አድባራተ ጥበብ

ጥልቅ አንባቢነት ለምንና እንዴት?

እንደማንኛውም ሌላ ልምድ በየቀኑ በማንበብ የንባብ ችሎታን የላቀ ደረጃ ማድረስ ነው – የንባብ ባህል። የንባብ ዓላማ የተጻፈውን ማንበብ ብቻ ሳይሆን የጽሑፉን ይዘት እና መልዕክት አብጠርጥሮ መረዳት ነው።

 ንባብ ዓለምን ከአዲስ እይታ አንፃር እንድንመለከት ስለሚያደርግ ባለ ብዙ አይን ያደርገናል። አእምሮን በተለያዩ ሀሳቦች መመገብ የተለያዩ እሳቤዎች ተዳቅለው አዲስ መረጃ እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህም ሥራ በፈጠራ እንዲታጀብ የራሱን ሚና ይጫወታል። ቲዮዶር ሩዝቬልት እንደሚለው ንባብ ንፁህ የምናብ ህክምና ነው። ራስን ጥሩ መጽሐፍ ውስጥ መዝፈቅ ምርጥ ፊልም እንደመመልከት ነው – ወደ አዲስ ዓለም ይዞ ይመነጠቃል። ጥሩ ጸሐፊና ንግግር አዋቂ ከማድረጉ በተጨማሪ የግባችንን አንካሴ ወደ ምንመኘው አቅጣጫ እንድንወረውር መደላድሉን ያመቻቻል። አንዳንድ ጊዜ ለአንዳንድ ነገሮች ልዩ አድናቆት አይኖረንም፤ ምክንያቱም ጉዳዩ ወይም ሁኔታው ምን ያህል አስደናቂ እንደሆነ መረጃው ወይም ዕውቀቱ ስለማይኖረን ነው። ንባብ በዙሪያችን ያሉትን ብቻ ሳይሆን አርቀንም ስለ ዓለም ያለን ዕውቀት እንዲሰፋ በዛው ልክ አድናቂ እንድንሆን ያደርጋል። ስለ ዓለም ብዙ ባወቅን ቁጥር ከተለያዩ ሰዎች ጋር በልበ ሙሉነት ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ርዕሰ ጉዳይም ታጥቀናል ማለት ነው።

በንባብ የተሳካላቸው ወይም ንባብ የለወጣቸው

 በርግጥ ንባብ ወይም ጥልቅ አንባቢነት የሰዎችን ማንነት ይቀይራል? ብዙ ማሳያዎች ስላሉ ምላሹ አዎ የሚል ነው። አሜሪካዊው ቢሊዮነር ዋረን ቡፌት የንግድ ሥራው እንዴት እንደተሳካለት ዘወትር ሲናገር እርሾውን ከንባብ ጋር ያያይዘዋል። “በቀን 500 ገፅ አንብብና ዕውቀት በህይወትህ ላይ እንዴት እንደሚሰራ ታውቃለህ” በማለት። ሥራውን በሚጀምርበት አካባቢ ከ600 እስከ 1000 ገፅ በየቀኑ ያነብ ነበር። ታዲያ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ዛሬም የንባብ ዕቅዱን 80 ከመቶ ያህል እየሸፈነ ነው። እንደ ቡፌት ሁሉ በዓለማችን ላይ በንባብ ምክንያት ሥራቸውንና ምኞታቸውን ያሸነፉ ሀብታሞች ጥቂቶች አይደሉም። በባለፀጋ ሰዎች ዙሪያ የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው 1200 ሀብታሞች ከንባብ ጋር የተቆራኘ ምስክርነት አላቸው።

ለአብነት ያህል ቢልጌት በዓመት 50 መጻሕፍትን ያነባል፣ ማርክ ኩባን በቀን ሦስት ሰዓታት ይመሰጣል። ማርክ ዙክበርግ በሳምንት አንድ መጽሐፍ ይጨርሳል። ኦፍራ ዊንፍሬ ከምትወደው አንድ መጽሐፍ እየመረጠች በየወሩ ለክበብ አባላቷ በማንበብ ለውይይት ታቀርባለች። በርግጥ በባለፀጎቹና በድሀዎች መካከል የንባብ ምርጫ ልዩነት እንዳለ ጥናቱ ጨምሮ ይገልፃል። Rich habit የተባለውን መጽሐፍ የደረሰው ቶም ኮርሌይ እንደሚለው ሀብታሞች በብዛት የሚያነቡት ራስን ስለማሻሻል፣ ስለ ሌሎች ሰዎች ልምድ፣ ጠቅላላ ዕውቀትና ውጤት ላይ የሚያተኩሩ መጻሕፍትን ነው። ድሀዎች በሌላ በኩል በአብዛኛው የሚያነቡት አዝናኝ ነገሮችን መሆኑ የልዩነታቸው አንደኛው መስመር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ንባብ ለፖለቲካው ዘርፍ ጫፍ ያደረሳቸው ታላላቆችም አሉ። የሚያነብበትና ንባብ ሲያደክመው የሚተኛበት ክፍል የነበረው ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን የተመረጠ ዕለት “እኔ የተማርኩ አይደለሁም፤ ነገር ግን መጻሕፍትን ማጣጣም እወዳለሁ” ማለቱ የአንባቢነት ፀጋውን ያሳያል። ቶማስ ጀፈርሠንን ለየት የሚያደርገው በፈረንሳይ፣ ኢጣሊያ እና ስፓኒሽ የተጻፉ ሥራዎችን ሁሉ ማንበቡ ነው። ሌላኛው አንባቢና ጸሐፊ ፕሬዚዳንት ጆን አዳምስ በግሉ ቤተ- መጻሕፍት ከፖለቲካ እስከ ሒሳብ የተካተቱ 3510 መጻሕፍት ነበሩት።

 የንባብ ባህልን ያሳደጉ ሀገሮች

 The world culture score index ሀገራት በሚያደርጉት ንባብ ላይ ጥናት አድርጓል። በዚህ ጥናት የተገኘው ውጤት አስገራሚ ነው። ምክንያቱም ብዙዎች እንደሚገምቱት አውሮፓውያንና አሜሪካኖች አይደሉም ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡት፤ የኤሺያ ሀገሮች እንጂ። በርግጥ የንባብ ባህልና ከመሃይምነት መላቀቅ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ስለሆኑ ሁለተኛውን ወደ ኋላ አነሳዋለሁ።

 በጥናቱ መሠረት ህንዶች በሳምንት 10 ሠዓት ከ42 ደቂቃዎች ለንባብ በመስጠት ከዓለማችን ቀዳሚ ሀገር ሆነዋል። በዚህ ሀገር ማንበብ የሚችለው ህዝብ 74 ከመቶ ያህል ነው። በሁለተኛ ደረጃ ታይላንድ ተቀምጣለች። በሳምንት 9 ሠዓት ከ24 ደቂቃዎች ለንባብ ያውላሉ። 88 ከመቶ የሚደርሰው ህዝብ የታተሙ ነገሮችን የማንበብ አቅም አለው። በሦስተኛ ደረጃ የምትገኘው ቻይና ናት። በሳምንት ስምንት ሰዓትን ለንባብ መድበዋል። ፊሊፒንስ 7፡36፣ ግብፅ 7፡30፣ ቼክ ሪፐብሊክ 7፡24፣ ስዊድን 7፡06 ፈረንሳይ 6፡54 ሃንጋሪ 6፡48 ሳዑዲ ዓረብያ 6፡48 ሰዓታት በማንበብ እስከ አሥረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ከላይ እንደጠቆምኩት መሃይምነትን በማስወገድ ወይም ማንበብና መጻፍን መሠረት ያደረገው ዓለም አቀፍ ጥናት እንደሚጠቁመው የኖርዲክ ሀገሮች ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግበዋል። ፊንላንድ፣ ኖርዌይ፣ አይስላንድ፣ ዴንማርክና ስዊድን እንደ ቅደም ተከተላቸው አብዛኛው ህዝባቸው የማንበብና መጻፍ ችግር የለበትም።

የኤሺያ ሀገራት እንዴት የንባብ ባህልን አጠናከሩ?

 በህንድ መንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በህፃናት፣ በወጣቶች፣ በሴቶችና አዛውንቶች ላይ ልዩ ተጽእኖ መፍጠር ችለዋል። ብሔራዊ የመጽሐፍ ትረስት (NBT) የተባለው ድርጅት በአውቶብሶች ላይ የሚወሰዱ መጻሕፍትን በማዘጋጀት ራቅ ወዳሉ ገጠራማ ስፍራዎች መድረስ ችሏል። በ1957 የተቋቋመው ይህ ተቋም በሁሉም የህንድ ቋንቋዎች መጻሕፍትን በማሳተም በቀላል ዋጋ ህዝብ ዘንድ ተደራሽ እንዲሆኑ እየሰራ ነው። በሩቅ አካባቢዎች በርካታ የመጽሐፍ ክበባትንና ተዘዋዋሪ ቤተ- መጻሕፍትን በማቋቋም ብዙዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል። በከተማ ለሚገኙም በእንግሊዝኛና በተለያዩ የህንድ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የኤሌክትሮኒክስ መጻሕፍትን ያቀርባል።

 ታይላንድ ኖውሌጅ ፓርክ (TK Park) እንዳጠናው ከሆነ ህዝቡ በብዛት እያነበበ ያለው ጋዜጦችን፣ የጠቅላላ ዕውቀት መጻሕፍትን እና አዝናኝ ጉዳዮችን ነው። ህዝቡ ከዲጂታል ሚዲያ ውጤቶች ይልቅ አሁንም ለታተሙ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጣል። የንባብ ባህሉን ለማሳደግ ወላጆች ልጆቻቸውን በጥልቀት እንዲያነቡ መገፋፋታቸውና በት/ ቤት የሚካሔዱ ንባብ ተኮር ትምህርታዊ ስልቶች ትልቅ እገዛ አድርገዋል። አሳታሚዎች መጻሕፍትን በቀላል ቋንቋና በሚስብ የሽፋን ስዕል አጣምረው ማውጣታቸው ሌላኛው መሠረታዊ ነጥብ ነው። በተጨማሪም ቤተ- መጻሕፍትን በብዛት ማቋቋማቸው ውጤቱን ሊያፋጥነው ችሏል። በነገራችን ላይ በታይላንድ 919 የህዝብ፣ 225 የዩኒቨርሲቲ ምርምር፣ 54133 የት/ቤት፣ 180 በመንግሥት የሚረዱ የምርምር ቤተ-መጻሕፍት ይገኛሉ።

በቻይና የንባብ ባህልን ካሳደገው አንደኛው ጉዳይ የኦዲዮ መጽሐፍ እየጨመረ መምጣት ነው። በ2017 በተደረገ ጥናት 22.8 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ተጠቃሚ ነበር። 84.8 ከመቶ የሚያህሉት ህፃናት እና ወጣቶች አንባቢዎች ናቸው። 71.3 ከመቶ የሚደርሰው የቻይና ቤተሰብ ልጆችን ጨምሮ የማንበብ ባህል አዳብሯል። በቻይና ከአሥር ጎልማሶች አንዱ በዓመት አሥር መጻሕፍት አንብቧል።

ጥልቅ አንባቢነት እንዴት ይገኛል?

ወደዚህ ስሜት መግባት የሚቻለው ብዙ መስዋዕትነትን በመቀበል ነው። ኦስቲን ፊሊፕስ እንደሚለው አሮጌ ኮት እየለበስክ አዲስ መጽሐፍ መግዛት ይኖርብህ ይሆናል። ወይም የቮልቴርን አዝናኝ መርህ እየሳቅክም ቢሆን መቀበል ይኖርብሃል። እናንብብ እንዲሁም እንደንስ እነዚህ ሁለት አስደሳች ነገሮች ዓለምን በፍፁም አይጎዱም ስለሚል። ጥልቅ አንባቢ ለመሆን ግላዊና ማህበራዊ ደንቦችን ማክበርም ያስፈልጋል።

 ለምሳሌ ያህል የማያወላዳ የንባብ የጊዜ ሰሌዳ ሊኖር ይገባል። በቀን 30 ደቂቃዎችን በቋሚነት ለንባብ ስትመድብ ጊዜውን ከእንቅልፍ በፊት፣ ከቁርስ በፊት፣ ከሥራ በኋላ ለይቶ ማስቀመጥ ይገባል። ደቂቃዎቹ ካልተመቹ ውሳኔህን በገጽ ብዛት ተርጉሞ መበየን ይጠቅማል። ጉጉትን መገንባት ሌላው ፈታኝ ጉዳይ ነው። ጉጉ ከሆንክ ራስህን ለንባብ መገፋፋት ላያስፈልግህ ይችላል – ጉጉትህን ለማርካት ውስጣዊ ስሜትህ ሳይታዘዝ መጽሐፍ ሊጨብጥ ስለሚችል። ጉጉትን መገንባት ማለት በዚህ ዓለም ላይ የማታውቃቸው በርካታ አስደሳች ነገሮች መኖራቸውን መረዳት ማለት ጭምር ነው። እነዚህን አስደሳች ነገሮች መፈለግ ደግሞ ህይወትን ጣፋጭ ያደርጋል።

 ንባብን እንደ ፀሎት ሰዓት አጥብቆ መያዝም ግድ ይላል። ለፀሎት ሃይማኖታዊ ግዴታ ካለብህ ለንባብም ህሊናዊ ትዕዛዝን መፍጠርና ለእሱም ተገዢ መሆን ይጠይቃል። የንባብ ፀሎትህን ሳቢ ለማድረግ ሻይ በማፍላት ወይም ብስኩት በመያዝ ወይም የተመቻቹ ትራሶችን በማዘጋጀት ማንበብ ይጠቅማል። ድባቡን ከፍም ዝቅም የማድረግ መብቱ ያንተ ነው። የንባብ ጣቢያህን እሳት ዳር ወይ ዛፎች ጥላ ሥር ብታደርግ አሊያም ሻማ እያበራህ ልዩ የማነቃቂያ ድባብ መፍጠር ብትሞክር ስህተት አይኖረውም።

 እንደሚታወቀው እስከዛሬ ድረስ በዓለማችን 130 ሚሊዮን የሚደርሱ መጻሕፍት ታትመዋል። ጠንካራ አንባቢዎች በነፍስ ወከፍ 6 ሺህ ያህሉን ሊያነቡ እንደሚችሉ ተገምቷል። እንደ እኔና እንደ አንተ በዝቅተኛ ወይም በመካከለኛ ደረጃ የሚገኝ አንባቢ ቁጥሩን በየጊዜው ከፍ ሊያደርግ የሚችለው ከላይ እንደገለጽኩት በዋዛ ፈዛዛ ሳይሆን ከማይመቹ እሾሆች የሚደርስበትን ጥቃትም ሆነ ምቾት አልባነት በመታገል ነው። አንደኛውና የዘመኑ ጥያቄ ደግሞ ግራና ቀኝ የከበበንን የማህበራዊ ሚዲያ ትኩረት እንደምን መቀነስ ይቻላል የሚለው ይሆናል። የብዙዎቻችንን ከመጠን ያለፈ ጊዜ የሚወስዱት ሚዲያዎች

በጥልቀት እንዳናነብ፣ እንዳናሰላስልና እንዳንጽፍ ያደርጋሉ። እንደ ውኃ የሚወርደው ጊዜያዊ እና ስሜታዊ ጉዳዮች ላይ እንጂ በመሠረታዊ ነጥቦች ላይ በጥልቀት እንዳናስብ ህሊናዊ መጋረጃ ይፈጥሩብናል

ፌስቡክና ቴሌቪዥኖች ናቸው። ሚዲያዎቹ በራሳቸው ጥሩ ቢሆኑም ከመጠን ያለፈ ትኩረት ከተሰጣቸው ግን ጉዳትም ሊያስከትሉ ይችላሉ። በጥልቀት እንዳናነብ፣ እንዳናሰላስልና እንዳንጽፍ ያደርጋሉ። እንደ ውኃ የሚወርደው ጊዜያዊ እና ስሜታዊ ጉዳዮች ላይ እንጂ በመሠረታዊ ነጥቦች ላይ በጥልቀት እንዳናስብ ህሊናዊ መጋረጃ ይፈጥሩብናል። እናም ስናነብ ከስልክ ጀምሮ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለመዝጋት ቆራጥ መሆን ይጠበቅብናል።

ስናነብ ዋና ሀሳቦችን ወይም የመሰጠንን አንቀጽ መምረጥ፣ ማስመር፣ መክበብ ወይም ልዩ ምልክት መተው ንባብና ሃሳቡን ደጋግሞ ለማየትና ለመሳብ ይረዳል። መጽሐፉን በአግባቡ እንድንጨርሰውም ያደርጋል። መጽሐፍን እንደ ኪስ ቦርሳ ቆጥሮ ከእጅ አለመለየት ሌላው የትልቅ አንባቢነት ምስጢር ነው። በእኛ ሀገር አረዳድ መጽሐፍ ከእጁ የማይለየው ደራሲ ነው። ወይም መጽሐፉን በእጁ ይዞ የሚታይን ሰው “አንባቢ ነኝ ለማለት ነው” የሚል ሃተታ ማቀበል ተለምዷል። ሆኖም ብዙ ሰው ከዚህ መሰል ድንቁርና ወጥቶ የምናገኝበት አጋጣሚ ስላለ ተስፋ አያስቆርጥም። በአውቶብስ ወይም በባቡር እየተጓዙ ወይም የሆነ ወረፋ ይዞ ጥቂት ማንበብ ጥቂት ደስታ ወይም ጥቂት ዕውቀት መጨመር ነው።

ከምታስበው በላይ አንብብ። አንድ ዝቅተኛ አንባቢ በዓመት ስድስት መጻሕፍትን ያነባል። ያንተ ጥግ ግን ይሄ መሆን የለበትም። በቀን 45 ደቂቃ የሚያነብ ሰው በዓመት 50 መጽሐፍ ያነባል የሚል ስሌት አለ። ቢያንስ ይህን አደርጋለሁ ብለህ ለራስህ ንገረው። ጎን ለጎን የተለያዩ ጉዳዮችን ማንበብ እንዳለብህ አትዘንጋ። የተለያዩ ርዕሰ ጉዳይ ያላቸው ሥራዎችን ማንበብ አሰልቺነትን ለመታደግ ፍቱን መድኃኒት ነው። በየጊዜው ከአዲስ ዓለምና ከአዲስ ሀሳብ ጋር ለመገናኘት ካሰብክም ስልቱ ይሄው ነው።

ትክክለኛውን መጽሐፍ መምረጥም የራሱ በጎ ሚና አለው። ጥያቄው ትክክለኛ ወይም ጠቃሚ መጻሕፍትን ማንበባችንን በምን እናውቃለን የሚለው ነው። የመጀመሪያው ደረጃ የሥነ-ልቦና መጽሐፍ ማንበብ ከፈለግክ ልቦለድን መምረጥ አስፈላጊ አለመሆኑ ነው። ጥሩ የፍልስፍና ወይም ኢኮኖሚ ነክ ሥራን ለማወቅ መጽሐፍን በጨረፍታ የማጥናት ልምድ ማዳበር ያስፈልጋል። የመጽሐፉን የፊትና የኋላ ገጽ፣ ስለ ደራሲው የተፃፉ ጉዳዮችን፣ መግቢያና ማውጫዎችን እንዲሁም ሌሎች ስለ ሥራው የሰጡትን አስተያየት ማንበብ መጠነኛ ጭብጥ ይሰጣል።

 ጀማሪ አንባቢዎች በአንድ ጊዜ ከአንድ መጽሐፍ በላይ ማንበብ የለባቸውም። በአንድ ጊዜ ሁለት እና ሦስት መጽሐፍ መግለጥ የጉዞ መስመር ያጠፋል፣ ከመጽሐፉ ምን እንደተገኘ በቅጡ ለመረዳትም ያስቸግራል። የጉዞ መስመር ከጠፋ አስሬ ወደ ኋላ መመላለስ ያስከትላል። ይህ ደግሞ ፈጣን አንባቢ ለመሆን የሚደረገውን ጉዞ ያደናቅፋል።

እኛስ ምን እናድርግ? የንባብ ባህላችን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው። ባህሉ በአስተማማኝ መልኩ ሥር ይዞ እንዲያቆጠቁጥ ከተፈለገ ህፃናትና ትምህርት ቤቶች ላይ የማይቆም ንቅናቄ መፍጠር ይገባል። ለዚህም ያለንን ሥርዓተ-ትምህርት ንባብን ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ ቢቀረፅ የተሻለ ውጤት ያስገኛል። በእንግሊዝ አንድ ተማሪ በሳምንት አንድ መጽሐፍ ወስዶ ማንበብና ስላነበበው ገለፃ ማድረግ ይጠበቅበታል። ፈጣን ተማሪዎች ከ40 በላይ መጻሕፍትን በዓመት ያነባሉ። በሀገራችን የመጽሐፍ ችግር ቢኖርም ከመጽሐፉ ውስጥ አንድ ታሪክ ወይም ሀሳብ በማስነበብ ውይይት እንዲፈጥሩ ማስቻል አይከብድም።

ንባብ መጀመር ያለበት ከሥር፣ መጠንከር ያለበት በወጣትነት ነው ሲባል የቤተሰብ ሚና የላቀ መሆኑን በማስረዳት ጭምር ነው። ቤተሰብ ለልጆቹ አቅሙ በፈቀደ መጠን መጽሐፍ ከመግዛት አልፎ መጻሕፍትን እንደ ጓደኞቻቸው እንዲያዩ መገፋፋትና መደገፍ ይኖርበታል። ልጆቹን ሲሸልም ወይም ልደታቸውን ሲያከብር ከኬክ ይልቅ መጽሐፍ ቢሰጥ ነገን ማመልከት ይሆናል። ተማሪዎች ከኮሌጅ ሲመረቁ የቪኖ አንገት ከማንጠልጠል ጎን ለጎን ነገም ማንበብ ወይም መመራመር አለብህ የሚል መልዕክት በመጽሐፉ ሽፋን ላይ በደማቁ ማሳየት ያስፈልጋል። የሰላም ሚኒስቴርን ለችግራችን እንዳቋቋምነው ሁሉ ንባብን የሚመራ ተቋም ቢኖር ይመረጣል። ይህ ደግሞ ለዓለም አዲስ አይደለም። ለምሳሌ በእንግሊዝ የንባብ ኤጀንሲ (The Reading Agency) አለ። ተቋሙ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን ከቤተ መጻሕፍት፣ ከኮሌጆች እና ከማረሚያ ቤቶች ጋር በመተባበር ህፃናት እና ጎልማሶች ንባብን እንዲያጠናክሩ ይሰራል።

ት/ቤት ሲዘጋ ለተማሪዎች የበጋ ወቅት የንባብ ውድድር ያዘጋጃል። ዝግጅቱ በቤተ መጻሕፍት የሚካሄድ ሲሆን እያንዳንዱ ተማሪ በእረፍት ጊዜው ስድስት መጻሕፍትን ማንበብ ይጠበቅበታል። ከታዋቂ ደራሲዎች እና አሳታሚዎች ጋር በመተባበር አጫጭር መጻሕፍትን (Quick reads) በማዘጋጀት ጎልማሶች በአነስተኛ ዋጋ ገዝተው እንዲያነቡ ያደርጋል። የዚህ ዓላማ ብቸኝነትና መነጠልን በመከላከል ከመጻሕፍት ጋር ንግግር ለማድረግ ነው። ምክንያቱም ንባብ ጭንቀትን፣ ድብርትን፣ የአእምሮ ህመምንና ብቸኝነትን ለመዋጋት ፍቱን መሆኑ በሳይንስ ተረጋግጧል።

 መንግሥት ትልቁ ባለ ድርሻ አካል ነውና ሚናውን መካድ ወይም ወደ ሌሎች ድርጅቶች መግፋት አይኖርበትም። ደራሲያንና አሳታሚዎች ውጤታማ የሚሆኑበትን መንገድ መፍጠር ይኖርበታል። ደራሲያንን በመደገፍ ለህፃናትና ለወጣቶች የሚያገለግሉ አማራጭ ህትመቶች እንዲበዙ ማገዝ ይገባል። በግለሰብ እና በተቋማት የተጀመሩ የንባብ ክበባትን በአቅሙ ልክ መደገፍ ግድ ይለዋል። የንባብ ሳምንት ዝግጅቶች ከዓመታዊ ካላንደርነት ወጥተው የቅርብ ሥራዎች እንዲሆኑ መትጋት ይኖርበታል።

ከምሁራን፣ ከለጋሾች እና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር የቤተ መጻሕፍት ግንባታን ማጠናከር ይጠበቅበታል። በ1998 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ታንብብ ድርጅት ከ70 በላይ የሆኑ ቤተ መጻሕፍትን ገንብቶ መሃይምነትን ለመዋጋት ጥሩ ጅማሮ አሳይቷል።

 ይህ የቤተ መጻሕፍት ቁጥር ለ100 ሚሊዮን ህዝብ ኢምንት በመሆኑ ድርጅቱን በራስህ ተወጣው ብሎ ማራቅ አይገባም። ንባብ ከሚዲያ ሥራ ጋር ተጣምሮ ይሰራ ዘንድም ማሰብ ከባድ አይደለም። ለምሳሌ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚሰሙ የሬዲዮ መጽሐፍ ትረካዎችን ሦስትና አራት አሊያም እንደ ዜና ዕለታዊ ማድረግ በህፃናትና ወጣቶች አእምሮ ላይ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ነው። ይህ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ሚዲያዎቹን ስፖንሰር በማድረግ ሊያግዝ ይችላል።

አፍሪካውያን ለመመልከቱ እንጂ ለንባብ ብዙም ግድ የላቸውም የሚባለውን ወቀሳ (በተለይም ለከተሞች) መቀልበስ ካልተቻለ ጠያቂና ተመራማሪ ማህበረሰብ መፍጠር አይቻልም። እንደ እኛ በርካታ ብሔረ-ሰቦች በበዙባት ሀገር ባህልንና የህዝቦችን መስተጋብር ለማወቅ ብሎም ለማስተሳሰር ንባብ ወሳኝ ነው። በመሆኑም ጥልቅ አንባቢያን፣ ደራሲያንና የደራሲያን ማበር ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ከሚለው መርሃቸው የተሻገረ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ መልካም ይሆናል። ልምዳቸውንና ሥራቸውን በት/ቤቶች፣ በክበቦችና በንባብ አዳራሾች ማካፈል ይጠበቅባቸዋል።

ማርክ ትዌን እንደሚለው የሚያነብ ሰው ማንበብ ከማይችለው ሰው የተለየ ጥቅም የለውም። ይህ መርህ የሚያስደነግጠን ከሆነ እያንዳንዳችንም በግለሰብ ደረጃ የንባብ ባህልን ለማሳደግ እንትጋ። እናንብብ። ግድ የላችሁም መጽሐፍ ለማግኘት የሚቸግረን ከሆነ እንኳ እየተዋስን እናንብብ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top