ከቀንዱም ከሸሆናውም

ቀብር በጠፈር

‹‹…… ሰው ሁሉ እንደ ዕብድ ሊቆጥረኝ ዳር ዳር ብሏል:: ….››› ራፋኤል ሮስ ከየአቅጣጫው የሚወረወርባቸውን የነገር ፍላፃ ተመልክተው የሚያደርጉት ቢያጡ ‹‹የ52 ዓመቱ ሐካሜ አዕምሮ የነደፉት የእርጋታ ፕሮዤ በእርግጥም ጨርቃቸውን ከቀደዱ አንጎለ ስንኩላን ተርታ ከማሰለፍ በቀር ከጤነኞች እርከን ሊያቆማቸው የሚችል አልመሰለም›› ሲሉ አንድ ብሪታንያዊ ሒሰኛ ያሠፈሩት ለጥቅስ የሚበቃ ነው:: በጉዳዩ በጊዜው የተቹ ብዙ ናቸው:: አጥላልተው የነቀፉ፤ በብርቱ የዘለፉም ሞልተዋል:: የጋዜጦች አእማድ በአንባብያን ይድረስ ተጨናንቀው ነበር በወቅቱ የሰነበቱት:: ግሩም ሊባል የበቃበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ያበደ ያድናሉ የተባሉት ሊቅ ራሳቸው ጤነኛ ሆነው ሊታዩ አለመቻላቸው ነበር::

 ‹‹….መቼም እንዲህ ያለ ሐሳብ የሚፈልቀው ከቀበጦቹ የአሜሪካ ነጋድያን እንጅ ከሌላ አይደለም:: ይሁንና በአንድ በኩል የእቅዱን ከንቱነት በመገንዘብ ያወገዙ መበርከታቸውን ስናይ በሌላ በኩል ደግሞ በዶክተር ሮስ የሰማየ ሰማያት ቀብር ለመሳተፍ የጓጉ መኖራቸውን ሳናረጋግጥ አልቀረንም›› በማለት በአንድ ወቅት አንድ በባስል(ስዊስ) የሚታተም የዕለተ ሰንበት ጋዜጣ ለገጸ ንባብ ያበቃው ጽሑፍ የዓይን ምስክርነት ተቸሮታል::

ዘጋብያኑ እንደጠቆሙት የራፋኤል ሮስ የጠፈር ፕሮግራም በአሥራ ዘጠኝ የምዕራብ አውሮፓ ሀገሮች የሚገኙትን በርካታ ሰዎች ሳየማልል የቀረ አልሆነም::‹‹…. በሕዋ ምርምር ድርሳን ልዩ ምዕራፍ ሊጨብጥ የሚበቃ ሳይንሳዊ ክስተት…›› ‹‹… ጥበብ ያበለጸገው ብልኃት ከተፈጥሮ ሕግ የተዛመደበት …›› ወዘተ… እነዚህ ከብዙዎቹ ደብዳቤዎች ጥቂቶቹ ናቸው::

 በአንፃሩም እንደ ዕውቁ ጀርመናዊ እንደ ኤፍሬም ኪሾን ያሉ ምፀተኞች /ሳተሪስትስ/ የየበኩላቸውን ብለዋል:: ኪሾን ለአንድ የዜና መጽሔት ይድረሳቸውን ሲያሳምሩ፤ ‹‹ለካ አሜሪካ ጻድቃን የሠፈሩባት ምድር ነችና!!! ጻድቃን ወደ ሰማይ ያርጋሉ፤ ስለ ብፅዕናቸው ዋጋቸውን በወዲያኛው ዓለም ያገኛሉ ማለትን ከዱሮ ጀምሮ እሰማ ነበር:: እነሆ ዛቴ ትንቢቱ በአሜሪካ በመፈፀሙ ሐዋርያቱ ደስ ይበላቸው::….. ግን ብቻ… የዋጋውን ሁናቴ ሲመረምሩት ሰማያዊው ጽድቅ ለባለጸጎች ብቻ የተመደበ ይመሰላልና የኒውዮርክ ነቢያት ብጹዓን ናቸው ብዬ አልተቀበልኳቸውም:: ወይስ የሚሊዮነሮች ዝና ሰማይ ቤትም መንፀባረቅ አለበት? መልስ ካላገኘሁ እኔ ራሴ ድሆች ፈልጌ ሌላ የሰማይ ቤት እንዳለ ላስስ መሄዴን እወቁ:: ይህን በወሬ የምንሰማውንማ ባለጸጎች ወሰዱት:: በሞታቸውም አልለቀቁልንም:: ሰማይም መሬትም ለሀብታሞች ብቻ ከተመደበ ሌላ ዓለም እንፈልግ›› ብለዋል::

በእርግጥም ዋጋው አለቅጥ የከበደ ነው:: ወደፊት እንደርስበታለን:: ደግማም የዋጋውን ነገር እንተወውና ‹‹ቀብር በጠፈር›› ሲባል ራሱ ለጊዜው እነደ ሳይንስ ልብ ወለድ የመቆጠር ዕድል ይገጥመዋል እንጂ ‹‹በእውን›› ይኸ ይደረጋል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ሳይሆን አልቀረም ነበር:: ዋል አደር ብሎ ‹‹እውነት›› ሊያሰኝ የሚያበቃ ማስረጃ ሲቀርብ ግን ሁሉም አመነ:: በዚያ እቅዳቸው ሳቢያ ‹‹አውቆ አበድ›› የተባሉት ዶክተር ራፋኤል ሮስ ‹‹ሬሳ በሮኬት›› ብለው የተነሡበት ‹‹የሕይወት በሕልፈት›› ፕሮዤ በተግባር የሚተረጉምበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ተዘግቧል:: ‹‹ሞቶ መቀበር›› ሳይሆን ‹‹ሞቶ መኖር›› ምንኛ ደስ እንደሚል ገምቱ!! ይላሉ ሰውየው::

 ታዛቢዎች እንደሚሉት እኒያው አሜሪካዊ ሐካሜ አእምሮ ዶክተር ሮስ ሙታን ወደ ሕዋ የሚያመጥቁበትን ብልኃት መቀየሳቸው አዲስ የዶላር መሥፈሪያ እንቅብ እንደሰፉ ተደርጎ ነበር የተቆጠረው:: የኒውዮርኩ ዘመናይ ቀባሪ ለጋዜጠኞች በዚያው ወቅት በሰጡት ቃል እቅዱ በሥራ እስኪተረጎም ጥቂት ጊዜ መፍጀቱ ባይጠረጠርም ሐሳቡ ግን በዕድሜው የገረጀፈ እንደሆነ ገልጸዋል:: ሮስ እንደጠቀሱት ከኃምሳ ያላነሱ የአመድ ብልቃጦች የሰማይ መንገድ ቲኬታቸውን አስቆርጠው ሥፍራ ከያዙ ቆይተዋል:: ከቃለ ምልልሱ እንደተረዳነው እነዚያ ሃምሳ ቢልቃጦች ‹‹ስንሞት አስክሬናችንን አቃጥላችሁ በሮኬት ወደ ሕዋ ተኩሱልኝ›› ብለው ተናዘው በሕልፈት ከተሰናበቱ ባለጸጎች የተገኘ አመድ ነው የያዙት:: በጽሑፉ መሠረት ሰዎቹ በቁማቸው ነበር ለዶክተር ሮስ ገንዘቡን የከፈሉት:: እኛስ ሀገር በቁማቸው ቤተ መቃብራቸውን በዕብነበረድ ያሳነጹ እንደነበሩ አይተን የለምን?

‹‹ላድ›› በሚል አሕጽሮት የሚጠራው ዶክተር ሮስ የቆረቆሩት ኩባንያ አደባባይ የዋለው የተመን መዘርዘር

እልፍ አዕላፍ -አዕላፋት የዓለም ሕዝብ በረሃብና በእርዛት በበሽታና በድህነት ሲማቅቅ የዩናይትድ ስቴትስ ከበርቴዎች ደግሞ የሚያደርጉት ቢያጡ ‹‹ሕይወት በሕልፈት›› በሚል ለሰሚ ግራ በሆነ የማታለያ ዘዴ የሚሊዮኒየሮችን ሬሳ ወደ ጠፈር ሊያጓጉዙ የተነሡበት ጊዜ ሲታሰብ ብዙዎችን ነበር ያስረገመው

እንደሚያመለክተው ሁለት ኪሎ አመድ ወደ ሕዋ ለመላክ በእኛ ገንዘብ ሲታሰብ የቱን ያህል እንደሚከፈል መገመት ይቻላል:: ምናልባት ‹‹የአንድ ሙሉ ሰው ቅሪት ነው›› ተብሎ የሚገመተውን ሁለት ኪሎ አመድ በሮኬት ለማሳፈር ገንዘብ ባይኖር ደግሞ ሩብ ኪሎ ብቻ በብዙ ሺህ ብር ከፍሎ መስደድና ተራፊውን እንደ ጥንቱ ከመሬት መቅበር እንደሚቻል ተረጋግጧል:: ከሩብ ኪሎ በታች ግን የሚፈቀድ አይደለም::

የዶክተር ሮስ አስክሬናዊ ምጥቀት በእፍኝ አመድ ብቻ የተወሰነም አይደለም:: ሬሳው ሳይቃጠል እንዳለ ከዋክብትን ዘለዓለማዊ ርስት አድርጎ እንዲኖር ነው እርሳቸው የሚመኙት:: እቅዱ የሚሠምርላቸው ከሆነም ምናልባት 80 ኪሎ ለሚመዝን ሬሳ ብዙ ሚሊዮን ብር ኩባንያቸው ገቢ አድርጎ መታንን ወደ ላይ ይልካል::

 ምፀተኛው ኤፍሬም ኪሾን እናዳሉት ‹‹ጽድቅ ለባለ ጸጎች ብቻ›› የተመደበ በመምሰሉ ከብዙኃን ኩናኔ ሊያመልጥ አልቻለም እንጂ በላድ ኩባንያ የተቀየሰው ‹‹ፍኖተ ሰማየ ሰማያት›› እውነትም ‹‹ሕይወት በሕልፈት›› ሊባል የሞካከረው ይመስላል:: ‹‹የአመድ ቢልቃጦቹም ሆኑ ሬሶቹ ከመሬት ሶስት ሺህ ኪሎ ሜትር ከፍታ ዓለምን ይዞራሉ›› ይህችን በዘመነ ሕይወታቸው የሠፈሩባትን ምድር ትተው በጠፈር ይኖራሉ:: ‹‹64 ሚሊዮን ዓመታት የሕይወት በሕልፈት ዋስትና እንሰጣለን›› ይላሉ ዶክተር ሮስ ‹‹ሞቶ መኖር!!!››

 በ36 ሺህ ኪሎ ሜትር ከፍታ ልክ እንደ ሕዋ መንኮራኩር እየተሸከረከሩ የሚኖሩበት ብልኃትም አልጠፋም:: ዋጋው ግን በ‹‹እጅጉ የከበደ›› መሆኑ ከመጠቀሱ በቀር ጥቁርና ነጭ ሆኖ በወረቀት አልሠፈረም:: እንደ ተመልካቾች ግምት ከሆነ በእኛ ገንዘብ ከብዙ ሚሊዮን ብር አያንስም:: በወቅቱ ከወደ አትላንቲክ ባሻገር የተደመጠ ወሬ እንደተጠቆመው ደግሞ የኒውዮርኩን ሐካሜ አእምሮ ያስጨነቀ አንድ ክስተት ሳይደርስ አልቀረም::

‹‹ዘመናይ ቀባሪ እኔ ብቻ›› ሲሉ ከርመው ገና ቃለ ነቢብ በገቢር ሳይተረጎም አንድ የቴክሳስ ኩባንያ በተወዳዳሪነት ተመዝግቦ ተገኝቶ ነበርና:: ‹‹ረስቲና ደሰቲ ሚለር›› የተሰኙ ሁለት ወንድማማቾች የቆረቆሩት ‹‹ስታርባውንድ›› የተባለው ኩባንያ ከአንድ የሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚ) ሊቃውንት ቡድን የተቸረውን ጠቢባዊ ረድኤት በመመርኮዝ ከዶክተር ሮስ በበለጠ ሁናቴ እንደሚያከናውን ማረጋገጫ የመስጠቱ ሁኔታ ነበር::

 አዲሱ የቴክሳስ ኩባንያ እንደ ዶክተር ሮስ ‹‹እጅግ ቢያንስ ሩብ ኪሎ አመድ›› እንደ ማይልክ ያስታወቁት ሬሳ ተኳሾች የኩል መያዣ በሚያካክሉ ትናንሽ ቢልቃጦች የተሠፈረ 15 ግራም አመድ በ7 ሺህ ብር ሂሳብ ወደ ‹‹ሰማይ ቤት›› ሊላክ እንደሚቻል ሳይጠቁሙ አላለፉም::

 ከሆነስ ሆነና ይኸ ሁሉ ለምን አስፈለገ? ምናልባት ምድር በጠበበችበት ወቅት አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል:: ለዚያውም ቢሆን ቦታ የሚለቁት ሚሊየነሮች ብቻ ናቸውና ለብዙኃኑ እንደተጣበበ መቅረቱን እናያለን:: የከበርቴዎች አስከሬን ጉዞ ግን ‹‹ቋሚ ይጠበዋል ሰው ይቸገራል›› ተብሎ የታሰበ ሳይሆን ኪሾን እንዳሉት ሰማይንም መሬትንም ርስታቸው ለማድረግ ነው አልያም ከተራው ሰው ለየት ብሎ ለመታየት ነው::

 አፈር ፍትግ ያለው ይመስል ‹‹ዝቋላ አውጡኝ፣ ዜጋመል አውርዱኝ………..›› የሚባለውን እንኳ ስንሰማ በመጠኑም ቢሆን የምንገረም አንጠፋም:: ስለምን? ጊዜና ገንዘብ መባከኑ ሰው ማድከሙ እንደ ዋዛ አይስተዋልምና!

እልፍ አዕላፍ -አዕላፋት የዓለም ሕዝብ በረሃብና በእርዛት በበሽታና በድህነት ሲማቅቅ የዩናይትድ ስቴትስ ከበርቴዎች ደግሞ የሚያደርጉት ቢያጡ ‹‹ሕይወት በሕልፈት›› በሚል ለሰሚ ግራ በሆነ የማታለያ ዘዴ የሚሊዮኒየሮችን ሬሳ ወደ ጠፈር ሊያጓጉዙ የተነሡበት ጊዜ ሲታሰብ ብዙዎችን ነበር ያስረገመው:: የዶክተር ሮስም ሆነ የእነሚለር የሬሳ ትኮሳ እቅድ የጥቂቶች አስክሬን ማዕረግ እንዲያገኝ የተሞከረበትን ድርጊት ከማሳየቱ በቀር ‹‹የሕይወት በሕልፈት ብሥራት የተሰማበት ነው›› ማለት አያስደፍርም::

‹‹ላይፍ አፍተር ዴዝ›› ‹‹ሞቶ መኖር›› እያሉ የወተወቱትና ሳይንስና ንግድ የተዛመዱበትን ብልኃት የቀየሱት እኒያው ነጋድያን ያወጡትን እቅድ ‹‹ይበጅ›› ያሉ ጥቂት ያበዱ ባለጸጎች ብቻ ነበሩና!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top