በላ ልበልሃ

በኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ ዙሪያ ያልተቀረፉ ችግሮች

ኢትዮጵያ ሰፊ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ ታሪክ ያህል ታሪኳ በሚገባ ተሰንዶ ከትውልድ ትውልድ ተላልፏል ብሎ ለመናገር አይቻልም። የሀገሪቱ ታሪክ በተገቢው መንገድ ተጽፎ ለትውልድ መድረስ አለመቻሉ አንዱ ክፍተት ሆኖ ሳለ ሌሎችም ችግሮች መኖራቸው የሚታይ እውነታ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ከሚነሱት ችግሮች መካከል አንዱ ከሀገሪቱ የታሪክ አዘጋገብ ጋር የተያያዘ ሆኖ እናገኘዋለን። ከእነዚህ ችግሮች መካከል ጎልተው የሚታዩትን የታሪክ አጻጻፍ ጉድለቶችን በጥቂቱም ቢሆን እየነቀስን እንመልከት።

 በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እንደ አንድ ጉድለት ተደርጎ በተደጋጋሚ የሚነሳው ጉዳይ “የኢትዮጵያ ታሪክ “ በሚል በስፋት የተጻፈው በአብዛኛው የሰሜን ታሪክ እንጂ ሁሉንም የሀገሪቱ ክፍልና ህዝብ የዳሰሰ ታሪክ አይደለም በሚል ነው። የዚህን አባባል እውነታነት መካድ አይቻልም። አንድን የኢትዮጵያ ታሪክ በሚል የተጻፈ መጽሐፍ ብድግ አድርጎ ማውጫውን የተመለከተ ሰው የተጻፈው ታሪክ ተጀምሮ የሚጠናቀቀው በዚያው በሰሜን መሆኑን በሚገባ ይገነዘባል። ዳዓማት፣ አክሱም፣ የጨለማው ዘመን፣ የዛግዌ ሥርወ መንግስት፣ የጎንደር ነገስታት ታሪክ፣ ዘመነ መሳፍንት፣ ዓፄ ቴዎድሮስ፣ ዓፄ ዮሐንስ፣ ዓፄ ምኒልክ በማለት ታሪኩን አንድ ብሎ ከሰሜን በመጀመር በዚያው በሰሜን የሚያጠናቅቅ የታሪክ ጸሐፊ እጅግ ብዙ ነው። እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ታሪኮች በሙሉ የኢትዮጵያ ታሪኮች ናቸው። ሆኖም የክንውን ቦታቸው ሰሜን ነው።

በተለይም ደግሞ በትግሬው በአማራውና በአገው ህዝብ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ታሪኮች መሆናቸው እሙን ነው። ከዚያ ውጪ ያለው የደቡቡ፣ የምስራቁ፣ የምዕራቡና የመካከለኛው ኢትዮጵያ ታሪክስ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ብዙ ሊያነጋግር የሚችል ነው። ቀደም ባለው ጊዜ አልፎ አልፎ በአንዳንድ የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የሚጠቀሱት የኦሮሞና የተወሰኑ ብሔረሰቦች ታሪክ ሲነሳ የሚታየው ከሰሜኑ ህዝብ ጋር በነበራቸው መስተጋብር ነው። ኦሮሞዎች ከሰሜን ደገኞች ጋር በነበራቸው የኃይል የሥልጣንና የግዛት ግብግብ እስከ ጎንደር ቤተመንግስት እንደዚሁም እስከ የጁና ራያ የዘለቀ የሰሜን አሻራ ታሪክ አላቸው። ይህም በመሆኑ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የኦሮሞ ታሪክ ከሰሜን ታሪክ ጋር ተሰናስሎ በየመጻሕፍቱ ሲቀርብ እንመለከታለን። ይህም ቢሆን በስሱ እንጂ ያን ያህል የጎላ ሆኖ አይታይም። እናም ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ከሰሜን ውጪ ያሉ ህዝቦችን ታሪክ ለመጻፍ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ይታያል። ነገር ግን እነዚህም የሚጻፉ ታሪኮች ቢሆኑ ጥልቅ ምርምር የተደረገባቸው ናቸው ለማለት አያስችልም።

ብዙዎቹ የተጻፉት ታሪኮች ከምንም ይሻላል ተብለው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው። ከሰሜን ውጪ ያለው የቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ በሚገባ ተሰንዶ ያልተቀመጠ መሆኑ አሁን ላሉት የዘርፉ ጸሐፊዎች እና ተመራማሪዎች ከባድ ፈተና ነው። እናም መረጃ ቁፈራው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነና ምርምር እየተደረገበት ወደ ታሪክ መዝገብነት እንዲቀየር ማድረግ ካልተቻለ በስተቀር የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ የተሟላ ነው ለማለት ያስቸግራል። በመሆኑም የፌደራሉ መንግስት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ብዙ መስራት የሚጠበቅባቸው መሆኑ እሙን ነው።

 በዚህ ረገድ የራሳቸውን ጥረቶች እያደረጉ ካሉት የመንግስት ተቋማት መካከል አንዱ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ነው። እንደሚታወቀው አብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ሲፃፍ ብዙውን ጊዜ አንድ ተብሎ የሚጀመረው ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወይንም እስከ ዛሬ አራት መቶ ዓመት ያለው ታሪክ ነው። ይህ ማለት የኦሮሞ ህዝብ አሁን ባለባቸው ቦታዎችና ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ መስፋፋት የጀመረባቸው ጊዜያት ተብለው ከሚነገርባቸው ጊዜያት ጀምሮ ማለት ነው። ከዚያ ቀደም ብሎ ኦሮሞ ማነው? ከየት ተገኘ?፣ ሀይማኖቱ፣ ባህሉ፣ ዕምነቱስ ምን ነበር? የሚለው ታሪክም ሆነ የታሪክ ዶኩመንት የለም በሚባል ደረጃ በእጅጉ የሳሳ ሆኖ ይገኛል።

 ነገር ግን በስፋት በቅብብሎሽ ከተጻፈው ድህረ 16ኛው የኦሮሞ ታሪክ ይልቅ ቅድመ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ታሪክ ላይ ትኩረቱን ያደረገ አንድ መጽሐፍ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በ1998 ዓ.ም ለህትመት አብቅቷል። ይህ የታሪክ መጽሐፍ ፤” የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ፤ እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን” በሚል ርዕስ የተፃፈ ነው። ቢሮው ቅድመ 16ኛው የኦሮሞን ህዝብ ታሪክ ለመጻፍ የፈለገው የተመለከተውን የታሪክ ዘገባ ክፍተት ለመሙላት እንደሆነ እሙን ነው። የመጽሐፉም አጠቃላይ ይዘት ሲፈተሽ ብዙ ምርምር የተደረገበትና በርካታ ምሁራን የተሳተፉበት እንደሆነ ይዘቱ ራሱ በሚገባ ይናገራል።

 እናም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ብዙም ሲጻፍ ያልታየውን ቅድመ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ተጠንቶ በመጽሐፍ መልክ እንዲሰነድ ማድረጉ በመልክዓ ምድራዊ ስርጭት ሰሜን ላይ ብቻ ሲሽከረከር የቆየውን ታሪካዊ የዘገባ መቼት፤ ወደ መሀል፣ ምዕራብና ምስራቃዊ ኢትዮጵያ ጭምር እንዲዘልቅ የሚያደርገው ይሆናል። ይህም አሰራርና አካሄድ የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ የተሟላ እንዲሆን ያደርገዋል። የሌሎች ክልሎች መሰል ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎችም ቢሆኑ በየአካባቢያቸው የየራሳቸውን የታሪክ ምርምር በማድረግና የሚገኙባቸውን ማህበረሰቦች ታሪክ በመጻፍ የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉንም እንዲወክል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

 ሌላኛው በኢትዮጵያውያን የታሪክ አዘጋገብ የሚታየው ክፍተት የታሪክ ዘገባችን ማጠንጠኛ ነገስታት እንጂ ህዝብ አለመሆኑ ነው። እያንዳንዱን የቀደመ የታሪክ መጽሐፍ ወደኋላ ሄደን ስንመረምረው ከመጽሐፉ ርዕስ ጀምሮ በነገስታቱ ሥም የሚጠራ ርዕስ ሆኖ እናገኘዋለን። የአቶ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ፣ የጳውሎስ ኞኞና የሌሎች ታሪክ ጸሐፊ ምሁራን መጻሕፍት እንደ አንድ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። ጸሐፊዎቹ የነገስታቱን የዘር ሀረግ፣ የትና መቼ እንደተወለዱ፣ እንዴት ወደ ሥልጣን እንደመጡና ፍፃሜያቸውን ይነግሩናል። ጸሐፊዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ጊዜያቸውን ሰጥተው እነዚህን የታሪክ መጻሕፍት ለትውልድ በማበርከታቸው መቼም ቢሆን ምስጋና ሊቸራቸው የሚገባ ነው። እነሱ ነገስታቱን ማዕከል አድርገው የኢትዮጵያን የየዘመኑን ታሪክ ለማሳየት የሞከሩትን ያህል፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያን

ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥንታዊ አኗኗር፣ የህዝብ ለህዝብ መስተጋብር፣ ማህበረሰባዊ ፍልስፍና፣ ሀይማኖታዊ ልምምድ እና የመሳሰሉትን ዙሪያ ገብ ታሪኮች ሰንደውልን ቢሆን ኖሮ ታሪካችን በእርግጥም የተሟላ ይሆን ነበር። በእርግጥ የኢትዮጵያን ታሪክ ለትውልድ ለማቀበል የየራሳቸውን ጥረት ያደረጉ የዘርፉ ምሁራን ስላደረጉት ጥረትና አበርክቶ ምስጋና ይገባቸዋል።

እነሱ ታሪክን የጻፉት በቅርበት ካገኟቸው የመረጃ ስብስቦች ተነስተው ነው። በቅርብ ለመሰብሰብ ቀላል የሆነላቸው መረጃ ደግሞ የነገስታት ግለ ታሪክን መሰረት ያደረገ የሀገር ታሪክ ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችለው በየጊዜው የነበሩ ነገስታት የየራሳቸው የዕለት ክንውናቸውን ተከታትሎ የሚጽፍላቸው የግል ጸሐፊ ስለነበራቸው ነው።

 እነዚህ ጸሐፊዎች የዜና መዋዕል ጸሐፊዎች (Chronicle Writers) ይባላሉ። እነዚህ ሰዎች ጦርነት፣ የንግስና ሹመትና የመሳሰሉት ወሳኝ ጉዳዮች ሲኖሩ በንጉሡ ትዕዛዝ ለታሪክ የሚሆን ዘገባ ይከትባሉ። በኢትዮጵያውያን አጠራር ጸሐፌ ትዕዛዝ የሚል ሥያሜ ተሰጥቷቸው እናያለን። ስሙ ወይንም ስያሜው እንደሚያመለክተው ጸሐፊዎቹ የየዕለቱን ድርጊት በብዕራቸው ከትበው የሚያስቀምጡት በንጉሱ ወይንም በነገስታቱ ትዕዛዝ ብቻ ነው። ታሪኩም ሲጻፍ ገና ከመንደርደሪያው በንጉሱ መወድስ ነው የሚጀምረው። ይህ የሀበሾች ብቻ ሳይሆን የአረቦችና የአይሁዳዊያን የታሪክ አጻጻፍ ዘዴም ነው። የአይሁዳዊያን መጻሕፍት ሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ አካል የሆኑት አንደኛ ነገስትና ሁለተኛ ነገስት መጻሕፍት እንደዚሁም አንደኛና ሁለተኛ ዜና መዋዕል መጻሕፍት እንደዚሁም መጽሐፈ መሳፍንት የዚህ እውነታ ማሳያዎች ናቸው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ዘመናዊ የታሪክ ጸሐፊዎች የኢትዮጵያን ታሪክ ሲጽፉ ጭብጡ በነገስታት የህይወት ታሪክ ዙሪያ እንዲያጠነጥን የማድረጋቸው ሚስጥር ሌላ ምንም ሳይሆን የቀደሙት ነገስታት ታሪክን በተመለከተ የተውት የጽሑፍ ማስረጃ የእነሱ የዜና መዋዕል ብቻ በመሆኑ ነው።

በኢትዮጵያ ታሪክ አዘጋገብና ዶክመንቴሽን ዙሪያ ሌላኛው የሚታየው ክፍተት ደግሞ የቀደሙት ጸሐፊዎች ከመንፈሳዊ ትምህርት ውጪ የዘመናዊ ትምህርት እድሉን ያገኙበት ሁኔታ አለመኖሩ ነው። ታሪክ አንድ የትምህርት ዘርፍ ነው። እንደማንኛውም ትምህርት የራሱ አዘጋገብና የምርምር ዘዴዎች አሉት። ሆኖም ይህ ሊሆን የሚችለው የግድ የታሪክ ዘጋቢው ወይንም ጸሐፊው በራሱ ጥረትም ይሁን በመደበኛ ትምህርት ይህንን ዘዴ ሲያውቅ ነው። ይህ ካልሆነ አሰራሩ ባህላዊ ዘዴን የሚከተል ይሆንና ግድፈቱ ይበዛል።

የታሪክ ግድፈት አንድ ቦታ ሲፈጠር ጽሑፉ ወደ ትውልድ እየተላለፈ በዋቢነት የሚሰራበት በመሆኑ እንደዚህ አይነቱ ችግር ተሳስቶ ያሳስታል ማለት ነው። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ጅማሮና ፊደል ቆጠራው የሚነሳው ከመንፈሳዊው ትምህርት ነው። እናም መንፈሳውያኑ በትምህርት ደረጃቸው ከፍ እያሉ ሲሄዱ የብሉይና የሀዲስ ሊቃውንት፣ የቅኔና የዜማ መምህር እንደዚሁም የቁም ጸሐፊዎች እየሆኑ ይሄዳሉ። በተለያዩ ሀገራት ቋንቋዎች ውስጥ የተደበቁ መንፈሳዊ ሚስጥራትንም ለመመርመር ሲሉ አረብኛውን፣ ግሪክኛውንና ሌሎች ቋንቋዎችንም ያጠናሉ። በዚሁ ሥራቸውም ታሪክን ሲዘግቡ ይታያል። በመጠኑም ቢሆን የኢትዮጵያን ታሪክ ዘግበው ያቆዩና ለአሁኑ ታሪክ ዘገባ እርሾ የሆኑት እነዚህ ጸሐፊዎች ናቸው። እንደ ምሳሌ ያህልም እንደ ክብረ ነገስትና፣ ፍትሀ ነገስት ያሉ የታሪክና የሕግ መጻሕፍት እንደዚሁም እንደ አቡሻክር ያሉ የዘመን አቆጣጠርን የሚያመለክቱ ይጠቀሳሉ።

 ሆኖም ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ጸሐፊዎቹ ከመንፈሳዊ ትምህርት በዘለለ ዘመናዊ ትምህርት የመቅሰም እድሉ ስላልነበራቸው ታሪክን ይጽፉ የነበረው ከቅዱሳን እና ከመላዕክት ገድሎች ጋር በመደበላለቅ ነበር። እናም ታሪኩ ሥጋዊ ወይንም ሴኩላር ሳይሆን መንፈሳዊ ትምህርት የተጫጫነው ሆኖ እናገኘዋለን። በአንድ አካባቢ የተካሄደን ጦርነት ታሪክ ጸሐፊው ከዘገበ በኋላ ንጉሱ ጦርነቱን ያሸነፈበትን ወይንም የተሸነፈበትን ሚስጥር ሲናገር ከፅድቅ ወይንም ከሀጢያት ጋር ያገናኘዋል። ወይንም የቀኑን የንግስ በዓል ጠርቶ ድሉን ከመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት (Devine Intervention) ጋር ያያይዘዋል። ይህ የቀደመው በመንፈሳዊ ቅመም የተቃኘ የታሪክ አጻጻፍ ዘዴ ነው። በእርግጥ ጸሐፊዎቹ

ታሪክ ጸሐፊዎች በእነዚህ ምንጮች ላይ ብቻ ተደግፈው መረጃን በጽሑፍ ለማስተላለፍ ከመቸኮል ይልቅ ከተለያዩ ግለሰቦች፣ ከተቋማትና ከሌሎች ምሁራን ጭምር በመጠየቅና በማጠያየቅ ማጥራትና ማጣራት ይጠበቅባቸዋል

ታሪኩን የጻፉት የተፈጠረ ድርጊትን ወይንም ሁነትን ይዘው ቢሆንም በአቀራረብ ረገድ ግን ሳይንሳዊነት የሚጎድለው ነው።

እናም የአሁኑ ዘመን የታሪክ ተመራማሪ ታሪክን ወደ መጻፉ ሲያመራ በራሱ የምርምር ዘዴ እነዚህን የታሪክ መዛግብት ማበጠር ግድ ይለዋል። የዘመኑ የታሪክ ጸሐፊዎች እነዚህን የታሪክ ምንጮች ሲጠቀሙ የታሪክ ምንጮቹን በሚገባ ከማበጠር ባለፈ ለአንባቢው ጭምር የምንጮቹን ውስንነት በችግሩ ማብራሪያ ክፍል (Statement of the Problem) ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል። ታሪክ ጸሐፊዎች በእነዚህ ምንጮች ላይ ብቻ ተደግፈው መረጃን በጽሑፍ ለማስተላለፍ ከመቸኮል ይልቅ ከተለያዩ ግለሰቦች፣ ከተቋማትና ከሌሎች ምሁራን ጭምር በመጠየቅና በማጠያየቅ ማጥራትና ማጣራት ይጠበቅባቸዋል።

 በኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ ዙሪያ ሌላ የሚታይ ችግርም አለ። ይሄኛው ችግር በስፋት ጎልቶ የሚታየው በአሁኑ ዘመን የታሪክ ጸሐፊዎች ነው። የአሁን ዘመን የታሪክ መጻሕፍት በስፋት ዘውግ ተኮር ወይንም ከማንነት ጋር የተያያዙ ናቸው። ይህ መሆኑ አይከፋም። ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው የኢትዮጵያ ታሪክ ሰሜናዊነት የሚጫጫነው እንደዚሁም ነገስታቱን ማዕከል አድርጎ የተጻፈ ነው። አሁን ብሔረሰቦችንና እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባማከለ መልኩ ታሪክን መጻፍ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ሳለ አንድ ችግር ደግሞ በጎን ብቅ ብሎ እናያለን። ይህም ችግር መጻሕፍቱ በደልን የሚቆሰቁሱ፣ በታሪክ ተሳፍረው ህዝብን ከህዝብ የሚያራርቁ ሆነው ይታያሉ።

 አንዳንዶቹ በግልፅ ጽሑፋቸው ድብቅ አላማን የሚያራምዱ መሆናቸውም ይስተዋላል። ቆምንለት የሚሉትን ህዝብ ታሪክ ለመጻፍ ሌላውን ህዝብ ማንቋሸሽና ማጥላላት ይቀናቸዋል። አንዳንዶቹ በታሪክ ስም በግልፅ ጥላቻን የሚሰብኩ፤ ሌሎቹ ደግሞ ስልታዊ በሆነ መልኩ የሴራ የታሪክ ትንታኔን የሚሰጡ ናቸው። የቀደሙት የታሪክ ጸሐፊዎች ቢሳሳቱ ባለማወቅ ነው። የአሁኖቹ ደግሞ አስበውና አቅደው ጥላቻን የሚሰብኩ ህዝብን ከህዝብ የሚያራርቁ የመርዝ ብልቃጥ ሆነው ይታያሉ። በዚህ ዙሪያ ብቻ አንድ ራሱን የቻለ ጥናት ቢካሄድ ህዝባችን በተዛባ የታሪክ ጸሐፊዎች ትርክት ምን ያህል እንደተበከለ ለመረዳት እንችላለን።

ሌላኛው በኢትዮጵየ ታሪክ አጻጻፍ ላይ ጎልቶ የሚታየው ችግር በውጭ ምንጮች ላይ ጥገኛ መሆን ነው። አውሮፓውያኑ በኢትዮጵያ ዙሪያ ብዙ ጽፈዋል። ኢትዮጵያውያን በዘመናዊ መልኩ ታሪክን መጻፍ ባልጀመሩበት የዛሬ አምስት መቶ ዓመት አካባቢ አውሮፓውያን ኢትዮጵያ ድረስ በመምጣት ስለኢትዮጵያ መጻፋቸው እሙን ነው። ፖርቱጋላዊው ፍራንቺስኮ አልቫሬዝን ጨምሮ አረባዊው አል-ማክሪዚና በርካታ የአይሁድ ጸሐፊዎችን በዝርዝር መጥቀስ ይቻላል። ጣሊያናዊው ኮንቲ ሮሲኒ እና ሪቻርድ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ሰፊ ምርምር ያደረጉ የታሪከ ምሁራን ናቸው። ኢትዮጵያውያን ታሪክን ሲጽፉ በአብዛኛው ምንጮቻቸው አድርገው የሚጠቀሙት የእነዚህን ጸሐፊዎች የምርምር ሥራዎች ነው።

 ለዚህም በማስረጃነት የመጽሐፎቻቸውን ማጣቀሻዎችና የግርጌ ማስታዎሻዎች መመልከቱ በቂ ነው። ታሪክን ከምንጭ ማጣቀሱ ይበረታታል እንጂ አያስወቅስም። ሆኖም በውጭ የታሪክ ጸሐፊዎች ላይ ጥገኛ መሆን የራሱ ውስንነቶች ስላሉት ጉዳቱም የዚያን ያህል ነው። እነዚህ መጻሕፍት የዋናው ምርምር ማሟያና ደጋፊ ሚና ሊኖራቸው ይገባል እንጂ ሙሉ በሙሉ በምንጭነት የመዋላቸው ጉዳይ የተዛባ የታሪክ ህፀፅን ለትውልድ የሚያስተላለፍ በመሆኑ በእጅጉ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ ዙሪያ ያሉ ችግሮች ዛሬም እንደትላንቱ ቀጥለዋል። ስለዚህም መነጋገሩ ወደመፍትሄው የሚያመጣን ስለሆነ ዛሬም ነገም መነጋገር አለብን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top