ወዶህ ነው እና እሱ መልሶ ይክስሃል።

ታዛ፡- በስራህ ሰው ሲጠብቅህ ምን ስሜት ነው ያለው ላንተ? በፊት ማንም አይጠብቅህምና የግል ብቻ ሳይሆን የስራ ፈጠራ ነፃነትም አለህ። አሁን ሰው የሚጠብቅህ መሆንህ የፈጠራ ነፃነትህን አይፈታተንብህም?

 ሮፍናን፡- ስትጠበቅ ያስጨንቅሃል። ይሄ ጥያቄ የለውም። ሙያህ ምንም ይሁን ስትጠበቅ ትጠነቀቃለህ። “ከአንተ ይህን ነው የምጠብቀው” ይልሃል። “ሮፍናን ፎርብስ ላይ ወጣ” ሲባል አንዳንዱ “አዎ ይሄ ይገባሃል” ይልሀል ። አንተ ደግሞ ሰው ነህ። እንደ ሰው ደካማና ስህተት የምትሰራ ነህ። የምንኖረው በማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ነው። የእኛ ትውልድ ሶሻል ሚዲያ ላይ የተጣደ ትውልድ ነው። ጥሩውንም መጥፎውንም ምላሽ ነው የምንቀበለው። ነገ የቱጋ እንደምትሄድ አታውቀውም።

ታዛ፡- ነገ (ቃለ-መጠይቁ በተሰራበት ዕለት) ወደ እስራኤል ትጓዛለህ። የምትሄደው ለግል ጉዳይ ካልሆነ የጉዞህ ዓላማ ምንድነው?

ሮፍናን፡- የእኔ ዓላማ ሀገር ማየት ነው። አንዳንድ ቦታ መሄድ እና መጨበጥ የምፈልጋቸውን ሰዎች ለመጨበጥ ነበር። መሄዴን የሚያውቁ ፕሮሞተሮች ስላገኙኝ ሁለት ሦስት መድረኮች ለውጭ ሰዎች እሰራለሁ። ቢዚ ሲግናል የሚባል ጃማይካዊ አርቲስት አለ። እሱ እዚያ ኮንሰርት ስላለው አብሬያቸው እንድሰራና መድረክ እንድከፍትላቸው ነግረውኛል። ሌላም አንድ ሁለት መድረኮች ሰርቼ እመለሳለሁ። እግዚአብሔር ከፈቀደ ደግሞ እማሆይ ፅጌ ማርያም ገብሩን ለማግኘትና ትንሽ ከእሳቸው ለመማር አስባለሁ።

 ታዛ፡- አንተ የምትሰራበት ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ዓለም ላይ ከታወቀ ምን ያህል ዓመት ይሆነዋል?

 ሮፍናን፡– በስርዓት ከታወቀ ከ10 ዓመት የዘለለ ዕድሜ የለውም። እነዲስኮ እና ቴክኖ ከ15 – 20 ዓመት ቢሆናቸው ነው። የወጣቱ የሙዚቃ ስልት ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ነው።

ታዛ፡- ይህ የሙዚቃ ስልት ዓለም ላይ በመጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ልትሳብበት ቻልክ?

ሮፍናን፡- ነፃነቱ በጣም ሰፊ ነው። እንደ ልሙጥ ሉክ ነው። የምትፈልገውን ድምፅ ማንም ሳያግድህ እንደ ሥዕል መሳል ትችላለህ። ነፃነት ሆነልኝ። እኔ ነፃነቴን እወዳለሁ ብዬሃለሁ። ለምሳሌ ዘመኔን በሙሉ የተማርኩትና ኮሌጅ ገብቼ የወጣሁት መስመር በሌለው የሥዕል ደብተር እየፃፍኩ ነው። በቀጥታ ወይም በጎን መፃፍ እንዳሰኘኝ ነው የምፅፈው። አስተማሪዎቼ የእኔን ደብተር ሲያርሙ ማዟዟር ስለሚሰለቻቸው እንደተናደዱብኝ ነው። የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃም የሰዎችንም ሆነ የባህላዊ መሳሪያዎችን ድምፅ እንደፈለግኩ ለመጠቀም ስለሚያስችለኝ ወደድኩት።

 ታዛ፡– ማስታወቂያ ሥራ ውስጥስ እንዴት ገባህ?

ሮፍናን፡- ጥሩ ጥያቄ ነው። እንግዲህ አባቴ ነፍሱን ይማረውና ንግድ ውስጥ ነው የኖረው። ምንም ይሁን ምን እንደ ወንድ ልጅ በእሱ ተፅእኖ ስር ላልገባ አልችልም። አባቴ ኑሪ ሙዘይን ይባላል። በጣም ነው የምወደው። እሱ ካሉት ምርጥ አስተሳሰቦች አንዱ ንግድ ላይ ያለው ፍልስፍና ነው። ነገሮችን እንዴት አድርጎ መሸጥ እንዳለበት ያውቃል። ሰዎችን እንዴት አድርጎ ማሳመን እንዳለበት ያውቃል። ይህን ከልጅነቴ ጀምሮ አስተውዬዋለሁ። ማስታወቂያ የመስራት ዕድሉን ሲያመጡልኝ ምርቱ ለማንና እንዴት መሸጥ እንዳለበት ማሰቡ ለእኔ አዲስ አልሆነም። ከዚያ ትልልቅ ማስታወቂያዎችን ሰራሁ። ማስታወቂያ ድርጅቶችም ሀሳቤንም ሙዚቃዬንም ፈልገው ወደ እኔ ይመጣሉ። ትልልቅ ብራንድ ያላቸውን ከ40 በላይ ማስታወቂያዎችን ሰርቻለሁ።

ታዛ፡- ማስታወቂያ አሁን ላይ ላንተ ምንድነው?

ሮፍናን፡- ጥበብ ነው። ፉገራ አይደለም። ተጠቃሚው ያላየውን አቅጣጫ ማሳየት ነው። ማስታወቂያ ማለት ለእኔ በፉገራ ሞልተህና ቀባብተህ ምርቱ እንዲሸጥ ማድረግ አይደለም። ራሱ ማስታወቂያ ጥበብ መሆን አለበት። ጥበብ ነው የሰውን ልብ መክፈት ያለበት። ማስታወቂያ ከማስታወቂያነት አልፎ አፋቸው ላይ እንዲቀር ማድረግ አለበት። ጥበብነቱ እሱ ላይ ይመስለኛል።

 ታዛ፡- የማስታወቂያ ስራ ከሚያመጣው ገንዘብ ሌላ ላንተ ምን ጨምሮልሃል?

ሮፍናን፡– ብዙ ነገር። ብዙ ትልልቅና የሚገርሙ ጭንቅላቶችን እንዳይ አድርጎኛል። ከሚገርሙ የማስታወቂያ ባለቤቶች ጋር ቆም ብዬ እንዳወራና ሀሳባቸውን እንዳይ አስችሎኛል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ከአንድ ባለስልጣን በላይ የህዝቡን ስሜት የሚያንቀሳቅሱ እና አቅጣጫ የሚያሰምሩ ናቸው። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ማውራት፣ ህይወት እና አስተሳሰባቸውን መረዳት ከአንድ ማስታወቂያ መሰራት በፊት ያላቸውን ልፋት፣ ጥናት እንዳይ ረድቶኛል። ልፋት እና ድካማቸውን አይቼዋለሁ። ይህን ልምድ በእኔ ህይወት ውስጥ እና ሙዚቃ እጠቀምበታለሁ። ህይወቴ ላይ ብዙ ነገር ነው የጨመረልኝ። በጣም ብዙ ነገር።

ታዛ፡- የነፀብራቅ አልበምህ መውጣት ካመጣልህ በረከቶች አንዱ ኮክ ስቱዲዮ ይመስለኛል። እስቲ ኮክ ስቱዲዮ ለድምፃውያን ምን ማለት ነው? ላንተስ ምን ሆነልህ?

ሮፍናን፡- ድምጻዊው ኮክ ስቱዲዮ ሲሄድ መጀመሪያ የሚያገኘው ራሱን በሌላ አካባቢ (የማይወደው ሊሆን ይችላል) ማስቀመጥ ነው። ከለመደው ሰው፣ ቋንቋ፣ ንግግር ጋር ራሱን ያገኘዋል። አብዛኛው የአፍሪካ ሀገር በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ስዋህሊኛ ቋንቋ ይግባባል። መቀራረቡ አለ፤ እኛ ግን አለመገዛት ከሌላው የአፍሪካ ሀገር ለየት አድርጎናል። ቅኝ ባለመገዛታችን ቋንቋችን ብቻ ሳይሆን ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቻችንም ሳይበረዙ የእኛ ሆነው የኖሩ ናቸው። እንዲህ በመሆኑ በጣም ደስ ይለኛል። ኮክ ስቱዲዮ ስንሄድ የሌሎች ሀገራት ድምፃውያን ብቻቸውን ሲሄዱ እኔ ግን የዋሽንት እና ማሲንቆ ተጫዋቾችን ይዤ ነው የሄድኩት።

ታዛ፡- ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ማለት ነው? አንድ ሁለቴ ሳትግባቡ ቀርታችሁ “እኔ ባልኩት ካልሆነ ይቅር” ብለህ በሦስተኛው ነው እንደገና ሀሳባቸውን ቀይረው ጠርተው የወሰዱህ?

ሮፍናን፡- አዎን። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከድምፃዊው ውጭ ማንም አይሄድም ብለው ትቼው ነበር። በኋላ ላይ በራሴ ወጪ እወስዳለሁ ስላቸው ተስማሙ። ግን የሁሉንም ወጪ እነሱ ናቸው የሸፈኑት። እኔ ምን ብዬ አምናለሁ መሰለህ? እኔን በትክክል ካላወቅከኝ አትወቀኝ። በቃ ይቅርብኝ ጊዜው ሲደርስ ታውቀኛለህ። ቀሪው አፍሪካ ሮፍናንን ማወቅ ካለበት እንደዚህ ነው ማወቅ ያለበት። ከእነማንነቱ ነው ማወቅ ያለበት። ቀሪው ዓለምም እንደዛው።

 ታዛ፡- ካንተ በፊት ኮክ ስቱዲዮ እንዲሆን የማይፈቅደውን እንዲፈቀድ በማድረግህ ለቀጣዮቹ አርቲስቶች በር ያስከፈትክ አይመስልህም?

ሮፍናን፡- እኛ ከሄድን በኋላ ኮክ ስቱዲዮ መመሪያውን ነው የለወጠው። “ባህል ወደ ኮክ ስቱዲዮ ሊመጣ ነው “ አይነት የሚል መሪ ርዕስ ነው የያዙት። ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያ ባህል እንደ ጥቁር ቀለም ነው። ከከተትክበት ይበርዛል። ምክንያቱም በጣም ጠንካራ ስለሆነ። ጥቁር ቀለምን ለመለወጥ በጣም ብዙ ቀለም መጨመር አለብህ። እሱም ከባድ ነው። ባህላችን እንደዛ ስለሆነ ወስደህ ጠብ ስታደርገው ብዙውን ቀለም ብርዝርዝ ያደርገዋል። ሰዎች በአንድ ጊዜ የአንተን ብዙ ቀለም ማየት ይጀምራሉ። ያ ደግሞ መታየት አለበት።

ታዛ፡- ኢትዮጵያዊነትህና የደም ዋጋ የተከፈለልህ ዜጋ መሆንህ ትልቅ የተባለውን ዕድል አንተ እንደምትፈልገው ካልሆነ በቀላሉ “ተዉታ! ይቅር!” እንዳስባለህ መልዕክቱ አዘጋጆቹ ጋ የደረሰ አይመስልህም? (ይህ እንደ ቀላል የወሰንከው ትልቅ ውሳኔ ነውና)።

ሮፍናን፡- በደንብ ደርሷቸዋል። በደንብ። The Voice of Africa ትልቅ ፕሮግራም ነው። የእሱ ዳይሬክተር ኮክ ስቱዲዮን በጊዚያዊነት ለማስተዳደር መጥታ ነበረ። መልበሻ ክፍል ድረስ መጥታ ባየችው ነገር (ያውም ልምምድ ላይ) እንደደነገጠች ነገረችኝ። እኛ ወደዚህ ከመጣን በኋላ ሁለት ሳምንት ሳይሞላት ያለፕሮግራሟ ጓደኛዋን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ መጣች። “ኢትዮጵያን መጥቼ ማዬት እፈልጋለሁ” ብላኝ ነበር ወዲያው። እንዳለችውም መጣች። መጥታም ጊዜዋን አራዝማ ነው የሄደችው። ላሊበላና በየጋራው ስትዞር ቆይታ ነው የሄደችው። ይህ ተጽዕኖ የማሳደር ውጤት ነው ።

ታዛ፡- አልበምህ ከወጣ ዓመት ከሶስት ወር ገደማ ሆኖታል። በቀጣይ የፊት ለፊት ዓላማህ ምንድነው? (በሙዚቃውም ሆነ በማስታወቂያው። ወይም ደግሞ በሌላ።)

ሮፍናን፡- እውነቱን ለመናገር “በቀጣይ ልሰራ የምፈልገው ይህን ነው” ማለት አልወድም። እቅዶቼ ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ሙሉ ዓመት ምን እንደማደርግ አውቀዋለሁ። ያንን መዘርዘር አልፈልግም። ለምሳሌ በዚህ ሰዓት የምሰራውን ብነግርህ ነገ እስራኤል ሄጄ ከውጭ ድምፃውያን ጋር ሁለት ሦስት መድረኮች አሉኝ። ከእስራኤል ተመልሼ ከአሥር ቀን በኋላ ዩጋንዳ “ነይጌ ነይጌ” የሚባል ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ነው። ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ድምፃውያን የሚጫወቱበት ነው። እዚያ ፌስቲቫል ላይ ከዋና ዋናዎቹ ድምፃውያን አንዱ ሆኜ እቀርባለሁ። እሱን ተጫውቼ እንደተመለስኩ በሳምንቱ “ቦይለር ሩም” የሚባል ሌላ መድረክ አለኝ። እዚያው ዑጋንዳ ውስጥ። ከዚያ ተመልሼ ደግሞ በሁለት ሳምንት ልዩነት ውስጥ ኬንያ እሄድና “ዘ አልኬሚስት” የሚባል የሙዚቃ ትርኢት አለ። እዚያ ላይ እሳተፋለሁ። በአሁኑ ወቅት እያደረግሁ ያለሁት በአብዛኛው ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ መስራት እና ግንኙነቴን ማስፋት ነው። ግራሚ አዋርድ ካሸነፉ ድምፃውያን ጋር ሰርቻለሁ። ጊዜው ሲደርስ ይወጣል። ከእነዚህ መልስ ተመልሼ ወደ ጥናቱ ነው የምገባው። ለእሱ የተመደበው ወራት ደግሞ አለ። ዓመቱ በዚህ ነው የሚያልፈው።

ታዛ፡- አፍሪካ ፎርብስ መጽሔት “ተፅእኖ ፈጣሪ” ሲልህ “በቅርብ ዓመት ውስጥ እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሚያገኙ” ብሎ እንደሚተነብይም ነግረኸኛል። የእስከዛሬውን እንቅስቃሴህንና ቀጣይ ዕቅድህን በመደመር የተጠቀሰውን ገቢ ማግኝት የሚከብድህ ይመስልሀል?

ሮፍናን፡- እግዚአብሔር ለእኔ ያስቀመጠው ሁሉ የእኔ ነው። ጊዜውን ጠብቆ የትም አይሄድም። ከእኔ የሚጠበቀው ስራዬን መስራት ነው። እሱን ደግሞ እየሰራሁ ነው።

ታዛ፡- በጣም እናመሰግናለን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top