በላ ልበልሃ

የአዲስ ዓመት እንቁጣጣሽ ለኢትዮጵያ ደሳኩርት ርዕይ – ባህላዊ የአይነጥላ መግፈፊያ

ሰሞኑን በትግራይ ቴሌቪዥን የአማርኛ ፕሮግራም፣ በአይነቱ ፍጹም የተለየ ፖለቲካዊ ውይይትና ክርክር ሲካሄድ በማየቴ በአያሌው ረክቻለሁ። ከፕሮግራሙ ፍሰት፣ የአገሬ ልሂቃን ችሎታና ምሁራዊ ስነምግባር ከምንጊዜውም በበለጠ ከተሻለ ደረጃ ላይ መድረሱን ተረድቼ ተደስቻለሁ። የውይይት መነሻ ሃሳቦችን የሰነዘሩት ምሁራን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለሁለት አሰርታት በቀጥታና በተዘዋዋሪ በመሳተፋቸው፣ ልምድና እውቀትን የገበዩ፣ ይህንን የተግባር ግኝት ከንባብ ባህልና ምርምር አጎዳኝተው አእምሯቸውን ያበለጸጉ፣ በምሁራዊ የአገላለጽ ዘይቤ ሀሳባቸውን በልኩ መጥነው በጥራት ለመፈንጠቅ የበቁ፣ ግለሰብን ማእከል ባላደረገ አግባብ ያልተስማሙበትን ሀሳብ ነጥለው በነጥብ ለመሟገት የቻሉ፤ በአጠቃላይ ተስፋ የሚያሰንቁ ልሂቃን ነበሩ።

 ልሂቃኑ፣ የአገራችን ማህበረ- ኤኮኖሚና ፖለቲካ በብርሀን ፍጥነት ቁልቁል እየተምዘገዘገ መንጎዱ ያሰቀቃቸው፣ የኢትዮጵያ ወደ አስከፊ ጥፋትና ውድመት መሮጥ ያስፈራቸው መሆኑን ከልብ ተጨንቀው- አምጠው ያፈለቁትና የሰነዘሩት ሀሳብ ይገልጻል። ሁሉም ደሳኩርት፣ ለእልፍ አእላፍ ዘመናት አብሮ የኖረ ህዝብ፣ በባህል መወራረስ ተጋምዶ ይተሳሰብ የነበረ ህዝብ፣ ለዘመናት ደስታንና ሀዘንን፣ ጥጋብና ረሀብን፣ ድልና ሽንፈትን በጋራ ሲያስተናግድ የኖረ ህዝብ፣ ከስልጣን እርካብ ተፈናጥጦ የልቡን ሊያረካ ባለመ ልሂቅ አነሳሽነት በቋንቋ፣ በጎጥ፣ በክልል ልዩነት ተቧድኖና ተደራጅቶ፣ ሊጠፋፋ ጦር እየሰበቀ መሆኑ ታይቷቸው፣ የራሳቸው መፍትሔ ያሉትን የሚያፈዙ መላምቶች ሰንዝረዋል። በጥቅሉ ሲታይ፣ ከአንዱ ልሂቅ በስተቀር፣ ሁሉም ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ በማዳን ማእቀፍ ሲናገሩ፣ አንዱ ምሁር ብቻ ሩቅ ሩቅ ተስፈንጥሮ ኢትዮጵያ ተበታትና፣ በኮንፌዴሬሽን ስትተሳሰር መፍትሄ እንደሚመጣ ደስኩሯል። ከወዳጃችን ከኤርትራ ጋር ተለያይተን በኮንፌዴሬሽን ልንተሳሰር እንዳልተቻለ እንኳን ልብ ሳይል ሲቀር አስደንግጦ አስነቀፈኝ።

 ይህ የኮንፌዴሬሽን ነገር ከጆሮዬ እንደ ዘለቀ፣ አንድ ፈረንጅ ጽፎ ያነበብኩት አሳሳቢ ትርክት ትውስ ብሎኝ ይበልጥ አሸበረኝ። ጽሑፉ፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ በተለይም ከቀይ ባህር አንስቶ ወደህንድ ውቅያኖስ ባካለላቸው አገሮች ዙሪያ የሚራኮቱትን ሀያላን መንግስታት ድብቅ ፍላጎት ለመሰወር ሲል ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያና ጂቡቲ ውስጥ ያለውን ተግዳሮት አግዝፎ ለማመልከት የጣረ ነበር። ለእነኚህ አገራት ብልጽግናና ሰላም መድሀኒቱ፣ የአገሮቹ በኮንፌዴሬሽን መተሳሰር እንደሆነ ምክር ብጤ የሰነዘረበት ጽሑፍ ነበር። የፈረንጁ ምክር በአንጻሩ ብልጭ ያደረገብኝ፣ ግን የሚያስደነግጥ ትንቢት ነበር።

ይህች ኢትዮጵያ የምትባል ከአፍሪካ ልዩ በሆነ ሁኔታ ፈረንጅ ወራሪን ድል በመምታት ያዋረደች አገር፣ ለአፍሪካ አገራት ነጻ መውጣት ከአቅሟ በላይ መስዋእትነትን የከፈለች አገር፣ ከነጻነታቸውም በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አስተባብራ አቅም የፈጠረች አገር፣ የልብ ልብ የሚሰማት አገር በዚህ የምስራቅ አፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ሰበብ ደብዛዋን ለማጥፋት እንዴት እንደተደገሰላት ታይቶኝ ዘገነነኝ። ድግሱ ደግሞ በቢሊዮኖች ዶላር ድጋፍና በላቀ አቅም በተደራጀ ሴራ መሆኑ አስጨነቀኝ። ሴራው፣ ‹ኢትዮጵያ› የሚለውን የሚሊኒየም ስያሜና የዛሬውን መንግስታዊ ግዛት ማእቀፍ በማስወገድ፣ እያንዳንዱን ከሰማንያ በላይ የሆነ ቋንቋ ተናጋሪ (ከፊሉን በመጨፈላለቅ)፣ በአንቀፅ 39 አማካይነት ክልልነቱን ወደ ሉአላዊ መንግስትነት በመለወጥ፣ የትግሬ መንግስት፣ የአማራ መንግስት፣ የኦሮሞ መንግስት፣ የሲዳማ መንግስት፣ የወላይታ መንግስት፣ የጉራጌ መንግስት … ወዘተ. እየተባለ ከተቋቋመ በኋላ፣ ከኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያና ጂቡቲ ተኮንፈድረው፣ ኢትዮጵያን በላጲስ ማጥፋት መሆኑን ስገምት ዘራፍ ለአገሬ! አሰኝቶኛል።

 እንዲህ አይነቱ የፈረንጅ ህልም፣ የኢትዮጵያን ህዘብ ማንነት ካለማወቅ፣ ከአድዋ ትምህርት ለመቅሰም ካለመቻልና ካለመፈለግ የመጣ፣ ጥንትም ሲሞከር የነበረ የውጭ ዘራፊዎችና ያገር ውስጥ ተባባሪዎች ቅንጅት እንደሆነ ሲታየኝ ነገሩ ቀለል ይልልኝና፣ እነኚህ ባለጊዜ ሀያላን የሚተኙልን ባለመሆናቸው ምናልባት ተሳክቶላቸው እንደ የመን፣ ሶሪያና ሊቢያ ያፈረካክሱን ይሆናል እያልኩ እፈራለሁ፤ አሁን ያለንበት ያገራችን ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ ፍርሀቴ ዕውን ይሆናል። በዚህ ከቀጠለ፣ ከጥቂት ወራት በኋላ አገሬ ኢትዮጵያን የሚያውዳት የእጣንና ከርቤ ሽቱ ጢስ ሳይሆን፣ በመድፍና በታንክ የጋየ፣ የዜጎቼ ስጋና አጥንት ክርፋት መሆኑ ወለል ብሎ ይታየኛል።  የፖለቲካ ልሂቃኑ ምናልባት እንደኔ ተሰምቷቸው የአገራችንን ችግር ሲጠቋቁሙ፣ በዋናነት ከህገመንግስቱ መመንጨቱን፣ በዘር ላይ ባተኮረ ፌዴራላዊ ስርአት መቸከሉን፣ ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑን፣ ምርጫ ይዘግይ ወይም አይዘግይ የሚለውን ነበር ያመለከቱት። መፍትሄውንም ከዚህ አንጻር ነበር የጠቆሙት፤–ሕገመንግስቱን ማሻሻል፣ በተለይም አንቀጽ 39ን ማስወገድ ወይ አለማስወገድ፣ ስልጣን ህዝብን እንዲያማክል ማድረግ፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ፣ ተመሳሳይ ውይይቶች እንዲካሄዱ ማድረግ ወዘተ. የሚሉትን ነበር እንደመፍትሄ ያወሱት። ፍየል ወዲህ-ቅዝምዝም ወዲያ! መጀመሪያ አገር ስትኖር አይደል ይህስ የሚታሰበው?

እውን እነዚህ ምሁራን ዋናውን የአገራችንን በሽታ ነቅሶ ማውጣት አቅቷቸው ነው ዘወትር ቴሌቪዥንና ሬዲዮ አንጎላችንን በሚያሻክረው የጨዋ መላምት የሚያደነዝዙን? ነው ወይስ ደሳኩርቱ እንደኛው ከዋናው የአገራችን ችግር በአንድ ወይ በሌላ መንገድ ተሳስረውና ወግነው ራሳቸውን ነጻ ባላደረጉበት አኳኋን አይነኬ አድርገውት ነው? ወይስ በተለመደው ለማያምኑበት የማደር ምሁራዊ ባህሪይ ሳቢያ ከዋነኛው ችግር መሪ ተዋናይ ጋር ላለመቀያየም ሌላ ቅያስ መቅደድ? እነኚህን ጥያቄዎች ሳላውቅ በስህተት፣ እያወቅኩ በድፍረት፣ በመጠየቄ ይቅርታ እየጠየቅኩ፣ ለዚህ የዳረጋቸው ያለፉት 27 አመታት የፕሮፓጋንዳ ምትሀት እውነቱን ፈልፍለው እንዳያገኙ አእምሯዊ አይነጥላ ጋርዷቸው ይሆናል በሚል ማስተካከያ ይነበብልኝ።

እና ታዲያ አገራችንን እያሽመደመዳት ያለ በሽታ ምንድነው ልትል ነው? በሉኝ። በሽታዋማ ግልጽ፣ ጸሀይ ላይ ተሰጥቶ የሚታይ፣ ሊደብቁት ቢታትሩም ፈንቅሎ የወጣ፣ እንደ ኖኅ ዘመን የውሃ መጥለቅለቅ አገርን ያሰመጠ፣ ከወንዞቻችን በላይ ሞልቶና ገንፍሎ የዋጠን የመርዝ ውሃ ነው። እና ምነው ታዲያ እንዲያ ቀና ስንል ጨረቃንና

መንግስት የደጋፊነትና የአስተባባሪነት ሚና ብቻ በሚጫወትበት አግባብ፣ የባህላዊ እርቅ ልምድና እውቀት ባካበቱ ያገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የህዝብ ተወካዮችና ምሁራን (ባለፈው ውይይት ላይ የነበሩ ልሂቃንን አካትቶ) አማካይነት ህዝብን የበደሉ ወንጀለኞች ይቅርታ ቢያገኙ፣ በዋስትና የሴራው ጎሬ ምሽግ ከየክልሉ ይደረመሳል

ጸሃይን በቀላሉ ልናይ በምንችልበት አግባብ ፍንትው ብሎ ያለ መርዝ ከሊቆቻችን ተሰወረ? እዚህ ላይ አትቀየሙኝና አገሬ ብዙ የተከበሩ ሊቃውንት ቢኖሯትም፣ በሽታዋን ለይቶ መድሀኒት የሚሰጣት በቂ ምሁር አላፈራችም። ደግሞ አይፈረድባትም፤ ወድዳ አይደለም። እንዴት? በሉኝ። እንዴት ማለት ደግ ነው። ልቀጥል።

 አገራችን ገና ከተደላደለ አገረ-መንግስትነት እርከን አልደረሰችም። ልክ እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ እህቶቿ፣ ዲቃላ ማህበረ ኤኮኖሚና ፖለቲካዊ ስርአት ወጥሮ የቀፈደዳት፣ ማለትም በአንድ ወገን የፊውዳል ስርአት ነቀርሳ ሰንኮፉ ሙሉ ለሙሉ ሳይነቀል ቀርቶ፣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተሰውሮ ሲያሰቃያት፤ በሌላ ወገኑ ደግሞ በአጤ ምኒልክ ዘመን ያቆጠቆጠው የካፒታሊዝም ስርአት በርትቶ የፊውዳሉን ስርአት ግብአተ-መሬት ለማረጋገጥ ሳይችል ቀርቶ በመቀንጨሩ፤ ሁለቱ ሥርዓት በወለዱት ዲቃላ ሥርዓት ተረግመን ያለን ነን። እንግዲህ ልሂቆቻችን አንድነትንና ዲሞክራሲን ከዚህ ዲቃላ ስርአት የምናገኝበትን መጠጋገኛ ዲስኩር ነው የሚያጠግቡን።

 ወንድሞቼና እህቶቼ፤ አንድ ሀገረ- መንግስት ሁሌ መጠየቅና ምላሽ መስጠት ያለበት ዋነኛው ቅራኔ የትኛው ነው? የሚለውን ነው። የዚህ መልሱ ተገኝቶ፣ ማን ከማን እንደሚፋጠጥ ካልታወቀ፣ ጎራ ለይቶ የሚተናነቀው በምን ታክቲክና ስትራተጂ እንደሚታረቅ ለመረዳት አዳጋች ይሆናል። መፍትሄ የሚገኝለትም አይሆንም። ለኔ እንደሚመስለኝ አሁን ባለንበት ወቅት አገራችንን የሚገዛት አብይ ቅራኔ የተቀነበበው፣ እየተዘረፈ፣ ቁምስቅሉን እያየና እየተገደለ ባለው የኢትዮጵያ ህዝብና፣ እየዘረፈ፣ ቁምስቅሉን እያሳየ፣ እየገደለ በተደላደለው ዲቃላ-ከበርቴ አዲስ የገዢ መደብ መሀል ነው። የዚህ መገለጫውም፣ ማለትም የኢትዮጵያን አጥንት ሰባብሮ የሚበትነው በሽታ፣ ፖለቲከኞችና የቋንቋ ሰዎች እያሽሞነሞኑ የሚያሞካሹት ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። መፍትሄ ፍለጋውም ከዚህ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ሊሆን ይገባዋል። ይህንን ሀቅ ነው ዘመዶቼ፣ የሰሞኑ ደሳኩርት ሳያፈርጡት ቀርተው፣ ከዋናው እሽክርክሪት ወጥተው፣ ዳር ዳር እየዞሩ ሲያዞሩብን የሰነበቱት። ታዲያ የሚያሽረው የፈረንጅ ሳይሆን የአገር ባህል መድሀኒት ምንድነው? ላመላክት።

 ሕዝብን ያልዘረፈ፣ ያልገረፈ፣ ያልተለተለ፣ ያልደፈረ፣ ያላንጨረጨረ፣ ያልገደለ መንግስት በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ከቶ አልነበረም። እንደአፍሪካ አገር ባልንጀሮቹ ያሻውን ሲያደርግ ነበር-እያደረገም ነው። ባለፈው ሶስት አሰርት የታየውም የዚህ ቅጥያ እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም። ዲቃላ ስርአት የሚያሰፍነው የተለመደ የማህበረ ኤኮኖሚና ፖለቲካ ዲያብሎሳዊ ባህርይ ነው። እውቀት፣ ሀይማኖት፣ ባህል፣ አመጽ፣ ባሩድ ሊገራው ያልቻለ ክፉ ዲቃላ ስርአት። ኢህአዴግን የተጠናወተውና የኢትዮጵያን ህዝብ በገሀነማዊ እቶን ሲጠብሰው የነበረውም ይሄው ነው። ‹ለህዝብ ልእልና እቆማለሁ ብዬ፣ በዘራፊነት፣ በጨካኝነት፣ በአሰቃይነት፣ በገዳይነት ሰልጥኜ በስብሻለሁ! ገምቻለሁ!› እያሰኘው በህሊና ግርፋት መሪዎቹንና ጭፍሮቹን ለአሰርታት ሲያስለፈልፍ የነበረውም ልክፍት ይሄው ነበር።

 ኢህአዴግ ለአመታት ባካሄዳቸው ተከታታይ ጉባኤዎቹ ላይ ይህ በሙስና መበስበስ ለአገሪቷ መፍረስ ዋና ምክንያት መሆኑን እያመነ፣ በየማጠቃለያው ላይ ግን ይህን ወደጎን እየተወ፣ ችግሩ የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የዴሞክራሲ አለመጎልበት እንደሆነ በመሸወድ የ‹ላም ባልዋለበት ኩበት› መፍትሄ ተብዬ ውሳኔ እያስተላለፈ መበስበሱን እንደቀጠለበት የሚታወስ ነው። የሙስና ስርአት ዋና አራማጅ ሆኖ ሙስናን ያስወግዳል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነበር። ሙስናን ለማስወገድ መሞከር አንድም ዞሮ ዞሮ ኢህአዴግን እራሱን በወንጀል አጋልጦ ግብአተ-መሬቱን እንደሚያፋጥን፣ አልያም የዘረፋ ቋቱን እንደሚያደርቅ ስለሚያውቅ፣ ለኢትዮጵያ ውድቀት ሌላ ሰበብ እያላከከ እየመነመነና እየኮሰመነ መዝለቁን መርጦ ለአይቀሬው የህዝብ ‹አልገዛም- አልበዘበዝም› አመጽ ተዳረገ።

 ይህም ሂደት ቅራኔውን በራሱ ድርጅት ውስጥ ጭምር በማፋፋሙ፣ በተካሄደው የውስጥ ትግል የሪፎርም ሀይል አቆጥቁጦ ስልጣንን ተቆጣጠረ። ይህም ሀይል የኢትዮጵያን አንድነት በማቀንቀኑና እንደ ኢህአዴግ የአሰርታት ወንጀሎቹን አምኖ መናዘዝ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ በመጠየቁ ታላቅ የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ ምድራችንን በተስፋ አጥለቀለቀ። ዋና የቅራኔ መፍቻ መሳሪያም ይቅርታ እና ፍቅር እንደሆነ አወጀ። የይቅርታና ፍቅር አዋጁም ሰላም በናፈቀው የአትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን፣ በሐጢያት በተዘፈቁትም ዘንድ ደስታን ፈጠረ። ተጠርጣሪ ወንጀለኛው ተጠያቂነቱ እንደተነሳለት በመተማማን መረጋጋት እንደጀመረ፣ ቀንደኛ ተዋንያንን በጎን ለፍትህ ማቅረብ ሲጀመር፣ በርግጎ ወደየክልሉ እየሸሸ ሀይሉን ማጠናከር ያዘ። ለማእከላዊ መንግስቱም ሆነ ለድርጅቱ አልታዘዝ አለ። ህልውናውን ለማረጋገጥ ሲል የተለያየ ገጽታ ባለው ስልት አገሪቷን ለብጥብጥ ዳረገ። በዚህም የኢትዮጵያ መበታተን አደጋ ከቋፍ ደረሰ። በዚህ ከቀጠለ የህዝቡ በአንድነት ቆሞ በሰላምና ብልጽግና ጎዳና የመሄዱ ተስፋ በቅርቡ የሚጨልም ይሆናል።

ከዚህ አደጋ ለመውጣት በሰዎች የሚሰነዘሩ አማራጮች ሁለት ናቸው። አንደኛው እንደተለመደው ሀይልን ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት መልሶ አስተማማኝ ማድረግ። ይሁንና፣ ይህን ለመከወን መንግስት በአሁኑ ወቅት ያለው ዝግጁነትና ጉልበት የሚያስተማምን አይመስልም። እንዲህ አይነቱ አማራጭ ወትሮም ለአገራችን ሆነ ለሌሎች አገራት ያመጣው መፍትሄ አልታየም። ይልቅስ ትርፉ የማያባራ የህዝብ የርስ በርስ እልቂት ሊሆን ይችላል።

ሁለተኛው አማራጭ፣ በለውጡ ሰሞን ጎልቶ ሲቀነቀን የነበረውን፣ ኋላ ላይ የደበዘዘውን ‹ይቅርታና ፍቅር› መልሶ እንደ ስልት በመጠቀም፣ የህይወት ዋስትና አጥቶ በየጎሬው የተሸጎጠውን ተጠርጣሪ ወንጀለኛ በባህላዊ አግባብ ይቅርታ ሰጥቶ ከምሽጉ እንዲወጣ የማርያም መንገድ መስጠትና ከሴራ ጉንጎናው ማላቀቅ ያስፈልጋል። ሁለተኛው አማራጭ ነው እንግዲህ እየጎመዘዘኝም ቢሆን እንደመፍትሄ የሚታየኝ። የቅራኔ መፍቻውና የግጭት ማስወገጃው ዘዴ በፈረንጅ መጽሐፍ ጥቅስ ወይንም ልምድ ላይ የሚተማመን ሳይሆን፣ በአገራችን ህዝብ ዘንድ ተካብቶ ባለና ለእልፍ አእላፍ ዘመናት ውጤት ሲያስመዘግብ በነበረ ባህላዊ ዘዴ ሊሆን ይገባል።

በአንድ የኢትዮጵያ ህዝብ ትውፊት አስደግፈን እንመልከት። በአንድ ጎጥ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው በቂም በቀል ወይ በእብሪት፣ ወይ ጥሎበት በስህተት አንዱን ሰው ይገድላል። ከገደለ ወንጀለኛ መሆኑን ስለሚያውቅ ጫካ ይገባል።

 ለእለት ጉርሱም ሲል ከተደበቀበት እየወጣ የአካባቢውን ነዋሪ ቁም ስቅል ያሳያል። ወንጀሉንም ያበራክታል። የተበዳይ ወገንም ጥቃት ይደርስብኛል እያለ እየበረገገ ሰላሙን ያጣል። ደሙን ለመመለስም የበዳይን ወገን ያሳድዳል፣ ይገድላል፣ እሱም ይሸፍታል። እሱም ለጎጧ ነዋሪ በአኳያው ህመም ይሆናል። ይሄኔ ህብረተሰቡ መልሶ ሰላሙን ሊያገኝ የእርቅ ትውፊቱን ያካሄዳል። ለወንጀለኛው ይቅርታ ተሰጥቶ ህይወቱን በሰላም ሊመራ እንደሚችል ዋስትና ሲሰጠው ከጫካው ይወጣና ይደራደራል። በዳይ ተበዳይን ይክሳል፤ ይቅር ለእግዜር ተባብሎ ተሳስሞ ይታረቃል። የበዳይ ተበዳይ ወገን እንደእሽኮኮ መበርገጉ ይቀርለትና ያለስጋት እንቅልፉን ይለጥጣል። ጎጧም እፎይ ትላለች። ሽማግሌዎቹ የገደለ ይሙት የሚል ብያኔ መስጠት አቅቷቸው አይደለም። ዘላቂ መፍትሄው ይሄው የይቅርታና ፍቅር መንገድ ብቻ መሆኑን ህብረተሰቡ ከትውልድ ትውልድ በተላለፈለት እውቀት አጥርቶ ስለሚገነዘብ ነው።

እናም አገራችንን ለብተና የዳረገውን ቅራኔ ለማርገብ የሚቻለው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቀድመው በጀመሩት የይቅርታ መንገድ ሲቀጥሉበት ነው። መንግስት የደጋፊነትና የአስተባባሪነት ሚና ብቻ በሚጫወትበት አግባብ፣ የባህላዊ እርቅ ልምድና እውቀት ባካበቱ ያገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የህዝብ ተወካዮችና ምሁራን (ባለፈው ውይይት ላይ የነበሩ ልሂቃንን አካትቶ) አማካይነት ህዝብን የበደሉ ወንጀለኞች ይቅርታ ቢያገኙ፣ በዋስትና የሴራው ጎሬ ምሽግ ከየክልሉ ይደረመሳል። ከዚያም ያኮረፈው ሁሉ፣ በሽምግልናው የካሳ ድርድር አድርጎ፣ ከመንግስትና ያገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉት የህዝብና የፖለቲካ ተወካዮች ጋር ጉባኤ ተቀምጦ በቅድሚያ አገር ከብተና በምትተርፍበት አጀንዳ ላይ ይመክራል። ሌላው በተነጻጻሪነት ቅንጦት ስለሆነ ፖለቲከኞች በሚነድፉት ስልት መስተካከል እየተደረገበት ይቀጥላል።

 እግረ መንገዱንም የሚፈጸም አንድ በጎ ተግባር አለ። ይህ የይቅርታ ውሳኔ መቼም የሚጸናው ኢህአዴግ በሚመራው መንግስት አዋጅ ነው። ለኢህአዴጎች ወንጀል ይቅርታ ይሰጥ ሲባል፣ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ከሚገኙ ወንጀለኞች የኢህአዴጉ ዝቅ ብሎ በመገኘቱ አይደለም። ኢህአዴግ በአገርና በህዝብ ላይ የፈጸማቸው ወንጀሎች፣ በቁጥጥር ስር ከሚገኝ ማንኛውም ወንጀለኛ የሚበልጥ እንጂ ያነሰ አይደለም። ስለዚህም በነካ እጅ በኢትዮጵያ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ፣ ከፖለቲካ ውጭ የተፈረደባቸው ወንጀለኞች (ከተበዳይ ወገን በሚገኝ የኢትዮጵያውያን የዘወትር ይቅር ባይነት ተደግፎ) እንዲሁ ይቅርታ ተደርጎላቸው ከልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይደባለቁ። ስደተኞችም የአገራቸውን ምድር ይሳለሙ። የህግጋት አንቀጽ መጠቃቀስ የትም አላደረሰንም፤ ምንስ የህግ ተፈጻሚነት ኖሮ አወቀና! እስቲ የኢትዮጵያ እስር ቤት በሮች በሙሉ ይበርገዱና ሰው አልባ ይሁኑ! የስቃይ ጎጆዎችን ለደም መጣጭ ትኋኖችና ቁንጫዎች እንተውላቸው። እስቲ ታሪክ እንስራ! ደሳኩርቱም ስለኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር ይሟገቱ።

ሳላውቅ በስህተት፣ እያወቅኩ በድፍረት ለጻፍኩት ይቅር በሉኝ! መልካም አዲስ ዓመት፤መልካም እንቁጣጣሽ! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top