ጣዕሞት

የአስቴር እና የቴድሮስ አልበሞች ጀሮ ገብ ሆነዋል!

የተወዳጅዋ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንግሥት አስቴር አወቀ ሰሞኑን “ጨዋ” የተሰኘ ሃያ ስድስተኛ አዲስ አልበሟን ገበያ ላይ አውላለች:: በአዲሱ አልበሟ ውስጥ 11 ነጠላ ዜማዎች የተካተቱሲሆን፤ በአድናቂዎቿም ዘንድ ከፍተኛ የሆነ አድናቆት እየተቸራት ነው::

በተመሳሳይ ሁኔታ ሰሞኑን ከዚህ ቀደም “ጋዜጠኛው” እና “ቅዳሜ” በተሰኙ ተወዳጅ ስራዎቹ የምናውቀው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ሞሲሳ፤ አሁንም “አለፈ” የተሰኘ አዲስ አልበም ጀሮ ገብ ሆኗል:: በተለይም በቪዲዮ ቅንብር የታገዘው “መልኬ” የተሰኘው ነጠላ ዜማው በአድማጮቹ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት እያተረፈ ይገኛል:: ከሙዚቃው ጎን ለጎን የጥብቅና ሙያ ላይ የተሰማራው ቴዲ “ጋዜጠኛው” በተሰኘው የቪዲዮ ክሊፕ ተደናቂነት እንዳተረፈ ይታወቃል::  

የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ጎምቱ ደራሲያንን አከበረ

“ብሌን” በምትባለው የማህበሩ መፅሔት ስያሜውን ያደረገው “ብሌን የኪነ ጥበብ ምሽት” ሰሞኑን ለሰባተኛ ጊዜ በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ተከብሯል፡፡ በዚህ “ክብረ አበው” በሚል መሪቃል በተዘጋጀው መርሃ ግብር ነው ለሀገራችን ኪነ-ጥበብ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበርከቱ ጎምቱ ደራሲን እውቅናና ምስጋና የተሰጣቸው፡፡

በዚህ መሰረት ማህበሩ ለደራሲና ሃያሲ አስፋው ዳምጤ፣ ለደራሲና ተርጓሚ ሣህለ ስላሴ ብርሀነማርያም እንዲሁም ለደራሲና አርታኢ አማረ ማሞ የእድሜ ልክ የክብርአባል ሰርተፍኬት ሰጥቷል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም የሰላም ሚኒስቴር በክብር እንግድነት በተገኙበት ፣ በርካታ የኪነ ጥበብ አፍቃሪዎች በታደሙበት በዚህ መርሀግብር የተለያዩ ኪነ ጥበብ ድግሶችም እንደቀረቡ የማህበሩ ህዝብ ግንኙነት ባልደረባ አቶ ጌታቸው አለሙ በተለይ ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

” ፍልስምና ፬ ” መጽሐፍ በድጋሚ ታተመ

ካሁን ቀደም ” ፍልስምና ፩ ” ፣ ” ፍልስምና ፪ ” እና ” ፍልስምና ፫ ” መጻሕፍትን አሳትሞ ለአንባቢያን ያደረሰው ጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ሀምሌ መጀመሪያ ላይ ” ፍልስምና ፬ “ን አሳትሞ ለገበያ ማቅረቡ ይታወቃል ። ይኸው ትኩረቱን በኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ላይ ያደረገው መጽሐፍ በቀናት ውስጥ ህትመቱ ተጠናቆና በድጋሚ ታትሞ ለገበያ ቀርቧል ።

204 ገጾች ያሉት ፍልስምና ፬ እንደ ሌሎቹ ተከታታይ ቅጾች ሁሉ በቃለ መጠይቅ መልክ የተሰናዳ ሲሆን በዚህ ቅጽ መሐመድ ዓሊ ( ቡርሀን አዲስ ) ፣ ሙሉጌታ ተስፋዬ ፣ ስንዱ አበበ ፣ ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኘሁ፣

አብዱልፈታህ አብደላህ ፣ እና መጋቢ ተሽቴ ሚደቅሳ የተባሉ ኢትዮጵያውያን አሳቢዎች ሀሳባቸው ተካቶበታል ። የመጽሐፉ አዘጋጅ ከፍልስምና መጻሕፍቱ በተጨማሪ ” ሦስተኛው ዓይን ” ፣ ” ሰዓት እላፊ ” ፣ ” ሩብ ጉዳይ ” እና ” ከትዳር በላይ ” የተባሉ ትያትሮችን ለዕይታ ማብቃቱ ይታወቃል።

የአለማሁ አዲስ መጽሐፍ አዲስ መንገድ …?

በድርሰት ስራውና በሃያሲነቱ የሚታወቀው አለማየሁ ገላጋይ 13ኛ መጽሐፉን ለገበያ ያዋለው ሰሞንን ነው፡፡ ይኸው “ውልብታ” የተሰኘ አዲስ ፤ መጽሐፉ በአጭር ወግ እና ልቦለድ የተሞላ ነው፡፡ አዲስ አቀራረብ ይዞ የመጣው አለማየሁ፤ በ160 ገፆች ውስጥ 72 ርዕሶች የተለያዩ ጉዳዮችን አንስቷል፡፡

 ይህ የአለማሁ አዲስ መጽሐፍ “አዲስ መንገድ” የሚያሳይ ነውን? ሲሉ አንዳንድ አንባቢን ግር መሰኘታቸውን ዝግጅት ክፍላችን ታዝቧል፡፡ ቅበላ፣ ኩርቢት፣ ኢሀድግን እከሳለሁ፣ ብርሃን ፈለጎች፣ ወሪሳ ፣ በፍቅር ስም እራ መልክአ ስብሃት ከቀደሙ ስራዎቹ ይጠቀሳሉ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top