ህግ ወጥቶላቸው በህብረተ-ሰቡ ዘንድ ወደ ተግባር የገቡ ቅጣቶች አያሌ ናቸው:: ቅጣቶቹ መኖራቸው ጥሩ ነው:: አስተማሪ ሆነው ወደ ፊት በጎ በጎው ተለምዶ መጥፎው ይወገዳል::
መጥፎውን ለማስወገድ የሚተጉ አስፈፃሚዎች ራሳቸው መጥፎ ነገር ሲደርጉ ማየት ግን በጣም ያማል::
አጥር አትጠር ያሉት ህግ አክብሮ ሲተው ከጎኑ ጃን ሜዳን የሚያህል ግቢ ሲያጥር አይተው እንዳላዩ ሲያልፉ ዕውን ህግ ለሁለቱም እኩል ነው ያሰኛል::
ጎኑ ትልቅ ህንፃ ሲሰራ ዝም ያሉት አንዱ ቱቦ ቢቀድ ይቀቱታል:: በማስጠንቀቂያ ወረቀት ያዋክቡታል:: በቃል ያስፈራሩታል::
መሥራት ያልቻለው ወገን ወደ ሊቢያ ተሰዶ ውሃ ሲበላው በዜና ላይ ሲያዩ ግን ከሰው ጎን ሆነው ያለቅሳሉ:: በፊት ሲያለቅስ የሳቁበት ወገን አስክሬኑ ሲመጣ ከቄሱ በፊት ነጠላ አጣፍተው ሰውን አላስገባ አላስወጣ የሚሉት እነሱ ናቸው:: ሟቹን አላስወጣ አላስገባ እንዳሉት ሞቶም አይተዉትም::
ህግ መከበር አለበት:: ለሁሉም በዕኩልነት:: አንዱ ስለሰጠ ሌላው ስላልሸጎጠ መጋፋት የለበትም:: ወይስ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ለነዚህም ኮሚሽነር ይመደብ?……
ብዙ ህጎች አሉ:: ወደፊት በየተራ እናያቸዋለን:: ለዛሬው ፅዳትን በተመለከተ እንሆ….
“መሽናት ክልክል ነው” የተባለ ቦታ አንድ ሰውዬ ፊታቸውን ወደ ግንቡ አዙረው ቆመዋል:: ደንብ አስከባሪዎቹ ከኋላቸው ሆነው የቅጣት ወረቀት ላይ ሊፅፉ አቆብቁበዋል::
ቢታይ … ቢታይ … ሰውዬው አይሸኑም::
ደንብ አስከባሪዎቹ ተናደዱ:: ሸንተው ዞር እንዲሉና ሌላው መጥቶ እንዲቀጣ ነው ፍላጎታቸው::
ሰውዬው ቆመዋል:: ደንቦች ተናደዱ::
“ስማ!” አለ አንዱ ደንብ
“አቤት!” ሽማግሌው መለሱ
“የቅጣት ወረቀት ተቀብለሃል?”
“ለምን?”
“የተከለከለ ቦታ ስለሸናህ” ቆጣ ብሎ ተናገረ ደንቡ
“ኧረ ህግ አክብሬያለሁ”
“አልሸናህም?” አንቱ ማለትን እንደ ክብር ቆጥሮ አናንቆ ጠየቀ::
“ይኸው!” ፌስታል ላይ የሸኑትን አሳዩት:: መሬቱ ላይ ጠብ ያለ ነገር የለም:: ፌስተሏ ቋጥራዋለች::
ደንቡ ተናደደ:: ማመስገን ሲገባ ናቃቸው:: አመናጭቆ ሸኛቸው:: እሳቸውም ሽንታቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው አዘገሙ::
ሀኪም ቤት ሊወስዱ ነው እያሉ ደንቦቹ ሳቁባቸው:: ግን አከባቢን ካለመበከልና የራስን ጤንነት (ከመቋጠር) አንፃር ሰውዬው ሊመሰገኑ ይገባ ነበር:: ግን መቅጣት ህግ ማስከበር ቢሆንም ማስተማር ቢቀድም ሸጋ ነበር::
የሆነ ሰውዬ ደግሞ አከባቢው መፀዳጃ ቤት ስለሌለ የተፈጥሮ ነገር አጣደፈው እና ግንብ ሥር ይሸና ጀመር::
ሁለት ባልቴቶች ደንብ ለማስከበር ካርኒ ይዘው ተጠጉት::
“አቤት!” አላቸው
“መሽናት ክልክል ነው” አሉት
“በተፈጥሮ?”
“ማለት እዚህ ቦታ….”
“ታዲያ እዚህ ቦታ በሉ ቦታ….ሆ!”
“እሺ!”
“እና!”
“አምስት ብር ቅጣት አለብህ!” አሉት አንደኛዋ ካርኒ ላይ ሊፅፉ እየዳዱ::
“እሺ… ይኸው አሥር ብር”
“ዝርዝር የለህም?” አሉ ጓደኛዋ
“የለኝም!”
“እሺ ዘርዝሬ ልምጣ” አሉ ሮጡ::
ቤንዚን ማደያ ሱቅ ጀብሎ ዘንድ ጭማቂ ቤት ሄደው ዝርዝር ስላጡ ተመልሰው መጡ::
“ልጄ ዝርዝር አጣሁ!” አሉት::
“እና?” ሰውየው ጠየቀ::
“አይይ….” ተቅለሰለሱና “እዚያ ጥግ ላይ
ያኛውንም ተፀዳዳና ይጣጣ!!” አሉታ::
17/10/2011
……………
ረዥም መንገድ ሲጓዙ ጨዋታ ከሌለ ድብርቱ አይጣል ነው:: ሹፌሩ እንቅልፉ ሊመጣ ይችላል:: የመኪናውን ድምፅ ሁሉም እያዳመጠ ብልሽት ያለ እየመሰለው ይሰጋል:: ቆም ብሎ ቡና የመጠጣት ሱስ ያለበት ሰው ቢኖር ጨዋታ እና ወግ ከሌለ ምኑም አይጣፍጥ:: አይጥመውም::
ይኸን ጊዜ ቀልደኛ ሰው በብርቱ ይፈለጋል:: ጨዋታ እንዲያመጣ ኃላፊነት ይጣልበታል:: እኔም ይኸው ገጠመኝ::
የሆነ ቦታ እየተጓዝን ነበር:: ዝምታ ሰፍኖ ሁሉም ውጪ ውጪውን ሲመለከት “ኧረ ደረጀ ጨዋታ አምጣ!” ተባልኩ::
ነገር ሳውጠነጥን ቆየሁ:: ለመፀዳዳት እና አየር ለመቀበል አንድ ሥፍራ ስንቆም ፈገግ የሚያሰኝ ነገር ልፈጥር ተሰናዳሁ::
ትንሽ እንደተጓዝን የሆነ ሰው አየሁና ሹፌሩን እንዲቆም ጠየቅሁት:: መኪናው ቆመ:: ሁላችንም ወረድን:: አየሩ ደስ ይላል:: ያየሁት ሰው ለጉዳዬ ምቹ የሆነ ይመስላል:: ሰውዬውን ጠጋ አልኩት:: ሁሉም ተጠጉት:: ሰላምታ ተለዋውጠን ጥያቄዬን ጀመርኩ::
“ግርማን ታውቀዋለህ?” አልኩ
“ግርማ…ግርማ…” አሰበ እና ራሱን
እንደመነቅነቅ አለ
“ግርማ…ረዥም” አለኝ
“አዎ!”
“ሲሄድ የሚያነክስ?”
“አ….አዎ!”
“መልኩ ጥቁር!”
“አዎ!”
“የፊት ጥርሱ ወላቃ?”
“አዎ!”
“ሞቷል እኮ….!” አለቀሰ::
ሰኔ19/2011
